Saturday, October 4, 2014

ሰልጣኙንም አሰልጣኙንም ያንገሸገሻቸዉ ሥልጠና

አባትና የ10ኛ ክፍል ተማሪ ልጁ አምርረዉ ሲጨቃጨቁ እናት ትደርስና . . . . እባክሽ ልጄ አባትሽ የሚልሽን ለምን አትሰሚም ብላ ልጇን ትቆጣታለች። ልጅት ከተቀመጠችበት ትነሳና ምነዉ እማዬ ምኑን ነዉ የምሰማዉ፤ አባዬኮ እሱ እራሱ የማያዉቀዉን ነገር ላሳይሽ እያለኝ ነዉ ብላ ንግግሯን ሳትጨርስ በቁጣዉ ብዛት ፊቱ እንደ ፊኛ ያበጠዉ አበቷ ካንቺ ማወቅ ዬኔ አለማወቅ ይሻላል፤ ይልቅ የምልሽን ስሚ ብሎ ጮኸባት። ወጣቷ ተማሪ ወላጅ አበቷ ከስምንተኛ ክፍል በላይ ዘልቀዉ እንዳልተማሩ ብታዉቅም ለግዜዉ ማድረግ የምትችለዉ ምንም ነገር አልነበረምና እሽ አባዬ ብላ አባቷን መስማት ጀመረች። ይህ የአባትና የልጅ ስሚኝ አልሰማም ጭቅጭቅ ባለፉት ሁለት ወራት መሀይሞቹ የወያኔ ካድረዎችና የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በየስልጠና አዳራሹ ያደረጉትን ፍጥጫ አስታወሰኝ። ይህ አብዛኛዉን ዕድሜያቸዉን ትምህርት በመማር በሳለፉት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችና በወጉ ስምንተኛ ክፍልን ባላጠናቀቁ የወያኔ ካድሬዎች መካከል በክረምቱ ወራት ተጀምሮ አሁን ድረስ የዘለቀዉ የ”አሰለጥናለሁ አታሰለጥንም” ትንግርታዊ ድራማ ወያኔ አስካሁን ከሰራቸዉ ድራማዎች በአይነቱ ለየት ያለ ድራማ ነዉ።
የወያኔ ምርጫዎች ምንም አይነት ዉድድር የማይታይባቸዉ ማንም ተወዳደረ ማንም ወያኔ ብቻ የሚያሸንፍባቸዉና ምርጫዎቹ ከመካሄዳቸዉ በፊት የት ቦታ እነማን ማሸነፍ እንዳለበቸዉ ተወስኖ ያለቀላቸዉ የለበጣ ምርጫዎች ናቸዉ። ወያኔ ግን “ሌባ ላመሉ ዳቦ ይልሳል” እንደሚባለዉ ምርጫዉ በቀረበ ቁጥር የሚያክለፈልፍ በሽታ ይይዘዋል። ኢትዮጵያ ዉስጥ በ1997ና በ2002 ዓም የተደረጉትን ምርጫዎችና እርግጠኞች ነን አሁንም በ2007 ዓም የሚደረገዉን ምርጫ የሚለያያቸዉ ነገር ቢኖር በእያንዳንዱ ምርጫ መኸል የአምስት አመት ልዩነት መኖሩ ነዉ እንጂ የምርጫዉን ዝግጅት፤ ሂደትና ዉጤት በተመለከተ ይህ ነዉ ተብሎ ሊነገር የሚችል ልዩነት የለም። ሁሉም ምርጫዎች የሚካሄዱት ወያኔ የምርጫ ተቋሞች፤ ሜድያዉንና ፍርድ ቤቶችን ሙሉ በሙሉ በሚቆጣጠርበት ሁኔታ ዉስጥ ነዉ። በዚህ ላይ ቅድመ ምርጫዎችን የሚቆጣጠረዉ፤ በምርጫዉ ብቸኛ ተወዳዳሪ የሆነዉና ህዝብ የሰጠዉን ድምጽ የሚቆጥረዉ ወያኔ እራሱ ነዉ። ይህም ሁሉ ሆኖ ወያኔ ከሱ ዉጭ ማንም ምርጫዉን እንደማያሸንፍ በልቡ እያወቀ አምስት አመት እየቆጠረ የሚመጣዉ ምርጫ በቀረበ ቁጥር ግርግር መፍጠር ይወዳል። በ1997 በተደረገዉ ምርጫ ማንም አያሸንፈኝም ብሎ ሜድያዉንና የፖለቲካ ምህዳሩን ትንሽም ቢሆን ለቀቅ አድርጎ የነበረዉ ወያኔ በ2002 ዓም ይጋፉኛል ብሎ የጠረጠራቸዉን ሁሉ ማሰር፤ መደብደብና እንቅስቃሴያቸዉን መግታት ጀመረ። አሁን በ2007 ዓም ደግሞ ገና በግንቦት ወር ለሚካሄደዉ ምርጫ የኢትዮጵያን ወጣት ካልተቆጣጠርኩ በሚል ትልቅ ዘመቻ ጀምሮ በከፍተኛ በሁለተኛ ደረጃና ዩኒቨርሲቲ ዉስጥ የሚገኙትን የአገሪቱ ወጣቶች በሥልጠና ሰበብ ወያኔያዊ የፖለቲካ ጠበል እያጠመቃቸዉ ነዉ።
ብዙ ኢትዮጵያዊያን ወያኔን ዘረኛ ነዉ፤ ጎጠኛ ነዉ፤ ነብሰ ገዳይ ነዉ ይሉታል። አዎ እነዚህ ሁሉ የወያኔን ማንነትና ምንነት በትክክል የሚያሳዩ ቃላት ናቸዉ። ወያኔ ግን ከእነዚህ ዉጭ ሌሎች ብዙ መገለጫዎች አሉት፤ ለምሳሌ ወያኔ መዋሻት የማይሰለቸዉ ዉሸታም ነዉ፤ ዕኩይ ነዉ፤ ጨካኝና የለየለት መብት ረጋጭም ነዉ። እነዚህ የወያኔ ባህሪያት ሁሉ ያናድዱናል ወይም ያስቆጡናል እንጂ አይገርሙንም ወይም እየኮረኮሩ አያስቁንም። ጉደኛዉ ወያኔ የሚገርሙና የሚያስቁ ባህሪያትም አሉት። ወያኔ የቁጥር ጨዋታ ይወዳል፤ በተለይ ከቁጥርና ከቁጥርም በዛ ካለ ቁጥር ጋር ለየት ያለ ፍቅር አለዉ። ለምሳሌ የኢትዮጵያ የአገር ዉስጥ ምርት ከዉጭም ከዉስጥም ተገፍቶ 5% ከጨመረ ወያኔ የሚነግረን 10% አደገ ብሎ ነዉ። ኢትዮጵያ ዉስጥ የትምህርት ጥራት ተንኮታኩቶ ከመዉደቁ የተነሳ ከዩኒቨርሲቲ ተመርቀዉ ወደ ስራ አለም በሚገቡ ተማሪዎችና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸዉን ጨርሰዉ ኮሌጅ በሚገቡ ተማሪዎች መካከል ያለዉ ልዩነት ትንሽ ነዉ፤ ወያኔ ግን በኔ ዘመነ መንግስት የዩኒቨርሲቲዉ ብዛት ብቻ ሳይሆን ከዩኒቨርሲቲ የሚመረቁ ተማሪዎች ብዛት ከ300% በላይ አደገ እያለ ይፏልላል። ካለፈዉ ሐምሌ ወር ጀምሮ ያለፍላጎታቸዉና ያለፈቃዳቸዉ በግድ ወደ ሥልጠና ማዕከላት እየገቡ የወያኔን ርካሽ ፕሮፓጋንዳ እንዲጋቱ የሚገደዱ ወጣቶችም ጉዳይ ይህንኑ ወያኔ ከቁጥርና ከብዛት ጋር የተጠናወተዉን ፍቅር የሚያሳይ ነዉ። ይህ ወያኔ በየክልሉ ሥልጠና ብሎ የጀመረዉ ቧልት የሰልጣኛቹን እዉቀት የሚያዳብር አይደለም ወይም ለአገራችን ለኢትዮጵያም በምንም መልኩ የሚጠቅም አይደለም። የሥልጠናዉ ብቸኛ አላማና ጥቅም በወጣቱ ላይ ተፅዕኖ በማሳደር የወያኔን አባላት ማብዛት ነዉ። ወያኔ ድርጅታዊ የፓርቲ ስራዎችን የሚሰራዉ መንግስታዊ ተቋሞችን በመጠቀም ከመንግስት ካዝና በሚወጣ ገንዘብ ነዉና እሱን የሚያስደስተዉ በሚሊዮን የሚቆጠሩ አባላት አሉት ተብሎ መነገሩ ነዉ እንጂ እነዚህ አባላት ታማኝ ይሁኑ አይሁኑ ወይም ድርጅታዊ ስራ ይስሩ አይስሩ ለወያኔ ጉዳዩ አይደለም።
ወያኔ በዕረፍት ላይ የሚገኙ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን ከያሉበት በግድ አስመጥቶ ሥልጠና እንዲወስዱ ለማድረግ የወሰዳቸዉ እርምጃዎች ሁሉ በወያኔና በተማሪዎቹ መካከል ያለዉን ሰፊ የፖለቲካ ልዩነት አጉልቶ ከማዉጣቱ ባሻገር ይህ ሳይጀመር የከሸፈዉ ስልጠና ለወያኔ ምንም የፈየደዉ ፋይዳ የለም። እንዳዉም አብዛኛዉ ተማሪ የወያኔ መሪዎችን አንገት የሚያስደፋ ጥያቄዎችን በመጠየቅ ሥልጠና የሚያስፈልገዉ ለተማሪዎቹ ሳይሆን ለራሳቸዉ ለአሰልጣኝ ነን ባዮቹ መሆኑን በተግባር አሳይቷል። በብዙዎቹ የስልጠና አዳራሾች የወያኔ ካድሬዎች ተማሪዎቹ የሚጠይቁትን ጥያቄ መመለስ አለመቻላቸዉ ብቻ ሳይሆን ካድሬዎቹ በሚጠየቁት ጥያቄ እየተበሳጩ ጥርሳቸዉን ሲነክሱ ታይተዋል። በእርግጥም ጎንደር ዉስጥ የነበረዉን ጄኔሬተር ነቅላችሁ ዬት አደረሳችሁት ከሚል አፋጣጭ ጥያቄ ጀምሮ አንዳርጋቸዉ ጽጌን የሚመለከቱ ጥያቄዎችን በጠየቁ ተማሪዎች ላይ አሰልጣኝ ካድሬዎች “ከእናንተ ጋር በኋላ እንገናኛለን” እያሉ ሲዝቱ ተደምጠዋል።
ኢትዮጵያ ትናንትም ዛሬም ካለ ለጋሽ አገሮች ዕርዳታ መንፈቅ መዝለቅ የማትችል ደሃ አገር ናት፤ ሆኖም የወያኔ መሪዎችና ቤተሰቦቻቸዉ የሚዘርፉትን ገንዘብና አላግባብ የሚያባክኑትን የአገር ሃብት የተመለከተ ማንም ሰዉ ድርጊታቸዉ ከደሃዋ አገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ጋር በፍጹም እንደማይገናኝ ለመገንዘብ ግዜ አይፈጅበትም። ወያኔ ገነባሁ ብሎ የሚያፈርሳቸዉንና በየስብሰባዉና በየጉባኤዉ ከሚያባክነዉ ግዙፍ የአገር ኃብት ዉጭ ከሰሞኑ ምንም አገራዊ ጥቅም በሌለዉና ሠልጣኞቹ አንፈልግም ብለዉ ለተዉት ሥልጠና የሚያባክነዉ የህዝብና የአገር ገንዘብ እጅግ በጣም ብዙ ነዉ። ለምሳሌ ለአሰልጣኝ ካድሬዎች ከሚወጣዉ የትርንፖርትና የዉሎ አበል ዉጭ ለእያንዳንዱ ሰልጣኝ ተማሪ በቀን የሚከፈለዉ ሃምሳ ብር ቁጥራቸዉ ከ600 ሺ በላይ በሆኑ ሰልጣኝ ተማሪዎች ልክ ሲሰላ እጅግ በጣም ብዙ ገንዘብ ነዉ።
ለመሆኑ ዜጎች የሚላስና የሚቀመስ አጥተዉ በሚራቡበት አገር፤ ወጣቶች ስራ ፍለጋ ያደጉበትን መንደር ጥለዉ ባሕር እየተሻገሩ በሚሰደዱበት አገርና የገንብዘብ እጥረት እየተባለ ብዙ ፕሮጀክቶች በሚታጠፉበት አገር ወያኔ ከየት እያመጣ ነዉ በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ እየከፈለ ምንም እርባና የሌለዉ የፖለቲካ ሥልጠና ሥልጠናዉ በፍጹም ለማያስፈልገዉ የህብረተሰብ ክፍል የሚሰጠዉ? ደግሞስ ከዉጭ አገር ምንጮች ምንም አይነት የገንዝብ እርዳታ እንዳያገኙ በህግ የተከለከሉ የፖለቲካ ድርጅቶች የስራ ማስኬጃ ወጪያቸዉን መሸፈን አቅቷቸዉ በሚንገዳገዱበት አገር ምን ቢደረግ ነዉ ወያኔ የራሱን ፓርቲ ስራዎች በመንግስትና በህዝብ ገንዘብ የሚያሰራዉ?
የወያኔና የገንዝብ ጉዳይ ከተነሳ እነዚህ ጉደኞች ቢነገር ቢነገር የማያልቅ ከገንዘብ ጋር የተቆራኘ ብዙ የቆሸሸ ታረክ አላቸዉ። ከሰሞኑ ኢትዮጵያ ዉስጥ የአገሪቱን የአየር ሞገዶች ከዳር እስከ ዳር ያጨናነቀዉ ከዚሁ ከወያኔ የረጂም ግዜ ቆሻሻ ታሪክ ጋር የተያያዘዉ የገንዘብ ጉዳይ ነዉ። ከሰሞኑ የኢትዮጵያን ባንኮች፤ ትላልቅ መደብሮችና ዘመናዊ የመገበያያ አዳራሾች በብዙ መቶ ሚሊዮኖች በሚቆጠር ሀሰተኛ ገንዘብ ተጨናንቀዋል። ይህ ማን፤ መቼ፤ ከየትና እንዴት እንዳሰራጨዉ የማይታወቅ የሀሰተኛ ገንዝብ ዝርጭት ኢትዮጵያ ዉስጥ እያንዳንዱን ሰዉ እያነጋገረ ነዉ። የወያኔ ፖሊሶች ከየባንኩና ከየገበያ አዳራሹ በየቀኑ ከፍተኛ ቁጥር ያለዉ ሀሰተኛ የብር ኖቶች እየሰበሰቡ መሆናቸዉን ቢናገሩም ከዚህ ሀሰተና ገንዘብ ስርጭት በስተጀርባ የማን እጅ እንዳለበት ግን ምንም የተነፈሱት ነገር የለም። እንደዚህ ብዛት ያለዉ ሀሰተኛ የገንዘብ ኖት ደግሞ አቅምና እዉቀት በሌላቸዉ ተራ ወንጀለኞች የሚሞከር ወንጀል አይደለም። ለዚህም ይመስላል ብዙ ኢትዮጵያዉያን በዚህ ሀሰተኛ ገንዘብ ስርጭት ዉስጥ ያለምንም ጥርጥር የወያኔ ባለስልጣኖች እጅ አለበት ብለዉ በድፍረት አፋቸዉን ሞልተዉ የሚናገሩት። መቼም መሬት ቆፍሮ ቦምብ እየቀበረ በተቃዋሚዎች የሚያሳብበዉና በፈንጂ ህዝባዊ ተቋሞችን እያፈረሰ ሽብርተኛ ብሎ በፈረጃቸዉ ድርጅቶች ላይ ጣቱን የሚቀስረዉ ወያኔ የደረሰበትን ከፍተኛ የገንዘብ ጉድለት ለመሙላት ሀሰተኛ ገንዘብ አሰራጭቶ ሊያጠፋቸዉ በሚፈልጋቸዉ ሰዎችና ቡድኖች ላይ አያመካኝም ማለት አይቻልም። ለሁሉም የወያኔ ነገር አንቺዉ ታመጪዉ አንቺዉ ታሮጪዉ ነዉና ይህ የሀሰተኛ ገንዘብ ስርጭት የራሱ የወያኔ ስራ እንደሆነ ከራሱ ዉስጥ አዋቂ ምንጮች የምንሰማበት ግዜ ሩቅ አይደለም። በነገራችን ላይ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዉያንን የሙጥኝ ብሎ ተጣብቆ የሚያሰቃያቸዉ የዋጋ ንረት መሠረታዊ መንስኤዉ መለስ ዜናዊ በህይወት ከነበረበት ግዜ ጀምሮ ከአገሪቱ የማምረት አቅም በላይ በሆነ መልኩ በገፍ እየታተመ ወደ ኤኮኖሚዉ ዉስጥ እንዲገባ የተደረገዉ የገንዘብ አቅርቦት ነዉ። ይህ ዘንድሮ ስሙን ቀይሮ “ሀሰተኛ የገንዝብ ስርጭት” ተብሎ አገራችንን የሚያምሳት በሽታም የዚሁ የተለመደ ወያኔ እያተመ የሚያሰራጨዉ የገንዘብ አቅርቦት ችግር አካል ለመሆኑ ምንም ጥርጥር የለዉም። አለዚያማ ወያኔ በነጋ በጠባ ሚሊዮንና ቢሊዮን እያለ የሚያባክነዉ ገንዘብ ከዬት ይመጣል?
ስልጠና በየትኛዉም ማህበረሰብ ዉስጥ የእዉቀትና የልምድ ልዉዉጥ ለማድረግ የሚረዳ ጠቃሚ ተግባር ነዉ፤ ሆኖም ስልጠና ሲባል አላማ፤ አትኩረትና ግብ ኖሮት በተወሰነ ቡድን ወይም ቡድኖች ላይ የሚያነጣጥር የእዉቀትና ልምድ መቀባበያ መሳሪያ ነዉ እንጂ እንዳዉ በጅምላ የአንድ አገር ህዝብ እንዳለ ተመሳሳይ ስልጠና ይዉስድ እየተባለ የሚደገስ የጨረባ ተዝካር አይደለም። ደግሞም ስልጠና አሰልጣኝና ሰልጣኝ ተግባብተዉና ሁለቱም ሚናቸዉን ወድደዉና ፈቅደዉ የሚካሄድ የጋራ እንቅስቃሴ ነዉ እንጂ ሠልጣኝ አልሰልጥንም ካለና አሰልጣኝ ደግሞ ጥያቄ የጠየቀዉን ሁሉ “ቆይ ጠብቀኝ” እያለ የሚዝትበት ከሆነ ነገሩ ሥልጠና መሆኑ ቀርቶ ጦርነት ይሆናል። ለመሆኑ ወያኔ የአገሪቱን ወጣቶች ሥልጠና ብሎ ሰብስቦ ምንድነዉ የሚላቸዉ? መልሱ ቀላል ነዉ። ከብዙዎቹ ሰልጣኞች አንደበት በግልጽ እንደሰማነዉ፤ የወያኔ ካድሬዎች በየስልጠናዉ አዳራሽ የሚናገሩት በሚቀጥለዉ ምርጫ ኢህአዴግን ካልመረጣችሁ የወደፊት ዕድላችሁ ይጨልማል፤ ከሐይማኖት አክራሪዎች እራሳችሁን አጽዱ ወይም ከሽብርተኛ ድርጅቶች ጋር እንዳትተባበሩ እያሉ ነዉ። ወያኔ በስልጣን ላይ በቆየባቸዉ አመታት ህይወቱ እንደ ሐምሌ ጨለማ የጨለመበት የኢትዮጵያ ወጣት ግን በየስልጠና አዳራሹ በተደጋጋሚ የሚጠይቀዉ እነሱ ሽብርተኛ ብለዉ ያሰሯቸዉን ጋዜጠኞችና የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች ባስቸኳይ እንዲፈቱና ወያኔዎችን እራሳቸዉን በሐይማኖት ጉዳይ ጣልቃ አትግቡ እያለ ነዉ።
ባለፈዉ የአዲስ አመት ዋዜማ ምሽት የግንቦት 7 የፍትህ፤ የነጻነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ሊ/መንበር ለኢትዮጵያ ወጣቶች ኑና ለነጻነት፤ ለፍትህና ለእኩልነት አብረን እንታገል የሚል አገራዊ ጥሪ አድረገዋል። በየዘመኑ ለወገኖቹ መብትና ነጻነት መከበር ሽንጡን ገትሮ የታገለዉ የኢትዮጵያ ወጣት የነጻነት መሪዉ ያቀረበለትን የፍትህና የእኩልነት ትግል ጥሪ ረግጦ ከወያኔ ጋር በተላላኪነት ከሚያስተሳስረዉ ሥልጠና ጋር በፍጹም እንደማይተባበር ሁላችንም እርግጠኞች ነን። ዛሬ ዕድሜዉ ከ35 አመት በታች የሆነ ኢትዮጵያዊ ወጣት አብዛኛዉን ዕድሜዉን በወያኔ ስርዐት ዉስጥ የኖረ ወጣት ነዉ። ከዚህ በተጨማሪ የዚህ ዘመን የኢትዮጵያ ወጣት ወንድሙ፤ ዘመዱ ወይም የቅርብ ጓደኛዉ በወያኔ ነብሰ ገዳዮች ሲገደሉ በአይኑ እየተመለከተ ያደገ ወጣት ነዉ። ይህ ወጣት የወያኔ በደልና ግፍ የሚነገረዉ ወጣት ሳይሆን ይህንን በደልና ግፍ ለማቆም ቆርጦ የተነሳ ወጣት ነዉ። ይህ ወጣት ወያኔ ሥልጠና እያለ የሚፈጥርለትን አጋጣሚ ሁሉ እየተጠቀመ እራሱንና ወገኖቹን ነጻ ያወጣል እንጂ በሥልጠና ስም ከወያኔ በሚመጣለት ኮቶቶ እጅና እግሩን አስሮ የወያኔ ባሪያ ሆኖ አይኖርም። ለዚህ ቆራጥና አርቆ አስተዋይ ለሆነ ወጣት ያለን መልዕክት አይዞህ፤ በርታ፤ ጽና በድል የምንገናኝበትና የአገራችን ባለቤት የምንሆንበት ቀን ቅርብ ነዉ የሚል ወገናዊ መልዕክት ነዉ።
source www.ginbot7.com

