Thursday, September 11, 2014

2007 ወሳኝ የትግል ዓመት!!!

September 11,2014
ሁለት ሺህ ስድስት ዓመተ ምህረት ለኛ ለኢትዮጵያዊያን በአብዛኛው በመጥፎ የሚታወስ ዓመት ነው። 2006፣ በመካከለኛው ምስራቅም ሆነ በአፍሪቃ በስደት ላይ የሚገኙ ወገኖቻችን ላይ የሚደርሰው ስቃይ ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰበት ዓመት ነበር። 2006፣ ቀደም ባሉ ዓመታት አገራቸዉን ለቅቀዉ የተሰደዱ ሳይደላቸው በርካታ አዳዲስ ስደኞች ከአገር ወጥተው በበረሃዎችን ቀልጠው፤ በባህር ሰጥመው ያለቁበት አሳዛኝ ዓመት ነው። 2006፣ ጥንቃቄ በተሞላበትና በተቆጠበ መንገድም ቢሆን የተቃውሞ ድምጽ ያሰሙ ወገኖቻችን ወደ እስር ቤቶች የተጋዙበት ዓመት ነው። 2006፣ በአምቦ፣ በለቀምት፣ በጅማ በሀረር በርካታ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች የተገደሉበት፤ በአስር ሺዎች የሚገመቱት ደግሞ የታሰሩበት ዓመት ነው። 2006፣ በአፋር፣ በኦሮሚያ፣ በደቡብ፣ በቤንሻንጉል፣ በጋምቤላ፣ በአዲስ አበባና አካባቢው በ100 ሺዎች የሚገመት ኢትዮጵያዊ የተፈናቀለበት ዓመት ነው። 2006 ቁጥራችው ቀላል ያልሆኑ የነፃነት ታጋዮች ከጎረቤት አገራት ታፍነው ወደ እስር ቤቶች የተጋዙበት ዓመት ነው። 2006 የንቅናቄዓችን ዋና ፀሐፊ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ በጉዞ ላይ እያለ በትራንዚት አውሮፕላን ለመቀየር ባረፈበት በየመን ዋና ከተማ ሰንዓ በየመን መንግሥት ወንበዴዎች ታፍኖ ለሸሪካቸው ህወሓት በህገወጥ መንገድ አስተላልፈው ለስቃይ እንዲዳረግ የተደረገበት ዓመት ነው። በእነዚህ ሁሉ ምክንያቶች ነው 2006 “ጥቁር ዓመት” የሚል ስያሜ ያገኘው።
ጭንቅላት የሚባል ነገር ያልፈጠረባቸው ድኩማን ሰላዮችና ፈንጋዮች የመጨረሻውን የመንግሥት ሥልጣን የያዙበትና ውሳኔያቸው “እሰረው፣ ክሰሰው፣ ግረፈው፣ ግደለው …” ብቻ የሆነበት ዓመት መሆኑ የ2006 ልዩ መታወቂያው ሆኖ ይቆይ ይሆናል። ይሁን እንጂ በ2006 ጨለማ ውስጥ የታዩ የብርሃን ጨረሮችም እንደነበሩና እንዳሉም መርሳት አይገባም።
በሁለት ሺህ ስድስት ዓመተ ምህረት የኢትዮጵያ ሕዝብ ከመቸውም በላይ በህወሓት አገዛዝ አምርሯል፤ በሁለገብ ትግል የህወሓትን አገዛዝ ለመፋለም የቆረጡ ወገኖች ትብብር ተጠናክሯል። በ2006፣ ኢትዮጵያ ዉስጥም ከኢትዮጵያም ውጭም የንቅናቄዓችን የግንቦት 7 ድርጅታዊ መዋቅር ተጠናክሯል። በ2006፣ ከህወሓት አገዛዝ ጋር ያለው መፋጠጥ ከሯል። እነዚህ ሁኔታዎች 2007 አገራችን በለውጥ ማዕበል የምትናጥበት ዓመት ሊሆን እንደሚችል ያመለክታሉ።
በአዲሱ ሁለት ሺህ ሰባት ዓመተ ምህረት፣ የግንቦት 7 አባላትና ደጋፊዎች ትልቁ ሥራ ድርጅታዊ አቅምን ማጎልበት ነው። በተለይ ወጣቶች በአምባገነን ሥርዓቶች ውስጥ ሕዝባዊ የትግል ድርጅቶችን እንዴት መመሥረት እንደሚቻል ማጥናት እና መፈተሽ ይኖርባቸዋል። ትናንሽ የግንቦት 7 ድርጅታዊ ቋጠሮዎች በመላው አገሪቱ መሠራጨት ይኖርባቸዋል። ወጣቶች ትናንሽ ኢ-መደበኛ ስብስቦችን ቶሎ መፍጠር እና አደጋ ሲያጋጥም ቶሎ ማፍረስ መልመድ ይኖርባቸዋል። ይህንን ክህሎት ደግሞ በቀጥታ ከሌሎች አገራት ከመዋስ ሀገር በቀል ቢሆን ይመረጣል።
በሁለት ሺህ ሰባት ዓመተ ምህረት፣ የጽዋ ማኅበሮች፣ መድረሳዎችና ጀማዎች፣ የስፓርት ቡድኖችና ደጋፊዎች፣ የመንደር ደቦዎችና የቡና ተርቲቦች፣ ስም ያላቸውም፣ ስም የሌላቸውም ስብስቦች የግንቦት 7 አባላት መገናኛዎች ይሆናሉ። በ2007 የግንቦት 7 አባል መሆን የምርጥ ዜግነት ምልክት መሆኑ በስፋት ተቀባይነት የሚያገኝበት ዓመት ይሆናል ብለን ተስፋ እናደርጋለን። በ2007 በህወሓት ካድሬዎች “ሽብርተኛ” መባል የሚያስደስትና እንደ ሽልማት ተደርጎ የሚወሰድበት ዓመት ይሆናል ብለንም ተስፋ እናደርጋለን። በ2007 እስር ማስፈራሪያ መሆኑ ያከትማል። በ2007 የኢትዮጵያ ወጣቶች በአርበኝነታቸው ይታወቃሉ። በ 2007 እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ የህወሓት ሹማንምትን ዘረፋ የሚያጋልጥበት ዓመት ይሆናል። 2007 ዳኞች “እንቢ፣ በሀሰት አንፈርድም”፤ የመንግሥት ጋዜጠኖች “እውነቱን ደብቀን አንዋሽም”፤ ፓሊሶች “ወገናችንን አንደበድብም፣ አናስርም፣ አንገርፍም”፤ ወታደሮች ደግሞ “በወገናችን ላይ አንተኩስም” የሚሉበት ዓመት ይሆናል ብለን ተስፋ እናደርጋለን።
በዚህም ምክንያት 2007ን የምንቀበለው በታላቅ ተስፋና ዝግጅት ነው። በ 2007 ነፃነትና አምባገነንነት፤ ዘረኛነትና አንድነት፤ እውነትና ውሸት፤ አድርባይነትና አርበኝነት፤ ዝርፊያና ንጽህና፤ ድህነትና ብልጽግና የሚፋጠጡበት ዓመት ይሆናል ብለን እንጠብቃለን። በአጭሩ 2007 የወሳኝ ትግል ዓመት ይሆናል።
ሁለት ሺህ ሰባት ዓመተ ምህረት፣ የኢትዮጵያ መፃዒ እድል የሚወሰንበት ዓመት በመሆኑ ሁላችንም በተነሳሳ የአርበኝነት መንፈስ እንድንቀበለው ግንቦት 7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ጥሪ ያደርጋል።
መልካም አዲስ ዓመት!
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ !
source ginbot7.org

