ህዝባዊ ተቀባይነቱን ያጣው ወያኔ በሽፍትነት ዘመኑ ትግራይ ውስጥ ሲያደርግ እንደረነበረው ሁሉ፣ መንግስታዊ ስልጣኑን ከያዘም በሁዋላ መሰልጠን አቅቶትና እንደመንግስት ማሰብ ተስኖት፣ አገዛዜን ይቃወማሉ ብሎ የሚጠረጥራቸውን ዜጎች የቅርብ ቤተሰቦችና የሩቅ ዘመዶች ሳይቀር ማሰቃየት መጀመሩን ከአራቱም የአገራችን ማዕዘናት በየቀኑ የሚደርሱን ሪፖርቶች ያመለክታሉ።
በቅርቡ በአርባ ምንጭ ከተማ ለአገራቸው ነጻነት በገዛ ፈቃዳቸው ተነሳስተው ታሪካዊ ግዴታቸውን ለመወጣት በሞከሩ ወጣቶች ላይ የስርዓቱ ታማኝ ጥቂት የደህንነት ሃይሎች የወሰዱት እርምጃ ዘግናኝና ልብ የሚያቆስል ነው። ይህም አልበቃ ብሎ የተፈላጊ ወጣቶች መኖሪያ ቤቶች በታጠቁ የደህንነት ሃይሎች ተወረው ፍተሻ ተካሂዶባቸዋል:: እናቶች ህጻናት ልጆቻቸው ፊት “የተደበቁ ልጆቻችሁን አምጡ ” ተብለው መሳሪያ ተደቅኖባቸው፣ ኢ-ሰብአዊ ድርጊት ተፈጽሞባቸዋል። በአገዛዙ ዘረኛና የተጨማለቀ ፖሊሲ ተማረው ተቃውሞአቸውን ለመግለጽ እርምጃ መውሰድ የጀመሩ የቴፒ ወጣቶችን ለማደን የተደረገው ሙከራ መክሸፉን ተከትሎ የፈደራል ፖሊስና መከላኪያ ሠራዊት በወላጆች ላይ ተመሳሳይ እርምጃ ወስደዋል። ወጣት ሴቶች እና እናቶች ርህራሄ በጎደላቸው የስርዓቱ ታማኝ ወታደሮች ተደብድበዋል፣ ተደፍረዋል፣ ታስረዋል። በሰሜን ጎንደርም እንዲሁ መብታችን ይከበር ብለው በተነሱ ወጣት ቤተሰቦች ላይ የገዢው ሃይል ታማኞች ፣ ግድያና አስገድዶ መድፈር ፈጽመዋል። እህትማማች ሴቶች መኖሪያ ቤታቸው ውስጥ እንዳሉ ተገድለዋል። በወታደሮች የተደፈሩ ሴቶች ቅስማቸው ተሰብሮ ወደ አደባባይ ለመውጣት እንኳ የማይችሉበት ደረጃ ደርሰዋል። በመርአዊ ከተማ መኳንንት ጸጋዬ የተባሉ በሰላማዊ ትግል ስርዓቱን የሚቃወሙ ግለሰብ፣ በልጆቻቸውና በባለቤታቸው ፊት አሰቃቂ በሆነ ሁኔታ ተደብድበዋል፤ የልጆችን ስነልቦና በሚነካ መልኩም ሰዋዊ ክብራቸው እንዲዋረድ ተደርጓል።
በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ እየተፈጸመ ያለው ግፍ ድንበር የለውም፤ የወያኔን የበቀል ዱላ ያልቀመሰ፣ ማንነቱና ክብሩ ያልተዋረደ ህዝብ ማግኘት አይቻልም። በገዳዩ ስርዓት እየደረሰ ያለው ግፍ አንድ ጊዜ በሰሜን፣ ሌላ ጊዜ በደቡብ፣ ሌላ ጊዜ በምስራቅ እያለ ቀጥሎአል። የዚህ ፍጹማዊ የአፈና አገዛዝ ህልውና እንዲቀጥል እስከተፈቀደለት ድረስ ጭቆናው፣ መዋረዱ፣ መታሰሩና መሞቱ አይቆምም። የአገዛዙ ባህሪ እነዚህን ሰይጣናዊ ድርጊቶች ለመፈጸም እንጅ መልካም ነገር ለመፈጸም አያስችለውም።
