Sunday, September 27, 2015

ነገረ – ኢሕአዴግ!!! ሥርዓቱ በሁለት ጫፍ የተሳለ አደጋ አፍጦበታል

ሥርዓቱ በሁለት ጫፍ የተሳለ አደጋ አፍጦበታል
በብዙ መልኩ ዴሞክራሲያዊ ገፅታን ያልተላበሰው ኢሕአዴግ ራሱን በገዥ መደብነት “አመቻችቶ” አስቀምጧል፡፡ ግንባሩ በቀደመው ዓመት አስረኛ ድርጅታዊ ጉባኤውን በዝግ በማካሄድ እንደተለመደው ባለ ዘጠኝ ነጥብ የአቋም መግለጫ በማውጣት አጠናቋል፡፡ በዚሁ ጉባኤ፣ ከዚህ ቀደም ከተካሄዱ ጉባኤዎች በተለይም በ1994 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ ከተካሄደው አራተኛው የድርጅቱ ጉባኤ ጀምሮ ይነሱ የነበሩ አጀንዳዎች ቅርፃቸውን ብቻ በመቀየር ይዘታቸውን እንደጠበቁ እስከ አስረኛው ድርጅታዊ ጉባኤ ድረስ ዘልቀዋል፡፡ በተለይም የመልካም አስተዳደር እጦትና የሙስና ጉዳይ ከድርጅቱ ጋር አብረው የተፈጠሩ እስኪመስሉ ድረስ ችግሮቹ ገንግነዋል፡፡ በ1994ዓ.ም የአዲስ አበባው ጉባኤ አብይ አጀንዳ በመሆን ጉባይተኛው የተወያየበት አጀንዳ “ጥገኛ ዝቅጠት አስተሳሰብ” የስርዓቱ አደጋ መሆኑን ነበር፡፡ የቃላት ሃብታሙ ኢሕአዴግ፣ “ጥገኛ ዝግጠት አስተሳሰብ” የሚለውን ሃረግ “ኪራይ ሰብሳቢ” በሚል አገላለጽ በመተካት በቅርቡ እስከተካሄደው አስረኛ ድርጅታዊ ጉባኤ ድረስ ይህንኑ አጀንዳ ሲመክርበት ኑሯል፡፡ ከግንባሩ ነገረ ታሪክ መረዳት እንደሚቻለውም ድርጅቱ በስልጣን ላይ እስካለ ድረስ ይሄው አጀንዳ (ኪራይ ሰብሳቢነት) ሲነሳና ሲወድቅ እንደሚኖር እሙን ነው፡፡ ርግጥ ይህ ጉዳይ በመንግስት መስሪያ ቤቶች እየታየ ካለው የመልካም አስተዳደር እጦት ጋር በተያያዘ የማታ ማታ የግንባሩን ፍጻሜ የሚያቀርበው ይሆናል፡፡ በርግጥም ግንባሩ እንደሚለው “ኪራይ ሰብሳቢነት የሥርዓቱ አደጋ ነው”፡፡ ከዚህ አኳያ ሥርዓቱ በሁለት ጫፍ የተሳለ አደጋ አፍጦበታል፡፡
“ኪራይ ሰብሳቢነት” ሲባል
ኪራይ ሰብሳቢነት ሲባል ያልተገባ የኢኮኖሚ ጥቅም በማጋበዝ ብቻ የሚተረጎም ሳይሆን ከዚህ ባለፈ የፖለቲካ ጥቅም ትስስር (ኔት ወርክ) እና ቡድንተኝነትን መሰረት ያደረገ የስልጣን መደጋገፍንም የሚጨምር የትርጉም ይዘት አለው፡፡ የአደጋው መንታ መልክም ይሄው ነው፡፡ የስርዓቱ መሪዎች ለማመን በሚከብዱ የሙስና መረቦች በመተብተባቸው በህዝቡ ላይ እየተፈጠሩ ያሉ ቅሬታዎችን መሰረት አድርጎ ሊፈጠር የሚችለው ህዝባዊ አመፅ የአደጋው አንዱ ገጽታ ሲሆን፤ ሁለተኛው የአደጋው መልክ ደግሞ ባለስልጣናቱ እንደ ቡድን በሚዘረጉት የሙስና መረብ ከጥቅም ትስስራቸው ጋር በተያያዘ እንደ መንግስታዊ መዋቅርም ሆነ እንደ ድርጅት የሚመጡ ግምገማዎችን በጋራ የሚመክቱበት እንዲሁም ባለስልጣናቱ የራሳቸውን የቡድን አባል ወደ ተሻለ የስልጣን ከፍታ ለማውጣት የሚያደርጉት ርብርብ የቡድን ፍላጎት የሚታይበት በመሆኑ፣ ፍላጎቱ ከሌላው ቡድን ጋር የሚጋጭ ከሆነ በዚህ መሀል የሚፈጠረው ልዩነት ከስርዓቱ አልፎ ለአገርም አደጋ የሚሆንበት እድል ይኖራል፡፡ በዚህ አግባብ ኢሕአዴግ በሁለት ጫፍ የተሳለ አደጋ አፍጦበታል፡፡ ‘የግንባሩን ቀጣይ እጣ ፈንታ ከሚወስኑት ጉዳዮች አንዱና ዋነኛው ኪራይ ሰብሳቢነት ነው’ የመባሉ እውነታም ከዚህ የመነጨ ነው፡፡ በተለይም የፖለቲካ ኪራይ ሰብሳቢነት አዝማሚያ ብሄርን መሰረት ያደረገ ቡድንተኝነት የሚንፀባረቅበት በመሆኑ አደጋው ጠባብነትን መታያው አድርጎ የሚከሰት ሲሆን ፤ ይህን ተከትሎ የሚፈጠረው ችግር ከሥርዓቱ አልፎ ለአገርም የከፋ መሆኑ የሚያከራክረን ጉዳይ አይደለም፡፡
ስርዓቱ “ኪራይ ሰብሳቢነት ለመታገል ጥረት እያደረኩ ነው” እያለ ዲስኩሩን ቢያሰማም፣ ችግሩ ከመባባሱ ውጭ ጠብ ያለ ለውጥ በአደባባይ ሊታይ አልቻለም፡፡ እጅግ አስደንጋጭ የሙስና ሪከርዶች በተወካዮች ምክር ቤት በኩል በሪፖርት መልኩ ሲታለፍ ማየት የሚደንቅ አይደለም፡፡ በመሬትና በፍትህ አስተዳደር እንዲሁም በመንግስት ንብረት ግዢና ሽያጭ ላይ እየታዩ ያሉ ግልጽ የስልጣን መባለጎችን ስናስተውል አገሪቷን እንደ “መንግስት” እያስተዳደራት ባለው ገዢው ግንባር ላይ እምነት እንድናጣ ያደርገናል፡፡
ባገባደድነው አመት የፌዴራል ዋና ኦዲት መስሪያ ቤት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረበው ሪፖርት ሃያ አምስት የሚሆኑ የፌዴራል መስሪያ ቤቶችና ዩኒቨርስቲዎች ህጋዊነት የሌለው የንብረት ግዢና ሽያጭ መካሄዳቸውን፣ ሥራቸውን የለቀቁ ሰራተኞች በሌሉበት እስከ ስድስት ወር የሚደርስ ደመወዝ እንደተከፈላቸው፣ ያለ ጨረታ የኮንስትራክሽን ግንባታ ስራዎች ለተለያዩ ተቋራጮች እንደተሰጠ፣ ህጋዊ የደመወዝ ጭማሪ ላልተደረገላቸው ሰራተኞች በህገ-ወጥ መንገድ ተጨማሪ ክፍያ የከፈሉ መስሪያ ቤቶች መኖራቸውን ያመለከተው ይሄው ሪፖርት፣ በዚህም እንደ አገር ከሶስት ቢሊዮን ብር በላይ ያልተመሳከረ ሒሳብ መኖሩን ይጠቁማል፡፡ ሪፖርቱ የፌዴራል መስሪያ ቤቶችንና የተወሰነ የኒቨርስቲዎችን ብቻ የሚመለከት ሲሆን፤ በየክልሉ ያለውን ምዝበራ ከዚህ ሪፖርት አኳያ ምን ያህል የከፋ ሊሆን እንደሚችል መገመት ይቻላል፡፡ የፌዴራል ዋና ኦዲት መስሪያ ቤት የንብረት ግዢና ሽያጭ ችግር አለባቸው፣ ህጋዊ የፋይናንስ አሰራር አልተከተሉም በሚል በሪፖርቱ የጠቆማቸው የፌደራል መስሪያ ቤቶችም ሆኑ ችግሩ የታየባቸው የዩኒቨርስቲ አመራሮች በህግ ሲጠየቁ ለማየት አልታደልንም፡፡ በርግጥ በኢህአዴግ ቤት ፖለቲካን እንጂ ገንዘብን መሰረቅ የስርዓቱ አንዱ ገጽታ ነውና የተለየ እርምጃ አይጠበቅም፡፡ ይሁንና እነዚህ ከፍተኛ አመራሮች ከገንዘብ ባለፈ የፖለቲካ ፍንገጣ ያሳዩ ቀን ‘ፋይላቸው’ ከመሳቢያ መውጣቱ አይቀሬ ነው፡፡
በኢህአዴግ ቤት፣ ከሁሉም የሙስና አይነቶች ከባዱ ሙስና የመሬት ወረራን ተከትሎ እየተፈጠረ ያለው ምዝበራ ዋናው ተጠቃሽ ነው፡፡ በዚህ ዘርፍ እየታ ያለው ሙስና “ውሻ በቀደደው ጅብ ይገባል” እንዲሉ የከፍተኛ አመራሮችን ፈለግ በመከተል ቀበሌ ድረስ ያሉ አመራሮች “ከድርሻቸው” በላይ በወዳጅ ቤተ ዘመድና በሙታን ስም ሳይቀር የመሬት ወረራዉን ተያይዘውታል፡፡ የታችኛው አመራር ምዝበራ አይን እያወጣ በመምጣቱ “ኪራይ ሰብሳቢነትን አየተዋጋሁ ነው” የሚለው ኢሕአዴግ፣ ለአስመሳይ ፖለቲካው ማሳያ ይሆን ዘንድ አልፎ አልፎ የታችኛውን አመራር ጭዳ ሲያደርገው ይታያል፡፡ ነገሩ ‘የኪራይ ሰብሳቢዎች መተካካት’ አይነት ነገር ነው፡፡ የበላ ይሻራል፡፡ ያልበላ ይሾማል፡፡ ኡደቱም በዚህ መልኩ እየቀጠለ ያለ ይመስላል፡፡ ለዚህ ማሳያ ሆኖ የሚቅበው ጉዳይ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ተሞክሮ ነው፡፡ የከተማ አስተዳደሩ የከተማ ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ምክትል ኃላፊ የሆነው አቶ ኃየሎም ጣውዩ በነሐሴ ወር ሦስተኛ ሳምንት ለንባብ ከወጣው ከሪፖርተር ጋዜጣ ጋር ባደረገው ቃለ መጠየቅ በ2007 የሥራ ዘመን ከመሬት ጋር በተያያዘ ብቻ በየደረጃው ያሉ 315 (ሦስት መቶ አስራ አምስት) አመራሮችና ፈፃሚዎች ከኃላፊነታቸው እንደተነሱ፣ ከእነዚህ ውስጥ በህግ የሚጠየቁ ኃላፊዎች እንዳሉ ተናግሯል፡፡ በተመሳሳይ መልኩ ከተማ አስተዳደሩ 221 (ሁለት መቶ ሃያ አንድ) አመራሮችንና 4100 (አራት ሺህ አንድ መቶ) የሚሆኑ የመንግስት ሰራተኞችን ከሥራ ሊያሰናብት እንደሆነ፣ በህግ የሚጠየቁ መኖራቸውንም ለፋና ብሮድ ካስት አስታውቋል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ የካቢኔ ሹም ሽር እስከማድረግ የሚደርስ እርምጃ ሊወስድ እንደሆነም መረጃዎች በመውጣት ላይ ይገኛሉ፡፡ በመቶዎች የሚቆጠሩ መካከለኛ አመራሮች ከሙስና ጋር በተያያዘ ከሥራ የሚሰናበቱበት አዲስ አበባ እንደ ትናንቱ ሁሉ ዛሬም ‘አንገት አልባ’ አመራሮችን ተሸክማ በማዝገም ላይ ትገኛለች፡፡ ነገሩ “ጉልቻ ቢቀየር …..” አይነት ነገር ነው፡፡ የበላ ይሻራል፡፡ ያልበላ ይሾማል፡፡ ዑደቱም ይቀጥላል….
