Sunday, May 31, 2015

ኢትዮ-እስራኤላዊው ወታደር የ100 ሺህ ዶላር ካሳ ጠየቀ

ገንዘቡን ለፍትህና እኩልነት ለሚታገሉ ድርጅቶች እሰጣለሁ ብሏል
 ባለፈው ወር መጨረሻ ላይ በእስራኤሏ ባት ያም ከተማ በፖሊስ የድብደባ ጥቃት የደረሰበት ኢትዮ-እስራኤላዊው ወታደር ዳማስ ፓካዳ፣ የተፈጸመብኝ ጥቃት ከዘረኝነት የመነጨ ነው ሲል በአገሪቱ ፖሊስ ላይ ክስ መመስረቱንና ለደረሰበት ጉዳት የ100 ሺህ ዶላር ካሳ እንዲሰጠው መጠየቁን “ታይምስ ኦፍ እስራኤል” ዘገበ፡፡የ19 አመት ዕድሜ ያለው ግለሰቡ ባለፈው ማክሰኞ በቴል አቪቭ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በአገሪቱ ፖሊስ ላይ በመሰረተው ክስ፣ ለደረሰበት ጉዳትና ጉዳዩን በህግ ለመከታተል ላወጣው ወጪ ካሳ እንዲሰጠው የጠየቀ ሲሆን፣ ጠበቃውም በግለሰቡ ላይ የተፈጸመው ጥቃት የአገሪቱ ፖሊስ በዜጎች ላይ በተደጋጋሚ የሚፈጽመውን ስነምግባር የጎደለውና ሃይል የተቀላቀለበት ጥቃት የሚያሳይ ነው ብለዋል፡፡
ግለሰቡ በፖሊሶች ጥቃት ሲፈጸምበት በካሜራ ባይቀረጽና ለማስረጃነት ባይቀርብ ኖሮ፣ ምናልባትም ፖሊስን በመድፈር ከባድ ወንጀል ተከሶ ሊቀጣ ይችል እንደነበር የገለጸው ክሱ፣ ጥቃቱ በግለሰቡ ላይ አካላዊና መንፈሳዊ ጉዳት ከማድረሱ ባሻገር የመላውን ኢትዮጵያዊ ቤተ እስራኤላዊ ልብ የሰበረ ነው ብሏል፡፡  ፓካዳ በፍርድቤት ተከራክሮ ካሸነፈና የጠየቀውን የገንዘብ ካሳ የሚያገኝ ከሆነ፣ የተወሰነ ያህሉን ገንዘብ ለፍትህና ለእኩልነት ለሚታገሉ የኢትዮጵያውያን ማህበረሰብ ድርጅቶች ለመስጠት ማሰቡን ተናግሯል፡፡
ሁለት የፖሊስ ባልደረቦች በግለሰቡ ላይ ጥቃት ሲፈጽሙ የሚያሳየው አጭር የቪዲዮ ምስል፣ በስፋት መሰራጨቱንና በቴል አቪቭ በሚኖሩ ቤተ እስራኤላውያን ዘንድ ከፍተኛ ቁጣና ተቃውሞ መፍጠሩን ተከትሎ፣ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታኒያሁና የፖሊስ ኮሚሽነሩ ዮሃናን ዳኒኖ ግለሰቡን በአካል አግኝተው ለተፈጸመበት ጥቃት በፖሊስ ስም ይቅርታ መጠየቃቸውና ከሁለት ሳምንታት በፊትም ጥቃቱን የፈጸመው አንደኛው ፖሊስ ከስራ መባረሩ ይታወሳል፡፡
ምንጭ አዲስ አድማስ ጋዜጣ

Wednesday, May 27, 2015

ፊታችንን ከምርጫ ፓለቲካ ወደ ሁለገብ ትግል እናዙር!- የአርበኞች ግንቦት 7 መግለጫ

ግንቦት 18 2007 ዓ.ም
ምርጫ 2007 ተጠናቆ ተወዳዳሪም አወዳዳሪም የሆነው ህወሓት ይፋ ውጤት እስኪገልጽ እየተጠበቀ ነው። ሁሉ በእጁ ነውና ባለሥልጣኖቹ ምን ዓይነት ውጤት እንደሚስማማቸው እስከሚነግሩን ጥቂት ቀናት ይወስዱ ይሆናል። ከፈለጉ ሁሉን የፓርላማ ወንበሮች ሊወስዷቸው ይችላሉ፤ ካሻቸው ደግሞ ጥቂቱን ለተቃዋሚዎች ሊሰጡ ይችላሉ። ወሳኞቹ እነሱ ናቸው። በዚህ የፓርላማ ወንበሮች እደላ የኢትዮጵያ ሕዝብ ድምጽ አንዳችንም ሚና የለውም።
ምርጫ የሕዝብ የሥልጣን ባላቤትነት ማረጋገጫ ከሆኑ አቢይ ዲሞክራሲያዊ ተቋማት አንዱ መሆኑ የታወቀ ነው። ሆኖም ግን ነፃ ተቋማት በሌሉበት፤ በአምባገነኖች አስፈፃሚነት የሚደረግ ምርጫ የመራጮች ነፃ ፍላጎት መግለጫ በመሆን ፋንታ የገዢዎች ሥልጣን ማረጋገጫ መሣሪያ ይሆናል፤ ከአገራችን እየሆነ ያለውም ይህ ነው።
የዘንድሮው ምርጫ 2007 ከዚህ በፊት ከነበሩ በባሰ ለአፈና የተጋለጠ የነበረ መሆኑ ከጅምሩ በግልጽ የታየ ጉዳይ ነበር። በአንድነትና በመኢአድ ፓርቲዎች ላይ አገዛዙ የወሰደው የግፍ እርምጃ የዚሁ የምርጫ ዘረፋ ስትራቴጂ አካል ነበር። ከዚያ በተጨማሪም መራጮች እውነተኛ ፍላጎታቸውን በነፃነት መግለጽ እንይችሉ ዘርፈ ብዙ ጫናዎች ሲደረግባቸው ቆይቷል። የተወዳዳሪ ፓርቲዎች አባላት እንደተፎካካሪ ሳይሆን እንደጠላት ሲሳደዱ፣ ሲታሰሩ፣ ሲደበደቡና ሲገደሉ ሰንብቷል። በምርጫው ሰሞንና በዕለቱ በተለይ ከተሞች በባዕድ ጦር የተወረሩ መስለው ነበር። ይህ ሁሉ ስነልቦናዊና አካላዊ ተጽዕኖ ታልፎ የተሰጠው ድምጽ ቆጣሪው ራሱ “ተወዳዳሪ ነኝ” ባዩ ህወሓት ነው።
በእንዲህ ዓይነት ምርጫ መሳተፍ ትርፉ “በሕዝብ ድምጽ ተመረጥኩ የማለትን እድል ለአምባገኑ ህወሓት መስጠት ነው”፤ “ለዓለም ዓቀፍ ማኅበረሰብም የተምታታ መልዕክት ማስተላለፍ ነው”፤ ”ለህወሓት ተጨማሪ ገንዘብ ማግኛና የኢትዮጵያን ሕዝብ መከራ ማራዘሚያ ነው“ በሚል በዚህ ምርጫ ላይ ማዕቀብ እንዲደረግ አርበኞች ግንቦት 7 ለኢትዮጵያ ሕዝብ ጥሪ ማድረጉ ይታወቃል። በርካታ ወገኖቻችን የምርጫ ካርድ ቢያወጡም የደረሰባቸውን ጫና ተቋቁመው በምርጫው ባለመሳተፍ ላሳዩት ጽናት አርበኞች ግንቦት 7 አድናቆቱን ይገልፃል።
ህወሓት በስልጣን ላይ እስካለ ድረስ የምርጫ ጉዳይ እና የምርጫ ፓለቲካ ግንቦት 7 ቀን 1997 ዓም የተጠናቀቀ ቢሆንም እንኳን ተጨማሪ ማስረጃ ለሚፈልጉ ግንቦት 16 ቀን 2007 መጥቶላቸዋል። አሁን ከፊታችን የተደቀነው ጥያቄ የሚከተለው ነው – አገራችን ከህወሓት አፈና ነፃ ለማውጣት ያለን አማራጭ መንገድ ምንድነው?
አርበኞች ግንቦት 7: የአንድነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ህወሓት ከኢትዮጵያዊያን ጫንቃ የሚወርደው ሕዝባዊ እምቢተኝነትና ሕዝባዊ አመጽን ባቀናጀ ሁሉገብ ትግል ነው ብሎ ያምናል። በዚህም መሠረት ለሁለቱም የትግል ዘርፎች ተስማሚ የሆኑ አደረጃጀቶችን አዘጋጅቷል።
ሕዝባዊ እምቢተኝነት፣ ታጋዩ ከመኖርያ ወይም ከሥራ ቦታው ሳይለቅ በህቡዕ የሚከናወን ትግል ነው። ሕዝባዊ አመጽ ደግሞ ከመኖሪያና ሥራ ቦታ ለቆ መንቀሳቀስን ይጠይቃል። ሁለቱም የትግል ዘዴዎች የህወሓትን ህጎች በመቃወም የሚደረጉ ናቸው። ሁለቱም የትግል ዘዴዎች ድርጅት፣ ዲሲሊንና ጽናትን ይጠይቃሉ። ለድላችን ሁለቱም የትግል ዘርፎች እኩል ዋጋ አላቸው። እናም ከዛሬ ጀምሮ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ እንደዝንባለውና አቅሙ በሚመቸው የትግል ዘርፍ ይሳተፍ። ሕዝባዊ ኃይልን መቀላቀል የቻለ ይቀላቀል፤ ያልቻለው በያለበት ተደራጅቶ በሕዝባዊ እምቢተኝነት ይታገል።
በየመኖሪያ ሠፈሩና በሥራ ቦታዎች የሚቋቋሙ የአርበኞች ግንቦት 7 ማኅበራት በርካታ ሥራዎች አሏቸው። ከሁሉ አስቀድሞ ድርጅትን ማጠናከር የሁላችንም ድርሻ መሆኑ ሊዘነጋ አይገባም፤ እናም ትኩረታችን እዚያ ላይ እናድርግ። እያንዳንዳችን ከሚመስሉንና ከምናምናቸው ጋር ተነጋግረን እንደራጅ፤ ወያኔ የሸረሸረብንን በራስ መተማመን እና የእርስ በርስ መተማመንን መልሰን እንገንባ። ውስጥ ውስጡን ጠንካራ አገራዊ ኅብረት እንፍጠር፤ የዕለት ተዕለት ተግባሮቻችን ደግሞ አካባቢያዊ ይሁኑ። ድርጅታችንን እያጠናከርን ወያኔን ከሁሉም አቅጣጫ እንሸርሽረው እንገዝግዘው። በዚህ መንገድ በሚደረግ ሕዝባዊ ትግል የሚገኝ ድል ፈጣን ከመሆኑን በላይ የድሉ ሕዝባዊነት ጥያቄ ውስጥ የማይገባ ይሆናል።
ስለሆነም እያንዳንዱ ለውጥ ፈላጊ ኢትዮጵያዊ ታጥቆ እንዲነሳ፤ ወደ ተግባራዊ ትግል ፊቱን እንዲያዞር አርበኞች ግንቦት 7 ጥሪ ያቀርባል።
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!!
የአርበኞች ግንቦት 7 መግለጫ
Source www.patriotg7.org