ሚሊየነሩ ጄ/ል (ከኢየሩሳሌም አርአያ)

(በፎቶው ጄ/ል ዮሃንስ ገ/መስቀል)
September 11,2014
የሕወሐት ታጋይ ጄ/ል ዮሃንስ ገ/መስቀል ቦሌ ቴሌ መድሃኒያለም ባለ6 ፎቅ ህንፃ እንዳስገነቡ የቅርብ ምንጮች አጋለጡ።
ከ95ሚሊዮን ብር በላይ በሚደርስ ወጪ እንደተገነባ የተነገረለት ይኸው ባለ6 ፎቅ ዘመናዊ ህንፃ ለተለያዩ የግልና የመንግስት ባንኮች፣ ኢንሹራንስ ድርጅቶች፣ ንግድ ቤቶችና የተለያዩ ድርጅት ቢሮዎች እንደተከራየ የጠቆሙት ምንጮቹ በወር ከ2.1 ሚሊዮን ብር የሚገመት ኪራይ ጄኔራሉ እንደሚሰበስቡ አስታውቀዋል።
ሌ/ጄ ዮሃንስ በግላቸው ባለ6 ፎቅ ዘመናዊ ህንፃ በከፍተኛ ወጪ በማስገንባትና ከፍተኛ የኪራይ ሂሳብ በየወሩ በመሰብሰብ ከሌሎቹ በቢዝነስ ከተሰማሩ የሕወሐት/ኢህአዴግ ጄኔራል መኮንኖች የተለየ እንደሚያደርጋቸው ምንጮቹ አመልክተዋል። በአገር መከላከያ ሚኒስቴር የመረጃ ዋና መምሪያ ሃላፊ ሆነው ለረጅም አመታት ሲሰሩ የቆዩት የህወሐቱ ጄኔራል ዮሃንስ ገ/መስቀል ከ1995ዓ.ም ጀምሮ ከጄ/ል ሳሞራ የኑስ ጋር የከረረ ቅራኔ ውስጥ ገብተው እንደቆዩና በሁለቱ የህወሀት ጄኔራሎች መካከል የተፈጠረው ቅራኔ እየተባባሰ ሄዶ ጄ/ል ዮሃንስ ከሃላፊነት እንዲነሱ መደረጉን ያስታወሱት ምንጮቹ የሁለቱ ቅራኔ ሙስናን መሰረት ያደረገ እንደነበረ አስረድተዋል። (በወቅቱ ስለግጭታቸውና መለስ ዜናዊ ዘንድ ቀርበው ስለተነጋገሩት በኢትኦጵ ጋዜጣ መረጃው ይፋ ተደርጐዋል)  ጄ/ል ዮሃንስ ከመከላከያ ሃላፊነታቸው እንዲነሱ የተደረጉት በጄ/ል ሳሞራ መሆኑን ያስታወሱት ምንጮቹ በወቅቱ “ጡረታ” በሚል እንደተነሱና ሲነሱም በሜ/ጄኔራል ማእረግ እንደነበሩ አስታውቀዋል።
በሙስና ባገኙት በመቶ ሚሊዮን የሚገመት ገንዘብ ሕንፃ ወደማስገንባት የግል ቢዝነስ የተሰማሩት ጄ/ል ዮሃንስ ከአራት አመት በኋላ በመከላከያ የሌተና ጄኔራልነት ማእረግ ባሳለፍነው ሰኔ ወር ተሰጥቷቸው በደቡብ ሱዳን የሚሰማራውን የተመድ ሰላም አስከባሪ ሰራዊት በጦር አዛዥነት እንዲመሩ መመደባቸው አስገራሚ ነው ያሉት ምንጮቹ ምክንያቱም ጡረታ ተብለው የተሰናበቱት ዮሃንስ የሌተና ጄኔራል ማእረግ እድገት ተሰጥቷቸው መመለሳቸው በመከላከያ ታሪክ የመጀመሪያው ሊያደርጋቸው ስለሚችል ግርምት ሊፈጥር ችሏል ብለዋል። ዮሃንስ የአገር መከላከያ ሚ/ር የሌ/ጄኔራል ማእረግ እንዲሰጣቸውና በተመድ እንዲመደቡ የተደረገው በአሜሪካ ትእዛዝ መሆኑን ምንጮቹ አመልክተዋል። በቦሌ ለንደን ካፌ ፊት ለፊት ዘመናዊ መኖሪያ ካስገነቡት ጄኔራሎች አንዱ ናቸው።
ምንጭ የኢትዮጵያ ሜዲያ መድረክ


Free Andargache​w – New website launched



Friends and families of  Andargachew Tsege have created a new website to help the campaign to free Andargachew Tsege from Ethiopian prison.
Here is the link to the Website dedicated to Andargachew. :  http://www.freeandargachew.com
source ethioforum.org

