ምኒልክ ሁሉን አስገበሩ። ጣሊያንንም አድዋ ላይ አሸነፉ። አንድ ስጋት ብቻ ቀረ ከወደ ደቡባዊ ከፍታዎች የመሸገ ባላንጣ። ከአርሲ ዘመቻ በፊት ምኒልክን በአንድራቻ ደጅ ያስጠና ጌታ።
የኝህ ጀግና መጠሪያ ስም ጭኔቶ ጋሊቶ ሲሆን የዙፋን ስማቸው ካፊ አቲዮ ጋኬ ሻረቾ (አጼ ጋኪ ሻረቾ) የካፋ ንጉሰ ንገስት ነው። ሕዝቡ ዝወትር በፍቅርና በአክብሮት የሚጠራቸው ግን ታተኖ ጭኒ እያለ ነበር።
የካፋና የሞቻ ሕዝብ በነገስታት መሪነት ቢያንስ ሶስት ምዕተ ዓመታት ወረራን በመከላከል የብሔር ህልውናውን አስከብሮ እነሆ ዛሬ የጎንጋ ሕዝብ ታሪክና ባህል ዋና አንጸባራቂ ምልክት ሆኖ ይገኛል። በተለይ የመጨረሻዎቹ ሶስት የካፋ ነገስታት፤
- አጼ ካዮ ሻረቾ (ኪም ዩሮ) እ. ኤ. አ. 1854 – 1870
- አጼ ጋሊ ሻረቾ (ታተኖ ጋሊ) እ. ኤ. አ. 1870 – 1890
- አጼ ጋኪ ሻረቾ (ታተኖ ጭን) እ. ኤ. አ. 1890 – 1897 የምኒልክን የግዛት መስፋፋት ዘመቻ መከላከል ዋና ወታደራዊና ፖለቲካዊ ተግባራቸው አድርገው ቆይተዋል።
የጎጃሙን የንጉስ ተክለ ሀይማኖትንና የራስ ደርሶን ሙከራ ሳይጨምር ከምኒልክ የመጨረሻ የካፋ ዘመቻ ጋር ከአራት መራራ ጦርነት በኋላ ነበር ጥንታዊው የካፋ መንግስት የተደፈረውና ዝነኛው የቡሻሼ ሜንጆ ስርወ መንግስት (ዳይናስቲ) የፈረሰው። ከሽንፈት በኋላም ቢሆን ግን የመጨረሻው የካፋ አቲዮ (የካፋ ንጉሰ ነገስት) ኩሩና ልበ ሙሉ እንደነበሩ ታሪክ ይመስክራል። ለምሳሌ በጠላት እጅ ከወደቀ ጊዜ እንኳ በወርቅ ሰንሰለት እንደታሰሩ እንጂ ብር ሰውነታቸውን እንዳይነካ ነበር የጠየቁት። ሆኖም ራስ ወልደጊዮርግስ አቦዬ (ቆቅማሪ) የወርቅ ሰንሰለት አላዘጋጁም ኖሮ በጥያቄው ተደነቁ። ይሁንና ተሸንፈው ንጉሱ ራሳቸው ባቀረቡት ሰንሰለት ታሰሩ። ጎደንፎ (ጎጀብን) ወንዝ በመሻገር ላይ ሳሉም “የካፋ መንግስት አለቀልሽ ከውሃ የተገኘሽ የንጉስ ወርቅ ከውሃ ውስጥ ሁኚ (አቼ ዳኔቲ ታቲ አቼኔ አጮች ቤበ)” ብለው የንግስና የወርቅ ቀለበታቸውን እወንዝ ውስጥ እንደከተቱት እስከ ዛሬ ይተረካል።
ካፊ አቲዮ ጋኬ ሻረቾ (አጼ ጋኪ ሻረቾ)
