Thursday, August 13, 2015

የኤልያስ ገብሩ ቆይታ ከጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ጋር (ዝዋይ እስር ቤት)

በኤልያስ ገብሩ
  • ታገሉ! ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ (ከዝዋይ እስር ቤት)
  • ተመስገን ደሳለኝ ስለሙስሊም መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት ፍርድም ሀሳቡን ሰንዝሯል
Temesgen Desalegn Fteh newspaper editor
ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ
ቦሌ አካባቢ ብርዱ ጠንከር ያለ ነበር፡፡ ከቦሌ ብራስ ወደሚሊኒየም አዳራሽ በሚወስደው ቀጭን መንገድ ላይ ወንዱም ሴቱም በፍጥነት ይራመዳል፡፡ ከታክሲ በሁለቱም አቅጣጫዎች የወረዱ ሰዎች ወደመደበኛ ሥራቸው ለመግባት ብሎም የግል ጉዳያቸውን ለመፈጸም ሲንቀሳቀሱ ነበር – ከትናንት በስትያ ሰኞ (ነሐሴ 04 ቀን 2007 ዓ.ም) ጥዋት 1፡45 ሰዓት፡፡
እኔ እና ወዳጄ አቤል ዓለማየሁ ወደከአዲስ አበባ 160 ኪሎ ሜትር ርቀት ወደሚገኘው ዝዋይ እስር ቤት አምርተን ጋዜጠኛ ውብሸት ታዬን እና ተመስገን ደሳለኝን ለመጠየቅ በዚህ ቀን ቀጠሮ ይዘን ነበር፡፡ አቤል ከቀጠሯችን 20 ደቂቃ ዘግይቶ፣ ቦሌ ጫፍ ደረሰና ወደቃሊቲ መናሃሪያ ሁለት ታክሲዎችን በመጠቀም ደረስን፡፡ ወደዝዋይ የሚጭኑ ሚኒባስ ታክሲዎች እና ‹‹አባዱላ/ዶልፊን›› የሚል መጠሪያ የተቸራቸው የህዝብ ማመላለሻ መኪኖች ቢኖሩም በተለምዶ ‹‹ቅጥቅጥ›› የሚባለውን መካከለኛ አውቶቡስ ምርጫችን አደረግን – የትራፊክ አደጋን በመስጋት፡፡
የተሳፈርንበት አውቶቡስ፣ ከቃሊቲ ትንሽ ወጣ ካለ በኋላ፤ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም፣ በእስር ላይ የሚገኙትን የግንቦት 7 ዋና ፀሐፊ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ “ልማቱን አሳዩኝ” ሲለን ከከተማ ወጣ እያደረግን የምነሳየው… [እውነት ግን፣ በከባድ እስር ላይ መሆናቸው የሚገመተው አቶ አንዳርጋቸው ‹ልማቱን አሳዩኝ› ይሏቸዋልን?!]