Saturday, November 30, 2013

የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀ-መንበር ኢ/ር ይልቃል በጀርመን- በስዊዘርላንድ – በሆላንድ – በዋሽንግተን ዲሲ ውይይት ያደርጋሉ

(ኢ.ኤም.ኤፍ) የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀ-መንበር ኢንጂነር ይልቃል ጌትነት የአውሮፓና የሰሜን አሜሪካ ጉብኝታቸውን ጀምረዋል። ትላንት ኖቨምበር 29 ጀርመን ፍራንክፈርት የገቡት ኢ/ር ይልቃል በመጪዎቹ ቀናት በአውሮፓ ከተሞች ተከታታይ የስራ ጉብኝት እንደሚያደርጉ አስተባባሪ ኮሚቴው በተለይ ለኢ.ኤም.ኤፍ አስታውቋል።
ለጊዜው በደረሰን የስራ ሰሌዳ መሰረት :-
- ቅዳሜ ኖቬምበር 30 በጀርመን ኑረንበርግ ከኢትዮጵያኖች ጋር ውይይት ያደርጋሉ።
- ሰኞ ዲሴምበር 2 በፍራንክፈርት የሚደረገው ሰላማዊ ሰልፍ ላይ ይገኛሉ።
- ዲሴምበር 5 ጄኔቭ ስዊዘርላንድ የሚደረገው የተቃውሞ ሰልፍ ላይ ይሳተፋሉ።
- ቅዳሜ ዲሴምበር 7 በሆላንድ ህዝባዊ ውይይት ያደርጋሉ።
ከአውሮፓ ቆይታቸው በኋላ ወደ ዋሺንግተን ዲሲ በመጓዝ በዲሴምበር 30 አርሊንግተን በተዘጋጀው ስብሰባ ከፕ/ር አል ማርያም ጋር ንግግር ያደርጋሉ።
Nov 30: Nuremberg : Public meeting and fundraising
Dec 02: Frankfurt: Appearance at a rally; Meet with invited guests for dinner
Dec 05: Geneva: appearance at a rally
Dec 07: Amsterdam: Public meeting
Washington DC Public Meeting with Semayawi Party Chairman Eng. Yilkal Getnet – Sunday Dec 15, 2013 – Sheraton Arlington Hotel.     Source Ethiopian media forum 
Blue-Party-at-USA1

Thursday, November 28, 2013

“ሁከት ፈጠሩ” የተባሉት የሰማያዊ ፓርቲ አባላት ጉዳይ ፍ/ቤት ቀረበ

(አራያ ጌታቸው) ዛሬ ህዳር 18 ቀን 2006 ዓ.ም ከላይ ባለው የክስ መጥሪያ የሰማያዊ ፓርቲ የምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ የሽዋስ አሰፋ እና የሰማያዊ ፓርቲ የምክር ቤት አባል አቶ ስሜነህ ጸሀይ አዲስ አበባ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ወንጀል ችሎት ቀርበው፤ አቃቤ ህግ ወንጀሉን ከዘረዘሩ በኋላ ፍርድ ቤቱም ጥፋተኝነታቸውን ያምኑ ወይም ይቃወሙ እንደሆነ ጠይቆ ተከሳሾቹም ምንም አይነት ጥፋት እንዳለጠፉ ገልጸዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ የምስክሮችን ቃል ለመስማት ለህዳር 26 ቀን 2006 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቶ አሰናብቷቸዋል፡፡
የክሱን ዝርዝር እንዲያነቡት ከዚህ ዜና ጋር አቅርበነዋል።                                                 ምንጭ የኢትዮጵያ ሜዲያ መድረክ

Sunday, November 24, 2013

“እኔ ራሴ ስድስት ያበዱ ሴቶችን ይዤ መጥቻለሁ..” ራውዳ ጀማል – ከሳዑዲ ተመላሽ ኢትዮጵያዊት (ቃለ ምልልስ)

በሃገር ቤት እየታተመ የሚወጣው አዲስ አድማስ ጋዜጣ ከሳዑዲ አረቢያ ወደ ሃገራቸው ከተመለሱ ኢትዮጵያውያን ጋር ቃለ ምልልስ አድርጓል። ቃለ ምልልሱ ዘ-ሐበሻ ከዚህ ቀደም ትዘግባቸው የነበሩ የሳዑዲ ሕይወቶችን የሚያጠናክሩ በመሆናቸው ጋዜጠኛ አበባየሁ ገበያው ያደረገችውን ቃለምልልስ ለአንባቢዎቻችን እንደወረደ ይኸው፦
ራውዳ ጀማል ትባላለች፡፡ የሃያ ዓመት ወጣት ናት፡፡ ስለራስዋም ሆነ በሳኡዲ ስላሉ ኢትዮጵያውያን ወቅታዊ ሁኔታ ስታወራ እያለቀሰችና እየተወራጨች ነው፡፡ ለማነጋገር ስቀርባት “ወንድ ከሆናችሁ ጋዜጠኞች ነን፣ የህዝብ አፍ ነን ካላችሁ፤ እዚህ ተቀምጣችሁ፣ “ሁለት ሰው ሞተ” እያላችሁ ከምታቅራሩ ሳኡዲ ሂዱና በየቀኑ ሁለት ሶስት ሰው የሚሞትበትን እልቂት ተመልከቱ፣ “ሰዎቹን ምን እየሰራችሁ ነው?” ብላችሁም ጠይቁልን” አለችኝ። መቅረፀ ድምፄን ሶስት አራት ጊዜ ያስጠፋችኝ ቢሆንም በመጨረሻ ግን ለቃለ ምልልስ ፈቃደኛ ሆነችልኝ፡፡

ስንት ዓመት ቆይተሽ መምጣትሽ ነው?
ከሁለት ዓመት በኋላ ነው የመጣሁት፡፡ እስከ አስረኛ ክፍል የተማርኩት አዲስ አበባ ቢሆንም፤ የኮምቦልቻ ልጅ ነኝ፡፡
እንዴት ነበር የሄድሽው?
በፓስፖርት… በኮንትራት ነበር የሄድኩት … ካላስ! የሰውየው ልጆች ግን “የማይሆን” ፊልም ተመልከቺ እያሉ ያስቸግሩኝ ነበር፡፡ ሲመረኝ ጠፍቼ ወጣሁ፡፡ ከዚያም ከጓደኞቼ ጋር በነፃነት ቤት ተከራይተን እየኖርን፣ በ1800 ሪያል ተቀጥሬ መስራት ጀመርኩኝ፡፡ ቤተሰቤንም ገንዘብ እየላኩ እረዳ ነበር፡፡
ወደ አገርሽ እንዴት ተመለስሽ?
ውጡ ሲባል… ረብሻ ሲነሳ.. ጓደኞቻችን ሲሞቱ.. ሲደፈሩብን.. ‘ድሮም ስደተኛ ክብር የለውም’ ብዬ ተመልሼ መጣሁ..ከሚገሉኝ ከሚያበለሻሹኝ ብዬ እጄን ሰጠሁ፡፡ ብዙ ኢትዮጵውያኖች ችግር ላይ ናቸው.. እባካችሁ ድረሱላቸው፡፡ ብርዱም ፀሃዩም ሲፈራረቅባቸው.. ያሳዝናሉ፡፡ ብዙ ያልመጡ አሉ፤ መምጣት እየፈለጉ፡፡ ስቃይ ላይ ናቸው፡፡ እኔ አሁን አስራ ሶስት ቀን ታስሬ ነው የመጣሁት፡፡ እስቲ ስለ እስሩ ንገሪኝ … ሁለት ቀን ያለ ምግብ ያለ ውሃ ነው የታሰርነው። ከዛ በኋላ ግን ጥሩ ምግብ ሰጥተውናል፣ ጥሩ መኝታም አግኝተናል፡፡ ብዙዎቹ ግን ከእኛ የባሰ ችግር ላይ ናቸው፡፡ መጠለያ ያላገኙ አሉ… ኤምባሲያችንም አይሰማም እንጂ ስንት ጊዜ ደውለን ተናግረናል መሰለሽ፡፡ ግን የሚሰማ የለም፡፡ ከአገራችን ውጡ ካሉ በኋላ ትዕግስት ያጡና መልሰው ይዩዙናል፡፡ በዛን ጊዜ አበሻው፣ ሻንዛ/ጩቤ ይመዛል፡፡ ፖሊስ ራሱን ለማዳን ይተኩሳል። እኔ እንደውም ደህና ነኝ፤ እዛ ላሉት ድረሱላቸው። በምድረ ዱርዬ እየተደፈሩ ነው ያሉት /ለቅሶ/ ስንት ህፃናት አሉ የሚሞቱ፣ የሚታመሙ፡፡ ስንመጣ ደሞ፤ ሻንጣ አትያዙ ተብለን ተመናጭቀን…በጥፊ ተመትተን..መከራችንን በልተናል፡፡
ወንዶችና ሴቶች ለብቻ ነበር የተቀመጣችሁት?
የተቀመጣችሁት አትበይ! የታሰራችሁት በይ፡፡ … የሴት እስር ቤት ለብቻው ነው በሴቶችና በህፃናት ለቅሶ የተሞላ ነው፡፡ እኔ ራሴ ስድስት ያበዱ ሴቶችን ይዤ መጥቻለሁ…/ለቅሶ/
አሁን ቤተሰብ እየጠበቅሽ ነው?
ነበረ ግን ሻንጣዬ ጠፋብኝ፡፡ በርግጥ ጤነኛ ሆኖ መምጣትም ቀላል አይደለም፡፡ እዛ ያሉትን ጥለናቸው ስንመጣ እያለቀስን ነው፡፡ እስር ቤቱ ውስጥ አንድ እርጉዝ ሞታብናለች፡፡ እዛው እስር ቤት እያለን ምጥዋ መጣ፤ ግን የህክምና እርዳታ ባለማግኘትዋ ሞተች፡፡
እስር ቤት ያሉት ምን ያህል ይሆናሉ?
ሰማኒያ ክፍል አለ..በየክፍሉ ስልሳ አምስት ስልሳ አምስት ሰው ነው ያለው፡፡ መካሲመሺ እስር ቤት ይባላል፡፡ የወንድና የሴት እስር ቤት የተራራቀ ነው፡፡ በጣም ረጅም ከመሆኑ የተነሳ በመኪና እንጂ በእግር አይሞከርም፡፡ በአሁኑ ሰዓት በከተማው ያለው እስር ቤት ሞልቶ የመዝናኛና የስብሰባ አዳራሹን ሁሉ እስር
ቤት አድርገውታል፡፡ የተደፈሩት የሞቱት..ሴቶች ብዙ ናቸው፡፡ አንዷን እርጉዝ ለሶስት ሲደፍሯት ሞታለች፡፡
የሌሎች አገር ስደተኞችም እየወጡ ነው ተብሏል…
አዎ፡፡ ኢትዮጵያዊው ከበደሉ ብዛት የተነሳ እየተናነቀው እኮ ነው ግጭቱ የሚከረው፡፡
ሚስቱን እህቱን ከእጁ መንትፈው ሊወስዱበት ሲሉ ነው ጦርነት የሚነሳው፡፡ አበሻ ወንድ እየሞተ ያለው ‹‹ሴቶቻችንን አትንኩብን..›› ስለሚል እኮ ነው፡፡ ኤምባሲው ሊደርስላቸው ይገባል፡፡
ምንጭ ዘ-ሐበሻ

Saturday, November 23, 2013

ኦባንግ – ከዓለምአቀፍ ተቋማት ጋር እየሠራሁ ነው አሉ የሳዑዲ ልዑል አንጋቾቻቸውን አወደሱ

November 22, 2013 09:19 pm By 
በሳዑዲ አረቢያ በኢትዮጵያውያን ላይ የደረሰውንና እየደረሰ ያለውን ፈር የለቀቀ አስነዋሪ ግፍ ዓለምአቀፍ ይዘት እንዲኖረው ለማድረግ ከሰብዓዊ መብት ተሟጋች እና ሌሎች ዓለምአቀፋዊ ድርጅቶች ጋር እየሠሩ መሆናቸውን አቶ ኦባንግ ሜቶ በተለይ ለጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ ተናገሩ፡፡ የሳዑዲ ልዑል ሰብዓዊነት የረገፈበትንና በግፍ የተሞላ የወሮበላ ተግባር የሚፈጸምበትን አሰቃቂ ተግባር የሚከናውኑትን አንጋቾች አሞካሹ፡፡
ያለ አንዳች ልዩነት ኢትዮጵያውያን በኅብረት ድምጻቸውን በማሰማት እየተቃወሙት ያለውን ኢሰብዓዊ ተግባር አስመልክቶ በተለያዩ መንገዶች ይፋ ከሆኑት በተጨማሪ ድብቅ መረጃዎች እየተሰበሰቡ መሆናቸውን ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ (አኢጋን) ዋና ዳይሬክተር አስታውቀዋል፡፡ ዳይሬክተሩ አቶ ኦባንግ ሜቶ የጋራ ንቅናቄው ከዓለምአቀፍ የመብት ተቋማት ጋር በቅርበት እየተሰራ ስላለው ዝርዝር ጉዳይ ግን ከሁኔታው ምስጢራዊነት አኳያ ማብራሪያ ከመስጠት ተቆጥበዋል፡፡
“አልዘገዩም” በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱም “አኢጋን ችግር በተከሰተ ቁጥር የሚቋቋምና የሚፈርስ የዕቁብ ይዘት ያለው ድርጅት አይደለም፡፡ ወይም እሣት ሲነሳ ድምጽ እያሰማ እንደሚከንፍ የእሣት አደጋ መኪና የሚመሰል ድርጅት አይደለም” በማለት የጋራ ንቅናቄውን የተጠና አካሄድ በመጠቆም የመለሱት አቶ ኦባንግ ይህ ችግር እንደሚከሰት አስቀድሞ ማስጠንቀቂያ መስጠታቸውን ተናግረዋል፡፡
ችግሩ አስቀድሞ እንደሚከሰት ቢታወቅም ምላሽ የሚሰጥ ብቃት ያለው አካል ባለመኖሩ አንገት የሚያስደፋና ኃፍረት የሚላብስ፤ “አገር አለኝ ወይ?” የሚል ጥያቄ የሚያስነሳ በኢትዮጵያ ታሪክ ተሰምቶና ታይቶ የማይታወቅ ኃፍረት ሊደርስብን ችሏል፡፡ “ይሁን እንጂ” አሉ ኦባንግ “ይህ መራር ዜና ከተሰማበት ሰዓት ጀምሮ የጋራ ንቅናቄው የበኩሉን” ሲያደርግ መቆየቱን አመልክተዋል፡፡
“ከተለያዩ ዓለምአቀፋዊ ተቋማት፣ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች፣ አግባብ ካላቸው መንግሥታዊ አካላትና በተለያየ ደረጃ ላይ ከሚገኙ የሳዑዲ ባለስልጣናት ጋር ተነጋግረናል” በማለት አቶ ኦባንግ ተናግረዋል፡፡ ለዓብነት ያህልም የሳዑዲ ም/ጠ/ሚ/ር እና የመከላከያ ሚ/ር፣ የውጭ ጉዳይ ሚ/ር፣ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚ/ር፣ የፍትሕ ሚ/ር እና ሌሎች ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸውን የመንግሥት መ/ቤቶችን ጨምሮ በአውሮጳና በሰሜን አሜሪካ የሚገኙትን የሳዑዲ ኤምባሲዎችን እንዲሁም የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ጉዳይ ኮሚሽነርን፣ የአፍሪካ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ACHPR)፣ ወዘተ ማነጋገራቸውንና በየደረጃውም ምላሽ ማግኘታቸውን አመልክተዋል፡፡
በመላው የመካከለኛው ምስራቅ አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ጉዳይ ዕረፍት የሚሰጥ እንዳልሆነ የጠቆሙት “ጥቁሩ ሰው” ሳዑዲ ካላትና ከምትከተለው “የበርህን ዝጋ ፖሊሲ” አንጻር በአካል በቦታው ላይ ከመገኘት ይልቅ አቅም ካላቸው ዓለምአቀፋዊ አካላት ጋር በአፋጣኝና በቅርበት መሥራቱ ድርጅታቸው የወሰደው አማራጭ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ የሎጂስቲክሱ ጉዳይ መስመር ሲይዝም የጋራ ንቅናቄው ከዚህ በፊት በየአገራቱ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ጉዳይ ሲያስፈጽምበት የነበረውንና በውጤታማነቱ የሚታወቀውን አማራጭ እንደሚተገብር ጨምረው ገልጸዋል፡፡
ኢህአዴግ አገርን እንደሚያስተዳድር ድርጅት በዜጎቹ ላይ እየደረሰ ያለውን አስነዋሪ ተግባር ትኩረት ሰጥቶ አለመመከቱ ተቃውሞ አስነስቷል፡፡ ይህንኑ አስመልክቶ አቶ ኦባንግ ሜቶ “ወገኖቻችንን ድንበር በማሻገርና ኤጀንሲ ከፍተው ወደ አረብ አገራት ሲልኩ የነበሩት ሁሉ ሕግ ፊት ቀርበው ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኙ የተለያዩ ተግባራት” እየተከናወኑ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
alamudi-ሼክ መሐመድ አላሙዲ የሠራተኛ ኃይል ወደ ሳዑዲ እንዲላክ ከኢህአዴግ ጋር በይፋ ስምምነት ማድረጋቸው የሚታወስ ነው፡፡ ኢንቨስትመንትን በተመለከተ ከሚፈልጉበት ክልል መሬት ለመውሰድ፣ ከሚፈልጉበት ባንክ ኮሪደር ገንዘብ ለመበደር ገደብ የሌላቸውና በሞቀበት ሁሉ ባለመጥፋት በጀት መድበው በሚያስተዳድሯቸው ሚዲያዎች እንዲሁም አንደበታቸውን በሙስና ላሰሯቸው ባለሥልጣናት “ኢትዮጵያዊ ነኝ” እያሉ በተገኙበት ቦታ ሁሉ ለሚዲያ ፍጆታ የሚደሰኩሩትና ግጥም የሚያስደረድሩት ሼክ መሐመድ አላሙዲ፣ “ወገኔ” የሚሉት ሕዝብ በአባታቸው አገር ወሮበሎች ሲያልቅና ሲጨፈጨፍ ዝም ማለታቸው ኢንቨስትመንቶቻቸውን ጥያቄ ውስጥ ከትቷል፡፡
አንዳንዶች እንደሚሉት ይህ አሰቃቂ ድርጊት መስመር ለቅቆ ከመውጣቱ በፊት የሳዑዲ አረቢያ ዜጎችን ከርስ እንዲሞላ በኢትዮጵያ የተቋቋመው ሳዑዲ ስታር ኩባንያ በገንዘብ እጥረት ሊዘጋ እንደሚችል መዘገቡ የሚታወስ ነው፡፡ በወቅቱ ሪፖርተር ባወጣው ዘገባ ሳዑዲ ስታር በኪሣራ ወደ መዘጋት መድረሱ የኩባንያው “ባለቤት የሆኑትን ሼክ ሙሐመድ አል አሙዲንና የሳዑዲ ዓረቢያን ስም የሚያጎድፍ ከመሆኑም ባሻገር፣ ኢትዮጵያ ውስጥ እስኪታክት የተወራለት ይህ ፕሮጀክት መና መቅረቱ ሁለቱን አካላት በሕዝቡ ዘንድ ለከፍተኛ ትችትና ወቀሳ እንደሚያጋልጣቸውም” ጠቁሞ ነበር፡፡
mohammed bin nayef
ልዑል ሞሐመድ ቢን ናይፍ
በአሁኑ ጊዜ “ሕገወጥ ናችሁ” በሚል ሰብዓዊነት የጎደው እርምጃ እየተወሰደባቸው ያለው የበርካታ አገራት ዜጎች በተለይም ኢትዮጵያውያን ላይ የሚፈጸመውን ሰቅጣጭ ተግባር ሕገወጦችን የማባረር “ዘመቻ” በማለት ያቃለሉት የሳዑዲው አገር ውስጥ ሚ/ር ልዑል ሞሐመድ ቢን ናይፍ ወንጀለኛ ሬንጀር ለባሾችን፣ ፖሊሶችንና ወሮበሎቹን ሸባቦች አደፋፍረዋል፡፡ “ዘመቻው ይቀጥላል … በተወሰነ ጊዜ የተገደበ አይደለም” በማለት “እስክንጨርስ እንጨርሳችኋለን” የሚመስል የማፊያ መሪ መሰል መልዕክት ለአንጋቾቻቸው አስተላልፈዋል፡፡
አብዛኛዎቹ ኢትዮጵያውያን በሕጋዊነት የሚኖሩትም ጭምር በሳዑዲ ያለው ሁኔታ አሳሳቢነት ወደፊት ችግር ውስጥ ሊከትታቸው እንደሚችል በመገመት ወደ አገራቸው መመለስ ይፈልጋሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት ለከፍተኛ ሰቆቃ የተጋለጡት ኢትዮጵያውያን “ቤት አለን ቤታችን መልሱ” እያሉ የሰቆቃና የድረሱልን ጥሪ በሚያስተላልፉበት ወቅት ሰብዓዊነት የጎደላቸው የኢህአዴግ መሪዎች ይህ ነው የሚባል አፋጣኝ ምላሽ መስጠት አለመቻላቸው “በእርግጥ ኢትዮጵያውያን አገር አላቸው?” ብሎ የሚያስጠይቅ እንደሆነ በርካታዎች የሚጋሩት ነው፡፡
አቶ ኦባንግ በበኩላቸውም የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለአንድ ሳምንት ሥራውን አቋርጦ እንኳን ቢሆን ስደተኞቹን ባፋጣኝ የማመላለስ ተግባር መፈጸም ይገባው ነበር በማለት ቁጭታቸውን ተናግረዋል፡፡ ዜጎች በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታ ህይወታቸው እየተቀጠፈ “3ሺህ ዛሬ ገቡ … ድምሩ 10ሺህ ሆኗል …” የሚል የሞላ ጎደለ ቁማር ዓይነት ጨዋታ በትዊተር መጫወት የቴድሮስ አድሃኖምን ዘመነኛነት ሳይሆን ለሰውልጅ ህይወት ያላቸውን ደንታቢስነት የሚያሳይ መሆኑን ሁኔታው ያስቆጣቸው አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ አቶ ኦባንግም “ቤቴ መልሱኝ” ብሎ ለሚለምን አንድ ዜጋ የተከፈለው ተከፍሎ ትራንፖርት በማቅረብ ክቡር ህይወትን በአስቸኳይ ለመታደግ አለመቻል ለትውልድ የሚተላለፍ የታሪክ ጠባሳ መሆኑን በአጽዕኖት ተናግረዋል፡፡
source http://www.goolgule.com

