Friday, September 5, 2014

አብርሃ ደስታን በተመለከተ፣ ከጠበቃ ተማም አባቡልጉ ጋር ያደረኩት ቃለ-ምልልስ

Saturday,september 6th,2014
በዛሬው ዕለት አብርሃ ደስታ ጊዮርጊስ በሚገኘው የአራዳ ፍርድ ቤት ቀርቦ የ28 ቀናት የጊዜ ቀጠሮ ተሰጥቶታል፡፡ አብርሃ ወደፍርድ ቤቱ ሁለት እጆቹ በካቴና እንደታሰሩና በአራት መሳሪያ በታጠቁ ፖሊሶች ታጅቦ ሲገባ በስፍራ የነበሩ ሰዎች ሞቅ ያለ ጭብጨባ አቅርበውለት ነበር፡፡ በፊቱ ላይ መረጋጋት እና ፈገግታ የሚነበብበት አብርሃ፣ በቻለው አቅም ሰዎችን ሰላምታ ለመስጠት ጥሯል፡፡ አብርሃ ወደችሎት ከገባ በኋላ፣ የታጠቁ ፖሊሶች ‹‹ለምን አጨበጨባችሁ? ረብሻ ፈልጋችሁ ነው፡፡›› በሚል በተለይ አንዱ ፖሊስ የያዘውን መሳሪያ አፈሙዝ ወደሰዎች በመወደር ‹‹ከግቢው ለቅቃችሁ ውጡ!›› ማለቱን ተከትሎ ሌሎች ፖሊሶችም ተመሳሳይ አቋም በመያዝ ታዳሚውን ለማስወጣት ጥረት አድርገው ነበር፡፡
በስፍራው የነበሩ የተለያዩ ሰዎች የፖሊሶችን አካሄድ በመቃወም ‹‹አንወጣም፣ ሕግ- አልጣስንም፡፡ አብርሃ ነጻ ሰው ነው ብለን ስለምናምን ለእሱ ያለንን አክብሮት እና አድናቆት ለመግለጽ እናጨበጭባለን›› በማለት ከፖሊሶች ጋር ክርክር ካደረጉ በኋላ በፖሊሶች በድጋሚ ‹‹ተፈትሻችሁ ግቡ›› በሚል አለመግባባቱ እልባት ለማግኘት ችሏል፡፡
አብርሃም፣ ከችሎት በፈገግታ ታጅቦ ሲወጣ ዝናብ እየዘነበ ነበር፡፡ ሆኖም በስፍራው ከነበሩ ታዳሚዎች ሞቅ ያለ ጭብጨባ እና ድጋፍ ተሰጥቶታል፡፡ እሱም በካቴና የታሰሩ እጆቹን ትንሽ ከፍ በማድረግ ‹‹አመሰግናለሁ›› ብሏል፡፡
እኔም የአብርሃ ደስታ ጠበቃ ለሆኑትን አቶ ተማም አባቡልጉን የተወሱን ጥያቄዎችን በማንሳት ተከታዩን ቃለ-ምልልስ አድርጌያለሁ፡፡
————————————————
ጥያቄ፡- የዛሬ የአብርሃ ደስታ የፍርድ ቤት ውሎ እንዴት ነበር?
ጠበቃ ተማም፡- የ28 ቀን የጊዜ ቀጠሮ ተሰጥቷል፡፡ ለመስከረም 22 ቀን 2007 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷል፡፡
ጥያቄ፡- ለምን ተሰጠ?
ጠበቃ ተማም፡- ፖሊስ ‹‹ተጨማሪ የምስክር ቃል እቀበላለሁ፤ ተጨማሪ የሰነድ ማስረጃ እሰባስባለሁ፤ ሰነድ አስተረጉማለሁ፡፡›› ብሏል፡፡ እነዚህ ነገሮች ባለፈውም ተብለዋል፤ በፊትም ተብለዋል፡፡ እኛ ግን ተቃውመናል፡፡
ጥያቄ፡- በምን ተቃወማችሁ?
ጠበቃ ተማም፡- በሁለት ነገር ተቃውመናል፡፡ ዛሬ የሚባሉ ነገሮች በሙሉ፣ ይሄ ልጅ ከመታሰሩ በፊት መጠናቀቅ ነበረባቸው፡፡ የጸረ-ሽብርተኝነት አዋጁ በአንቀጽ 19 ላይ ‹‹አንድ ሰው ሽብር ለመስራት በቂ ምክንያት / ጥርጣሬ ካለ ..›› ይላል፡፡ ‹ሽብርን ያቋቁማል› የተባለው ጉዳይ በተራ ወንጀልነት በወንጀለኛ መቅጫ ሕጉ ላይ አለ፡፡ ስለዚህ ይህ መሆን አለመሆኑን አጣርተው ነው አብርሃ ማሰር የነበረባቸው፡፡ ያን ለማድረግ ደግሞ የምስክር ቃለ ሰምተው፤ የሰነድ መስረጃ ሰብስበው ነው ምክንያታዊ ጥርጣሬ አደረባቸው የሚባለው፡፡ ይሄንን ምክንያት አድርገው፣ ለሁለት ለሶስት ጊዜ የጊዜ ቀጠሮ ማድረጋቸው በራሱ የአሰራር ሕገ-ወጥነትን ያሳያል፡፡ ሁለተኛ ደግሞ፣ የታሰረው ምንም ማስረጃ ሳይኖር ነው፡፡ ለዚህ ማሳያው፣ የተጠረጠሩትን ይዘው፣ መረጃዎች በብርበራ የተያዙ መሆኑ ነው፡፡ ይሄ ሕገ-ወጥ ነው፡፡
ጥያቄ፡- እርስዎ በዚህ ላይ ምን አሉ?
ጠበቃ ተማም፡- ይህ ሕገ-ወጥ አሰራር ነው ብዬ አመለከትኩኝ፡፡ ይሄ የሚያመለክተው፣ ምስክር የሚጠይቁት፣ ‹‹ከእነሱ ኤሌክትሮኒክስ መሳሪያ አገኘን›› የሚሏቸው ነገሮች ከእነሱ መጀመሪያ ምንም ነገር ሳያገኙ ነው ያሰሯቸው፡፡ ይሄ ራሱ ሕገ-ወጥ ነው፡፡ ‹‹የመራራ ዛፍ ፍሬ መርዛማ ነው›› ስለዚህ ‹‹ሕገ-ወጥ ሥነ-ሥርዓት በማድረግ የሚመጣ ፍሬ በራሱ ውጤቱ መርዛማ ነው›› አልኩኝ፡፡
ጥያቄ፡- ይሄንን እርስዎ ሲሉ ዳኞች ምን አሉ?
ጠበቃ ተማም፡- ዳኛው ማስጠንቀቂያ ነው የሰጡኝ፡፡ ይሄ የተለመደ የሕግ አባባል ነው፡፡ የሥነ- ሥርዓት ሕጎች መብት ማስጠበቂያ ናቸው፡፡ እነዚህን ጥሰህ የምታገኛቸው ነገሮች በሙሉ ሕገ-ወጥነታቸውን ለማስረዳት ነው የተጠቀምኩት፡፡ ለፍርድ ቤቱም አመልክቻለሁ፡፡ ለምን? አስተሳሰሩ ሕገ-ወጥ ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች በሽብር ተግባር ለመሰማራቸው በቂ ማስረጃ እና ጥርጣሬ ኖሮ አይደለም የታሰሩት፡፡ ያ ሁሉ የተደረገው ከታሰሩ በኋላ በቤታቸው በተደረገ ማስረጃ ነው፡፡ ይሄንን ‹‹ሕገ-ወጥነት ነው›› ስል አመለከትኩኝ፤ ለደንበኛዬም ‹‹ዋስትና ይፈቀድልኝ›› በማለት አመለከትኩኝ፡፡ ዳኛው ይሄንን ተውትና ወደእኔ ዞሩ፡፡ ማስጠንቀቂያም ሠጡኝ፡፡
ጥያቄ፡- ምን ብለው?
ጠበቃ ተማም፡- ‹‹ከዚህ በፊት በሌላ ችሎት ላይ ማስጠንቀቂያ ሰጥጬሃለሁ፤ በሄዱበት ይረብሻሉ›› አሉኝ፡፡ ያ ከዚህ ጋር ምን እንደሚያያይዘው አይታወቅም፡፡ አንደኛ፣ እኔ ማንንም ሰው ነክቼ አላውቅም፤ አልነካምም፡፡ ምክንያቱም፣ ከ14 ዓመታት በላይ በጥብቅና ሰርቻለሁ፡፡ እዚህ ፍርድ ቤት ካሉ ከብዙ ሰዎች በተሻለ ሥነ-ሥርዓት አውቃለሁ፡፡ ማንንም ሰው፣ ፖሊስንም ጨምሮ አልተናገርኩም፡፡ ከፍርድ ቤት ከወጣሁ በኋላ ፖሊሶች ይነዘንዙኝ ነበር፡፡ ‹‹እዚህ ባይሆን ኖሮ እንዲህ እናደርግህ ነበር›› እያሉ ያስፈራሩኝ ነበር፡፡ ቢቸግረኝ ‹‹ዳኞች እኛን ሊያጣሉን ነው›› አልኳቸው፡፡ በዚህ ላይ ፍርድ ቤት ጊዜ ወሰደና የ28 ቀን የጊዜ ቀጠሮ ሠጠ፡፡
ጥያቄ፡- በዛሬው ችሎት አብርሃ ያለው ነገር ነበር?
ጠበቃ ተማም፡- አዎን፡፡ ‹‹ከታሰርኩ ጀምሮ ከጠበቃዬ ጋር የተገናኘሁት አንድ ቀን ብቻ ነው›› በማለት ለችሎቱ አቤቱታ አቅርቦ ነበር፡፡ ዳኛውም ‹ ከአሁን በኋላ እንደዚህ ዓይነት ቅሬታ መስማት አልፈልግም፡፡ ከጠበቃው ጋር አገናኙት፡፡ ካልሆነ እቀጣችኋለሁ›› ብለዋል፡፡
ጥያቄ፡- በዚህ መሠረት አብርሃን መቼ ያገኙታል?
ጠበቃ ተማም፡- ነገ አርብ ነው፤ አገኘኋለሁ፡፡
ጥያቄ፡- አንድ ቀን ሲያገኙት ስሜቱ እንዴት ነበር?
ጠበቃ ተማም፡- ባለፈው ለችሎት ያመለከተውን ነበር የነገረኝ፡፡ መጎሸሙን፣ መሰደቡን፣ ሰብዓዊ መብቱ መጣሱንና አስፈራተውት መፈረሙን ነግሮኝ ነበር፡፡
ጥያቄ፡- የፍርድ ቤቱ ዳኛ እርስዎን የሚያሥጠነቅቁ ነገሮች ተናግረዋል፡፡ ተገቢ ነው? እርስዎስ በዚህ ጉዳይ ላይ ምን ተሰማዎት?
ጠበቃ ተማም፡- እኔ ስለምንም ነገር አልሰጋም፡፡ ለምን እሰጋለሁ? በሰፈሬ እና በሀገሬ ነው ያለሁት፤ ምንም አልፈራም፣ አልሰጋም፡፡ ምንም ስላላደረኩኝ ልፈራ አይገባም፡፡ እንደዛ የሚያስቡ ሰዎች ናቸው በፍራት ያለባቸው፡፡ ሕገ-ወጥ ሥራ የሚሰሩ ሰዎች ናቸው መፍራት ያለባቸው፡፡ አንተን የሚያስፈራሩ ሰዎች መፍራት አለባቸው፡፡ ለምን? በእንደዚህ አይነት ጉዳይ መፍራት ለራሴ ውርደት ይመስለኛል፡፡ ማንም ጉልበተኛ ነኝ ባይ ሁሉ፣ እንደቦዘኔ ሊያስፈራራኝ በፈለገ ቁጥር ከፈራሁና ከሰጋሁ ውርደት ነው – በዚህ ዕድሜዬ! የሆነ ሀገር ሄደህ ቢሆን እኮ፣ ‹‹ከሀገራቸው ያባርሩኛል፤ እንዲህ ያደርጉኛል›› ልል እችላለሁ፡፡ በሀገሬ ግን ለምን እሰጋለሁ፡፡ በመጀመሪያ፣ ምንም ነገር አይመጣም፡፡ ሁለተኛ፣ ነውር ነው፡፡ አንተ በሀገርህ እያለህ ማንም ሊያሠጋህ አይገባም፡፡ ምክንያቱም፣ አንዱ በሀገርህ ላይ የመኖርህ መገለጫ ሳትሰጋህ መኖር ነው፡፡ ሌላ ሀገር ያለ ይመስል አልሰጋም፡፡
ጥያቄ፡- ከዚህ ጋር በተያያዘ ጠቅለል ባለ መልኩ ማለት የምትፈልገው ነገር?
ጠበቃ ተማም፡- ለአንድ ሀገር እና ሕዝብ አብሮነት ማኅበራዊ መስተጋሩ ተጠባብቆ መኖሩ አስፈላጊ ነው፡፡ ሁለተኛ፣ ሕግ መከበር አለበት፡፡ ሶስተኛ፣ ሕገ-ወጥ ሕጎች እየበዙ ነው፣ ማብቃት አለባቸው፡፡ ስለዚህ ተከባብረን፣ ተረዳድተንና ተዋውቀን መኖር አለብን፡፡ ሁሉም ሰው አንዱ የአንዱን መብት እየጠበቀ መኖር አለበት፡፡
ምንጭ ዘ-ሐበሻ