›› ሲሉ ለቪኦኤዋ ጋዜጠኛ ትዝታ በላቸው የገለጹትን፣ የአዲስ አበባ አዳማ አዲሱ የፍጥነት መንገድ (Express way)ን ተቀላቀለ፡፡ በዚህ መንገድ ሁለታችንም ሄደን አናውቅም ነበር፡፡ ሆኖም እስከዛሬ ካየኋቸው የመኪና መንገዶች በደረጃው ከፍ ያለ ይመስላል፡፡ [በሀገራችን አምረው የተሰሩ የመኪና መንገዶች በጥቂት ዓመታት ውስጥ በከፍተኛ ሁኔታ የመቦርቦር፣ የመፈረካከስ፣ ውሃ የማቆር ችግሮች ገጥሟቸው እንዲሁም ከመንገዱ ዳር እና ዳር የሚገኙ የብረት አጥሮች ተሰርቀው፣ ተገጭተው፣ ተጨረማምተው፣ ተነቃቅለው … አደጋ ሲያደርሱና የተለመደ የሬንጅ የመለጠፍ ሥራ ሲሰራላቸው በገሃድ የምናየው ሀቅ መሆኑን ማስታወስ ግን የግድ ይላል] ይሄኛው መንገድ ከጠቀስኳቸውና ካልጠቀስኳቸው ችግሮች ምን ያህለ ነጻ ነው? ለሚለው ትክክለኛ መስክርነት መስጠት ያለበት ለእውነት የቆመ የዘርፉ ባለሙያ ቢሆንም በኢህአዴግ ‹ልማት› ላይ የጥራት መተማመኛ ማግኘት እጅግ ከባድ መሆኑን ግን አምናለሁ፡፡ አስፋልቱ ለፍጥነት አመቺ መሆኑን ግን በቀላሉ መረዳት ይቻላል፡፡
በሶስት ሰዓታት ጉዞ ዝዋይ በመድረስ ምሳ ከበላን በኋላ ወደእስር ቤቱ የፈረስ ጋሪ መጠቀም ግዴታችን ነበር፡፡ አቧራማው አስቸጋሪ መንገድ፣ ከፊሉ ደቃቅ አሸዋ መልበስ ጀምሯል፡፡ የእስር ቤቱ የማስፋፊያ ግንባታ ሥራ፣ በፊት ውብሸትን ለመየጠቅ ስመጣ ከማውቀው ተፋጥኗል፡፡ አንዱ የሥርዓቱ “የልማት ውጤት” እስረኛ ማብዛት አይደለ ታዲያ?!
ከቀኑ 7፡30 ሰዓት ላይ የምንጠይቀውን እስረኛ በማስመዝገብ ተፈትሸን ገባን፡፡ ሁለት እስረኛ በአንዴ መጠየቅ ስለማንችል እኔ ተመስገን ጋር፣ አቤል ደግሞ ውብሸትን ለመጠየቅ ተስማምተን ነበር፡፡ አቤል ውብሸትን ከጠየቀ በኋላ እንደምንም ብሎ ተመስገንን ለመጠየቅ ጥረት እንደሚያደርግ ግን ቀድሞ ነገረኝ፡፡
ተመስገን እና ውብሸት የታሰሩበት ዞን ስለሚለያይ እኔ እና አቤል ሌላ የውስጥ ፍተሻ ካደረግን በኋላ መለያየታችን ግድ ነበር፡፡ የእስር ቤቱ ፖሊሶች የሚኖሩበትን ጉስቁልና ያጠቃቸው፣ መኖሪያ ቤቶችን አልፌ መጠየቂያው ጋር ደርሼ የታሳሪው ስም ያለባትንና በፖሊሶች የምትጻፈዋን ቁራጭ ወረቀት እስረኛን ለሚጠራው ፖሊስ ሰጠሁትና በአጣና እንጨት ርብራብ በተሰራው መጠየቂያው አግዳሚ ላይ ተቀመጥኩ፡፡ ከቅርብ ርቀት የፖሊሶች ማማ ይታያል፡፡ መሳሪያ የታጠቁ ፖሊሶች ማማው ላይና ከማማው ሥር በዛ ብለው ተቀምጠው ያወጋሉ፡፡ አብዛኞቹ ፖሊሶች ከላይ የለበሷት እና “Federal prison” የሚል የታተመባት አረንጓዴ ዩኒፎርምም በፀሃይ ብዛት ነጣ ወደማለት ደርሳለች፡፡ አንዱ ፖሊስ መጣና ከእኔ በትንሽ ሜትር ራቅ ብሎ ተቀመጠ፡፡ ‹‹አዳማጭ ነው›› አልኩ በልቤ፡፡ ወደፊት ለፊቴ ወደሚታየኝ የእስር ቤት ግቢ አማተርኩ፡፡ ለእይታ የሚጋብዝ አንዳች ነገር አጣሁ፡፡ የተበታተኑ ዛፎች፣ ቅርጽ አልባ ሳሮች፣ አስታዋሽ ያጡ አረሞች፣ ግድግዳ እና ጣራቸው በቆርቆሮ የተሰሩ የእስረኛ መኖሪያዎች፣ …ብቻ ጭርታ እና ድብታ የወረረው የግዞት መንደር ይመስላል፡፡
