Monday, February 23, 2015

ድል የአላማ ጽናት እንጂ የመሳሪያ ጋጋታ ዉጤት አይደለም

ጣሊያን ዋና ከተማ ሮም ዉስጥ ዋና ከተማዋን ከተለያዩ የጣሊያን ከተሞችና ጣሊያንን ከፓሪስ፤ከሙኒክ፤ከጄኔቫና ከቪዬና ጋር የሚያገናዉና በአመት ከ 150 ሚሊዮን በላይ መንገደኞችን የሚያስተናግድ አንድ ትልቅ የባቡር መስመር አለ። ይህ የባቡር መስመር የሚጠራዉ ሮማ ተርሚኒ እየተባለ ሲሆን የባቡር መስመሩ አድራሻ ደግሞ የአምስት መቶዎቹ አደባባይ በመባል ይታወቃል። ወደዘህ ትልቅ ባቡር መስመር ሲገባ አንድ እጅግ በጣም ትልቅ ሀዉልት ወለል ብሎ ይታያል፤ ይህም ሀዉልት የአምስት መቶዎቹ አደባባይ ወይም ፒያዛ ዴ ቺንኮቼንቶ በመባል የታወቃል። የፒያሳ ዴ ቺንኮቼንቶ መታሰቢያ ሀዉልት የተሰራዉ ወራሪዉ የጣሊያን ጦር አገራችንን ለመወረር ሲመጣ ዶጋሌ ላይ በራስ አሉላ ጦር የተገደሉትን አምስት መቶ የጣሊያን ወታደሮች ለማስታወስ ነዉ። በ1877 ዓም ዘመናዊ መሳሪያ ታጥቆ ጦርና ጎራዴ በታጠቀዉ የራስ አሉላ ጦር ዉርደት የተከናነበዉ የጣሊያን ወራሪ ሠራዊት ብድሩን ለመመለስ በ1888 ዓ.ም ብዛት ያለዉ ካባድ መሳሪያ፤ መድፍና መትረየስ ታጥቆ አድዋ ድረስ ቢመጣም በዳግማዊ ሚኒሊክ የተመራዉ ጀግናዉ የኢትዮጵያ ሠራዊት እንደገና ዉርደት አከናንቦት በጥቁር ህዝብ ታሪክ ዉስጥ ትዝታዉ ምንግዜም የማይደበዝዝ ድል አስመዝግቧል። የኢትዮጵያ ሠራዊት ዶጋሌና አድዋ ላይ እስካፍንጫዉ የታጠቀዉን የጣሊያን ወራሪ ጦር ደጋግሞ ያሸነፈዉ በመሳሪያ በልጦ ወይም የተሻለ የዉትድርና ችሎታ ስለነበረዉ ሳይሆን ከወራሪዉ ጦር የበለጠ ቆራጥነትና የአለማ ጽናት ሰለነበረዉ ነዉ።
በሃያኛዉ መቶ ክፍለ ዘመን የተደረጉ ሌሎች የነጻነት ትግሎችን ስንመለከት በወቅቱ የአየር ኃይል ያልነበራት ትንሿ አገር ቬትናም በባህር፤ በአየርና በየብስ ጦርነት የገጠማትን ትልቁን የአለማችን ሀይል አሜሪካንን አሸንፋ ነፃነቷን ያስከበረችዉ በመሳሪያ ጋጋታ ሳይሆን የዛፍ ላይ ቅጠልና የተቦጫጨቀ ጨርቅ በለበሱ ነገር ግን ከፍተኛ የአላማ ጽናት በነበራቸዉ ጀግኖች ልጆቿ አማካይነት ነዉ።
አለማችን ትልቅ የጦርነት አዉድማ ናት ቢባል አባባሉ እምብዛም ከእዉነት የራቀ አባባል አይደለም። በእርግጥም አለም የጦርነት መድረክ ናት። ወደድንም ጠላን ወይም ብናምንም ባናምንም ጦርነቶች ሁሉ የተካሄዱት የህዝብን ነፃነት በሚደፍሩ ኃይሎችና መብቴንና ነጻነቴን አትንኩ በሚሉ ኃይሎች መካከል ነዉ። የአለማችን ታሪክ ወለል አድርጎ እንደሚያሳየን ደግሞ ይዋል ይደር እንጂ ሁሉም ዘለቄታዊ ድሎች