Tuesday, November 19, 2013

የሳዑዲ ጉዳይ፡ ካስጨነቀ፣ ካስጠበበን የመንፉሃ ሁከት መልስ! – ነብዩ ሲራክ ከሳዑዲ (ጋዜጠኛ)

    ትናንት እንደ ቀልድ  …      የማለዳ ወግ
        በያዝነው የፈረንጆች 2013 ዓም በወርሃ መጋቢት አጋማሽ የሳውዲ አረቢያ መንግስት ” ህጋዊ ሰነድ ያልያዙትን አስወጣለሁ !” ብላ አወጀች ። ቀጠለና አፈሳ አሰሳው ተከተለ! አስፈሪው ያ ክፉ የጭንቅ ቀን በሳውዲው ንጉስ ሌላ የምህረት አዋጅ ተተክቶ ህገ ወጥ  የተባሉትን ህጋዊ በሚያደርግ ህግ ተተካና የምህረቱ አዋጅ በያዝነው ህዳር መባቻ እንደሚያልቅ በተጠቆመው አዲስ የምህረት አዋጅ ተተካ ! በሂደቱ የታደሉት የተበላሸ መኖሪያ ፍቃድን ከማደስ ጀምሮ አዲስ ፈቃድን አገኙ ። ያላለላቸው ከፖስፖር እድሳት መዘግየት ጀምሮ አዲስ ለማውጣት ባለው ውስብስብ የኢንባሲና የቆንስል አሰራሮች ህልማቸው ሳይሰምር እዚህ ደረሱ …ወደ ሃገር ለመግባት ፈልገው ከሃገራቸው ተወካዮች ህጋዊ ሰነድ ለማግኘት ሳይችሉ ቀሩና ተሰነካክለው ቀሩ  !  በላይ በታች ብለው የመውጫ ሰነዱን ያገኙት ጥቂቶች በሰላም ወደ ሃገራቸው በሰላም ሲሸኙ የቀሩት ብዙዎች ደግሞ ሳውዲዎች እንደለመዱት ይለሳለሳሉ ብለው ከፉውን ጥቂት ቀን እቤታቸው መሽገው ሊያሳልፉ ተዘናጉ …
    አደጋውን በቅርብ የሚያዩት የመንግስታችን ተወካዮች ዜጎቻቸውን ሰብስበው መምከር ሳይችሉ ቀሩ! እንዲህ እያለ ቀን ቀንን ወልዶት የምህረቱ አዋጁ ህዳር ላይ ባባተ ማግስት ግን ዜጎች አደጋ ላይ ወደቁ … ይህ በሁሉም ሃገር ዜጎች የመጣ ነበርና በጸጋ መቀበል የግድ ነበር ። ፍተሻ አሰሳው በመላ ሳውዲ ተጠናክሮ ሲቀጥል ቤት ” ለበቤት ፍተሻ አይደረግም !” የሚል መመሪያ ወጣ ። ይህ መመሪያ ብዙዎችን አስደሰተ! ሪያድ መንፉሃ ላይ ግን መመሪያው በእኛ ዜጎች ላይ ብቻ ተጣሰ  … ህጋዊ የመንፉሃ ነዋሪዎች ሳይቀር የጥቃቱ ዳፋ ቀማሽ ሆኑ ። መንፉሃ ተሸበረች ! የሃበሻ ልጅ ቤቱ እየተሰበረ ያለ ገላጋይ በወሮበላ አረብ ወጣቶች ተቀጠቀጠ  ፣ ንብረቱ ተዘረፈ ፣ ተደፈረ ! የጸጥታ ሃይሎች ቤት እየሰበሩ በመፈተሽ ወንዶችን ወደ እስር ቤት እየተለዩ ሲልኩ “ጅብ በቀደደው ውሻ …!”  እንዲሉ በፈታሾች እግር”ሸባብ ” የሚባሉት ወጣት አረቦች ንብረት ከመዝረፍ ጀምሮ አቅመ ደካማ ሴት እህቶችን አጠቁ!  ቁጣ ተቀሰቀሰ!
       ይህን ግፍ  የተመለከቱ ደራሽ ገልጋይ አጥተው ተስፋ የቆረጡት ወጣት ኢትዮጵያውን ወንድሞች በአካባቢው ሳውዲዎች ዝር እንዳይሉ በማድረግ መኪናዎችን መሰባበር ያዙ! ሁከቱ ግሞ የበቀል እርምጃው በነጭ ላባሾች ተካሄደ! ጥቃቱን የአካባቢውን ነዋሪ እርምጃ ያስከፋው ነዋሪ ሻንጣውንና ቤተሰቦቹን ይዞ አደባበይ በመውጣት “ሴቶቻችን አይደፈሩ ፣ ከነቤተሰቦቻችን ወደ ሃገራችን መልሱን! ” የሚል ድምጹን በአደባባይ ሲያሰማ ከጸጥታ አስከባሪዎች ጋር ወደ አላስፈላጊ ግጭት አመሩ ! ተነግሯቸው መስማት ያልቻሉት የመንግስት ተወካዮች ጣልቃ ገብተው መብት ማስከበሩ ቢቀር  መሸምገል ሳይችሉ ቀረና የተፈራው ደረሰ  !
ዛሬ …በተስፋ 
ዛሬ ሌላ ቀን ነው! መንፉሃ ላይ ቁጥሩ በውል ያልታወቀ የወገን ደም ተገብሮ የሳውዲ መንግስት ህገ ወጥ ባላቸው ዜጎች ላይ የጣለው የመቶ ሽህ ብር ቅጣትና የሁለት አመት እስራት ተነሳ  ! እስካሁን ባለው መረጃ 50 ሺህ የሚገመት ወገን ወደ ሃገሩ ለመግባት በማቆያ እስር ቤት እና በመጠለያ ከትሟል! የእኛ ነገር “ሰርገኛ መጠሰ በርበሬ ቀንጥሱ !” ሆነና  የመንግስት ተወካዮች በስደተኛው መብት መከበር የማይተጉ ሃላፊዎችን በቅርብ መልምሎ እርምጃ በመውሰድ የስደተኛውን ህይወት ያልደገፈው መንግስታችን ዜጎች በከፋ ችግር ማጥ ስንወድቅ አለሁላችሁ እያለን ነው ። ” የምትኮሩበት ሃገር አላችሁ!  ኑ በእቅፍ እንቀበላችኋለን! ” ማለትም ጀምሯል!  አዎ!  ደስ ይላል!

ዛሬ የሰሞኑ ሮሮ በረድ ብሎ ብሏል! በውጭ ሃገራት የሚገኙ ኢትዮጵያውያንም የሳውዲ መንግስት በወገኖቻቸው የደረሰውን አሰቃቂ በደል ተመልክቷልና ሰብአዊ መብት ረገጣውን ከማውገዝ ባለፈ እርዳታ እያሰባሰቡ መሆኑን መስማት ያሰደስታል!  ለዚህ መሰሉ አለም አቀፍ እንቅስቃሴ  ታላቅ አክብሮት አለኝ !  በሳውዲ የከተምን ከአራት መቶ ሺህ በላይ የምንገመት የዚያች ሃገር ዜጎች አለንና ተቃውሞው በቀልን እንዳያጭር ያሳስበናል ።
ሳውዲና የእኛ ስደት   …
     ሰማችን ማንቴስ ብለንና እድሜያችን ቆልለን ከደላንና ከቀናን በጠያራ ፣ አልሆን አልመች ሲል የባህር የበርሃውን ሰቆቃ ተፋጥጠን እዚህ ለደረስነው ኢትዮጵያውያን ሳውዲ አረቢያ ባለውለታችን ናት !  በአብዛኛው በሳውዲ አሰሪዎችና በአንዳንድ የመንግስት ተቋማት ሰራተኞች የሚደርስብንን የመብት ጥሰት ችለን ላለፍን ሰላማዊ ነዋሪዎች “በሰብአዊ መብት ጥሰት የምትወነጀለው አረባዊቷ ሀገር ከሀገራችን የተሻለች ናት! ” እስከ ማለት መድረሳችን እውነት ነው ። ስለ እውነት እንነጋገር ከተባለና የሰብአዊ መብቱን ነገር ችላ ብለን ራስን መደገፉ ካመራን ሳውዲ አረቢያ  ራሳችን ጠቅመን ቤተሰቦቻችን መጥቀም የቻልንባት ሁለተኛ ሃገራችንናት ብል ማጋነን አይቦንም ። ይሁንና ይህች የምናመሰግናት ሃገር አልፎ አልፎ  ከምታወጣው ህግ ጋር በተገናኘ  የእኛን መብት የሚያስከብርልን ጠንካራ ተወካይ  አጥተን ህግ እየተጣሰ ተጎድተናል። ይህ ብቻ አይደለም በግርድፉ እናውራው ካልን ህግና ስርአትን ተከትለው የማይኖሩ ወገኖች በሚሰሩት ህገነወጥ ስራ በሚሰጠን ስም ገጽታችን ከመጉደፉ አልፎ ተርፎን “ለሃጥአን የመጣው ለጻድቃን !” እንደሚባለው  የሃጥአኑ ጥቃት ለቀረው ሰላማዊ ነዋሪ ሲተርፈው የመንግስት ተወካዮቻችን ዋቢ አልቆምልን እያሉ ኑሯችን ከፍቷል ። ካለን የገቢ ምንጭ አንጻር አኗኗራችን በህብረት መሆኑም ጎድቶናል። ይህ ከጥቂቱ ጉዳት መካካል ጥቂቱ ቢሆንም ኑሯችን ካከፋው ምክንያትነት ቀዳሚ ለመሆኑ ጥርጥር የለኝም!  ከዚህ አንጻር በሰሞኑ አሰሳና ፍተሻ በላቡ ከሚያድረው ጎልማሳ እና ጉብሏ ጀምሮ አባወራው ሆነ የቤት እመቤቷ ህገ ወጥ ተብለን እንደወጣን ልንቀር የምንችልበት አደጋ ተደቅኖብናል። ዜጎች በከባድ ውጣ ወረድ ለአመታት ያፈራነው  ሀብት ቀርቶ የአብራክ ከፋይ ልጆች ቤተሰቦቻቸውን ሳይሰናበቱ ከሀገር ለሚባረሩበት አካሄድ በምክክር መላ ካልተበጀለት  አሰፈሪና አስደንጋጭ ነው !
የወገን ቁጭትና ቁጣ እና ቁጣው የደረሰው የሳውዲ መንግስት …
    በመንፉሃን የተፈጸመብንን ቅጥ ያጣ ጥቃት ተከትሎ ግፍ በደል መከራውን በዘመንኛው የመረጃ መረብ ሲናኝ ሃዘናችን የተጋራው ከሃገር ቤት ጀምሮ በመላ አለም ከጫፍ እስከ ጫፍ በቁጣ የተነሳው የኢትዮጵያን ቁጣ መልዕክት ለሳውዲዎች ደርሷቸዋል። ወደ ቀጠለው አለም አቀፍ  ከጅምሩ ሳውዲን ከአልቃኢዳ ጋር በመወንጀል የተጀመረው አስፈሪ የነበረ ቢሆንም  በቀጣይ ሰልፎች ጥያቄው ሰብአዊ መብትን አክብሩ በሚል መሻሻሉ ለሳውዲ ንጉሳዊ ቤተሰቦች እያስተላለፈ ያለው መልዕክት ቀላል አይደለም ባይ ነኝ ።  በዋሽንግተኑ የመጀመሪያ ተቃውሞ የተሰማው ሳውዲን ከአልቃኢዳ ጋር አጎዳኝቶ የመወንጅል እና ከበቂ ማነስ የተነሳ የብዙሃን ሙስሊማንን መመሪያ የቁርአን መልዕክት በነጭ ቀለም የተጻፈበትን ደማቅ አረንጓው የሳውዲ አረቢያ ባንዴራን ወደ ማንቋሸሽ  እንዳያመረ የነበረን ስጋት መወገዱ ያስደስታል ። ይህም ብዙ የሳውዲ ነዋሪዎችን አስደስቶናል!
ለተፈጸመው ግፍ ማካካሻ ባይሆንም በመጠለያዎች የምንሰማው የሰቆቃ ጩኸት ረገብ ብሏል። የሳውዲ መንግስት በመጠለያ ያሉትን ዜጎች መጠለያ ሲታይ የሰነበተውን የምግብ ፣ የውሃ እና የህክምና አቅርቦት እያስተካከለው መገኘቱን ከመጠለያው ከሚገኙ ግፉአን ማረጋገጥ ችያለሁ ። በቀን አንድ ሚሊዮን ብር የሚደርስ ወጭን የሳውዲ መንግስት ፣ ከማውጣት ጀምሮ ወደ ሃገር ቤት መግባት የሚፈልጉ ኢትዮጵያውንን ለማሰባሰብ 300 ያህል አውቶቡሶች በሪያድ በመካ ተመድበው የማጓጓዙን ሂደት ከጀመሩ ቀናት ተቆጥረዋል።  ወጭውን ይሸፍነዋል ተብሎ ከተነገረኝ ከኢትዮጵያ አየር መንገዳችን ወደ ሃገር ቤት የማጓጓዙ ዘመቻ ጎን ለጎን የሳውዲ መንግስት በሳውዲ አየር መንገድ በኩል ነጻ የማጓጓዝ ስራ  በመካሄድ ላይ መሆኑን መረጃዎች ደርሰውኛል ።
መልካሙ ጅምር ፣ ሰው ሃይልና የመረጃው እጥረት…