ከመሬት ወረራ ጋር በተያያዘ በተለይም ሀሰተኛ የመሬት ባለይዞታነት መረጃ በማዘጋጀትና ህጋዊ ቅድመ ሁኔታ ላላሟሉ ሰዎች በጥቅም ትስስር መሬት የመስጠቱ ሁኔታና የአመራሩ የመሬት ቅርምት ከአዲስ አበባ ከተማ በከፋ መልኩ በሌሎች የክልል ከተሞች እንዳለ ከአንባቢ የተሰወረ አይደለም፡፡ በፍትህ አስተዳደር በኩልም አስደንጋጭ የሙስና ተግባር እየተከሰተ እንዳለ የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡ ከ30 ሺህ እስከ 350 ሺህ ብር የሚደርስ ገንዘብ በመቀበል በሀሰተኛ የፍርድ ቤት ትዕዛዝ ፍርደኞችን የለቀቁ የፌደራልና የክልል ማረሚያ ቤቶች መካከለኛ አመራሮችን እንዲሁም ከሙስና ጋር በተያያዘ የዳኞችን ክስ/ስንብት መስማት ከአመት አመት እየተለመደ መጥቷል፡፡ እንግዲህ በ”ሕግ በምትመራ” አገር ላይ ከአመት አመት አስደንጋጭ የሙስና ዜናዎችን በሪፖርትም፣ በክስም መልክ እየታየ በመሆኑ “መንግስት” የሚባለው አካል ምን እየሰራ እንዳለ መጠየቅ ግድ ይለናል፡፡ የመሬትና የፍትህ አስተዳደርን እንደ ማሳያ አንስተን ተመለከትን እንጂ በሌሎች መንግስታዊ ተቋማቶች ዘንድ ምን አይነት ጉድ ሊፈጸም እንደሚችል መገመት የሚከብድ አይደለም፡፡ በቅርቡ እንኳ የኦሮሚያ ክልል ገቢዎች ቢሮ ኃላፊ የነበረው አቶ ወንድሙ ቢራቱ በሙስና ወንጀል ተጠርጥሮ የ500 (አምስት መቶ) ሚሊዮን ብር ኦዲት እየተጣራበት ይገኛል፡፡ የምርመራው ውጤት ምን ይሁን ምንም አንድ የክልል ከፍተኛ ባለስልጣን በዚህን ያህል የብር መጠን በሙስና ወንጀል መጠርጠሩ (ኦዲት መደረጉ) ሥርዓቱ በምን ያህል መጠን እንደ ነቀዘ ጥሩ ማሳያ ይሆነናል፡፡
በየአመቱ ተዝቆ ከማያልቁ መንግስታዊ ጉዶች መካከል ጥቂቱን ቆንጥሮ የሚያሳየን የፌደራል የስነ-ምግባርና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን እንቅስቃሴ ከአሳ ነባሪዎች ይልቅ ትንንሽ አሳዎች ላይ ትኩረት አድርጎ “መረቡ”ን የጣለ በመሆኑ፣ አህአዴግ ስልጣን ላይ እስካለ ድረስ ሙስና የምንግዜም ቀዳሚ አጀንዳ ሆኖ ይኖራል፡፡ ገዢዉ መደብ ኢህአዴግ፣ በጉምቱ ባለሥልጣናቱ ላይ የሚታየውን ሙስና ከመቅረፍ ይልቅ “ሂስና ግለ ሂስ” በሚል ድርጅታዊ ቀኖናዉ ለጉዳዩ ከሚያሳየው መለሳለስ የተነሳ የሙስና ጉዳይ ለፖለቲካዊ አለመግባባቶች የመፍትሄ ማፈላለጊያ እየሆነ መጥቷል፡፡ ግንባሩ እንደሁልጊዜው ሁሉ በአስረኛ ድርጅታዊ ጉባኤው “የፖለቲካዊ ኢኮኖሚ ኪራይ ሰብሳቢነት ሚናን በልማታዊ አስተሳሰብ በመተካት የኢትዮጵያን ሕዳሴ እናረጋግጣለን” ቢልም፣ ጉዳዩ ከተለመደው የአቋም መግለጫነት የዘለለ ጠብ የሚል ነገር እንደማይኖረው የድርጅቱ የቀደመ ተሞክሮ ይነግረናል፡፡
እንደ-መዉጫ
በመቶ ብሮች የሚቆጠር የወር ደመወዝተኛ በበዛባት አትዮጵያ፣ በየመስሪያ ቤቱ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ብር ምዝበራ መካሄዱን፣ ይህን ተከትሎ እንደ አገር ቢሊዮን ብሮች በየዓመቱ በመንግስት ሌቦች መመዝበሩን የሚያመለክቱ ሪፖርቶች ከመንግስታዊ ተቋማት ጭምር መስማት መደበኛዉን የትራፊክ አደጋ ሪፖርት የመስማት ያህል እንኳን አላስደነግጠን ብሏል፡፡ በፖለቲካና በነጻ ተቋምነት መሃከል የዋልሉ ተቋማት አሁን አሁን የጠቅላዩ ኢህአዴግ ክንፍ መሆናቸዉን በተግባር እያሳዩን ነዉ፡፡ መንግስት በከሳሽነት በሚቀርብባቸዉ ፖለቲካ-ቅብ የክስ ጉዳዮች ተሸናፊ ሆኖ የታየበት አጋጣሚ የለም፡፡ የፍርድ ቤት ዉሳኔ በማረሚያቤት አመራሮች ሳይፈጸም ሲቀር የታዘብንባቸዉ አጋጣሚዎች ከጣቂት በላይ ናቸዉ፡፡ “ፍትህ”ን በብረትና በገንዘብ የገዙ አካላት አንገታቸዉን ቀና አድርገዉ በሚሄዱባት ኢትዮጵያ፣ የግፉአን ድምጽ በርክቶባታል፡፡ ጎን ማሳረፊያ ያጡ ዜጎች በበረከቱባት ሃገር፣ ከግማሽ ደርዘን በላይ ቪላ ቤቶች በተለያዩ ግለሰቦች ስም ያለዉ የኢህአዴግ መካከለኛ አመራር ፈልጎ ማግኘት ያን ያህል የሚከብድ አይደለም፡፡ በቦታ ርቀት፣ በግንዛቤ ማነስ፣ ከበቂ የምግብ አቅርቦት እጦት ጋር በተያያዘና መሰል ማህበረ-ኢኮኖሚያዊ ችግሮች የተነሳ በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ህጻናትና ወጣቶች በየአመቱ ትምህረታቸዉን ለማቋረጥ በሚገደዱባት አትዮጵያ፣ ልጆቻቸዉን ከአንድ ቀበሌ የግማሽ አመት በጀት ጋር የሚስተካከል የዉጭ አገር ትምህርት ቤት የሚያስተምሩ የአህአዴግ ከፍተኛ ባለስልጣናት ቁጥር እንደ ኢኮኖሚ “እድገቱ” ሁሉ በሁለት አሃዝ የሚገለጹ ናቸዉ፡፡ ንጹህ የመጠጥ ዉሃ ያጣ ህዝብ በበረከተባት አገር፣ የአልኮል መጠጥ ፋብሪካ በአክሲዮን ስም የገነቡ፤ ሚለዮኖች የዕለት ጉርሳቸዉን በጡበት ሁኔታ የግል ባንክ ባለቤት የሁኑት ባለስልጣናት የደም እንጀራ እየጎረሱ እንደሆነ ሊረዱት አልቻሉም፡፡
የኢህአዴግ ባለስልጣናትን ነገረ-ስራ በቅጡ ያስተዋለ ሰዉ የሚከተለዉ ድምዳሜ ላይ መድረስ ይቻለዋል፡፡ እርሱም፡- ‘ማንኛዉም የኢህአዴግ ከፍተኛ ባለስልጣናት ከህግ በላይ ናቸዉ፡፡ የትኛዉም የህዝብም ሆነ የአገር ሃብት የባለስልጣናቱ እንጂ የህዝብ አይደለም’ ባልተጻፈ ህግ እየተተገበረ ያለዉ እዉነታ ይህ ነዉ፡፡ ኢህአዴግ “የ አስራ ሦስት ወር ጸጋ” የተባለላትን አገር ወደ አስራ ሦስት ወር የፖለቲካ ጭቆናና የኢኮኖሚ ብዝበዛ አሻግሯታል፡፡ የአገሪቱ ማህበራዊ ቀዉስ ሲጨምር እንጂ ሲቀንስ አላየንም፡፡ አይነ ስዉሩን ደርግ ሸኝተን ደንቆሮዉን አህአዴግ ተክተናልና ዛሬም እንደ ትላንቱ በደል የማንነት አካል ሆኗል፡፡ አስር፣ እንግልት፣ ስቅየት፣ ስደት፣ ሞት … ከገዥዉ መደብ በተቃራኒ የተሰለፉ ኢትዮጲያዉያን እጣ ፋንታ መሆኑን ሩብ ክፍለ-ዘመን ያካለለዉ የአገዛዙ ተሞክሮ ጮሆ ይመሰክራል፡፡ ገዥዉ መደብ በብዙ መልኩ ኮረብታዉ እርቆት ቁልቁለቱን በሚገርም ፍጥነት ተያይዞታል፤ የአይቀሬዉን አብዮት ማፍጠኛ የተጫነዉ ኢህአዴግ የህልዉናዉ ማክተሚያ ጊዜ ሩቅ አይደለም፡፡ በየአመቱ እንደ “መንግስት” አዋጂ አዲስ ዓመት መግባቱን በሚዲያ ስንሰማ ኑረናል፡፡ አዲስ ነገር በማናይበት ሁኔታ “አዲስ ዓመት” ብሎ ነገር ምናችን ነዉ?! እኛ ኢትዮጵያዊያን አዲስ አመት ሳይሆን አዲስ ስርዓት እንሻለን!!
(የዚህ ጦማር አቅራቢ ጋዜጠኛ ሙሉዓለም ገ/መድህን ሲሆን በቅርቡ “የኢሕአዴግ ቁልቁለት” በሚል ርዕስ የጻፈው መጽሀፍ ለንባብ በቅቷል፡፡ ይህ ጽሁፍ በተለይ ለጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ የተላከ ነው፡፡)
ምንጭ ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ

Thursday, September 17, 2015

ምኞትና ተግባር ምንና ምን ናቸው? ርዕዮት አለሙ

በአዲሱ አመት ዋዜማ የፖለቲካ እስረኞችን ለመጠየቅ ወደ ቂሊንጦ እስርቤት ከእህቴ ጋር ሄጄ ነበር፡፡ ስማችንን እና የምንጠይቃቸዉን እስረኞች ስም ካስመዘገብን በኋላ መታወቂያችን አሳይተን ወደዉስጥ ልንገባ ስንል መታወቂያዉን የምትመለከተዉ ፖሊስ ስማችንን ካነበበች በኋላ "ቆይ ቆይ የእናንተማ መጠየቅ አለበት" አለችንና መታወቂያችንን ይዛ ከበር መለሰችን፡፡ ከበሩ አጠገብ በሚገኝ ጎብኝዎች ወረፋ በሚጠብቁበት የእንጨት መቀመጫ ላይ አረፍ እንዳልን በሃሳብ ላይ ታቹን ማለት ጀመርኩ፡፡ እንድንገባ ይፈቅዱልን ይሆን ወይስ የቃሊቲዎቹ እንዳደረጉት "ፍቃድ የላችሁም" የሚል አስቂኝና አናዳጅ መልስ በመስጠት ይመልሱን ይሆን? ለሚለዉ ጥያቄ መልሱ እኔዉ ጋር ያለ ይመስል አጎንብሼ ማሰቤን ቀጠልኩ፡፡ ቀና ስል ከፊት ለፊቴ "ማረሚያ ቤቱ" ለእስረኛ ቤተሰቦች መልካም ምኞቱን የገለፀበት ወረቀት ተለጥፎ ተመለከትኩ፡፡ ከአራት አመታት በላይ በመኖር የእስርቤቶቹን አሰራር አዉቀዋለሁና ተመሳሳይ የመልካም ምኞት መግለጫ የያዘ ወረቀት ለእስረኛዉም ተለጥፎ እንደሚሆን አልተጠራጠርኩም፡፡ ሰላም እየነሳ ሰላም "የሚመኝ"፣ ህክምና እየከለከለ ጤንነትን "የሚመኝ"፣ የሚዋደዱ ሰዎችን ከሽቦ ወዲያና ወዲህ ሆነዉ እንኳን እንዳይተያዩ እየከለከለ ፍቅርን "የሚመኝ" . . .ተቋም ! አንድ ፖሊስ ወደኛ እየቀረበ ሲመጣ ሀሳቤ ተቋረጠ፡፡ መታወቂያዬን እየመለሰልኝ መግባት እንደማልችል ነገረኝ በኋላ ለእህቴም ተቀራራቢ መልስ በመስጠት መታወቂያዋን መለሰላት፡፡ ለምን ለሚለዉ ጥያቄያችን "አላዉቅም፡፡ የተወሰነውን ንገር ተብዬ ነው" የሚል ምላሽ ሰጠን፡፡ ምን አይነት አምባገነንነት ነው? እስር ቤት እያለሁ በሌሎች የመጎብኘት መብቴን የነፈገው ስርዐት ዛሬ ደግሞ የጠያቂነት መብቴን እየነፈገው ነው፡፡ ሙሉውን ቀን ሊባል በሚችል መልኩ ስለፖለቲካ አሳሪዎቻችን ጉዳይ እያሰብኩ ስብሰለሰል ዋልኩ፡፡ የእኔና የሌሎች በርካቶች መብሰልሰል ምክንያት የሆኑት የኢህአዴግ ባለስልጣናት ደግሞ በአሉን ምክንያት በማድረግ ፍትህ እያዛቡበተ፣ እያሰሩትና እየገደሉት ላሉት ህዝብ የመልካም ምኞት መግለጫቸዉን ሲያዥጎደጉዱለት ዋሉ፡፡ ይህንን የኢህአዴግ ምኞትና ተግባር መራራቅ እያሰብኩ እያለሁ "ኢህአዲግን ለመለወጥ የምንፈልግ ሰዎች ምኞትና ተግባርስ ምን ይመስላል? " የሚል ጥያቄ ሽው አለብኝ፡፡ ጥያቄው በርካታ መልሶች ቢኖሩትም በዚህ ጽሁፍ ለማቅረብ የመረጥኳቸው ግን ሁለቱን ብቻ ነው፡፡ አጉል ህልመኞች በዚህ ስርዓት ተጠቃሚ በመሆናቸው ብቻ የሌሎችን ወገኖቻቸውንና የሀገርን ጉዳት ማየት ካልቻሉ ወይም ካልፈለጉ ሆዳሞችና በህወሓት የዘረኝነት መርዝ ከተበከሉ ጥቂቶች በቀር የኢህአዴግን መሰንበት የሚፈልግ ዜጋ ስለመኖሩ እጠራጠራለሁ፡፡ በተለያዩ አጋጣሚዎች የማገኛቸዉ ሰዎች ምኞትም የስርዓት ለውጥን ማየት ነው፡፡ ነገር ግን "እነዚህ ሁሉ ሰዎች