ረሀብ በአገራችን ላይ እያንዣንበበ ነው። በአፋርና በሱማሌ ከከብቶች አልፎ ሕፃናት እየሞቱ ነው። የረሀቡ አደጋ ወደ ኦሮሚያና ሌሎች የደቡብ ገጠሮች እየተዛመተ ነው፤ ሰሜን ኢትዮጵያም ከአደጋ ውጭ አይደለም።
“ከአስር ዓመታት በላይ በተከታታይ በየዓመቱ ከአስር በመቶ በላይ የኢኮኖሚ እድገት አሳይተናል” የሚለው ዓይን ያወጣ ውሸት፤ “ድህነትን ተረት እናደርጋለን” የሚለው ጉረኛ መፈክር፤ “መካከለኛ ገቢ ያላቸው አገሮች ተርታ እንደርሳለን” የሚለው ባዶ ተስፋ፤ የወያኔዎችና ጀሌዎቻቸው በፎቅና ቪላዎች መንበሽበሽ፤ የድግሶችና የስብሰባዎች መብዛት ለሕዝባችን ቁርስ፣ ምሳና እራት አልሆኑም።
አገዛዙ ጉራውና ባዶ ተስፋ መስጠቱ እንዳለ ሆኖ የረሀቡን ምክንያት በተፈጥሮ ላይ ማላከኩን ተያይዞታል። ለመሆኑ ተፈጥሮ ብቻውን እየተደጋገመ ለሚመጣ ችጋርና ቸነፈር በቂ ምክንያት ሆኖ ያውቃልን? አስከፊ የረሀብ ዜናዎች የሚሰማባቸው አገሮች በሙሉ ነፃነት የታፈነባቸው አገሮች መሆናቸው የአጋጣሚ ጉዳይ ነውን? ለምንድነው አንድ ዓይነት ችግር እየተደጋገመብን መላ መፈለግ ያቃተን? መልሱ አጭርና ቀጥተኛ ነው። “ችግር የመሳካት እናት” የምትሆነው በነፃነት ማሰብ የሚችል ጭንቅላት ሲኖር ነው። በባርነት ጨለማ ውስጥ ያለ ጭንቅላት ለችግሮች መፍትሄ የማፍለቅ አቅም የለውም። እንዲያውም እንዲህ ዓይነቱ ድኩም ጭንቅላት ችግሮችን ማሸነፍ ሳይሆን ተሸናፊነትን ተቀብሎ ከችግሮች ጋር ተስማምቶና ተወዳጅቶ መኖርን ይመርጣል። ነፃነት ያለው ሕዝብ ረሀብን እንደሚያሸነፍ ተደጋግሞ የታየ ጉዳይ ነው። ለዚህም ነው ረሀብን የተፈጥሮ ሚዛን መዛባት ውጤት ብቻ አድርጎ ማቅረብ እውነትን መሸፈጥ የሚሆነው። ረሀብ የብልሹ አስተዳደር ውጤት ነው።
አገራችንን የረሀብ ቀጠና ካደረጉ የ24 ዓመታት የህወሓት “ድሃን ዘርፈህ ብላ” የኢኮኖሚ ፓሊሲ ውጤቶች መካከል አንዳንዱን ለአብነት ያህል መዘርዘር ይቻላል።
1. ገበሬና መሬት ተለያይተዋል። ለም መሬቶች በኢንቨስትመንት ስም በዘመኑ የህወሓት ጉልተኞች በመያዛቸውና እነሱ ደግሞ በተራቸው ለባዕዳን እየሸጡ በመሆኑ ባለሀገሩ ጭሰኝነት እንኳን አጥቶ ለቀን ሠራተኝነትና ልመና ተዳርጓል። አዳዲሶቹ ባለሃብቶች ለፈጣን ኪስ መሙላት እንጂ ለዘለቄታ የአፈር ልማት ፍላጎቱም እውቀቱም የላቸውም። በዚህም ምክንያት ገበሬው ትንሽ የዝናብ ዝንፈት እንኳን መቋቋም እስከማይችልበት ደረጃ ተዳክሟል።
2. በዘር ላይ በተመሰረተ ክልላዊ ድንበር ሳቢያ ኢትዮጵያዊያን ገበሬዎች በአገራቸው ውስጥ ተዘዋውረው መሥራት አልቻሉም። ከሰሜን ወደ ደቡብ ከተሰደደ የአገራችን አርሶ አደር ይልቅ ለቻይና ገበሬ መሬት ማግኘት ይቀለዋል። እንዲያውም ኢትዮጵያዊው ድሀ ገበሬ በዱላ ሲባረር፤ ከውጭ አገር የመጣው ቱጃር ገበሬ ብድርና ማበረታቻዎች ይሰጠዋል።
3. ደኖቻችን ተጨፍጭፈው፣ ለም መሬታችን ተሸርሽሮ በማለቁ የግብርናችን ምርታማነት በእጅጉ ቀንሷል። በዘመነ ወያኔ የደን ጭፍጨፋና የመሬት መሸርሸር በአስደንጋጭ ሁኔታ ጨምሯል። አገሪቷ በፍጥነት ወደ ምድረበዳነት እየተቀየረች ነው።
4. ፋይዳ ያለው የስነ ሕዝብ ፖሊሲ ባለመኖሩ የሕዝብ ብዛት አሻቅቧል። እንደ ኢኮኖሚው ሁሉ ወያኔ የኢትዮጵያን ሕዝብ ብዛት ሊቆጣጠር የሚሞክረው ቢሮ ውስጥ ቁጭ ተብሎ በሚደረግ የቁጥር ጨዋታ ነው። የስታተስቲክሱ ባለሥልጣን ቁጥራችንን በትክክል ሊነግረን ባይፈልግም እንኳን ረሀብ መብዛታችንን እየነገረን ነው።