       ከላይ ለመጠቆም እንደሞከርኩት በሪያድና በመካ ስደተኛን የመቀበሉ ስራ እየተሰራ ቢሆንም በማቆያው ባለው የስደተኛ ብዛት አንጻር በጅዳ ወደ ሃገር መግባት የሚፈልጉትን  ወደ ማረፊያ የማጓጓዙም ሆነ ባሉበት የመመዝገቡ እንቅቃሴ በጅዳ ገና አልተጀመረም ። በጅዳ የሽሜሲማረፊያ እስር ቤትና በሪያድ መጠለያ ያለውን ምዝገባ እና የመጓጓዣ ሰነድ አቅርቦት ለማሳለጥ የኢትዮጵያ መንግስት ልዑክ እና ድጋፍ የሚሰጡ ሃላፊዎችን አሰማርቶ ስራው እየተሰራ ቢሆንም ከፍተኛ ቁጥር ላለው ዜጋ ግልጋሎት ለመስጠት የሰው ሃይል እጥረት መስተዋሉ አልቀረም። ለዚህ ጥሩ ምሳሌ የሚሆነን በቅርቡ ለቀናት ዝግ የነበረውን የጅዳ ቆንስል አመዘጋት መጥቀስ ይቻላል። ምንም እንኳን ቆንስል መስሪያ ቤቱ ስራውን ለቀናት የዘጋበትን ምክንያት በግልጽ ባወጣው ማስታወቂያ አልተገለጸም ። ምክንያቱ ባልተገለጸው የጅዳ ቆንስል መዘጋት ብዙዎችን አስቆጥቷል ” የታመመ ቢሞት እንዴት እንቅበር? ፖስፖር ለማሳደስ ፣ የታደስ ለመቀበል ፣ ሰነድ ማስተካከል ቢያስፈልግ ፣ የጋብቻ ወረቀት ማረጋገጫና እና ተመሳሳይ ግልጋሎት ስንፈልግ የት እንሂድ? ” ሲሉ በማጠየቅ በአስቸኳይ ቆንስሉ እንዲከፈት ነዋሪዎች መንግስትን ተማጽነዋል። የቆንስሉን መዘጋት ምክንያት ሃላፊዎችን ጠይቀን መላሽ ብናጣም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩም ቴዎድሮስ አድሃኖም “የጅዳ ቆንስል አገልግሎት እንዳይሰጥ የተዘጋው የቆንስላው ሰራተኞች ስደተኞቹን ወደ ሀገራቸው ለመመለስ እንዲያግዙ ስለተፈለገ ነው ” ብለው በትዊተር መረጃ አቀብለውናል። ይህ የሚያሳየው የሰው ሃይል እና የመረጃ ልውውጥ እጥረት መሆኑን ለመረዳት መማር መመራመርን አይጠይቅም። ይህ እውነታ ፈጦ እያለ የጅዳ ቆንስል ሃላፊዎች ግልጋሎት ለመስጠት ፈቃደኛ የሆኑትን የኮሚኒቱ መስሪያ ቤትና ችግሩ ችግራችን ነው በሚል መክረውና ዘክረው አቤቱታ ያቀረቡ ወገኖችን ለመቀበል አልደፈሩም። ምክንያቱን የሚያውቁት ሃላፊው ቢሆኑም ሲሆን ነዋሪውን አስቸኳይ ሰብሰባ ጠርተው ፣ ያ ቢገድ የድጋፍ ጥያቄውን በበጎ ተመልክተው አፋጣኝ እርምጃ መውሰድ አለመቻላቸው ሂደቱን ከመሳለጥ እንዳይገታው ስጋት አለ። ሌላው በሪያድና በጅዳ ሃላፊዎች ዙሪያ የሚታየው የመረጃ ክፍተት የግልጋሎት አሰጣጡን አልፎ አልፎ የሚስተዋለውን የመብት ገሰሳ ከቁጥጥር ውጭ እንዳያወጣው ትኩረት ሊሰጠው ይገባል። ለዚህም በሪያድ መንፉሃና በተለያዩ አካባቢዎች ፣ በጅዳና በመካ “ወደ ሃገራችን ውሰዱን ?” በሚሉ ዜጎች እና በመንግስት ጸጥታ አስከባሪዎች መካከል የሚፈጠሩ  ፍጥጫና ግጭቶችን በመንፉሃ የታየውን አደጋ እንዳይደግመው ለመከላከል ይረዳል። በመንፉሃ ባየነው የተንቀሳቃሽ ምስል ባየነው ድብደባና ውክቢያ አድራሻቸው የጠፋ ወገኖች በፖሊስ ጣቢያዎች፣ በሆስፒታልና በመጠለያው ፈልገው ያጧቸውን ወገኖቻቸውን በሚመለከት መረጃ ለመስጠት ፈልገው ወደ መንግስት ሃላፊዎች ቢደውሉም ምላሽ  እንዳላገኙ በምሬት የገለጹልኝ በርካታ ናቸው ። በውክበቱ ጉዳት የደረሰባቸው ወገኖች የትየለሌ የመሆናቸውን ያህል የደረሱበት የማይታወቅ ዜጉች ጉዳይ ከሚሰራው የማጓጓዝ ስራ በተጓዳኝ በመረጃ ልውውጥ ተደግፎ መሰራት ያለበት ስራ ነው ። ይህንና ይህን መሰል ጉዳዮችን ስንመለከት በመንግስት ሃላፊዎች የመረጃ ተቀባይ አለመኖር ነገ  ቢያንስ ለህሊናችን ተወቃሽ እንዳያደርገን ዛሬ መሰራት ያለበት ስራ ነው ባይ ነኝ።  ከዚህ አንጻር መረጃ ትልቅ አስተዋጽጾ እንዳለው በቦታው የሚገኙ የመንግስት ተወካዮች ሊያጤኑት ይገባል። ይህን ክፍተት ለመዝጋትም  የአደጋ ጊዜ ተጠሪና መረጃ ተቀብሎ የሚያጣራ ኮሚቴ በአፋጣኝ ሊቋቋም ይገባል። የኮሚቴው አባላትም ነዋሪውን ሃያ አራት ሰአት ክፍት የሆነ ነዋሪውን የሚያስተናግዱበት ስልክ ሳይውል ሳያድር መሰራት ካለበት ስራ አንዱ መሆኑን ማጤን ብልህነት መሆኑን ጠቁሜ የማለዳ ወጌን ልቋጨው ወደድኩ ..
እስኪ ቸር ያሰማን!
ነቢዩ ሲራክ
source -ze-habesha

Saturday, November 16, 2013

ዓለምአቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያውያን መብት በሳኡዲ አረቢያ Global Alliance for the Rights of Ethiopians in Saudi Arabia

ህዳር 6 ቀን 2006 ዓ/ም

 አስቸኳይ መግለጫ

በቅርቡ፤ በተከታታይና በሚዘገንን ደረጃ በሳውዲ አረቢያ በኢትዮጵያዊያን ላይ የሚካሄደውን እልቂት ለማስቆም ብሄራዊ
ግብረ ኃይል እአ በ November 12, 2013 በተደረገ አስቸኳይ ስብሰባ ተመሰርቷል።

በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን፤ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ለሰብአዊ መብቶች፤ ለሰዎች ክብርና የህይወት ክቡርነት
የቆሙ ሁሉ የሳውዺ የጦር፤ የፖሊስ፤ የጥበቃና ሌሎች በመንግሥት የተደራጁ ወጣት ቡድኖች በሰላማዊ ኢትዮጵያዊያን ላይ
የሚያደርጉት ግድያ፤ አስገድዶ መደፈር፤ ግለሰቦችን በገመድ አንቆ ዛፍ ላይ መስቀል፤ ገረፋ፤ በሓያኛው መቶ ክፍለ ዘመን
ከሰለጠነ መንግሥት በማይጠበቅ ደረጃ ግለሰቦችኝ እንደ እንሰሳ አስሮ በመንገድ መጎተት ወዘተ ለህሊና የሚቀፍ ድርጊት።
እኛም በንፁሕ ኢትዮጵያዊያን ላይ መፈፀሙ አስቆጥቶናል፤ አሳዝኖላን፤ አበሳጭቶናል፤ ቀስቅሶናል፤ ለወገኖቻችን መብት
እንድንነሳና ከሚመለከታቸው ጋር አብረን ድምጻችንን እንድናሰማ አስገድዶናል። በመጀመሪያ ደረጃ የምንጠይቀው፤ የሳውዲ
መንግሥት ሃላፊነቱን በመወጣት ይህ አሰቃቂ እልቂት እንዲቆም ማድረግ ነው። ከዚህ ጋር አብረን የምናሳስበው ለሰብእነትና
ለሰው ክብር የቆመው የዓለም ህብረተሰብ ሁሉ ይህን አሰቃቂ ድርጊት ተቀዳሚነት በመስጠት እንዲቆም ማድረግ የሞራል
ሃላፊነት አለበት የሚል ነው። የኢትዮጵያዊያን ህይወት እንደ ማንኛውም ሰባዊ ፍጡር ትልቅ ዋጋ ያለው መሆኑን
እናሳስባለን።
ይህን የተቀደሰ ዓላማ ስኬታማ ለማድረግ የሚከተሉትን ለሰብአዊ መብት፤ ለሰው ክብርና ነጻነት፤ ለእውነተኛ እኩልነት
የቆሙ ሶስት ግለሰቦች በአሰባሳቢነት መርጠናል፤
1. አቶ አበበ ገላው
2. አቶ ብርሃኑ ዳምጤ (አባ መላ) እና
3. አቶ ታማኝ በየነ።
ኢትዮጱያዊያን፤ በተለይ ወጣት ወንዶችና ሴቶች በሳውዲ አረቢያና በሌሎች የመካከለኛው ምስራቅ አገሮች በገፍ
የሚሰደዱበትና በሰላም ሰርተው ለመኖር የሚፈልጉበት ምክንያት በአገራቸው የስራ፤ በሰላም የመኖር፤ የራሳቸውን ስራ
የመፍጠር፤ መብታቸውን የማስከበር እድል ስለሌላቸው ነው። ስለሆነም፤ የሳውዲ አረብያ የጥበቃ፤ ፖሊስና ወጣት አፋኝ
ቡድኖች በኢትዮጵያዊያን ላይ የሚደርጉት ግድያ፤ አፈናና ማሳደድ ከዚህ በፊት ታይቶ የማይታወቅ፤ ለህሊና የሚቀፍ፤
በተባበሩት መንግሥታት ውሎች የተከለከለ፤ የሰለጠነው ዓለም የማይቀበለው በሰብእነት ላይ የተፈፀመ ወንጀል ነው። ይህን
አሰቃቂ ድርጊት የአይን ምስክሮች፤ የቢቢሲ፤ የአልጀዚራና የግል ታዛቢዎች በቪዲዮ ቀርፀው ለዓለም ሕዝብ
አሰራጭተውታል። ከዚህ የበለጠ ምስክር ሊኖር አይችልም። የሳውዲ አረቢያ መንግሥት ሆነ ብሎ የሚያደርገው ህገ ወጥ
ድርጊት መሆኑን አንጠራጠርም፤ ስለሆነም፤ ይህን አሰቃቂ ተግባር ማቆም ያለበት የሳውዲ አረቢያ መንግሥት መሆኑን
እናሳስባለን።

ከላይ እንዳሳየነው፤ ኢትዮጵያዊያን አገራቸውን ለቀው እንዲሰደዱ፤ ሲሰደዱ አሰቃቂና ለህሊና የሚዘገንን ግድያ፤ እስራትና
ሌላ ኢ-ሰብአዊ ወንጀል የሚፈፀምባቸው ወደው አይደለም። አብዛኛው የኢትዮጵያ ወጣት ትውልድ በአገሩ ህይወቱንና
ቤተሰቡን የሚደግፍበት ስራ የለውም፤ የኑሮ ዋስትና የለውም። የሕግ የበላይነት ስለሌለ፤ ከሕግ ውጭ የሆነ አፈና፤ ግድያ፤
እስራት፤ ኢ-ሰብአዊ ቅጣት፤ የውስጥና የውጭ ስደት፤ መባረር ወዘተ እጣው ሆኗል። ስለዚህ ነው ብዙ ሽህ ኢትዮጵያዊያን
ብዙ ሽህ ብር ከፍለው ለህይወታቸው አደጋን የሚጋብዝ ጉዞ የሚያደርጉት። አሰቃቂ ሆኖ ያገኘነው፤ ኑሯችንን እናሻሽል
ይሆናል ብለው ያደረጉት ተስፋ ወደ ጨለማ መርቶ ለህይወታቸው መጥፊያ፤ ለአካለ ስንኩልነት፤ ለክብራቸው መገፈፊያ
ወዘተ ምክንያት መሆኑ ነው። ይህ በሃያ አንደኛው መቶ ክፍለ ዘመን የመጣ “የባርነት” ሁኔታ መፈጠሩን ያመለክተናል፤
መቆም አለበት የምንለው የእነዚህ ወገኖቻችን መዋረድ የሁላችንም ክብር መገፈፍ መሆኑን ስለምንረዳ ጭምር ነው።
ኢትዮጵያዊያን በያሉበት በመገናኛ ብዙሃን፤ በድህረገጾች፤ በሰላማዊ ሰልፍና በሌሎች መንገዶች የሚያሳዩት ጥረት የሚያኮራ
ጅምር ነው። በዚሁ መሰረት የሳውዲ አረቢያ መንግሥት የሚያደርገውን አሰቃቂ ግፍ ለዓለም ህብረተሰብ ለማጋለጥ፤
ወንጀሉን የፈፀሙ ሁሉ በሃላፊነት ለፍትህ ለማቅረብ የሚደረገው ተግባር በተከታታይና አስተማማኝነት ባለው ደረጃ
እንዲካሄድ ቆርጠን ተነስተናል። የተቋቋመው ግብረ ኃይል ዋና ሚና በሳውዲ አረቢያ የሚካሄደውን ወንጀል
ለሚመለከታቸው የዓለም ህብረተሰብ የሰብአዊ መብቶች፤ የፍትህ ተቋሞች፤ የለጋስ ድርጅቶችና ሃላፊዎች ማሳወቅ፤ ቅስቀሳ
ማድረግ፤ የገንዘብና ሌላ ቁሳቁስ ድጋፍ ለወገኖቻችን ለማቅረብ ጥረት ማድራግን ይጨምራል። በዚህም መሰረት፤ ግብረ
 ዓለምአቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያውያን መብት በሳኡዲ አረቢያ
Global Alliance for the Rights of Ethiopians in Saudi Arabia







ኃይሉ፤ እውቅና፤ ተቀባይነትና አስተማማኝ የሆኑ የሰብአዊ መብቶች ድርጅቶችን፤ ሊቆችን፤ ጠበቃዎችን ወዘተ፤ በመቅረብና
በመቀስቀስ፤ የሳውዲ መንግሥት በሰብአዊነት ላይ ያደረገውንና የሚያደርገውን ወንጀል (Crimes against humanity)


ለፍትህ ለማቅረብ የተቻለውን ሁሉ ያደርጋል። በተጨማሪ፤ በሳውዲ አረቢያ ያለውን ሁኔታ በቀጥታ ለመመራመርና
እውነተኛውን ዝርዝር ሁኔታና ስእል ለመገንዘብ አንድ ቡድን ለመላክ አቅዷል።
ይህ የተቀደሰና ሁሉም ኢትዮጵያዊያን፤ የሰው ክብርና መብቶች ደጋፊ የሆኑ ድርጅቶችና ግለሰቦች እንዲሁም መንግሥታት
በያሉበት የሚጋሩት አስቸኳይ ጥሪ ፋታ አይሰጥም። ግድያው፤ ገረፋው፤ እስራቱ፤ የሴቶች ክብር ድፍረቱ ወዘተ የሁላችንም
ስለሆነ ዓለም አቀፍ ጥረት ያስፈልገዋል። ሁላችን ሌሎችን በመቀስቀስ ይህ ግፍ በፍጥነት እንዲቆም በተግባር ማሳየት
የሞራል ግዴታችን ነው። ወንጀሉን የፈፀሙት የሳውዲ አረቢያ ባለስልጣናትና ሌሎች ተሳታፊዎች በሃላፊነት ተጠያቂ መሆን
አለባቸው። የሳውዲ መንግሥት ባለስልጣናት የኢትዮጵያዊያንን መብቶች ገፈው፤ ገድለው፤ አዋርደው፤ አሳደው፤ ሰቅለው፤
ክብር ገፈው በኢትዮጵያ ያላቸውን ዘላቂ ጥቅም ለማስከበር እንደማይችሉ ማመን አለባቸው። ይህን ማሳመን መቻል
አለብን።

የተፈጸመውን አሰቃቂ ግድያ፤ ድፍረትና ሰቆቃ ኢትዮጵያውያንና የዓለም ሕብረተሰብ እንዲያወግዝልን ድርጅታችን ጥሪውን
ያቀርባል። በተጨማሪም፤ በኢትዮጵያዊያን ስደተኞች ላይ አስከፊና ኢሰብአዊ ድርጊት የፈጸሙት ሁሉ ተጠያቂ እንዲሆኑ
እናሳስባለን። እንዲሁም፤ በመረጃና ተሞክሮ መጋራት፤ ኢትዮጵያውያንን ከሳውዲዎች ሰቆቃና ግድያ ለማትረፍ
ስለሚያስፈልገው እርዳታ ሁሉ ኢትዮጵያውያንና ለሰብአዊ መብት የሚታገሉ ድርጅቶች እንዲተባበሩልን ከአደራ ጋር
እንጠይቃለን።

ይህን ለማድረግ የምንችለው ለዚህ ዓላማ በያለንበት ስንነሳ፤ አብረን ተባብረን ስንሰራ፤ ለወገኖቻችን መቆማችንን በተግባር
ስናሳይ፤ ዜና፤ ሃሳብ፤ እውቀት፤ ልምድ፤ ስንለዋወጥ፤ የገንዘብ ሆነ ሌላ አስተዋፅኦ ስናደርግ ነው። ይህን በተቀነባበረና ስልት
ባለው መንገድ ከሰራን በወገኖቻችን ላይ የደረሰውንና የሚደርሰውን እልቂት ለማቆም እንችላለን። የወገኖቻችንን ክብር
በመታደግ፤ የራሳችንን ክብር ለማስከበር እንችላለን።



ሁሉም ህይወት እኩል ዋጋ አለው!!!


Contact information:

Telephone: (877)RING-ETHIOPIA or (877)746 -4384

Email address: Alliance4rightsofethiopians.sa@gmail.com
source quatero

Thursday, November 14, 2013

በሳውዲ አረቢያ በሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ላይ የሚደርሰው ሰቆቃ አሁኑኑ ይቁም!!!