የኢድ አል አድሀ አረፋ በዓልን በማስመልከት ከድምፃችን ይሰማ የተላለፉ 4 ነጥቦች

ዒዳችንን ‹‹የአንድነት ዒድ›› ስንል ሰይመነዋል!
አርብ መስከረም 23/2007
ዒዳችንን ‹‹የአንድነት ዒድ›› ስንል ሰይመነዋል! ላለፉት ሶስት ዓመታት አላህን በብቸኝነት በማምለክ ገመድ ተሳስረን፣ ከመቼውም ጊዜ በተለየ ሁኔታ ለአንድነታችን ትኩረት ሰጥተን የተቃጣብንን ሃይማኖታዊ የመብት ጥሰት በመቃወም ቆይተናል፡፡ የዛሬዋ የዒድ ዕለት ተፈጥሯዊ ባህሪዋ ኾኖ በልዩ መልኩ ከምትዘከርባቸው ክስተቶች አንዱ አላህን በብቸኝነት በማምለክ በአንድነት መተሳሰር፣ ይህንኑም በተግባር ማሳየት ነው፡፡ በተጨባጭ በዓለም እየሆነ ያለውም ይኸው ነውና እኛም ይህንኑ ወርቃማ አጋጣሚ ተጠቅመን አንድነታችንን በአንድያው ጌታችን ይበልጥ ለማጠንከር ተነስተናል፤ አንድነታችን የድላችን መሰረት ነውና!
muslim 1
በዘንድሮው ዒድ አል-አድሃ ለዲናችን መከበር ያለንን ፅናት የምናጎለብትበት፣ አንድ ሆነን በአንድነት የምንታይበት፣ አንድነታችን እንዲሳሳ ለሚፈልጉ ሁሉ እንደማይሳካላቸው የምናሳይበት ይሆናል፡፡ ሁላችንም በአዲስ አበባ ስታዲየም በመገኘት በክልሎች ደግሞ በተለመዱት የስግደት ቦታዎች በመገኘት ስግደታችንን አንፈፅማለን፡፡ ምንም ዓይነት ተቃውሞ ባለማሰማት ተቃውሞ በድምፅ ብቻ ሳይሆን በልቦና ውስጥ በሚኖር ፍፁም አንድነት እንደሚፀባረቅም ጭምር የምናሳይበት ዒድ ይሆናል፡፡ ህገ ወጥ መንገድ መከተልን ምርጫው ላደረገው መንግስትም ለሚከተለው ህገ ወጥ መንገድ የማንመች፤ በሰላማውያን ላይ ግፍ መፈፀምን ለሚሻው አካል በጅ የማንል መሆኑን፣ በተመሳሳይ ህዝብን የሚንቁ አካላት በምንከተለው የሰከነ መንገድ አላማቸው እንዲከሽፍና ነገም ከተጠያቂነት እንዳያመልጡ ሁኔታዎችን በማመቻቸት ሰላማዊነታችንን ጠብቀብ ሚዛናችንን የማንስት መሆኑን በተግባር የምናሳይበትም ነው፡፡
በመጨረሻም
1. ባለፉት ረጅም አመታት እናደርገው እንደነበረው ሁሉ በበዓላችን ሁላችንም በአንድ ላይ በአዲስ አበባ በስታዲየም፣ በክልሎች ደግሞ በተለመዱት የስግደት ቦታዎች በመሰባሰብ በጋራ ሃይማኖታዊ ሥነ- ስርዓታችንን በአላህ ፈቃድ እንፈፅማለን፡፡ በነገው የዒድ አል-አድሃ በዓል ባለፈው የዒድ አል-ፈጥር በዓል ላይ በከፊል እንደተስተዋለው በየቦታው ተበታትኖ ከመስገድ ተቆጥበን ሁላችንም ለዒድ ሰላት ወደ ስታዲየም በአንድ ላይ ሆነን እንድንጎርፍ፣ መንገዶች ሁሉ ወደ ስታዲየም እንዲያመሩ ጥሪው ተላልፏል፡፡
2. በዒድ ቀን ከሰላት በፊትም ሆነ ከሰላት በኋላ ምንም ዓይነት ተቃውሞ አይኖርም፡፡ በመሆኑም ምንም ዓይነት ተቃውሞ ከሰላት በፊትም ሆነ በኋላ ባለማሰማት ተቃውሞ በድምፅ ብቻ ሳይሆን በልቦና ውስጥ በሚኖር ፍፁም አንድነት እና የአምልኮ መንፈሳዊነት እንደሚፀባረቅም ጭምር እናሳያለን፡፡
3. ይሁንና በማይወክሉን ሹመኛ የመጅሊስ አካላት እና ግፍና በደል እየፈፀሙብን በሚገኙት የመንግስት አካላት ንግግር ከተደረገ ፈፅሞ የሀሰት ፐሮፓጋንዳ የምንሰማበት ጆሮ እንደሌለን ለማሳየት ጆሯችንን በእጃችን በመያዝ ለመስማት ፈቃደኞች እንዳልሆንን ተምሳሌታዊ በሆነ ስርዓት እንገልፃለን እንይዛለን፡፡
4. ከዒድ ሰላት መልስ የ ‹‹ኡድሂያ›› እርድ ላይ በትግሉ ተጎጂ የሆኑ ቤተሰቦችን፣ ደካሞችን እና የተቸገሩ ወገኖቻችንን በጠንካራ ወንድማዊነት እንድናስታውስም አደራ እንላለን፡፡
ትግላችን እስከድል ደጃፎች በአላህ ፈቃድ ይቀጥላል!
ድምፃችን ይሰማ!
አላሁ አክበር!
ምንጭ ዘ-ሐበሻ

Friday, October 3, 2014

የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮች 28 ቀን ተቀጠረባቸው

• በሽብርተኝነት ተጠርጥረው የተያዙ ሌሎች 10 ያህል ዜጎችም ቀርበዋል
በሽብርተኝነት ተከሰው ማዕከላዊ የሚገኙት የሰማያዊ ፓርቲ የጋሞጎፋ ዞን አመራሮች ዛሬ መስከረም 23/2007 ዓ.ም ከሰዓት በኋላ 8፡00 አራዳ ችሎት ቀርበው 28 ቀን ተቀጠረባቸው፡፡ የሰማያዊ ፓርቲ የጋሞጎፋ ዞን ምክትል ሊቀመንበር አቶ ፍቃዱ አበበ እንዲሁም የዞኑ የድርጅት ጉዳይ ኃላፊ ኢንጅነር ጌታሁን አርባምንጭ ውስጥ ወር ከ15 ቀን ያህል ታስረው የነበር ሲሆን ወደ ማዕከላዊ ከተዛወሩ 24 ቀናት በላይ እንደሆናቸው ታውቋል፡፡ አመራሮቹ ጥቅምት 21 ከሰዓት ይቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ታሳዎቹ በቤተሰብ፣ በኃይማኖት አባትና በጠበቃ እንዳይጎበኙ የተከለከሉ ሲሆን ለመጎብኘት ፈቃድ አግኝተው የነበሩትም እንደገና እንደተገለከሉ ተገልጾአል፡፡ ለአብነትም የሰማያዊ ፓርቲ የጋሞጎፋ ዞን ምክትል ሊቀመንበር አቶ ፍቃዱ አበበ አባት ከሳምንት በፊት ልጃቸውን እንዲጠይቁ ተፈቅዶላቸው ቢጠይቁም ከሳምንት በኋላ ዳግመኛ ለመጠየቅ በሄዱበት ወቅት ‹‹ከሳምንት በፊት ጠይቀሃል፡፡ ይበቃሃል!›› ተብለው መመለሳቸውን የሰማያዊ ፓርቲ የህግ ጉዳይ ኃላፊ አቶ ይድነቃቸው ከበደ ለነገረ ኢትዮጵያ ተገልጾአል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም በዛሬው ችሎት ቤተሰብ፣ የኃይማኖት አባት፣ ጠበቃና ሌሎችም ዜጎች እንዳይገቡ የተከለከሉ ሲሆን የህግ ጉዳይ ኃላፊው ድርጊቱ በታሳሪዎቹ ላይ እየጠፈጸመ ያለውን ህገ ወጥነት ያሳያል ብለዋል፡፡ ኃላፊው ጨምረውም ‹‹ችሎት በዝግ የሚታየው ታሳሪዎቹ ላይ ችግር ይደርሳል ተብሎ ሲታሰብ ነው፡፡ በአሁኑ ሁኔታ በችሎት ሊገባ የሚችለው ህዝብ በታሳሪዎቹ ላይ ችግር እንዳይደርስባቸው መንግስትን የሚጠይቅ እንጅ ችግር ሊያደርስ የሚችል አይደለም፡፡ ያም ሆኖ ግን ታሳሪዎቹ ይህ ነው ተብሎ ባልተነገረ ምክንያት ጉዳያቸው በዝግ ችሎት እንዲታይ ተደርጓል፡፡ ይህ ህገ ወጥነት ነው፡፡›› ሲሉ ሁኔታውን ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡
በሌላ በኩል አዲስ አበባ ውስጥ በሽብርተኝነት ተጠርጥረው የተያዙና ለ4ኛ ጊዜ 28 ቀን ቀጠሮ ተሰጥቶባቸው ከሰማያዊ ፓርቲ አመራሮች ጋር ችሎት የቀረቡ 10 ያህል ግለሰቦች መኖራቸውን የነገረ ኢትዮጵያ ምንጮች ገልጸዋል፡፡ ይሁንና የታሳሪዎቹ ቤተሰቦች አለብን ባሉት ስጋት ስለ ታሳዎቹ አያያዝና ሌሎች ጉዳዮች መረጃ ለመስጠት ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ነገረ ኢትዮጵያ በጉዳዩ ላይ ዝርዝር መረጃ ማቅረብ አልቻለችም፡፡
ባለፈው ሳምንት ወደማዕከላዊ እየታፈኑ የሚወሰዱት ዜጎች ቁጥር መበራከቱንና 12 ያህል ዜጎች ከኦሮሚያ ታፍነው በማዕከላዊ እንደሚገኙ ከእነ ስም ዝርዝራቸው ማቅረባችን ይታወሳል፡፡
source Negre Ethiopia 

አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ የያዘችውን ፓሊሲ ትመርምር

October 2,2014
መስከረም 15 ቀን 2007 ዓም፣ የዩ. ኤስ. አሜሪካ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦቦማና ባልደረቦቻቸው በአንድ በኩል ኃይለማርያም ደሣለኝና አለቆቹ በሌላ በኩል ሆነው የሁለትዮሽ ስብሰባ ተደርጎ ነበር። በዚህ ስብሰባ ላይ ፕሬዚዳንት ኦባማ ያደረጉት ንግግር የዲፕሎማሲ ጨዋነት ከሚጠይቀው ርቀት በላይ ተጉዘው ሸሪኮቻቸው ባልሠሯቸው ጀብዶች ማሞገሳቸው አሳዝኖናል። ፕሬዚዳንት ኦባማ ከላይ በተጠቀሰው ቀን ያደረጉት ንግግር ላይ በርካታ ስህተቶች፣ ህፀፆችና ግድፈቶች የያዘ ከመሆኑም በላይ አንዳንዱ አስተያየት የኢትዮጵያዊያንን ክብር የሚነካ ሆኖ አግኝተነዋል።
ፕሬዚዳንቱ ንግግራቸውን የጀመሩት “ኢትዮጵያ በዓለም ከሁሉም በላይ በከፍተኛ ፍጥነት በማደግ ላይ ያለች አገር ነች“ በሚል ዓረፍተ ነገር ነበር። የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ ጽ/ቤት የፈጠራ ቀመሮች በዓለም ባንክ በኩል ዞረው በሚስ ሱዛን ራይስ ተቀነባብረው በባራክ ኦባማ አንደበት መስማት የሚያሳፍር ነው። የኢትዮጵያ ሕዝብ ኦባማ የተናገሩትን ዓረፍተ ነገር ከኢትዮጵያ ቴሌቪዥና ራድዮ ደጋግሞ ሰምቶ ሰልችቶታል። ኦባማ፣ ይህ የተሰለቸ ዓረፍተ ነገር በእሳቸው አንደበት ሲነገር ስለሚሰጠው ትርጉም ጥቂት ቢያስቡ ኖሮ ለእሳቸውም ለአሜሪካም የተሻለ ነበር ብለን እናምናለን። “በአንድ ወቅት ራሷን መመገብ ያቅታት የነበረችው አገር ዛሬ ከፍተኛ እድገት የሚታይባት ሆናለች፤ አሁን የግብርና ብቻ ሳይሆን [የኤሌክትሪክ] ኃይልንም በመሸጥ በቀጠናው ቀዳሚነት ይዛለች” ሲሉ ያሞካሿት ኢትዮጵያን ኢትዮጵያዊያን የማያውቋት መሆኑን፤ እሳቸው የሚያወድሷት ኢትዮጵያ በህወሓት ፕሮፖጋንዳ እንጂ በመሬት ላይ የሌለች መሆኑን ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ማወቅ ነበረባቸው። በአንፃሩ የእውነተኛዋ ኢትዮጵያ 70% ሕዝብ በድህነት ወለል በታች በሆነ ኑሮ ሕይወቱን እየገፋ እንደሆነ፤ የሚሊዮኖች ኢትዮጵያዊያን የእለት ጉርስ ምንጭ የአሜሪካና የአውሮፓ አገሮች እርዳታ መሆኑን ፕሬዚዳንት ኦባማ አያውቁም ማለት ይከብዳል። ፕሬዚዳንት ኦባማ የተናገሩለት የመብራት ኃይልም ለኢትዮጵያ ሕዝብ የተስፋ ተረት መሆኑን፤ ዛሬም የኢትዮጵያዊው የምሽት ኑሮ የሚገፋው በባትሪ፣ በሻማና በኩራዝ መሆኑን ፕሬዚዳንት ኦባማ አያውቁም ማለት ያስቸግራል።
ፕሬዚዳንት ኦባማ ከተናገሩት ውስጥ ትርጉም የሚሰጥ ነገር ቢኖር ስለ “ሰላም ማስከበር” የተናገሩት ነው። የህወሓት አገዛዝ፣ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊትን ገንዘብ ባለበት እና አሜሪካ ወደ ፈለገችው ቦታ ሁሉ የሚልክ መሆኑ ይታወቃል። ስለሆነም የጦሩ የሰላም ማስከበር ሥራ ማሞካሸታቸው የሚጠበቅ ነው። እንዲያውም የፕሬዚዳንቱ ሙሉ ንግግር የተቃኘው ከዚህ አቅጣጫ ይመስላል። እንደዚያ ባይሆን ኖሮ የራሳቸው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ያወጣውን የሰብዓዊ መብት አያያዝ ሪፖርትን ውድቅ የሚያደርግ ነገር ባልተናገሩም ነበር። አንዳችም ነፃ ተቋማት በሌሉበት አገር ውስጥ ፍትሃዊ ምርጫ የሚባል ነገር ሊኖር እንደማይችል አውቀው ቀዳሚው ጥያቄዓቸው የሰብዓዊ መብቶች መከበር እና የነፃ ተቋማት ግንባታ ጉዳይ ባደረጉት ነበር። ፕሬዚዳንት ኦባማ ስለኢትዮጵያ ተጨንቀው ቢሆን ኖሮ የራሳቸው ስቴት ዲፓርትመን የዘንድሮውን የሰብዓዊ መብት አያያዝ ሪፓርት ያስታውሱ ነበር። ሪፓርቱን በማስታወሳቸው ብቻ በግፍ እየታሰሩ ስላሉት ዜጎች፣ በኦጋዴን፣ በኦሮሚያ፣ በጋምቤላ፣ በአፋር እና በአማራ እየተጨፈጨፉ ስላሉ ዜጎች፣ ስለ መሬትና የሀብት ዘረፋ፣ ስለፍትህ እጦት፣ ስለ ተቋማዊ ዘረኝነት እና ሌሎችም በርካታ ጉዳዮች እንዳነሱ ይቆጠር ነበር፤ ምክንያቱም ያ ሪፓርት የያዘው ይህንን ሁሉ ነው። ፕሬዚዳንት ኦባማ ግን የንግግራቸው ግብ ዘማች ወታደር ማግኘት በመሆኑ የራሳቸውን የስቴት ዲፓርትመንት ሪፓርት ትተው የወያኔን ሪፓርት ይዘው የቀረቡ አስመስሎባቸዋል። ይህ አካሄድ አሜሪካ ወደማትፈልገው የጦር አረንቋ የሚላኩ የሠራዊት አባላት ሊያስገኝ ቢችልም የሚያስከትላቸው ጉዳቶችም መታየት ነበረባቸው። የንግግራቸው ፈጣን አሉታዊ ውጤት ለማየት ቀናትም አልፈጀም፤ እነሆ በኦባማ አይዞህ ባይነት የተነቃቁት የህወሓት ገዳዮች ከኢትዮጵያ አልፈው በአሜሪካ ምድርም በኢትዮጵያዊያን ላይ መተኮስ ጀምረዋል።
የኦባማ ንግግር ትኩረት የፀጥታ ጉዳዮች ሆኖ ኢኮኖሚ የግኑኝነት ማሳለጫ ሆኖ ቀርቧል፤ የሰብዓዊ መብት አጠባበቅና የዲሞክራሲ ጉዳዮች ደግሞ ፈጽመው ተገፍተው ወጥተዋል። ይህ ንግግር አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ የምትከተለውን ፓሊሲ አመላካች ነው።
ግንቦት 7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ በፀጥታ ጉዳይም ቢሆን አሜሪካ የያዘችው አቋም በረዥም ጊዜ የኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን የአሜሪካን ጥቅም የሚጎዳ ነው ብሎ ያምናል። ኢትዮጵያ ለአሜሪካ ከወታደር ምንጭነት በላይ የምታገለግል አገር ናት። ኢትዮጵያ ውስጥ ከራሱ ሕዝብ ጋር የታረቀ መንግሥት መኖር ለቀጠናው ሰላም እና ብልጽግና ወሳኝ ከመሆኑም በላይ የቀጠናው ሰላምና ብልጽግና የአሜሪካም ስትራቴጂያዊ ጥቅም ነው ብለን እናምናለን። የአጫጭር ጊዜ ጊዜዓዊ ጥቅሞችን ብቻ በመመልከት አምባገነኖችን መደገፍ አሜሪካን ምን ያህል ውድ ዋጋ እያስከፈላት እንደሆነ በዓይኖቻችን እያየነው ያለ ሀቅ ነው። አሜሪካ አምባገነኖችን መደገፏን ከቀጠለች ፈጥኖም ይሁን ዘግይቶ የምታገኘው እስካሁን ስታገኝ የነበረውን ውግዘትና የጽንፈኞች መጠናከር ነው። አሜሪካ የተሳሳተ ፓሊሲ በያዘችባቸው አገሮች ሁሉ ግንባር ቀደም ተጎጂዎች ለዘብተኞችና ዲሞክራቶች ሲሆኑ እየተጠናከሩ የሚመጡት ደግሞ ጽንፈኖች ናቸው። አሁንም አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ የያዘችውን ፓሊሲ የአገሪቱን የዲሞክራሲ ኃይሎችን የሚያዳክም እና ጽንፈኛ ኃይሎችን የሚያበረታታ እንደሆነ ከወዲሁ ሊጠን ይገባዋል።
ዩ. ኤስ አሜሪካ የምትመራባቸው የነፃነት፣ የእኩልነትና የፍትህ እሴቶች የግንቦት 7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ እሴቶችም ናቸው። ኢትዮጵያዊያን እንደ አሜሪካ ዜጎች ሁሉ ፍትህን፣ ነፃነትን፣ እኩልነትንና ዲሞክራሲን ይሻሉ፤ እነዚህ መሻት ደግሞ መብታቸው ነው ብሎ ግንቦት 7 ያምናል፤ ለዚህም ይታገላል። አሜሪካ ይህን ትግል ማገዝ ይገባታል። በተግባር የምናየው ግን የዚህ ተቃራኒ ነው። አሜሪካ ለአጫጭር ጊዜ ጥቅም ስትል ከአምባገነን ኃይሎች ጋር ማበሯ የዓላማ ተጋሪዎቿን እያዳከመ መሆኑ የወቅቱ የዓለም ሁኔታ የሚመሰክረው ሀቅ ነው። በኢትዮጵያ ላይ እየተከተለችው ያለው ፓሊሲው ተመሳሳይ የረዥም ጊዜ መዘዝ እንዳያመጣ ያሰጋል። ይህ እንዳይሆን እርምት የሚገባው አሁን ነው።
ስለሆነም፣ ግንቦት 7፡ የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ፣ ዩ. ኤስ. አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ የያዘችውን ፓሊስ እንደገና እንድትመረምር እና ዘረኛና አምባገነኑን የህወሓት አገዛዝን መርዳት እንድታቆም አበክሮ ያሳስባል።
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!!
source www.ginbot7.org

