ድሬዳዋ የኢትዮጵያዊያን ከተማ ነበረች። ኢትዮጵያዊያን የጎሳቸውን አጥር አፍርሰው በኢትዮጵያዊነታቸው ብቻ ለረዥም ዘመን አብረው በድሬዳዋ ኑረዋል። በዚህ ሁኔታ የሚኖረው ህዝብ አብሮ ስቆ ፤አብሮ ተደስቶ፤ ያለው ለሌለው አካፍሎና ተቻችሎ መኖርን የሚያውቅ ነበር። ዛሬ ግን ያች ቀድሞ የምናውቃት ድሬዳዋ ተረት ሁናለች። ሁሉ ስቆና ተደስቶ የሚኖርባት ከተማ ሳትሆን በየወቅቱ በእሳት እንድትጋይ ሁና ብዙዎች እንባቸውን በመዳፋቸው የሚያፍሱባት ከተማ ሁናለች። ብዙዎች የንግድ ሥፍራቸው ተቀነባብሮ በተነሳ እሳት በመጋየቱ ባዶ እጃቸውን ቀርተዋል። ልጆቻቸውም ድሃ አደግ እንዲሆኑ ሁኗል። ይባስ ብሎ ንብረቶቻቸውን ከእሳት ቃጠሎ ለመከላከል እሳቱን ለማጥፋት የተነሱ ዜጎች በአሸባሪነት ተከሰው ህወሃቶች “ ፍርድ ቤት” ብለው ወደ ሚጠሩት ሥፍራ እንዲቀርቡ ሁኗል።
ገ/መድህን ገ/መስቀል፤ ቢኒያም ጌታቸው፤ መቻል አብራር፤ ምትኩ ውብየ፤ ኢዮብ ገብሬ፤ ሃቢብ ሸምሱ፤ ለዒላ ዓሊ ፍትህን በማያውቀው በህወሃት ፍርድ ቤት ቀርበዋል። ከእነዚህ ውስጥ ከገ/መድህን ገ/መስቀል በቀር ሌሎቹ የዋስ መብት ተነፍጓቸው ወሂኒ እንዲቆዩ ተደርጓል። ገ/መድህን ገ/መስቀል በምን ሁኔታ ከሌሎቹ ተለይቶ “ነፃ ሰው” ሊባል እንደቻለ የሚያውቅ የለም። ብዙ ሰዎች ግን በትግራይ ተወላጅነቱ አፍቃሬ ህወሃት ” ተደርጎ እንዲታይ ለማድረግ ነው ይላሉ። ህወሃት በልዩ አፈና የራሱ ዋሻ ያደረገውን የትግራይ ህዝብ ከሌላው ኢትዮጵያዊ ወገኑ ለማቆራረጥ እንዲህ አይነት ያፈጠጠና ያገጠጠ የዘር መድልዎ ሲያደርግ የመጀመሪያው አይደለም። ድህረ ምርጫ 97 ከአዲስ አበባ ከተማ ተግዘው ወደተለያየ ማጎሪያ ከተላኩት በርካታ ሺዎች ውስጥ የትግራይ ተወላጆችን መርጦ “እናንተ ነፃ ናችሁና ወደ ቤታችሁ ሂዱ” ብሎ እንዳሰናበተ የማያውቅ የለም። የዘረኞቹ ቁንጮ መለስ ዜናዊ በህይወት በነበረበት ወቅት ሲደረግ የነበረውና ከህልፈቱም ቦኋላ ቀጥሎ ያለው የህወሃት የዘረኝነት መገለጫ አንዱ መንገድ ይሄው ነው። በትግራይ ወጣቶች የህወት መስዋዕትነት ለስልጣን በቅተው እራሳቸውን ያነገሱ የህወሃት መሪዎች ትግሬን ነፃ ማውጣት ማለት ከሌላው ወገኑ ጋር ውሎ አድሮ ደም የሚያቃባ አድልአዊነት እንዲህ በአደባባይ መፈጸም ነው ብለው ያምናሉ። እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል እንዳለቺው እንስሳ ለህወሃቶች እንዲህ አይነት ዘረኝነት ወደፊት ሊፈጥር የሚችለው አደጋ አይታያቸውም ወይም ስለርሱ ማሰብ አይፈልጉም። ።ከአማራና ከአፋር የሚዋሰኑትን ለም ቦታዎችንና በበከርሰ ምድር ማዕድን የከበሩ ሥፍራዎችን ቀምተው ወደ ክልላቸው ሲጠቀልሉና ነዋሪውን በማፈናቀል የቀድሞ ታጋዮቻቸውን ሲያሰፍሩባቸው አልሰቀጠጣቸውም። ወያኔ የራሱ ዋሻ አድርጎ በሚቆጥረው የትግራይ ክልል ውስጥ እያደረሰ ያለው ስቃይና መከራ የክልሉን ግንብ ጥሶ በመላው አለም በመሰማት ላይ ባለበት በአሁኑ ወቅት በተለያየ የአገሪቱ ክፍል ተበትኖ የሚኖረውን ጥቂት የትግራይ ተወላጅ ተጠቃሚ በማድረግ የትግሬ ነጻ አውጪ ለመምሰል የሚደረገው ጥረት በትግራይ ህዝብ ዘንድ ሳይቀር እየተወገዘ ነው። ዘረኞቹን የህወሃት መሪዎች እረፍት የነሳውና እንዲቅበዘበዙ እያደረገ ያለውም የዚህ ዘረኛ አላማቸው የራሴ ነው በሚሉት የቀድሞ ምሽጋቸው ሳይቀር እየታወቀ መምጣቱ ነው።