Posted by 
በሳውዲ አረቢያ በሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ላይ የሚደርሰው መከራ መስማት ህሊና መሸከም ከሚችለው በላይ ሆኗል። ኢትዮጵያዊን እህቶቻችን ወንድሞቻችን በአሰቃቂ ሁኔታ እየተገደሉ፤ አካሎቻቸው በስለት እየተቆራረጠ፤ እየተደበደቡና እየተደፈሩ ነው።
ይህ ሁሉ የሚፈፀው በሪያድ፣ ጂዳና አዲስ አበባ የሚገኙ የወያኔ ዲፕሎማቶች መልካም ፈቃድና ሙሉ ተባባሪነት መሆኑ ደግሞ ይበልጥ የሚያንገበግብ ነው። ወያኔ ለአረብ ሀብታም ሸሪኮቹ ለም መሬቶቻችንን ሰጥቶ ኢትዮጵያዊ በአገሩ ሠርቶ የእለት ጉርሱን መሸፈን የማይችልበት ደረጃ ላይ እንዲደርስ አደረገው። ቀጥሎ ደግሞ በሺዎች የሚቆጠሩ ልጃገረዶችና ወጣት ኢትዮጵያንን እየደለለ ከባርነት ላልተሻለ ግርድና አሳልፎ ሰጣቸው። ይህ ሁሉ ግፍ አልበቃ ብሎ “በሏቸው፤ ቀጥቅጧቸው፤ ህገወጦች ናቸው” እያለ በወገኖቻችን ላይ የሚደርሰውን ሰቆቃ በአጋፋሪነት እያስተናገደ ነው።
በኩየት በሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ላይ ተመሳሳይ ሰቆቃ ሊደርስ የሚችል መሆኑ ምልክቶች እየታዩ ነው። በኩዌት ያለአንዳች ምክንያት ቁጥራቸው በአንድ ሺህ በላይ የሆኑ ኢትዮጵያዊያን በድንገት ከሥራ ተባረዋል። እዚህም የወያኔ እኩይ እጆች እንዳሉት መረጃዎች አሉ። በሌሎች የመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች የሚገኙ ኢትዮጵያዊያንም ሕይወታቸው በዘወትር ስጋት ላይ ወድቋል።
የኢትዮጵያዊያን እጣ ፈንታ በአገር ውስጥም ከአገር ውጭም ሰቆቃና እንግልት መሆኑ የሚያሳዝን ብቻ ሳይሆን የሚያስቆጭ፤ ለመራራ ትግል የሚያነሳሳም ነው። ለአገሩ ሕዝብ የሚቆረቆር መንግሥት ኑሮን ቢሆን ኖሮ ሕይታችን እንዲህ የተመሰቃቀሰ ባልሆነም ነበር።
ግንቦት 7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ የሳውዲ አረቢያ እና ሌሎችም የመካከለኛ ምሥራቅ አገራት መንግሥታት ለኢትዮጵያዊያን እህቶቻንና ወንድሞቻችን ሰብዓዊ ክብር እንዲሰጡ አበክረን እናሳስባለን። ሰብዓዊ መብቶችን መድፈር ዓለም ዓቀፍ ወንጀል መሆኑን ልንነግራቸው እንፈልጋለን። በወገኖቻችን ላይ የሚደርሰው ሰቆቃ አሁኑኑ ይቁም!!! ሰቆቃ ፈፃሚዎች ለፍርድ ይቅረቡ!!!
በተቻለው ፍጥነትና ባገኘነው እድል ሁሉ ተጠቅመን ሕይወታቸው አደጋ ላይ ላሉት ወገኖቻችን እንድንደርስ ግንቦት 7 ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጥሪ ያደርጋል።
በኢትዮጵያዊያን ላይ የሚደርሰው ሰቆቃ በዘላቂነት የሚወገደው ወያኔ ከሥልጣን ተባሮ የኢትዮጵያ ሕዝብ የመረጠው መንግሥት ሲያስተዳድር በመሆኑ ለዚህ ታላቅ ግብ በኅብረት እንነሳ።
በወገኖቻችን ላይ የሚደርሰው ሰቆቃ ይቁም!!
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!!

Monday, November 11, 2013

ኢህአዴግና የሃይማኖት ነፃነት (ተመስገን ደሳለኝ)

ኢህአዴግና የሃይማኖት ነፃነት

…ኢሠፓ መራሹ መንግስት በኢህአዴግ ከተተካ ጥቂት ወራት ቢያልፈውም፣ የተራዘመው የእርስ በእርስ ጦርነት
ያልደረሰባቸው በደቡብ ኢትዮጵያ የሚገኙ አንዳንድ ከተሞችን ገና በቅጡ አልተቆጣጠራቸውም፤ በአናቱም
በኢሠፓ መንግስት ሽንፈት ሳቢያ እንዲበተን ከተገደደው የሀገሪቱ መደበኛ ወታደር፣ አብዛኛው ከእነ ትጥቁ
የትውልድ መንደሩንና ቤተሰቡን መቀላቀሉ በሀገሪቱ ላይ ከባድ ፍርሃት አንብሯል፤ በሰላም ወጥቶ ለመመለስ
እርግጠኛ መሆን የማይቻልበት ከበባዊ አየርም አስፍኗል፡፡ በበርካታ ቦታዎች ተጠንተውና ታቅደው የሚፈፀሙ
ወንጀሎችም፣ ከአምስት እስከ አስራ አምስት በሚደርሱ ወታደሮች የተደራጁ ልዩ ልዩ ህገ-ወጥ ቡድኖች
በየማዕዘኑ እያቆጠቆጡ መሆኑን አመላክቷል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ የአዲስ አበባ ቆዳ ስፋትና የነዋሪዎቿ የአኗኗር ዘይቤን በቀላሉ ለመልመድ የተቸገሩት
‹ተጋዳላዮች›፣ ለትንሽ ትልቁ ግርግር ጠብ-መንጃን እንደ መፍትሄ መምረጣቸው ችግሩን አባብሶታል፤ ጉዳዩ እያሳሰባቸው የሄደው
የኢህአዴግ ዋነኛ መሪዎችም እንዲህ አይነት አለመረጋጋቶችንና ስርዓት አልበኝነቶችን ለመቆጣጠር የመንፈሳዊ መሪዎች አስተዋፅኦ ወሳኝ
መሆኑን ከስምምነት ላይ ደርሰዋል (እንደቀድሞው ስርዓቶች ሁሉ ‹ለቅብሉነት› ከሚጠቀሙበት በተጨማሪ ማለት ነው)፤ ይሁንና
በመንበሩ ላይ የነበሩት አቡነ መርቆርዮስ ሀገር ለቀው እንዲወጡ በመደረጉ ክፍተት ተፈጥሯል፡፡

ይህን ጊዜም ነው ከ1973 ዓ.ም. ጀምሮ መኖሪያቸውን አሜሪካን ሀገር ያደረጉ አንድ መንፈሳዊ አባት ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጡ
የተወሰነው፤ በጥሪው መሰረትም ወደ ሀገራቸው ሲገቡ መንግስት የክብር አቀባበል አደረገላቸው፤ እኚህ ሰው ዛሬ በፓትርያርኩ መንበር
የተቀመጡት አቡነ ማቲያስ ነበሩ፡፡ ሆኖም ከሳምንት ሽር-ጉድ በኋላ አቡኑ የኢዲዩ አባል እንደነበሩ በአመራሩ አካባቢ ወሬው በስፋት
መሰራጨቱ ያልተጠበቀ ዱብ-ዕዳ አስከተለ፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ኢህአዴግ እና ኢዲዩ በ1970ዎቹ መጀመሪያ ትግራይና ጎንደር ውስጥ
በርካታ መስዋዕትነት ያስከፈለ ውጊያ ማድረጋቸው ብቻ አይደለም፤ የመጀመሪያዎቹ ሊቀ-መንበሮች ስሁል ገሰሰና መሀሪ ተክሌ (ሙሴ)
‹‹የተገደሉት በኢዲዩ ነው›› የሚለው ወሬ በድርጅቱ ውስጥ ከጫፍ ጫፍ የተናኘና የታመነበት ጉዳይ መሆኑ ነበር፤ በዚህም ላይ የህወሓት
መሪዎች ግራ ዘመምነት ተደማምሮ አቡነ ማቲያስ በወቅቱ ወደ ታሪክነት ከተቀየረ ዓመታትን ባስቆጠረው ‹‹ኢዲዩ›› ተፈርጀው፣
ከታጩበት የ‹ፕትርክና መንበር› ተገፈተሩ፡፡

ከዚህ በኋላ ነበር አብላጫውን የትጥቅ ትግል ዘመን በአሜሪካ ያሳለፉት አሰፋ ማሞ እና ብርሃነ ገ/ክርስቶስ ‹ውድብ› የሰጠቻቸውን
ተልዕኮ ተቀብለው ወደ ዋሽንግተን ዲሲ ያመሩት፤ እናም ቀድሞም ትውውቅ ወደ ነበራቸው ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ዘንድ ሄደው
ለ‹ፕትርክና ወንበር› መታጨታቸውን አበሰሯቸው፡፡ በእንዲህ ያለ መንገድ መንግስት የቀባቸው ታጋዩ አባ ጳውሎስም እስከ ህልፈታቸው
ድረስ አወዛጋቢ መሪ ሆነው ዘልቀዋል (በነገራችን ላይ በአሜሪካን ሀገር ለመጀመሪያ ጊዜ ከሲኖዶሱ ተነጥሎ የቆመ ቤተ-ክርስቲያን
የመሰረቱት አቡነ ጳውሎስ እንደነበሩ ይነገራል፡፡ አቡኑ ደርግ ለጥቂት አመት አስሮ ከለቀቃቸው በኋላ ወደ አሜሪካ ሄደው የፈጣሪያቸውን
ሰማያዊ መንግስት ሲሰብኩ ቆይተው፣ የህወሓት ሠራዊት ክንዱ እየበረታ በቁጥጥሩ ስር ያዋላቸው ከተሞችም እየበዙ ሲሄዱ፣ እርሳቸውም
ስብከታቸውን ወደ ትግርኛ ቋንቋ ከመቀየራቸውም በላይ፣ ለ‹ነፃ አውጪ›ው ድርጅት የገንዘብ ድጋፍ ያሰባስቡ ጀመር፡፡ የስርዓት ለውጥ
መደረጉን ተከትሎም በፖለቲከኞች በተቀነባበረ ሴራ ከአቡነ ጳውሎስ ጋር ቦታ የተለዋወጡት አቡነ መርቆርዮስም፣ እዛው አሜሪካን ሀገር
‹ተተኪ›ያቸው የጀመሩትን ብሔር ተኮርና ከሲኖዶሱ የተገነጠለ ቤተ-ክርስቲያን አስፋፍተው ዛሬ ለደረሰበት ‹የጎንደሬ ማሪያም›፣ ‹የትግሬ
ገብርኤል›… ለተሰኘ አሳፋሪ ክፍፍል ዳርገውታል፡፡ በርግጥ ለአቡኑ ከሀገር መባረር የኢህአዴግ እጅ እንዳለበት እንድናምን የሚያስገድደን
በቅርቡ ታምራት ላይኔ ‹‹በእኔ ፊርማ ነው ያባረርናቸው›› ማለቱን ዊክሊክስ ካደረሰን መረጃ በተጨማሪ፣ በትጥቅ ትግሉ ዘመን ህወሓት
በተቆጣጠራቸው በትግራይና ወሎ ነፃ መሬቶች በሚገኙ ከተሞች ያሉ ነዋሪዎችን ቀስቅሶና አደራጅቶ ፓትርያርኩ ላይ ‹‹ሽጉጥ ታጣቂ
ጳጳስ››፣ ‹‹ቀይ ደብተር ያለው /ለኢሠፓ አባላት የሚሰጥ ነው/ የሸንጎ ተወካይ››… የመሳሰሉትን መፈክሮች እያሰሙ በተቃውሞ ሰልፍ
እንዲያወግዟቸው ማስተባበሩን ስናስታውስ ነው)

 ዛሬስ የሃይማኖት ነፃነት የት ድረስ ነው?
ከላይ ታሪክን ወደ ኋላ መለስ ብዬ በደምሳሳው ለመጠቃቀስ እንደሞከርኩት፣ ኢህአዴግ በሃይማኖት ጉዳይ እጁን ጣልቃ ማስገባት
የጀመረው ክንዱ ሳይፈረጥም፣ ገና በርሃ ሳለ ነበር፡፡ በዚህ ሁኔታ የተጀመረው ጣልቃ-ገብነት ዛሬም ድረስ ተባብሶ ቀጥሏል፤ ምንም እንኳን
በሃይማኖት ጉዳዮች ጣልቃ እንደማይገባ በደፈናው ከህገ-መንግሥቱ አንቀፅ 11ን በመጥቀስ በተደጋጋሚ ለማስተባበል ቢሞክርም፣
ያለፉት ዓመታት ተጨባጭ ተግባሮቹ የሚመሰክሩት ግልባጩን ነው፡፡ ድርጅቱ ራሱም ቢሆን ጥያቄው በተነሳ ቁጥር ከህገ-መንግሥቱ
አንቀፅ 11ን የሚጠቅሰው ለማጭበርበሪያነት እንጂ ህጉ ገቢር አለመሆኑን ሳይረዳ ቀርቶ አይደለም፡፡ ተፈራ ዋልዋም በ1998 ዓ.ም
ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ህዳር/ታኀሣሥ ወር ከታተመችው ‹ሐመር› መፅሄት ጋር ባደረገው ቃለ-መጠይቅ ጉዳዩን አስመልክቶ የሰጠው አስተያየት የኢህአዴግን
አጭበርባሪነት ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ ነው፡-

‹‹ኢህአዴግ እኮ የሚመራው መንግስት፣ በደርግም ጊዜ፣ በኃይለ ሥላሴም ጊዜ እንደ ሚታወቀው ‹የቤተ-ክርስቲያን ሥራ አስኪያጅ
ሹምልን› ተብሎ ተጠይቆ ‹የለም ራስዋ ቤተ-ክርስቲያኒቱ ትሾማለች እንጂ እንደ ቀድሞው መንግስት አይሾምላችሁም› የሚል መልስ የሰጠ
መንግሥት ነው፡፡››

 በህዝበ ሙስሊሙ ተመርጦ ለእስር የተዳረገው የኮሚቴ አባላትም በአንድ ወቅት ለሚመለከተው የመንግስት ባለስልጣን የፃፈው ደብዳቤ
ጣልቃ ገብነቱን በግልፅ ያሳያል፡-

‹‹መንግስት እንደ መንግስት ህዝቡ ተበድያለሁ፣ ምርጫ ይካሄድ፣ የመጅሊሱን አመራር አላመንኩበትም፣ አልመረጥኩትም፣ ውክልና
የለውም እና ህገ ወጥ ነው ያለውን አካል ህገ ወጥነቱ እንዲረዝም ምርጫውን እሱው እንዲያካሄድ መወሰን ህዝብን ግራ አጋቢ ነው››

ስርዓቱ በሃይማኖት ጉዳዮች ላይ ጣልቃ እንደማይገባ ለማሳመን ይህን ያህል ቢዳክርም፣ በቅርቡ ‹‹የፀረ-አክራሪነት ትግል፣ የወቅቱ ሁኔታና
ቀጣይ አቅጣጫዎች›› በሚል ርዕስ የተዘጋጀው ባለ 44 ገፅ ሰነድ፣ መንግስት በዘወርዋራ በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ መግባቱን ሙሉ
በሙሉ የሚያምን ሆኖ አግኝቸዋለሁ፡-

‹‹የመንግስት መዋቅራትን ሴኩላር መንግስት መሆናችንን አውቆ የመንግስትን መዋቅር ተጠቅሞ የራሱን ሃይማኖት መሰረት ያደረገ
አገልግሎት ከመስጠት ሙሉ በሙሉ ያልፀዳ መሆኑን የተለያዩ ጥቂት የማይባሉ ገሐድ የወጡ መገለጫዎች አሉ፡፡ እንዲያውም የትኛውም
አክራሪ ኃይል ከመዋቅር (ከመንግስት) አካል ‹በርታ› ሳይባልና ‹ሽፋን› ሳይሰጠው የሚንቀሳቀስ እንደሌለ በገሐድ አማኞቹ ይገልጻሉ፡፡››

መቼም ይህንን ያነበበ ዜጋ መረጃው የተገኘው በመንግስት ከተዘጋጀ ሰነድ ሳይሆን በ‹ኒዮ ሌብራሊስት›ነት ከተፈረጁት እነ‹ሂዩማን ራይት
ወች› እና ‹አምኒስቲ ኢንተርናሽናል› ቢመስለው አይደንቅም፤ ሀቁ ግን ይኸው ነው፡፡ አገዛዙ ላለፉት ሃያ ሁለት ዓመታት ‹መንግስትና
ሃይማኖት› እንዲለያዩ ማድረጉን ሲደሰኩር ከመቆየቱም በላይ በኃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ መግባቱን የዘገቡ ጋዜጠኞችን ከስሶ ዛሬም ድረስ
ፍርድ ቤት እያመላለሳቸው እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ከዚህ አንፃር ይመስለኛል አለም አቀፍ ማህበረሰብን ጨምሮ በርካታ ኢትዮጵያውያን
በእስር ላይ የሚገኙት የእነ አቡበከር መሀመድ ክስ፣ የሼህ ሁሴን ኑር ግድያ፣ በማህበረ ቅዱሳን ላይ እየተሰነዘሩ ያሉ ውንጀላዎችና መሰል
ፍረጃዎችን አምኖ ለመቀበል የተቸገሩት፡፡