Sunday, September 7, 2014

የለውጡ አካል መሆኛው ግዜው አሁን ነው

september 7,2014
እኔም አንዳርጋቸው ነኝ የሚል ድምፅ ከአጥናፍ እስከ አጥናፍ እያሰተጋባ ነው። ይሄን ድምፅ የሚያቆመው አንዳችም ምድራዊ ኃይል አልተገኘም። ኢትዮጵያዊ ባለበት ሥፍራ ሁሉ ይሄ ድምፅ ከፍ ብሎ እየተሰማ ነው። ይህንንም ተከትሎ “ላንቺ ነው ኢትዮጵያ፤ ላንቺ ነው ኢትዮጵያ” የሚለው መዝሙር በኢትዮጵያ ተራሮች እናት ላይ እየተዘመረ ነው። ፍትህ ተዋርዳለች፤እኩልነት ጠፍቷል፤ ነፃነት የለም ያሉ ምርጥ ኢትዮጵያዊያን ሳያቅማሙ አያቶቻቸው በተመላለሱበት ተራሮች ላይ ተሠማርተዋል። ሞትንም ንቀው ጋሻ አንስተዋል፤ ሰይፋቸውንም መዘዋል። ለፍትህ፤ ለዕኩልነት እና ለነፃነት የተመዘዘው ሰይፍ ከእንግዲህ ወደ ሰገባው እንደማይመለስ ህወሃቶች እንዲያውቁት እንፈልጋለን።
በኢትዮጵያችን ፍትህ ከጠፋ ብዙ ዘመን ሁኖታል። ከሁሉም ዘመን የህወሃቶች ዘመን ግን የተለየ ነው። ህወሃቶች ህግን ዜጎችን የማጥቂያ መሣሪያ አድርገው መጠቀማቸው ከሌሎች እንዲለዩ ያደርጋቸዋል። እነዚህ ቡድኖች ሥፍር ቁጥር የሌላቸው ቂም መወጣጪያ ህጎችን አውጥተዋል። እንዲህ በማድርጋቸውም ሠላም እናገኛለን ብለው ያስባሉ። የህወሃቶች አስተሳሰብ ደካማና እርባና ቢስ መሆኑን ከሚያሳዩ ተግባሮቻቸው መካከል አንዱ ይሄው በፍትህ ሳይሆን በህግ ብዛት ሠላም እናገኛለን ብለው ተስፋ ማድረጋቸው ነው። የህግ ብዛት ሠላምን አያስገኝም፤ ፍትህንም ማስፈን አይችልም። እንዲያውም ህግ በበዛ ቁጥር ፍትህ እየጎደለች እንደምትሄድ የህወሃቶች ድርጊት ደህና ምስክር ነው። እነርሱ ዜጎችን ለመበቀያ ብለው የሚያወጧቸው ጥቃቅን ህጎች እነርሱ “ህገ መንግስት” ብለው የሚጠሩትን የሚንዱ እና ፍትህን ዋጋ የሚያሳጡ ሁነው እያየናቸው ነው። የፀረ ሽብር ህጉ በህገ መንግስቱ የተቀመጠውን የዜጎችን የመናገር የመደራጀትና በሰላማዊ መንገድ የመንግስትን እኩይ ተግባራት የመቃወምን መብት የገፈፈ ነው። የፀረ ሙስና ህጉም ቢሆን እንዲሁ ነው። በፀረ ሙስና ህጉ የሚጠየቁ በህወሃት የተጠሉ ብቻ ስለመሆናቸው በሙስና የተጨማለቁት የህወሃት ሹማምንት ህያው ምስክሮች ናቸው። በህወሃቶች ህግ ሁሉም ዜጎች እኩል አይደሉም። ህወሃቶች ከሌሎች ይበልጣሉ። የህወሃቶች ምኞት እነርሱ ከህግ በላይ፤ ሌላው ህዝብ ከህግ በታች ሁነው ህወሃትን ተሸክመው እንዲኖሩ ነው። እንዲህ ዓይነቱን ኢ-ፍትሃዊነት መታገል ግዜው የሚጠይቀው ታሪካዊ ግዴታ ነው። መሪያችን አንዳርጋቸው ፅጌ የተነሳውም ህወሃቶች መሣቂያ መሳለቂያ ያደረጓትን ፍትህ ወደ ሚገባት ክብር ለመመለስ ነው። በአገራችን የህግ የበላይነት ሠፍኖ ጥቂቱ ብዙሃኑን ሳይጫን፤ ማንም ማንንም ሳይሸከም ሁሉም በህግ እና በፍትህ እኩል ሁኖ የሚኖሩባት ሠላም የበዛላት ሥፍራ እንድትሆን የመሪያችን የአንዳርጋቸው ምኞት ነው። ይሄን ምኞት ሚሊየኖች አንግበው ተነስተዋል።
ህወሃቶች አገራችንን አደጋ ላይ ከጣሉባቸው አንኳር ድርጊቶቻቸው መካከል አንዱ በዜጎች መካከል እየፈጠሩ ያሉት ግልፅ ልዩነት ነው። ህወሃቶች ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር እኩል ነን የሚል እምነት የላቸውም። የህወሃቶች ዕምነት እነርሱ ከሌላው ኢትዮጵያዊ ከፍ እንደሚሉና በዚያች አገር ውስጥ የተለየ መብት እንዳላቸው ነው። ለመገድልም፤ ለመዝረፍም፤ዜጎችን ለማሳቃየት እና ከአገር ለማባረርም መብቱ የእኛ ነው የሚል ጅላጅል እምነት አላቸው። ይህ የሞኝ እምነታቸው በዜጎች መካከል ቂመ በቀል ሊያተርፍ የሚችል