Thursday, September 4, 2014

በቂ የገንዘብ ድጋፍ ሲገኝ መንግስት በ1997 ጉዳት ላደረሰባቸው ወገኖች ካሳ እንዲከፍል የሚጠይቀው ክስ እንደሚከፈት ስዊድናዊው የህግ ባለሙያ አስታወቁ

ነሃሴ ፳፱(ሃያዘጠኝ)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በ1997 ምርጫ ወቅት ለ200 ሰዎች ሞት እና በመቶዎች ለሚቀጠሩት ቁስለኞች ተጠያቂ በሆኑ 13
ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት እና ወታደራዊ  አዛዦች ላይ ለፖሊስ የክስ አቤቱታ አስገቡት በስዊድን ታዋቂ የሆኑት ጠበቃ ስቴላ ጋርደ ከኢሳት ጋር
ባደረጉት ቃለምልልስ፣ በቅርቡ ለፖሊስ ከገባው አቤቱታ በተጨማሪ የኢትዮጵያ መንግስት በግፍ ለተገደሉት፣ ለቆሰሉት ፣ ለታሰሩት፣ ከስራ ለተፈናቀሉት
አስፈላጊውን ካሳ እንዲከፍል ለማስገደድ የገንዘብ ማሰባሰብ ስራ እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።
አብዛኛውን የምርመራ ስራ የሚሰራውና ወጪውን የሚሸፍነው የስዊድን ፖሊስ ቢሆንም፣ ምስክሮችን ለማስመጣትና ተጨማሪ ሰነዶችን ለማሰባሰብ ገንዘብ
እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል።
ገንዘብ የሚያስፈልገው ክሱን ለሚመሰርቱት የህግ ባለሙያዎች አይደለም የሚሉት ስቴላ፣ በክርከሩ ወቅት የኢትዮጵያ መንግስት ቢያሸንፍ፣ መንግስት ለሚያቆመው
ጠበቃ ወጪ መከፈል ስላለበትና ወጪውን የሚሸፍነውም የተረታው አካል በመሆኑ ነው ብለዋል። የኢትዮጵያ መንግስት በክሱ ከተረታ ግን በውጭ ያለው ሃብቱ
ታግዶ ለተጎጂዎች እንዲሰጠጥ ይደረጋል ብለዋል።
በ13 የመንግስት ባለስልጣናት ላይ የክስ አቤቱታ ቢቀርብም በመንግስት ላይ እስካሁን አልቀረበም ያሉት ስቴላ፣ ኢትዮጵያውያን አስፈላጊውን መዋጪ ማድረግ
ከቻሉና በቂ ገንዘብ እንዳለ ሲታወቅ የካሳ መጠየቂያ ክሱ ወዲያው ይከፈታል ብለዋል። ማንኛውም ገንዘብ አለማቀፍ ደረጃ ባላቸው የሂሳብ ሰራተኞች እንደሚታይና
የተዋጣው ገንዘብ ለህዝብ ይፋ እንደሚሆን ገልጸዋል።
ሰሞኑን ለፖሊስ የቀረበውን አቤቱታ በተመለከተ ጥያቄ የቀረበላቸው ስቴላ፣ ፖሊስ ማመልከቻውን ተቀብሎ ምርመራ መጀመሩንና በሁለት ወይም ሶስት ሳምንታት
ውስጥ ለስዊድን አለማቀፍ ወንጀል  አቃቢህግ እንደሚያስተላልፍ ተናግረዋል። አቃቢ ህግ የቀረቡትን መረጃዎች አይቶ ክሱን ወደ ፍርድ ቤት ለመውሰድ ወይም
ላለመውሰድ እንደሚወስን የገለጹት ስቴላ፣ የቀረቡት ማስረጃዎች ክሱ በአጭር ይቋጫል ብለው ለመናገር እንደማያስድፈራቸው ገልጸዋል።
ከአለፉት አስር አመታት ወዲህ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች እና የጦር ወንጀሎች በየትኛውም አገር መታየት መጀመራቸው ክሱን ለመመስረት እንዳነሳሳቸው ጠበቃው
ገልጸዋል።
አቃቢ ህግ ክስ ለመመስረት ከወሰነ ስዊድን ውስጥ ያሉ ተጠያቂዎች በቁጥጥር ስር እንደሚውሉ፣ ሌሎች ከስዊድን ውጭ የሚኖሩ ባለስልጣናት ደግሞ በኢንተርፖል
በኩል ስማቸው ተላልፎ ተይዘው ክሳቸውን እንዲከታተሉ እንደሚደረግ አክለው ገልጸዋል።
ከጠበቃ ስቴላ ጋርደ ጋር ያደረግነውን ቃለመጠይቅ በነገው ዝግጅት ይዘን እንቀርባለን።