የሚፈልጉትን ለውጥ ለማየት ምን አይነት አስተዋፅኦ እያደረጉ ነው?" ብለን ብንጠይቅ የምናገኘው ምላሽ አስደሳች አይደለም፡፡ አንዳንድ ለዉጥ ፈላጊዎች ቁጭ ብሎ ከመመኘት በቀር ለለዉጡ መምጣት የሚያደርጉት ምንም ነገር የለም፡፡ ለምን አንዳች ነገር እንደማያደርጉ ስትጠይቋቸው ከምታገኟቸዉ መልሶች መሃከል "እነዚህን መዥገሮች እሱ ይንቀላቸዉ እንጂ በሰው ሃይልማ የሚሆን አይደለም፤ ህዝቡን ከፋፍለውታል እኮ ምን ማድረግ ይቻላል? . . ." የሚሉት ይገኙበታል፡፡ እነዚህ ሰዎች ምንም እንዳይሰሩ ያደረጋቸዉ ትልቁን ምክንያት ጠጋ ብላችሁ ስትመረምሩ ግን ፍርሃት ሆኖ ታገኙታላችሁ፡፡ ፕ/ር መሳይ ከበደ "The Impasse of Fear in Ethiopia and the Necessity of Comprehensive struggle ” በተሰኘ ፅሑፋቸዉ እንዳስቀመጡት ፍርሃት የጨመደደው ህዝብ ሁሌም ምንም ላለማድረጉ የሚያቀርባቸው በርካታ ምክንያቶች ይኖሩታል፡፡ ሌሎቹ ለዉጥ ፈላጊዎች ደግሞ ለዉጥ ሊያመጡ የሚችሉ እንቅስቃሴዎቸን በማድረግ ረገድ ከላይኞቹ የተሻሉ ቢሆኑም የጀመሩትን መጨረስ ግን የማይሆንላቸው ናቸው፡፡ እያደረጉ በነበረዉ እንቅስቃሴ ሳቢያ አንዳች ችግር ሲደርስባቸው ከመንገዳቸው ይወጣሉ፡፡ "በዚህኛው አመተምህረት በተደረገው ምርጫ ሳቢያ ለእስር ተዳርጌ ነበር፤ በዛኛው ወቅት በተደረገው ሰልፍ ላይ ተገኝቼ ተደብድቤያለሁ" ማለት ይቀናቸዋል፡፡ አሁንስ? ስትሏቸው ግን መልሳቸው "ጎመን በጤና" ነው፡፡ እንደነዚህ አይነቶቹ ሰዎች መጀመሪያዉኑ እየታገሉት የነበረውን መንግስት ግፈኝነት በሚገባ ያወቁት አይመስሉም፡፡ የቆረጡ ለዉጥ ፈላጊዎች እነዚህኞቹ አስቀድሞ ከተጠቀሱት ጋር የለዉጥ ፍላጎታቸው ቢያመሳስላቸውም ለውጥን ለማምጣት የሚያደርጉት እንቅስቃሴ መኖሩና ቁርጠኝነታቸው ደግሞ የተለዩ ያደርጋቸዋል፡፡ "እሱ ያመጣዉን እሱ እስኪመልሰው" በማለት እጃቸውን አጣጥፈው አይቀመጡም፡፡ ለለውጡ እዉን መሆን የሚችሉትን ሁሉ ያዋጣሉ፡፡ ከነዚህ ሰዎች መሀከል በግንባር ቀደምትነት ሊጠቀስ የሚገባው ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋን መዉሰድ ይቻላል፡፡ እስክንድር ለለዉጡ ያለውን ሁሉ እየከፈለ ያለ ሰው ነው፡፡ ወደስምንት ጊዜ ያህል ሲታሰርና ሲፈታ፣ የመፃፍ መብቱን ሲገፈፍ፣ ሲደበደብ፣ ንብረቱ ሲወረስና ከሚወዳት ባለቤቱና ልጁ ጋር በአካል መለያየት ግድ ሲለዉ ሁሉ በአላማው ከመጽናት ውጭ ለአፍታ እንኳን ሸብረክ ሲል አልታየም፡፡ እስክንድርና መሰሎቹ ዲሞክራሲ እንዲሰፍንና ነፃነት እንዲገኝ ካስፈለገ ከምኞት ባለፈ ስራና መስዕዋትነት እንደሚጠይቅ ገብቷቸዋል፡፡ ለገባቸው እውነት ደግሞ እየኖሩ ነው፡፡ እነ እስክንድር ይሄን ሁሉ መስዕዋትነት ሲከፍሉ ታዲያ ሁኔታው ያማያማቸው ሆኖ አይደለም፡፡ ህመሙን ጥርሳቸውን ነክሰው እየቻሉ እንጂ! አቶ ኤፍሬም ማዴቦ "ከዊሃ እስከ ኦምሃጀር-አንድ ሰሞን ከአርበኞች ጋር" በሚል ርዕስ በቅርቡ ባስነበቡን ጽሑፋቸዉ የአርበኞች ግንቦት 7 ጦርን ለመቀላቀል ከአሜሪካን ሀገር ከተደላደለ ኑሮዋቸው ተነስተው ሲሄዱ ይሰማቸው የነበረዉን ከሚወዱት ልጃቸው የመለየት ህመም በዉብ አገላላፅ ተርከዉልናል፡፡ አቶ ኤፍሬም አውሮፕላን ማረፊያ ድረስ ሊሸኛቸው የመጣዉን የ17 አመት ልጃቸውን ሲሰናበቱ "ልጄ ይሄን ማድረግ አልፈልግም ነገር ግን ማድረግ አለብኝ" ያሉት ፊታቸው በእንባ እየታጠበ ነበር፡፡ የማይፈልጉትን ነገር ለማድረግ እራሳቸዉን ያስገደዱበትን ምክንያት የገለጹት "የምወደውን አንድ ልጄንና ጥሩ ስራዬን ደህና ሁኑ ብዬ በረሃ የገባሁት ሃገሬ ዉስጥ ፍትህ፣ ነፃነት፣ እኩልነትና ዲሞክራሲ አብቦ ለማየት ነው" በማለት ነው፡፡ ጋዜጠኛ እስክንድርና አቶ ኤፍሬም ምንም እንኳን ለውጥን ለማምጣት የሚሄዱበት መንገድ ለየቅል ቢሆንም ሁለቱም ግን ለለውጡ ያላቸውን ሁሉ ለመስጠት ተዘጋጅተዋል፡፡ አንደኛቸው ለውጡ ግድ ብሎአቸው ቤታቸው እስርቤት ሲሆን ሌላኛቸው ዱርቤቴ ብለዋል፡፡ ሁለቱም ከሚወዷቸው ወንዶች ልጆቻቸው ጋር ተለያይተዋል፡፡ ሁለቱም ለውጥ በምኞት ብቻ እንደማይመጣ ያውቃሉና እራሳቸው ሄደው ይገናኙት ዘንድ በተለያየ መንገድም ቢሆን በጉዞ ላይ ናቸው፡፡ በመጨረሻም . . . በኢትዮጵያ እኩልነት ዴሞክራሲ ነፃነትና ፍትህ እንዲሰፍን የምንመኝ ሁላችን ከቀን ህልማችን መንቃትና ምኞቶቻችንን ወደ ተግባር ለመለወጥ መንቀሳቀስ ያስፈልገናል፡፡ ከመንቀሳቀስ ያገደን ፍርሃታችን ከሆነ በቀደመው ንዑስርዕስ ስር የጠቀስኩት የፕ/ር መሳይ ጽሑፍ ፍርሃትን ለመዋጋት የሚያስቀምጠው አንድ መፍትሄ አለ፡፡ ድርጊት! ራሳችንን ለፈሪነት የተመደብን አድርገን የምንቆጥርና በሌሎች ደፋርነት መንፈሳዊ ቅናት የሚያድርብን ሰዎች ካለን ፕ/ሩ የጠቀሱት የፈላስፋው አርስቶትል ሃሳብ ሳይጠቅመን አይቀርም፡፡ አርስቶትል "ጀግና ለመሆን ጀግንነትን መለማመድ ያስፈልጋል" ይለናል፡፡ ለአርስቶትል ድፍረት እንደሌሎቹ የሞራል እሴቶች ሁሉ አብሮን የሚወለድ እምቅ ሃይል ሲሆን እውን ለመሆንና ለመዳበር እንዴሎቹ እሴቶች ሁሉ ልምምድ ያስፈልገዋል፡፡ አስፈላጊዉ ጥንቃቄ እንደዳለ ሆኖ እስኪ እስከዛሬ ያላደረግነዉን አንድ ድፍረት የተሞላበት ድርጊት እናድርግ፡፡ ፕ/ሩ እንደሚሉንና እኔም እንደማምነው ድርጊት ስኬትን ያመጣል፡፡ ስኬቱ የቱንም ያህል ትንሽ ቢሆን በራስ መተማመንን ይወልዳል፡፡ በራስ በተማመን ሲኖር ደግሞ ፍርሃት ይጠፋል ወይም ችግር ሊሆን በማይችልበት ደረጃ ዝቅ ይላል፡፡ ከፍርሃታችን ወጥተን እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ሳለን ከኢህአዴግ በሚወረወርብን ዱላ ተሰብረን ከመንገዳችን ላለመውጣት ደግሞ የገዢዉን ፓርቲ ማንነት ጠንቅቆ ማወቅና ቢያንስ የስነልቦና ዝግጅት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ለማንጠብቀው ነገር አንዘጋጅም፡፡ ያልተዘጋጀንበት ነገር ደግሞ ሁሌም ይጥለናል፡፡ በመሆኑም የምንታገለው ስርዓት ስልጣኑን ላለማጣት የቱንም አይነት ጭካኔ የተሞላው እርምጃ እንደሚወስድ ማወቅና ለዛም እራስን ማዘጋጀት ግድ ይላል፡፡ ደግሞስ ኢህአዴግ ምን ሊያደርገን ይችላል? ሊያደርገን የሚችለው ሁሉ አስቀድሞም ከአፈር በታች እንዲዉል የተወሰነበት ስጋችን ላይ አይደለምን? መልካም አዲስ አመት! መስከረም 3/ 2008 – Ethiomedia.com – September 14, 2015
Source Ethiomedia.com

Wednesday, September 9, 2015

ቴዲ “የፍቅር ነብዩ”ን ተውት ስለ ፍቅር ደግሞ ደጋግሞ ይዘምር… (ፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማርያም)

ከፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማርያም
ትርጉም በነጻነት ለሀገሬ
እረ ተዉኝ ባትነኩኝ ምናለበት
አባካችሁ ሰዎች ስራዬን ልስራበት።
ታላቁ ጥላሁን ገሠሠ
ፍቅር ሁሉንም ድል ያደርጋል !
ሸክስፒር “አስራሁለተኛው ሌሊት“ በሚለው የትያትር ፁሁፋቸው ላይ የኦርሲኖ መስፍን በአዳራሹ ተሰባስበው ለነበሩት ድምጻውያንና ሙዚቀኞች  እንዲህ በማለት ተናግረው ነበር፣ “ሙዚቃ የፍቅር ምግብ እስከሆነ ድረስ አሁንም ዘምሩ፣ በርካታ ሙዚቃዎችን ደግማችሁ ደጋግማችሁ ዘምሩልኝ…“Teddy Afro, Ethiopian popular singer
እራሱን ህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ (ህወሀት) እያለ የሚጠራው የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ በቅጽል ስሙ ቴዲ አፍሮ እየተባለ የሚጠራውን ቴዎድሮስ ካሳሁንን በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ከብዙ ጊዜ በፊት ጀምሮ ለመንፈሳቸው እርካታ ምግብ የሆነውን የህዝቦች የፍቅር ሙዚቃ እንዳይጫወት እገዳ ሲጥልበት ቆይቷል፡፡
የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ የቴዲን ህይወት እንደ እነርሱ በመከራ የታጀበ እንዲሆን አጥብቀው ይሰራሉ፡፡ እንደ እነርሱ “የመከራ ፍቅር ኩባንያ“ እንዲሆን ይፈለጋል፡፡
ቴዲ ግን ስለሰው ልጆች ፍቅር ደስታ እንጅ በምንም ዓይነት መልኩ ስለመከራ አይዘምርም፡፡
ቴዲ የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብን ለማገልገል የተፈጠረ ድምጻዊ ከያኒ አይደለም፡፡ ስለመከራ እና ስቃይም አይዘምርም፡ መዘመርም አይችልም።
ቴዲ መቸውንም ጊዜ ቢሆን ለወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ ባዶ ፕሮፓጋንዳ ማድመቂያ የሆኑትን የጥላቻ፣ የበቀል፣ ኢፍትሀዊ እና ጥልቅ ጥላቻዎችን የሚያነግሱ ሙዚቃዎችን በምንም ዓይነት መልኩ አያቀነቅንም፡፡
እርሱ የሚያቀነቅናቸው ስለደስታ፣ ስለሰላም፣ ስለአንድነት፣ ስለሀገር እና አህጉራዊ ፍቅር፣ ስለኢትዮጵያዊነት፣ ስለአፍሪካዊነት እና በአጠቃላይ ስለሰው ልጆች ፍቅር ነው፡፡ እንደ ሙዚቀኛ ሊዘምር የሚፈልገው እና በተግባር እያሳየ ያለው ስለዚያ ብቻ ነው፡፡ ስለፍቅር ብቻ ነው፡፡
ጥቂት ሰዎች ጥላቻን ለማራገብ የተፈጠሩ ናቸው፣ ሌሎቹ ደግሞ የዕድል ዕጣ ፈንታቸው ስለፍቅር መኖር ነው የሚል አባባል አለ፡፡
ቴዲ የተፈጠረው እና የዕድሉ ዕጣ ፈንታም የፍቅርን ድል አድራጊነት ወንጌል በዓለም ላይ ለሚገኙ ህዝቦች ሁሉ ለመስበክ ነው፡፡ ይኸው ነው ሌላ ተክዕኮ የለውም፡፡
ቴዲን ከሚወዳት ኢትዮጵያ ለማለያየት እና ጥሏት እንዲሰደድ ሌት ከቀን ጥረት የሚያደርጉት ለምንድን ነው?
