ገንዘቡን ለፍትህና እኩልነት ለሚታገሉ ድርጅቶች እሰጣለሁ ብሏል
ባለፈው ወር መጨረሻ ላይ በእስራኤሏ ባት ያም ከተማ በፖሊስ የድብደባ ጥቃት የደረሰበት ኢትዮ-እስራኤላዊው ወታደር ዳማስ ፓካዳ፣ የተፈጸመብኝ ጥቃት ከዘረኝነት የመነጨ ነው ሲል በአገሪቱ ፖሊስ ላይ ክስ መመስረቱንና ለደረሰበት ጉዳት የ100 ሺህ ዶላር ካሳ እንዲሰጠው መጠየቁን “ታይምስ ኦፍ እስራኤል” ዘገበ፡፡የ19 አመት ዕድሜ ያለው ግለሰቡ ባለፈው ማክሰኞ በቴል አቪቭ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በአገሪቱ ፖሊስ ላይ በመሰረተው ክስ፣ ለደረሰበት ጉዳትና ጉዳዩን በህግ ለመከታተል ላወጣው ወጪ ካሳ እንዲሰጠው የጠየቀ ሲሆን፣ ጠበቃውም በግለሰቡ ላይ የተፈጸመው ጥቃት የአገሪቱ ፖሊስ በዜጎች ላይ በተደጋጋሚ የሚፈጽመውን ስነምግባር የጎደለውና ሃይል የተቀላቀለበት ጥቃት የሚያሳይ ነው ብለዋል፡፡
ግለሰቡ በፖሊሶች ጥቃት ሲፈጸምበት በካሜራ ባይቀረጽና ለማስረጃነት ባይቀርብ ኖሮ፣ ምናልባትም ፖሊስን በመድፈር ከባድ ወንጀል ተከሶ ሊቀጣ ይችል እንደነበር የገለጸው ክሱ፣ ጥቃቱ በግለሰቡ ላይ አካላዊና መንፈሳዊ ጉዳት ከማድረሱ ባሻገር የመላውን ኢትዮጵያዊ ቤተ እስራኤላዊ ልብ የሰበረ ነው ብሏል፡፡ ፓካዳ በፍርድቤት ተከራክሮ ካሸነፈና የጠየቀውን የገንዘብ ካሳ የሚያገኝ ከሆነ፣ የተወሰነ ያህሉን ገንዘብ ለፍትህና ለእኩልነት ለሚታገሉ የኢትዮጵያውያን ማህበረሰብ ድርጅቶች ለመስጠት ማሰቡን ተናግሯል፡፡
ሁለት የፖሊስ ባልደረቦች በግለሰቡ ላይ ጥቃት ሲፈጽሙ የሚያሳየው አጭር የቪዲዮ ምስል፣ በስፋት መሰራጨቱንና በቴል አቪቭ በሚኖሩ ቤተ እስራኤላውያን ዘንድ ከፍተኛ ቁጣና ተቃውሞ መፍጠሩን ተከትሎ፣ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታኒያሁና የፖሊስ ኮሚሽነሩ ዮሃናን ዳኒኖ ግለሰቡን በአካል አግኝተው ለተፈጸመበት ጥቃት በፖሊስ ስም ይቅርታ መጠየቃቸውና ከሁለት ሳምንታት በፊትም ጥቃቱን የፈጸመው አንደኛው ፖሊስ ከስራ መባረሩ ይታወሳል፡፡
ምንጭ አዲስ አድማስ ጋዜጣ
No comments:
Post a Comment