Tuesday, May 19, 2015

“ለውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ” ከአንዳርጋቸው ጽጌ እህት (ወ/ሮ ብዙአየሁ ፅጌ)

ይድረስ ለኢትዮጵያ ሕዝብ በኢትዮጵያ ውስጥም ሆነ ከኢትዮጵያ ውጭ እንዳሸዋ ተበትናችሁ የምትገኙ ወገኖቼ እኔ የተጎዳሁትን ያህል እናንተም የተጎዳችሁ መሆናችሁን በተለያዩ ሀገሮች በተደረጉ ሰልፎች ፤ የዉይይት መድረኮች ላይ በንዴት፤ በቁጭት እና በእልኸኝነት በእንባ ስትራጩ በመሃላችሁ ተገኝቼ ያየኻችሁ ሲሆን ይህም በጣም በኢትዮጵያዊነቴ እንድኮራ አድርጎኛል። አንዳርጋቸውም በወያኔ የጨለማ እስር ቤት እየከፈለ ያለውን መከራና መስዋትነት የትም እንዳልወደቀና እንዳልቀረ በማሰብ እጽናናለው።Letter from Andargachew Tige’s sister
ዛሬ አንዳርጋቸው ፅጌ በመላው ኢትዮጵያዊያን ዘንድ  “የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጅ“፤ “የኢትዮጵያ ልዩ አፈር“፤ “የኢትዮጵያ የበኩር ልጅ ” ወዘተ…. የሚሉ መገለጫዎችን እና መጠሪያዎችን የተጎናፅፈው ታናሽ ወንድሜ አንዳርጋቸው ፅጌ በእኔ እይታ ደግሞ የቤተሰባችን ልዩ ልጅ ነው።
አንዳርጋቸው የቤተሰባችን የመጀመረያ ወንድ ልጅ ስለነበረ ብርቅዬ መሆን  የጀመረው የካቲት 1 ቀን 1947 ዓ.ም አዲስ አበባ በሚገኘው ቀዳማዊ  ኃይለ ስላሴ ሆስፒታል ከእናታችን ከወ/ሮ አልታዬ ተሰማ  ሮቢ እና ከአባታችን ከአቶ ፅጌ  ሀብተማርያም ጨሜሳ ከተወለደ ቀን ጀምሮ ነው።
አንዳርጋቸው ለወላጅ አባታችን እና እናታችን፤ ለአያቶቻችን እና ለቅድመ አያቶቶቻችን ፤ ለእህቶቻን እና ለወንድሞቻችን ፤ ለዘመድ አዝማድ፤ ለአብሮ አደግ ጓደኞቹ በአጠቃላይ በአካባቢው ለነበሩት ዘመድ እና ወዳጅ ሁሉ ትልቅ እና ትንሽ ፤ ሐብታም እና ደሃ ፤ ወንድ እና ሴት ሳይል እንዲሁም በትምህርት ቤት አክብሮት እና ትህትና ሲያሳይ የኖረ ነው። የአንዳርጋቸው ሌላው ትልቁ እና አስገራሚው ስጦታዉ ወደር የማይገኝለት ትግስቱ ነው።
በቅርበት ከነበርው  አካባቢው ሰፋ ባለው ክልል ወስጥም ቢሆን አንዳርጋቸው ስለ ሀገሩ እና ስለኢትዮጵያ ህዝብ ክብር እና ደህንነት የነበርው የተቆርቋሪነት ስሜት ገና የአንደኛ ደርጃ ትምህርት ቤት ተማሪ ከነበረበት ዘመን የጀመረ ነበር። ለዚህም ነው ዛሬ “ለአንቺነው ነው ሀገሬ ” የሚል ግጥም ለገጠመላት የልጅነት ፍቅረኛው“ኢትዮጵያ” ሲል ልጆቹን ቤተሰቡን እና ጓደኞቹን ጥሎ የሀገርን ጥቅም እየነገደ  የቡድን ምቾትን እና ሀብትን በማካበት ላይ የሚገኘውን  የዘረኛ ባንዳ ወያኔ መንግስት በቁርጠኝነት ለመታገል የተነሳው።
አንዳርጋቸው  አገሩን  በበጎውም በክፉም ዘመን የሚያውቃት የ1960ቹ ትውልድ አካል በመሆኑ ነው፡ በዚህም በዚያም የተነሳ ይችን አገር ለማዳን የመጨርሻው ትውልድ እንደመሆኑ ይህንን አደራ ለመሸከም ታረክ የጣለበትን ሀላፌነት ከዚህ የመነጨ ነው ብዬ አስባለው ስለሆነም አንዳርጋቸው ቁጭ ብሎ ከመፅፅት በላይ እራሱን ለዚች አገር የመስዋት ጠቦት አድርጎ ማቅረቡና ታፍኖ ያለው ነጻነት ናፋቂው የኢትዮጵያ ህዝብም ይህንን ተረድቶ በልቡ መሀደር ላይ በክብር የጻፈው በመሆኑ ማንም ምድራዊ ሀይል ምንም አይነት ጥላሸት በመቀባት ሊቀይርው እንደማይችል ባለፉት 10 ወራት የታየው አብሮነት ትልቅ ምስክር ነው።
እነሆ! ይህ ጉዞው ዛሬ በወረበላው የየመን መንግስት ሹማምንት ተባባሪነት በጠላቶቹ እጅ እንዲወድቅ አድርጎታል። አንዳርጋቸው በጠላቶቹ  እጅ ከወደቀ አስርኛ ወራቶች በላይ ቢቆጠሩም  እስከ ዛሬ ድርስ  ከአረመኔዉ ወያኔ አፋኞች ውጭ እና ከፈጣረው በስተቀር የት ስፍራ በምን ሁኔታ እንደሚገኝ የሚያውቅ ሰው የለም።
አንዳርጋቸው በዚህ አይነት አሰቃቂ ሁኔታ ውስጥ መዉደቁ  ልቤ ውስጥ የተቀመጠ የእሳት ረመጥ ሆኖ በየቀኑ እያቃጠለኝ ቢገኝም  በሀገሬ ኢትዮጵያ ፤ ከአሜረካ እስከ ካንዳ ፤ከጃፓን እስክ ደቡብ ኮረያ፤ ከአዎሮፓ እስከ ደቡብ አፍረካ፤ ከአውስትራሊያ እሰከ እስራኤል እንዲሁም በተለያዩ የአርብ አገራት ባለው የአለማችን ስፋት ውስጥ የሚገኙ  ኢትዮጵያን ወገኖቼ ” እኔም አንዳርጋቸው ፅጌ ነኝ !” ፡ “ሁላችንም አንዳርጋቸው ፅጌ ነን” ብለው በመነሳት የወያኔን እና የተባባሪዎቹን  እብሪት፤ትዕቢት እና ህገወጥነትን ለማጋለጥ እያደረጉ ያለው ትግል ታላቅ መፅናናትን ይሰጠኛል።
አንዳርጋቸው የትናንሽ ልጆች አባት ከመሆኑ በላይ በተጨማሪ የ 85 ዓመት እድሜ ባለፅጋ የሆኑ አባታችን እዚያው ታፍኖ በተቀመጠበት ኢትዮጵያ ውስጥ ይኖራል። ከዚህ በተረፈ በጣም ከሚወዱት እና ከሚያፈቅሩት ከቅርብ ቤተሰቦቹ አልፎ አሁን ግን በአንዳርጋቸው የሀገር ፍቅር ፤ ለነጻነት ፤ ለፍትህ ፤ ለእኩልነት እና ለዴሞክራሲ የሚታገሉ በሚሊዮን የሚቆጠሩ አባት እና  እናቶች ፤ ወድም እና እህቶች ፤ ልጆች አፍርቶ ይገኛል።
ይችን አጭር ፅሁፍ ለመፃፍ ያነሳሳኝ ዋናው ምክንያት ለዚህ በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ቤተሰቤ ልባዊ ምስጋናዬን በአንዳርጋቸው ስም ለማቅረብ ነው። በዚህ ክፉ ጊዜ የታየው ቆራጥነት በወያኔ ታፍኖ የተወሰደው  ወንድማችንን ሙሉ ነጻነቱን እንዲሁም በወያኔ እስር ቤት እየማቀቁ ላሉት የነጻነት ታጋዮች እንዲሁም መብትና ነጻነቱን ተገፎ በሰፊዉ እስርቤት እየማቀቀ ላለው መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ትግሉን እንደሚቀጥል እና ከግቡ እንደሚያደርስ ባለ ሙሉ ተስፋ ነኝ።
በመጨርሻም ውድ ኢትዮጵያን ወገኖቼ አንዳርጋቸው እና እሱን የመሰሉ የነጻነት ታጋዮች እና የፖለቲካ መሬዎች ካለፍርድ በየስር ቤቱ በግፍ ታጉረው ላሉ ሁሉ እና ለቤተሰቦቻቸው ጭምር ፍጣሪ አምላካችን  ብርታቱን ይስጥልኝ። የመጨርሻውም ፍርድ የሚመጣው ከሱ ከእግዛብሄር ስለሆነ ይችን የምንወዳትን የጋራ ሀገራችንን ለመታደግ በጋራ የጀመርነውን በጋራ እንውጣው ስል በወያኔ ጭለማ እስር ቤት ውስጥ በሚሰቃዩት ወገኖች ስም እማፅናለው።
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!!!
ወ/ሮ ብዙአየሁ ፅጌ
Source http://ecadforum.com/Amharic/archives/15048/