ከአንደኛው የእስረኛ ቆርቆሮ ቤት ጣሪያ ላይ ሁለት ተለቅ ተለቅ ያሉ ሙቀት ማቀዝቀዣዎች ይሽከረከራሉ፡፡ ወደፖሊሱ ዞሬ ‹‹ለሙቀት ነው?›› አልኩት ወደ ጣራው በመጠቀም፡፡ ‹‹አዎ፣ ወባ አደገኛ ነው›› አለኝ፡፡ ‹‹እስረኞች ሲታመሙ እንዴት ይሆናሉ?›› ስል ጥያቄ ሰነዘርኩ፡፡ ‹‹ያው እዚሁ ይታከማሉ›› አለኝ ድምጹን ቀሰስ አድርጎ፡፡ የእኔም ሆነ የእሱ ልብ፣ በማረሚያ ቤቱ (በእነሱ አጠራር) በቂ ህክምና እንደማይሰጥ ግን ያውቃል ብዬ አሰብኩ፡፡ ቀጭኑ ፖሊስ፣ ‹‹ለወባ ህመም ምግብ ወሳኝ ነው›› አለኝ አስከትሎ፡፡ ‹‹በቂ ምግብ የለም ማለት ነው?›› ስል ድጋሚ ጠየኩት፡፡ ‹‹በፊት በፊት አቀራረቡ ዝም ብሎ ነበር፤ ሙያ ባሌላቸው ሴቶች ነበር የሚሰራው፡፡ አሁን ግን ለውጥ አለ›› አለኝ፡፡ ‹‹ምን አይነት ለውጥ? ጥቂትም ቢሆን ታስሬ፣ ለእስረኞች የሚቀርበውን በጣም ደረጃውን ያልጠበቀ ምግብ አይቻለሁ›› አልኩት፡፡ ‹‹በፊት ጥቁር ጤፍ ነበር የሚቀርበው፤ አሁን የነጭ ጤፍ እንጀራ ነው የሚበሉት፤ እስረኞች ችግር የለባቸውም፤ ባለሙያ ሴቶችም ናቸው የተቀጠሩት …›› ‹‹(ውስጤ አላመነምና) ለእስረኛ የነጭ ጤፍ እንጀራ እያቀረባችሁ ነው?!›› …‹‹አዎ›› ብሎ ሊያብራራልኝ እያለ ከታች ከርቀት ‹‹አረንጓዴ ኮፊያ፣ ቲ-ሸርትና ስካርፍ ያደረገ ሰው አየሁ፡፡ ትኩረቴን ከፖሊሱ አዙሬ ቁልቁል ተመለከትኩ – ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ነበር፡፡ ተሜም፣ ረጋ ብሎ በራስ በመተማመን መንፈስ ወደመጠየቂያው ሥፍራ ቀረብ ብሎ ጠያቂውን ለማወቅ ጥረት አደረገ፡፡ ሳየው አንዳች የሀዘን ስሜት ውስጤ ገባ፡፡ ቆሜ ጠበኩት፡፡ ፈገግ እያለ መጣና ተጨባብጠን አራት አምስቴ ያህል ተቃቀፍን፡፡ ‹‹በዚህ በጸሐይ ለምን መጣህ?›› ሲል ጠየቀኝ፡፡ ከአቤል ጋር መምጣታችንን፣ እሱ ውብሸትን ሊጠይቀው መሄዱን ነገር ግን ከቂሊንጦ በኋላ እስከአሁን ዝዋይ ድረስ መጥቼ ባለመጠየቄ የጸጸት ስሜት ውስጤ እንዳለ ገለጽኩለት፡፡ ‹‹መንገዱ ረዥም ነው፣ ባትመጡም እረዳለሁ›› ካለ በኋላ፤ ‹‹ምን አዲስ ነገር አለ?›› በማለት ፊት ለፊት በእንጨት አጥር ተከልለን በመቀመጥ ጨዋታችንን ቀጠልን፡፡