ዛሬ ከትግራይ ጀምሮ በመላው አገሪቱ ማለት ይቻላል የወያኔን ዘረኝነትና ዘረፋ የሚቃወሙ ሁሉ ሥልጣንን በተቆጣጠሩ በእነዚህ ዘረኞች እጅ የመከራ ፅዋቸውን እየተጎነጩ ነው። የአሬና አመራርና አባላት ብቻ ሳይሆን በቤተሰቦቻቸው ጭምር ላይ ትግራይ ውስጥ እየተፈጸመ ያለው ግፍ የሚያረጋግጠው ይህንኑ ሃቅ ነው። የታገልነውና የደም መስዋዕትነት የከፈልነው እናንት ጥቂት ዘረኞችንና ቤተሰቦቻችሁን በራሳችን ላይ ለማንገስ አልነበረም እያሉ ያሉ እንደነ አቶ አሰግድ ገብረስላሴ ያሉት ልጆቻቸው ጭምር በጎዳና እየተደበደቡ እስር ቤት ሲወርወሩ ነፍሳቸውንና ስጋቸውን ለህወሃት መሪዎች ያስረከቡት ጥቂት የትግራይ ተወላጆች ግን ከዘረፋ በተገኘ ሃብት ቢጠሩዋቸው የማይሰሙ ዲታ ሆነዋል። በልማትና እድገት ሥም በጋምቤላ ድሆችን ከኖሩበት መሬት አፈናቀለው እና ሜዳ ላይ በትነው መሬት ከተቀራመቱት ባዕዳን በቁጥር የሚበልጡት የዘረኞቹ ጋሻ ጃግሬ የሆኑ ትግሬዎች ናቸው። በአዲስ አበባ በዜጎች ደምና አጥንት ላይ የተገነቡ የትላልቆቹ ህንፃ ባለቤቶች የፋሽስቱ የህወሃት አባላት ናቸው። የአገሪቷን የንግድ ማዕከል ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ተቆጣጥረው በዚያች አገር የሚዘባነኑት እነዚሁ በትግራይ ሥም የሚነግዱ ቡድኖች መሆናቸውን ህዝቡ የሚያውቀው እውነት ነው።ለትግራይ ነፃ አውጪዎች ሲባል የመከራውን ፅዋ በመጎንጨት ላይ ያለው ህዝብ ቁጣ የዶፍ ዝናብ ሊጥል የተዘጋጀ ሰማይን ይመስላል።ያ ቁጣ የፈነዳ ግዜ የሚያቆመው ምዳራዊ ኃይል እንደሌለ በሚቾት የደነዘዘው የህወሃት አመራር የተገነዘበው አይመስልም።
ስለዚህ ዘረኛና ወንጀለኛ ቡድን እጅግ የሚያሳዝነው ሌላው ነገር 23 አመት ሙሉ የአገሪቱን በትረ ሥልጣን እንዳሻው እያሽከረከረም ቢሆን ከመንደርተኝነት ስሜት ሊላቀቅ አለመቻሉ ነው። ዛሬም እንደትናንቱ ትግራይን መደበቂያ ዋሻ ፤ ዞሮ ዞሮ መግቢያ ለማድረግ የማይፈነቅለው ድንጋይ የለም። ቅድሜ ወያኔ የአገሪቱ ህዝብና መንግሥት ንብረት የነበሩ ንግድ ድርጅቶችን በመውረስ የደለበና ዛሬ በአገሪቱ ብቸኛ የሥራ ተቋራጭ፤ ዕቃ አቅራቢና አገልግሎት ስጪ የሆነው ኢፌርት በስም የትግራይ ህዝብ በተግባር ግን የህወሃት ባለሥልጣኖች የገቢ ምንጭ መሆኑን ያልተረዳ የለም።