ከምኒልክ ፊት እንደቀረቡም “ራስህን እንደታላቅ ንጉስ ትቆጥራለህ። ንገር ግን ይሄ ግምትህ ከእኔ ጋር ፈጽሞ ሊወዳደር አይችልም። ላንተ ዘውድ የተጫነው በሰው እጅ ሲሆን የኔው ግን ከላይ ከአንድ አምላክ ከ (ኢኬ የሮ) የወረደልኝ ነው” ማለታቸው ኩሩና አይበገሬ ለመሆናቸው ማስረጃ ነው።
ሕዝቡም እንደ ንጉሱ በቀላሉ አለመበገሩም ጸሐፊ ገብረስላሴ ሲገልጹ “… ነገር ግን ስለስፍራው ከፋት እየተዋጋ አልገብርም ብሎ ንጉሱ ከአንድ ቦታ ወደ አንድ ቦታ እየተዘዋወረ የካፋ አገሩም ጠፋ። ሰውም አለቀ። ከዘማቹም ከክርስቲያኑም ብዙ ሰራዊት አለቀ። ከዚህ በኋላ 9 ወራት ሙሉ ተዋግቶ በነሐሴ 29 ቀን የካፋው ንጉስ ተማረከ። የተረፈውም አገር ሲማረክ ዘውዱ የወርቅ፣ ወንበሩ የወርቅ፣ አለንጋው ስንቴል ነጋሪት ያውም ነጋሪቱ አንዱ የብር አንዱ የነሀስ ነው። በነጋሪቱም ላይ ስሙ ተጽፎበታል። ይህ ሁሉ ከንጉሱ ጋር ተያዘ” በማለት ነበር የገለጹት።
የካፋ መንግስት ለአጼ ምኒልክ አላድርም ብሎ 17 ዓመት ሙሉ እጁን ሳይሰጥ ቆየ። ከአድዋ ጦርነት በኋላ ግን ማለትም ጣሊያን በተሸነፈ በዓመቱ ተረታ። ይህም ሊሆን የቻለው ከጣሊያን ሽንፈት በኋላ መሳሪያ በመገኘቱ በ20000 (ሀያ ሺህ) ዘመናዊ ጠመንጃ በሶስት አቅጣጫ ተከቦ 9 ወራት ገትሮ ከተዋጋ በኋላ ነበር።
አጼ ጋኪ ሻረቾና አጼ ምኒልክ እጅግ ተፎካካሪ ነገስታት ነበሩ። ፉክክሩ በገብር አልገብርም ብቻ የተወሰነ ሳይሆን የስርወ መንግስት (የዳይናስቲ) ጥያቄ ውዝግብ ስለነበረበት ነው። ስለዚህም የካፋ ሕዝብ በታሪኩና በማንነቱ እንደሚመካ ባወቀ ጊዜ አደገኛነቱ ስለታያቸው ፔርሀም እ.ኤ.አ 1948 ሶንታንደን የተባለው አገር አሳሽ ጠቅሶ እንደዘገበው አጼ ምኒልክ የስዊስ አማካሪያቸው የካፋ ነገስታትን የወርቅ ዘውድ ወደ አገሩ እንድወስድ አደረጉ።
አጋራሻ እተሞ የተባሉት ታሪክ አዋቂ አዛውንት እንዳጫወቱኝ ሁለት ካፋዎች ዘውዱን በትረ መንግስቱንና ሌላም ወርቃ ወርቅ የንግስና እቃዎችን ከአንኮበር ይዘው ካፋ ከገቡ በኋላ ከምኒልክ የተላከ ጦር ሰዎቹን አሳዶ ከገደላቸው በኋላ እቃው ወደ አንኮበር ተመለሰ። ከዚያ በኋላ ይሆናል እንግዲህ የዘውዱ በኢትዮጵያ ምድር መኖር ምኒልክን ያሰጋቸው።