‹‹አሁን ምን እየሰራችሁ ነው?››፣ ‹‹ክስህስ እንዴት ሆነ?››፣ ‹‹አዲስ ጋዜጣ ለማቋቋም ለምን ጥረት አታደርጉም?›› ከተመስገን በተከታታይ የተነሱ ጥያቄዎች ነበሩ፡፡ አጠር አጠር አድርጌ መለስኩለት፡፡ የጋዜጣ /የመጽሔት ህትመትን ድጋሚ መጀመር የግድ አስፈላጊ መሆኑን ግን ተመስገን አጽንኦት የሰጠበት ጉዳይ ነበር፡፡ …ስለተወሰኑ ጋዜጠኞችና የዞን 9 ጦማሪያን ከእስር መፈታት፣ ስለኦባማ የአዲስ አበባ ጎብኝት፣ በቂሊንጦ ዞን አንድ ከእነአብበከር አህመድ፣ ጦማሪ አቤል ዋበላና ዘላለም ክብርት ጋር ስለነበረው ቆይታ፣ እሱ ወደዝዋይ ከወረደ በኋላ እኔም በዚያ ዞን ገብቼ በነበረበት ጊዜ እነአቡበከር፣ አቤልና ዘላለም እሱን በተመለከተ ስለነገሩኝ ነገሮች ሳቅ እያልን አወጋን፡፡
ሰፊ ውይይት ያደረግነው በሙስሊም መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት ላይ በቅርቡ ከ7 እስከ 22 ዓመት የሚደርስ ጽኑ እስራት ፍርድን በተመለከተ ነበር፡፡ ‹‹እኛ ከሙያ ጋር በተያያዘ ነው የታሰርነው፡፡ ታስረንም እንወጣለን፡፡ ከባዱ የሙስሊሞቹ እስር ነው፡፡ ኢህአዴግ እውነተኛ ሰላም ከፈለገ እነአቡበከርን በነጻ መፍታት አለበት፡፡ እኔ የእነሱ መከላከያ ምስክር ሆኜ ምስክርነቴን ሰጥቻለሁ፡፡ በወቅቱ ዘንግቼው ያልተናገርኩት አንድ ነገር ነበር፤ አሁን ሳስበው ትንሽ ይቆጨኛል – በተናገርኩ ብዬ፡፡ ያኔ (በምስክርነት ጊዜ)፣ ‹የኮሚቴዎቹ እንቅስቃሴ ሰላማዊ ነበር ወይስ አልነበረም?› የሚለው ጥያቄ በራሱ መነሳት አልነበረበትም፡፡ እንቅስቃሴያቸው፣ ሰላማዊ ባይሆን ኖሮ እንዴት ሶስት ዓመት ሙሉ በክስ ሂደት ይቀጥላል?! ሰላማዊ ስለሆኑ እኮ ነው፣ ባለፉት ሶስት ዓመታት ምንም ያልተፈጠረው፡፡ እስኪ በእነሱ አንድ የተሰበረ መስታወት አለ?! ቅንጣት የወደመ ንብረት አለ?! የማንንስ ሕይወት አጠፉ?! በእነሱ የተፈጠረ አንድም ነገር የለም፡፡ ጥያቄያቸው ኃይማኖታዊ እንጂ ፖለቲካዊ አይደለም፡፡ ፖለቲካዊ ቢሆን ኖሮ ትግሉ አቅጣጫውን ይቀይር ነበር፡፡ ‹የመጅሊስ አመራሮችን ካለመንግሥት ጣልቃ ገብነት እንምረጥ!