 ያም ሆነ ይህ ሃይማኖትን ብቻ ሳይሆን እድርና ዕቁብንም ሳይቀር ‹ካልተቆጣጠርኩ ሞቼ እገኛለሁ› በሚል የቁጥጥር ልክፍት የተያዘው
ኢህአዴግ፣ በተለይም ‹‹99.6 ድምፅ አግኝቼ አሸንፌያለሁ›› ብሎ ካወጀበት ከምርጫ 2002 ማግስት ጀምሮ ‹‹አናት ላይ ከተቀመጡ
መሪዎቻቸው በቀር ሙሉ በሙሉ አልተቆጣጠርናቸውም›› የሚላቸውን የእስልምናና የኦርቶዶክስ ክርስትና እምነትን ዋነኛ አጀንዳው
አድርጎ እየሰራ ለመሆኑ በርካታ መረጃዎች አሉ፡፡ በ2003 ዓ.ም. ህዳር ወር ‹‹የአምስት አመት የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድና
የኢትዮጵያ ህዳሴ›› በሚል ርዕስ በአቶ መለስ ዜናዊ ተሰናድቶ የተሰራጨው ጥራዝ፣ የስርዓቱን ቀጣይ አካሄድና ይህንን ሁናቴ የሚያሳይ
ከመሆኑም በተጨማሪ፣ ዛሬም ድረስ በሃይማኖት ጉዳዮች ላይ መንግስት የሚያዘጋጃቸው ስልጠናዎችም ሆኑ ጥናታዊ ፅሁፎች መነሻ
ሃሳባቸው ይኸው ዳጐስ ያለ ጥራዝ እንደሆነ ይነገራል፡፡

 ጥራዙ የእምነት ተቋማትን በተመለከተ ከገጽ 128-132 ያካተተው ሃሳብ፣ ለኪራይ ሰብሳቢነት ዋነኛ ምክንያት ‹‹የሃይማኖት
አክራሪነት›› መሆኑን ከጠቃቀሰ በኋላ፣ ችግሩን ‹‹ተኪ የሆነ ልማታዊ አስተሳሰብ›› በማምጣት ማስወገድ እንደሚቻል ይመክራል፡፡
ይህንን ከግብ ለማድረስ ደግሞ ሚዲያዎችንና ተያያዥነት ያላቸውን ማህበራት መጠቀሙ አዋጭ እንደሆነ ይተነትናል፡፡ የኢህአዴግ አባላት
በየእምነት ተቋሞቻቸው ያሉ ማህበራትን በአይነ ቁራኛ መከታተል እንዳለባቸውም ያሳስባል፡- ‹‹(አባላት) ከእምነት ተቋማት ውጭ
ባላቸው አደረጃጀት አማካይነት በሰፊው መስራት አለብን››፡፡ በርግጥም የእስልምና እምነት ተከታዮች ‹‹የሃይማኖት ነፃነት ይከበር››
የሚል ተቃውሟቸውን ባጠናከሩበት ሰሞን፣ አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ ክልሎች የሚገኙ ሙስሊም አባላቱን ለብቻ እየሰበሰበ
እንቅስቃሴውን የማክሸፍ ስራ መስራት ግዴታቸው መሆኑን የሰበከው ከዚሁ መለስ ዜናዊ አዘጋጅቶት ከነበረው ጥራዝ ነው ብሎ
መከራከር ይቻላል፡፡

ከጣልቃ ገብነት ወደ ጠቅላይ ተቆጣጣሪነት

 በዘወርዋራም ቢሆን በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ መገባቱን ሙሉ በሙሉ የሚያምነው ከላይ የተጠቀሰው ሰነድ በሀገሪቱ ‹‹የሃይማኖት
አክራሪነት›› መከሰቱን ካተተ በኋላ፣ ዋነኛ ተጠያቂዎች አድርጎ ያቀረበው እንደወትሮው ሁሉ ለተደጋጋሚ መሸማቀቅ የተዳረጉትን
መንፈሳዊ መሪዎችንና ማህበራትን ሳይሆን መንግስትን ነው፡-
‹‹የመንግስት መዋቅራችን አካል ሆነው አክራሪነቱን በድብቅም/በገሐድም የሚደግፍ አካል በፌዴራልም በክልልም ከሞላ ጎደል የሚታወቁ
ናቸው፡፡ እነዚሁ አካላት በተቻላቸው ሁሉ በመድረክ ጤናማ እየመሰሉ የሚኖሩ ናቸው፡፡ የፀረ-አክራሪነቱን ትግል ማጧጧፍ
የሚፈልገውን የመዋቅር አካልም ይሁን የህዝብ አካል በተደራጀና በመረባቸው አማካኝነት ከፍተኛ ጫና የሚያሳድሩ፤ የተቋማቸውን ምቹ
ሁኔታ ተጠቅመው በፀረ-አክራሪነት የሚንቀሳቀሱትን አካል የሚቀጡ፣ አሉባልታ እየፈጠሩ የሚያሸማቅቁ፣ ሆን ብለው ድጋፍ የሚነፍጉና
በሐሰት ምስክርም ጭምር ዜጐችን የሚያሳስሩ ናቸው፡፡ የመንግስትን አቅሞች ተጠቅመው አክራሪነትን የሚያስፋፉና ከአክራሪነት
እንቅስቃሴ ጋር በተለያዩ ጥቅሞች የተሳሰሩ ናቸው፡፡››

እነሆም በእንዲህ አይነቱ የውንብድና ተግባር የተሰማሩ ባለስልጣናት የተሰባሰቡበት፣ ውንብድናው መኖሩንም የሚያምን መንግስት
አንድም ተጠያቂዎቹን ለህግ አሳልፎ አለመስጠቱ፣ አሊያም ሥልጣኑን በፍቃዱ አለመልቀቁ በሀገር ላይ ሊያስከትል የሚችለውን አደጋ
ለመረዳት ነብይነትን አይጠይቅም፡፡ በአናቱም ስርዓቱ ለህግ የበላይነት ተገዥ አለመሆኑን የሚያሳየው በዚህ ደረጃ ‹‹ችግሩን
ተረድቸዋለሁ›› እያለም እንኳ፣ ዛሬም የቅጣት በትሩን ያሳረፈው ከመዋቅሩ ጋር አንዳችም ንክኪ በሌላቸው መንፈሳዊ መሪዎች ላይ መሆኑ
ነው፡፡ በርግጥ ይህ አይነቱ አሰራር ከአምባገነን አስተዳደር መገለጫዎች አንዱ ነው፡፡ ኢህአዴግም ያለፉትን አራት ምርጫዎች ጨምሮ
በተለያየ ጊዜ የዴሞክራሲም ሆነ የሰብዓዊ መብትን በአደባባይ መጣስ፣ የሀሰት ክሶችንና ፍረጃዎችን እንደ ምክንያት መጠቀም ነባር ስልቱ
እንደሆነ ይታወቃል፡፡ በማህበረ ቅዱሳን ላይ እየዘረዘረ ያለው የፈጠራ ውንጀላ እና ለሙስሊሙ ጥያቄ ‹‹መፍትሄ አፈላላጊ›› ተብለው
በተመረጡት የኮሚቴ አባላት ላይ የወሰደው እመቃ መግፍኤ ይኸው ነው፡፡

ሌላው ቀርቶ ከዚህ ቀደም በተቃዋሚ ፓርቲ አባላት ላይ ለሚፈፅመው የግፍ ግድያዎች ይሰጥ የነበረውን ምክንያት በመንፈሳዊ ሰዎችም
ላይ ያለአንዳች የይዘት ለውጥ ለመጠቀም አላመነታም፡፡ እንደሚታወሰው በድህረ-ምርጫ 97 በአምቦና በኢተያ በታጣቂዎች የተገደሉትን
የኦህኮ አባላት ከተፈጥሮ ህመም ጋር አያይዞት ነበር፡፡ በያዝነው ዓመት ጥቅምት ወር መጀመሪያ በተካሄደው የሲኖዶሱ ጉባኤ ላይ ደግሞ
የምዕራብ ወለጋና አሶሳ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ሄኖክ ‹‹ቤጊ›› ወረዳ በመንግስት ባለስልጣናት ተፈፀመ ያሉትን ግድያ ለፌደራል
ጉዳዮች ሚኒስትር ተወካይ፡-

‹‹በቤተ-ክርስቲያን 70 ሜትር ርቀት ላይ የሌላ እምነት ተከታዮች የራሳቸውን ቤተ-ክርስቲያን እንዲሰሩ መፈቀዱን ከተቃወሙት መካከል
አንድ ዲያቆን ተደብድቦ በሶስተኛው ቀን ህይወቱ ሲያልፍ ‘በወባ በሽታ ነው የሞተው’ ተብሎ ለፍርድ ቤቱ የሐሰት ማስረጃ ከዶክተሩ
እንዲቀርብ ታዘዘ፡፡›› ማለታቸውን መጥቀሱ ለጉዳዩ አስረጂነት በቂ ይመስለኛል፡፡

የሆነው ሆኖ አገዛዙ በዘረጋው ግዙፍ መዋቅሩ ውስጥ ያልታቀፉ ማህበራትንም ሆነ የሃይማኖት ተቋማትን የስጋት ምንጭ አድርጎ ማየቱ፣
በእምነት ነፃነት ላይ ጣልቃ ለመግባትም ሆነ ምንም አይነት ገለልተኛ ተቋማት እንዳይኖሩ እንቅልፍ አጥቶ መስራቱን ያሳያል ብዬ
አስባለሁ፤ በሚቆጣጠራቸው የኤሌክትሮኒክስና የህትመት ሚዲያዎች ቀን-ከሌት የፕሮፓጋንዳ ከበሮ የሚመታበት የ‹አክራሪ›ነት ፍረጃም
መነሾው ይህ ይመስለኛል፡፡ ሰነዱን ከዚህ ቀደም ካየናቸው ለየት የሚያደርገው፣ በመንግስት መዋቅር ውስጥ አሉ ከሚላቸው ወንበዴዎች
በተጨማሪ የሚከስሳቸውን ማህበራት በደፈናው ‹‹በክርስትና እምነት ውስጥ ያሉ›› ብሎ አለማለፉ ነው፤ ቃል በቃል እንዲህ ይላልና፡-
‹‹በማሕበረ ቅዱሳን ውስጥ የመሸጉ የትምክህት ኃይሎች፣ ጽንፈኛ የፖለቲካ ኃይሎች አካል በመሆን በጋዜጣና በመጽሔት ህዝባችንን
ለአመፅና ሁከት ለማነሳሳት ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል፡፡ …በራሳችንም ኃይል እንደሌላው ሰልፍ ልንወጣ ይገባል በሚል የአመፅና የሁከት
ቅስቀሳ ለማድረግ ይፈልጋሉ፡፡››

ይህ ሁኔታ መንግስት መንፈሳዊ ማህበራትን ጠቅልሎ ለመቆጣጠር በመፈለጉ ለተቃዋሚዎች ያሰመረውን ‹ቀይ መስመር› መጣሱን
ያሳያል፡፡ አስገራሚው ጉዳይ ደግሞ የሃይማኖት ተቋማትን የፖለቲካ መሳሪያ አድርጎ መጠቀሙ አልበቃ ብሎት፣ ወደ ማህበራቱ መዞሩ
ነው፤ በገሀድ እንደሚታወቀው የክርስትናም ሆነ የእስልምና መንፈሳዊ መሪዎች በተለያየ ጊዜ ከስርዓቱ ጎን ተሰልፈው ‹ናዳን ለመግታት›
ያደረጉት አበርክቶ በቀላሉ የሚገመት አለመሆኑ ነው፡፡ በርግጥም ‹‹የቄሳርን ለቄሳር›› በሚል አስተምህሮ የሚያድሩ፣ ደሞዛቸው በምድር
ያልሆነ መንፈሳዊ አባቶች በድህረ ምርጫ 97 ህፃናትን ሳይቀር በጥይት የፈጀውን ስርዓት ማውገዝ ቀርቶ መምከር ያለመፈለጋቸው
ምክንያት ፍርሃት ብቻ ሳይሆን፣ የግል ጥቅምን ታሳቢ ያደረገው ግንኙነታቸው ያሳደረው ተፅዕኖ ይመስለኛል፡፡ ከቅዱሳን መጽሐፍት
ይልቅ፣ አብዮታዊ ዴሞክራሲን ‹አዳኝ› አድርገው የመቀበላቸው መግፍኤ ይኸው ነው፡፡ ኢህአዴግም ‹ነገረ መለኮት›ን ለሲኖዶሱና
ለመጅሊሱ አስከማስተማር ድረስ የደፈረው፣ የእነርሱ ‹ለሁለት ጌታ› መገዛት ነው፤ ለፈጣሪና ለገንዘብ፡፡

 የሲኖዶሱ እና የመንግስት ፍጥጫ
 በኦርቶዶክስ ክርስትና እምነት ዶግማ ‹‹ሲኖዶስ›› ከፍተኛውን ስልጣን የሚይዝ ሲሆን፣ ፓትርያርክንም የመሾምና የመሻር ስልጣን
አለው፡፡ ሆኖም ይህ የላዕላይ መዋቅር እስከ አቡነ ጳውሎስ ህልፈት ድረስ ለእርሳቸውም ሆነ ለስርዓቱ ሰጥ-ለጥ ብሎ የሚገዛ ‹ጥርስ
የሌለው አንበሳ› በመሆኑ ለትችት ከመዳረጉም በላይ በአማኞች ዘንድ ለመንፈሳዊ አባቶች የሚሰጠውን ክብርም ነስቶት ቆይቷል፡፡
 ይሁንና በያዝነው ዓመት ጥቅምት ወር መጀመሪያ በተካሄደው ‹‹የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ 32ኛው አመታዊ
ስብሰባ›› ላይ ከመንግስት የተወከሉ ኃላፊዎች ‹‹የብዝኃነት አያያዝ፣ አክራሪነት/ጽንፈኝነት ዝንባሌዎቹና መፍትሔዎቹ›› በሚል ርዕስ
ያቀረቡትን ጥናት ተከትሎ ከስድስት በላይ ጳጳሳት ቀድሞ ባልታየ መልኩ ጠንካራ ተቃውሞ ማቅረባቸው፣ በብዙዎች ዘንድ የሀይማኖት
መሪዎች ለመንፈስ ልዕልናቸው ሊገዙ ይሆን? ከምድራዊውን ይልቅ ሰማያዊውን ሊመርጡ ይሆን? ‹እመን እንጂ አትፍራ› የሚለውን
አስተምሮአቸውን ሊተገብሩ ይሆን? የሚል ጥያቄ አጭሯል፡፡ በዕለቱ የመጀመሪያው ተናጋሪ የነበሩት የሰሜን ወሎና ዋግ ኹምራ አህጉረ
ስብከት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ቄርሎስ በጥናቱ ላይ መቻቻል መጥፋቱን አስመልክቶ የቀረበውን ድምዳሜ እንዲህ ሲሉ ነበር ያጣጣሉት፡-
‹‹ይኼ አክራሪነት ጽንፈኝነት የሚለውን ቋንቋ እናንተው ናችሁ ያሰማችሁን፤ ከዚህ በፊትም አይታወቅም፤ በደርግም ይሁን በሌላ፡፡
እንደገና ደግሞ ብዙ ጊዜ ጽንፈኝነት፣ አክራሪነት እያላችሁ እድሜ ሰጥታችሁ ያበለጸጋችኋቸው እናንተው ናችሁ፡፡››

በርግጥም አቡኑ የተቹት ስርዓቱ የፕሮፓጋንዳው ፋሽን ያደረገውን ‹‹መቻቻል››ን ብቻ አይደለም፤ ‹‹በመቃብሬ ላይ ነው የሚሻሻለው››
የሚለውን የመሬት ፖሊሲንም ነው፡፡ በተጨማሪም ጥናት አቅራቢዎች በነገስታቶቹ ዘመን ቤተ-ክርስቲያኗ በርካታ መሬት መያዟንና ‹ሁሉ
በእጇ ሁሉ በደጇ› እንደነበር አድርገው ማቅረባቸውንም አልተቀበሉትም፡፡

‹‹በፊት መሬትም ህዝብም የነገስታቱ ነበር፤ አሁንስ የማን ነው? ይልቁንም ከአንድ ቤት ‹ግድግዳው የቤቱ ባለቤት ነው፣ ሳሎኑ የመንግስት
ነው› የሚለው አዋጅ የአሁኑ አይደለም እንዴ? ለኢትዮጵያዊነቱ ዋስትና የለውም፤ ይኼ የእኔ ነው የሚለው ከሌለ ምንድን ነው? ይህች
የእኔ የኢትዮጵያዊነቴ መገለጫ ናት ካላለ፣ ምንድን ነው ኢትዮጵያዊነት? አሁንም መሬቱም ህዝቡም የእናንተው ሁኖ ሳለ ለፊቱ፣ ለነገስታቱ
መስጠታችሁ በምን ተመልክተውት ነው?››

የደቡብ ጎንደር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ አቡነ እንድርያስም በሚያስተዳድሩት አካባቢ ያለውን የመንግስት ጣልቃ ገብነትና ተፅዕኖን
ከዘረዘሩ በኋላ፣ ለተሰነዘረው ፍረጃና ማሸማቀቂያ እንዲህ የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡-
‹‹የተበደለ ሰው ሲናገር ‹ፖለቲካ ተናገረ› እየተባለ የውሸት ውሸት ሲያተራምሱን የሚኖሩ ብዙዎች ናቸው፡፡… እንዴ! የመንግስት ስልጣን
የተረከቡ ወንድሞች የእኛን አፍ፣ የእኛን አንደበት ብቻ ነው እንዴ የሚጠብቁት፣ ለሌሎቹ ሞራል ይሰጣሉ ማለት ነው? …ለምንድን ነው
ግን በሽፋን የምትጠቀሙብን? መንግስት እኛን ሽፋን አድርጎ ነው ሲበዘብዘን የምንኖረው፡፡ ሌባውም ቀጣፊውም ሰርጎ ገቡም
ሲያጭበረብረን ሲያታኩሰን መንግስትን ሽፋን አድርጎ ነው፡፡››

የወላይታ ሀገረ ስብከት ስራ አስኪያጅም በተመሳሳይ መልኩ መንግስት በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ መግባቱን ቤተ-ክርስቲያኗ ስትቃወም
ጉዳዩን ወደ ፖለቲካ እየቀየሩ ማስፈራራቱ እንደተለመደ እና ለቀብር ማስፈፀሚያ የሚሆን መሬት ከመስተዳደሩ በሚጠየቅበት ጊዜ
የሚሰጠው መልስ በሀሰት መወንጀል እንደሆነ ከገለፁ በኋላ፣ ጉዳዩ መፍትሄ ካላገኘ ሊከተል የሚችለውን ስጋታቸውን ተናግረዋል፡-
 ‹‹‘የፖለቲካ ጉዳይ ነው፤ ህዝብን በሃይማኖት ሽፋን ታንቀሳቅሳላችሁ’ እየተባልን እየተሸማቀቅን ያለንበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ ይህን
እንዴት ታዩታላችሁ? መቻቻልስ የሚመጣው ከምን አኳያ ነው? ዝም ብለን የምንቀመጥ ከሆነ ምናልባት ኃላፊነት ለመውሰድ
ስለሚከብደን ይህን ወርዳችሁ እንድትፈትሹ ለማለት ነው፡፡››