አድሎዎ እንዲፈጥሩ አድርጓቸዋል። አድሎአቸውንም ይበልጥ የከፋ የሚያደርገው ህወሃቶች ሁሉን አድራጊ እኛ ነን ብለው ሲያበቁ የህወሃት የበላይነት የለም ብላችሁ እምኑ ብለው ዜጎችን መጫናቸው ነው። ይህ ድርጊታቸው ብዙ ዜጎችን አስቆጥቷል። ህወሃቶች ግን የዜጎችን ቁጣ የሚያይ ዓይን፤ የሚያስተውል ሂሊና ርቋቸዋል። በኢትዮጵያችን በህወሃቶች አማካኝነት እየተፈጠረ ያለው ግልፅ አድልዖ ለአገራችን ህልውና ከፍተኛ አደጋ ነው። በህዝብ መካከል አድልዖ መፈፀም እና ቂምና በቀልን መትከል የህወሃቶች የመኖሪያ ድንኳናቸው ሁኗል። መከፋፈልና አድልዖ ባለበት አገር ውስጥ ሠላም ይኖራል ማለት አይቻልም። አድልዎ የታላላቅ ግጭቶችና ለውጦች ጥሩ ምክንያት መሆኑን መርሳት አይገባንም።መሪያችን አንዳርጋቸውም ሆነ ግንቦት ሰባት ንቅናቄ የተነሳው እንዲህ በዜጎች መካከል የሚፈፀመውን አድልዖ ለማስቆምና ዜጎች በገዛ አገራቸው በእኩልነት የሚኖሩበትን ሁኔታ ለመፍጠር ነው። ይህ የእኩልነት ጥያቄ የግንቦት ሰባት ንቅናቄ ብቻ ሳይሆን የሁሉም ዜጎች ጥያቄ ሁኖ ከኢትዮጵያ እስከ ውጪ አገራት ድረስ እያሰተጋባ ነው።
ሌላው ህወሃቶች አገሪቷን እያዋረዱ ካሉበት ነገሮች መካከል አንዱ የነፃነት ጥያቄ ነው። እኛ ከመጣን በኋላ በኢትዮጵያ ነፃነት ሰፈነ እያሉ ያላዝናሉ። ህወሃቶች ከነፃነት ጋር ተያይዞ ሊመጣ የሚችለውን ኃላፊነት ለመረዳትና ለመሸከም ከፍተኛ የሆነ የአስተሳሰብ ድክመት አለባቸው። ከነፃነት ጋር የሚመጣውን ኃላፊነት ለመሸከም ብቻ ሳይሆን የነፃነትንም ትርጉም ለመረዳት ከፍተኛ የሆነ የእውቀት ማነስ ችግር ያለባቸው መሆኑም ይታወቃል። ራሳቸውን ከታሰሩበት የድንቁርና ሰንሰለት ማስፈታት ሳይችሉ ከሰሞኑ የከፍተኛ ተቋም ተማሪዎችን ሰብስብው የእኛን አብዮታዊ ዲሞክራሲ ካልስተማርናችሁ ትምህርታችሁን አትቀጥሉም ሲሉ ማሰብ ማቆማቸውን ቁልጭ አድርጎ የሚያሳየን አንድ እውነት ሁኖ አግኝተነዋል። ማሰብ የሚችሉ ቢሆኑማ ኑሮ ነፃነት ማለት ‘የእናንተን አብዮታዊ ዲሞክራሲ መስማት አልፈልግም ማለትን’ እንደሚጨምር ያውቁ ነበር። ነፃነትን የማያውቁት ነፃ አውጪዎች ነን ባዮቹ ህወሃቶች ግን ተማሪው መስማት የማይፈልገውን አብዮታዊ ዲሞክራሲ አስገድደው እየጋቱት ይገኛሉ። ለሚቀጥለውም አርባና ሃምሳ ዓመት ስልጣኑን ለማንም አሳልፈን የምንሰጥ አይደለንም ሲሉ በድፍረት ተናግረዋል። የዚህ ሁሉ ድፍረት ምንጭ ህወሃቶችን የተፀናወታቸው እኔ ብቻ ከሚል ከንቱ አስተሳሰብ የመነጨው ስግብግብነታቸው መሆኑን መገነዘብ ያስፈልጋል።
እንግዲህ ፍትህ መቀለጃ ሁናለች፤ እኩልነት ተጓድሏል፤ ነፃነት ጠፍቷል የሚሉ ዜጎች ከሁሉም አቅጣጫዎች ድምፃቸውን እያሰሙ ነው። የህዝቡ ብሶትም ፅዋውን ሞልቶ እየፈሰሰ ነው፤ ቁጭቱም ከመቸውም ግዜ በላይ ግሏል። ከሰሞኑ በሃያ ስድስት ታላላቅ ከተሞች የተደረጉት ውይይቶችም ያሳዩን አንድ እውነት ህዝቡ ይበልጥ መቆጣቱን ነው። ቁጣውም የተገለፀበት መንገድም ሌላው አስደማሚ ጉዳይ ነው።“እኛም አንዳርጋቸው ነን” ሲሉ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው አሰምተዋል። ከእንግዲህ ፍርሃት ሆይ መወጊያህ ወዴት አለ የሚሉ ኢትዮጵያዊያን ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ላንቺ ነው ኢትዮጵያ፤ ላንቺ ነው ኢትዮጵያ እያሉ ዘምረዋል። ይሄ ለፍትህ፤ ለእኩልነትና ለነፃነት ለሚታገሉ ታጋዮች ተስፋ ሰጪ ምልክት ነው።