ማርስ ግሩል ስለ ጦርነቱ ያገኘውን መረጃ ሲተነትን “ወረራውን የአቢሲኒያ ጦር ለመመከት የካፋ ጦር ያሳየውን የጀግንነት ስራ በተለይም ስለመጨረሻው ፍልሚያ የሚያወሳውን ገጣሚ ወይም ተራኪ ገና አልተነሳም። ሆኖም ይህ የጀግንነት ስራና አሳዛኝ ፍጻሜው በሰው ልጅ የታሪክ ማህደር ውስጥ ቦታ ሊኖረው የሚገባ ነው” ይላል። በምኒልክ የረጅም ጊዜ የመስፋፋት ጦርነት “የካፋ ዘመቻ” የመጨረሻው ምዕራፍ ነበር። በመጨረሻ የተሸነፈው ካፋ ነው። የመጨረሻው ከባድ በትር ያረፈው በእሱ ላይ ነበር።
ምኒልክ የኦሮሞን ክልል በቁጥጥራቸው ስር ካደረጉ በኋላ ፊታቸውን ወደ ካፋ አዞሩ። አሁንም ማክስ ግሩል እንዳስቀመጠው “በዚህ የሰሜን ምስራቅ አፍሪካ ክፍል ለፖለቲካ የበላይነት ከተደረጉ ጦርነቶች የመጀመሪያው ወሳኝ ፍልሚያ በምኒልክና በካፋ መንግስት መካከል የተደረገ ነው” ብሏል፡፡
በ1881 እ .ኤ .አ ምኒልክ ገና የሸዋ ንጉስ ብቻ እንደነበሩ ራስ ጎበናን ወደ ካፋ ላኩ። ሆኖም ካፋዎች በቀላሉ መለሱዋቸው። ምኒልክም ካፋ መገበሩን ገና ሳያረጋግጡ “የሸዋ የካፋና የኦሮሞ አገር” ንጉስ ብለው ራሳቸውን ስለሰየሙ የወቅቱ የኢትዮጵያ ንጉሰ ነገስት አጼ ዮሀንስ አራተኛ ተቆጥተው የጎጃሙን ራስ አዳል ንጉስ ተክለህይማኖት ብለው በካፋ ላይ ሾሙ። በዚህ ምክንያት ምኒልክና ንጉስ ተክለሃይማኖት አምባቦ ላይ ጦርነት ገጥመው ንጉስ ተክለሃይማኖት ተማረኩ።
እ ኤ አ 1885 ዓመተ ምህረትም ራስ ጎበና እንደገና ወደካፋ ዘመቱ። በዚህ ጊዜ ለማሟሟቂያ እንዲያደርግ ይመስላል ለጎበና ማእረጋቸው ከፍ ብሎ “የካፋ ንጉስ” ከሚባል ሚካኤል የሚል አዲስ ስም እንዲወጣላቸው ተደረገ። ሆኖም በዚህ ጊዜም ቢሆን ካፋ ባለመሸነፉና ምንም አይነት የመበገር ምልክትም ባለማሳየቱ የራስ አዳልም ሆነ የራስ ጎበና “የካፋ ንግስና” ባዶ ክብር ሆኖ ቀረ።
በጥቅምት 19 ቀን 1886 እ. ኤ. አ. የኢትዮጵያ አካል ያልሆነው ካፋ ለባሻ አቦዬ ተሰጠ። ባሻው ደጃች ተብለው ራስ ጎበና ሁለቴ ሞክረው ያቃታቸውን አገር ባንዴ ድባቅ መተው ካፋ አናት ላይ ቁጭ ለማለት ጨርቀን ማቄን ሳይሉ በከፍተኛ ወታደራዊ ፍጥነት ገስግሰው ጎጀብ (ጎደፎ) ወንዝ ደረሱ። ካፋዎች ግን አስቀድመው የጎደፎን ዳርቻ ከላይ እስከ ታች ዘግተው ስለመሸጉ ፉከራቸው መና ሆኖ ቀረ። በመጡበት ተመለሱ።