(በነገራችን ላይ የሲኖዶሱ ጉባኤ በተጠናቀቀ ማግስት ከማህበረ ቅዱሳን የአመራር አባላት መካከል ሶስት ሰዎች በፌደራል ጉዳዮች ቢሮ
ተጠርተው ዶ/ር ሽፈራውን ጨምሮ ከሚመለከታቸው ኃላፊዎች ጋር ውይይት ማድረጋቸውን ከመስሪያ ቤቱ ምንጮቼ ሰምቻለሁ፡፡
ሚኒስትሩ ከአመራሩ ጋር ለመወያየት የተገደደው ካልተጠበቀው የሲኖዶሱ አባላት ድፍረት ጀርባ ‹የማህበረ ቅዱሳን እጅ አለበት› የሚል
ጥርጣሬ በመያዙ ነው፡፡ በውይይቱም ላይ የተንፀባረቀው የባለስልጣናቱ መለሳለስ፣ ማህበሩን ‹አክራሪ› ብለው እንደማያምኑ እና ከዚህ
ቀደም የተሰራጩት ወንጃይ ሰነዶችን ሳይቀር ‹አናውቃቸውም› እስከማለት የደረሰ እንደነበር አረጋግጫለሁ፡፡ ይሁንና ይህ አይነቱ ‹እሳት
ማጥፊያ› ስልት፣ ከስርዓቱ ጋር የቆየ መሆኑ ይታወቃል፤ የማህበሩ አመራርም ይህ ይጠፋዋል ብዬ ባላስብም፣ ኢህአዴግ መስከረም
22/1998 ዓም ቅንጅትን እንዴት አቂሎ ለታሪካዊ ስህተት መዳረጉን አለመርሳቱ ይጠቅመዋል)

 የሆነ ሆኖ በዕለቱ ከፌደራል ጉዳዮች ተወከለው ከመጡት ሶስት ሰዎች መካከል አቶ ገዛኸኝ ጥላሁን አብዛኛውን ጥያቄ በተመለከተ
የሰጠው ምላሽ፣ የወከለው መንግስት ዛሬም በተሳሳተ የታሪክ ንባብ እያሸማቀቀ፣ እያስፈራራ፣ ህግን እየጠመዘዘ፣ እስር ቤት እየከተተ…
የፖለቲካ ጥቅሙን ማስከበር ላይ ያተኮረ መሆኑን ያሳያል፤ ኃላፊው ማስጠንቀቂያውን ያስተላለፈው እንዲህ በማለት ነው፡-
‹‹መጀመሪያ ግንዛቤ ላይ እንስራ በሚል እርምጃ አልወሰድንም፡፡ ኮሽ ባለቁጥር ወደቃሊቲ መፍትሄ አይሆንም፡፡››

 …‹ቃሊቲ›ን ምን አመጣው? መቼም ለጣልቃ ገብነቱ ከዚህ የበለጠ ማሳያ መፈለግ ‹አውቆ የተኛን…› እንደመሆን ነው፡፡ ‹መንግስትና
ሃይማኖት የተለያዩ ናቸው› ብሎ መከራከሩም ጊዜ ያለፈበት ፕሮፓጋንዳ ይመስለኛል፡፡ እናም የተሻለው መንገድ ከላይ በጠቀስኩት ሰነድ
‹‹በየማዕከላዊ ኮሚቴው በሚካሄደው የስምሪት ተግባር በፀረ-አክራሪነት ትግል ላይ ያለው የእያንዳንዱ ግለሰብ ቁመና መፈተሽ አለበት›› ተብሎ የተገለፀውን ማሳሰቢያ በፍጥነት በመተግበር፣ በቅድሚያ ራስን ከአክራሪነትና አሸባሪነት ማራቅ ነው፡፡ ማረጋገጫ የማይቀርብበትን
አፈ-ታሪክንም እየለቃቀሙ በአንድ ሃይማኖት ላይ መለጠፉ አስተማሪ አይመስለኝም፡፡

 ከዚህ ባለፈ ‹የሃይማኖት ኮማንድ ፖስት አቋቁመን ለችግሩ እልባት እንሰጣለን› የምትሉት ጉዳይ ቀጥታ መንግስት በሃይማኖት ጉዳይ
እጁን ማስገባቱን በአደባባይ ከማመን ያለፈ የፖለቲካ ጠቀሜታ አይኖረውም፡፡ ጳጳሳቶቹም ሆኑ ሼኼዎች ኃላፊነትና ግዴታቸው
ሰማያዊውን መንግስት መስበክ እንጂ፣ ከሰላይ አለቆችና ከፖሊስ አዛዦች ጋር ቢሮ ዘግተው የመንፈስ ልጆቻቸውን ‹ትምክተኛ›፣
‹አሸባሪ›፣ ‹አክራሪ›… እያሉ እንዲፈርጁ መፈታተኑ ያልታሰበ ህዝባዊ ቁጣ መቀስቀሱ አይቀርም፡፡






ኢትዮሚድያ - Ethiomedia.com
November 10, 2013

Saturday, November 9, 2013

ሰማያዊ ፓርቲ የስደተኛ ዜጐች እንግልት እንዲቆም ጠየቀ

 ሰማያዊ ፓርቲ አረብ አገር በሚገኙ ስደተኛ ኢትዮጵያውያን ላይ እየደረሰ ያለው እንግልትና ስቃይ በአስቸኳይ እንዲቆም ጠየቀ፡፡ ፓርቲው ትላንትና ረፋድ ላይ በጽ/ቤቱ “በመንግስት ቸልተኝነት በስደት ላይ ባሉ ዜጐች እየደረሰ ያለው ግፍና መከራ ይቁም” በሚል መርህ በሰጠው መግለጫ እንዳብራራው፤ ዜጐች በኢህአዴግ ዘመን በሚደርሱባቸው ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ጫናዎች በህጋዊና ህጋዊ ባልሆኑ መንገዶች ከሀገራቸው መሰደዳቸውንና ለእንግልት፣ ለሞትና ለስቃይ መዳረጋቸውን ጠቁሟል፡፡
“ፓርቲያችን የዜጐች ስደትና እንግልት ያሳስበዋል፤ መንግስት አስቸኳይ መፍትሔ እንዲሰጥም ድምፃችንን እናሰማለን” ብለዋል፤ የፓርቲው አመራሮች፡፡ የፓርቲው ሊቀመንበር ኢ/ር ይልቃል ጌትነት፣ የፓርቲው የወጣቶች ጉዳይ ሃላፊ ወጣት ዮናታን ተስፋዬ እና የፓርቲው የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ ወጣት ብርሃኑ ተክለ ያሬድ በጋራ በሰጡት መግለጫ፤ ዜጐች የሚሰደዱት በአገሪቱ ላይ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ፍትህ ባለመኖሩ ነው ያሉ ሲሆን በነዚህ ጫናዎች ምክንያት ዜጐች በየበረሃው በኮንቴይነር ታሽገው እየሞቱ፣ በባዕዳን ኩላሊታቸው እየተሸጠ፣ በባህር ላይ ሲያቋርጡ በባህር አውሬዎች እየተበሉ መሆኑን አብራርተዋል።
በተለይም ሰሞኑን በሳኡዲ አረቢያ የሚገኙ ዜጐች እየደረሰባቸው ያለውን አስከፊ እንግልትና ስቃይ አጥብቀው እንደሚያወግዙ ተናግረዋል፡፡ “ዜጐች በባዕድ አገር በሚደርስባቸው በደል የኢህአዴግ መንግስት ከዜጐች ጐን በመቆም ስቃያቸውና በደላቸው እንዲቆም በመጠየቅ አጋር መሆን ሲገባው፣ በአገር ውስጥ ባሉ ሚዲያዎች “ሀገሪቱ በልማት እያደገች ባለችበትና ስራአጥነት እየተቀረፈ ባለበት ወቅት ዜጐች ሀገር ለቀው መሰደዳቸው ስህተት ነው” በሚል በዜጐች ላይ ማላገጡን ያቁም ሲል ፓርቲው አሳስቧል፡፡ “በተለይ በሳውዲ አረቢያ በዜጐች ላይ እየደረሰ ስላለው እንግልት፣ የአለም ትልልቅ ሚዲያዎች አጀንዳ አድርገው እየተነጋገሩበት፣ የኢትዮጵያ መንግስት ቸልታ “ይህቺ አገር መንግስት የላትም ወይ’ ያስብላል” ያሉት ኢ/ር ይልቃል የኢትዮጵያ ሚዲያስ ይህን አጉልቶ ካላወጣና ከዜጐቹ ጐን ካልቆመ ፋይዳው ምንድን ነው ሲሉ ጠይቀዋል፡፡
የስዊድን ጋዜጠኞች በህገ ወጥ መንገድ አገር አቋርጠው ወደ ኢትዮጵያ ሲገቡ እና ሲታሰሩ የአገራቸው መንግስት ጥፋተኛ ናቸው ብሎ ችላ ሳይል ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ተደራድሮ በአጭር ጊዜ እንዲፈቱ ማድረጉንና አገራቸውም ሲገቡ የጀግና አቀባበል እንደተደረገላቸው የገለፁት ሊቀመንበሩ የኢትዮጵያ መንግስት ዜጐቹ በግልጽ እየተሰደዱ እየተንገላቱና እየሞቱ እጁን አጣጥፎ መቀመጡ የሚያስተቻቸው እንደሆነ አብራርተዋል፡፡ የፓርቲው የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ ወጣት ብርሃኑ በበኩሉ፤ በእድሜና በእውቀት ያልበሰሉ ህፃናት በህጋዊና ህጋዊ ባልሆነ መንገድ ከአገር እየወጡ ለስቃይ ሲዳረጉ፣ በኤጀንሲዎች እና በህገወጥ ደላሎች ላይ ጥብቅ እርምጃ መውሰድና ዜጐቹን በተለያየ መንገድ ማስገንዘብ ሲገባው፣ ጭራሽ በየክልላቸው ፓስፖርት እንዲያገኙ እያደረገ ማበረታታቱ እንደሚያሳዝነው ተናግሯል፡፡ “ኤጀንሲዎችን ማገድና ፓስፖርትና ቪዛ መከልከል አሁንም ትክክለኛ መፍትሔ አይደለም” ያለው ብርሃኑ፤ መንግስት ፖሊሲዎቹን ማሻሻልና ማስተካከል እንዳለበት አሳስቧል፡፡
የፓርቲው የወጣቶች ጉዳይ ሃላፊ ወጣት ዮናታን በበኩሉ፤ “ኢህአዴግ ለወጣቶች ስራ የሚሰጠውና የሚያደራጀው አባል እስከሆነ ድረስ ብቻ ነው” ካለ በኋላ፤ “አብረን ከዩኒቨርሲቲ የወጣን ሆነን አባል ስለሆኑ ብቻ ትልልቅ ስራና ሃላፊነት ላይ የተቀመጡ ወጣቶች አሉ፡፡ እነሱ በመኪና እኛ በእግር እንተላለፋለን” ሲል አማሯል፡፡ “ኢትዮጵያ ውስጥ ልማትና እድገት ካለ ዜጐች ለቅንጦት አይሰደዱም” ያሉት የፓርቲው አመራሮች፤ በመንግስት ቸልተኝነት በኢትዮጵያ የስራ አጥ ቁጥር 40 በመቶ መድረሱን ገልፀዋል - አለም አቀፍ መረጃ መሆኑን በመጥቀስ፡፡ የኢትዮጵያ የውጭ አገር ብድር ከ12 ቢሊዮን ዶላር በላይ መሆኑን፣ የአገር ውስጥ የብድር መጠን 80 ቢሊዮን ብር መሆኑን፣ ባለፉት 10 ዓመታት ከኢትዮጵያ 11.7 ቢሊዮን ዶላር በህገወጥ መንገድ መውጣቱን እና መሰል መረጃዎችን የገለፁት አመራሮች፤ እነዚህ መረጃዎች የአለም ባንክና የአይኤምኤፍ መሆናቸውን ገልፀው፤ “ይህ ባለበት ስራ አጥነት ተቀርፏል፤ ልማት አለ የሚባለው በህዝብ ላይ ማሾፍ ነው” ብለዋል፡፡
ፓርቲው ባወጣው ባለአምስት ነጥብ የአቋም መግለጫ፤ የዜጐችን ህይወት ለመታደግ መንግስት በአስቸኳይ ከሳኡዲ መንግስት ጋር እንዲነጋገር፣ የሳኡዲ አረቢያ መንግስት በዜጐች ላይ እያደረሰ ያለው በደል የሰብአዊ መብት ጥሰት በመሆኑ በአስቸኳይ እንዲያቆም፣ ዜጐችን ለስደትና ለስቃይ የሚዳርጉ የችግሩ መንስኤዎች፣ ድርጅቶችና ግለሰቦች ለፍርድ እንዲቀርቡ እና ዜጐች የሚሰደዱበትን ምክንያት በጥልቅ በመመርመር አስከፊውን ስደት ለማቆም መንግስት የፖሊሲ ማሻሻያ እንዲያደርግ… የሚሉት ይገኙበታል፡፡ ፓርቲው በቀጣይነት ጥናቶችንና መረጃዎችን በማሰባሰብ ዘላቂ መፍትሔ ለማምጣት ጥረት እያደረገ መሆኑን ገልፆ፤ ለዚህ ስኬት ህብረተሰቡ፣ የሲቪክ ተቋማት፣ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችና አለም አቀፉ ማህበረሰብ ከጐኑ እንዲቆሙ ጥሪ አስተላልፏል፡፡
ምንጭ እዲስ እድማስ

Thursday, November 7, 2013

ሀገራዊ ውርደት እንዲያበቃ ወያኔን ከሥልጣን ማስወገድ!!!

November 7,2013 posted by admin
የወያኔ ገዢ ጉጅሌ በባህርዩ ኢትዮጵያ ከዚህ በፊት አጋጥሟት የማያውቅ ፍጹም ኢሰብዓዊና ነውረኛ ስብስብ እንደሆነ ለመረዳት ኢትዮጵያዊያንን ለማዋረድ የሚጠቀሟቸውን ተግባራትና ቃላትን ማጤን ይበቃል።
በሶማሌ ክልል የኦብነግን ታጣቂዎች ቅስም ለመስበር ልጃገረዶችንና እናቶችን ብቻ ሳይሆን ወንዶችንም ጭምር በቤተሰብ ፊት በደቦ የሚደፍሩ፤ ለዚህ ተግባር የሠለጠኑ የልዩ ጦር አባላት መኖራቸው በስፋት የሚታወቅና በተደጋጋሚም የተዘገበ ጉዳይ ነው። ወያኔ፣ የኦጋዴን ወገኖቻችን በዚህ ጥቃት ተሸማቀው ያነገቡትን መሣሪያ ጥለው ፀጥ-ለጥ ብለው ይገዛሉ ብሎ ተስፋ ያደረገ ቢሆንም እየሆነ ያለው ግን የዚህ ተቃራኒ ነው። ዛሬ የሶማሌ ክልል ወንዱም ሴቱም፤ ወጣቱም አዛውንቱም በፀረ-ወያኔ አቋም የጋራ መግባባት ላይ ደርሷል። በኦጋዴን የወያኔ አስነዋሪ ጥቃት የፈጠረው ምሬት በውጭ አገራትም በሚደረጉ የፀረ ወያኔ ትግሎች የኢትዮጵያ ሶማሌ ተወላጆች ተሳትፎ እንዲጎለብት አድርጎታል። በሶማሌ ወገኖቻችን ላይ የደረሰው ጥቃት በሁላችንም ላይ የደረሰ ነውና ቁጭታቸውን እንጋራለን። በሶማሌ ወገኖቻችን ላይ የደረሰው ጥቃት ሀገራዊ ውርደት ነው።
በአፋር ክልልም ተመሳሳይ ጥቃት የዘወትር ትዕይንት እየሆነ መጥቷል። የአፋር የወል የግጦሽ መሬቶች ለሸኮራ አገዳ ልማት በሚል ሰበብ ሲነጠቁ የተቃወሙ የአገር ሽማግሌዎች ተደብድበዋል፤ ሚስቶቻቸውና ልጆቻቸው ተደፍረዋል። በአፋርም ውስጥ ለጾታዊ ጥቃት የሰለጠነ የወያኔ ልዩ ጦር ተሰማርቶ በሴቶች ብቻ ሳይሆን በወንዶችም ላይ አስነዋሪ ጥቃት አድርሷል። በአፋር ወገኖቻችን ላይ የደረሰው ጥቃት በሁላችንም ላይ የደረሰ ነውና ቁጭታቸውን እንጋራለን። በአፋር ወገኖቻችን ላይ የደረሰው ጥቃት ሀገራዊ ውርደት ነው።
በጋምቤላ ውስጥ ወያኔ ወገኖቻችን ከፈጀ በኋላ በሕይወት የተረፉትም ቅስማቸውን ለመስበር ጾታዊ ጥቃት በመሣሪያነት ተጠቅሟል፤ አሁንም እየተጠቀመ ነው። በጋምቤላ ወገኖቻችን ላይ የደረሰው ጥቃት በሁላችንም ላይ የደረሰ ነውና ቁጭታቸውን እንጋራለን። በጋምቤላ ወገኖቻችን ላይ የደረሰው ጥቃት ሀገራዊ ውርደት ነው።
የወያኔ ዝቅጠት ዘግናኝ ነው። ወያኔ ከላይ የተጠቀሰው ዓይነት ጾታዊ ጥቃት ያላደረሰበት የአገራችን ክፍል የለም። ኦሮሚያ፣ አማራ፣ ደቡብ፣ ቤንሻንጉል … በሁሉም ቦታዎች ያልተነገሩ ጥቃቶች በዜጎታችን ላይ ደርሷል፤ እየደረሰም ነው።
በአንድ ወቅት በመሀል አገር፤ በሰሜን ሸዋ አንዲት ኢትዮጵያዊት እናት በእብሪተኛ ወያኔ የተገደለውን ባለቤትዋን ብልት ይዛ አስክሬኑን እንድትጎትት መደረጉን ከዓይን እማኞች አንደበት ሰምተናል። በመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ሰበብ መስዋዕትነት እየተቀበሉ ያሉ ወገኖቻችን “ሽንታም አማራ” እየተባሉ ብልቶቻቸው ይቀጠቀጥ እንደነበር የሰማነው እና የምናውቀው ጉዳይ ነው። በወያኔ መዳፍ ውስጥ ውስጥ ገብተው በእስር ቤቶች በሚገኙ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ላይ ዘግናኝ ተግባራት እንደሚፈፀሙ መረጃዎች አሉ። በአዲስ አበባ በየቦታው ባሉት ስውር የማሰቃያ ቤቶችም ተመሳሳይ ተግባራት ዘወትር እንደሚፈፀሙ ይታወቃል።
ወያኔ ለጾታዊ ጥቃት ያሰለጠናቸው ሰዎችን በከተሞችም ውስጥ አሰማርቷል። በእነዚህ ጥቃቶች ግለሰቦች ግንባር ቀደም ተጠቂዎች ቢሆንም የተደፈርነው፣ የተዋረድነው ሁላችንም መሆናችን አጽንዖት ሊሰጠው ይገባል። የተደፈርነው እኛ ኢትዮጵያዊያን በሙሉ ነን። የተዋረደችው የምንወዳት አገራችን ኢትዮጵያ ነች።
ኢትዮጵያ አገራችን እፍረት ባልፈጠረባቸው ነውረኛ የወያኔ ዋልጌዎች እንድትገዛ እንድትረገጥ በመፍቀዳችን ጥፋቱ የኛም ጭምር ነው። ይህን ነውረኛ ቡድን በሥልጣን ላይ እንዲቆይ በፈቀድንለት መጠን በኢትዮጵያዊያን እና በኢትዮጵያችን ላይ የሚደርሰው በደል እየባሰ እንደሚመጣ በዓይኖቻችን እያየን በጆሮዎቻችን እየሰማን ነው።
ሰሞኑን በአንድነት ፓርቲ የምክር ቤት አባል ላይ የደረሰው ጥቃት የዚሁ አካል ነው። እኚህ ወገናችን የደረሰባቸውን ዘርዝሮ ለመናገር የሚከብድ መሆኑ ገልፀዋል። ማፈር የነበረባቸው ጥቃት አድራሾቹ መሆን ይገባቸው ነበር፤ ሆኖም ግን ይሉኝታ አልፈጠረባቸው። ምንም ይሁን ምን በወገናችን ላይ የደረሰው ጥቃት በእሳቸው ላይ ብቻ የደረሰ ሳይሆን በሁላችንም ላይ የደረሰ መስሎ የሚሰማን መሆኑን ልንነግራቸው እንወዳለን። የተዋረደችው ኢትዮጵያ አገራችን ነች።
ይህ ውርደት እንዲያበቃ ወያኔ ከሥልጣን መወገድ ይኖርበታል።
ግንቦት 7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ “ወያኔን ከሥልጣን ማስወገድ” ቀዳሚ ሥራችን ነው የሚለው ኢትዮጵያን ለማዳን ከዚህ የሚበልጥ አንገብጋቢና አጣዳፊ ሥራ ስለሌለ ነው። ወያኔን ለማስወገድ እንተባበር።
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!!

