Saturday, February 21, 2015

የዛሬ የቂሊንጦ አጭር ቆይታ አብርሃን መጠየቅ ከጀርባ ሰው ያስከትላል (ከኤልያስ ገብሩ ጎዳና )

‹‹ዕድሜያችንን መቼ ሰራንበት፣ ልደት ማክበርም ያስፈራኛል፡፡
እንኳን ተወለድክ ላላችሁኝ በሙሉ ከልብ አመሰግናለሁ››
ጦማሪ እና ጋዜጠኛ በፍቃዱ ኃይሉ
ከዛሬ ከሰዓት በኋላ ከወዳጄ አቤል አለማየሁ ጋር ወደ ቂሊንጦ እስር ቤት አምርተን ነበር፡፡ አካሄዳችን በዞን ሁለት የሚገኙትን አብርሃ ደስታን፣ ጦማሪ እና ጋዜጠኛ በፍቃዱ ኃይሉንና ጦማሪ አጥናፍ ብርሃንን ለመጠየቅ ነው፡፡
የቃሊቲ እና የቂሊንጦ ጸሐይ ከረር ያለች ብትሆንም በቦታው ደርሰን ወደፖሊሶች ለምዝገባ ተጠጋን፡፡ ጠያቂና ተጠያቂ መዝጋቢ የሆነችው ሴት ፖሊስ ‹‹ማንን ነው የምትጠይቀው?›› ብላ አቤልን ጠየቀችው፡፡ በፍቃዱን እና አጥናፍን መሆንኑ ነገራት፡፡ መዘገበችውና ሂድ አለችው፡፡ ‹‹አንተስ ማንን ነው?›› ስትል ጠየቀችኝ፤ ‹‹አብርሃ ደስታን›› አልኳት፡፡ ቀና ብላ አየችኝና ‹‹ቆይ፣ ቁጭ በል›› የሚል መልስ መለሰች፡፡ ሌሎች ሰዎችን መመዝገቧን ቀጠለች፡፡ ‹‹ሰዓት እየሄደ ነው፣ ችግር አለ ወይ?›› አልኳት፡፡ ‹‹አይ ችግር የለም›› ካለች ከተወሰኑ ደቂቃዎች በኋላ ሌላ መዝገብ አምጥታ ፓስፖርቴን መዘገበችው፡፡ (መታወቂያዬ አልታደሰም) ከመዘገበች በኋላም ሌላ የፎርም መሙያ አውጥጣ በድጋሚ መዘገበች፡፡ ይሄንን ስትመዘግብ እኔ እንዳይባት ስላልፈለገች ስትደብቀው አስተውያታለሁ፡፡ …ከሌላ ወንድ ፖሊስ ጋር ከተነጋገረች በኋላ ግባ አለችኝ፡፡Elias Gibru
የጸሐይ መነጽር ማውለቅ ግድ ነበር፡፡ ያው ፍተሻውን አልፌ ወደዞን ሁለት አመራሁ፡፡ ከኋላዬ አንድ ሲቪል የለበሰ ወንድ በቅርብ ርቀት እየተከተለኝ ነበር፡፡ አብርሃን አስጠራሁት፡፡ ከኋላዬ የሚከተለኝ ሰው ከጎኔ ሆኖ ሌሎች ጠያቂዎችን ለመጠየቅ ማስመሰል ሞከረ፡፡ በውስጤ ፈገግ መጣ፡፡
አስተናባሪዎቹ ‹‹አብርሃ እዚህ የለም፤ የዞን ሁለት መጠየቂያ ተቀይሯል›› አሉኝ፡፡ በእርግጥም ዞን አንድ ታስሬ በነበረበት ጊዜ የማውቃቸውን እስረኞች ተመለከትኳቸውና ሰላም ተባባልን፡፡ ልወጣ ስል ኡስታዝ አቡበከር አሕመድ በርቀት አይቶኝ ሰላም አለኝ፡፡ በደስታ ሰላም አልኩት፡፡ ነገር ግን ተመልሼ በእጄ ሰላም እንዳልለው ያ ከጀርባዬ ያለ ሰው ነበር፡፡ ከዚህ ቀደምም ‹‹አቡበከርን ለምን ጠየከው?›› ተብዬ የተፈጠረውን ግርግር አስታወስኩኝ፡፡ አብበከርም ይሄ ስለገባው በርቀት ሰላም ብሎኝ በእጁ ሂድ አለኝ፡፡