ለነጻነት የሚደረገው ትግል በመሬት ላይ አድማሱን እያሰፋ በመጣ ቁጥር የጥቃቱ አይነትና መጠንም እየጨመረ እንደሚመጣ ስናስብ፣ ይህን ጥቃት የምናስቆምበት ወይም የምንቀንስበትን መንገድም መሻት ተገቢ ነው። ወያኔ በነጻነት ታጋይ ቤተሰቦች ላይ ጥቃቱን ሲፈጽም ከሚጠቅሳቸው ምክንያቶች መካከል አንዱ “ልጅህ ወይም ወንድምህ መንግሥታችንን ለመናድ ሌት ተቀን እየሰራ አንተ በሠላም ልትኖር አትችልም” የሚል ነው። ይህ ሁዋላ ቀር አስተሳሰብ ወያኔን ከሚመሩ ሰዎች የሚጠበቅ ቢሆንም፣ ፖለቲካ ወይም የነጻነት ጉዳይ በደም የሚወረስ ሳይሆን ከግለሰቦች ማንነት ጋር ተያያዞ የሚመጣ መሆኑን፣ ቀድም ብለው በሁለት ጎራ ለይተው ሲፋለሙ የነበሩ ወጣቶችን ታሪክ ማስታወስ በቂ ነው። ከአንድ ማህጸን የወጡ የአንድ እናት ልጆች የተለያዬ የፖለቲካ አመለካከት እንደሚይዙ ታሪካችን ብቻ ሳይሆን፣ የወያኔ ታሪክ ራሱ ምስክር ነው። እውነታው ይህ ሆኖ ሳለ፣ በጅምላ በቤተሰብ ላይ የሚደርሰው ጥቃት፣ ከሁዋላ ቀርነትና ከግንዛቤ ማነስ የመጣ ነው ተብሎ የሚመጣ ብቻ ሳይሆን፣ ድርጊቱን ከሚፈጽሙት ሰዎች ስነልቦና ቀውስና የሁዋላ ታሪክ ጋር የሚያያዝ ነው። በንጹህ ዜጎች ላይ ጭካኔና ግፍ የሚፈጽሙ ሰዎች፣ የሰው ማንነት የሌላቸው፣ ከአስተዳደጋቸው ጀምሮ የተበላሹና ማህበረሰቡ “አይመጥኑም” ብሎ የተፋቸው ናቸው። አሁን በስልጣን ላይ ያሉና በህዝባችን ላይ የጭካኔ ዱላቸውን የሚያሳርፉ ገዢዎች የሁዋላ ታሪክ ቢጠና ከዚህ የተለየ እውነታ አይኖረውም።
ሌላው የወያኔ ስልት ደግሞ በአገር ውስጥ ያሉትን ብቻ ሳይሆን ከአገር ውጭ የሚንቀሳቀሱ የነጻነት ታጋዮችን ቤተሰቦችና ዘመዶች እየተከታተሉ ” እባካችሁ ዘመዶቻችሁ ከፖለቲካው እንዲርቁ አድርጉ፣ እንዲህ ካደረጋችሁ የምትፈልጉትን ነገር እናድርግላችሁዋለን፣ ለእነሱም የፈለጉትን ነገር እናደርግላችሁዋለን” በማለት ለመደለል መሞከራቸው ነው።
ለወያኔ ነጻነት ማለት ገንዘብ ነው፤ ቤት ነው፤ ሆድ ነው፤ ነጻነት የህሊናና የማንነት ጉዳይ መሆኑን ገና አላወቀም። ሁሉም ሰዎች ነጻነታቸውን በገንዘብ፣ በቤት፣ በሆድ ወይም በብልጭልጭ ምድራዊ ነገር ይሸጣሉ ብሎ ያስባል፤ በርግጥ በእነዚህ አላፊና ጠፊ ነገሮች ተታለው ነጻነታቸውን የሸጡ ቢኖሩም፣ ሁሉም ሰው ግን እንደዛ አይደለም። የወያኔን የግፍ አገዛዝ ተቃውመው ለነጻነት የሚታገሉ ሃይሎች ሁሉ፣ ቁሳዊ ፍላጎታቸውን ትተው፣ ህሊናዊና ማንነታዊ ፍላጎትን ለራሳቸውም ለህዝባቸውም ለማምጣት የሚታገሉ ናቸው። በወያኔና በእነዚህ ታጋዮች መካከል ያለው ልዩነትም ይህ ነው፤ ወያኔ ለአላፊ ጠፊው ምድራዊ ህይወት ሲጨነቅ፣ እነዚህ ተጋዮች፣ ዘላለማዊ ለሆነው ለነጻነትና ለማንነት ክብር ይጨነቃሉ። ስለዚህ ወያኔ ለህሊናቸውና ለማንነታቸው የሚታገሉ ሃይሎችን በቁሳዊ ፍላጎት ለመደለል የሚያደርገው ጥረት መቼውንም ፍሬ አያፈራምና ቤተሰቦችን እየጠራ ባያንገላታቸው ይመረጣል።