Thursday, October 2, 2014

በትግራይ ኣፅቢ 5 ጣልያናውያንና 2 ኢትዮዽያውያን በሕወሓት ፖሊሶች ለሰዓታት ታገቱ

የህወሓት ፖሊሶች ጋዘጠኞቹን ኣግቶ፣ ፈትሾ፣ ኣንገላትቶ ለቋቸዋል።

newsትናንት ሰኞ 19/ 01 / 2007 ዓ/ ም ለስራ ጉዳይ ወደ ኢትዮዽያ የመጡት በኣንድ ጣልያን የሚገኝ ቴሌቭዥን ጣብያ የሚሰሩ 4 ጣልያናውያን ጋዜጠኞችና ኣንድ ሌላ ኣገር ጎብኚ ጣልያናዊ ከሁለት ኣብሯቸው የሚሰሩ ኢትዮዽያውያን ጋራ ወደ ተለያዩ የገጠር ቀበሌዎች የጎበኙ ሲሆኑ እገታው ያጋጠማቸው ወደ ኣፅቢ ወንበርታ ወረዳ, ሩባ ፈለግ ቀበሌ የዓረና ኣባል የሆነው ኣቶ ሕድሮም ሃይለስላሴ መኖርያ ቤት በመሄዳቸው ነው።
የወረዳው ፖሊስ መኪናቸው ወደ ፖሊስ ጣብያ እንድት ሄድ በማዘዝ ከኣስተዳዳሪዎች ጋራ በመሆን ቪድዮና ፎቶ ካሜራዎቻቸው እንዲፈተሹ በማድረግ፣ ፓስፖርታቸው ፎቶ ኮፒ በማድረግ፣ ወደ የዓረናው ኣባል ለምን ጉዳይ እንደገቡ በመጠየቅና ታስረው እንዲያድሩ ብሎው ውሳኔ ኣስተላልፈው ነበር።
ኣምስቱ ታጋቾች ኣዲስ ኣበባ ወዳለው የጣልያን ኢንባሲ ደውለው በመነጋገር ማታ 2:30 ኣከባቢ ሊለቀቁ ችለዋል።የህወሓት መንግስት እነዚህ ጋዘጠኞች ኣግቶ፣ ፈትሾ፣ ኣንገላትቶ ከፌደራል መንግስት በተሰጠው ትእዛዝ ሊለቃቸው ተገደዋል።
ምንጭ ዘ-ሐበሻ