› ነው አንዱ ሰላማዊ ጥያቄያቸው፡፡ ያው ምስክር ስትሆን ከዚህም ከዚያ ጥያቄ ሲነሳ ስለምትዘናጋ መመስከር ያሰብከውን ነው ቅድሚያ የምትሰጠው እንጂ አሁን የምልህን ያኔ ብገልጸው በጣም ደስ ይለኝ ነበር …›› በማለት በኢትዮጵያ ውስጥ ከታሪክ አኳያ፣ በሁለቱ ትልልቅ ሃይማኖት ተከታዮች መካከል ስለነበረው ግንኙነት በዝርዝር የራሱን ምልከታ እና ሀሳብ ደጋግሞ አወጋኝ፡፡ ኃይማኖታዊ መቻቻል ነበር ወይስ አልነበረም? የሁለቱም እምነት ተከታዮች ጉርብትና ነበራቸው ወይስ አልነበረባቸውም በሚሉት አንኳር ጉዳዮችም የራሱን አቋም አንጸባረቀልኝ፡፡
ኡስታዝ አቡበከር አሕመድን አስመልክቶም አንድ ጥሩ ምሳሌም አንስቶልኝ ነበር ተመስገን፡፡
‹‹አሁን ባለሁበት ዞን፣ በአንድ የወንጀል ክስ ግብረ-አበር ተብለው አምስት ዓመት የተፈረደባቸው አንድ ቄስ አሉ፡፡ እኚህ ቄስ ለጠበቃ የሚከፍሉት አጥተው የጠበቃ ክፍያ የፈጸመላቸው አቡበከር እንደሆነ ነግረውኛል››
እኔም ፣ በህዳር ወር ቂሊንጦ ዞን አንድ በነበርኩበት ጊዜ ከዚህ ጋር ተመሳሳይ የሆነ ነገር፣ ስለአቡበከር ሰምቼ ነበር፡፡ ታሪኩ እንዲህ ነው፡- አንዱ እነአቡበከር ይገኙ በነበረበት ዞን 1 8ኛ ቤት ውስጥ የቀጠሮ እስረኛ ነበር፡፡ ዋስትና ይጠየቅና በዚህ ክፍል ውስጥ በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው የታሰሩ አንድ የናጠጡ ሀብታም (ልጃቸው 22 አካባቢ እጅግ ዘመናዊ ሆቴል አለው) ጋር ጠጋ ብሎ ለዋስትና የሚሆን ብር ተጨንቆ በአክብሮት ይጠይቃቸዋል፡፡ እሳቸውም ‹‹እኔም እንደአንተው እስረኛ እኮ ነኝ!›› በማለት ይመልሱለታል፤፡፡ ልጁም ያዝናል፡፡ ይህ ጉዳይ አቡበከር ጆሮ ይገባና ለልጁ የሚስፈልገውን የዋስትና ብር ከፍሎ ልጁን ከእስር እንዲወጣ አድርጎታል፡፡ እንግዲህ፣ ከሁለቱ እውነተኛ ምሳሌዎች በመነሳት፣ አቡበከር ለወገኖቹ ሃይማኖትን መሰረት ሳያደርግ፣ በሰብዓዊነት ደግ መሆኑን እንማራለን፡፡
ከተመስገን ጋር በነበረን ሰፋ ባለ የጨዋታ ጊዜ፣ ከጎኔ የነበረው ፖሊስ በተመስጦ ቢያዳምጥም፣ አንዴም አላቋረጠንም ነበር፡፡ …ስለ 100% ቱ የዘንድሮ ምርጫ ፍጻሜ፣ በሰሞኑ በአፋር ክልል ስለደረሰው የድርቅ አደጋ፣ በአይ ኤስ አሸባሪ ቡድን ስለተቀሉና ስለተገደሉት ኢትዮጵያኖች፣ ድርጊቱን በማውገዝ በመስቀል አደባባይ በተጠራው ሰልፍ ላይ ስለተፈጠረው ረብሻ፣ ጉዳትና እስር ተመስገን የራሱን አተያይ በስሜት ተውጦ የግሉን ሀሳብ አብራራልኝ፡፡ በተጨማሪም፣ አይ ኤስ ያንን ድርጊት፣ ያንን ጊዜ መርጦ አደረገ ያለበትን የራሱን የተለየ (ከማንም ያላደመጥኩትን፣ ተጽፎም ያላነበብኩትን) ሀሳብ አጋራኝ፡፡ የተለየ ሃሳብ በመሆኑም ‹‹አሃ!›› ብያለሁ፡፡