ህወሃቶች በሠላማዊ መንገድ ለሚደረገው ትግል መንገዱን ሲያደናቅፉ እሰከ ዛሬ ዘልቀዋል። አሁን ጭራሹን ገና ሃምሳ የመከራ ዘመን እየተመኙልን ነው። ይሄ ምኞታቸው ቅዥት ሁኖ እንደሚቀር እኛ ልናስታውሳቸው እንፈልጋለን። በዚያች አገር ለውጥ መምጣት አለበት። ለውጡ በዛፍ ላይ የተንጠለጠለ የጎመራ ፓፓያ አይደለም በራሱ ወደ ምድር የሚወርድ፤እኛ ራሳችን ልናወርደው የሚገባን እንጂ። ተፈላጊውን ለውጥ ለማምጣት እያንዳንዱ ዜጋ በቻለው መሣሪያና ባለው አቅም ሁሉ ለልውጡ ሳያቅማማ መታገል ይኖርበታል። ህወሃቶች ነፃነታችንን አይሰጡንም፤ ፍትህም ከእነርሱ እጅ የምትገኝ አይደለችም፤ እኩልነትንም የሚያውቁ አይደሉም እነዚህ ወርቃማ እሴቶች በትግል የሚገኙ ናቸው። እነዚህን ክቡር ስጦታዎች አስነጥቆ ዝም ያለ ወደ መታረጃው ሥፍራ የሚነዳ ከብትን ይመስላል። ብዙ ኢትዮጵያዊያን እንዲህ መሆንን የሚምርጡ አይደሉም። በየከተሞቹ በተደረገው ውይይት ከተገነዘብናቸው እውነቶች መካከል አንዱ ዜጎች ለፍትህ፤ለእኩልነት እና ለነፃነት አስፈላጊውን መሥዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ መሆናቸውን ነው።
በህወሃት ዘመነ መንግስት የመከራ እንባችሁን በመዳፋችሁ የምታፍሱ፤ ህወሃት በአገሪቷ ላይ እያደረሰ ያለው የጥፋት ድርጊት የሚያነገበግባችሁ እና ምን እናድርግ መሪ አጣን የምትሉ ስሙን! መሪ ካጣችሁ እንዲህ አድርጉ “ራሳችሁ ተነሱና መሪ ሁኑ!”። ከምታምኗቸው ጥቂት ወዳጆቻችሁ ጋር ሁናችሁ ተደራጁ፤ አንዳችሁ አንዳችሁን አድምጡ፤ ጥሩ ተመሪ መሆን ከቻላችሁ ጥሩ መሪ ወጥቷችኋል ማለት ነው። የአገራችን ፈርጀ ብዙ ችግር በጥቂት ዜጎች ብቻ የሚቀረፍ አይደለም።የሁሉንም ቁርጠኛ ዜጎች ትግል የሚጠይቅ ነውና በየመንደራችሁ ተደራጅታችሁ የጎበዝ አለቃ መርጣችሁ ዘረኞችን፤ ዘራፊዎችንና አድሎዋዊ ሥርዓት የዘረጉባችሁን ታገሏቸው። እንዲህ ካደረጋችሁ ከእኛ ጋር ለመገናኘት መንገዱ ቀላል ይሆናል።
የግንቦት ሰባት ንቅናቄ ጥያቄ አጭርና ግልፅ ነው። ፍትህ፤ ነፃነትና እኩልነት በኢትዮጵያችን ይሰፈን ነው። የህወሃትን ዘረኝነትና አምባገነንነት የሚፀየፍ ሁሉ የንቅናቄያችን ደጋፊ ነው። እነዚህን ነገሮች በኢትዮጵያ ለማስፈን በሚችለው ሁሉ ርምጃ መውሰድ የጀመረ የንቅናቄያችን አካል ነው። እኛም ከጎኑ አለን። እንዲህ በማድረግ የማይቀረውን ለውጥ አናመጣለን። ለውጡ ይመጣል አንድም የተፈጥሮ ህግ ስለሆነ፤ አንድም ደግሞ እኛ ሳናቅማማ የፈለግነውን ለውጥ ለማምጣት ስለተነሳን።
ህወሃቶች መስልጠን የማይችሉ፤ ከአዲስ አስተሳሰብ ጋር ራሳቸውን ማዋሃድ የማይሆንላቸው ፍፁም ግትሮች መሆናቸውን በተዳዳጋሚ አይተናል። ይሄን ግትርነታቸውን እንደ ጀግንነት ይቆጥሩታል። በአገራችን ደህና አባባል አለች እንዲህ የምትል “ሞኝ አሸነፈ ምን ብሎ? እምቢ ብሎ” ይባላል። ህወሃቶችን በዚህ አባባል መግለፅ ሞኝ ያስመስላቸዋል እነርሱ ግን ሞኞች አይደሉም ጨካኞች እንጂ። የጭካኔያቸው ምንጭ ደግሞ በራሳቸው የማይተማመኑ ደካሞች መሆናቸው ነው። እነርሱ ከዛሬ ሠላሳ ዓመት በፊት በመስታወት ውስጥ ያዩትን የራሳቸውን ምሥል ዛሬም መልሰው ያንኑ ምሥል እያዩት ነው። ከሠላሳ ዓመት በኋላም ሊቀየሩ አልቻሉም። ከዚያ ካረጀው ምሥላቸው ላይ ዓይናቸውን ነቅለው ግዜው እና ሁኔታው የፈጠረውን በአካባቢያቸው ያለውን አዲስ ምሥል ለማየት አቅቷቸውል። ስለዚህ ህወሃቶችን ማስወገድ ግድ ነውና ሁሉም በያለበት ለሚመጣው ለውጥ ራሱን ያዘጋጅ፤ የለውጡም አካል ይሁን እንላለን።
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ !
source www.ginbot7.org