የተመዘገቡት የአላማ ጽናት ባላቸዉ መብቴንና ነጻነቴን አትንኩ በሚሉ ኃይሎች ነዉ እንጂ የመሳሪያ ጋጋታ በተሸከሙ ኃይሎች አይደለም። የመሳሪያ ጋጋታ የተሸከመና ብዛት ያለዉ ወታደር ያሰለፈ ነገር ግን ለምን እንደሚዋጋ የማያዉቅና የአላማ ጽናት የሌለዉ ሠራዊት ግዜያዊ የጦር የጦር ሜዳ ድል ለያገኝ ይችላል፤ ሆኖም ጦርነቱን አሸንፎና የህዝብን ነጻነት ቀምቶ መዝለቅ በፍጹም አይችልም።
የአለም ታሪክ በነጭ ወረቀት ላይ በጥቁር ቀለም ቁልጭ አድርጎ የጻፈዉ አንድ ግዙፍ ሀቅ ቢኖር እልፍ ታንክና እልፍ አዕላፋት መድፎች ቢታጠቁም አምባገነኖች ለግዜዉ እንደተቆጣ ነብር ያስፈራሉ እንጂ ህዝባዊ አለማና ጽናት ያለዉ ጦር ፊት ሲቆሙ ፀሐይ እንደገላመጠዉ በረዶ ሟሽሸዉ የሚጠፉ ደንባራ ፈረሶች ናቸዉ። ለዚህም ነዉ ህዝብ አምባገነኖችን የወረቀት ላይ ነብር እያለ የሚጠራቸዉ።
ዛሬ ዕድሜዉ 35 እና ከዚያም በላይ የሆነ ኢትዮጵያዊ ሁሉ የሚኒልክን ቤ/መንግስት ተቆጣጥረዉ የረገጡትን፤ የገደሉትንና መብቱንና ነጻነቱን ገፍፈዉ ያዋረዱትን ሁለት የወረቀት ላይ ነብሮች ያስታዉሳል የሚል ሙሉ እምነት አለን። ደርግ በ1967 ዓም “ያለ ምንም ደም እንከኗ ይዉደም” እያለ ወደ ሥልጣን ሲመጣ በፊዉዳሉ ስርዐት ጀርባዉ የጎበጠዉን ኢትዮጵያዊ ሁሉ ደስ አሸኝቶ ነበር። እየቆየ ሲሄድና የተደበቀ ትክክለኛ መልኩ አደባባይ ሲወጣ ግን ያንን “ያለ ምንም ደም” የሚለዉን መፈክሩን ረስቶ ኢትዮጵያን የደም ገንዳ ሲያደርጋት በኢትዮጵያ ህዝብ ተጠልቶ አይንህን ለአፈር ተባለ። በሩሲያ ሰራሽ ዘመናዊ የጦር መሳሪያዎች አስካፍንጫዉ የታጠቀዉና በቁጥሩና በወታደራዊ ብቃቱ አፍሪካ ዉስጥ ትልቁን ሠራዊት የገነባዉ ደርግ “እንደ ዉኃ የሚያጥለቀልቅ ኃይል አለኝ” እያለ ቢፎክርም እሱ እራሱ ተጥለቅልቆና በያለበት ተሸንፎ አገራችን ኢትዮጵያን ለዘረኛ አምባገነኖች ያስረከበዉ ለእግሩ ጫማ ለወገቡ መታጠቂያ በሌለዉ የገበሬ ጦር ተሸንፎ ነዉ። ደርግ እንደታጠቀዉ መሳሪያ ብዛት፤ እንዳደራጀዉ ወታደራዊ ብቃትና እንደ ወታደራዊ መሪዎቹ ችሎታ ቢሆን ኖሮ ደርግን እንኳን ተዋግቶ ለማሸነፍ በዉግያ ለመግጠምም የሚያስብ ኃይል በፍጹም አይነሳም ነበር፤ ነገር ግን ድል ምን ግዜም ቢሆን የመሳሪያ ጋጋታ ዉጤት ሳይሆን የራዕይ ጥራትና የአላማ ጽናት ዉጤት በመሆኑ በወቅቱ ይህንን የተገነዘቡ ኃይሎች ህብረትና አገር ዉስጥ የተቀሰቀሰዉ ህዝባዊ ቁጣ አንድ ላይ ሆነዉ ደርግን ጠራርገዉ የታሪክ ቆሻሻ ዉስጥ ሊጨምሩት ችለዋል።