መመኪያ ዋሻየ ከሚለው የትግራይ ህዝብ መነጠሉን እየተረዳ የመጣው ይሄ ፋሽስታዊ አስተሳሰብ ያለው ነውረኛ ቡድን ሰሞኑን ሌላ አሳፋሪ ድርጊት እየፈፀመ ነው። ”ከትግራይ ህዝብ ጋር መታረቅ” የሚል ዜማ ይዞ ብቅ ብሏል። ህወሃት የነፃ አውጪ ስሙን እንኳን ሳይቀይር የ80 ሚሊዮን ህዝብ ገዢ እኔ ነኝ ብሎ ድርቅ ማለቱን እናውቃለን። ስማችሁን ቀይሩና አገሪቷን ግዙ ቢባሉም በጀ አላሉም። ይሄን ስም ይዘው በትግራይ ህዝብ ላይ ተንጠላጥለው አገሪቷን ሲዘርፉ ኖሩ። በዚህም ዘረፋ ትናንት ወደ ሥልጣን ሲመጡ ሲሙኒ እክሳቸው ውስጥ ያልነበራቸው ዛሬ በዓለማችን ከሚታወቁ ሃብታሞች ተርታ ለመግባት ችለዋል። መሪያቸው የነበረው መለስ ዜናዊ 3 ቢሊየን ዶላር ባለቤት በመሆን ከዓለም ሃብታም መሪዎች ተርታ ስሙ የሚነሳ ሁኗል። ሌሎችም እንደየአቅማቸው በሚሊየን የሚቆጠር ንብረት ዘርፈው ኢንቨስተሮች እኛ ነን ብለዋል። በትግራይ ነጣ አውጪነት ሥም ተደራጅተው የብዙ ንፁሃን ዜጎችን ደም አፍሰው፤ ብዙዎችን ለስደት ዳርገው፤ የብዙ ዜጎችን ቤተሰብ በትነው ሲያበቁ የትግራይን ህዝብ ይቅርታ እንጠይቅ ተባብለው ትግራይ ወርደዋል። ይሄን የሰማ ሌላው ህዝብ ሊሰማው የሚችለውን ቁጣ የትግራይ ህዝብ ያጣዋል ብለን አናስብም።ሌላው በተበደለ፤ ሌላው በተገፋ፤ ሌላው ጦሙን ባደረ፤ ሌላው ለስደት በተዳረገ የትግራይ ህዝብ ይቅርታ የሚጠየቅበት ምክንያት ምን እንደሆነ ግልፅ አይደለም። ለማንኛውም የትግራይ ህዝብ የህወሃት ዋሻና መደበቂያ አልሆንም ብሎ እንቅስቃሴ ጀምሮአል። ይሄ እጅግ የሚደገፍና ግዜው የሚጠይቀው የሞራል ግዴታም ነው። በትግራይ ሥም ተደራጅተው “ለትግሬ ብለን” እያሉ የንፁሃንን ደም ሲያፈሱ እና ቤተሰብ እየበተኑ ሜዳ ላይ ሲጥሉ እያዩ ዝም ማለት የግፉ ተባባሪ ያደርጋል እንጂ ከደሙ የሚያነፃ አይሆንም። ለዚህም ነው የትግራይ ህዝብ ወያኔ በስሙ መነገዱን እንዲያቆም ጠመንጃ ይዞ እስከመፋለም የተነሳው። የትግራይ ህዝብ ዲሞክራሲያዊ ድርጅት /ደሚት/ የትግል አላማ ይህንን ወያኔ የፈጠረውን ጥላቻ የመስበር ተልዕኮ ያለው ነው። የትግራይ መሬትና የትግራይ ህዝብ ከእንግዲህ የወንጀለኛው ህወሃት መደበቂያ ዋሻ አይሆንም።
ህወሃት ከህዝብና ከአገር ለመታረቅ ከፈለገ በትግራይ ሥም ላለፉት 23 አመታት ለፈጸመው ወንጀል ይቅርታ ፍለጋ ትግራይ መንደሮች ድረስ መዝለቅ አይጠበቅበትም። ከትግራይ ውጪ ተጀምሮ ትግራይን ባጥለቀለቀው ኢፍትሃዊነት፤ ግፍና መከራ ጸጸት ከተሰማው ሥልጣን ለመልቀቅ መዘጋጀትና ለኢትዮጵያዊያን ለማስረከብ በመወሰን እዚያው ምንሊክ ቤተመንግሥት ሆኖ አዋጅ ማስነገር ይችላል። ለዚህ ዝግጁነት ተግባራዊ እርምጃ ለምሳሌ የታሰሩትን የፖለቲካ እስረኞች፤ ጋዜጠኞች፤ የሃይማኖት መሪዎችን መልቀቅ፤ የሥልጣን ማስጠበቂያ አድርጎ በዘረኝነት መስፈርት የገነባውን የአፈና ተቋማት ማፍረስ፤ ህዝብ ሃሳቡን በነጻነት የሚገልጽበትንና መሪዎቹን በነጻነት የሚመርጥበትን ዕድል በመፍቀድ ማረጋገጥ ይችላል።
ይህ እስካልሆነ ድረስ ከአደዋ ወይም ከሸሬ የወያኔን ዕድሜ የሚያራዝም ይቅርታ ጨርሶ የሚታሰብ አይደለም። በ23 አመት የሥልጣን ዘመን የተገኘው ዘረፋ አልበቃ ብሎ ሥልጣን ላይ ለመንጠልጠል መንከላወስ ውጤቱ ሁሉንም ማጣት ነው።
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!!!
source www.ginbot7.org
No comments:
Post a Comment