Wednesday, September 3, 2014

ሐሰን ሺፋ ከፌደራል ፖሊስ ም/ኮሚሽነርነት ሥልጣናቸው ተነሱ

(ዘ-ሐበሻ) የሕወሓት ነባር ታጋዮች መካከል አንዱ የነበሩትና ሕወሓት በተከፋፈለበት ወቅት የነስዬ አብርሃ ወገንን ተቀላቅለው በኋላም ወደ አቶ መለስ ወገን ይቅርታ ጠይቀው የተመለሱት የፌደራል ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር አቶ ሐሰን ሺፋ ከስልጣናቸው እንዲነሱ መደረጉ አነጋጋሪ መሆኑን ለዘ-ሐበሻ የደረሱ መረጃዎች አመለከቱ።
hasen shifa
የፌዴራል ፖሊስ የዘ-ሐበሻ ታማኝ ምንጮች እንደገለጹት አቶ ሐሰን ሽፋ በተለይ የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ሰላማዊ እንቅስቃሴን የሕወሓት መንግስት እንዳሰበው በተንኮል ሊቆጣጠረው ካለመቻሉና በስርዓቱ ባለስልጣናት ውስጥ በተነሳው ያለመተማመን ችግር ጋር ተያይዞ ካሉበት ቦታ እንዲነሱ ተደርገዋል። አቶ ሐሰን በምክትል ኮምሽነርነት የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነሩን ከታች ሆነው ሲዘውሩ የቆዩ ሲሆን በአዲስ አበባ፣ በኦሮሚያ፣ በአፋር፣ በጋምቤላ፣ በትግራይ፣ በአማራ ክልል፣ በደቡብና በሌሎችም ስፍራዎች ሥርዓቱ ለፈጸማቸው ጭፍጨፋዎች ተጠያቄ እንደሆኑ የሚናገሩት የዘ-ሐበሻ ምንጮች በድንገት ከዚህ ስልጣናቸው ተነስተው ወደ ፌደራል ጉዳዮች ሚ/ር መስሪያ ቤት ውስጥ እንዲሰሩ መላካቸው የስርዓቱን ደጋፊዎች ሳይቀር “ድርጅቱ በውስጡ ምን እየሆነ ነው?” በሚል እያነጋገረ ነው ብለዋል።
በሕወሓት/ኢሕአዴግ አገዛዝ ስር ያሉ ባለስልጣናት እርስበእርሳቸው አለመሰማማታቸው እንዲህ ያሉ ከስልጣን መነሳቶችና/ መዘዋወሮች በግልጽ የሚያሳዩ ናቸው የሚሉ አስተያየት ሰጪዎች አሉ።
ምንጭ ዘ-ሐበሻ

Monday, August 25, 2014

ከጥቅሙ ጉዳቱ ይበልጣል (ፕ/ር መስፍን ወልደ ማርያም)