Friday, September 5, 2014

አብርሃ ደስታን በተመለከተ፣ ከጠበቃ ተማም አባቡልጉ ጋር ያደረኩት ቃለ-ምልልስ

Saturday,september 6th,2014
በዛሬው ዕለት አብርሃ ደስታ ጊዮርጊስ በሚገኘው የአራዳ ፍርድ ቤት ቀርቦ የ28 ቀናት የጊዜ ቀጠሮ ተሰጥቶታል፡፡ አብርሃ ወደፍርድ ቤቱ ሁለት እጆቹ በካቴና እንደታሰሩና በአራት መሳሪያ በታጠቁ ፖሊሶች ታጅቦ ሲገባ በስፍራ የነበሩ ሰዎች ሞቅ ያለ ጭብጨባ አቅርበውለት ነበር፡፡ በፊቱ ላይ መረጋጋት እና ፈገግታ የሚነበብበት አብርሃ፣ በቻለው አቅም ሰዎችን ሰላምታ ለመስጠት ጥሯል፡፡ አብርሃ ወደችሎት ከገባ በኋላ፣ የታጠቁ ፖሊሶች ‹‹ለምን አጨበጨባችሁ? ረብሻ ፈልጋችሁ ነው፡፡›› በሚል በተለይ አንዱ ፖሊስ የያዘውን መሳሪያ አፈሙዝ ወደሰዎች በመወደር ‹‹ከግቢው ለቅቃችሁ ውጡ!›› ማለቱን ተከትሎ ሌሎች ፖሊሶችም ተመሳሳይ አቋም በመያዝ ታዳሚውን ለማስወጣት ጥረት አድርገው ነበር፡፡
በስፍራው የነበሩ የተለያዩ ሰዎች የፖሊሶችን አካሄድ በመቃወም ‹‹አንወጣም፣ ሕግ- አልጣስንም፡፡ አብርሃ ነጻ ሰው ነው ብለን ስለምናምን ለእሱ ያለንን አክብሮት እና አድናቆት ለመግለጽ እናጨበጭባለን›› በማለት ከፖሊሶች ጋር ክርክር ካደረጉ በኋላ በፖሊሶች በድጋሚ ‹‹ተፈትሻችሁ ግቡ›› በሚል አለመግባባቱ እልባት ለማግኘት ችሏል፡፡
አብርሃም፣ ከችሎት በፈገግታ ታጅቦ ሲወጣ ዝናብ እየዘነበ ነበር፡፡ ሆኖም በስፍራው ከነበሩ ታዳሚዎች ሞቅ ያለ ጭብጨባ እና ድጋፍ ተሰጥቶታል፡፡ እሱም በካቴና የታሰሩ እጆቹን ትንሽ ከፍ በማድረግ ‹‹አመሰግናለሁ›› ብሏል፡፡
እኔም የአብርሃ ደስታ ጠበቃ ለሆኑትን አቶ ተማም አባቡልጉን የተወሱን ጥያቄዎችን በማንሳት ተከታዩን ቃለ-ምልልስ አድርጌያለሁ፡፡
————————————————
ጥያቄ፡- የዛሬ የአብርሃ ደስታ የፍርድ ቤት ውሎ እንዴት ነበር?
ጠበቃ ተማም፡- የ28 ቀን የጊዜ ቀጠሮ ተሰጥቷል፡፡ ለመስከረም 22 ቀን 2007 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷል፡፡
ጥያቄ፡- ለምን ተሰጠ?
ጠበቃ ተማም፡- ፖሊስ ‹‹ተጨማሪ የምስክር ቃል እቀበላለሁ፤ ተጨማሪ የሰነድ ማስረጃ እሰባስባለሁ፤ ሰነድ አስተረጉማለሁ፡፡›› ብሏል፡፡ እነዚህ ነገሮች ባለፈውም ተብለዋል፤ በፊትም ተብለዋል፡፡ እኛ ግን ተቃውመናል፡፡
ጥያቄ፡- በምን ተቃወማችሁ?
ጠበቃ ተማም፡- በሁለት ነገር ተቃውመናል፡፡ ዛሬ የሚባሉ ነገሮች በሙሉ፣ ይሄ ልጅ ከመታሰሩ በፊት መጠናቀቅ ነበረባቸው፡፡ የጸረ-ሽብርተኝነት አዋጁ በአንቀጽ 19 ላይ ‹‹አንድ ሰው ሽብር ለመስራት በቂ ምክንያት / ጥርጣሬ ካለ ..›› ይላል፡፡ ‹ሽብርን ያቋቁማል› የተባለው ጉዳይ በተራ ወንጀልነት በወንጀለኛ መቅጫ ሕጉ ላይ አለ፡፡ ስለዚህ ይህ መሆን አለመሆኑን አጣርተው ነው አብርሃ ማሰር የነበረባቸው፡፡ ያን ለማድረግ ደግሞ የምስክር ቃለ ሰምተው፤ የሰነድ መስረጃ ሰብስበው ነው ምክንያታዊ ጥርጣሬ አደረባቸው የሚባለው፡፡ ይሄንን ምክንያት አድርገው፣ ለሁለት ለሶስት ጊዜ የጊዜ ቀጠሮ ማድረጋቸው በራሱ የአሰራር ሕገ-ወጥነትን ያሳያል፡፡ ሁለተኛ ደግሞ፣ የታሰረው ምንም ማስረጃ ሳይኖር ነው፡፡ ለዚህ ማሳያው፣ የተጠረጠሩትን ይዘው፣ መረጃዎች በብርበራ የተያዙ መሆኑ ነው፡፡ ይሄ ሕገ-ወጥ ነው፡፡
ጥያቄ፡- እርስዎ በዚህ ላይ ምን አሉ?
ጠበቃ ተማም፡- ይህ ሕገ-ወጥ አሰራር ነው ብዬ አመለከትኩኝ፡፡ ይሄ የሚያመለክተው፣ ምስክር የሚጠይቁት፣ ‹‹ከእነሱ ኤሌክትሮኒክስ መሳሪያ አገኘን›› የሚሏቸው ነገሮች ከእነሱ መጀመሪያ ምንም ነገር ሳያገኙ ነው ያሰሯቸው፡፡ ይሄ ራሱ ሕገ-ወጥ ነው፡፡ ‹‹የመራራ ዛፍ ፍሬ መርዛማ ነው›› ስለዚህ ‹‹ሕገ-ወጥ ሥነ-ሥርዓት በማድረግ የሚመጣ ፍሬ በራሱ ውጤቱ መርዛማ ነው›› አልኩኝ፡፡
ጥያቄ፡- ይሄንን እርስዎ ሲሉ ዳኞች ምን አሉ?