አሁን በቅርቡ በአማርኛ ቋንቋ ተዘጋጅቶ በድረ ገጽ የግንኙነት መስመር በተለቀቀ ዘገባ መሰረት ይፋ እንደተደረገው የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ ቴዲን ከሀገር ለማስወጣት እና በግዞት ወይም ደግሞ ከዚያ በከፋ መልኩ እንዲኖር ለማድረግ የወሰነ መሆኑን በግልጽ አመላክቷል፡፡
የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ የሚወዳትን ሀገሩን ጥሎ እንዲሰደድ ለበርካታ ዓመታት በቴዲ አፍሮ ላይ የስነ ልቦና፣ የሕግ እና የኢኮኖሚ ጦርነቶችን እና ጫናዎችን ሲያካሂድበት እና ሲፈጽምበት ቆይቷል፡፡
እነዚህ የጥላቻ እና የበቀል ጎተራዎች ታዋቂውን ድምጻዊ ከያኒ አሳንሶ የማየት፣ ስብዕናውን በማንኳሰስ ዝቅ አድርጎ እንዲያስብ እና የማዋረድ ዕኩይ ድርጊቶችን ሲፈጽሙበት ቆይተዋል፡፡
እ.ኤ.አ በ2008 የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ በቴዲ አፍሮ ላይ ሰውን በመኪና ገጭቶ በማምለጥ የሚል የፈጠራ ክስ በመክሰስ በቁጥጥር ስር እንዲውል አድርገዋል፡፡
ይህንን የፍብረካ ወንጀል በመጎንጎን ለይስሙላው የዝንጀሮ/የጦጣ ፍርድ ፍቤት እንዲቀርብ በማድረግ ለ6 ዓመታት ያህል በእስር ቤት እንዲማቅቅ ውሳኔ ተላልፎበት ነበር፡፡
ሆኖም ግን ድምጻዊው በእስር ቤት ቆይታው ወቅት ባሳየው ጥሩ ስነምግባር በሚል በአመክሮ 6 ዓመታት የነበረው የእስራት ጊዜ ወደ 2 ዓመታት ዝቅ እንዲል ተደርጓል፡፡
በድምጻዊው ላይ የሀሰት ውንጀለቀ ተፈብርኮ የተቀነባበረውን የፈጠራ ክስ በማስመልከት “ጀግናው ከያኒ፡ የቴዲ አፍሮ የሙዚቃ ግጥም ስንኞች“ በሚል ርዕስ ትችት አቅርቤ የነበረ ሲሆን በዚያ ትችት ላይ ሰውን ገጭቶ በመግደል እና በማምለጥ በሚል የፈጠራ የውንጀላ ክስ ላይ የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ አቀረብኳቸው ያላቸውን ማስረጃዎች በመመርመር ከሕግ አንጻር ምንም ዓይነት ውኃ የማይቋጥር እና በተራ በቀልተኝነት ላይ የተመሰረተ እና በደፈናው ከያኒውን ለማጥቃት በማሰብ የእስራት ቅጣት የተወሰነበት መሆኑን አጋልጨ ነበር፡፡
ቴዲ እ.ኤ.አ በ2012 “ጥቁር ሰው“ የሚለውን አልበሙን በለቀቀበት ጊዜ የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ በቴዲ አፍሮ ላይ በማህበራዊ የግንኙነት ዘዴዎች አማካይነት ከፍተኛ በሆነ የማዋረድ እና ስም የማጥፋት ዕኩይ ዘመቻ ከፈተ፡፡
የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ ማንነታቸውን በደበቁ አጥቂ ተዋጊ ሰው አልባ ስም አጥፊ ተዋጊዎች በማህበራዊ ድረ ገጾች እና ሌሎች የመገናኛ ዘዴዎችን በመጠቀም ቴዲን ጥላሸት የመቀባት ዘመቻ ላይ ተጠመደ፡፡
የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስቦች በ19ኛው ክፍለ ዘመን ዳግማዊ አጼ ምኒልክ የአፍሪካዊ ክብር መገለጫ እና የነጻነት ታጋይ በማለት በሀሰት በመኮፈስ ይልቁንም ጨካኝ እና ጨፍጫፊ የነበረ ንጉስ ነው በማለት የሀሰት የውንጀላ ክስ በማሰማት ቴዲ በሙዚቃው ንጉሱን የገነነ እና ታዋቂ ለማድረግ ጥረት አድርጓል በማለት የባጥ የቆጡን ቀባጥረዋል፡፡
ይህንን የወያኔውን ክህደት እና ቅጥፈት፣ እንዲሁም ተራ ውሸት እና የደንቆሮ የበታችነት ስሜት የበቀል ቅጥፈት በቴዲ አፍሮ የሙዚቃ የግጥም ስንኞች እና ቃና ባለው ዜማው የተዜመ ብቻ ሳይሆን መላው የአፍሪካ ህዝብ እና ዓለም ያደነቀው እና የመሰከረለት ታላቅ ገድል ነው፡፡ ምኒልክን አክብሯቸው፣ አድንቋቸው ታላቁ እና እውነተኛው ሀገር እና ህዝብ አፍቃሪ ንጉሳችሁ የነበሩ እንጅ አሁን እናንተ ሌት ቀን እንደበቀቀን እንደምትለፈልፉለት ከሀዲ እና የባንዳ ዝርያ፣ ሀገር ሻጭ እና በጎሳ ከፋፋይ የሀገር እና የህዝብ ጠላት አልነበሩም፡፡
በእርግጥ ቴዲ በሙዚቃ አልበሙ ለሀገራቸው ሉዓላዊነት እና ክብር ሲሉ ሁሉም ጎሳዎች እና ቡድኖች ሲዋደቁ እና የህይወት መስዋዕትነትን ከፍለው ይህችን ሀገር ያስረከቡንን ጀግኖች እና ታዋቂ ሰዎችን አንበሳ አድርጎ በመሳሉ እና በመዘከሩ ምክንያት ይህ ለወያኔው ታላቅ ሸክም እና ጥላቻ ነው፡፡
እ.ኤ.አ ታህሳስ 2013 የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ በቴዲ ላይ የማጠልሸት፣ ጥለሸት የመቀባት፣ የማዋረድ እና ዝቅ አድርጎ የማየት ሌላ ዘመቻ ከፈተ፡፡
ቴዲ “ለእኔ የምኒልክ የአንድነት ዘመቻ ቅዱስ ጦርነት ነበር“ ብሎ ቃለ መጠይቅ ላይ ተነግሯል ብለው የሐሰት ወሬ በመንዛት የውንጀላ ውርጅብኝ ክስ በመመስረት አደንቋሪ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻቸውን ቀጠሉ፡፡
ለመሆኑ ህዝብን ሰውን ሁሉ አንድ ማድረግን እና በፍቅር እንዲተሳሰሩ ከማድረግ በላይ ምን ቅዱስነት ነገር አለ!?
በጎሳ መለያየት፣ እርስ በእርስ ማባላት፣ በህዝብ መካከል የጥላቻ መርዝ መዝራት፣ ጎጠኝነትን ማስፋፋት፣ የኃይማኖት ጽንፈኝነትን በማራገብ ልዩነትን መፍጠር፣ ህዝብን በረሀብ እና በችጋር እየለበለቡ ኢኮኖሚው በሁለት አሀዝ አድጓል፣ ተመንድጓል እያሉ መቀባጠር፣ ትውልድ ገዳይ የትምህርት ፖሊሲ ነድፎ ለምንም ለማንም የማይጠቅም ትውልድን እየፈጠሩ የጫት እና የሌሎች አደንዛዥ ዕጽ ሰለባ እያደረጉ ብሎኬቶች በመቆለል ብቻ እድገት እና ልማት ይመጣ ይመስል ህዝብ ግብር እየከፈለ በሚያስተዳድራቸው በብዙሀን መገናኛ ዘዴዎች ሌት ቀን ፕሮፓጋንዳ መስራት????
ለእናንተ ዕድገት ማለት ይኸ ነው፡፡
በህዝባቸው ዘንድ እምዬ ምኒልክ የሚል ተቀጽላ ስም የተሰጣቸው እናንተ በፈጠራ ውሸት ተክናችሁ ሁሌ እውነትን ሀሰት፣ ሀሰትን እውነት፣ ቀዩን ጥቁር፣ ጥቁሩን ነጭ እያላችሁ እንደምታቀርቡት የበሬ ወለደ ዓይነት አስተሳሰብ ላይ ተመስርቶ የተሰጠ ስያሜ ሳይሆን በእርግጥም ምኒልክ ለአንድ ጎሳ፣ ቡድን፣ ብሄረሰብ፣ ዘር፣ ኃይማኖት፣ ማንነት ሳይሆን ለሁሉም ኢትዮጵያዊ ወገኖቻቸው ሁሉ የእናትነትን ባህሪ የተላበሱ፣ እንደ እናት ፍቅርን የሚለግሱ እውነተኛ አፍሪካዊ መሪ በመሆናቸው ብቻ ነው፡፡
ይህ ታሪካው እውነት የማይካድ ነው።
ከዚህ አንጻር በቴዲ አፍሮ “ቅዱስ ጦርነት” ብሏል የተባልዌ ሐሰት ኢትዮጵያን አንድ ለማድረግ የተደረገውን ተጋድሎ የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ ጠምዝዞ እና በሚያውቅበት ሸፍጥ የመስራት ተንኮሉ በማጣመም “ዘር ማጥፋት” ብሎ ፈረጀው፡፡
የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ በቴዲ አፍሮ ላይ የከፈተው ዋና ስም የማጠልሸት ተልዕኮ ማጠንጠኛው የዳግማዊ ምኒልክን ስም የማጠልሸት ዘመቻ ነው፡፡
በእርግጥ  ያ ሁሉ ድንፋታ በመንግስትነት ደረጃ ስልጣንን ተቆጣጥሪያለሁ ከሚል ድርጅት የማይጠበቅ የወረደ እና ተራ ወሮበልነት ነው፡፡ የሀገሩ መሪ በህዝቡ፣ በአህጉር እና በዓለም አቀፋዊ መድረኮች ሁሉ ስለደግነቱ እና ስለጀግንነቱ ሲወደስ ደስ ሊለው እና ሊኮራ ይገባዋል እንጂ መሰሪ ቀናተኛ ጠላት ሆኖ መቅረብ ከአስተሳሰብ ዝቅጠት የመነጨ ነው ከማለት ሌላ ምን ሊባል ይችላል!