መስፍን ወልደ ማርያም
ሐምሌ 2006
ፕ/ር መስፍን ወልደ ማርያም
ፕ/ር መስፍን ወልደ ማርያም
ጉልበት አራዊት የሚተዳደሩበት ሕግ ነው፤ ሕገ አራዊት የሚባለው አራዊት የሚተዳደሩበት ጉልበት ነው፤ በአራዊት ዓለም ማናቸውም ነገር በጉልበት ያልቃል፤ በሰዎችም መሀከል ጉልበት አድራጊ-ፈጣሪ ሆኖ ጎልቶ ሲወጣ የአእምሮንና የኅሊናን መዳከም ወይም ጭራሹኑ አለመኖር ያመለክታል፤ ጉልበት አለን በማለት፣ ወይም ተመችቶናል በማለት፣ ወይም ጠያቂ የለብንም በማለት የማንኛውንም ሰው ሰብአዊ መብቱንና ሰብአዊ ክብሩን መግፈፍ ሦስት ነገሮችን ያመለክታል፤ አንደኛ ጉልበት እንጂ አእምሮና ኅሊና እንደሌለ፣ ሁለተኛ ጉልበት እንጂ ሕግ እንደማይከበር፣ ሦስተኛ በአንተ ላይ እንዲያደርጉብህ የማትፈልገውን አንተም በሰዎች ላይ አታድርግ የሚለውን ሕግ መጣስን ያሳያል፤ በመጨረሻም፣ ዘግይቶም ቢሆን በራስ ላይ ቅሌትን መጋበዝን ያስከትላል፤ የሌላውን ሰውነት ስናረክስ ሰውነትን በጠቅላላው ማርከሳችን ነው፤ ሰውነትን በጠቅላላው ስናረክስ ራሳችንን ከነጉልበታችን ማርከሳችን ነው፤ ራሳችንን፣ ሰውነታችንን ካረከስን በኋላ ዋጋ የለንም፤ ለራሳችን ዋጋ ከሌለን ለሌለች ሰዎችም ዋጋ አንሰጥም፤ ያኔ ክፉ በሽታ ይይዘናል፤ እግራችን ስር በወደቀ ሰው ስቃይ የምንደሰትና የምንስቅ፣ የምንፈነድቅ እንሆናለን፤ ያን ጊዜ የለየለት በሽተኛ ሆነናል።
ይሄ በሽታ ያቃዣል፤ ከሰው ሁሉ በላይ ያሉ ያስመስላል፤ አግሩ ስር የወደቀው አንድ ሰው የሰው ልጅ በሙሉ ይመስለዋል፤ በሽተኛነቱን ስለማያውቅ በሽታው ከሰው በላይ ያደረገው ይመስለዋል፤ እንዲህ ዓይነቱ በሽተኛ በሕግ አሰከባሪነት ሥራ ውስጥ ሲገባ ሕግ የአንድ ማኅበረሰብ ትምክህትና መከታ በመሆን ፋንታ የበሽተኞች በትር ይሆናል፤ በደርግ ዘመን የአራት ኪሎው ግርማ የሠራውን እናውቃለን፤ ዛሬ ደግሞ ልዩ ግርማዎች አሉ፤ መልካቸውን ከካሜራው ጀርባ ደብቀው በሰው ስቃይና አበሳ በሳቅ እየተንከተከቱ ጀብዱዋቸውን በቴሌቪዥን የሚደረድሩ ጀግኖች መጥተዋል፤ መሣሪያ ይዞ መሣሪያ ባልያዘ ሰው ላይ ጀግና መስሎ ለመታየት የሚሠራው ጨዋታ ራስን ክፉኛ ከማጋለጥ በቀር ሌላ ፋይዳ የለውም።
በኢትዮጵያዊ ሰውነት ላይ ማናቸውንም ከሕግና ከሰብአዊነት ውጭ የሆነ ሙከራ ለማድረግ የውጭ አገር ሰዎች ዕድሉን ይፈልጉት ይሆናል፤ ለነሱ ሰዎች ስላልሆን ሰብአዊነት አይሰማቸውም፤ ከአገራቸው ሕግም ውጭ በመሆናቸው በሕግ አይገዙም፤ ዋናው ውጤት ግን ለኢትዮጵያ ሕግ አስከባሪዎች የሚያስተምሩት ግዴለሽነት ነው፤ መታሰር በብዙ ምክንያቶች ይመጣል፤ ስለዚህ በሠለጠነው ዓለም የተለያዩ እስረኞች በተለያየ ሁኔታ ይጠበቃሉ፤ አንዳንዶቹ እንዲያውም በቤታቸው ውስጥ እየተጠበቁ ይቆያሉ፤ ኢትዮጵያ በራስዋ ሥልጣኔ በምትተዳደርበት ዘመን መሳፍንትና መኳንንት የሚታሰሩት በወርቅ ወይም በብር ሰንሰለት ነበር፤ ግዞትም፣ የቁም እስርም ነበር፤ ዛሬ በኢትዮጵያ ውስጥ እስረኞች ሁሉ እኩል ናቸው፤ በቃሊቲ ለየት ያለ አያያዝ የሚታየው ለሙስና ወንጀል ተጠርጣሪዎች ብቻ ነው።
ጉልበትን በጉልበት እቋቋማለሁ የሚል ሰው ሲሸነፍ አያስደንቅም፤ አዲስም አይደለም፤በአለፉት አርባ ዓመታት እየተሸነፉ ከትግሉ ሜዳ ወጥተው በተለያዩ የምዕራባውያን አገሮች የሙጢኝ ብለው የተቀመጡ አሉ፤ በተባበሩት መንግሥታት ደንብ የሙጢኝ ማለት መብት ነው፤ ይህንን መብት መጣስ የመንግሥተ ሰማያትን በር መድፈር ነው፤ በጎንደር የአደባባይ ኢየሱስን ቤተ ክርስቲያን በር መድፈር ነው፤ በአዲስ አበባ የቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያንን በር መድፈር ነው፤ በአዲስ አበባ የአንዋር መስጊድን በር መድፈር ነው፤ ወደመሬት ስንወርድም የሙጢኝ የተባለው አገርን መንግሥት መድፈር ነው፤ የተባበሩት መንግሥታት ደንብን መጣስ ነው፤ ለነገሩ የመንግሥተ ሰማያትን በር መድፈር ከተቻለ ሌላው ምን ያቅታል!
የሙጢኝ ያለን ሰው በአፈና መያዝና ወደአገር ማስገባት አንድ ችግር ነው፤ ይህ የጉልበተኛነት መገለጫው ነው፤ ሁለተኛው ችግር የተያዘው ሰው መብቱና ክብሩ ሳይጓደልበት ማስረጃዎችን ሰብስቦ ለነጻ ፍርድ ቤት አለማቅረቡ ነው፤ በቴሌቪዥን እንደታየው አካላዊ ጉዳት እንደደረሰበት ባይታወቅም፣ ጥልቅ መንፈሳዊ ጉዳት እንደደረሰበት ይታያል፤ በብዙ አገሮች ሕጎች አንድ ሰው ራሱን እንዲወነጅል አይገደድም፤ ሕጋዊ ምርመራም በቴሌቪዥን በአደባባይ አይካሄድም።
ስለዚህም በተጠርጣሪው ላይ የተደረገው ሁሉ ሕጋዊ አይደለም፤ በነጻ ፍርድ ቤት ቢቀርብም በቴሌቪዥን የተናገረው ሁሉ ቢያስታውሰውም በማስረጃነት የሚያገለግል አይመስለኝም፤ ስለዚህም ከጥቅሙ ጉዳቱ ይበልጣል።
ከአፍሪካ አህጉር ወጥቶ የቀይ ባሕርን አቋርጦ አንድ ሰው፣ ገና ወደፊት ክፉ ሊሠራ ይችላል በሚል ሂሳብ በጉልበት አፍኖ ማምጣት የብዙ ነፍሶች ዕዳን ተሸክመው በኢጣልያ ኤምባሲ የሙጢኝ ብለው ተደላድለው የተቀመጡትን የደርግ አባሎች ማስታወስ ግዴታ ይሆናል፤ አድርጋችኋል የተባሉትን ሰዎች የሙጢኝ የማለት መብት አክብሮ አስበሃል የተባለውን ሰው የሙጢኝ የማለት መብት መጣስ ከጥቅሙ ጉዳቱ ይበልጣል።
ከፖሊቲካና ከምናምኑ፣ ጉልበተኛነትንም ከማረጋገጡ በላይ ሌላ ትልቅ ነገር አለ፤ አገር የሚባል ነገር አለ፤ ይህ በአንድ ግለሰብ ላይ የተገኘ ጊዜያዊ ድል የአገርን ከብር የሚያጎድፍና የሚያቀል ይሆናል፤ የአንድ አገርን የመንግሥት ሥልጣን የያዘ አካል አንድ ግለሰብን በአደባባይ ከሕግ ውጭ ለማጥቃት ሲሞክር የራሱን ክብር ዝቅ ያደረግበታል፤ ስለዚህም ከጥቅሙ ጉዳቱ ይበልጣል።
በእኔ ዕድሜ ሰው በአደባባይ ሲገረፍ አይቻለሁ፤ ሰው ተሰቅሎ አይቻለሁ፤ የዚያን ዘመን የእውቀት ደረጃ የዚያን ዘመን የሰው ልጆች የመንፈስ እድገት ደረጃ ያመለክታል፤ የእውቀትም የመንፈስም ደረጃ በጣም ዝቅተኛ ነበረ ማለት ነው፤ ስለዚህም ይህንን ያደረጉትን ዛሬ አንወቅሳቸውም ይሆናል፤ የታሪካችን ጉድፍ መሆኑን ግን ልንፍቀው አንችልም፤ ስለዚህም ሌላ ጉድፍ እየጨመርንበት ታሪካችንን ማቆሸሹ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ይበልጣል።
ቅጣት በሕግና በሥርዓት ይደረግ ማለት ያጠፋ ሰው አይቀጣ ማለት አይደለም፤ ነገር ግን ምንም አቅም የሌለውን ሰው ይዞ በአደባባይ ማሰቃየትና ማዋረድ አገርንና ሕዝብን ማዋረድ ነው፤ የሰብአዊነትንም የሕጋዊነትንም ሚዛኖች ይሰባብራል።
ምንጭ ዘ-ሐበሻ

