ኢትዮጵያ እሥር ላይ የምትገኘውን ጋዜጠኛ ርዕዮት ዓለሙን፤ ቪየትናም ደግሞ የኢንተርኔት ፀሐፊዋን ወይም ብሎገሯን ታ ፎንግ ታንን እንዲለቅቁ ዩናይትድ ስቴትስ ጠየቀች፡፡
የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቃል አቀባይ ጄፍ ራትካ ናቸው ዛሬ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ይህንን የመንግሥታቸውን ማሳሰቢያ ያስተላለፉት፡፡
የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት በዚህ ሣምንት እያወጣቸው ባሉ ተከታታይ የፕሬስ መግለጫዎች በዓለም ዙሪያ በየእሥር ቤቱ ያሉ ጋዜጠኞችን በየቀኑ እያነሣ ይገኛል፡፡
በዚህ “FREE THE PRESS” ወይም “ፕሬስን ነፃ አውጡ” በሚለው ዘመቻው የዛሬው የመሥሪያ ቤቱ መግለጫ ካተኮረባቸው ሁለት ጋዜጠኞች አንዷና ቀዳሚዋ የቀድሞ የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የእንግሊዝኛ መምህር ኢትዮጵያዊቱ ፍሪላንስ ጋዜጠኛ ርዕዮት ዓለሙ ነች፡፡
በፀረ-ሽብር ሕጉ መሠረት በተመሠረተባት ክሥ ጥር 10/2004 ዓ.ም ተፈርዶባት እስከዛሬ ወኅኒ ቤት እንደምትገኝ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ ቃል አቀባይ ጄፍ ራትካ ጠቁመዋል፡፡
“… ርዕዮት ኢትዮጵያ ውስጥ ከሥራቸው ጋር በተያያዘ በተመሠረቱባቸው ክሦች ምክንያት ከታሠሩ 18 ጋዜጠኞች አንዷ ስትሆን ይህ ሁኔታም ኢትዮጵያ በአህጉሩ ብዙ ጋዜጠኞችን በማሠር ቀዳሚዋ እንድትሆን አድርጓታል …” ብለዋል፡፡
ርዕዮት የመንግሥቱን ፖሊሲዎች የሚተቹ ፅሁፎችን በጋዜጣ በማውጣቷ ምክንያት በሰኔ 2003 ዓ.ም ተይዛ የሽብር ፈጠራ ክሥ ከተመሠረተባት በኋላ የ14 ዓመት እሥራት ተፈርዶባት እንደነበረ ያስታወሱት ራትካ የእሥራት ዘመኗ ወደ አምስት ዓመት ዝቅ እንዲል ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ በነሐሴ 2004 ዓ.ም መወሰኑን ተናግረዋል፡፡
ይሁን እንጂ ክሡ ሙሉ በሙሉ እንዲሠረዝላት በተከታታይ ያቀረበቻቸው የይግባኝ አቤቱታዎች ውድቅ መደረጋቸውንም ራትኮ አመልክተዋል፡፡
“… ሃሣብን የመግለፅ ነፃነት መብቷን ተግባራዊ በማድረጓ ብቻ ታሥራ የምትገኘውን ርዕዮትን እንዲፈታ ለመንግሥቱ ጥሪያችንን እናቀርባለን - ያሉት ራትኮ - መንግሥቱ ፀረ-ሽብር አዋጁን ሃሣብን በነፃነት የመለዋወጥን ተግባር ለመጠምዘዝ ጉዳይ ከመጠቀም እንዲቆጠብም እናሳስባለን …” ብለዋል፡፡
የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ቃል አቀባይ ጄፍ ራትኮ በመቀጠልም በአውሮፓ የዘመን አቆጣጠር የ2013 ዓ.ም ጀብዱ ፈፃሚ ሴቶች ዓለምአቀፍ ሽልማት ያሸነፈችውና የቪየትናምን መንግሥትና ኮምዩኒስት ፓርቲውን የሚተቹ ፅሁፎችን ኢንተርኔት ላይ በማውጣቷ የአሥር ዓመት እሥራት ተፈርዶባት ወኅኒ የምትገኘው ታ ፎንግ ታንን የቪየትናም መንግሥት በአፋጣኝ እንዲለቅቅ መንግሥታቸው እንደሚያሳስብ አስታውቀዋል፡፡
ምንጭ- ቪኦኤ አምሃሪክ
No comments:
Post a Comment