የዋሽግተኑ ጉዳይ ከዓለም አቀፍ ሕግ አንፃር ሲታይ

ከጌታቸው በቀለ
”ዓለም አቀፍ ሕግ፣ዓለም አቀፍ ሕግ” የምትል ቃል በእየቦታው ትሰማ ጀመር።እሰይ! እንዴት ደስ ይላል።ይህንን ሰሞኑን በማኅበራዊ ድረ-ገፅ ላይ የሚጠቅሱት ደግሞ የስርዓቱ አድናቂዎች ናቸው።ጉዳዩን የሚያነሱትደግሞ በዋሽግተን ኢትዮጵያ ኤምባሲ ላይ በተደረገው ተቃውሞ ሳብያ ነው።እስኪ ለህሊናችን መጀመርያ በሀገር ውስጥ እራሱ ላወጣው ሕግ መገዛት ቢያቅተው ለዓለም አቀፍ ሕግ እንዲገዛ ስርዓቱን እንምከረው።እንዲህም እንጠይቅ-
ለመሆኑ ዓለም አቀፍ ሕግን እንደ ዓለም ዋንጫ ቅሪላ በእግሩ የሚያጦዛት ማን ነው?
embassy shooter
ማን ነው የኖርዌይ ዜግነት ያላቸውን የጋምቤላ አስተዳዳሪ ከደቡብ ሱዳን ጠልፎ ወስዶ ያሰረው? ዓለም አቀፍ ሕግ ጥሰት ቁጥር ስንት እንበለው?
ማን ነው የእንግሊዝ ፓስፖርት የያዙትን አቶ አንዳርጋቸውን ከየመን ጠልፎ ያሰረው? ዓለም አቀፍ ሕግ ቁጥር ስንት እንበለው?
ዓለም አቀፍ ሕግ የአፍ ማሟሻ አደለም! በተግባር ለእራስ ሲሉ የሚያከብሩት ነው።ዛሬ የዋሽግተን ኤምባሲ ሲደናገጥ ”ሕግ ምናምን” አትበሉ።የዋሽግተኑን ጉዳይ በዓለም አቀፍ ሕግ አንፃር ካየነው የኤምባሲው የሕግ ከለላ ከባዕዳን ነው እንጂ ከሀገሩ ተወላጆች አይደለም! አንድ ትውልደ ኢትዮጵያዊ በሀገሩ ጉዳይ በሰላማዊ መንገድ አራት ኪሎ ቤተ መንግስት ውስጥ ገብቶ የመቃወምም ሆነ ዋሽግተን ላይ ባለው በሀገሩ ኢምባሲ ውስጥ ገብቶ የመቃወም መብቱን ዓለም ዓቀፍ ሕግ አይገድበውም።የሰንደቅ አላማው ጉዳይም ሰንደቅ አላማው በሌላ ሰንደቅ አላማ ተተክቶ ቢሆን ነበር የሚያሳዝነው።ይህ ቢሆን ኖሮ በሕግም አከራካሪ ይሆን ነበር።የሉዓላዊነት ጥያቄም አብሮ ሊነሳ ይችል ነበር።የሆነው ግን ለሕግ ወቀሳም አይበቃም። ተቃዋሚዎቹ የተኩት ቀድሞ የኢህአዲግ አርማ ያለበትን በእራሷ በኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ ነው።
አንድ ሀገር የውጭ ቆንስላ ወይንም ኤምባሲን የመጠበቅ ኃላፊነት አለበት።ይህ የሚያደርገው ግን ከእዛ ሀገር ዜጎች የበለጠ ኃላፊ ሆኖ አይደለም።የኤምባሲው ሀገር ተወላጅን ወደ ኤምባሲው ‘ግባ አትግባ’ ማለት ሌላ ሳይሆን አንድን ኢትዮጵያዊ ወደ እራሱ ሀገር ‘ግባ አትግባ’ ንትርክ ውስጥ መግባት ማለት ነው።የዋሽግተኑ የኢትዮጵያ ኤምባሲም ጉዳይ ይሄው ነው።ኢትዮጵያውያን በኤምባሲያቸው ቅጥር ግቢ ሆነው የሚያደርጉት ሁሉ በኢትዮጵያ ምድር ላይ እንዳደርጉ ነው የሚቆጠረው።የኢምባሲ ግቢ ማለት የታፈረ የተከበረ ኢምባሲው የተጠራበት ሀገር ምድር ማለት ነው።ለእዚህ ነው አንድ ስደተኛ ወደ አንዱ ሀገር ኤምባሲ ገብቶ ጥገኘነት ቢጠይቅ ኤምባሲው ሀገር እንደገባ የሚቆጠረው እና ኤምባሲው ያለበት ሀገር ፖሊስ ዘሎ ሊገባ የማይችለው።ኢህአዲግ አዲስ አበባ ሲገባ ጣልያን ኤምባሲ እጃቸውን የሰጡ ባለስልጣን የፌድራል ፖሊስ መያዝ ያልቻለው ለእዚህ ነው።ግቢው ሃገሩ ነው።ተቃዋሚዎችም ዋሽግተን ውስጥ ያለው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ግቢ ሀገራቸው ነው።የመቃውም መብታቸው ላይ አሜሪካን አይመለከታትም።ጉዳዩ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ነው።አሜሪካ የሚመለከታት በምድሯ ላይ የማይፈቀደው የመግደል ሙከራ፣ማስፈራራት እና ድምፁ በግቢው ውስጥ መወሰን ያልቻለው አካብቢውን ያሸበረው የተኩስ ድምፅ ነው።
ባጭሩ አሜሪካ ኃላፊነት ያለባት የጦር መሳርያ ይዘው ወይንም የሚያሸብር ነገር ይዘው ወደ ኢምባሲ የመጡትን የመጠበቅ እንጂ በሀገራቸው ጉዳይ ላይ ለመቃወም ሰንደቅ ዓላማ እና የታሰሩ እስረኞች ፎቶ ይዘው ለመጡ አይደለም። እንዲያውም አሜሪካ በእንዲህ አይነቱ ጉዳይ ከገባች አሁንምበኢትዮጵያ የሀገር የውስጥ ጉዳይ እንደገባች ነው የሚቆጠረው።በነገራችን ላይ ከእዚህ በፊት ለአመታት ኢትዮጵያውያን በዋሽግተንም ሆነ ሌሎች ኢምባሲዎች ፊት ሰልፍ ካደረጉ በኃላ የሰልፋቸውን ጥያቄ የያዘ ደብዳቤ ለአምባሳደሩ ለመስጠት ሲጠይቁ የኢህአዲግ የኤምባሲ ሰራተኞች ከፎቅ ላይ ሆነው ቪድዮ ማንሳት እንጂ ደብዳቤ አይቀበሉም።እናም ዜጎች እንዴት ሃሳባቸውን ይግለፁ? ተቃዋሚዎቹ ሌላ አማራጭ ነበራቸው ወይ? የሚለውን የአሜሪካ መንግስትም የሚመለከተው ነው። በሰልፍ ሲወጡ ፖሊስ እንዲጠራ ይደረጋል።በፅሁፍ ሲያቀርቡ ኤምባሲው ለፎርማልቲም ቢሆን አይቀበልም።ልክ ‘ምናምን’ እንደነካው እንጨት ይጠየፋል።
ይህ ትልቅ የኢምባሲዎቹ የትዕቢት መገለጫ ነው።አንድ ዜጋ የፈለገው ጉዳይ ላይ የመቃወም ሃሳቡን በቃልም ሆነ በፅሁፍ የማቅረብ መብት አለው።ኢምባሲው እዝያ በተሰለፈው ሕዝብ እና በቤተሰቡ ገንዘብ ደሞዙን እንደሚያገኝ ዘንግቶ የተቃውሞ ደብዳቤ አለመቀበሉን በምን እንግለፀው? አዲስ አበባ ላይ ሆኖ ”እሰይ ደግ አደረካቸው” እያሉ መፎከር አይደለም።አሰራርን መፈተሽ፣ትዕቢትን መቀነስ ነው የሚያስፈልገው። መጨረሻ ምን ሆነ ዜጎች ”ስሙን!!! ኡ ኡ ኡ !!” እያሉ ወደ ኤምባስያቸው ገቡ።አሳፋሪው ድርጊት ግን የሀገራቸው ኤምባሲ ተኮሰባቸው።ይህ ነው አሳፋሪ ተግባር የሚባለው።ዓለም የገረመው ይህ ነው።ኢትዮጵያውያን ምን አይነት አሳፋሪ አገዛዝ ስር እንደወደቁ የተረዳው እዚህ ላይ ነው።በሀገራቸው የፖለቲካ ጉዳይ የተናደዱ፣ያዘኑ ዜጎች ዋሽግተን ላይ ሃሳባቸውን መግለፅ ካልቻሉ በሃገራቸውማ ቢሆን በታንክ ነው የሚሏቸው ብሎ የደመደመው ለእዚህ ነው።የአሜሪካ ስቴት ዲፓርትመንት ቶሎ መግለጫ አላወጣም።ጉዳዩን የሚመለከተው ከላይ ከተጠቀሱት ነጥቦች አንፃር እንደሚሆን ይታወቃል።የውጭ መገነኛ ብዙሃን በተቃዋሚዎች ላይ የመተኮሱን ጉዳዩን ከገለፁበት ቃላት ውስጥ ”በካሜራ የተያዘ ድራማዊ እንቅስቃሴ” ብሎ የዘገበው የእንግሊዝን ”ዴይሊ ሜይል” ይጠቀሳል።
ከሰሞኑ ዋሽግተን ላይ ከተከሰተው ክስተት አንፃር ኢትዮጵያውያንም ለሁሉም ወገን ማስረዳት ያለባቸው ከላይ ከተጠቀሱት የአፈና ደረጃዎች አንፃር መሆን ይገባዋል።ፀሐፊዎች፣ጋዜጠኞች፣በውጭ ሀገር በልዩ ልዩ ኃላፊነት ላይ ያሉ ሁሉ ለዓለም (ለአሜርካኖችም ጭምር) ማስረዳት በእንግሊዝኛም መፃፍ ይጠበቅባቸዋል።የኢህአዲግ አድናቂዎችም ከህሊናችሁ ጋር ኑሩ! እውነታውን መርምሩ።መንግስታችሁ እንዴት ወዴት እየሄደ እንዳለ እና በውስጡ የተሰገሰጉት የትዕቢት አባቶች አደብ እስካልገዙ ድረስ ከትርፍ ይልቅ ኪሳራው እየበዛ መሄዱ አይቀርም።ዓለም አቀፍ ሕግን ግን ለቀቅ አድርጉት።
ጉዳያችን
መስከረም 21/2007 ዓም (ኦክቶበር 1/2014)
ምንጭ ዘ-ሐበሻ