Friday, August 22, 2014

የውሸት አባት 2ኛ ሙት ዓመት ነዶ የማያልቀው [ሻማ] የኢትዮጵያ ሕዝብ

ግንቦት 20፣ 1983ዓም መለስ ወይም ለገሠ ወይም አስረስ ወይም ዜናዊ ወይም … ትክክለኛ ስሙን በውል የማናውቀው ከነጭፍሮቹ ቤተመንግሥት ገብቶ ራሱን አጼያዊ ፕሬዚዳንት፣ ቀጥሎም አጼያዊ ጠቅላይ ሚኒስትር፣ … በማድረግ ከሾመበት ቀን ጀምሮ የኢትዮጵያ ሕዝብ በኦፊሴል እንደ ሻማ ወይም እንደ ኩራዝ ተለኩሷል።
አቀጣጣዮቹ ምስለኔዎች ከሻማና ከኩራዝ ከፍ ብለው ብርጭቆ የለበሱ ፋኖሶች ሆነዋል። ለመለስና ለጭፍሮቹ የሚያበሩ ፋኖሶቹም (ኦህዴድ፣ ብአዴን፣ …)፣ ኩራዞቹም፣ ሻማዎቹም የበራላቸው ማሾዎች (ህወሃቶች) ሁሉም በአንድነት ዛሬ ላይ ደርሰዋል። ለኳሹም ተለኳሹም እያበሩ የአስለኳሹን ሁለተኛ ሙት ዓመት “እያከበሩ” ነው። በሌላ አነጋገር ለሙት መንፈስ እሣት አንድደው እየሰገዱ ነው። ተገድዶ እየነደደ ያለውን ሕዝብ፣ አዳዲሶቹ አስለኳሾች (የኃይለማርያም ደቦ አስተዳደር) ሕዝብን ሻማ ላደረገውና ከስሙ ጀምሮ በውል ማንነቱ ላልታወቀው ግለሰብ “ሻማ አብሩ” አሉለት።
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ ለሁለተኛው ሙት ዓመት “የውርስ መታሰቢያነት” ከዚህ በታች ያለውን የመክብብ ማሞን ጽሑፍ ሲያቀርብ በመለስ ሞት ላዘኑ ሁሉ ለሃዘናቸው መጉመጥመጫ እንዲሆን በማሰብ ነው። “የውሸት አባት” መለስ ነፍስ ካወቀበት ጊዜ ጀምሮ ስዩመ አብዮታዊ ዴሞክራሲ አጼ አድርጎ ራሱን በመሰየም ሕዝብን እንደሻማ ባነደደበት ዘመናት ከአንደበቱ ሲወጡ የተመዘገቡ ውሸቶች ስፍር ቁጥር የላቸውም።
በተለይ ግን በ1997ቱ ምርጫ ሰሞን ሕዝብ እንደ ሻማ ከመቃጠልና ከመንደድ የራሱን መሪ እንዳይመርጥ የዋሸው ውሸት ከዚህ በታች ሰፍሯል። ታዲያ ሕዝብ እንደ ሻማ ከመቅለጥ የሚያድነውን እንዳይመርጥ ለገደበ ግለሰብ እንዴት ሻማ ይበራለታል?!
“ማሾዎቹ” ደረት ቢደቁ፣ ከበሮ ቢደልቁ፣ ፈንዲሻ ቢበትኑ፣ አሸንዳ ቢዘሉ፣ ሠርግና ምላሽ ቢያደርጉ፣ “አንጓይ ፍስስ” ቢሉ፣ … ምክንያት አላቸው። እንደ ዱር አውሬ “የአገር ቅርስ” ሲሉት ውለው ቢያድሩ ከልካይ ሊኖራቸው አይችልም። በሚሊዮን ሕዝብ ችግር ላይ ቆመው ለሙት መንፈስ ቢንደባለሉ ደንታ የላቸውም። ሚሊዮኖች በሚያዝኑበት አገር፣ እስር ቤትና ማጎሪያዎች ውሥጥ የታፈኑት ሲቃ በሚያሰሙበት አገር እነርሱ ሙት ዓመትን አስረሽ ምቺው ቢያደርጉት ማን ተዉ ሊላቸው ይችላል?! ምክንያቱም ብርሃን ይፈልጋሉ፤ ለዚያ ደግሞ ነዶ የማያልቅ ሻማ ያስፈልጋል።
ለማንኛውም መጪው የምርጫ ጊዜ ነውና የወደፊቱን ውሸት ከዚህ በታች በሰፈረው የመክብብ ማሞ ጦማር እያጣቀሳችሁ የ… ዜናዊን ሙት ዓመት አክብሩ። ለኢትዮጵያ እውነተኛ ስም ያለውና ለዘመናት በዚያው ስሙ የሚጠራ መሪ ይስጣት።
“ውሸታም!”
ሰሞኑን (ይህ ጽሁፍ የተጻፈው በመስከረም 2002/Sept. 2009 ነው) የመገናኛ ብዙሃንን ትኩረት የሳበ አንድ ክስተት በአሜሪካ ተፈጽሟል። ፕሬዚዳንት ኦባማ በምርጫ ዘመቻቸው ጊዜ ቃል የገቡለትን የጤና ጥበቃ ማሻሻያ አዋጅ እንዲጸድቅ የሕዝብ ተወካዮችን ሰብስበው ንግግር በሚያደርጉበት ወቅት ከተቃዋሚ የሪፓብሊካኑ ወገን የማርጎምገምና የተቃውሞ ድምጽ ተሰማ። በተለይ ግን የጤናው ማሻሻያ አዋጅ “ሕገወጥ ስደተኞችን አያካትትም” የሚል ንግግር ባደረጉ ጊዜ ከደቡብ ካሮላይናው እንደራሴ “ውሸታም!” የሚል ድምጽ አስተጋባ።
እንደ እውነቱ ከሆነ በረቂቅ ሕጉ ላይ ሕገወጥ ስደተኞች የጤና መድኅን ዋስትና እንደማያገኙ በማያሻማ መልኩ የሰፈረ ጉዳይ ነው። እዚህ ላይ “ማነው ውሸታም?” የሚለውን ለመመርመር አይደለም ጉዳዩን የጽሁፌ መነሻ ያደረኩት። ሆኖም ግን ይህንን የሰማሁ ምሽት እንደራሴው ኢትዮጵያ ቢሆኑ ኖሮ ከምርጫ 97 ጀምሮ እስካሁን (2002ዓም) ድረስ ምን ያህል ጊዜ “ውሸታም!” እያሉ ይጮኹ ይሆን በማለት ያለፉትን አምስት ዓመታት (1997-2002ዓም) በምናቤ መቃኘት ጀመርኩና ከዚህ በፊት የተደረጉ ቃለመጠይቆችን ለመመርመር ወደኋላ ሄደኩ።
ማርክሲስታዊው ህወሃት ከበረሃ ወጥቶ የምኒልክን ቤተመንግሥት ከተቆጣጠረበት ጊዜ ጀምሮ ላለፉት 18 (አሁን 23) ዓመታት ከአመራሮቹ ስንሰማ የቆየነው ውሸት ጆሮ የሚገነጥል ሲሆን በተለይም የኢትዮጵያ ሕዝብ ድምጽ ከተሰረቀበት 1997ዓም ጀምሮ “ጠቅላይ ሚኒስትሩ” ለተለያዩ ምዕራባዊ የመገናኛ ብዙሓን “ሥልጣኔን እለቃለሁ” በማለት ሲቀደድ የነበረው ከቁጥር በላይ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም። ጥቂቱን ግን ከዚህ በታች አቅርቤዋለሁ። (ከአዘጋጆቹ፤ መለሳውያን በሙሉ የሙቱን መንፈስ 2ኛ ዓመት ስትዘክሩ የውሸት ውርሱንም አትዘንጉ)።
የቢቢሲው ጋዜጠኛ ስቲፈን ሳኩር ከምርጫ 97 በኋላ ለ“ጠቅላይ ሚኒስትር” ዜናዊ ሰኔ 27 ቀን 1997 ዓም ቃለመጠይቅ ባደረገበት ወቅት የሚከተሉትን ጥያቄዎች ጠይቆት ነበር።candle1
ስቲፈን፡- አሁን ስላለው አጀንዳ እንድጠይቅ ይፈቀድልኝ። እንደው እንደበልና የምርጫው ውጤት ፓርቲህን አሸናፊ አደረገው እንበል እና ይህ ከሆነ እንደገና ለሚቀጥሉት አምስት ዓመታት እንደገና በሥልጣን ላይ ትቆያለህ?
ዜናዊ፡- ያ ፓርቲዬ የሚወስነው ጉዳይ ነው።
ስቲፈን፡- አንተ ግን ምን ለማድረግ ነው የምትፈልገው?