ዛሬ ደርግን አሸንፈዉ ደርግ የተቀመጠበት ወንበር ላይ የተቀመጡት ዘረኞቹ የወያኔ መሪዎች የአገርን ኃብት ከመዝረፍ፤ የተቃወማቸዉን ከመግደልና የኢትዮጵያን አንድነት ከማፍረስ ዉጭ እንዴትና ለምን ደርግን የመሰለ ሠራዊት እንዳሸፉ የተገነዘቡ አይመስልም። ወያኔዎች ደርግ ከወደቀ ከ24 አመት በኋላ ዛሬም በየቀኑ ደርግን ቢኮንኑም ተቀምጠዉ አገር የሚገዙት ልበቢሱ ደርግ የተቀመጠበት ወንበር ላይ ነዉና የደርግ በሽታ ተጋብቶባቸዉ እነሱም እንደደርግ ልበቢሶች ሆነዋል።
ኢትዮጵያ በየዘመኑ እያደገና እየዘመነ የመጣ፤ ከተለያዩ የአገራችን ክፍሎች የተዉጣጣና ሞያን፤ ችሎታንና ወታደራዊ ሳይንስን አዳብሎ የታጠቀ ዘመናዊ የአገር መከላከያ ተቋም የነበራት አገር ነበረች። ዘረኞቹ የወያኔ መሪዎች አዲስ አበባን ሲቆጣጠሩ ይህንን ዘመናዊ የአገርና የወገን መመኪያ የሆነ ሠራዊት አፍርሰዉና በየበረሃዉ ለእናት አገሩ የተዋደቀዉን ሰራዊት ለማኝ አድርገዉት ነዉ እነሱ ወርቃማዉ ዘር ብለዉ በሚጠሩት ዘር የበላይነት ላይ የተመሰረተ የመከላከያ ተቋም የገነቡት። ወያኔ የገነባዉ የመከላከያ ተቋም ባለፉት ሃያ አራት አመታት ዉስጥ አዲስ አበባ፤ ኦጋዴን፤ ጋምቤላ፤ ደቡብ ኦሞና በተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች የወሰዳቸዉን ፀረ ህዝብና ፀረ አገር እርምጃዎች ስንመለከት ተቋሙ እዉነትም ለአገር ጥበቃ ሳይሆን የወያኔን የበላይነት ለማረጋገጥ የተቋቋመ ኃይል መሆኑን በቀላሉ መረዳት ይችላል።
ይህ ሙሉ በሙሉ በትግርኛ ተናጋሪዎች የሚታዘዘዉ መከላከያ ሠራዊት ጋምቤላና ኦሞ ሸለቆ ዉስጥ ገበሬዉ ከቀዬዉ ተፈናቅሎ መሬቱ ባዕዳን ሲቸበቸብ አፉን ዘግቶ እንዲመለከት አድርጓል። ይሄዉ ሠራዊት በ1997 ዓም በአግአዚ ነብሰ ገዳዮች እየተመራ የህዘብ ድምጽ ይከበር ያሉ ከ200 በላይ ሠላማዊ ዜጎችን በግፍ ጨፍጭፏል፤ ከዚህ በተጨማሪ የወያኔ መከላከያ ሠራዊት አጋዴንና ጋምቤላ ዉስጥ የዘር ማጥፋት ወንጀል ፈጽሟል አሁንም እየፈጸመ ነዉ። እዚህ ላይ የኢትዮጵያ ህዝብ አንድ ትኩረት ሰጥቶ ሊመለከተዉ የሚገባዉ ነገር አለ፤ እሱም ዘረኞቹ የወያኔ መሪዎች ልማታዊ ሠራዊት ብለዉ እያሞካሹና “የመከላከያ ኃይሎች ቀን” የሚል ስያሜ ሰጥተዉ በየአመቱ ማክበር የጀመሩት በዐል የሚያወድሰዉ ይህንኑ አንድነቱንና ነፃነቱን እጠብቃለሁ ብሎ ቃል ኪዳን የገባለትን ህዝብ ያለ ርህራሄ የሚጨፈጭፈዉን የወያኔ ሠራዊት ነዉ። በተለይ ወያኔ ባለፈዉ ሳምንት ባህር ዳር ዉስጥ ያለ የለሌ የመሳሪያ ጋጋታዉን አደባባይ አዉጥቶ ለህዝብ እያሳየ ባከበረዉ የመከላከያ ቀን በዐል ለህዝብ ማስተላለፍ የፈለገዉ መልዕክት ቢኖር “ይህንን እያያችሁ ከወያኔ ጋር በእሳት አትጫወቱ “ የሚል የሞኝ መልዕክት ነዉ።