ይልቁንም የወያኔው ድብቁ እና እውነተኛው አጀንዳ አሁን በህይወት የሌለውን እና በጨፍጫፊነቱ እና በአምባገነንነቱ እውቅና ያለውን እ.ኤ.አ በ2005 የተካሄደውን ሀገር አቀፍ ምርጫ ተከትሎ ተከስቶ በነበረው ውዝግብ በእራሱ ትዕዛዝ በመቶዎች የሚቆጠሩ ንጹሀን ሰላማዊ ዜጎች ምርጫው መጭበርበሩን በማስመልከት ተቃውሟቸውን ሰላማዊ በሆነ መልኩ የገለጹትን ወገኖቻችንን በአደባባይ እንዲጨፈጨፉ ያደረገውን የመለስ ዜናዊን የዘር ማጥፋት ወንጀል ለመሸፋፈን እና ለመደበቅ ሲባል የሚደረግ ሸፍጥ ነው፡፡
ይህ ብቻ አይደለም ከዚያ ቀደም ሲልም ሆነ ከዚያ ወዲህ በበደኖ፣ በአሰበ ተፈሪ፣ በጎንደር በእየሱስ ቤተክርስቲያን ቅጥር ግቢ፣ በአርሲ፣ በጋምቤላ፣ በኦጋዴን እና በሌሎች በተለያዩ ቦታዎች እና አካባቢዎች ዘርን መሰረት ያደረገ የዘር ማጥፋት ፍጅት መፈጸሙን ልብ ይሏል! የአቦን ቅጠል የቀመሰች ፍየል ያስለፈልፋታል ይባል የለ! ነገሩ እንደዚያ ነው፡፡
የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ በፈጠረው ውዝግብ ምክንያት ቴዲ አፍሮ በአሁኑ ጊዜ የደች/ሆላንድ ንብረት በሆነው በሄይከን ኩባንያ እየተዳደረ ከሚገኘው ከበደሌ ቢራ ፋብሪካ ጋር ስምምነት በማድረግ ሊያቀርብ የነበረውን ኮንሰርት እንዲሰረዝ ተደርጓል፡፡
እ.ኤ.አ በ2014 የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ ”ግብር ማጭበርበር” የሚል ሌላ የፍብረካ ውንጀላ በማቀነባበር ቴዲ አፍሮን እንደገና በእስር ቤት ለማማቀቅ ሙከራ አደረገ፡፡ የውንጀላ ክሱ የቀረበው ከ7 ወይም ደግሞ ከ8 ዓመታት በፊት ከውጭ ወደ ሀገር ውስጥ ላስገባው ተሽከርካሪ ግብር አልከፈለም የሚል ነበር፡፡
ሊገመት ከሚችለው በላይ ድፍረትን በተላበሰ መልኩ ፍርድ ቤቱ የግብር ማጭበርበሩን ጉዳይ ለማጣራት ተጨማሪ ቀናትን ለፖሊስ ለመስጠት እና ቴዲ አፍሮም በእስር ቤት ይቆያል የሚለው አስፈላጊ አይደለም ይህንንም አልቀበልም አለ፡፡ (ደፋር ዳኛው ከወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ ፊት ለፊት በመቆም! አይታመንም!!)
እ.ኤ.አ በ2015 የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ ጆሮ ጠቢዎች ቴዲ በሚሄድበት ቦታ ሁሉ እንደጥላ ይከታተሉት ጀመር፡፡
ቴዲ እናቱን ለመጎብኘት በሚሄድበት ጊዜ አነፍናፊ አዳኝ ውሾችን ያስከተሉ ጆሮ ጠቢ ወሮበሎች ተከትለውት ሄዱ፡፡
ወደ ከተማ በሚሄድበት ጊዜ ሞተር ብስክሌት በሚይዙ ወሮበሎች አማካይነት መሰናክል እንዲፈጠርበት ይደረጋል፡፡
የሲቪል ልብስ የለበሱ ወሮበሎች አንገቱን እንቅ አድርገው ይይዙታል፡፡ በመንገድ ላይ በመጓዝ ላይ እያለ ድንገት ያስቆሙት እና ያስፈራሩታል፡፡
የስልክ መስመሮቹ ይጠለፋሉ፡፡
ቤቱ ቀጣይነት ባለው ሁኔታ በፖሊስ ምርመራ ስር ነው፡፡
በየጊዜው በወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ የይስሙላ የዝንጀሮ ፍርድ ቤቶቸ እየቀረበ የማስፈራሪያ ድርጊት ይፈጸምበታል፡፡
የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ በኤፍ ኤም የሬዲዮ ጣቢያው በመጠቀም ቴዲን በገንዘብ ኪሳራ ውስጥ እንዲወድቅ እና የገነባውን ታላቅ ስሙን ለማጥፋት ሌት ቀን የፕሮፓጋንዳ ስራውን ይቀጥላል፡፡ ስሙን በማብጠልጠል ላይ ይገኛሉ፡፡ ያለምንም የሕግ ተጠያቂነት እያወገዙት እና ስም የማጥፋት ዘመቻቸውን ቀጥለውበት ይገኛሉ፡፡
በሀገር ውስጥም ሆነ ወደ ውጭ ሀገር በመሄድ ህይወቱን መምራት እንደማይችል ከፍተኛ የሆነ ችግር እየፈጠሩ ከህዝብ ለመለየት ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛሉ፡፡
አሁን በቅርቡ የቴዲ አፍሮ ባለቤት ለህክምና ጉዳይ ወደ ኬንያ ሄዳ በነበረችበት ጊዜ የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ አውሮፕላኑን በማስቆም ቴዲን ምንም ዓይነት ክፍያ ሳይከፍል ተደብቆ ለመሄድ ሲሞክር እንደተያዘ ሕገ ወጥ ሰው እየገፉ እና እየጎተቱ በአደባባይ ሲያንገላቱት በህዝብ ተስተውሏል፡፡
እንደዚሁም በሌላ ጊዜ የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ  ቴዲን በማዋረድ እና የሞራል ስብዕናውን ዝቅ በማድረግ እነርሱ የእርሱ ጌቶች እንደሆኑ የማሳየት ስራ ሰርተዋል፡፡
ቴዲ ያለው ትልቁ ጌታው ወያኔ ሳይሆን ታላቁ የፍቅር ኃይል ነው!
የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ ተከታታይነት ባለው ሁኔታ ቴዲ አፍሮን ያስፈራሩታል ምክንያቱም ቴዲ የእነርሱን ሙዚቃ አይዘምርም፣ የእነርሱን ዳንስ አይደንስም፣ እንደዚሁም የእነርሱን የጥላቻ ከበሮ አይደልቅም፡፡
ለዚህም ነው እትብቱ ከተቀበረችባት እና ከሚወዳት ሀገሩ እንዲሰደድ ጥረት በማድረግ ላይ ያሉት፡፡
ሆኖም ግን ቴዲ እስከ አሁን ድረስ በሚወዳት ሀገሩ ቆይቷል፡፡ የእራሱን ሀገር ትቶ በማንም ወሮበላ አስገዳጅነት የትም ቦታ ቢሆን አይሄድም፡፡
በውጭ ሀገር ተሰድዶ ነጻ ሆኖ ከመኖር ይልቅ በሀገሩ ውስጥ ሆኖ እጆቹ በካቴና ታስረው በግፈኛ አምባገነኖች እየተሰቃዬ እና ሰብአዊ መብቱ እየተደፈጠጠ መኖርን ይመርጣል፡፡
የእውነተኛ አርበኝነት ባህሪ እንደዚህ ነው!
ጥላቻ የበለጠ እየከረረ እና እየመረረ በሄደ መጠን ጥቂቶች ሀገር ለቀው ይሰደዳሉ፣ ሌሎች ጥቂቶች ደግሞ መከራውን እና ስቃዩንም አሳቱንም ችለው በሀገራቸው ይቆያሉ ይባላሉ፡፡
ቴዲ ግን የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብን እሳት ፊት ለፊት ተቋቁሞ በሀገሩ በመኖር ላይ ይገኛል፡፡
ቴዲ የኢትዮጵያ ነገስታት የነበሩትን ዳግማዊ ምኒልክን እና ቀዳማዊ አጼ ኃይለ ስላሴን በማወደሱ እና ጀግንነታቸውን በመመስከሩ ብቻ የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ ከልቡ ምርር አድርጎ ጠልቶታል፡፡
የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ አመራሮች እና አባላት “የኢትዮጵያን ታሪክ ጥላሸት መቀባት“ በሚል ርዕስ አዘጋጅቸው በነበረው ትችቴ ላይ ከዳግማዊ አጼ ምኒልክ እና ከቀዳማዊ አጼ ኃይለስላሴ ይልቅ አሁን በህይወት የሌለው አምባገነኑ መለስ ዜናዊ የፈጸማቸው ትግባራት የበለጡ ናቸው የሚለውን ቅጥፈታቸውን ለማጋለጥ ሞክሪያለሁ፡፡
ቴዲ አሁን በህይወት ለሌለው ለአምባገነኑ መለስ ዜናዊ እና ለእርሱ ታዛዥ ሎሌዎቹ የሚዘምር ቢሆን ኖሮ የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ በዚህ ከያኒ ላይ እንደዚህ ያለ ማቋረጫ የሌለው ጦርነት እና የማሰቃዬት እኩይ ድርጊት ሊፈጽሙበት ይችሉ ነበርን?
ቴዲ በእውነታው ዓለም ላይ ያሉትን ጅቦች አንበሳ አድርጎ ቢያቀርባቸው ኖሮ ጆቦቹ ለምን እንደ አንበሳ ተደርገን ተፈረጅን ብለው ቅሬታዎቻቸውን ያቀርቡ ነበርን?
አሁን በህይወት ስሌለው አምባገነኑ መለስ ዜናዊ የሌለውን ስብዕና እንዳለው በማስመሰል “የአፍሪካ አባት” የሚል የሙገሳ መዝሙር ቢያሰማ ኖሮ በቴዲ ላይ እንደዚያ ያለ ጥላሸት የመቀባት እና የማዋረድ ድርጊት ይፈጸምበት ነበርን?
ቴዲን መዘለፍ አልፈልግም ሆኖም ግን የመለስ ዜናዊ ምስል ያለበትን ቲ ሸርት (ካናቴራ) በመልበስ በኮንሰርቱ ላይ ቢታደም ኖሮ በወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ የማስፈራራት ድርጊት ይፈጸምበት ነበርን?
በቴዲ ላይ ማቋረጫ የሌለው ስቅይት እና ማስፈራራት ቢፈጸምበትም ቅሉ ምንም ዓይነት ቅሬታ አላሰማም፡፡ ሌላ ምንም ነገር ትንፍሽ አላለም፣ እንዲህ ነበር ያለው፣ “ፍቅር ሁሉንም ነገር ያሸንፋል፡፡“
የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ ለ25 ዓመታት ያህል በስልጣን ኮርቻ ላይ ተፈናጥጦ “ጥላቻ ሁሉንም ነገር ያሸንፋል“ በማለት የእራሱን ደስታ በመግለጽ ላይ ይገኛል፡፡
ጥላቻ ለተወሰነ ጊዜም ቢሆን አሸናፊ ሆኖ ሊታይ ይችላል፡፡
የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ የሚወዱት ብቸኛው ነገር ቢኖር ጥላቻን እራሱን ነው፡፡
ሆኖም ግን ቴዲ የማይበገር ጀግና ነው፡፡ እንዲህ እንደሚሉትን የዶ/ር ማርቲን ሉተር መርሆዎች እያስተጋባ የሚኖር ይመስላል፣ “ጥላቻን ጥላቻ አያስወግደውም፣ ይህንን ማድረግ የሚችለው ፍቅር ብቻ ነው፡፡“ በሌላ አባባል “ፍቅር ሁሉን ነገር ያሸንፋል፡፡”
የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ ቴዲ አፍሮን የሚፈራው ለምንድን ነውቴዲን እንደዚህ ጥቁር ጥምድአድርገው የሚጠሉት ለምንድን ነው!?
እስቲ ስለቴዲ የማያወዛግቡ ጥሬ ሀቆችን ይፋ እናድርግ፡
እንደ ድምጻዊ አቀንቃኝ ቴዲ አፍሮ አቻ የማይገኝለት ድምጻዊ ነው! ምንም ዓይነት ተወዳዳሪ የለውም!
ቴዲ እንዲህ የሚሉትን ባህሪት የተላበሰ ምጡቅ ድምጻዊ ነው፡  በስብዕናው አንድ ዓይነት ወጥ ነው፣ የግጥም ስንኞቹ ምትሀታዊ ኃይልን የተላበሱ ናቸው፣ የዜማ ቅላጼዎቹ ማራኪ፣ መንፈስን በደስታ ስሜት ውስጥ የማስጋለብ እና የሰውን ቀልብ የመቆጣጠር ኃይል ያላቸው ናቸው፣
ቴዲ አፍሮ ልዩ ተሰጥኦ ያለው የሙዚቃ ሰው ነው! ምንም ዓይነት ጥያቄዎች ሊነሱበት የሚገባ ጉዳይ አይደለም! ምንም ዓይነት!
እንደዚሁም ሁሉ ቴዲ አፍሮ ነገሮችን በጥልቀት የማየት ችሎታ ያለው የጥልቅ ሀሳብ ባለቤት ሰው ነው፣ ለሁሉም ነገር ጥንቃቄን የሚያደርግ፣ በፍቅር የተሞላ እና ብሩህ አዕምሮ ያለው ሰብአዊ ፍጡር ነው፡፡
በሚያቀርባቸው በሁሉም ሙዚቃዎቹ ስለህይወት ፍልስፍናው ያስተምረናል፡፡ ይህ ፍልስፍናው በሶስት ቃላት እንደሚከተለው ተጠቃሎ ሊቀርብ ይችላል፡ “ፍቅር ሁሉንም ያሸንፋል”፣ ይኸው ነው! ሌላ ምንም ነገር የለም!