ከተመስገን በጣም የገረመኝ፣ የማስታወስ ችሎታው ነበር፡፡ በጥቅምት ወር፣ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ‹‹ጥፋተኛ›› በተባለበት ማግስት ጥዋት አምስተኛ ፖሊስ ጣቢያ ልጠይወቅ ሄጄ በማያመች ሁኔታ ውስጥ ሆነን አብዮትን አስመልክቶ የተለዋወጥናቸውን ሃሳቦችን፣ እንዲሁም ከአቤል ጋር ቂሊንጦ ስንጠይቀው ያነሳናቸውን ሀሳቦች ድጋሚ በማስታወስ በዚህ ቀን ለተነሱት ርዕሰ ጉዳዮች የውይይት ማጠናከሪያ ሀሳብ ሲያደርጋቸው አስተውያለሁ፡፡
ለተመስገን አሁን ስለሚገኝበት ዞን ሁኔታ ጥያቄ አቀረብኩለት፡፡ ቀደም ሲል ከእነውብሸት ጋር አብሮ እንደነበረ ጠቅሶ፣ ‹‹የኢትዮጵያ ገመና›› በሚል ርዕስ በእስር ቤት ውስጥ ስላወቀው ነገር ሁለት ተከታታይ ጽሑፎችን ካወጣ በኋላ ወደዚህ ዞን መዘዋወሩን ይገልጻል፡፡ አሁን ባለበት ክፍል 80 የሚሆኑ እስረኞች አብረውት አሉ፡፡ ብዙዎቹ ከደቡብ ክልል የመጡ ናቸው፡፡ ከእሱ ጋር አንድም የፖለቲካ እስረኛም ሆነ ጋዜጠኛ አብሮት የለም፡፡ [አቶ በቀለ ገርባ ከወራቶች በፊት የ3 ዓመት ከ7 ወር የእስር ጊዜያቸውን አጠናቅቀው ከዝዋይ እስር ቤት በተፈቱ ማግስት ተመስገን ከባድ ወደሆነው ወደዚህ ዞን መሸጋገሩን ነግረውኝ ነበር] አሁን ባለበት ዞንም ከእሱ ጋር እስረኞች እንዳያወሩ እና እንዲያገልሉት በዘዴ ተደርጓል፡፡ ከእሱ ጋር በቅርበት ሆነው የሚያወሩ ካሉ፣ እንደትልቅ ተስፋ በሚጠብቁት አመክሯቸው ላይ እንደመፍረድ ይቆጠራል እንደተመስገን አባባል፡፡ ‹‹በዚህ ጉዳይ ማናቸውም ላይ አልፈርድም፤ ከእኔ ጋር አውርተው የአመክሮ ጊዜያቸውን እንዲያጡ አልሻም፡፡ ግን እንዲህ ያደረጉት ሌሎች የፖለቲካ እስረኞች ቢሆኑ ኖሮ ይሰማኝ ነበር፡፡›› ሲል ያለበትን ከባድ ሁኔታ ያስረዳል፡፡
‹‹ማንበብ፣ ማጸፍስ ትችላለህ?›› ሌላኛው ጥያቄዬ ነበር፡፡ ‹‹መጽሐፍ አይገባም ተልክሏል፤ ያነበብኳቸው ጥቂት ልብወለድ መጽሐፍቶች አሉ፡፡ መጻፍ ትንሽ ጀምሬ በእስረኞች በኩል ተጠቁሞ የጻፍኩት ተወሰደ፡፡ ሁለት ሶስቴ ለመጻፍ ሞክሬ ነበር፡፡ ግን ተመሳሳይ እርምጃ በመወሰዱ ተውኩት፡፡›› ይላል ተመስገን፡፡ ‹‹ቀኑን እንዴት ነው የምታልፈው?›› የሚለው የመጨረሻ ጥያቄዬ ነበር፡፡ ‹‹ሁለት የማውቃቸው የአዲስ አበባ ልጆች አሉ፤ ጫናውን ችለው ያናግሩኛል፡፡ ከእነሱ ጋር ቼዝ እጫወታለሁ፡፡ የእግር ኳስ ፕሮግራም የሚተላለፍባቸው ቻናሎች ቢኖሩም መገለሉን አስበውና ደስ ስለማይለኝ ወደክፍሌ እገባለሁ›› የሚለው የተመስገን መልስ ነበር፡፡