ዜናዊ፡- እኔ ማድረግ የምፈልገውን ቆየት ብዬ የማስብበት ነው። ውሳኔዬም በሁኔታዎች ላይ የተመሠረተ ነው።
ስቲፈን፡- በእርግጥ ማድረግ የምትፈልገውን ወስነሃል። ማለቴ ለመመረጥ ተወዳድረሃል፤ ይህም ማለት ሥልጣኑን ትፈልገዋለህ ማለት ነው። (በሥልጣን መቆየት ባትፈልግ አትወዳደርም ነበር)
ዜናዊ፡- ሥልጣኑን የምፈልገው አገሬን ለማገልገል ነው። የማገለግለው ግን የምጨምረው እሴት ሲኖር ነው። … የምጨምረው እሴት አለኝ። ይህንንም እቀጥልበታለሁ የምጨምረው እሴት እስካለኝ ድረስ። በተመሳሳይ መልኩ ፓርቲዬ እሴት የማልጨምር መስሎ ሲያገኘው በማንኛውም ጊዜ ጠቅላይ ሚኒስትር ሊቀይር ይችላል።
“ውሸታም!”
ህወሃት/ኢህአዴግ ምርጫውን ካጭበረበረ 1 ዓመት ከ7 ወር በኋላ የዋሽንግተን ፖስት ጋዜጠኛ ስቴፋኒ ማክሩመን ታህሳስ 5፤1999ዓም ተመሳሳይ ጥያቄ አቅርባ ነበር።
ስቴፋኒ፡- ለሦስተኛ ጊዜ ለመመረጥ ዕቅድ አለህ?
ዜናዊ፡- ፓርቲዬ? ፓርቲዬ ለሦስተኛ ጊዜ ብቻ ሳይሆን ለአስረኛ ጊዜም ቢሆን ሊሞክር ይችላል።
ስቴፋኒ፡- አንተስ በግልህ?
ዜናዊ፡- እኔ በግሌ ይበቃኛል ነው የምለው።
“ውሸታም!”
ቀጥሎም ከዘጠኝ ወር በኋላ አሌክስ ፔሪ ከ“ታይም” መጽሔት ጳጉሜ 1፤1999ዓም የሚከተሉትን ጥያቄዎች አቀረበ።
አሌክስ፡- አብዛኛውን ጊዜ የአፍሪካ መሪዎች ሥልጣን ለመልቀቅ ሲያመነቱ ይስተዋላሉ። ሆኖም ግን ከዚህ በፊት በሥልጣን እንደማትቆይ ፍንጭ ስትሰጥ ቆይተሃል።
ዜናዊ፡- አሁን ሦስት ዓመት ብቻ ነው የቀረኝ።
አሌክስ፡- ከዚያ ሥልጣንህን ትለቅቃለህ?
ዜናዊ፡- ከዚያማ ሒደቱ ይቀጥላል።
አሌክስ፡- ለምንድነው ሥልጣን መልቀቅ የምትፈልገው?
ዜናዊ፡- እስካሁን ብዙ ቆይቻለሁ። ከዚህ በኋላ ባለው ጊዜ አዲስ ነገር ለማድረግ የማስብበት ይሆናል።
“ውሸታም!”
ዜናዊ ቀጣዩን ቃለመጠይቅ ሲያደርግ ደግሞ ከታይም መጽሔቱ አሌክስ ጋር ያደረገው ሦስት ወር እንኳን አልሞላውም ነበር። ጠያቂው የአልጃዚራው መሃመድ አዶው ምልልሱን ያደረገው ኅዳር 12፤ 2000ዓም ነበር።
መሃመድ፡- በቅርቡ ከጠቅላይ ሚኒስትርነት ሥልጣን የመልቀቁን ጉዳይ እያሰብክበት ነውን?
ዜናዊ፡- ከዚህ በፊት እንደተናገርኩት በጠቅላይ ሚኒስትርነት የማገለግልበት ይህ የመጨረሻው የሥልጣን ዘመኔ ነው (2002ዓም ማለቱ ነበር)።
“ውሸታም”
በዚሁ በ2000ዓም ግንቦት 4ቀን awate.com ከተሰኘ ድረገጽ ጋር ቃለምልልስ ያደረገ ሲሆን ጠያቂውም ሳሌህ ጆሃር ነበር።
ሳሌህ፡- በህይወት ዘመኔ ከሥልጣንህ ለቅቀህ “የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር” እየተባልክ በመጠራት ዩኒቨርሲቲ ውስጥ በማስተማር፣ መጽሐፍ በመጻፍ ወይም አንድ ፋውንዴሽን ስትመራ የማይበት ጊዜ ይመጣ ይሆን? እስቲ ንገረኝ።
ዜናዊ፡- በጣም ትክክል ነው። እኔም ያንን ቀን እየናፈኩት ነው። ሩቅ እንደማይሆን አስባለሁ።
ሳሌህ፡- ይህ ማለት እንግዲህ ለሌሎች ሁሉ ምሳሌ ትሆናለህ ማለት ነው?
ዜናዊ፡- ምንም ጥርጥር የለውም። ነገን ልትኖረው እንደምትችል እርግጠኛ ልትሆን አትችልም። ሆኖም ግን እንደማንኛውም ሰው እኖራለሁ ብዬ በማሰብ ከሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት በኋላ (ከ2002ዓም ጀምሮ ማለቱ ነበር) “የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር” ብለህ ልትጠራኝ ትችላለህ።
“ውሸታም!”
ውሸቱ ግን በዚህ አላቆመም። በመጋቢት 24፤ 2001ዓም የቢቢሲዋ ዘይነብ ባዳዊ ቃለመጠይቅ ባደረገችለት ጊዜ ይህንኑ ሥልጣን የመልቀቅ ጥያቄ አንስታ ነበር።candle 2
ዘይነብ፡- ከዚህ በፊት (ባቀረበችው ጥያቄዎች) እንደጠቆምኩት ከ1983 ዓም ጀምሮ በሥልጣን ላይ ነበርክ። አንዳንድ ጊዜ ከሥልጣን የምትለቅበት ጊዜ እንደደረሰ ስትናገር ቆይተሃል። ሌላ ጊዜ ደግሞ ራስህን የፓርቲህ ወታደር አድርገህ ስትናገር ትደመጣለህ። መቼ ነው (ከሥልጣን የምትለቅበትን) እርግጠኛውን ቀን የምትነግረን? ምክንያቱም ከምናያቸው ነገሮች ስንነሳ ይህ በአፍሪካ መሪዎች ዘንድ የሚታየውን “ያለኔ …” የሚለውን አስተሳሰብ ትደግፋለህ እንድንል እያደረከን ነው ያለኸው። ማለትም ምትክ የሌለው መሪ ዓይነት (እየሆንክ ነው)፤ ለሁለት ዓስርተ ዓመታት በሥልጣን ቆይቻለሁ የሚል ዓይነት?
ዜናዊ፡- ራሴን ምትክ የሌለው መሪ አድርጌ አላውቅም። እናም ማንኛውም ሰው ራሱን ለፓርቲም ሆነ ለአገር ምትክ የሌለው አድርጎ የሚቆጥር ከሆነ ያ ፓርቲም ሆነ አገር መኖር ይገባዋል ብዬ አላምንም።
ዘይነብ፡- ታዲያ መቼ ነው ቁርጥ ያለውን ቀን የምትናገረው?
ዜናዊ፡- ፓርቲዬ ካቀረብኩት ዕቅድ ጋር ሲስማማ ያኔ ይሆናል።
ዘይነብ፡- ዕቅድህ ምን እንደሆነ ልትነግረን ትችላለህ? በ2002ዓም ምርጫ ይካሄዳል?!
ዜናዊ፡- ዕቅዴማ ይህ የመጨረሻው የሥልጣን ዘመኔ እንደሚሆን ማረጋገጥ ነው።
“ውሸታም!”
በዚህ አላበቃም! ሰኔ 10፤2001ዓም የፋይናንሺያል ታይምስ የአፍሪካ ቢሮ አርታኢ የሆነው ዊሊያም ዋሊስ ይህንኑ ማለቂያ የሌለውን የሥልጣን መልቀቅ ጥያቄ አቅርቦ ነበር። ሆኖም አጠያየቁን ቀየር አድርጎት ስለነበረ የውሸቱ ለከት የት እንደደረሰ በግልጽ እንዲያሳይ አድርጎታል።
ዊሊያም፡- ከዚህ ቀደም ከሥልጣን ለመውረድ ፈቃደኛ እንደሆንክ ስትናገር ቆይተሃል። በዚህ ዙሪያ ያለውን እንቅስቃሴ ምን እንደሚመስል ብታስረዳን?