ጠበቃ ተማም፡- ዳኛው ማስጠንቀቂያ ነው የሰጡኝ፡፡ ይሄ የተለመደ የሕግ አባባል ነው፡፡ የሥነ- ሥርዓት ሕጎች መብት ማስጠበቂያ ናቸው፡፡ እነዚህን ጥሰህ የምታገኛቸው ነገሮች በሙሉ ሕገ-ወጥነታቸውን ለማስረዳት ነው የተጠቀምኩት፡፡ ለፍርድ ቤቱም አመልክቻለሁ፡፡ ለምን? አስተሳሰሩ ሕገ-ወጥ ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች በሽብር ተግባር ለመሰማራቸው በቂ ማስረጃ እና ጥርጣሬ ኖሮ አይደለም የታሰሩት፡፡ ያ ሁሉ የተደረገው ከታሰሩ በኋላ በቤታቸው በተደረገ ማስረጃ ነው፡፡ ይሄንን ‹‹ሕገ-ወጥነት ነው›› ስል አመለከትኩኝ፤ ለደንበኛዬም ‹‹ዋስትና ይፈቀድልኝ›› በማለት አመለከትኩኝ፡፡ ዳኛው ይሄንን ተውትና ወደእኔ ዞሩ፡፡ ማስጠንቀቂያም ሠጡኝ፡፡
ጥያቄ፡- ምን ብለው?
ጠበቃ ተማም፡- ‹‹ከዚህ በፊት በሌላ ችሎት ላይ ማስጠንቀቂያ ሰጥጬሃለሁ፤ በሄዱበት ይረብሻሉ›› አሉኝ፡፡ ያ ከዚህ ጋር ምን እንደሚያያይዘው አይታወቅም፡፡ አንደኛ፣ እኔ ማንንም ሰው ነክቼ አላውቅም፤ አልነካምም፡፡ ምክንያቱም፣ ከ14 ዓመታት በላይ በጥብቅና ሰርቻለሁ፡፡ እዚህ ፍርድ ቤት ካሉ ከብዙ ሰዎች በተሻለ ሥነ-ሥርዓት አውቃለሁ፡፡ ማንንም ሰው፣ ፖሊስንም ጨምሮ አልተናገርኩም፡፡ ከፍርድ ቤት ከወጣሁ በኋላ ፖሊሶች ይነዘንዙኝ ነበር፡፡ ‹‹እዚህ ባይሆን ኖሮ እንዲህ እናደርግህ ነበር›› እያሉ ያስፈራሩኝ ነበር፡፡ ቢቸግረኝ ‹‹ዳኞች እኛን ሊያጣሉን ነው›› አልኳቸው፡፡ በዚህ ላይ ፍርድ ቤት ጊዜ ወሰደና የ28 ቀን የጊዜ ቀጠሮ ሠጠ፡፡
ጥያቄ፡- በዛሬው ችሎት አብርሃ ያለው ነገር ነበር?
ጠበቃ ተማም፡- አዎን፡፡ ‹‹ከታሰርኩ ጀምሮ ከጠበቃዬ ጋር የተገናኘሁት አንድ ቀን ብቻ ነው›› በማለት ለችሎቱ አቤቱታ አቅርቦ ነበር፡፡ ዳኛውም ‹ ከአሁን በኋላ እንደዚህ ዓይነት ቅሬታ መስማት አልፈልግም፡፡ ከጠበቃው ጋር አገናኙት፡፡ ካልሆነ እቀጣችኋለሁ›› ብለዋል፡፡
ጥያቄ፡- በዚህ መሠረት አብርሃን መቼ ያገኙታል?
ጠበቃ ተማም፡- ነገ አርብ ነው፤ አገኘኋለሁ፡፡
ጥያቄ፡- አንድ ቀን ሲያገኙት ስሜቱ እንዴት ነበር?
ጠበቃ ተማም፡- ባለፈው ለችሎት ያመለከተውን ነበር የነገረኝ፡፡ መጎሸሙን፣ መሰደቡን፣ ሰብዓዊ መብቱ መጣሱንና አስፈራተውት መፈረሙን ነግሮኝ ነበር፡፡
ጥያቄ፡- የፍርድ ቤቱ ዳኛ እርስዎን የሚያሥጠነቅቁ ነገሮች ተናግረዋል፡፡ ተገቢ ነው? እርስዎስ በዚህ ጉዳይ ላይ ምን ተሰማዎት?
ጠበቃ ተማም፡- እኔ ስለምንም ነገር አልሰጋም፡፡ ለምን እሰጋለሁ? በሰፈሬ እና በሀገሬ ነው ያለሁት፤ ምንም አልፈራም፣ አልሰጋም፡፡ ምንም ስላላደረኩኝ ልፈራ አይገባም፡፡ እንደዛ የሚያስቡ ሰዎች ናቸው በፍራት ያለባቸው፡፡ ሕገ-ወጥ ሥራ የሚሰሩ ሰዎች ናቸው መፍራት ያለባቸው፡፡ አንተን የሚያስፈራሩ ሰዎች መፍራት አለባቸው፡፡ ለምን? በእንደዚህ አይነት ጉዳይ መፍራት ለራሴ ውርደት ይመስለኛል፡፡ ማንም ጉልበተኛ ነኝ ባይ ሁሉ፣ እንደቦዘኔ ሊያስፈራራኝ በፈለገ ቁጥር ከፈራሁና ከሰጋሁ ውርደት ነው – በዚህ ዕድሜዬ! የሆነ ሀገር ሄደህ ቢሆን እኮ፣ ‹‹ከሀገራቸው ያባርሩኛል፤ እንዲህ ያደርጉኛል›› ልል እችላለሁ፡፡ በሀገሬ ግን ለምን እሰጋለሁ፡፡ በመጀመሪያ፣ ምንም ነገር አይመጣም፡፡ ሁለተኛ፣ ነውር ነው፡፡ አንተ በሀገርህ እያለህ ማንም ሊያሠጋህ አይገባም፡፡ ምክንያቱም፣ አንዱ በሀገርህ ላይ የመኖርህ መገለጫ ሳትሰጋህ መኖር ነው፡፡ ሌላ ሀገር ያለ ይመስል አልሰጋም፡፡
ጥያቄ፡- ከዚህ ጋር በተያያዘ ጠቅለል ባለ መልኩ ማለት የምትፈልገው ነገር?
ጠበቃ ተማም፡- ለአንድ ሀገር እና ሕዝብ አብሮነት ማኅበራዊ መስተጋሩ ተጠባብቆ መኖሩ አስፈላጊ ነው፡፡ ሁለተኛ፣ ሕግ መከበር አለበት፡፡ ሶስተኛ፣ ሕገ-ወጥ ሕጎች እየበዙ ነው፣ ማብቃት አለባቸው፡፡ ስለዚህ ተከባብረን፣ ተረዳድተንና ተዋውቀን መኖር አለብን፡፡ ሁሉም ሰው አንዱ የአንዱን መብት እየጠበቀ መኖር አለበት፡፡
ምንጭ ዘ-ሐበሻ