ይህ ባህር ዳር ላይ የተላለፈዉ መልዕክት ለማን እንደሆነና በተለይ ባህር ዳር የመልዕክቱ ማስተላለፊያ ቦታ ሆና የተመረጠችበት ምክንያት ለማንም ኢትዮጵያዊ ግልፅ ይመስለናል። የዘረኞቹ የወያኔ መሪዎች መሰባሰቢያ የሆነዉ ህወሓት የተወለደዉም ሞቶ የሚቀበረዉም ሰሜን ኢትዮጵያ ዉስጥ መሆኑን እሱም ደጋፊዎቹም ካወቁ ቆይቷል። ዉቧና የጀግኖች መፍለቂያ የሆነችዉ ባህር ዳር ደግሞ ይህንን የወያኔን የቀብር ጉዞ ከጀመረች አመታት አስቆጥራለች። እንገዲህ ወያኔ በየቀኑ ከባድ መሳሪያና ስፍር ቁጥር የሌለዉ ወታደር ወደ ሰሜን ኢትዮጵያ የሚያጓጉዘዉ ከዚሁ ከማይቀርለት ዉድቀቱ የሚያድኑት እየመሰለዉ ነዉ። እዚህ ላይ አንድ ወያኔ በፍጹም ያልተረዳዉ ነገር ቢኖር ህወሓትን ከኢትዮጵያ ምድር ጠራርጎ የሚያጠፋዉና ግብዐተ መሬቱን የሚፈጽመዉ ይሄዉ ወያኔ በነጋ በጠባ ወደ ሰሜን ኢትዮጵያ የሚያጓጉዘዉ ሠራዊት መሆኑን አለመረዳቱ ነዉ። የወያኔ አይን ያወጣ ዘረኝነት በከፍተኛ ደረጃ ከተንጸባረቀባቸዉና በየቀኑ በዘረኝነት እሳት ከሚለበለቡ የህብረተሰብ ክፍሎች ዉስጥ አንዱና ዋነኛዉ የመከላከያ ሠራዊት ነዉ። ይህ ሰራዊት እንደ መሬት የሚረግጡትን የወያኔን አለቆቹን ትዕዛዝ ተቀብሎ ከታሰረበት የዘረኝነት እስር ቤት ነፃ ሊያወጡት በሚታገሉ የኢትዮጵያ ህዝብ የነጻነት ኃይሎች ላይ መሳሪያዉን ያዞራል ብሎ የሚያምን ኢትዮጵያዊ ያለ አይስለንም፤ በሌላ በኩል ደግሞ የወያኔን የመሳሪያ ጋጋታ አይቶ ለእናት አገሩ አንድነትና ለኢትዮጵያዉያን ወገኖቹ ነጻነት ህይወቱን ከመስጠት ወደ ኋላ የሚል ኢትዮጵያዊ ቢኖር እሱ ከወያኔ ጋር በጥቅም የተጋባ ከሃዲ መሆን አለበት። የኢትዮጵያ ህዝብ ምንግዜም ቢሆን በወሬ ቱማታና በመሳሪያ ጋጋታ ትጥቁን ፈትቶ አያዉቅም። በ1930ዎቹ ፋሺስት ጣሊያኖችንና በ1970ዎቹ ወታደራዊዉን ደርግ ተዋግቶ ያሸነፈዉ እነዚህ ኃይሎች የታጠቁትን መሳሪያ እየቀማ በተዋጋቸዉ ነጻነት የጠማዉ ኃይል ነዉ። የዛሬዎቹ የወያኔ ፋሺስቶች እጣም ጣሊያንና ደርግ ከገጠማቸዉ ሽንፈት የተለየ አይሆንም።
የአገራቸዉን የኢትዮጵያን ዳር ድንበር ከጠላት ለመከላከል የመከላከያ ሠራዊትን የተቀላቀሉ የኢትዮጵያ ልጆች “ዶሮን ሲያታልሏት በመጫኛ ጣሏት” የሚለዉን የአባቶቻቸዉ ምሳሌያዊ አባባል ምንነት በሚገባ የሚረዱ ይመስለናል። ስለሆነም ዘረኛዉ የወያኔ አገዛዝ በዘር ለይቶ እየረገጣቸዉ፤ እያዋረዳቸዉና ከሰዉ በታች አድርጎ እየተመለከታቸዉ ይህንን ቅጥ ያጣ በደል