Saturday, December 21, 2013

የሸራተን ሰራተኞች “መብታችን ተጣሰ” በማለት ሰላማዊ ሰልፍ ሊወጡ ነው!!!!

የሸራተን አዲስ ሆቴል ሰራተኞች፤ የውጭ አገር ዜጋ በሆኑት የሆቴሉ ስራ አስኪያጅ የሚደርስብን ችግር ከአቅም በላይ በመሆኑ ሰላማዊ ሰልፍ ልንወጣ ነው አሉ፡፡ ከዚህ በፊት  የመብት ጥሰት እንደደረሰብን ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና ለሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በደብዳቤ ብንገልፅም ምላሽ ባለማግኘታችን በድጋሚ ደብዳቤውን አስገብተናል ብለዋል - ሰራተኞቹ፡፡ 
በትምህርት ደረጃና በእውቀት ከሀበሾቹ የማይበልጡ የውጭ ዜጐች አሰሪዎቻችን ያንቋሽሹናል፤ ዛሬ ፆም ነው ይህን አንበላም ስንል “ድሮ ረሀብተኞች ስለነበራችሁ ረሀባችሁን ለማስታወስ የምታደርጉት ነው” ይሉናል፤ ጥቅማጥቅሞቻችን አይከበሩም፣ እድገት እንከላከላለን ያሉት ሠራተኞቹ፤ “ፈረንሳዊው ስራ አስኪያጅ ዲፓርትመንቶችን በመበታተን፣ ሰራተኞችን ወዳልፈለጉትና ወደማይመለከታቸው ቦታ ይመድባሉ፤ ይህን ስንቃወም እስከመደብደብ እንደርሳለን” ብለዋል፡፡ 
“የዜጐች ደህንነት ጥበቃ ከአገር ውስጥ ይጀምራል፤ በአገራችን ነጮች እያንቋሸሹን እና ሞራላችን እየተነካ ነው” የሚሉት ሰራተኞቹ፤ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ችግራችንን በዝምታ ማለፋቸው አሳዝኖናል ብለዋል፡፡ 
“ችግራችን ሲብስ ፒቲሽን ተፈራርመን ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያስገባነው ደብዳቤ፤ ለሆቴሉ ስራ አስኪያጅ ለሚስተር ዦን ፒይር ማኒንጐፍ ከደረሰ በኋላ፣ ስቃያችን በዝቷል ያሉት ሰራተኞቹ፤ አንድ ነገር ለማስፈቀድ፣ አቤቱታ ለማሰማትና ለእድገት ለመወዳደር ስንጠይቅ ስራ አስኪያጁ  ፒቲሽን የፈረሙትን ሰራተኞች ስም ያወጡና “በእኔ ላይ ፈርመሀል፤ እድሜ ልክህን እድገት አታገኝም፣ ይህ አይፈቀድም” እያሉ እንደሚያንገላቷቸው ተናግረዋል፡፡ ሸራተን አዲስ ሆቴል ከ800 በላይ ቋሚ ሰራተኞች እንዳሉት የገለፁት ሰራተኞቹ፤ ይህ ሁሉ ሰራተኛ ባለበት ስራ አስኪያጁን ጨምሮ አንዳንድ የውጭ አሰሪዎቻችን እያንጓጠጡንና ጫና እየፈጠሩብን ስለሆነና የሚመለከተው የመንግስት አካል ምላሽ ስላልሰጠን በቅርቡ ሰላማዊ ሰልፍ ለመውጣት አስበናል ብለዋል፡፡ 
የሆቴሉ ሰራተኞች ማህበር ሊቀመንበሩ አቶ ዳንኤል አለሙ ታሪኩ በበኩላቸው፤ “ሰራተኞቹ ከማህበሩ ወጥተው በራሳቸው ተደራጅተዋል፤ ነገር ግን ማኔጅመንቱና ሰራተኛው ተቀራርበው እንዲሰሩና በውይይት ችግራቸውን እንዲፈቱ ብዙ ርቀት ብንሄድም የሆቴሉ ስራ አስኪያጅ ሚስተር ዦን ፒይር ማኒንጐፍ ፈቃደኛ አልሆኑም” ብለዋል፡፡ 
የሆቴሉን ስራ አስኪያጅ  ሚስተር ዦን ፒይር ማኒንጐፍን ለማነጋገር ብንሞክርም እረፍት ላይ በመሆናቸው ሳይሳካልን ቀርቷል፡፡ ሌላ ሃላፊ ለማነጋገር ፀሃፊዋን ጠይቀን፤ በጉዳዩ ላይ ምላሽ የሚሰጡት ስራ አስኪያጁ ብቻ እንደሆኑ ገልፃልናለች፡፡ 
   ምንጭ
 አዲስ አድማስ

No comments:

Post a Comment