ዜናዊ፡- በአሁኑ ጊዜ በፓርቲያችን ውስጥ ውይይት እያደረግን ነው። ይህም በፓርቲያችን ውስጥ የምናደርገው ውይይት ሰዎች ሊገምቱት ከሚችሉት በላይ በጣም ብስለት የተሞላበት ነው። ስለ መለስ ብቻ አይደለም የምንነጋገረው። በትጥቅ ትግሉ የተሳተፈው የቀድሞው ትውልድ በአዲስና የትጥቅ ትግል ተሞክሮ በሌለው ትውልድ እንዴት ሊተካ ስለሚችልበት ሁኔታ እየተወያየን ነው። ለፓርቲያችን ሲባል ይህ መሆን ያለበት ጉዳይ ነው። ስልትን በተመለከተ ማለትም ጊዜው መቼ ይሆናል የሚለው ቁርጥ ያለ መልስ ላይኖር ይችላል። (ምርጫ መጣ ክህደት ተጀመረ) ክርክሩም በዚሁ የሚቀጥል ነው። ሆኖም ግን የቀድሞው አመራር በአዲስ መተካት አለበት በሚለው ላይ ግን አለመስማማት የሚባል ነገር አይኖርም። ይህ ከመፍትሔዎቹ አንዱ ነው፤ ብቸኛው መፍትሔ ግን አይደለም። ስለዚህም የእኛ ግምባር በአመዛኙ ሌሎች ግምባሮች ከሚያጋጥማቸው የመፈረካከስ አደጋ አምልጧል ብዬ አምናለሁ።
ዊሊያም፡- እና የሚቀጥለው ዓመት (2002 ማለቱ ነበር) በሚደረገው ምርጫ አትወዳደርም ማለት ነው?
ዜናዊ፡- እያልኩ ያለሁት እኔ በግሌ ይበቃኛል ነው የምለው። እኔ ብቸኛው ተኳሽ አይደለሁም። ለበርካታ ጊዜያት ጠቅላይ ሚኒስትር በነበርኩበት ጊዜም በድምጽ ብልጫ በመሸነፍ የማልፈልገውን ነገር ሳደርግ ቆይቻለሁ። በተለይም በኤርትራ ጦርነት ወቅት ሳልፈልገው የማልስማማበትን ሆኖም ግን የፓርቲዬ ውሳኔ በመሆኑ ብቻ ያንን ሳስፈጽም ኖሬአለሁ። በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታዎች ወቅት ሁለት አማራጮች አሉኝ። ለሥልጣን መልቀቅ ወይም የብዙሃኑን ውሳኔ መቀበል። ይህ ሲሆን እኔ የራሴን አቋም አቀርባለሁ፤ ሌሎችም የራሳቸውን አቋም ያቀርባሉ፤ ክርክሩም ይቀጥላል። ተስፋ የማደርገው ሁላችንም አንድ የመግባቢያ ነጥብ ላይ እንደርሳለን ብዬ ነው። ያም ሲሆን እኔም ህይወቴን ሙሉ ከተዋጋሁለት ፓርቲዬ መልቀቅ ሳያስፈልገኝ እንደቀጥል ይሆናል። ከመንግሥት ሥልጣኔ ከለቀቅሁ በኋላም እንኳን በፓርቲዬ በአባልነት መቀጠል እፈልጋለሁ። እናም ተስፋ የማደርገው ሁላችንም አንድ የመግባቢያ ነጥብ ላይ እንደርሳለን ብዬ ነው። ልዩነቶቻችን ደግሞ ያንን ያህል ትልቅ አይደሉም።
ዊሊያም፡- ታዲያ ይህ የሚሆነው መቼ ነው? በቅርቡ የምታደርጉት የፓርቲ ስብሰባ አላችሁ?
ዜናዊ፡- አዎን፤ መስከረም ላይ ስብሰባ አለን።
ዊሊያም፡- እናም ያኔ ነው በውሳኔው ላይ የምትከራከሩት?
ዜናዊ፡- አዎን፤ ግን ከዚያ በፊት ውይይቱ ይካሄዳል፤ …
ዊሊያም፡- ወደፊት ማነው የሚተካህ?
ዜናዊ፡- ያንን ውሳኔ ለፓርቲዬ እተወዋለሁ፤ …
ዊሊያም፡- ኢትዮጵያውያን ለምንድነው በእርግጥ ሥልጣን ትለቃለህ ብለው የማያምኑት?
ዜናዊ፡- ምክንያቱም ከዚህ በፊት በኢትዮጵያ ሲደረግ ስላላዩ ነው።
ዊሊያም፡- ነገር ግን እያደረክ ያለው ያንኑ የሚከተል እንደሆነ ነው።
ዜናዊ፡- እኔ ይህንን ዓይነት አስተሳሰብ ለማስወገድ ነው የምፈልገው፤ …
ዊሊያም፡- እናም ይህ ማለት ሙሉ በሙሉ ከማንኛውም ተግባር ትገለላለህ ማለት ነው?
ዜናዊ፡- ያ ካልሆነማ የአመራር ለውጥ ሊኖር አይችልም። ነገር ግን ያንን ካደረግን በኋላ ፓርቲዬ ወይ መጽሐፍ እያነበብኩና እየጻፍኩ እንድቀመጥ ወይም ሌላ የፓርቲ ሥራ እየሠራሁ እንድቀጥል ይወስናል።
ዊሊያም፡- የፓርቲ ሥራ ማለት ሊቀመንበርነት?
ዜናዊ፡- አይመስለኝም፤ ምክንያቱም ጠቅላይ ሚኒስትሩ የፓርቲው ሊቀመንበር መሆን አለበት። ያ ደግሞ ጡረታ ለወጣ ሰው ሊሰጠው የሚገባ ሥልጣን አይደለም።
“ውሸታም!”
እንግዲህ የኢትዮጵያ ሕዝብ እንደዚህ ዓይነት ቅጥፈት (እና ተራ የቁጭ በሉዎች ቀደዳ) ላለፉት 18ዓመታት (ጽሁፉ በ2002ዓም የተጻፈ ነው) ሲቀደድለት ቆይቶ ህወሃት በሚቆጣጠረው ቴሌቪዥን ለአዲሱ ዓመት አዲስ ዜና – ትኩስ ዜና – ሰበር ዜና – ተሰበረለት። “ምትክ አልባው ጠቅላይ ሚኒስትር ከመጪው 2002 ጀምሮ ሥልጣናቸውን ለአምስት ዓመታት እንዳራዘሙት …” አበሰረልን። ሞት ቀድሞ candle bombበ“ውርስ” መታወቅ ጀመረ እንጂ በመጪው 2007 ምርጫም ወይ ፍንክች ይል ነበር። መለስ “ሥልጣኔን እለቃለሁ” ሲል ፓርቲው ደግሞ “አትለቅም” እያለ ገመድ ሲጓተቱ ኖረው የመለስ ሞት ለምን የሰማዕት ሆነ? “አልለቅም” ያለው የፓርቲው (ኢህአዴግ) ስህተት መሆኑ በግልጽ እየታወቀ እስካሁን ድረስ በተለይ የህወሃት ፖሊት ቢሮ አባላት መሪያቸውን “አንድደው በመግደል” ለምንድነው ያልተከሰሱት?
ውሸታሙን መለስ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከተገላገለው ሁለት ዓመት ሆኗል። የውሸቱ መጠን ቀንሷል ለማለት ባይቻልም ሕዝብ ግን በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ያሉትን የተቀናቃኝ ፖለቲካ ፓርቲዎችም ሆነ ህወሃት/ኢህአዴግ የሚያቅሙትን ውሸት እየሰማ ይታዘባል፤ ታሪክም ትዝብቱን ይመዘግባል።
ታዲያ ላለፉት 23ዓመታት “የኤሌክትሪክ ኃይል” በነጻነት በሌላት አገር ራሱን ሻማ አድርጎ ሲያበራ በግፍ የኖረ ሕዝብ ለምን በግድ “ሻማ አብራ” ማለት ያስፈልገዋል? ግፍን የሚያይ አለ! ያንን ግፍ ቆጥሮ ደግሞ ፍዳ የሚያስቆጥር፤ በሰፈሩት መስፈሪያ የሚሰፍር ከሁሉ የበላይ፤ ልዕለኃያል አለ። ነዶ የማያልቀው ሕዝብ እየደረሰበት ያለውን ግፍ ይመለከታል። “አንድ ቀን ግፍ ወደተነሣበት ይመለሳል”።
source www.goolgule.com