የማለዳ ወግ: ሳውዲ አረቢያ እና ዘንድሮ … እንዲህም ይኖራል!








ከነብዩ ሲራክ (ጋዜጠኛ)
መስዋዕትነት መክፈል ካለብኝ ዝግጁ ነኝ ! ስለእኔ አትዘኑ !
እለተ ሰኞ – ጥቅምት ሊሸኝ ህዳር ሊገባ የቀሩት ጥቂት ቀናት ብቻ ናቸው። በሳውዲ አረቢያ በህጋዊ መንገድ ገብተው ከአሰሪዎቻቸው ጋር ባለመግባባትና ፈርጀ ብዙ በሆነ ምክንያት መኖሪያ ፍቃድ የተበላሸባቸው ማደስ እንዲችሉ፣ ከአሰሪዎቻቸው ጠፍተው ያለ ህጋዊ ሰነድ በግል ሲሰሩ ለነበ ፣ ከአምስት አመታት በፊት በህጋዊ መንገድ በሃጅ በኡምራ ገብተው ወደ ሃገራቸው ሳይመለሱ በህገ ወጥ መንገድ ያለ መኖሪያ ፈቃድ በሳውዲ የሚኖሩትን ወደ ሁለት ሚሊዮን የሚቆጠሩ የተለያዩ ሃገር ዜጎች ህጋዊ ሰንዳቸውን እንዲያስተካክሉ የሚፈቅደው አዋጅ ተጠናቋል። የጭንቁ ቀን ቀርቧል!
የሳውዲ መንግስት ለሁለተኛ ጊዜ የሰጠው የምህረት ሲጠናቀቅ ህገ ወጥ ተብለው የተፈረጁ በሳውዲ የሚኖሩ የተለያዩ ሃገር ዜጎች ከተያዙ የሁለት አመት እስራት እና የሳውዲ ሪያል 100. 000 ( አንድ መቶ ሽ የሳውዲ ሪያል በግምት ግማሽ ሚሊዮን የኢትዮጵያ ብር) ቅጣት እንደሚጣል አስታውቋል ! …የምህረት አዋጁ ማለቁን ተከትሎ ከፍተኛ ፍተሻ እንደሚደረግ መንግስት ጠንከር ጠንከር ያሉ መግለጫዎችን ሰጥቷል። የውጭ ዜጎች በብዛት የሚገኙባቸውን የሳውዲ ከተሞች እስከ ደንበር የገጠር መንደሮች በልዩ ልዩ ሞተር ሳይክሎች መኪኖች እና ሂሊኮፕተር ሳይቀር በመጠቀም ፍተሻውን እንደሚያጠናክር አስታውቋል ። መንግስት በዚሁ አሰሳና አፈሳ ስራ ተሳታፊ የሚሆኑ የመንግስት ሚኒስትር መስሪያቤት በዋናነት ከሰራተኛ ሚኒስትር ። በፖሊስ እና ከደህንነት በተውጣጡ ኮሚቴዎች ስልጠና ሰጥቶ ፍተሻውን እንደሚያከሂድ ያስታወቀበት ቀን ደርሷል ። በማስጠንቀቂያው ህገወጥ የተባሉትን ብቻ ሳይሆን ህገ ወጥ የተባሉተን ማስጠጋት በራሱ ከከፍተኛ ገንዘብ ቅጣት ከሃገር እሰከ መባረር የሚያደርስ እርምጃ ይወሰድበታል የሚል ተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ መሰጠቱ በእርግጥም ከሰባት ሚሊዮን በላይ ለሚሆነው የውጭ ዜጋ አስፈሪና አሳሳቢ ጉዳይ ነው!
በተፈራው ቀን ሰኞ ጅዳ ከወትሮው በተለየ ጸጥና ረጭ ብላለች ፣ ግህ እንደቀደደ በማለዳው ልጆቸን ይዠ ወደ ጅዳ የኢትዮጵያን አለም አቀፍ ትምህርት ቤት ተጓዝኩ። በትምህርት ቤቱ ስደርስ የምህረት አዋጁን ማብቃት ተከትሎ መምህራን እና ሰራተኞች ባለመምጣታቸው ተረዳሁ። ትንሽ ቆየት እንዳለኩ በስጋት ላይ የነበረው የ3000 ታዳጊዎች የትምህርት ማዕከል መማር ማስተማር ሂደት በትምህርት ቤቱ አስተዳደር፣ በኮሚኒቲና በመንግስት ተወካዮች የቅርብ ክትትልና ግልጽነት ያለው አካሔድ አለመከተል መኮላሸቱ አበሳጭቶ ቀኔን አጨልሞ ጀመረው! ከሃገረ ጀርምን ትናነት ምሽት ያረፉትን የምሰራበት ኩባንያ የስራ ባልደረቦቸን ፊቴ በርቶ እንዳልቀበላቸው ምክንያት የሆነኝን ትምህርት ቤት ልጆቸን ወደ ቤት ከመለስኩ በኋላ በትካዜ ወደ ቢሮየ አመራሁ…!
(ነብዩ ሲራክ)
እለተ ማክሰኞ – ከአመት እስከ አመት ሞቅና ደመቅ ያለ እንቅስቃሴ በሚታይባቸው የጅዳ ፣ የመካ ፣ የመዲናና ዋና ከተማዋ ሪያድ ወትሮ የነበረው እንቅስቃሴ በከፍተኛ ሁኔታ የቀነሰ ሲሆን የተወረሩ ከተማ መስለው መታየታቸው ተጠቅሷል። በመንግስት ጠንካራ ፍተሻ ግራ የተጋቡ ዜጎች በአፈሳና ፍተሻው ፍርሃቻ ከቤት ባለመውጣት ጊዜውን በማሳለፍ ላይ ሲሆኑ በውጭ ዜጎች ይንቀሳቀሱ የነበሩ ሱቆች እና አንዳንድ ግልጋሎት መስጫዎች በመዘጋታቸውም ከተሞቹ ጸጥና እረጭ እንዲሉ በማድረግ በንግድ ልውውጡ ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ ማሳደራቸውን መገናኛ ብዙሃን ሳይቀር በመዘገብ ላይ ናቸው ። የምህረት አዋጁን በመጠቀም እንድም መኖሪያ ፈቃድ አለያም የመውጫ ሰነድ ማግኘት ያልቻሉ ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ የተለያዩ ሃገር ዜጎች ለጉዳያቸው መጓተት ሰበቦች የሳውዲ መንግስትን መስሪያ ቤቶች የተቆላለፈ ቢሮክራሲያዊ አሰራር እና የየሃገራቸው ቆንስልና ኢንባሲ ጽህፈት ቤቶችንም ሰነዶችን በጊዜ አለማቅረብ እንደሆነ ገልጸውልኛል ። ይህም ለአሁኑ አፈሳውና መዋከቡ አደጋ እንደጣላቸው ተጨናንቀውና ተስፋ ቆርጠው በምሬት ሲናገሩ መስማት በራሱ ያማል …
የሳውዲ መንግስት ለወራት የሰጠውን የምህረት አዋጅ መጠቀም ካልቻሉት መካከል ቀዳሚ የሆንነው ኢትዮጵያውያን እንደ ቀረው ዜጋ ለፍተሻ ውክበቱና እስሩ ተጋላጭ ሆነናል ። በባህር አድርገው በህገ ወጥ መንገድ በየመን በኩል ወደ ሳውዲ የገቡትን ጨምሮ በአብዛኛው በግል የመኖሪያ ፈቃድ ገዝተው በአሰሪዎቻቸው ውጭ በተለያዩ ድርጅቶችና ኩባንያዎች ተቀጥረው የሚሰሩ ፣ በአሰሪዎቻቸው እጅ አዙር ክፍያ በመክፈል በግል ሱቅ የከፈቱ ፣ በግል መኪና ገዝተው ኮንትራት ተማሪና ሰራተኞችን የሚያመላልሱና ፣ በአሰሪዎቻቸው ስም ጥቃቅን ንግድ ስራን ከፈተው በመስራት ይተዳደሩ የነበሩ በአስር ሽዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን የምህረት አዋጁ ካለቀበት ቀን ጀምሮ ከሞላ ጎደል ስራቸውን አቁመው የሚሆነውን በስጋት ቋፍ ላይ ሆነው በመከታተል ላይ ናቸው።
ፍተሻው ተጠናክሮ ከመቀጠሉ አስቀድሞ አብዛኛው ህጋዊ እና ህገወጥ ተብሎ የተፈረጀው ነዋሪ ስጋት ከፍተሻው ጋር ሊፈጠር የሚችለው ማዋከብና ቤት ለቤት ፍተሻ ይደረጋል የሚለው የነበረ ቢሆንም በምህረት አዋጁ ማለቂያ ዋዜማ መንግስት በሰጠው መግለጫ ፍተሻው በኮሚቴ የተሚመራ በመሆኑ ማዋከብ የሌለበት እንደሚሆን በማሳወቅ “የቤት ለቤት ፍተሻ የለም!” የሚል መግለጫ በመሰጠቱ አፎይታን ፈጥሮ ነበር ። ይሁን እንጅ እለተ ሰኞ ምሽትና ማክሰኞ እስኪነጋጋ መንግስት የሰጠው መመሪያ ተጥሶ በሪያድ ነዋሪ በሆኑ ኢትዮጵያውያን ጥቃት ተሰንዝሮባቸው ሰምቻለሁ፣ አረጋግጨማለሁ! በተለይም በሪያድ ውስጥ ጩቤ እየታጠቁ እስከ መጋደል ባደረሰ እርምጃቸው የሃበሻውን ስም ያረከሱት “ባህር ሃይል ” በሚል ቅጽል ስም የሚጠሩት ህገ ወጥ ዜጎቻችን መናህሪያ የሆኑ የከተማው ክፍሎች ቀደም ሲል በተደረገ ጥናት የመንግስ ኢላማ ሆነው ነበር ። በየመን በኩል በባህር የሚመጡት ኘእኒሁ ኢትዮጵያውያን የሚኖሩበት መንፉሃ ደግሞ የመጀመሪያው የመንግስት የብረት ዱላ አረፈባት! “ለሃጣን የመጣ ለጻድቃን !” እንዲሉ ሁለት ኢትዮጵያንን ህይዎት እስከ መቅጠፍ እና በበርካታዎችን ላይ የአካል ጉዳት እስከ ማድረስ የደረሰ የቤት ለቤት ፍተሻ ተካሔዶ በሰላማዊና በህጋዊ የአካባቢው ነዋሪ ኢትዮጵያውያን ላይ ቤተሰቦች ላይ ግፍ ተፈጸመ… መረጃው በደረሰኝ ቅጽበት ወደ ሪያድ ስልክ በመደወል ያነጋገርኳቸው ኢትዮጵያውያን እያነቡ የገለጹልኝን በትክክል ላመስቀመጥ ይከብደኛል … ብቻ የእኛ ዜጋ ተለይቶ ሲታደን ውሎ አደረ ….