ለማረሳሳት የመከላከያ ቀን እያለ በሚያከብረዉን የይስሙላ በዐል እንድም የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አባል ሊታለል አይገባም። ከአግአዚ ነብሰ ገዳዮች ዉጭ ያለዉ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት እንደማንኛዉም የወያኔ እስረኛ እንደሆነ የህብረተሰብ ክፍል ነፃ መዉጣት የሚገባዉ ክፍል ነዉ። ይህ የህዝብ ወገን የሆነዉ የመከላከያ ሠራዊት እራሱን ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያዉያን ወንድሞቹንና እህቶቹን ጭምር ከወያኔ ዘረኝነት ነጻ ሚያወጣት አለበት። እስከቅርብ ግዜ ድረስ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አባላት ብዙም አማራጭ ስላልነበራቸዉ አንገታቸዉን ደፍተዉ የጠላታቸዉን የወያኔን ትዕዛዝ እየተቀበሉ ሲፈጽሙ ቆይተዋል፤ አሁን ግን አንገታቸዉን ቀና አድርገዉ የወያኔን አንገት የሚያሰደፉበት አመቺ ሁኔታ ተፈጥሮላቸዋል። ዛሬ ለእናት አገራቸዉ ነጻነት በህይወታቸዉ ቆርጠዉ ብረት ያነሱ የነጻነት አርበኞች የመከላከያ ሠራዊት የወያኔ አለቆቼን ትዕዛዝ ላለመቀበልም ሆነ ወይም የታጠቀዉን መሳሪያ ወደ ጠላቱ ወደ ወያኔ ማዞር የሚችልበትን አመቺ ሁኔታ ፈጥረዉለታል።
ዉድ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አባላት ሆይ ጨለማዉ ሊጠራ ሲል ይበልጥ ይጨልማልና ወያኔ ወደ ሰሜናዊዉ የአገራችን ክፍል የሚያጓጉዘዉ የመሳሪያ ጋጋታና የሠራዊት ብዛት በፍጹም ልትደናገጥ አይገባም። ወያኔን ካንተ በላይ በቅርብ የሚያዉቀዉ የለም፤ የወያኔ ኃይለኝነትና ትልቅ መስሎ መታየት አንተ በዉስጡ ስላለህበት ብቻ ነዉ። ስለዚህ ይህንን ፀረ ኢትዮጵያ ኃይል ለቅቀህ በያለህበት ላንተ፤ ለወገኖችህና ለእናት አገርህ ነፃነት መከበር ከቆረጡ ወገኖችህ ጋር በፍጥነት ተቀላቀል። ይህንን ማድረግ የማትችለዉ ደግሞ ወያኔ ከገዛ ወገኖችህ ጋር እንድትዋጋ ትዕዛዝ ሲሰጥህ የታጠከዉን መሳሪያ ወደ ወገኖችህ ሳይሆን ወደ ራሱ ወደ ወያኔ አዙር። ወያኔ ለትንሽ ግዜ የማይበገር መስሎ ሊታይ ይችል ይሆናል የማይቀረዉ የዘለቄታ ድል ግን ምን ግዜም የህዝብ ነዉ፤ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ደግሞ ትናንት አንደነበረ ሁሉ ዛሬም የኢትዮጵያ ህዝብ አለኝታ ነዉ።
ድል የህዝብ ነዉ!
source www.ginbot7.org

No comments:

Post a Comment