ቴዲ ስለይቅርታ ማድረግ እና ዕርቀ ሰላም ስለማውረድ ይዘምራል፡፡
ስለሀገሩ እና አህጉሩ ፍቅር ይዘምራል፡፡
ስለብሄሮች እና ስለኃይማኖቶች ተቻችሎ መኖር ይዘምራል፡፡
ስለኢትዮጵያ ዝና አጥብቆ ይዘምራል፡፡
ኢትዮጵያ ነጻነቷን እንድትቀዳጅ፣ ከቅኝ ገዥነት ነጻ እንድትወጣ፣ ከውጭ የበላይነት ነጻ እንድትሆን ሉዓላዊነቷን አስጠብቃ እንድትኖር መተኪያ የሌላት ህይወታቸውን ገብረው ላቁዩአት ጀገኖች ልጆቿ ይዘምራል፣ ያቀነቅናል፡፡
የነጻነት መዝሙሮችን ይዘምራል፡፡
ቴዲ እንደ ቦብ ማርሌይ ሁሉ እንዲህ የሚሉ የሙገሳ ሙዚቃዎችን ይዘምራል፡
እነዚህን የትንሣኤ ሙዚቃዎች ለመዘመር እገዛ አታደርጉምን/እነዚህን የነጻነት ሙዚቃዎች?/እስከ አሁን ያሉኝን ሁሉ ዘምሩ፡/የትንሣኤ ሙዚቃዎች/እስከ አሁን ያሉኝን በሙሉ፡/የትንሣኤ ሙዚቃዎች፡/እነዚህን የነጻነት ሙዚቃዎች፡፡/የነጻነት ሙዚቃዎች አብራችሁኝ አትዘምሩም።
ሁሉም የትንሣኤሙገሳ ሙዚቃዎች የቴዲ አፍሮም ናቸው፡፡
ቴዲ እንዲህ በማለት ይጠራዋል፣ “የኢትዮጵያ ትንሳኤ” (የኢትዮጵያ የሙገሳ/ትነሳኤ)፡፡
የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ በአሁኑ ጊዜ ቴዲ አፍሮን ማቋረጫ በሌለው መንገድ ለምን እያሰቃዬው እንዳለ ምንም ሀሳብ የሌኝም ፈፅሞ  አይገባኝም፡፡
ቴዲ እውነታውን በመዘመሩ ምክንያት ሊሆን ይችላልን?
እውነትን በሚጠሏት መካከል ጠላቶችን እንዴት እንደሚያፈራ ልገንዘብ እችላለሁ፡፡
ቴዲ ስለፍቅር በመዘመሩ ምክንያት ሊሆን ይችላልን?
ጥላቻ በደም ስሮቻቸው በተዋሀዱት መካከል የማይሞቱ ጠላቶች እንደሚያፈራ እገነዘባለሁ፡፡
ቴዲ ስለይቅርታ አድራጊነት በመዘመሩ ምክንያት ሊሆን ይችላልን?
በበቀል እና በጥላቻ በተዘፈቁት መካከል ጠላቶችን እንዴት እንደሚያፈራ ልገነዘብ እችላለሁ፡፡
ቴዲ ስለዕርቀ  ሰላም በመዘመሩ ምክንያት ሊሆን ይችላልን?
የህይወት ተልዕኳቸው ከፋፍሎ መግዛት በሚሉት መካከል ጠላቶች እንዴት እንደሚያፈራ ልገነዘብ እችላለሁ፡፡
ቴዲ ስለ ኢትዮጵያ ትንሳኤ በመዘመሩ ምክንያት ሊሆን ይችላልን?
በኢትዮጵያ ገዳዮች መካከል ጠላቶች እንዴት እንደሚያፈራ ልገነዘብ እችላለሁ፡፡
ቴዲ ስለኢትዮጵያ አንድነት በመዘመሩ ምክንያት ሊሆን ይችላልን?
ኢትዮጵያን በመክተፊያ ቢላዋ በመተሯት እና እንዴት የጎሳ፣ የብሄረሰብ ቡድኖች፣ የኃይማኖት እና የክልል ጎጠኛ ደሴት ባደረጓት መካከል ጠላቶች እንዴት እንደሚያፈራ ልገነዘብ እችላለሁ፡፡
ቴዲ ስለለሁሉም ኢትዮጵያውያን የወደፊት የተሻለ ህይወት በመዘመሩ ምክንያት  ሊሆን ይችላልን?
በዕኩይ ምግባራቸው ምክንያት ዕጣ ፈንታቸው ወደ ታሪክ ቆሻሻ ማጠራቀሚያ መጣል ባለባቸው መካከል ጠላቶች እንዴት እንደሚያፈራ ልገነዘብ እችላለሁ፡፡
ቴዲ ስለኢትዮጵያ ጥንታዊ ዝና በመዘመሩ ምክንያት ሊሆን ይችላልን?
በጥላቻ በተሞሉ ሰይጣኖች፣ በቀልተኞች፣ እምነተቢስ መርህ አልባ ፍጡሮች እና በጫካ ወሮበሎች መካከል ጠላቶች እንዴት እንደሚያፈራ ልገነዘብ እችላለሁ፡፡
ቴዲ ስለኢትዮጵያ ተፈጥሯዊ ውበት እና ስለህዝቧ በመዘመሩ ምክንያት ሊሆን ይችላልን?
በሀሳብ የለሽ ጋጠወጦች እና በጭካኔ በተሞሉት ድድብና በተጠናወታቸው ወሮበሎች መካከል ጠላት እንዴት እንደሚያፈራ ልገነዘብ እችላለሁ፡፡
ሆኖም ግን ቴዲን ለመጥላት ወይም ደግሞ ለመፍራት ጥሩ ምክንያቶች አይደሉም፡፡
ሙሉ ህይወቱ ስለፍቅር፣ መልካም ጉርብትና፣ ስለሀገር ፍቅር እና ክብር፣ ስለአህጉር ፍቅር፣ ስለታሪክ ፍቅር እና ክብር፣ ስለሀገሩ ብዝሀነት እና ስለህዝብ ፍቅር እና ክብር መርሁ እና ተሞክሮው አድርጎ የሚንቀሳቀስን ሰው እንዴት መጥላት ይቻላል?
የሰው ልጆች ፍቅር የሆነ ሐዋርያትን እንዴት መጥላት ይቻላል?
ፍቅርን እራሱን የሚጠሉትን ምንነት የሚገልጽ እራሱን የቻለ ቃል/ሀረግ አለ፡፡ ይህም ቃል/ሀረግ “በሰዎች መጥፎ ዕድል ላይ የሚረካ“ እየተባለ የሚጠራ ሲሆን ቃሉም የተገኘው ከጀርመን ሆኖ አንድ ሰው በተፈጥሮው በሰዎች መጥፎ ዕድል፣ ስቃይ እና መከራ እጅግ የበዛን ደስታ የሚያደርግ እኩይ ሰይጣናዊ አስተሳሰብ ያለው የሚል የእንግሊዝኛ ትርጉም ያለው ሆኖ ይገኛል፡፡ በጥላቻ የተሞሉ ሰው መሳይ ሰይጣኖች ብቻ በሌሎች መከራ፣ ስቃይ እና ውርደት ሀሴትን ይጎናጸፋሉ፡፡
በሰዎች መጥፎ ዕድል ላይ የሚረካ ግብዝ ሸፍጠኛ/sadist በሌሎች ሰዎች ላይ በሚደርሰው ስቃይ፣ መከራ እና መጥፎ ዕድል እጅግ በጣም ደስተኛ እና ሀሴትን የሚያደርጉ፣ ለዚህ እኩይ ምግባርም ለእራሳቸው አዎንታዊ ምላሽ የሚሰጡ ሰው መሳይ በሸንጎዎች የሆኑ ሰይጣኖች ናቸው፡፡
በእንደዚህ ያለ በሰዎች ስቃይ እና መከራ ከፍተኛ የሆነ ሀሴት ባህሪያትን በተጎናጸፉ ሰዎች ሰይጣናዊ አስተሳሰብ ውስጥ ስቃይ፣ ሀዘን፣ እና የሌሎች ሰዎች መጥፎ ዕድል ማግኘት ማለት ለእነርሱ ደስታ፣ የሌሎች ስቃይ የእነርሱ ሀሴት፣ የሌሎች መከራን መቀበል ለእነርሱ ፍጹም የሆነ እርካታ ማለት ነው፡፡
በሌላ አባባል ከጥላቻ የመጨረሻ የሆነውን ደስታ ያገኛሉ፡፡ ይኸ ልዩ የሆነ ሰይጣናዊ ድርጊት ዋነኛ የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ አመራር እና አባላት መገለጫ ባህሪ ነው!
ለፍቅር ፍቅር ያላቸውን እና ፍቅርን እራሱን የሚጠሉ የፍቅር ጠላቶች ናቸው፡፡
ከተቃዋሚዎች ጋር ህብረት ፈጥሯል በሚል እሳቤ ነውን?
የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ ቴዲ አፍሮ ተቃዋሚዎችን ይደግፋል የሚል ውንጀላ ያሰማል፡፡ ይህ እራሱ ምን ማለት ነው?
በእርግጥ እነዚህ የጥላቻ ዕኩይ ምግባር አራጋቢዎች ቴዲ አፍሮን ፖለቲከኛ እንጅ ሙዘቀኛ አይደለም የሚል ሀሳብ ለማራመድ ይሞክራሉ፡፡
ቴዲ ፖለቲከኛ የሚሆንባት ዕለት የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ ከሸፍጥ ነጻ የሆነ (ለዝንጀሮው/ጦጣ ፓርላማው ከ547 መቀመጫዎች ውስጥ 547ቱንም አሸንፊያለሁ ብሎ የሚያውጅ ሳይሆን) እውነተኛ ዴሞክራሲ እና የሰብአዊ መብት ጥበቃን እውን በሚያደርግባት ዕለት ነው፡፡
ያም የማይሆን ነገር ነው፡፡
የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ ተቃዋሚ ቡድኖችን ማገዝ ወንጀል ነው በማለት በዝንጀሮው/ጦጣው የይስሙላ ፍርድ ቤት ክስ መስርቶ ንጹሀን ዜጎችን ያሰቃያል!
አንድ ሰው የፈለገውን የፖለቲካ ፓርቲ ለመደገፍ ሕገ መንግስታዊ እና የሰብአዊ መብት ምርጫው አይደለምን?
ሆኖም ግን ቴዲ የፖለቲካ ሰው አይደለም፡፡ እርሱ የሙዚቃ ሰው ነው፡፡
በተጻራሪ መልክ አስገራሚው ነገር ደግሞ የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ ቴዲ ገንዘብ በመስጠት፣ በሙዚቃ ኮንሰርት በማዘጋጀት እንዲያቀነቅንላቸው፣ እነርሱ እንዲዘምርላቸው የሚፈልጉትን ሙዚቃ በመስጠት በአደባባይ እንዲዘምርላቸው እና በፖለቲካ እንዲደግፋቸው ይፈልጋሉ፡፡
የቴዲ አጭር መልስ ግን አመሰግናለሁ ሆኖም ግን ይቅርታ አላደርግም የሚል ነው፡፡
እውነታው ፍርጥርጥ ተደርጎ ሲታይ ግን የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ ቴዲ እንዲያደርግለት የሚፈልጋቸውን ነገሮች ሁሉ ለሌሎች የፖለቲካ ድርጅቶችም በተመሳሳይ መልኩ አንድም ነገር አላደረገም፡፡ ለምንድነው ለወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ እንዲህ ዓይነቱን ድርጊት የሚጀምረው?
የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ አለቆች ከተራ ሀሳብ ይልቅ የበለጠ ገንዘብ አላቸው፡፡
እንዲህ የሚለውን አባባል መዳመጥ እና መተግበር ይኖርባቸዋል፣ “ገንዘብ ፍቅር ሊገዛልኝ አይችልም፡፡“
“ገንዘብ ፍቅር ሊገዛልኝ አይችልም/ፍቅርን ሊገዛልኝ አይችልም፣ እያንዳንዱ ሰው ይህንን ነገር ይነግረኛል/ፍቅርን ሊገዛልኝ አይችልም፣ በፍጹም፣ በፍጹም፣ በፍጹም፣ በፍጹም…“
የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ በማንኛውም መንገድ የኢትዮጵያን ህዝብ ፍቅር ወይም ደግሞ የፈለገውን ያህል ገንዘብ እንደጎርፍ ቢያወርድ የኢትዮጵያን ህዝብ ድምጽ ፍቅር ቴድን በምንም ዓይነት መልኩ አያገኝም! ሊገዛ አይችልም።
እኔ የቴዲ አፍሮ ቁጥረ 1 አድናቂ ነኝ!