የዞን አንድ መጠየቂያ ለዞን ሁለት ታሳሪዎች፤ የዞን ሁለት ደግሞ ለዞን አንድ ታሳሪዎች መጠየቂያ ሆኗል፡፡ አቤል በፍቄንና አጥናፍን አስጠርቷል፡፡ እኔም አብርሃን አስጠራሁ፡፡ በፍቄና አጥናፍ ወዲያው መጡ፡፡
ያ ከጀርባዬ የነበረ ሲቪል ኮፍያ ለባሽ ከጎኔ ቆሟል፡፡ ለአጥነፍ ‹‹በቃ እናንተ ከአቤል ጋር አውሩ፡፡ እኔ አብርሃን ስላጠራሁ ልጠብቀው፡፡ ከአንድ ሰው በላይ መጠየቅ አይቻልም ብለዋል›› አልኩት፡፡ አጥናፍ ከዚህ ቀደም የደረሰብኝን አስታውሶ ‹‹አብርሃ አሁን ጠበቃ ተማንን ሊያገኝ ሄዷል፤ ከጎንህ የቆመው የግቢው ደህንነት ነው፡፡ ይሄን ንገረውና እስከዚያው ከእኛ ጋር ሁን›› አለኝ፡፡ ያን ሰውዬ ትከሻውን ስነካው ደንገጥ ብሎ ዞር አለ፡፡ ስለሁኔታው ነገርኩት፡፡ ‹‹እሱ (አብርሃ) እስኪመጣ ብቻህን ተቀምጠህ ጠብቅ›› አለኝ፡፡ ‹‹እስኪዚያ እነሱን ላናግራቸው›› አልኩት፡፡ ‹‹ብቻህን ብትቀመጥ ይሻልሃል አለኝ›› ተናድጄ ወደውጪ ወጥቼ ሌሎች ፖሊሶችን ስለሁኔታው አስረዳኋቸው፡፡ ኃላፊነት የሚወስድ ጠፋ፡፡ በመጨረሻም አንዱ ፖሊስ ‹‹እሱ አስኪመጣ ውስጥ ጠብቀው›› የሚል ምላሽ ሰጠኝ፡፡ የመጣው ይምጣ በሚል ገብቼ ከበፍቄ ጋር ማውራት ጀመርኩ፡፡
‹‹በፍቄ እንኳን ተወለድክ›› አልኩት፡፡ አሜን ካለኝ በኋላ ‹‹ዕድሜያችንን መቼ ሰራንበት፡፡ ልደት አክብሬ አላውቅም፡፡ ልደት ማክበርም ያስፈራኛል፡፡ ግን እንኳን ተወለድክ ላላችሁኝ በሙሉ ከልብ አመሰግናለሁ›› ሲል እየሳቀ መለሰልኝ፡፡
አቤል እና አጥናፍ ጋር የጦፈ ጨዋታ ይዘዋል፡፡ እኔም ከበፍቄ ጋር ባለችን አጭር ደቂቃ ስለሀገር ጉዳይ፣ ስለዘንድሮ ምርጫ፣ ስለአልጀዚራ ዘስትሪም የሰሞኑ ዘገባ፣ ስለ ክሳቸው እና እስራቸው ጉዳይ፣ ስለእኔ የክስ ሁኔታ፣ በአንድነት ፓርቲ ስለደረሰው ሁነትና አደጋ …በጥቂቱ አወጋን፡፡የመለያያ ደወል ተደወለ፡፡ አብርሃም ሳይመጣ ቀረ፡፡ ያው፣ ቻው ብሎ መለያየት ግድ ነበርና ተለያየን!!!
Source ecadforum.com

No comments:

Post a Comment