ሐምሌ 12 2007 ዓ.ም.
ህወሓት በኢትዮጵያዊያን እና በኢትዮጵያ ላይ ያሰፈነው ዘረኛና ፋሽስታዊ አገዛዝ እንዲያበቃ፤ በምትኩም ፍትህ፣ ነፃነት፣ እኩልነትና ዲሞክራሲ የሰፈኑበት የፓለቲካና የኢኮኖሚ ሥርዓት እንዲመሠረት እና የሀገራችን አንድነት በጠንካራ መሠረት ላይ ለማኖር አርበኞች ግንቦት 7: የአንድነትና ዲሞክራሲ ንቅናቄ ተገዶ የገባበት የመረረ የአመጽ ትግል መጀመሩን ይፋ ማድረጉ ይታወቃል። በዚህም መሠረት ኢትዮጵያዊያን የነፃነት አርበኞች በጀግነትና በጽናት እየታገሉ ነው።
ይህ ትግል በባርነትና በነፃነት መካከል የሚደረግ ወሳኝ ትግል ነው። የዚህ ትግል ውጤት የእኛ የዚህ ዘመን ትውልድ ሕይወት ብቻ ሳይሆን የአገራችንን የወደፊት ታሪክ፤ የልጅ ልጆቻችንን ሕይወት ይወስናል። በዚህም ምክንያት ይህንን ትግል በድል መወጣት ግዴታችን ነው። በዚህ ወሳኝ ወቅት ለነፃነት ግድ ያለው ኢትዮጵያዊ ሁሉ ከጎናችን ሊቆም ይገባል።
አርበኞች ግንቦት 7 አመራሩን ሁኔታዎች በፈቀዱ መጠን እና ትግሉ በሚጠይቀው ቦታ እንዲገኙ የሚያደርግ መሆኑ ሲገልጽ ቆይቷል። አሁን ትግሉ በደረሰበት ደረጃ የአመራሩ በትግሉ ሜዳ ውስጥ መገኘት አስፈላጊ መሆኑ ታምኖበት ሊቀመንበሩን ጨምሮ አመራሩን ወደ ትግሉ ሜዳ አንቀሳቅሷል። በዚህም መሠረት የንቅናቄው ሊቀመንበር ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ወደ ትግል ሜዳ ወርዷል።
ትግሉ መሯል። ወሳኝ የሆነ ትግል ውስጥ ገብተናል። የትግሉ መሪዎች የሕይወት መስዋዕትነት እሚከፈልበት ቦታ ይገኛሉ። በአሁኑ ሰዓት የንቅናቄው አመራር በተሟላ ሁኔታ በትግሉ ሜዳ ውስጥ እንዲገኝ ማድረግ ተችሏል። ኢትዮጵያዊያን እጅ ለእጅ ተያይዘን ዘረኛው የህወሓት አገዛዝን ከጫንቃችን ለማስወገድ ቆርጠን እንድንነሳ አርበኞች ግንቦት 7 ጥሪ ያደርጋል።
ኢትዮጵያን ከህወሓት አገዛዝ ነፃ የሚያወጣው አርበኞች ግንቦት 7 ብቻ አይደለም። ስለሆነም ከሌሎች ድርጅቶች ጋር የሚደረገው ትብብር ቀዳሚ ትኩረት ከተሰጣቸው ሥራዎች አንዱ ነው። አርበኞች ግንቦት 7 ከሌሎች ኢትዮጵያዊያን ድርጅቶች ጋር በመተባበር የተቀጣጠለው ሕዝባዊ አመጽ ለድል እንዲበቃ ይታገላል። ኢትዮጵያዊያንም በያሉበትም በተመሳሳይ ልዩነቶቻቸውን አቻችለው በህወሓት ፋሽስታዊ አገዛዝ ላይ ክንዳቸውን እንዲያነሱ አርበኞች ግንቦት 7 ጥሪ ያደርጋል።
እነሆ የአርበኞች ግንቦት 7 ሊቀመንበር ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ በአካል ትግል ሜዳ ውስጥ ይገኛል። የሚችል ሁሉ እንዲከተል፤ መከተል የማይችል በያለበት ሁኖ ሁለገብ ትግሉን እንዲያጧጥፍ አርበኞች ግንቦት 7 ጥሪ ያደርጋል።
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!!
አርበኞች ግንቦት 7 ለአንድነትና ዴሞክራሲ ንቅናቄ
source www.patriotg7.org
No comments:
Post a Comment