ለበርካታ ዓመታት የቴዲ አፍሮ ቁጥር 1 አድናቂ ነኝ፡፡
በእርሱ ሙዚቃ ስዘምር እና ስደንስ ቆይቻለሁ፡፡ የሮጌን የሙዚቃ ምቶች እንዴት አድርጎ ወደ ኢትዮጵያ ባህላዊ የሙዚቃ ቅላጼ እንደሚቀይራቸው አደንቃለሁ፡፡
በአንድ በተወሰነ ቦታ ወይም አካባቢ የሙዚቃ ኮንሰርት በሚያዘጋጅበት ጊዜ ከሁሉም ወጣቶች ህዝቦች ጋር በመቀላቀል መልካም ጊዜን አሳልፋለሁ፡፡
በተለያዩ አጋጣሚዎች ስለቴዲ አፍሮ ጽፊያለሁ፡፡
እ.ኤ.አ በ2010 በሁሚንግ ፖስት ትችት ቴዲ በአካል በሚተላለፍ ትዕይንት ባቀረበው ስራው ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ በመገኘት ከተመለከትኩ በኋላ እንዲህ የሚል ጽሁፍ አቅርቤ ነበር፡
ቴዲን በአካል በሚተላለፍ ስራው ላይ በመገኘት ያቀረበውን ኮንሰርት ከዚያ በፊት ያልተመለከትን እና በአዳራሹ ከአፍ እስከ ገደቡ ጢም ብሎ ሞልቶ የነበረውን የተመልካች ብዛት በማየት ምስክርነቱን ለምንሰጥ ሰዎች ሁሉ በሀሳብ አውሮፕላን ወደ ኋላ ጭው ብሎ በመብረር በትዝታ ማዕበል ውስጥ እንድንዋኝ ያደርገናል፡፡ እንደዚህ ያለ በህዝቡ እና በከያኒው መካከል ጥልቅ የሆነ ትስስር በህይወቴ የተመለከትኩት ከብዙ አስርት ዓመታት በፊት እ.ኤ.አ ግንቦት 30/1978 በሜኖሶታ ዩኒቨርስቲ እየተማርኩ በነበርኩበት ቦታ ቦብ ማርሌይ በመምጣት አቅርቦት በነበረው (ካያ ቱር/Kaya Tour) እና እ.ኤ.አ ህዳር 15/1979 (ሰርቫይቫል ቱር/Survival Tour) የተሰኙትን ኮንሰርቶች ያቀረበባቸው ጊዚያት ትዝ አሉኝ፡፡ በእነዚያ ቦብ ማርሌይ ባቀረባቸው ኮንሰርቶች ላይ የመገኘት አጋጣሚ ዕድሉን ያገኛችሁ በእርግጠኝነት ምን ለማለት እንደፈለግሁ በትክክል ትገነዘባላችሁ የሚል እምነት አለኝ፡፡
እ.ኤ.አ ሰኔ 2014 ኮካኮላ የተባለው ድርጅት ቴዲ አፍሮን የማግለል ድርጊት ፈጽሞ ስለነበር ማንም ቢሆን ይህን ለውፍረት የሚዳርገውን እና በስኳር የተሞላውን ኮካኮላ የሚባለውን እርባናየለሽ መጠጥ ባለበት ድርሽ እንዳትሉ የሚል ትችት አቅርቤ ነበር፡፡
ኮካኮላ የተባለው ድርጅት ለ2014 በብራዚል ተደርጎ በነበረው የዓለም እግር ኳስ ጨዋታ ሻምፒዮን 32 የአካባቢ ድምጻውያን ስራዎቻቸውን እንዲያቀርቡ እና እንዲወዳደሩ ጋብዞ ነበር፡፡
ኮካኮላ ይፋ በሆነ መልኩ ከቴዲ አፍሮ በስተቀር የሁሉንም ተወዳዳሪዎች ስራዎች ለቅቆ ነበር፡፡ በእርግጥ ኮካኮላ በወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ አለቆች ትዕዛዝ መሰረት የቴዲ አፍሮን ስራ ውድቅ እንዲያደርግ ትዕዛዝ ተሰጥቶት ነበር፡፡
ይህ ድርጊት ሁይትነይ እንደዘመረው ሁሉ ትክክል አይደለም ሆኖም ግን እሽ ከሚለው ጋር ተመሳሳይ እንደምታ አለው፡፡
(በዚያ እኩይ ድርጊቱ እስከ አሁንም ድረስ የኮካኮላ ምርት ውጤት የሆኑት ባሉበት ቦታ ድርሽ አልልም! ከዚህ አንጻር የኮካኮላ ምርትን ከምጠቀም ይልቅ የምጠጣው አጥቼ በውኃ ጥም ድርቅ ማለትን እመርጣለሁ፡፡ ይህ ለእኔ ሌላ ለምንም ነገር ሳይሆን ቀላል የመርህ ጉዳይ ነው፡፡ እንደዚህ ያለ ምርመራን እና አድልኦን የሚፈጽም ዓለም አቀፋዊ የንግድ ድርጅትን ልደግፍ የምችልበት ሞራሉ የለኝም፡፡ በዚያን ጊዜ ባቀረብኩት ትችቴ ላይ “ኮካኮላ ገሀነም ይግባ” በማለት ተናግሬ ነበር፡፡ በአሁኑ ጊዜ ኮካ ኮላ ገሀነም እንደደረሰ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡)
ቴዲ በእንግሊዝኛ ቋንቋ ብዙም የሙዚቃ ኮንሰርት አያቀርብም፣ ሆኖም ግን በዓለም እንደ የአፍሪካ የሬጌው ንጉስ እየተባለ ሲወደስ እንደነበረው እንደ ቦምብ ማርሌይ በፍቅር መንፈስ የህዝብን ልብ ያስተሳሰረ ከያኒ መሆኑ ይነገርለታል፡፡ እንግዲህ ቴዲ አፍሮ በሙዚቃ ጥበቡ፣ በፍቅር ዘማሪነቱ እና በአጠቃላይ የዘርፉ ልቅናው የዚህን ያህል ክብር እና ሞገስ ያለው ከያኒ ነው፡፡
(“ሬጌ” የሚለው ቃል ከላቲን “ሬጊ” ከሚለው እና ንጉስ የሚል ትርጉም ካለው ቃል የመጣ ስለመሆኑ ስንቶቻችን እንደምናውቅ ብገነዘብ የሚገርመኝ ይሆናል፡፡ የሬጌ ሙዚቃ “የንጉስ ሙዚቃ” ነው፡፡)
እራሱን ህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ እያለ የሚጠራው ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ ደናቁርት ቴዲ የንጉሱን ሙዚቃ በማቀንቀኑ እና በሙዚቃ ሰራ ቅላጼዎቹ የዳግማዊ አጼ ምኒልክን እና የቀዳማዊ አጼ ኃይለ ስላሴን ስም እያነሳ በማወደሱ ምክንያት ወንጀል ተደርጎ በይስሙላው የዝንጀሮ/ጦጣው ፍርድ ቤት አንዳያንገላታው ተስፋ አረጋለሁ፡፡ (ሬጌ ሙዚቃ “የንጉስ ሙዚቃ” ነው ለጃማይካ ራስ ተፈሪያውያን፡፡)
እኔ ቴዲ አፍሮን የማውቀው በሰራቸው ቪዲዮ፣ በሚያዘጋጃቸው የሙዚቃ ኮንሰርቶች፣ በድረ ገጽ የግንኙነት መስመር በሚሰጣቸው ቃለ መጠይቆች እና ከሁሉም በላይ ደግሞ በሚያስተላልፋቸው የፍቅር፣ የመግባባት፣ የይቅርታ አድራጊነት እና ዕርቀ ሰላም ናፋቂነት ነው፡፡
ለዚህም ነው አንግዲህ የእርሱ ቁጥር 1 አድናቂው ለመሆን የበቃሁት፡፡
በእኔ የግል የግምገማ መስፈርት መሰረት ቴዲ አፍሮ እንደሙዚቃ ባለሞያነቱ ከፖፕ ሰታር (pop star) በላይ የመጠቀ እና የላቀ ድምጻዊ ከያኒ ነው፡፡ በእኔ አመለካከት ለዶ/ር ኪንግ፣ ለማንዴላ እና ለማህተመ ጋንዲ እሴቶች እና መርሆዎች ተግባራዊነት የቆመ የሙዚቃ ሐዋርያ ነው፡፡
ቴዲ ከፍተኛ የሆነ ክብር፣ ምስጋና እና አድናቆት ያለው ከያኒ ነው፡፡ በእርግጠኝነት ቴዲ ከእርሱ ትውልድ የተስፋ፣ የእምነት፣ የብሩህ አመለካከት እና የጽናት ተምሳሌት ቀንዲል ነው፡፡
(ለእኔ እውን ሆኖ የሚታይ ጉዳይ ነው!!! ቴዲ አፍሮ ከእርሱ የተስፋ፣ እምነት፣ የብሩህ አመለካከት እና የጽናት ተምሳሌት ቀንዲል ሆኖ በመገኘቱ ምክንያት በወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ መሰቃየት ሊኖርበት ይችላልን?)
በቅርቡ ኢትዮጵያዊው ገጣሚ ሄኖክ የሽጥላ  ስለቴዲ ክብር በአማርኛ ጥቂት የግጥም ስንኞችን ቋጥሮ ነበር፡፡
እርሱ የቋጠራቸው ሶስት የስንኝ ግጥሞች ወደ እንግሊዝኛ እንዲመለሱ በማድረግ ያቀረብኩ ሲሆን እንደገና የአማርኛ ትርጉማቸው በግጥም ስንኝ መልክ እንዲመለሱ በማድረግ ሁሉንም መተርጎም እችል ነበር፣ ሆኖም ግን የግጥሙ አንኳር የሆኑት ሶስቱ ስንኞች እንደሚከተለው ቀርበዋል፡
ቴዲ እንደ ዳዊትዘይት በቀንድ ዋንጫ
ቀብቶታል አምላክ ፣ ለብርሃን መውጫ !
ነፃነት ለሀገሬ ደግሞ አንዲህ ይለዋል:
ቴዲ እንደ ንጉስ ዳዊት ለብሶ ካባ፤
ከቀንዱ ቅዱሱን ቅባት የተቀባ፣
ጨለማን ሊያስወግድ የመጣ ያምላክ መባ፡፡
ለቴዲ አፍሮ ሰላማዊት አበባየሁ የፃፈችዉን ተደናቂ ግጥም ለመስማት እዚህ ይጫኑ
አሜን!
ሰይጣኖች እባካችሁን ቴዲን ለቀቅ አድርጉትአባካችሁ ተዉት ስራዉን ይስራበት !!!
ታላቁ የኢትዮጵያ የሙዚቃ ንጉስ ጥላሁን ገሠሠ አንደዚህ ብል ዘፍኖ ነበር “እረ ተዉኝ ባትነኩኝ ምናለበት” ሙዚቃዉን ለመስማት  እዝህ ይጫኑ
(ይህን የጥላሁንን ሙዚቃ ለቴዲ በክብርና በወንድምነት አቀርብለታለሁ።) 
እረ ተዉኝ ባትነኩኝ ምናለበት
አባካችሁ ሰዎች ስራዬን ልስራበት።
የሰው ሃሳብ አመረረ በተንኮል እየከረረ
ሰው ካልኖረ ስራ ሰርቶ
ባለው አቅሙ ዘር አምረቶ
በችሎታው በያለበት
ሰርቶ ቢኖር ምናለበት
ነገር ሲጭር ስራ አይሰራም
ሌላዉንም አያሰራም።
እረ ተዉኝ ባትነኩኝ ምናለበት
አባካችሁ ሰዎች ስራዬን ልስራበት ።
አምሮ በነገር ሰግዶ
በወሬ ከሆነ ኑሮ
ምን ሊሆን ነው ምን ሊጠቅም
በስራ ካልሆነ ጥቅም
ባቅሜ ሰርቼ ስራ
ለሀገር ጥቅም ላፈራ
ነው አንጂ የባከንኩኝ
ምን አለበት ባትነኩኝ።
እረ ተዉኝ ባትነኩኝ ምናለበት
አባካችሁ ሰዎች ስራዬን ልስራበት።
የተንኮል ምንጩ ይደፈን
ስራ ሰርተን መኖር አርፈን
ይሻለናል ስራ ስሩ
ምን ይገኛል ካፈሩ
ፍቅር  ሰላም ከኛ ጋራ
አስወጥተው ባላጋራ
አንደየአቅማችን ሰርተን
መኖሩ ነው የሚበጀን።
እረ ተዉኝ ባትነኩኝ ምናለበት
አባካችሁ ሰዎች ስራዬን ልስራበት።
የሕግ የበላይነትን ለወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ ማስተማር እና መስበክ ማለት ለአሕዛብ መጽሐፍ ቅዱስን ማሰትማር መሞከር አንደማለት ነው። አለዝያም  በጥቁሩ ባልጩት ድንጋይ ላይ ውኃ እንደማፍሰስ ነው፡፡
አሁን ደግሞ ስለፍቅር፣ ስለይቅርታ አድራጊነት እና ስለዕርቀ ሰላም ለወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ ማስተማር እና መስበክ ማለት ለጀርመን ብሄራዊ የሰራተኞች ሶሻሊስት ፓርቲ (ናዚዎች) አባላት ስለፍቅር፣ ስለይቅርታ አድራጊነት እና ስለዕርቀ ሰላም ማስተማር እና መስበክ እንደማለት ነው፡፡
የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ እንዲያዳምጠኝ ጥያቄ ማቅረቤ አይደለም፡፡ ለዚህማ የሚያዳምጡበት ልቦና የላቸውም እንጅ ሁልጊዜ በየሳምንቱ ትምህርት እያቀረብሁ አይደለምን?
ለወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ ጥያቄ የማቀርብላቸው ግን የቴዲ አፍሮን ሙዚቃ በጥሞና እንዲያዳምጡ ነው፡፡ በእውነት የእርሱን እውነተኛ ሙዚቃ፣ መሳጭ የሆኑ የግጥም ስንኞቹን እና መንፈስን የሚያድሰውን የድምጹን ቅላጼ ብያዳምጡ የመቀራረብን እና የፍቅር ስሜትን በተላበሱ ነበር፡፡
ከቴዲ ሙዚቃ በሚወጣው ፍቅር፣ እያንዳንዱ ቃሉ በክፋት የተሞላውን የግፈኞች አዕምሮ ወደ ስምምነት እና ፍቅር በመለወጥ፣ የእርሱ የሙዚቃ ምት የእነርሱን የልብ ምት በመምታት በፍቅር እንዲሸነፉ እና እጃቸውን እንዲሰጡ ያደርጋል፡፡
የእንግሊዝ የተውኔት ጸሐፊ እና ገጣሚ የነበሩት ዊሊያም ኮንግሬቭ እንዲህ በማለት ጽፈው ነበር፣ “ሙዚቃ ጨካኙን አውሬ ሩህሩህ የማድረግ፣ ጠንካራ አለቶችን የማለስለስ ወይም ደግሞ የተቋጠረ ጠንካራ የዋርካ ዛፍ ግንድን እንዲለነበጥ የማድረግ ኃይል አለው፡፡“
የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ የቴዲ አፍሮን ሙዚቃ የሚያዳምጡ ከሆነ ሩህሩህ መንፈስን እንደሚላበሱ፣ የተዘጉ ልቦቻቸው ለስላሳ እንደሚሆኑ፣ አውሬያዊው ኋላቀር መንፈሳቸው የተረጋጋ እንደሚሆን እና የተቋጠሩት ልቦቻቸው ሊፈቱ እንደሚችሉ ምንም ዓይነት ጥርጣሬ የለኝም፡፡
የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ የቴዲን ጣፋጭ የሙዚቃ ምግቦች በመመገብ እና በመሳተፍ ከእኛ ጋር ተቀላቀሉ፣ መንፈስ ይቀርባችኋል ከእኛ ጋር ሁኑ፡፡
በፖለቲካ፣ በሕግ ወይም ደግሞ በሰብአዊ መብት ጥበቃ ቋንቋ ከወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ ጋር ለመነጋገር የሚታሰብ ነገር አይደለም፡፡
ሆኖም ግን ሙዚቃ የዓለም ህዝብ የመግባቢያ ቋንቋ ነው የሚለው እውነት ከሆነ በመጨረሻው ሰዓት በቴዲ አፍሮ ሙዚቃ አማካይነት ከወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ ጋር መነጋገር እንችላለን ማለት ነው፡፡
በቴዴ  ያስተሰርያል በሚለው ፈዋሽ ድምጹ መሰረት ከወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ ጋር መነጋገር እችላለሁ ብዬ አስባለሁ!
የወያኔ ወንድሞች! የቴዲን የፍቅር ሙዚቃዎች ለማዳመጥ ሞክሩ፣ በእርግጠኝነት አዳምጡ!
ከጥላቻችሁ በስተቀር የምታጡት ምንም ነገር የለም!
ሙዚቃ የፍቅር ምግብ ከሆነ ቴዲ እባክህን ዘምር፡፡ ደግመህ ደጋግመህ ተጫወት፣ ዘምር፡፡
ፍቅር ሁሉንም ያሸንፋል፡፡ ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ)
አሜን!   
ቴዲ፣ እንወድሀለን፡፡ እናከብርሀለን፡፡ እናደንቅሀለን!!!
ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!
ጳጉሜ 2 ቀን 2007 ዓ.ም
Source ecadforum.com

Friday, September 4, 2015

ረሀብን ለማጥፋት ህወሓትን ማስወገድ

ረሀብ በአገራችን ላይ እያንዣንበበ ነው። በአፋርና በሱማሌ ከከብቶች አልፎ ሕፃናት እየሞቱ ነው። የረሀቡ አደጋ ወደ ኦሮሚያና ሌሎች የደቡብ ገጠሮች እየተዛመተ ነው፤ ሰሜን ኢትዮጵያም ከአደጋ ውጭ አይደለም።
“ከአስር ዓመታት በላይ በተከታታይ በየዓመቱ ከአስር በመቶ በላይ የኢኮኖሚ እድገት አሳይተናል” የሚለው ዓይን ያወጣ ውሸት፤ “ድህነትን ተረት እናደርጋለን” የሚለው ጉረኛ መፈክር፤ “መካከለኛ ገቢ ያላቸው አገሮች ተርታ እንደርሳለን” የሚለው ባዶ ተስፋ፤ የወያኔዎችና ጀሌዎቻቸው በፎቅና ቪላዎች መንበሽበሽ፤ የድግሶችና የስብሰባዎች መብዛት ለሕዝባችን ቁርስ፣ ምሳና እራት አልሆኑም።
አገዛዙ ጉራውና ባዶ ተስፋ መስጠቱ እንዳለ ሆኖ የረሀቡን ምክንያት በተፈጥሮ ላይ ማላከኩን ተያይዞታል። ለመሆኑ ተፈጥሮ ብቻውን እየተደጋገመ ለሚመጣ ችጋርና ቸነፈር በቂ ምክንያት ሆኖ ያውቃልን? አስከፊ የረሀብ ዜናዎች የሚሰማባቸው አገሮች በሙሉ ነፃነት የታፈነባቸው አገሮች መሆናቸው የአጋጣሚ ጉዳይ ነውን? ለምንድነው አንድ ዓይነት ችግር እየተደጋገመብን መላ መፈለግ ያቃተን? መልሱ አጭርና ቀጥተኛ ነው። “ችግር የመሳካት እናት” የምትሆነው በነፃነት ማሰብ የሚችል ጭንቅላት ሲኖር ነው። በባርነት ጨለማ ውስጥ ያለ ጭንቅላት ለችግሮች መፍትሄ የማፍለቅ አቅም የለውም። እንዲያውም እንዲህ ዓይነቱ ድኩም ጭንቅላት ችግሮችን ማሸነፍ ሳይሆን ተሸናፊነትን ተቀብሎ ከችግሮች ጋር ተስማምቶና ተወዳጅቶ መኖርን ይመርጣል። ነፃነት ያለው ሕዝብ ረሀብን እንደሚያሸነፍ ተደጋግሞ የታየ ጉዳይ ነው። ለዚህም ነው ረሀብን የተፈጥሮ ሚዛን መዛባት ውጤት ብቻ አድርጎ ማቅረብ እውነትን መሸፈጥ የሚሆነው። ረሀብ የብልሹ አስተዳደር ውጤት ነው።
አገራችንን የረሀብ ቀጠና ካደረጉ የ24 ዓመታት የህወሓት “ድሃን ዘርፈህ ብላ” የኢኮኖሚ ፓሊሲ ውጤቶች መካከል አንዳንዱን ለአብነት ያህል መዘርዘር ይቻላል።
1. ገበሬና መሬት ተለያይተዋል። ለም መሬቶች በኢንቨስትመንት ስም በዘመኑ የህወሓት ጉልተኞች በመያዛቸውና እነሱ ደግሞ በተራቸው ለባዕዳን እየሸጡ በመሆኑ ባለሀገሩ ጭሰኝነት እንኳን አጥቶ ለቀን ሠራተኝነትና ልመና ተዳርጓል። አዳዲሶቹ ባለሃብቶች ለፈጣን ኪስ መሙላት እንጂ ለዘለቄታ የአፈር ልማት ፍላጎቱም እውቀቱም የላቸውም። በዚህም ምክንያት ገበሬው ትንሽ የዝናብ ዝንፈት እንኳን መቋቋም እስከማይችልበት ደረጃ ተዳክሟል።
2. በዘር ላይ በተመሰረተ ክልላዊ ድንበር ሳቢያ ኢትዮጵያዊያን ገበሬዎች በአገራቸው ውስጥ ተዘዋውረው መሥራት አልቻሉም። ከሰሜን ወደ ደቡብ ከተሰደደ የአገራችን አርሶ አደር ይልቅ ለቻይና ገበሬ መሬት ማግኘት ይቀለዋል። እንዲያውም ኢትዮጵያዊው ድሀ ገበሬ በዱላ ሲባረር፤ ከውጭ አገር የመጣው ቱጃር ገበሬ ብድርና ማበረታቻዎች ይሰጠዋል።
3. ደኖቻችን ተጨፍጭፈው፣ ለም መሬታችን ተሸርሽሮ በማለቁ የግብርናችን ምርታማነት በእጅጉ ቀንሷል። በዘመነ ወያኔ የደን ጭፍጨፋና የመሬት መሸርሸር በአስደንጋጭ ሁኔታ ጨምሯል። አገሪቷ በፍጥነት ወደ ምድረበዳነት እየተቀየረች ነው።
4. ፋይዳ ያለው የስነ ሕዝብ ፖሊሲ ባለመኖሩ የሕዝብ ብዛት አሻቅቧል። እንደ ኢኮኖሚው ሁሉ ወያኔ የኢትዮጵያን ሕዝብ ብዛት ሊቆጣጠር የሚሞክረው ቢሮ ውስጥ ቁጭ ተብሎ በሚደረግ የቁጥር ጨዋታ ነው። የስታተስቲክሱ ባለሥልጣን ቁጥራችንን በትክክል ሊነግረን ባይፈልግም እንኳን ረሀብ መብዛታችንን እየነገረን ነው።
5. የህወሓት ባለሥልጣኖችና በየክልሉ ያደራጇቸው ምስለኔዎች ራሳቸውን ባለሚሊዮኖች አድርገዋል። እነዚህ በአንድ ጀምበር የበቀሉ ቱጃሮች ከገንዘብ በተጨማሪም የጄኔራልነት፣ የሚኒስቴርነት፣ የክልል ገዢነት፣ እጅግ ቢያንስ የቢሮ ኃላፊነት ሥልጣንን ኪሳቸው ውሰጥ ከተዋል፤ ልባቸው የተመኘውን ዲግሪ ሸምተዋል። የመንግሥት ሥልጣንና ሃብት ይኸን ያህል የተቆራኙበት ሥርዓት በኢትዮጵያ ኖሮ አያውቅም። የጥቂቶች ያለአገባብና ያለቅጥ መክበር በአንፃሩ ደግሞ የብሃኑን ሕዝብ መደህየት ድህነትን መዋቅራዊ አድርጎታል።
6. በአቋራጭና በፍጥነት ለመክበር አስተማማኙ መንገድ የገዛ ራስ ጥረትና ታታሪነት ሳይሆን ቅጥፈት፣ አጭበርባሪነትና ሎሌነት መሆኑን የወያኔ ካድሬዎች በተግባር እያሳዩ ጥሮ ማደርን “ኋላ−ቀር አሠራር” አድርገውታል። በህወሓት የኢኮኖሚ ፓሊሲ የተበረታቱት አድርባይነት፣ ስንፍናና እና ልመና ችግርን የመጋፈጥ አቅማችንን ሰልበውታል።
እነዚህና የመሳሰሉት ጭብጦችን በማንሳት የረሀቡ መሠረታዊ ምክንያት የህወሓት አገዛዝ እንጂ ተፈጥሮ አለመሆኑን አስረግጠን እንናገራለን። ሕዝባችን በነፃነት ማሰብ፣ መመራመር፣ መፈተሽ ቢችል ኖሮ ረሀብን ማጥፊያ ብልሃት ማግኘት ባላቃተውም ነበር። ወደፊትም ቢሆን ተፈጥሮ እኛ እንደፈለግናት አትሆንም፤ መተማመኛችን የሰው ልጅ ወሰን የለሽ የፈጠራ ችሎታና ችግሮችን የመፍታት አቅም ነው። ለዚህ ደግሞ ችግሮችን በልጦ መገኘት ያስፈልጋል። ወያኔ የኢትዮጵያን ሕዝብ ከችግሮች በታች ሆኖ መፍትሄ ከአገዛዙ የሚጠብቅ ደካማ እንዲሆን አድርጎታል። በዚህም ምክንያት ነው የችግሮቻችን ቁንጮ ራሱ ወያኔ ነው የምንለው።
ህወሓትን ከመንግሥት ሥልጣን ሳናስወግድ ድህነትንና ረሀብ እናስወግዳለን ማለት ዘበት ነው:: ድህነት የህወሃት ዋነኛ የገቢ ምንጭ በመሆኑ ህወሓት ሥልጣን ላይ እስካለ ድረስ በወሬ ካልሆነ በስተቀር ድህነት በተግባር ሊቀጭጭ አይችልም። ችጋርና ህወሓት እጅና ጓንት ናቸው። ረሀብ የህወሓት ባለውለታ ነው። ረሀብ የህወሓት የቁርጥ ቀን አጋሩ ነው። ህወሓት በረሃ እያለ በአሸዋ የተሞሉ ጆንያዎችን እህል አስመስሎ በመሸጥ ለእርዳታ በመጣ ገንዘብ ራሱን አደራጅቷል። ስልጣን ከያዘም በኋላ “ረሀብን እየተዋጋሁ ነው” በማለት የምዕራባዊያንን ድጋፍ ለማግኘት ጠቅሞታል። ረሀብና ችጋር የወያኔ “ጪስ አልባ” እንዱስትሪዎች ናቸው። ሕዝባችን ተራበ ማለት የወያኔ ኩባንያዎች ሥራ አገኙ ማለት ነው። ህወሓት ረሀብን ለመቀነስ ቅንጣት ታህል ፍላጎት ቢኖረው ኖሮ በዚህ ወር ውስጥ በተደረጉ ስብሰባዎች በወጣው ወጪ ብቻ በአገራችን ላይ ያንዣበበውን ረሀብ በቁጥጥር ማዋል በተቻለ ነበር።
አርበኞች ግንቦት 7: የአንድነትና ዲሞክራሲ ንቅናቄ ለወገኖቻቸን መራብ ተጠያቂው የህወሓት ዘረኛ አገዛዝ ነው ይላል። ረሀብን ከኢትዮጵያ ምድር ለዘለቄታው ለማስወገድ የህወሓት አገዛዝን አስወግደን በምትኩ ለሕዝብ ደህንነት የቆመ፣ በሕዝብ የተመረጠ እና ከሕዝብ አብራክ የወጣ መንግሥት እንዲኖረን እንታገል ይላል።
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!!
Source www.patriotg7.org