Thursday, August 21, 2014

የግንቦት 7 ሕዝባዊ ስብሰባዎች በዓለም ሃያ ስድስት ታላላቅ ከተሞች

ግንቦት 7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ በመላው ዓለም ላይ ከሚገኙ አባላት፣ ደጋፊዎቹና በአጠቃላይ ከኢትዮጵያውያን  ጋር በወቅታዊ ሁኔታዎች ላይ ለመመካከር ዝግጅቱን አጠናቋል።
በዚህም መሠረት ከዚህ በታች በተዘረዘሩት 26 የዓለም ታላላቅ ከተሞች ሕዝባዊ ስብሰባዎችን ተጠርቷል።
  1. በላስቤጋስ                   ዩ ኤስ አሜሪካ              ረቡስ ኦገስት 27 ቀን
  2. በሂውስተውን               ዩ ኤስ አሜሪካ              ቅዳሜ ኦገስት 30 ቀን
  3. በአትላንታ                   ዩ ኤስ አሜሪካ              እሁድ ኦገስት 31 ቀን
  4. በዋሺንግተን ዲሲ                     ዩ ኤስ አሜሪካ              እሁድ ኦገስት 31 ቀን
  5. በቦስተን                    ዩ ኤስ አሜሪካ              እሁድ ኦገስት 31 ቀን
  6. በሎስ አንጀለስ              ዩ ኤስ አሜሪካ              ቅዳሜ  ሴፕተምበር 6 ቀን
  7. በሳንቲያጎ                   ዩ ኤስ አሜሪካ              እሁድ ሴፕተምበር 7 ቀን
  8. በቶሮንቶ                    ካናዳ                        እሁድ ኦገስት 31 ቀን
  9. በካልጋሪ                    ካናዳ                        ሴፕቴምበር 1 ቀን
  10. በደርባን                     ደቡብ አፍሪቃ               እሁድ ኦገስት 31 ቀን
  11. በጆሃንስበርግ                ደቡብ አፍሪቃ               እሁድ ኦገስት 31 ቀን
  12. ቬሪኒንፍ                    ደቡብ አፍሪቃ               እሁድ ኦገስት  31 ቀን
  13. ሩስተምበርግ                ደቡብ አፍሪቃ               እሁድ ኦገስት 31 ቀን
  14. ፍራክፈርት                  ጀርመን                     ቅዳሜ ኦገስት 30 ቀን
  15. ሙኒክ                       ጀርመን                     እሁድ ኦገስት 31 ቀን
  16. ሄልሲንኪ                   ፊንላንድ                    ቅዳሜ ኦገስት 30 ቀን
  17. አምስተርዳም                ኒዘርላንድስ                   ቅዳሜ ሴፕተምበር 13 ቀን
  18. ኦስሎ                        ኖርዌይ                      እሁድ ኦገስት 31 ቀን
  19. ለንደን                       እንግሊዝ                   ቅዳሜ ሴፕተምበር 6 ቀን
  20. ስቶክሆልም                 ስዊድን                      ቅዳሜ ሴፕተምበር 6 ቀን
  21. ፐርዝ                        አውስትራሊያ               እሁድ ኦገስት 31 ቀን
  22. ሜልቦርን                             አውስትራሊያ               እሁድ ሴፕቴምበር 7 ቀን
  23. ቴላቪቭ                     እስራኤል                    ሐሙስ ሴፕቴምበር 11 ቀን
  24. ብራሰልስ                             ቤልጂየም                   እሁድ ሴፕቴምበር 14 ቀን
  25. ኦክላን                      ኒዩ ዚላንድ                 እሁድ ኦገስት 31 ቀን
  26. ሲኡል                      ደቡብ ኮርያ                 እሁድ ኦገስት 31 ቀን
በእነዚህ ስብሰባዎች ሁሉ የንቅናቄዓችን ዋና ፀሐፊ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ሥራዎች ይወሳሉ። ወያኔን ማስወገድ በሚቻልበት ስልቶች ላይ ውይይት ይደረጋል። እስከዛሬ ድረስ ንቅናቄዓችንን ለመቀላቀል የተቸገራችሁ ወገኖች ይህንን አጋጣሚ እንድትጠቀሙበት ጥሪ እናደርጋለን።  በማናቸውም ምክንያት አባል ሳይሆን ደጋፊ መሆን ለምትፈልጉ ወገኖቻችንን የደጋፊዎች ምዝገባ ሥርዓት አዘጋጅተናል፤ እድሉን ተጠቀሙበት።
ኑ! ኢትዮጵያ አገራችንን፣ ኢትዮጵያዊ ወገናችንን እና ራሳችን ነፃ ለማውጣት እና በሀገራችን ፍትህ እንዲሰፍን ለማድረግ የሚደረገውን ትግል ይቀላቀሉ። ከዘወትር የህሊና ወቀሳ ይገላገሉ። ለዚህ ትግል ሁሉም የሚያበረክተው ነገር አለ። ስለሆነም በአቅራቢያዎ ወደሚደረገው የግንቦት 7 ስብሰባ ይምጡ፤ ጥያቄዎች ካልዎት ይጠይቁ።
አሁን ወሳኝ የትግል ምዕራፍ ላይ እንገኛለን። ትግላችን ሶስት የትግል ስልቶችን ያስተባበረ ነው – ሕዝባዊ ተቃውሞ፣ ሕዝባዊ እምቢተኝነት እና ሕዝባዊ አመጽ። ትግላችን በአገር ውስጥም ከአገር ውጭም ነው።
በውጭ አገራት የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ከድጋፍ ሰጪነት ወደ ተግባራዊ ተሳትፎ የተሸጋገሩበት ወቅት ነው። ይህ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባዋል። የወያኔ ድርጅቶችና የወያኔ ሹማምንት በየትኛው አገር ተዝናንተው እንዲኖሩና እንዲነግዱ አንፈቅድላቸውም። በእነዚህ ስብሰባዎች ስለዚህ ጉዳይ ይመከራል።
ኢትዮጵያዊያን ወጣቶች ለኢትዮጵያ ክብርና ነፃነት ሕይወታቸውን ለመሰዋት ተነስተዋል። በእነዚህ ስብሰባዎች የአርበኛ ወጣቶቻችንን ጥረት እንዘክራለን። ሺዎች እንዲቀላቀሏቸው ጥሪ እናደርጋለን። በሁሉም ስብሰባዎች በአገር ውስጥም በውጭ አገርም የሚገኝ ኢትዮጵያዊ ወጣት ትግሉን እንዲቀላቀል ጥሪ ይደረግለታል።
በሁሉም ስብሰባዎች ለኢትዮጵያ የመከላከያ ሠራዊት አባላት ጥሪ  ይደረጋል። የሠራዊቱ መሪዎች የፋሽስት ወያኔ ባለሟሎች ቢሆኑም ሠራዊቱ ግን ከኢትዮጵያ አብራክ የወጣ ኢትዮጵያዊ ነው። ሠራዊቱ የወያኔ መጠቀሚያ ከመሆን የነፃነት ታጋዮችን እንዲቀላቀል፤ ያ ካልተቻለም ለወያኔ ሥልጣን እንዳይሞት፤ ወገኑን እንዳይገል ጥሪ ይደረግለታል።
መጥተው የእነዚህ ታሪካዊ ስብሰባዎች አካል ይሁኑ።
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!!
source www.ginbot7.org

Saturday, August 16, 2014

በሰማያዊ ፓርቲ የአርባ ምንጭ አስተባባሪዎች የተጀመረው እስር ተጠናቅሮ ቀጥሏል

ሰማያዊ ፓርቲ እንደዘገበው፦
blue party
ከአሁን ቀደም አራት የሰማያዊ ፓርቲ የአርባ ምንጭ አስተባባሪዎች በሽብርተኝነት ስም መታሰራቸው ይታወቃል፡፡ እነዚህን እስረኞች ያሉበትን ሁኔታና የዞኑን አደረጃጀት ለመጎብኘት ከአዲስ አበባ (ከማዕከል) የድርጅት ጉዳይ ኃላፊው አቶ ብርሃኑ ተክለያሬድና የድርጅት ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ አባል የሆነው ዮናስ ከድር ለጉብኝት በሄዱበት ወቅት ሲያስተባብሩ የነበሩት አባላት ከማዕከል የሄዱት የፓርቲው አመራሮች ሲመለሱ ለእስር መዳረጋቸውን ከአካባቢው የደረሰን መረጃ ይጠቁማል፡፡
በመሆኑም አቶ ከሳሁን አየለ የተባለው የሰማያዊ ፓርቲ አርባምንጭ አስተባባሪ ከአዲስ አበባ የመጡትን የፓርቲው አመራሮች ጋር በመሆን የዞኑን አደረጃጀትና በእስር ላይ ያሉትን የፓርቲው አስተባባሪዎች አስጎብኝቷል በሚል መታሰራቸው ታውቋል፡፡ በተመሳሳይ ሻምበል ካሳ የታሰሩትን ጠይቀሃል በሚል ለእስር መዳረጋቸውንና ነፃነት የተባለው የፓርቲው አስተባባሪ ከሰማያዊ ፓርቲ ጋር እንዳይሰራና በታሰሩት ላይ እንዲመሰክር በማስፈራሪያ መለቀቁ ታውቋል፡፡
በዞኑ የሚገኙ የሰማያዊ ፓርቲ አባላትና ደጋፊዎች እስራትና መከባ እየደረሰባቸው ሲሆን በአሁኑ ወቅትም ሉሉ መሰለ፣ በፈቃዱ አበበ፣ ካሳሁን አየለ፣ ሻምበል ካሰና ኢ/ር ጌታሁን የተባሉት የፓርቲው አስተባባሪዎችና አባላት በእስር ላይ እንደሚገኙ ለመረዳት ተችሏል።
ምንጭ ዘ-ሐበሻ