መሸነፍን በአሸናፊነት የተቀበሉ መሪዎች

“ሕዝብን መታዘዝ ይገባል!”
በቅርቡ በሥልጣን ላይ እያሉ በምርጫ መሸነፋቸውን ባመኑበት ጊዜ ሥልጣናቸውን ያስረከቡት የናይጄሪያው ጉድላክ ዮናታን በአፍሪካ የ65 ዓመታት የምርጫ ዴሞክራሲ ጉዞ ከሚጠቀሱ ጥቂቶች መካከል አንዱ ሆነው ሰንብተዋል፡፡ ይህም ተግባራቸው በናይጄሪያ ብቻ ሳይሆን በመላው አፍሪካ ታላቅ ሥፍራ የሚሰጣቸው የፖለቲካ ሰው አድርጓቸዋል፡፡
በአፍሪካ በተካሄዱ በርካታ ምርጫዎች የሕዝብን ድምጽ በማክበር ሥልጣናቸውን ለተቀናቃኛቸው በማስረከብ የሕዝባቸውን ድምጽ ያከበሩ መሪዎች በጣም ጥቂቶች ናቸው፡፡ ሁሉንም ለአሁኑ ማቅረብ ባንችልም የተወሰኑት ተጠቃሾች እነዚህ ናቸው፡-
1. ኤደን አብዱላ ኦስማን ዳር (ሶማሊያ) – በተለምዶ ኤደን ዳር ተብለው የሚጠሩት እኚህ ፖለቲካኛ የሶማሊያ የመጀመሪያው ፕሬዚዳንት ነበሩ፡፡ በሥልጣን በነበሩበት ጊዜ ሶማሊያን እኤአ ከ1960 እስከ 1967 መርተዋል፡፡ (በዚህ ጽሁፍ ላይ የሰፈሩት ዓመታት በሙሉ እኤአdaar ነው)
የሶማሊያ ወጣት ሊግ አባል በመሆን የፖለቲካ ጉዟቸውን የጀመሩት ዳር አገራቸው በ1960 ነጻነቷ ስትጎናጸፍ ስመጥር እየሆኑ በመምጣታቸው የሶማሊያ የመጀመሪያው ፕሬዚዳንት በመሆን ተመርጠው ለ7 ዓመታት አገልግለዋል፡፡ ሆኖም በ1967 በተደረገ ምርጫ በቀድሞው ጠ/ሚ/ር አብድራሺድ አሊ ሸርማርክ ተሸንፈው ሥልጣናቸውን በጸጋ አስረክበዋል፡፡ በዚህም በዴሞክራሲያዊ መንገድ ለተመረጠ መሪ ሥልጣን በማስረከብ ከአፍሪካ የመጀመሪያ ተብለው ከሚጠቀሱት አንጋፋው በመሆን ታሪክ ሠርተዋል፡፡
2. ኬነት ዴቪድ ካውንዳ (ዛምቢያ) – ከነጻነት በኋላ ኬነት ካውንዳ የአገራቸው የመጀመሪያ ፕሬዚዳንት በመሆን ከ1964 እስከ 1991 መርተዋል፡፡ አገራቸው ከእንግሊዝ ቅኝ ነጻ ለመውጣት ባደረገችው ትግል ቀዳሚውን ሥፍራ በመያዝ የታገሉት ካውንዳ በሥልጣን ዘመናቸው የተቀናቃኝ ፖለቲካ ፓርቲዎችን በሙሉ አግደው የራሳቸው ፓርቲ ብቻ እንዲንቀሳቀስ ማድረጋቸው በታሪካቸው የሚነሳ አንዱ አሉታዊ ጉዳይ ነው፡፡
ሆኖም እኤአ በ1970ዎቹ በተከሰተው የነዳጅ ዘይት ቀውስ ጋር በተያያዘ የዛምቢያ ኢኮኖሚ ከፍተኛ ችግር ውስጥ በመግባቱ በካውንዳ አገዛዝ ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድር መስሎ ቢታይም በተቃራኒው ፕሬዚዳንቱ በሥልጣን እንዲቆዩ ምክንያት ነው የሆናቸው፡፡ በሌላ ጎኑ ይኸው ቀውስ ውሎ አድሮ የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት በአገሪቷ እንዲጀመርና ዛምቢያ ወደ ነጻ ምርጫ እንድትደርስ አድርጓታል፡፡Kaunda
በ1991 በተካሄደ ምርጫ የካውንዳ ተቀናቃኝ ሆነው የተወዳደሩት ፍሬዴሪክ ቺሉባ አሸናፊ ሆኑ፡፡ በዚህ ወቅት ካውንዳ የወሰዱት እርምጃ ዓለምን አስደመመ፤ አስደነቀ! ኬነት ካውንዳ ገና ከጅምሩ ምርጫውን ማጭበርበር ይችሉ ነበር፤ አላደረጉም፡፡ በወቅቱ በሥልጣን ላይ የነበሩ በመሆናቸው የምርጫውን ውጤት ወደፈለጉት አቅጣጫ እንዲሄድ ማድረግ ይችሉ ነበር፤ ይህንንም አላደረጉም፡፡ ከዚህ ይልቅ በምርጫ መሸነፋቸውን አምነው ተቀበሉ፤ ሥልጣናቸውን ሕዝብ ለመረጣቸው ቺሉባ አስረከቡ፤ ሕዝባቸውን አከበሩ፤ አገራቸውን ታደጉ!
3. ሩፒያ ብዌዛኒ ባንዳ (ዛምቢያ) – ኬነት ካውንዳ በጀመሩት የምርጫ ዴሞክራሲ ፈር ተከትለው ሥልጣን የያዙት መሪዎች በሥልጣን ላይ እያሉ በምርጫ ሲሸነፉ ሥልጣናቸውን ለማስረከብ ብዙም ሲቸገሩ አልታዩም፡፡ ምክንያቱም የካውንዳ ራዕይና ውርስ (ሌጋሲ) ለትውልድ የሚተላለፍ በመሆኑ ነው፡፡
በመሆኑም ዛምቢያን ከ2008 እስከ 2011 በፕሬዚዳንትነት የመሯት ባንዳ በ2011 በሥልጣን ላይ እያሉ በተደረገ ምርጫ ሲሸነፉ ለሕዝብ ድምጽ አክብሮት በመስጠት ሽንፈታቸውን በጸጋ በመቀበል መደበኛ ኑሯቸውን ጀምረዋል፡፡ በካውንዳ ዘመን የተለያዩ ዲፕሎማሲያዊ ተግባራት ሲያከናውኑ የኖሩት ባንዳ እስከ ምክትል ፕሬዚዳንትነት ደርሰው ነበር፡፡ በወቅቱ r bandaዛምቢያን ይመሩ የነበሩት ፕሬዚዳንት ሌቪ ምዋናዋሳ በድንገት በደረሰባቸው የጤና መታወክ ባንዳ ቦታቸውን ተክተው ሠርተዋል፡፡ ወዲያውኑ በተደረገ ምርጫ ባንዳ በጠባብ ውጤት በማሸነፍ የመሪነቱን ሥልጣን በይፋ ተቆጣጠሩት፡፡