ከጅዳ ከተማ አራት እና አምስት መቶ ኪሎ ሜትር ርቀት በመስክ ስራ ላይ ተሰማርቸ በምገኝበት የሰማዩ የከረረ ጸሃይና ከፊት ለፊቴ የተገጠገጠው በአሸዋ የተዋጠ በርሃ ወበቅ ሳያንገኛታኝ በሚጢጢዋ ከከምፒተሬ የፊስ ቡክ የውስጥ ገጽ እና በተንቀሳቃሽ ስልኬ የሚደርሱኝ በምስል የረደገፉ ሲያንገላቱኝ ዋሉ! እንዳልናገር ሊናገሩት የሚከብድ ፣ ዝም እንዳልለው ዝም የማይባል የወገን ጩኸት ነውና ይህን መረጃ አልሰሜ የሚሰማበትን መንገድ ሳፈላልግ ትናንት ረፋዱ ላይ ጋዜጠኛ ሽዋየ ለገሰ የላከችልኝን ማስታወሻ አስታወስኩና አትኩሮት ሰጥቸ አነበብኩት ” ነቢዩ ስለ ሳውዲ የምህረት አዋጅ ማለቅ መስራት የምትችል ከሆነ ዜና ሰርተህ ላክልን ፣ የማችል ከሆነ ግን ከዚህ እንድንሰራው የአንዳንድ ነዋረሀዎችን የስልክ አድራሻ ላክልን …” ይላል! ለሽዋየ ዜናውን እንደምሰራው ገልጨላት በቀጥታ ወደ ስራው ገባሁ! መረጃየን አሰባስቤ የምህረት አዋጁን ተከትሎ በሪያድ ኢትዮጵያውያነደ ላይ እና በጅዳ ትምህርት ቤት መዘጋትና በአደጋ ላይ መሆነደ ዙሪያ ዜናውን ለእለተ ረቡዕ ምሽት አደረስኩት …
የምሽቱ ዜና ሲተላለፍ እኔ ጅዳ እየገባሁ ነበር ፣ ዜናወ ተላልፎ እንዳለቀ እቤት ብደርስም ከድካም እረፍት የማይሰጡ መልእክቶች ይደርሱኝ ይዘዋል ….በሪያድ የሞቱት ሰዎች ቁጥር ወደ አምስት ማደጉን ፣ በርካታ የመኖሪያ ፈቃድ ያላቸው ኢትዮጵያውያን መንገላታታቸውን ፣ “በመንፉሃ በኢትዮጵያውያን ላይ የተፈጸመው ግድያ ጩቤ ይዘው ለማጥቃት በመሞከራቸው ነው!” ፣ “ሰርገኛ መጣ በርበሬ ቀንጥሱ !” እንደ ሚባለው በጅዳ ትምህርት ቤት ዙሪያ ለመምከር የጅዳ ቆንስል፣ የኮሚኒቲ እና የወላጅ ኮሚቴ ከፍተኛ ሃላፊዎች ስብሰባ መቀመጣቸውና ሌላም ሌላም መረጃዎች ደርሰውኝ አስተናገድኩ ….
አንድ ብርቱ ወዳጀ ስልክ ደውሎ እየሆነ ስላለው መረጃ ጠይቆኝ በሪያድ እየሆነ ያለውን ከፍቶኝ ከገለጽኩለት በኋላ የሰጠኝ ምክርና የእኔን ምላሽ የዛሬ ማለዳ ወጌ ማሳረጊያ ማድረጉን ፈቅጃለሁ.
..
በጥሞና መረጃውን ሰጥቸው እንዳበቃሁ ወዳጀ መናገር ጀመረ ” ነቢዩ ራስክን ጠብቅ! ለልጆችህ ኑርላቸው !” ሲል የወንድም የወዳጅና የአብሮ አደግነቱን ምክር መከረኝ …በአክብሮት ሰማሁት! አመሰገንኩትም! ግንስ ጥቂት ወረበሎች በፈጠሩት ሁከት ብዙሃን ሰላማዊ ነዋሪ ኑሮው ሲናጋ እየሰማሁና እያየሁ ፣ ወገን ልናገረው በሚከብደኝ አሰቃቂ ሁኔታ ግፍ የተፈጸመባቸው ጭብጥ መረጃዎች ይደርሱኛል! ከነ አሰቃቂው በብለት የተተለተለ የወገን ሬሳን ምስል እና በጥይት የተበሳሳና የተቆራረጠ ሰቅጣጭ መረጃ እየደረሰኝ እንዴት ራሴን መጠበቅ ይቻለኛል? አዎ ለልጆቸ እና እንድኖርላቸው ለሚፈልጉ ወገኖቸ ለመኖር ስል የወገንን የመከራ ጸአር ፣ የታፈነ የድረሱልኝ ጩኸት እየሰማሁ እና እያየሁ ዝም ማለቱ ለእኔ ከባድ ነው! እንዴትስ አድርጌ እንደኔ የሚፈልጋቸው ወላጅ ያላቸው ወገኖቸ እያነቡ እንባቸውን ባልጥርግ ለልጆቸ እና ለጠገብኩት የተንደላቀቀ ኑሮ ስል ዝምታን ልምረጥ ? እንዴትስ የህሊና እዳ ተሸክሜ ለልጆቸና ለሚፈልጉኝ ልኑር? እንዴትስ ይቻላል? አዎ ! ፈጣሪ ሁሉንም ያያል …የማይሳነው አምላክ አጥፍተን ከሚያዘንብብን ሰቆቃ ይታደገን ዘንድ በርትታችሁ ጸልዩ! ለእኔንም የፈራችሁ የሰጋችሁ ፣ አንድየ የታይታውን ሳይሆን የልቤን አይቶ እሱ ጽናት ብርታቱን ይስጠኝ ዘንድ ግን በርትታችሁ ጸልዩልኝ !
ይቅርታ የምክራችሁ ምንጩ ፍቅርና አክብሮት እንደሆነ ጠልቆ ቢገባኝም ቅሉ “ለልጆችህ ለወገኖችህ ኑር ! ” ብላችሁ ግን አትምከሩኝ ! መስዋዕቱን እኔው ልቀበለው ስለቆረጥኩ እውነቱን በመናገሬ ለሚደርስብኝ ስቃይ መከራ የተዘጋጀሁ ነኝና ስለእኔ አትፍሩ ፣ አትዘኑ ! ልጆቸን ለማሳደግ እና የእለት እንጀራየን ለማግኘት ደፋ ቀና ከማለቱ ጎን ለጎን ባለችኝ ውሱን ጊዜ ህሊናየ ፈቅዶት ማድረግ ያለብኝን እያደረግኩ እስከ ወዲያኛው እዘልቃለሁ! በግል ጨካኝ አውሬ ፣ ሰላቢ ምቀኛ ፣ ሆዳም አድርባይ ፣ ዋሾ አስመሳይ ቀጣፊ ልሆን ብቸልም በአረብ ሃገር ኑሮ ከከተምኩ ጀምሮ በአደባባይ የምሰጣችሁ መረጃ ከተጨበጠ አሁን አሁን በግላጭ እየታየ ከመጣው ሰቆቃ ሰብዕና የማይጎዳውን እየመረጥኩ ከሞላው እየጨለፍኩ ያቃመስኳችሁ መሆኑን ታምኑኝ ዘንድ ልማጸናችሁ ግድ ይለኛል! አዎ ወገን ሲገፋ ፣ ሲበደል መረጃ በማቀበሌ መስዋዕትነት መክፈል ካለብኝ አስፈላጊውን ሁሉ መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ ነኝ ! ይህ ቂል ሆኝ አለያም ራሴን ለመኮፈስ ወጥኘ የኝረጨው ከንቱ ፉከራ እንዳይመስላችሁ! እናም ቃሌን ልድገመው እየሆነ ስላለው ነግ በየግል ቤታችን ስለሚገባው መከራ እሰቡ እዘኑ እንጅ ስለእኔ አትዘኑ … ! ደግሞም መፍትሔ ሃሳብ ከመረጃየ ባታገኙ አይድነቃችሁ … መፍትሔ ይፈልጉ ዘንድ ህዝብና ሃገር ለመጠበቅ ቃል ገብተው ሃገር የሚያስተዳድሩትን በርትታችሁ ጎትጉቱ! መፍትሔው የወገንን መብት የሚከበርበትን መላ ይፈልጉ ዘንድ እስኩሰሟችሁ ጩሁባቸው! እኔ እስክጠፋ መረጃ ከማቀበል የሚያሸሽ ህሊና አጥቻለሁ ! እናም ስለእኔ በፍጹም አትዘኑ ! ቢቻል ማለት ካለባችሁ እንደ መለኩሴዋ እናቴ ” ለእውነት ግንባርክን ስጥ ፣ ዋጋህን ከባለእግዚአብሔር ታገኘዋለህ! ” ብላችሁ ጽናትን ተመኙልኝ ፣ ፍርሃትን ፈርቸው በተገላገልኩት መባቻ ፍርሃትን አታስተምሩኝ ! እውነትን አፍኘ ለልጆቸና ለሚወዱኝ የመኖር አባዜው ትርጉሙ እየኖሩ አለመኖር ነውና ግንባሬን ሊደርስ ከሚችልብኝ የጨካኞች ኢላማ የማሸሸት ሞራሉ የለኝም! ጠባቂየ እውነትን ስበኩ የሚለው አንድ አምላክ እንጅ እኔ አይደለሁም! ልጆቸም የሚጠበቁት በአንድ ፈጣሪ እንጅ በእኔ አይደለም ! እሱ ሁላችንን ይጠብቀን ! በቃ የእኔ ምላሽ ይህ ነው ! ቸር ያሰማን!
ክባሪያችሁ
ነቢዩ ሲራክ

Tuesday, November 5, 2013

አንዷለም አራጌ አርዓያክብር (ICON) ነው!!

ዳንኤል ተፈራ
ወጣቱ የነፃነት ሰላማዊ ታጋይ ፖለቲከኛ አንዷለም አራጌ ዋለ የፃፈው ‹‹ያልተሄደበት መንገድ›› ገበያ ላይ ዋለ፡፡ አንዷለም አርአያ ክብር ነው፡፡ ምሳሌና አርአያ ብናደርገው የምንጠቀምበት ምርጥ ኢትዮጵያዊ ነው፡፡ በቅርበት ስለማውቀው ብቻ እራሴን እንደ ዕድለኛ እቆጥራለሁ፡፡ ማርቲን ሉተር ኪነግንና ማህተመ ጋንዲን አንስቶ አይጠግብም፡፡ ስለፍቅር ሲል ሁሉን አሳልፎ መስጠት የሚችል፤ ስለ ኢትዮጵያ የሚሰስተው የሌለው ውድ ወጣት ነው፡፡ ለአላማው በፅናት መቆምን ተክኖበታል፡፡ እነሆ አሁን ደግሞ ጨለማው ሳይበግረው ያልተሄደበት መንገድን ሊያሳየን በመፅሐፍ መጣ፡፡ የማይበገር ራዕይ ያላቸው ሰዎች እንደዚህ ናቸው፡፡ እድለኛ ካልሆኑ በስተቀር እንደዚህ መሆን ከባድ ነው፡፡

ለቅምሻ ያህልም ከመግቢያው እነሆ ብያለሁ፡-
‹‹….መታሰር ነገሮችን በጽሞና ለማየት እድል ይሰጣል፡፡ በስራ የተጠመደ ሰው ነገሮችን በአንክሮ ለማሰብ የሚፈልገውን ያህል ጊዜ አያገኝም፡፡ ድንገት የሚከሰቱ ነገሮች ማእበል ከአንዱ ጉዳ ወደ ሌላው ያላጋዋል፡፡ እኔ አሁን ከእንዲህ አይነት ሁኔታ ነፃ ነኝ፡፡ስለዚህ ፍፁም አስቸጋሪ በሚባል ሁነታም ቢሆን በግፍ ከተለየሁት የኢትጵያ ህዝብ ጋር በሃሳብ ለመገናኘት መሞከር እንደሚገባኝ ወደንኩ፡፡ ጥረቴ የሚገትመው ፈተና በጣም አስቸጋሪ እንደነበር ግልፅ ነበር፡፡ በመሆኑም የሃገራችን አንዳንድ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ነገሮችን አንስቼ ለመወያየት በማሰብ ‹‹ከዚህ ወዴት እንሄዳለን? ትላንት ዛሬና ነገ›› የሚል ርእስ መዘገብኩ እንደሃገር ካለፈው ይልቅ ስለሚመታው አብዝትን ልንጨነቅ እንደሚገባን ባምንም ያለፈውና አሁን ያለንበት ደግሞ ወደሚመጣው ዘመን የምንደርስበት ሜዳ በመሆኑ መዳሰስ ተገቢ እንደሆነ አምናለሁ፡፡ ያለሁባት ክፍል እጅግ ጠባብ ከመሆኗ የተነሳ ስድስት ሆነን እግርና ጭንቅላታችንን ገጥመን ከዳር እስከዳር ሞልተናታል፡፡ መኝታውም መቀመጫውም ፍራሽ ነው፡፡ እጅና እግር ሲጠጋጉ የጠረጴዛና ወንበር ሚና ይጫወታሉ፤ እጅም የመፃፍ ስራውን ይሰራል፡፡ ለመቀመጥ አስቸጋሪ ከመሆኑ የተነሳ ግን የጀርባ ህመም ማስከተሉ አልቀረም፡፡ በዚህ ሁኔታ ለመፃፍ ሌሊቱን መጠቀም ነበረብኝ፡፡ ለምን ቢሉ እኔ ምን እንደምሰራ እንዲከታተሉ የተመደቡ ወንደሞች በመኖራቸው እነርሱም በማዳከም እንቅልፍ ባለውለታዬ ነው፡፡ ከጎኔ ተኝተው እንቅልፋቸውን ሲያጣጥሙ እኔ ደግሞ በሃሳብ ፈረስ ጋልቤ የምወዳት ሃገሬን የእስር ቤት አጥር ሳይገድበኝ እዞራታለሁ፡፡ በሃሳብ ዶሴዎቿን ከመሳቢያ እያወጣሁ አገላብጣለሁ፤ የሚመስሉኝን ሃሳቦች እሰነዝራለሁ፤ እፅፋለሁ፡፡

በዚህ ሁኔታ ሆኜ ወረቀትና ብእርን ማገናኘት ቀላል ባይሆንም ከሁሉ የሚያስቸግረው ግን ዋቢ መፅሃፍትን ሰብስቦ እያጣቀሱ በጥሩ ሁኔታ የተጠና መፅሃፍ ማዘጋጀት ነበር፡፡ መፅሃፍትን ማስገባት በጣም ከባድ ነው፡፡ ማስገባት ቢቻል እንኳን መፅሃፍቱን በሚገባ አመሳክሮና ጊዜ ወስዶ አንድ መፅሃፍ ማበርከት በጣም ከባድ ነው፡፡ የጊዜ ጉዳይ ሞልቷል፡፡ ነገርግን የሚፃፉ ፅሁፎች በየጊዜው በሚደረግ ፍተሻ ይወሰዳሉ፡፡ የዶ/ር ኪንግን መፅሃፍ ትርጉምን አጥቻለሁ፡፡ ሌላ ተመሳሳይ ችግር ደግሞ ማስተናገድ ከባድ ነው፡፡ ስለዚህ ከጊዜ ጋር የሚደረገው ግብግብም ወሳኝ ነው፡፡ ስለዚህ በተለያዩ ምክንያቶች ዋቢ መፅሃፍትን ማመሳከር አለመቻሌን እንዳለመታደል እቆጥረዋለሁ፡፡ አንባቢም ይኸንን ውሱንነት እንዲረዳልኝ በአክብሮት እጠይቃለሁ፡፡ በእርግጥ ያም ሆኖ እጄ ላይ ያሉ ውሱን መፃህፍትን ማገላበጥ ችለሁ፡፡

በመሆኑም ለመፃፍ እቅድ ማውጣት በንፅፅር ሲታይ ቀለል ቢልም በተለይ አሁን ባለሁበት ሁኔታ ሃሳብን አደራጅቶ ለመከራከር ብሎም ለመፃፍ መሞከር በጣም ከባድ ነበር፡፡ ፈጣሪ ፀጋውን አብዝቶልኝ ግን ለመፃፍ ሞክሬያለሁ፡፡ ለእኔ ትልቁ ቁምነገር በዚህ አይነት ሁኔታም ሆኜ ለሃገሬ ይበጃል የምለውን ነገር ሃሳቤን የመግለፅ ተጠቅሜ መፃፍ መቻሌ ነው፡፡እንደመሸበብ ክፉ ነገር ይኖር ይሆን?
በእኛ ሃገር የፖለቲካ ባህል ውስጥ ላደገ ሰው በግፍ ከሚስቱ፣ ከልጆቹና በዙርያው ካሉ ወዳጅ ዘመዶቹ ተለይቶ በወህኒ ቤት ሆኖ የጭቆናን ገፈት የሚጎነጭ ሰው ስሜታዊ እንደሚሆንና የመጠቃት ስሜትም ሊታይበት እንደሚችል ይጠበቃል፡፡ ከደረሰብኝ ነገር ሁሉ አንዳች ያልጠበኩት ነገር ባይኖርም አንዳንድ ጊዜ ስሜቴ መጎዳቱ አልቀረም፡፡ ስሜቴ በምፅፍበት ወቅትም ሚዛናዊ እንዳልሆን ይልቅስ ስሜቴን ብቻ እንደወረደ እንዳስተናግድ በተደጋጋሚ ቢፈትነኝም በተቻለኝ መጠን ፈተናውን ለማለፍ ጥረት አድርጌያለሁ፡፡ በግል በደል ወይንም ጥቅም ላይ ተመርኩዞ ከመፃፍ ይልቅ ለሁላችን የሚጠቅመውን በተለይም ከዛሬ ይልቅ ለነገ ይበጀናል የምለውን ሃሳብ ለማመላከት ሞክሬያለሁ፡፡ የጊዜ ጉዳይ እንጂ ሞት ለሁላችንም ማይቀር እዳ ነው፡፡ ከሞት በኋላም ግን ዛሬ ያላነሳነው አጀንዳና ያነገብነው እውነት በልጆቻችን ፊት መቅረቡ አይቀርም፡፡ ዛሬ የያዝነው ሃሳብ የጊዜን ፈተና አልፎ በትውልድ ፊት ሞገስ ቢያገኝ ፍሬም ቢያፈራ ትልቅ መታደል ነው፡፡ ስለዚህ በተቻለኝ መጠን ሚዛናዊ ለመሆን አቅሜ የፈቀደውን ጥረት አድርጌያለሁ፡፡

ከዚህ በተጓዳኝ ሌላም የሃሳብ ውጣ ውረድ ለማስተናገድ ተገድጃለሁ፡፡ እንደሚታወቀው የሃገራችን ፖለቲካ በብዙ መልኩ ጠርዝ የያዘ ነው፡፡ ሚዛናዊ ለመሆን ስሞክር በኢህአዴግ በኩል‹‹ ክንዳችንን አቀመስነው፣ አስተነፈስነው›› የሚል ስሌት ውስጥ ሊገቡ እንደሚችሉ በመገመቴ ይኼን አይነት ስሜት በማይፈጥር መልኩ ለመፃፍ መታገል ነበረብኝ፡፡ ይኼን ሳደርግ ደግሞ እኔም ደግሞ በቃራኒው ከእምነቴ ውጪ የሆነ ነገር እንዳላራምድ መጠንቀቅ ከባድ ኃላፊነት ነበር፡፡ በሌላ ወገን አንባቢ የተሳሳተ ግምት እንዳያድርበትም እንዲሁ መጠንቀቅ ነበረብኝ፡፡ በተቀውሞው ጎራ ያለው ወገን ደግሞ ‹‹ተሸጠ፣ተለወጠ፣ ከኢህአዴግ ጋር ተሞዳሞደና እጅመንሻ የውዳሴ መፅሃፍ ፃፈ›› የሚል የተሳሳተ ሃሳብ ውስጥ እንዳይገባ ለመጠንቀቅ ሞክሬያለሁ፡፡በእነዚህ ሁለት ፅንፎች ውስጥ ለማለፍ ስሞክር ማስተላለፍ የፈለኩትን መሰረታዊ ሃሳብና ልከተል የፈለኩትን የሃሳብ መስመር ላለመልቀቅ ተፍጨርጭሬያለሁ፡፡ እንዲህ አይነት የሃሳብ ማእበል ሲኖር ምንም ያህል ቢደከምም የሚፈለገውን ያህል ሌላውን ቀርቶ እራስንም ለማስደሰት ይከብዳል፡፡ ኃላፊነት ከባድ ነው፡፡ ሁላችንም ከልዩነቶቻችን ይልቅ ወደአንድነታችንና በጎ ነገሮቻችንን እንደናይ የሚያስችል ፅሁፍ ለመፃፍ ሞክሬያለሁ፡፡ ስሜቴ አሸንፎኝ ልዩነቶቻችንን የሚያሰፋ ጎዳና ተከትዬ ከሆነ አንባቢ እኔ ያልሄድኩበትን መንገድ እንዲሄድበት እጋብዛለሁ፡፡ ምናልባት በለስ ቀንቶኝ አንድነታችንን የሚያጠናክርና እራሳችንን እንድናርም፤ ያለመቆጠብ ወደ ውስጣችን እንድናይ፣ ልዩነቶቻችንም በሰከነ መንገድ ለመፍታት እንድንችል ሃሳብ ሰንዝሬ ከሆነ በእንዲህ አይነት ሁኔታ ከተዘጋጀ መፅሃፍ ክፍተት አይጠፋምና አንባቢ ክፍተቶችን ለመሙላት ይሞክር፡፡ ውይይቱንም በማስፋት የተሸለና የተሞረደ ሃሳብ እንዲወለድ ሃገራችንም ከምትገኝበት አዘእቅት ውስጥ እንድትወጣ የበኩሉን አስተዋፅዎ ያድርግ ቢለዋ ከቢለዋ ሲፋጭ ስለት ይወጣዋልና፡፡››
 ምንጭ ዘ-ሐበሻ