ይሁንና የጅማው አባ ጅፋር ብዙም ሳያንገራግር ስለገበሩ ካፋም ይገብራል ተብሎ ተጠብቆ ነበር። ሆኖም የካፋው ንጉስ ይባስ ብለው ለምኒልክ የገበሩበትንም ሊወጉ ይዘጋጁ ጀመር። የካፋ መንግስትም ምንም አይነት ግብር ሳይልክ ድንብሩን በሰራዊት አጥሮ ተቀመጠ። ጅማና ኢሉባቦርንም ሊለውጥ እየተዘጋጀ ነው የሚለው ስጋትም ጨመረ። በዚህን ጊዜ ምኒልክ ታላቅ የዘመቻ ውሳኔ አሳለፉ።
“የካፋ ዘመቻ” በ1889 እ ኤ አ ተጀመረ። የንጉሱ የእህት ልጅ በአውሳ ጦርነት መልስ ራስ ተብለው በካፋ ላይ ተሾሙ። ከራስ ወልደጊዮርጊስ ጋርም የኢሉባቦር ገዢ የሆኑት ራስ ተሰማ ናደውና የወለጋው ደጃች ደምሰው ታዘው ወደ ካፋ ዘመቱ። ይሁንና ራስ ወልደጊዮርጊስ ቀጥታ ካፋ መግባት ስላዳገታቸው ከካፋ በስተምስራቅ የሚገኙትን የዳውሮና የኮንታ መንግስታትን አስከድመው በቁጥጥር ስር ማዋል ነበረባቸው። የካፋ መንግስትም በዚህን ወቅት ከሶስት አቅጣጫ የጦርነት ስጋት አንዣበበበት።
ምኒልክ በቦንጋና አንድራቻ
ምኒልክ ካፋን በጦርነት ሆነ በዲፕሎማሲ ሊያስገብሩ ጥረት አድርገዋል። ራሳቸው ቦንጋና አንድራቻ ድረስ ሄደው ከማንም ሌላ ንጉስ ጋር ያላደረጉትን ውይይት አካህደው ነበር። በ1894 ለወዳጅነት ጉብኝት አንድራቻ እንደደረሱም “ቤቴ ቤትህ ነው” በሚል ባህላዊ አክብሮት ስሜት የካፋው አትዮ ጋኪ ሻረቾ በጥሩ መስተንግዶ ተቀብሎ ሸኛቸው። ምኒልክ በውቅቱ በአርሲ ላይ ከባድ ዘመቻ ከፍተው ስለነበር የካፋ ጦር ከኋላ እንዳይወጋቸው ነበር ስጋት ያደረባቸው።
በመጨረሻ ምኒልክ ካፋ እንዲገብርላቸው አግባብተው “እሽታ” አገኙ። በመልካም ንጉሳዊ ዲፕሎማሲያቸው ረክተው ቢመለሱም ግን የካፋው አጼ ተጠብቀው ምንም ዓይነት የመበገር ምልክት ሳያሳዩ ቆዩ። እንዲህ በመሆኑ የመጨረሻው ፍልሚያ ከአድዋ ጦርነት በኋላ ተካሄደ። የከበባው አቅጣጫ:-
- ራስ ወልደጊዮርግስ ከምስራቅ በኩል ኮንታ አደርገው ቦንጋ አንድራቻ ገቡ።
- ራስ ተሰማ ጫካ ጫካውን ተጉዘው ቢጣ፣ ጫናዋቻ እንዲሁም በገሻ ድረስ ዘመቱ።
- ደጃች ደምሴውም መሐሉን በጌራ በኩል በአባጅፋር እየተረዱ ተሻግረው በገዋታ በኩል ወደ መሀል ካፋ ዘለቁ። በግጭቱም ከፍተኛ የሕይወት ጥፋትና የንብረት ውድመት ተከሰተ።