Wednesday, October 1, 2014

የፓርቲዎቹ አባላት ጠበቃ ደረሰብኝ ባሉት ጫና ለጊዜው ሥራቸውን ማቆማቸውን አስታወቁ

በሕገመንግስቱ መሠረት ለደንበኞቼ አገልግሎት መስጠት አልቻልኩም፤ ከፍርድ ቤትና ከፖሊስም ማስፈራሪያ ደርሶብኛል ያሉት የአንድነት፣ የሰማያዊና የዓረና ፓርቲ አባላት ጠበቃ አቶ ተማም አባቡልጉ ራሳቸውን ማግለላቸውን አስታወቁ። ደንበኞቼ የምርመራ ቃላቸውን ለፖሊስ ከመስጠታቸው በፊት ላገኛቸው ሲገባ ይህ አልተደረገም ያሉት ጠበቃው፤ የጊዜ ቀጠሮው ችሎት እስኪጠናቀቅ ድረስ ለቀጣዩ አንድ ወር ደንበኞቻቸውን እንደማያገኙና ሕግን ባልጠበቀ መንገድ ለሚከናወን ተግባር የፕሮፓጋንዳ ሽፋን መሆን እንደማይፈልጉ አስታውቀዋል።
ጠበቃ ተማም አባቡልጉ ለአንድነት ፓርቲ አባላቱ ለሀብታሙ አያሌውና ለዳንኤል ሺበሺ፤ ለአረናው አብርሃ ደስታ እና ለሰማያዊ ፓርቲው የሽዋስ አሰፋ ጠበቃ ሆነው በማገልገል ላይ ይገኙ የነበሩ ሲሆን፤ ደረሰብኝ ባሉት ጫና እና ኢ-ሕገመንግስታዊ አሰራር ምክንያት ከደንበኞቻቸው ጋር ያላቸውን ግንኙነት ለጊዜውም ቢሆን ማቋረጣቸውን ለፓርቲዎቹ አመራሮች መግለፃቸውን አስረድተዋል። ይህም በመሆኑ ሦስቱ ፓርቲዎች (ማለትም አንድነት፣ ዓረና እና ሰማያዊ) በእስረኞቹ ላይ እየደረሰ ያለውን ኢ-ፍትሐዊ ድርጊት በተመለከተ ዛሬ መስከረም 21 ቀን 2007 ዓ.ም በአንድነት ቢሮ ጋዜጣዊ መግለጫ ይሰጣሉ ተብሎ ይጠበቃል።
እንደማንኛውም ጠበቃ ደንበኞቼን ማግኘት ቢኖርብኝም፤ ላገኛቸው አልቻልኩም፤ በፍርድ ቤት የምናቀርባቸው አቤቱታዎች እና ስሞታዎች በሙሉ ያለበቂ ምክንያት ውድቅ ይደረጉብናል፣ ይባስ ብሎም ኢ-ፍትሐዊ አሰራር በመኖሩ ለስርዓቱ ሕጋዊ ከለላ መሆን አልፈልግም የሚሉት አቶ ተማም አባቡልጉ፤ በዚህም ምክንያት የታሰሩት የፖለቲከኛ እስረኞች ምንም ዓይነት ሕጋዊ ከለላ ማግኘት አልቻሉም ሲሉ ነገ በሚደረገው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንደሚያነሱ ምንጮች ጠቁመዋል።
በጥቅምት 15 ቀን 2007 ዓ.ም ተጠርጣሪዎቹ በጊዜ ቀጠሮ ችሎት የሚቀርቡት ያለጠበቃ ቢሆንም፤ ምናልባትም ከወር በኋላ ዐቃቤ ሕግ ክስ የሚመሰርት ከሆነ፤ በችሎት ተገኝቼ ደንበኞቼን አገለግላለሁ የሚሉት ጠበቃ ተማም አባቡልጉ፤ ደንበኞቼ ቃላቸውን ከመስጠታቸው በፊት እኔን ማግኘት ሲገባቸው ሳያገኙኝና ቃላቸውን ሰጥተው ከፈረሙ በኋላ ባገኛቸው ምን አደርግላቸዋለሁ? ሲሉ ጥያቄ አዘል ኀሳባቸውን ይሰነዝራሉ። ከዚህም ባሻገር ደንበኞቼ ከተጠረጠሩበት ጉዳይ ውጪ በሆነ መልኩ የሚደረግባቸው ምርመራ በፓርቲ ጉዳይ ላይ ሆኗል ሲሉ ቅሬታቸውን የሚያቀርቡት ጠበቃው፤ ለዚህም ጠንካራ አባል ማነው? የገንዘብ ምንጫችሁ ከየት ነው? የሚሉ ጥያቄዎች ቀርበውላቸው እንደነበር ደንበኞቼ ለፍርድ ቤት ቀርበውም አመልክተዋል ሲሉ ያስረዳሉ።
      ይህም በመሆኑ የተላላኪነት ስራ ከመስራት ውጪ የምፈይደው ነገር የለም በሚል ለጊዜው ከደንበኞቼ ጋር መገናኘቱን አቁሜያለሁ ያሉት ጠበቃ ተማም፤ በዚህ አጋጣሚ ደንበኞችዎ ምን ሊያጋጥማቸው ይችላል ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ፤ “የሚደርስባቸው ሁሉ ደርሶባቸዋል፤ እኔም ኖሬ ምንም አይነት የሕግ ከለላ አላገኙም” ሲሉ መልሰዋል።
ምንጭ፡ የኢትዮጵያ ሜዲያ መድረክ