ሩፒያ ባንዳ በምርጫ ተሸንፈው ሥልጣናቸውን ለተቀናቃኛቸው እንደሚለቁ ባስታወቁበት ሽንፈትን የመቀበያ ንግግር የዛምቢያ ሕዝብ በዴሞክራሲዊ መንገድ ሃሳቡን መግለጹን ጠቁመውሕዝብን መታዘዝ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ ሲቀጥሉም “ጊዜው አሁን አርቆ የማሰብ፣ የመረጋጋትና የርኅራኄ ነው፤ ለአሸናፊዎች ይህንን ልበል፡ ያገኛችሁትን ድል በደስታ የማክበር መብት አላችሁ ግን በቸርነትና በበጎነት አድርጉት፤ እያንዳንዱን ሰዓት ተደሰቱበት፤ ነገር ግን የመንግሥት ሥልጣን ዓመትን ጠብቆ የሚያበቃ መሆኑን አስታውሱ”፡፡
4. አብዱ ዲዩፍ (ሴኔጋል) – ወደ ሥልጣን ሲመጡም ሆነ ሲለቁ በሰላማዊ መንገድ ያጠናቀቁ ሁለተኛው የሴኔጋል ፕሬዚዳንት አብዱ ዲዩፍ ናቸው፡፡ የኮሌጅ ትምህርታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ በተለያዩ የመንግሥት መ/ቤቶች በኃላፊነት በማገልገል በአጭር ጊዜ ውስጥ በወቅቱ ፕሬዚዳንት የነበሩት ታዋቂው ሊዎፖልድ ሴዳር ሴንግሆር ካቢኔ ዳይሬክተር ሆኑ፡፡ ቀጥሎም ወደ ጠቅላይ ሚኒስትርነት ማዕረግ በማደግ ሴንግሆር ሥልጣን ሲለቁ ፕሬዚዳንት ሆኑ፡፡Abdou-Diouf1
በሴኔጋል በተደጋጋሚ በተካሄዱ ምርጫዎች ያሸነፉት ዲዩፍ የተቀናቃኝ ፖለቲካ ፓርቲዎችን ለማዳከም ሲሉ ፓርቲዎች በቁጥር በዝተው በኅብረት ተዳክመው ምርጫ እንዲወዳደሩ ማስደረጋቸው፤ ተቀናቃኝ ፓርቲዎች ጥምረት እንዳይፈጥሩ በሕገመንግሥት ማስከልከላቸው (በኋላ ቢፈቀድም) የሚወቀሱበት ጉዳይ ነው፡፡ ሆኖም የረጅም ጊዜ ተቀናቃኛቸው አብዱላያ ዋድ በ2000ዓም በተደረገ ምርጫ በሁለተኛ ዙር በተደረገ ቆጠራ ሲያሸንፏቸው ሥልጣናቸውን አስረክበዋል፡፡ ባላንጣቸው ዘንድ ስልክ በመደወል እንኳን ደስ አለዎት ባሉበት ወቅት ፕሬዚዳንትነት “ታላቅ ኃላፊነት የሚጠይቅ መሆኑን በመጥቀስ መልካሙን ሁሉ እመኝልዎታሁ” ብለዋቸዋል፡፡ የ74 ዓመቱ ዋድ የተወዳደሩበት የተቃዋሚ ፓርቲዎች ጥምረት “ቅንጅት 2000 ለለውጥ” የሚባል ነበር፡፡
5. አብዱላያ ዋድ (ሴኔጋል) Wadeአብዱ ዲዩፍን አሸንፈው የሴኔጋል ሦስተኛ ፕሬዚዳንት የሆኑት ዋድ ከ12 ዓመት የፕሬዚዳንትነት ቆይታ በኋላ በ2012 በተደረገ ምርጫ በተቀናቃኛቸው ተሸንፈው መንበሩን አስረክበዋል፡፡ በሥልጣን ዘመናቸው በርካታ አወዛጋቢ ክስተቶች የነበሩና እርሳቸውም በዚህ የሚወነጀሉ ቢሆንም የአብዱ ዲዩፍን ሌጋሲ (ውርስ) ተግባራዊ በማድረግ እውነተኛ “መተካካት” በአገራቸው ፈጽመዋል፡፡
6. ጉድላክ ዮናታን (ናይጄሪያ) - በሰሞኑ ምርጫ ባልተጠበቀ ሁኔታ ሥልጣናቸውን በምርጫ ላሸነፏቸው ሙሃማዱ ቡሃሪ አስረክበው ተሰናብተዋል፡፡ ዮናታን በሥልጣን ቆይታቸው የሚወቀሱበት በርካታ ጉዳዮች ቢኖሩም ይህgoodluck Jየሕዝብን ድምጽ የማክበራቸው ጉዳይ ግን የቡሃሪ ደጋፊዎችን ያስደሰተ፤ ምዕራባውያንን አፍ ያስዘጋ፣ አምባገነኖችን ያስደነገጠ፣ ምርጫ ሲመጣ “ሥራ የሚበዛባቸውን” “በእኛ አገር ይህ አይሆንም” ያስባለ ሲሆን “ዮናታን ያሸንፋል” በማለት “ታይቶኛል፣ ተገልጾልኛል፣ ተከስቶልኛል፣ …” በማለት የተናገሩ የሃይማኖት መሪዎችንና ጠንቋዮችን ያሳፈረ ነው፡፡
ኢህአዴግ አካሂደዋለሁ ብሎ ካወጀው ምርጫ አኳያ ለአብነት ያህል በመጥቀስ ለትምህርት እንዲሆን አቀረብነው እንጂ በሥልጣን ላይ እያሉ በምርጫ ተሸንፈው ሥልጣናቸውን በማስረከብ የሕዝብን ድምጽ ያከበሩ መሪዎች በደቡብ አፍሪካ፣ በቤኒን፣ በኬፕ ቬርዴ፣ ወዘተ ይገኛሉ፡፡
ድል የሚገኘው በማሸነፍ ብቻ ሳይሆን በመሸነፍም ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ ሽንፈት በቃል ሽንፈት ተብሎ ቢጠራም ዋናው ትርጉሙ የሕዝብን ድምጽ ማክበር ነው፡፡ አንድ ፓርቲ የፈለገውን ያህን አገዛዙ ዴሞክራሲያዊ፣ “መሪው ባለራዕይ”፣ አካሄዱ “ልማታዊ”፣ ርዕዮቱ “አብዮታዊ”፣ ዕቅዱ “ሕዳሴያዊ”፣ … ቢሆንም የማብቂያ ጊዜ (date of expiration) ሊኖረው ይገባል፤ አለበለዚያ መልካም አስተዳደር እንኳን ቢሆን ይሰለቻል፡፡ ስለዚህ ሕዝብ ለውጥን ይሻል፤ ሕዝብ ይናገራል፤ ሕዝብ ተናግሮ ድምጹን ሲያሰማ ማድመጥ ከውድመት ያድናል፤ ሩፒያ ባንዳ እንዳሉት “ሕዝብን መታዘዝ ይገባል”!