ተመስገን አቤልን ከርቀት አይቶት ‹‹ያ አቤል ነው አይደለ?›› አለኝ፡፡ ዞሬ አየሁት፣ አቤል ውብሸትን ጠይቆት ከርቀት ወደመውጪያው በር እየሄደ ነበር፡፡ ‹‹ግን እንዴት አስገቧችሁ?፤ ይመልሱ ነበር እኮ›› አለኝ፡፡ አቤልም ተመስገንን ተመስገንም አቤልን ማግኘት ፈልገው ነበር፡፡ ብዙም ሳይቆይ አቤል አንዱን ፖሊስ እንደምንም አናግሮ ተመስገንን ሊጠይቅ መጣ፡፡ ተቃቅፈው ተሳሳሙ፡፡ የሶስትዮሽ ጨዋታችንን ለግማሽ ሰዓት ያህል አደራነው፡፡ ተመስገን ከታሰረ በኋላ የግራ ጆሮው እንደማይሰማለት እና ወገቡም ሕክምና በማጣቱ አሁንም ድረስ እንደሚያመው አልሸሸገንም – ‹‹እዚህ ያለው መድኃኒት ፓናዶል ብቻ ነው›› በማለት፡፡ አያይዞም ‹‹ሰው መጥቶ ሲጠይቅህ ደስ ይላል፤ ጥሩ እንቅልፍ ትተኛለህ፤ግን የመንገዱን ርቀት ሳስበው ሰው ባይመጣ እላለሁ›› አለን በድጋሚ፡፡
የእስረኛ መጠየቂያ ጊዜ መጠናቀቁን ፖሊሶች ነገሩንና ተቃቅፎ መለያት ግድ ሆነ፡፡ ‹‹አይዞህ የምትባል አይደለህምና ሰላም ሁን›› አልኩት፡፡ ‹‹ምን መልዕክት አለህ?›› ስል የመጨረሻ ጥያቄዬን ሰነዘርኩለት፡፡ ተመስገንም ‹‹ታገሉ!›› ሲል መለሰና በመጣበት መንገድ ቻው ብሎን እርምጃውን ቀጠለ፡፡ ሲሄድ አራት እና አምስት ጊዜ ያህል ዞረን አየነው፡፡ ስለገኘነው ደስ ቢለንም በሳሮች መካከል ባለው መንገድ ወደታሰረበት ክፍል ሲያመራ ማየት ዳግመኛ የመረበሽ እና የማዘን ስሜት በውስጤ ፈጥሮብኝ ነበር፡፡ ስሜቱ በጣም የሚገባው በቦታው ላይ ሲገኙ ነው!
ተመስገን፣ ያመነበትን ሀሳብ በድፍረት ስለጻፈ ነበር በኢ-ፍትሃዊነት ሶስት ዓመት እስር የተፈረደበት፡፡ ሰው መታሰሩ ሳያንስ፤ ከቤተሰቡ፣ ከወዳጁ፣ ከዘመዱ፣ ከጓዳኞቹ እርቆ እንዲታሰር ማድረግ ሌላ ቅጣት ነው! ሰው መታሰሩ ሳያንስ፣ ህክምና መከልከሉ፣ በሌሎች እስረኞች እንዲገለል መደረጉ፣ መጽሐፍ ማንበብ እና የግል ማስታወሻዎቹን እንዳይጽፍ መከልከሉ ይሄም ሌላ ቅጣት ነው! ሰው ግን በስንቱ ይቀጣል?! እንዲህም ሆኖ፣ ትናንት የምናውቀው ጋዜጠኛ ተመስገን፣ አሁንም ድረስ ያ ያመነበትን የመናገር ድፍረቱ፣ መንፈሳዊ ብርታትና ጥንካሬው አብሮት አለ!!! አካል ቢታሰር ህሊና መቼም አይታሰር!!!
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!!!
Source ecadforum.com

No comments:

Post a Comment