የወያኔ መንግስት የኢትዮጵያን ብሄር ብሄረሰቦች አጋጭቶ በመካከላቸው ጥርጣሬና መፈራራት አንግሶና የታሪክ ጠባሳዎችን እንደ አዲስ በመጓጐጥ እያደማ ከፋፍሎ ለመግዛት ካለመታከት ያደረጋቸው ሙከራዎች ገና ፍሬ ባያፈሩም ቁጥቋጦዎቹ መብቀል ጀምረዋል። እዚህም እዚያም በካድሬዎች የውስጥ ለውስጥ ተልእኮ የሚለኮሱ እሳቶች መብለጭለጭ ጀምረዋል። ሌላው ቀርቶ በአንድ ብሄረሰብ መሃል ሳይቀር በከባቢ ልዩነቶች ብቻ መናቆሮችና መጋደሎች እያስተዋልን ነው። ሰሞኑን በጉጂና በቦረና ኦሮሞዎች መካከል የወያኔ ሎሌዎች በሚያበረታቱት አተካሮ የብዙ ወገኖቻችን ህይወት ጠፍቷል። ሰዎች ከኑሮአቸው ተፈናቅለዋል። ወያኔ እንደኳስ ጨዋታ ተመልካች ዳር ሆኖ ይመለከታል፣ ያጨብጭባል።
ሰሞኑን ባህርዳር ከተማ ውስጥ በተካሄደ የስፖርት ውድድር ላይ አሳፋሪ ክስተት ነበር። ለሰሚው የሚቀፍ ብልግና የተቀላቀለበት ስድብና ቁርቋሶ አይተናል። ከበስተጀርባ ሆነው ይህንን ለፍቅር ብቻ ሊውል የሚገባ የስፖርት ዝግጅት መርዝ ረጭተውበታል። ከዚህ ላቅ ያሉ የተንኮል ድግሶችም ተደግሰው ህዝብ ውስጥ በወያኔ ከተነዙ የመርዝ ቢልቃቶች ውስጥ ስራ ላይ ሳይውሉ ቀርተዋል።
ይህ በታሪካችን ታይቶ የማይታወቅ ዘር የሚዘራው ወያኔ ያልተከፋፈለ ህዝብ አይገዛልኝም በሚል ፍልስፍና እንደሆነ በተደጋጋሚ እያየን ነው። ሶማሌ ክልል ውስጥ በተቋቋሙ ልዩ ፖሊስ በሚል ስያሜ በሚጠሩ የመንግስት ሃይሎች ጥቃት ቁጥሩ እጅግ በርካታ የሆነ የኦሮሞ ማህበረሰብ ከኖረበት መሬት ተጠራርጎ እንዲወጣ ተደርጓል። ብዙዎቹ ተገድለዋል። ብዙ ደም መቃበት ተፈጥሯል። በየክልሉ ምስኪን የአማራ ገበሬዎችን መሬት ንብረት በመንጠቅ አከባቢውን ለቀው እንዲሄዱ አድርገዋል። መሄጃ የለንም ያሉትንም ቀጥቅጠው እንደገደሏቸው ሰሞኑን ከጅባትና ሜጫ አካባቢ ያሉ መረጃዎችን አይተናል።
እነዚህ በየቦታው የሚብለጨለጩ እሳቶች በዚህ ከቀጠሉ ሁላችንም ወደ ሚያቃጥልና የሚለበልብ የሰደድ እሳት ማደጉ አይቀርም። የወያኔ ባለሟሎች ካለምንም ይሉኝታና ማሰላሰል ይህንን እሳት እያራገቡ ይገኛሉ።
ይህንን አደገኛ አዝማሚያ በንጭጩ ማስወገድ የሚችለው ራሱ ህዝቡና የኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ የነጻነት ሃይሎች ድምጽና ህብረት እንጂ የወያኔ መንግስት አይደለም። ስለዚህ ህዝቡ በተለይም ወጣቶች ከዚህ ወጥመድ ሰብረው እንዲወጡ ግንቦት 7 የነጻነት፣ የፍትህና የዲሞክራሲ ንቅናቄ አጥብቆ ያሳስባል። ተመሳሳይ ተንኮሎችንም ማጋለጡን ይቀጥላል። የብሄርሰብ ልሂቃንም ይህንን መርዝ እንዲቋቋሙ፣ ይልቁንም ወያኔ እንዳይመቸው ይበልጥ መቀራረብና ፈተናውን በጋራ እንድንቋቋም ጥሪያችን በድጋሜ እናቀርባለን።
ያልተዘራ አይታጨድም። ወያኔ የዘራልን መርዝ የሚያፈራው መርዝን እንጂ ሌላ አይደለም። ልዩነቶቻችን እንደዘመኑ በሰለጠነ ዲሞክራሲያዊ መንገድ እንጂ በተያዘው መንገድ ማስወገድ አይቻልም።
ዞሮ ዞሮ በዚህ ሳይጣናዊ የወያኔ መሰሪ ሴራ ለምትፈስ ለእያንዳንዶ የደም ጠብታ ተጠያቂው የወያኔ ጉጅሌ መሆኑን አጥብቀን እናሳስባለን። በመሆኑም ለመከፋፈል ከመመቻቸት ይልቅ አንድነታችን በማጥበቅ የነጻነት ሃይሎችን በመቀላቀል ራሳችን እና የሀገራችንን ህልውና ከዚህ ከወያኔ የመከፋፈል መርዝ እንታደግ።
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!!!
source www.ginbot7.org
No comments:
Post a Comment