Friday, May 15, 2015

አይሲስን ስንቃወም ህወሓትን አለመርሳት!

May 13, 2015
በአይሲስ በግፍ በታረዱብን ወገኖቻችን የተሰማን ሀዘንና ቁጭት ከፍተኛ ቢሆንም እንኳን ከአዕምሮዓችን መውጣት የሌለበት ሀቅ አለ። ይህ ሀቅ “ያስጠቃን፣ ያሳረደን ወያኔ ነው” ከሚለውም ያለፈ ነው። መረሳት የሌለበት ሀቅ፣ ከአይሲስ የከፋ ጨካኝ በአገራችን የመንግሥት ሥልጣን የተቆጣጠረ መሆኑ ነው።
የህወሓት ፋሽስት ጦር በበደኖ፣ በአዋሳ፣ በሀረር፣ በጋምቤላ፣ በጎንደር፣ በኦጋዴን፣ በአዲስ አበባ፣ በሸካና መዠንገር፤ እንዲሁም በሚታወቁም በማይታወቁም የማሰቃያ እስር ቤቶች አይሲስ እየፈፀመ ካለው የባሱ ወንጀሎች በወገኖቻችን ላይ ፈጽሟል፤ አሁንም እየፈፀመ ነው። ባሳለፍነው ሣምንት እንኳን በሁመራ ወገኖቻችን የራሳቸውን መቀበሪያ ጉድጓድ ቆፍረው በጅምላ ተገድለዋል። በአይሲስና በህወሓት መካከል ያለው ልዩነት አይሲስ ነውረኛና አረመኔዓዊ ተግባሩን በቪዲዮ እየቀረፀ ለዓለም ሲበትን ህወሓት ግን እነዚሁኑ ነውረኛና አረመኔዓዊ ተግባሮችን እየፈፀመ መረጃዎች አፍኖ መያዙ ብቻ ነው። ከዚህ ውጭ ግን ህወሓት ሰዎችን ከነሕይወታቸው ጉድጓድ ውስጥ የቀበረ አረመኔ፣ እኩይ ድርጅት ነው።
ስለሆነም ለዓለም ሰላም ስጋት የሆነውን አይሲስን ስንቃወም የራሳችንን አይሲስ – ህወሓትን – አለመርሳት እጅግ አስፈላጊ ነገር ነው።
በሌላ በኩል ደግሞ ህወሓት፣ የአይሲስን እኩይ ተግባራት ከኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች የመብት ጥያቄ ጋር እና ከዲሞክራሲያዊያዊ ፓለቲካ ፓርቲዎች እንቅስቃሴ ጋር ለማገናኘት እያደረገ ያለው ጥረት ምን ያህል አደገኛ ተግባር እንደሆነ የኢትዮጵያ ሕዝብ እንዲረዳው ያስፈልጋል። ዓይን አውጣ ሌባ ንፁሁን ሰው “ሌባ” እንደሚለው ሁሉ የኛው አይሲስ ራሱን ንፁህ አስመስሎ ሌሎችን “አይሲስ” ማለቱ ሊነቃበት ይገባል።
ሌላው ተያያዥ ጉዳይ ደግሞ ስለስደተኝነት የሚሰጠው ገለፃ ነው። ህወሓት ለስደተኝነት ምክንያቱ ደላሎች እንደሆኑ ይናገራል። ይህ የጉዳዩን ግንድ ትቶ ቅርንጫፎች ላይ ማትኮር ነው። ህገወጥ ደላሎች ራሳቸው ሊኖሩ የቻሉት ገንዘብ ከፍለውና የሕይወት ሪስክ ወስደው ለመሰደድ የሚፈልጉ ዜጎች በመኖራቸው ነው። ችግሩን በቅንነት ለመመርመር የሚፈልግ “ይህን ያህል ሰው የሕይወት ሪስክ እየወሰደ ከአገር ለመሰደድ ምን አነሳሳው?” ብሎ መጠየቅ እና ምላሽ ማግኘት ይኖርበታል። በሀገር ውስጥ በነፃነት ተረጋግቶ መኖር፣ ሠርቶ የማደግ ተስፋ ቢኖር ኖሮ ይኸን ያህል ሰው የአደጋውን ከፍተኛነት እያየ ለመሰደድ ይነሳሳ ነበርን? ኢትዮጵያዊው ከስደት ሊያገኝ የሚሻው ምንድነው? እንደ ወያኔ ካድሬዎች ገለፃ ከሆነ ከስደት ሊያገኝ የሚችለው አገሩ ውስጥ እያለለት ነው ኢትዮጵያዊ የሚሰደደው። ይህ ምን ዓይነት አመክኖ ነው? ከዚህ የባሰው ደግሞ ስደትንም የእድገት ውጤት አድርጎ የማቅረብ በሽታ ነው። ይህ እውነት ከሆነ፤ ህወሓት ለኢትዮጵያ አመጣሁላት የሚለው እድገት ውጤት ረሀብ፣ ስደት፣ መርዶ፣ እስር፣ ስቃይ፣ ሞት ከሆነ እንዴት “እድገት” ብለን እንጠራዋለን። ለስደተኝነት መብዛት ህገወጥ ደላሎችን ብቻ ተጠያቂ ማድረግ፤ “እኔ ከደሙ ንፁህ ነኝ” የማለት ያህል ነው። በህጋዊዎቹም በህገወጦቹም ደላሎች ውስጥ የወያኔ ሰዎች በቀጥታም በተዘዋዋሪም እንዳሉበት መረጃዎች ያመለክታሉ። ገንዘብ ባላበት ሁሉ የወያኔ እጅ መኖሩ ፀሐይ የሞቀው ሀቅ ነው። የሰዎች ዝውውር የህወሓት አንዱ ከፍተኛ የገቢ ምንጭ መሆኑ የማይታበል፤ በቀላሉ ማረጋገጥ የሚቻል ሀቅ ነው።
አርበኞች ግንቦት 7: የአንድነትና ዲሞክራሲ ንቅናቄ፣ በዓለም አቀፉ አይሲስ አረመኔያዊ ተግባሮች በደረሰብን የመጠቃት ስሜት ተውጠን የራሳችንን አይሲስ – አረመኔውን ህወሓት – እንዳንረሳ ያሳስባል። መቆሚያው ለማይታየው የዜጎቻችን መሰደድ መንስኤዎች የነፃነት እጦት እና የኑሮ እድሎች መጥበብ መሆናቸው እንዳንዘነጋ ይጠይቃል። ንቅናቂያችን እነዚህ ተያያዥ ችግሮች ሁሉ የሚቃለሉት ህወሓትን አስወግደን በምትኩ ፍትህ፣ ነፃነት፣ እኩልነትና ዲሞክራሲ የሰፈኑባት ኢትዮጵያን ስንመሰረት ብቻ ነው ይላል። ለዚህም ደግሞ ሁላችንም በያለንበት የበኩላችንን ተሳትፎ ማድረግ ይገባናል። ሁለገብ ትግል ማለት፤ እያንዳንዱ ከሚመስለው ጋር እየተደራጀ በያለበት ወያኔ ማስጨነቅ፣ ማዋከብና ማዳከም፤ በመጨረሻም በጋራ ትግል ማስወገድ ማለት እንደሆነ ልብ እንበል። በሁለገብ ትግል ለውጥ የሚመጣው ሁሉም እንደ አቅሙ
በሚያደርገው ተሳትፎ በመሆኑ፣ የሚቻለንን በማድረግ የለውጥ ጠባቂ ሳንሆን፣ የለውጥ አምጭ አካል እንሁን ይላል።
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!
Source www.patriotg7.org