5. የህወሓት ባለሥልጣኖችና በየክልሉ ያደራጇቸው ምስለኔዎች ራሳቸውን ባለሚሊዮኖች አድርገዋል። እነዚህ በአንድ ጀምበር የበቀሉ ቱጃሮች ከገንዘብ በተጨማሪም የጄኔራልነት፣ የሚኒስቴርነት፣ የክልል ገዢነት፣ እጅግ ቢያንስ የቢሮ ኃላፊነት ሥልጣንን ኪሳቸው ውሰጥ ከተዋል፤ ልባቸው የተመኘውን ዲግሪ ሸምተዋል። የመንግሥት ሥልጣንና ሃብት ይኸን ያህል የተቆራኙበት ሥርዓት በኢትዮጵያ ኖሮ አያውቅም። የጥቂቶች ያለአገባብና ያለቅጥ መክበር በአንፃሩ ደግሞ የብሃኑን ሕዝብ መደህየት ድህነትን መዋቅራዊ አድርጎታል።
6. በአቋራጭና በፍጥነት ለመክበር አስተማማኙ መንገድ የገዛ ራስ ጥረትና ታታሪነት ሳይሆን ቅጥፈት፣ አጭበርባሪነትና ሎሌነት መሆኑን የወያኔ ካድሬዎች በተግባር እያሳዩ ጥሮ ማደርን “ኋላ−ቀር አሠራር” አድርገውታል። በህወሓት የኢኮኖሚ ፓሊሲ የተበረታቱት አድርባይነት፣ ስንፍናና እና ልመና ችግርን የመጋፈጥ አቅማችንን ሰልበውታል።
እነዚህና የመሳሰሉት ጭብጦችን በማንሳት የረሀቡ መሠረታዊ ምክንያት የህወሓት አገዛዝ እንጂ ተፈጥሮ አለመሆኑን አስረግጠን እንናገራለን። ሕዝባችን በነፃነት ማሰብ፣ መመራመር፣ መፈተሽ ቢችል ኖሮ ረሀብን ማጥፊያ ብልሃት ማግኘት ባላቃተውም ነበር። ወደፊትም ቢሆን ተፈጥሮ እኛ እንደፈለግናት አትሆንም፤ መተማመኛችን የሰው ልጅ ወሰን የለሽ የፈጠራ ችሎታና ችግሮችን የመፍታት አቅም ነው። ለዚህ ደግሞ ችግሮችን በልጦ መገኘት ያስፈልጋል። ወያኔ የኢትዮጵያን ሕዝብ ከችግሮች በታች ሆኖ መፍትሄ ከአገዛዙ የሚጠብቅ ደካማ እንዲሆን አድርጎታል። በዚህም ምክንያት ነው የችግሮቻችን ቁንጮ ራሱ ወያኔ ነው የምንለው።
ህወሓትን ከመንግሥት ሥልጣን ሳናስወግድ ድህነትንና ረሀብ እናስወግዳለን ማለት ዘበት ነው:: ድህነት የህወሃት ዋነኛ የገቢ ምንጭ በመሆኑ ህወሓት ሥልጣን ላይ እስካለ ድረስ በወሬ ካልሆነ በስተቀር ድህነት በተግባር ሊቀጭጭ አይችልም። ችጋርና ህወሓት እጅና ጓንት ናቸው። ረሀብ የህወሓት ባለውለታ ነው። ረሀብ የህወሓት የቁርጥ ቀን አጋሩ ነው። ህወሓት በረሃ እያለ በአሸዋ የተሞሉ ጆንያዎችን እህል አስመስሎ በመሸጥ ለእርዳታ በመጣ ገንዘብ ራሱን አደራጅቷል። ስልጣን ከያዘም በኋላ “ረሀብን እየተዋጋሁ ነው” በማለት የምዕራባዊያንን ድጋፍ ለማግኘት ጠቅሞታል። ረሀብና ችጋር የወያኔ “ጪስ አልባ” እንዱስትሪዎች ናቸው። ሕዝባችን ተራበ ማለት የወያኔ ኩባንያዎች ሥራ አገኙ ማለት ነው። ህወሓት ረሀብን ለመቀነስ ቅንጣት ታህል ፍላጎት ቢኖረው ኖሮ በዚህ ወር ውስጥ በተደረጉ ስብሰባዎች በወጣው ወጪ ብቻ በአገራችን ላይ ያንዣበበውን ረሀብ በቁጥጥር ማዋል በተቻለ ነበር።
አርበኞች ግንቦት 7: የአንድነትና ዲሞክራሲ ንቅናቄ ለወገኖቻቸን መራብ ተጠያቂው የህወሓት ዘረኛ አገዛዝ ነው ይላል። ረሀብን ከኢትዮጵያ ምድር ለዘለቄታው ለማስወገድ የህወሓት አገዛዝን አስወግደን በምትኩ ለሕዝብ ደህንነት የቆመ፣ በሕዝብ የተመረጠ እና ከሕዝብ አብራክ የወጣ መንግሥት እንዲኖረን እንታገል ይላል።
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!!
Source www.patriotg7.org
No comments:
Post a Comment