አውሮፓውያን በነዚህ የካፋ ተራራዎች ስለተፈጸመው ጦርነት ድራማ የነበራቸው እይታ ወይም ስሜት ትንሽ ነበር። ብቻ ስለጦርነት ፍጻሜው አጭር ዘገባ አትመው እንደነበር ይታውሳል። ሆኖም ይህ ጸሀፊ ይህን እትም ሊያገኝ አልቻለም። ስለሆነም በአውሮፓውያንም ሆነ በኢትዮጵያዊያን በኩል ስለ ጦርነቱ ድራማ ጥልቀት ያለው ዘገባ ገና አልተገኘም። በዚህ ረገድ ወደፊት ለጸሀፊ ተውኔትና ለፊልም አቀናባሪዎች ስራ ለዛና ወዘና ያለው ገና ያልተቀዳ የታሪክ ምንጭ መኖሩን ላስታውስ እወዳለሁ።
ሆነም ቀረ ጊዜው በሰጣቸው ኃይል ሚዛን በልጠው በመገኘታቸው ምኒልክ ዘመቻቸውን አሳኩ። እናም እ. ኤ.አ. መስከረም 1897 የመጨረሻው የካፋ የቲዮ (የካፋ ንጉሰ ነገስት) አጼ ጋኪ ሻረቾ የጦር እስረኛ ሆነው ወደ አንኮበር ተውሰዱ። አብረዋቸው የነበሩት ውድ ባለቤታቸውም እ.ኤ.አ. በ1906 አረፉ።
ቁምላቸው ገ/መስቀል አምቦ
ከአንኮበር የካፋ ዘውድ በካፎች በተሰረቀ ጊዜ በተመሳሳይ መልኩ እስረኛ የነበሩት ንጉስ አምልጠው ካፋ አገር ቢገቡ ሌላ ጦርነት ይፈጠራል የሚል ስጋት ስለተፈጠረ ከአንኮበር ወደ ደሴ ወሎ ተወስደው በንጉስ ሚካኤል ጦር ጥበቃ ስር ቆዩ። ሆኖም ልጅ ኢያሱ እንደንጉሱ ወደ አገራቸው (ካፋ) እንዲመልሱ ስልጣን እንዳያዙ ወስነውላቸው ነበር። ይሁን እንጂ የአቤቶ ኢያሱ ፍታዊና ዲፕሎማሲያዊ የፖለቲካ ስልት በተፈሪ መኮንን አሲረኞች በመቀጨቱ ሁሉ ነገር ተገለበጠ።
ስለሆነም የካፋ ንጉሰ ነገስት (ካፊ እቱዩ) አጼ ጋኪ ሻረቾ የመጨረሻው የካፋ ወርቅ ዘውድ ጫኝ፣ የወርቅ ዙፋን ባለቤት፣ የወርቅ በትር መንግስት ያዥ፣ ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚተላለፍ የወርቅ የንግስና ቀለበት ጠባቂ ተወዳጅና ተመላኪው ንጉስ በችግር ኖረው ለሀገራቸው አፈር ሳይበቁ እ ኤ አ 1917 ሲያርፉ አስከሬናቸው ደብረሊባኖስ እንዲያርፍ ተደረገ። ከሁለት አሽከሮቹና ከጥቂት ንብረት በስተቀር ምንም ሀብት አልነበራቸውም። ልጃቸው በዛብህ ወደካፋ ሄዶ እንዲኖር ቢፈቀድለትም ከጥቂት ዓመታት በኋላ ግን እንደገና ታስሮ ወደ አዲስ አበባ ተወሰደ። ግን የሚገርመው ነገር ከአጼ ምኒልክ በኋላም የመጡት የኢትዮጵያ መሪዎች የካፋን ሀገር በቁጭትና በበቀል መግዛታቸው ነው።
(ከኖቾ ወደቡሾ)
source www.goolgule.com