Friday, May 8, 2015

ምርጫው አዲስ “ጠቅላይ ሚ/ር” አግኝቷል

“የተለቀቁት ኢትዮጵያውያን መሆናቸውን እናጣራለን?” ኢህአዴግ
በሊቢያ ታፍነው የነበሩ ወደ 30 የሚጠጉ ኢትዮጵያውያን በግብጽ ጦር ኃይል ነጻ አውጪነት መለቀቃቸውን የግብጽ መንግሥት አስታወቀ፡፡ የግብጹ ፕሬዚዳንት አልሲሲ የተለቀቁትን ኢትዮጵያውያን አውሮፕላን ማረፊያ ድረስ በመገኘት አቀባበል አደረጉላቸው፡፡ ኢህአዴግ እንደተለመደው “የተለቀቁት ኢትዮጵውያን መሆናቸውን አጣራለሁ” እንደማይል ተገምቷል፡፡ “ተይዘን የነበረው በሊቢያ የኢሚግሬሽን ባለሥልጣናት ነበር” ከተለቀቁት አንዱ ኢትዮጵያዊ፡፡
በተለያዩ የዓለም መገናኛ ብዙሃን ሐሙስ በተሰራጨው የዜና መረጃ መሠረት በሊቢያ ደርና እና ምስራታ በተባሉ ከተሞች ታፍነው የነበሩ 30 የሚደርሱ ኢትዮጵያውያን በግብጽ ጦር ኃይል እና በሊቢያ ድጋፍ ነጻ መለቀቃቸው ተሰምቷል፡፡
ዜናውን ከካይሮ አውሮፕላን ማረፊያ የግብጽ የዜና አውታሮች በቀጥታ ለአገራቸውና ለዓለም ሕዝብ እንዲሰራጭ አድርገውታል፡፡ ኢትዮጵያውያኑን የጫነው የምስር (አልምስሪያ) አውሮፕላን መሬት ሲነካ ከፓይለቱ ክፍል አካባቢ የግብጽ ሰንደቅ ሲውለበለብ ተመልክቷል፡፡ ቀጥሎም የተለቀቁት ከአውሮፕላኑ ከመውጣታቸው በፊት የግብጹ ፕሬዚዳንት አብደል ፈታህ አልሲሲ እስኪመጡ እንዲጠብቁ ተደረገ፡፡ እርሳቸውም እንደደረሱ ኢትዮጵያውያኑ የግብጽን ሰንደቅ እያውለበለቡ ሲወጡ ፕሬዚዳንቱ እያንዳንዳቸውን “እንኳን ለምስር አፈር አበቃችሁ” በሚል ፈገግታ እየጨበጡ ተቀብለዋቸዋል፡፡
ከጥቂት ሳምንታት በፊት ኢትዮጵያውያን በግፍ ከታረዱ በኋላ በዚያ ስለሚገኙት ኢትዮጵያውያን ወንድሞቻችን ሁኔታ ግብጽ በጥልቀት ስታስብ ነበር፤ ለዚህም ነው እነዚህ ኢትዮጵያውያን ወንድሞቻችን ወደቤታቸው እንዲመለሱ በጣም ጥረት ስናደርግ የነበረው” በማለት የቀድሞው የጦር ጄኔራል አልሲሲ እዚያው አየር ማረፊያው የተለቀቁትን ኢትዮጵያውያን ከኋላቸው አድርገው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አስረድተዋል፡፡
ይኸው ከሳምንታት በፊት በኢትዮጵያውያን ላይ የደረሰው አሰቃቂ ግድያ እጅግ ያሳመማቸው መሆኑን የተናገሩት ፕሬዚዳንቱ እነዚህን ኢትዮጵያውያን በህይወት አስለቅቆ ወደ ግብጽ ለማምጣት የተፈለገው ጥረት ሁሉ መደረጉን በንግግራቸው ገልጸዋል፡፡ “የግብጽ (የጦር ሠራዊትና የደኅንነት) አገልግሎቶች በዚህ ኢትዮጵያውያን ወንድሞቻችን በመከላከል፣ በማዳንና በማስለቀቅ ተግባር ተሳትፈዋል” ያሉት ፕሬዚዳንቱ “በሊቢያ የሚከሰተው ነገር ሁላችንንም ይመለከተናል” ብለዋል፡፡
ዜናው እንደተሰማ ለጎልጉል አስተያየታቸውን የሰጡ እንዳሉት “ከመጪው ምርጫ አኳያ ይህ የግብጽ ተግባር እና የፕሬዚዳንቱ ቁርጠኝነት እንዲሁም ደመላሽነት አብዱል ፈታህ አልሲሲ በመጪው ምርጫ ጠቅላይ ሚኒስትራችን ቢሆኑ ሳይሻል የሚቀር አይመስለኝም” በማለት ከአዲስ አበባ አካባቢ በላኩት ዋዛ አዘል መልዕክት አስታውቀዋል፡፡
የወገኖቻችን አሰቃቂ ግድያ እንደተሰማ “ኢትዮጵያውያን መሆናቸውን እያጣራን ነው” በማለት ሲያላግጥ የነበረው ኢህአዴግ ሦስት ቀን “ብሔራዊ ሃዘን” በማለት ቢያውጅም ከአንድ ቀን በላይ መቀጠል አለመቻሉ ብዙዎችን ያጠያየቀ ጉዳይ ሆኗል፡፡ ከዚህም ሌላ ደርግን “በጦርነትና በጀግንነት” አሸንፈን “ነጻ አወጣን”፣ “ተራራ ያንቀጠቀጠ ትውልድ” ነን የሚለው ህወሃት “ካስፈለገም ጦርነትን እንሰራለን” ሲል እንዳልኖረ ሁሉ 30ኢትዮጵያውያን በግፍ ከታረዱ በኋላ ምንም ዓይነት የጀግንነት፣ የአርበኝነት ወይም የጦረኝነት ምላሽ ቢያንስ እንኳን ለማሳየት አለመቻሉ ከመጀመሪያውኑ ባዶ ጀግንነት የተሸከመ በምዕራባውያን ድጋፍ የራሱን ወገን በመሸጥ ሥልጣን ላይ የተቀመጠ፤ ኢትዮጵያዊነት ስሜት፣ ኩራትና ወኔ የሌለው በከንቱ ጀብዱ የተሞላ ባዶውን የቀረ ቀፎ ድርጅት መሆኑን አስመስክሯል፤ ለዚህም ነው ለሃዘን የወጣው ሰልፈኛ “ያገር አንበሳ የውጭ ሬሳ” ብሎ የፈከረው በማለት ብዙዎች ለጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ አስተያየታቸውን ሲሰጡ ከርመዋል፡፡
ከዚህ ዜና ጋር በተያያዘ የግብጽ ሚዲያ ኢትዮጵያውያኑ ከታፈኑበት ተለቀቁ ቢልም ከተፈቱት መካከል አስተያየቱን የሰጠ አንድ ኢትዮጵያዊ እንደተናገረው ተይዘው የነበረው በሊቢያ የጸረ ሕገወጥ ኢሚግሬሽን አካል እንደነበረና የግብጽ መንግሥት መጥቶ እንዳስለቀቃቸው ተናግሯል፡፡
ከፕሬዚዳንት አልሲሲ ጽ/ቤት የተለቀቀው መረጃ እንደጠቆመው ፕሬዚዳንት ሲሲ “የመጀመሪያውን ዙር ከሊቢያ ተመላሽ ኢትዮጵያውያን ወንድሞችን” መቀበላቸውንና ይህም በቀጣይነት የሚካሄድ ዘመቻ መሆኑን አመላክቷል፡፡
Source (http://www.goolgule.com)