የአገዛዝ ዕድሜን ለማራዘም ሲባል በነጻነት ታጋይ ቤተሰቦች ላይ እየተወሰደ ያለው ጥቃት ከዚህ ቀደም በነበሩ ሁለት መንግሥታት ዘመን እንኳ ታይቶ የማይታወቅ ለመሆኑ ማስረጃ ማቅረብ አያስፈልግም:: መለስ ዜናዊ ከዚህ አለም በሞት በተለየበት ሰሞን የአገዛዙ ጋዜጠኞች አደዋ የሚገኘውን የወላጆቹን መኖርያ ቤት በቴለቪዥን ለህዝብ ዕይታ አቅርበው ፣ መለስ ዜናዊ ከጫካ እየሾለከ መጥቶ ያርፍ እንደነበር በገዛ ወንድሙ አፍ እንዲነገር አድርገዋል::
በአጭሩ ፓለቲካ በደም አይተላለፍም፤ ደምን ቆጥሮ በፖለቲካ ታጋይ ቤተሰቦች ላይ የሚደርስ ጥቃትም፣ ቂምና በቀልን ከመውለድ ውጭ የሚያመጣው ለውጥ አይኖርም። ህዝባዊ የነጻነትን ትግልን፣ የታጋዮችን ቤተሰቦች በማሰቃየት ወይም በመደለል ማስቆም አይቻልም። አፈናና ሰቆቃ ባለበት ቦታ ሁሉ፣ የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በቀር፣ አመጽ የማይቀር ማህበራዊ ክስተት ነው :: በተለይ “የህዝብ ብሶት ወለደኝ” በማለት መሣሪያ አንስቶ 17 አመት ታገልኩ ለሚለው ወያኔ ይህ ግልጽ እውነታ ምርምር የሚጠይቅ ውስብስብ ፍልስፋና ሊሆንበት ባልቻለ ነበር :: ዳሩ ከተጣመመ አፈጣጠሩ፣ ከመሪዎቹ ምንነትና ማንነት እንዲሁም ስልጣን ከተያዘም በሁዋላ በዘረፋ የተሰበሰበው ሃብት የፈጠረው የኑሮ ምቾትና የተከማቸው የጦር መሳሪያ ያቀዳጀው እብሪት አይነ ልቦናውን ጋርዶታልና ለወያኔ ይህ ሃቅ ሊገባው አይችልም።
አርበኞች ግንቦት 7 የወያኔ የአፈና ክንዶች ሺ ጊዜ ቢፈረጥሙም ፤ በተቃዋሚዎችና የነጻነት ታጋዮች ቤተሰብ ላይ የሚወሰደው እርምጃ የህይወት መስዋትነት እያስከፈለ ቢመጣም እንኳ ለነጻነት የሚያደረገው ትግል ይበልጥ አጠናክሮ ይቀጥላል እንጂ ለአፍታም ቢሆን አይዘናጋም። የታጋይ ቤተሰቦችና ዘመዶችም፣ አሁን በወያኔ የሚደርስባችሁ ግፍና በደል፣ ለመላው አገራችን ነጻነት ሲባል የሚከፈል ዋጋ በመሆኑ ልትኮሩ እንጅ ልለትሸማቀቁ አይገባም ። በህዝብ ፊት የነጠሉዋችሁና ከማህበራዊ ህይወታችሁ እንድትገለሉ ያደረጉዋችሁ ቢመስላችሁ፣ እውነታው ተቃራኒው ነው፤ ከህዝብ የተገለሉት እነሱ ናቸው፤ የሚዋረዱትና የሚያፍሩት እነሱ ናቸው።
በዘረኛው የወያኔ አገዛዝ ሥር የሚማቅቅ እያንዳንዱ ዜጋ አርበኞች ግንቦት 7 የለኮሰውን የነጻነት ትግል ችቦ አንግቦ በወያኔ ከርሰ መቃብር ላይ የታፈረች የተከበረችና የዜጎቿን መብት በእኩልነት የምታስከብር አገር ለመገንባት በሚደረገው ትግል እንዲቀላቀል አርበኞች ግንቦት 7 ጥሪውን ያቀርባል:: የወያኔ የጥቃት እጆች የሚያጥሩትና ዜጎች በአገራቸው ተከብረው የሚኖሩት ወያኔ ሲወገድ ብቻ ነው!
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ !
source www.patriotg7.org
No comments:
Post a Comment