Wednesday, May 6, 2015

የቁልቁለቱን ጉዞ እናስቁም፤ ውርደት ይብቃን!!!

የህወሓት አገዛዝ ፋሽስታዊ ባህርያት እያደር መረን እያጣ፤ ነውረኛ እየሆነ መጥቷል። በአሳለፍነው ሣምንት ብቻ እንኳን አስነዋሪ ይዘት ያላቸው ሁለት ፋሽስታዊ ክስተቶችን አስተውለናል።
አንዱ በምርመራ ስም በታሳሪዎች ላይ የሚደረገው አሳፋሪ ሰቆቃ ነው። በገላቸው በሚያፌዙና በሚሳለቁ ተቃራኒ ፆታ መርማሪዎች ፊት ለሰዓታት ተመርማሪዎች ራቁታቸውን እንዲሆኑ የሚደረግበት እና እየተፌዘባቸው የሚደበደቡበት ሥርዓት መኖሩ የጉዳቱ ሰለባዎች ይፋ ሲያወጡ እፍረቱ ለመርማሪዎቹ ብቻ ሳይሆን ይህንን ጉድ ተሸክመን ለኖርነው ኢትዮጵያዊያን ሁሉ ነው። በተለይም ደግሞ እንዲህ ዓይነት ክብረነክ ሰቆቃ በሴቶች ላይ እየተፈፀመ መሆኑን ስንሰማ አገራዊ ውርደቱ ያሸማቅቀናል። እንዲህ ዓይነቶችን በሰው ስቃይና እፍረት የሚዝናኑ ጉዶችን ተሸክመን የምኖር መሆናችን ሁላችንን ያዋርደናል። ይህንን አስነዋሪ “የምርመራ ዘዴ” ያጋለጡት የዞን 9 ብሎገሮች፣ ጋዜጠኞችና ፓለቲከኞች ክብርና ሞገስ የሚገባቸው ጀግኖች ሲሆኑ የተዋረዱት እነሱ ሳይሆኑ እኛ ኢትዮጵያዊያን መሆናችን ሊሰማንና “ውርደት በቃ” ልንል ይገባናል።
ሁለተኛው አሳፋሪ ድርጊት ደግሞ ወገኖቻችንን በግፍ ባረደው አይሲስ በተሰኘው አሸባሪ ድርጅት ላይ የህወሓት አገዛዝ የተለሳለሰ አቋም ወስዷል ብለው ራሱ ህወሓት በጠራው ሰልፍ ላይ ተቃውሞዓቸውን ባሰሙ ወጣቶች ላይ አገዛዙ የወሰደው የኃይል እርምጃና ከዚያም ወዲህ እየተደረገ ያለው ነገር ነው። አገዛዙ ለፕሮፖጋንዳው ይጠቅመኛል ብሎ በጠራው ሰልፍ ወጥተው ተቃውሞዓቸውን የገለፁ ወጣቶች በአሰቃቂ ሁኔታ ተደብድበዋል፤ በጅምላ ወደ እስር ቤቶች ተግዘዋል። የአገዛዙ ካድሬዎች ወገኖቻችንን የፈጀውን አይሲስን በመቃወም ፋንታ የራሱ የህወሓትን ውል አልባ ህግ አክብረው በመንቀሳቀስ ላይ ያሉትን ሰማያዊ ፓርቲ፣ ኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞችን እና አረና ፓርቲን እየወነጀሉ መሆኑ አጅግ አሳፋሪ ነገር ነው። የአይሲስን አረመኔአዊ ድርጊት ከኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች የመብት ጥያቄ ጋር ለማገናኘት በህወሓት የደህንነት ቢሮ አማካይነት እንቅስቃሴ መጀመሩ እየተሰማ ነው። ለወጣቱ በብዛት መሰደድ በምክንያትነት የሚያቀርቡት ደላሎችን መሆኑ አላዋቂነት ሳይሆን በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ቅራኔው በኢትዮጵያዊያን መካከል እርስ በርስ እንዲሆን ያለመ መሠሪነት ነው። ከዚህም አልፎ የትግራይ ወጣቶችን ነጥሎ በመሰብሰብ “ትምክህተኞች ሊበሉህ ነውና ታጥቀህ ሳይቀድሙህ ቅደም” እያሉ መቀስቀስ በመንግሥት ደረጃ የእርስ በርስ እልቂትን ከማደራጀት ተለይቶ አይታይም። የሥርዓቱ ይሉኝታ ቢስነት የደረሰበት ዝቅጠት ገላጭ ከሆኑ ነገሮች አንዱ “እስከምርጫ መጨረሻ ድረስ ልጆቻችሁን አስረን እናቆይላችሁ” እያሉ ወላጆችን እስከመጠየቅ መድፈራቸው ነው።
ከላይ በአጭሩ የተዘረዘሩት ኩነቶች የሚያረጋግጡት ህወሓት የተማከለ አመራር አጥተው መንገድ የጠፋቸው፤ ሆኖም ግን እጃቸው ውስጥ የገባው ስልጣንና ሀብት ላለማጣት ምንም ነገር ከማድረግ የማይመለሱ አውሬዎች ስብስብ መሆኑ ነው። እንዲህ ዓይነቱን የአውሬዎች ስብስብ የሚገዛው የህግም ሆነ የሥነ-ምግባር ገደብ የለም። ህወሓት እስር በርሳችንን አባልቶ አገራችንንና ሕዝቧን ወደ ማንወጣው አዘቅት ከመክተቱ በፊት ራሱ ህወሓትን ማስወገድ እና በምትኩት ፍትህ፣ ነፃነት፣ ዲሞክራሲና እኩልነት የሰፈነባት ኢትዮጵያን መገንባት የዚህ ትውልድ ኃላፊነት ነው። ይህ ካላደረግን አሁን በወህኒ ቤቶች የሚደረገው ዜጎችን ልብስን አስወልቆ የማዋረድ አስነዋሪ ተግባር ነገ በአደባባዮች የማይደረግ ስለመሆኑ ምንም ማረጋገጫ የለንም። ይህ ትውልድ ኃላፊነቱ ካልተወጣ ህግን አክብረው ከአገዛዙ የተለየ ሀሳብ እናራምዳለን የሚሉ ወገኖቻችን በሙሉ አደጋ ውስጥ ናቸው። በህወሓት መሠሪ ተግባራት ሳቢያ በክርስትናና እስልምና እምነት ተከታይ ኢትዮጵያዊያን መካከል ያለው መግባባት እንዲሻክር እየተደረገ ነው። ዜጎችን በማዋረድ የሚደሰት አገዛዝና ለመዋረድ የፈቀደ ሕዝብ እስካለ ድረስ የቁልቁለቱ ጉዞ መጨረሻ የለውም። ይህንን ማስቆም ያለብን እኛ ሁላንችንም ነን። በአደባባይ መደራጀት ሲከለከል በምስጢር መደራጀትን መልመድ የኛ ኃላፊነት ነው። የኢትዮጵያ አርበኞች ድል መታሰቢያ በዓልን ስናከብር ከቀደምቶቻችን ልንወርስ ከሚገቡን እሴቶች አንዱ ለክብራችን ዋጋ መክፈል ያለብን መሆኑን ጭምር ነው። የኢትዮጵያዊያን ክብር በወያኔ ሲዋረድ እያየን ዝምታን ከመረጥን ከዚህም የባሰ እንዲመጣ መፍቀዳችንን እንወቀው።
አርበኞች ግንቦት 7:የአንድነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ የዜጎችና የአገር ውርደት ይብቃ! በተባበረ ክንድ ህወሓት ይወገድ፤ በምትኩም ፍትህ፣ ነፃነት፣ ዲሞክራሲና እኩልነት የሰፈነባት ኢትዮጵያን ለመመሥረት መሠረት እንጣል፤ ይህንን ታላቅ ኃላፊነት ለመወጣት በኅብረት እንነሳ ይላል።
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!
Source www.patriotg7.org

Saturday, May 2, 2015

እውነቱ ይውጣ!ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ- ማርያም

ሴቶችን በወንዶች ፊት፣ ወንዶችን በሴቶች ፊት ልብስ እያስወለቁ የአካላቸውን ክፍሎች ሁሉ ለማየት የሚያስችል እንቅስቃሴ አንዲሠሩ ማስገደድ በሽተኞችን ያስደስታል፤ የምርመራ ዘዴ ግን አይደለም፤ ውርደት እንዲሰማቸው ከሆነ በወራዶች ሰዎች ፊት የምን መዋረድ አለ? ወራዶች እነሱ ደረጃ ላይ ከእነሱ ጋር ያስተካክላሉ አንጂ አያዋርዱም፤ በሌላ አነጋገር ወራዶች አያዋርዱም፤ ወራዶቹ ደንቆሮዎችም ሆነው ነው እንጂ ልብስ የሚያስወልቁ እነሱ ብቻ አይደሉም፤ ሀኪሞችም ልብስ አስወልቀው፣ አጋድመው በጣታቸውም ሆነ በመሣሪያ የፈለጉትን የአካል ክፍል አንደፈለጉ ያደርጉታል፤ ወራዶቹና ደንቆሮዎቹ ከሚያደርጉት የሀኪሞቹ የሚለየው ሀኪሞቹ ሰዎችን ለማዳን ሲሉ ነው፤ ወራዶቹና ደንቆሮዎቹ ግን የራሳቸውን ሱስ ለማርካት፣ የራሳቸውን ህመም ለማስታገስ ነው፤ ወራዶቹንና ደንቆሮዎቹን ከመለዮአቸው አራቁቻቸዋለሁ!
ከነውር በቃላት ወደነውር በተግባር፣ ያውም በመሥሪያ ቤት!
ዱሮ ዱሮ ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ቲያትር ፊት ለፊት የአንድ ኢጣልያዊ ቡና ቤት ነበር፤ እዚያ ውጭ ተቀምጠን ቡና ስንጠጣ አንዲት ውብ ሴት ወደጸጉር መሥሪያው ቤት ስትመጣ የሁላችንም ዓይኖች እየዘለሉ እስዋ ላይ ዐረፉ፤ ከሦስታችን አንዱ ስለሴትዮዋ የወሲብ ችሎታ በዝርዝር መናገር ሲጀምር ሁለታችን ተያየንና አፈርን፤ ጨዋታው የጣመለት መስሎት ሲቀጥል የሕግ ባለሙያ የሆነ ጓደኛዬ አቋረጠውና ‹‹ስማ! ይህን ጊዜ እናትህ በአንድ ቦታ ስታልፍ አንዱ እንዳንተ ያለ ስለእርስዋ ችሎታ ያወራ ይሆናል!›› አለው፤ ሊጠጣ ወደአፉ ያስጠጋውን ስኒ ቁጭ አደረገና ተነሥቶ ሄደ፡፡
ሥልጣን ተሰጥቷቸው ሴቶችን ልብስ እያስወለቁ ምርመራ ነው የሚሉ በእናቶቻቸውና በእኅቶቻቸው ላይ ሊደርስ እንደሚችል አይገነዘቡም ይሆናል፤ ደንቆሮ የሚያደርጋቸውም ይኸው ነው፤ የአንዱ እናት አንድ ቦታ ላይ ራቁትዋን ቆማ በሽተኞች ተሰብስበው ሲስቁባት፣ በሌላ ቦታ ደግሞ ጓደኛው የእሱን እናት ወይም እኅት ያንኑ እያደረገ ያስቅባት ይሆናል፤ አንተ በእኔ እናትና በእኔ እኅት አስቅባቸው፤ እኔ ደግሞ በአንተ እናትና በአንተ እኅት አስቅባቸዋለሁ፤ ይህንን እየሠራን ኑሮአችንን እናቃናለን፤ እቤታቸው ሲገቡና ከእናቶቻቸውና ከእኅቶቻቸው ጋር ሲቀመጡና ሲበሉ (?!) ሰው ይመስላሉ፤ እነዚያም ግፉ የተፈጸመባቸው እናቶችና እኅቶች ‹ነውራቸውን› ምሥጢር አድርገው ለሰው ስለማይናገሩ ግፈኞችና የግፍ ሰለባዎች አብረው ይበላሉ!
አሁን ለመጀመሪያ ጊዜ አንዳንድ ሴቶች የደረሰባቸውን ተናገሩ፤ አሁን ያፍራሉ የተባሉት እውነቱን ራቁቱን አወጡትና ከእፍረት ነጻ ወጡ! እውነቱ ሲወጣ የሚያፍረው ማን ነው? ደካማዎቹና የግፍ ሰለባ የነበሩት በጭራሽ አያፍሩም፤ የሚያፍሩት ግፈኞቹ ናቸው፤ የሚያፍሩት የሕዝብን አደራ በማቆሸሻቸው፣ በሥልጣን በመባለጋቸው፣ የሕዝብንና የአገርን ክብር በማዋረዳቸው ያፍራሉ፤ ኅሊናቸው በየቀኑ ነፍሳቸውን አርባ ሲገርፋት እየሳሳች እንቅልፍ ትነሳቸዋለች፡፡
ለመሆኑ በአገሩ ሊቃነ ጳጳሳት፣ ጳጳሳት፣ መነኮሳት፣ ቀሳውስት — ሼሆች፣ ሽማግሌዎች በአገሩ የለንም?
ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ- ማርያም