Thursday, September 4, 2014

በቂ የገንዘብ ድጋፍ ሲገኝ መንግስት በ1997 ጉዳት ላደረሰባቸው ወገኖች ካሳ እንዲከፍል የሚጠይቀው ክስ እንደሚከፈት ስዊድናዊው የህግ ባለሙያ አስታወቁ

ነሃሴ ፳፱(ሃያዘጠኝ)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በ1997 ምርጫ ወቅት ለ200 ሰዎች ሞት እና በመቶዎች ለሚቀጠሩት ቁስለኞች ተጠያቂ በሆኑ 13
ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት እና ወታደራዊ  አዛዦች ላይ ለፖሊስ የክስ አቤቱታ አስገቡት በስዊድን ታዋቂ የሆኑት ጠበቃ ስቴላ ጋርደ ከኢሳት ጋር
ባደረጉት ቃለምልልስ፣ በቅርቡ ለፖሊስ ከገባው አቤቱታ በተጨማሪ የኢትዮጵያ መንግስት በግፍ ለተገደሉት፣ ለቆሰሉት ፣ ለታሰሩት፣ ከስራ ለተፈናቀሉት
አስፈላጊውን ካሳ እንዲከፍል ለማስገደድ የገንዘብ ማሰባሰብ ስራ እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።
አብዛኛውን የምርመራ ስራ የሚሰራውና ወጪውን የሚሸፍነው የስዊድን ፖሊስ ቢሆንም፣ ምስክሮችን ለማስመጣትና ተጨማሪ ሰነዶችን ለማሰባሰብ ገንዘብ
እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል።
ገንዘብ የሚያስፈልገው ክሱን ለሚመሰርቱት የህግ ባለሙያዎች አይደለም የሚሉት ስቴላ፣ በክርከሩ ወቅት የኢትዮጵያ መንግስት ቢያሸንፍ፣ መንግስት ለሚያቆመው
ጠበቃ ወጪ መከፈል ስላለበትና ወጪውን የሚሸፍነውም የተረታው አካል በመሆኑ ነው ብለዋል። የኢትዮጵያ መንግስት በክሱ ከተረታ ግን በውጭ ያለው ሃብቱ
ታግዶ ለተጎጂዎች እንዲሰጠጥ ይደረጋል ብለዋል።
በ13 የመንግስት ባለስልጣናት ላይ የክስ አቤቱታ ቢቀርብም በመንግስት ላይ እስካሁን አልቀረበም ያሉት ስቴላ፣ ኢትዮጵያውያን አስፈላጊውን መዋጪ ማድረግ
ከቻሉና በቂ ገንዘብ እንዳለ ሲታወቅ የካሳ መጠየቂያ ክሱ ወዲያው ይከፈታል ብለዋል። ማንኛውም ገንዘብ አለማቀፍ ደረጃ ባላቸው የሂሳብ ሰራተኞች እንደሚታይና
የተዋጣው ገንዘብ ለህዝብ ይፋ እንደሚሆን ገልጸዋል።
ሰሞኑን ለፖሊስ የቀረበውን አቤቱታ በተመለከተ ጥያቄ የቀረበላቸው ስቴላ፣ ፖሊስ ማመልከቻውን ተቀብሎ ምርመራ መጀመሩንና በሁለት ወይም ሶስት ሳምንታት
ውስጥ ለስዊድን አለማቀፍ ወንጀል  አቃቢህግ እንደሚያስተላልፍ ተናግረዋል። አቃቢ ህግ የቀረቡትን መረጃዎች አይቶ ክሱን ወደ ፍርድ ቤት ለመውሰድ ወይም
ላለመውሰድ እንደሚወስን የገለጹት ስቴላ፣ የቀረቡት ማስረጃዎች ክሱ በአጭር ይቋጫል ብለው ለመናገር እንደማያስድፈራቸው ገልጸዋል።
ከአለፉት አስር አመታት ወዲህ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች እና የጦር ወንጀሎች በየትኛውም አገር መታየት መጀመራቸው ክሱን ለመመስረት እንዳነሳሳቸው ጠበቃው
ገልጸዋል።
አቃቢ ህግ ክስ ለመመስረት ከወሰነ ስዊድን ውስጥ ያሉ ተጠያቂዎች በቁጥጥር ስር እንደሚውሉ፣ ሌሎች ከስዊድን ውጭ የሚኖሩ ባለስልጣናት ደግሞ በኢንተርፖል
በኩል ስማቸው ተላልፎ ተይዘው ክሳቸውን እንዲከታተሉ እንደሚደረግ አክለው ገልጸዋል።
ከጠበቃ ስቴላ ጋርደ ጋር ያደረግነውን ቃለመጠይቅ በነገው ዝግጅት ይዘን እንቀርባለን።

Wednesday, September 3, 2014

ሐሰን ሺፋ ከፌደራል ፖሊስ ም/ኮሚሽነርነት ሥልጣናቸው ተነሱ

(ዘ-ሐበሻ) የሕወሓት ነባር ታጋዮች መካከል አንዱ የነበሩትና ሕወሓት በተከፋፈለበት ወቅት የነስዬ አብርሃ ወገንን ተቀላቅለው በኋላም ወደ አቶ መለስ ወገን ይቅርታ ጠይቀው የተመለሱት የፌደራል ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር አቶ ሐሰን ሺፋ ከስልጣናቸው እንዲነሱ መደረጉ አነጋጋሪ መሆኑን ለዘ-ሐበሻ የደረሱ መረጃዎች አመለከቱ።
hasen shifa
የፌዴራል ፖሊስ የዘ-ሐበሻ ታማኝ ምንጮች እንደገለጹት አቶ ሐሰን ሽፋ በተለይ የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ሰላማዊ እንቅስቃሴን የሕወሓት መንግስት እንዳሰበው በተንኮል ሊቆጣጠረው ካለመቻሉና በስርዓቱ ባለስልጣናት ውስጥ በተነሳው ያለመተማመን ችግር ጋር ተያይዞ ካሉበት ቦታ እንዲነሱ ተደርገዋል። አቶ ሐሰን በምክትል ኮምሽነርነት የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነሩን ከታች ሆነው ሲዘውሩ የቆዩ ሲሆን በአዲስ አበባ፣ በኦሮሚያ፣ በአፋር፣ በጋምቤላ፣ በትግራይ፣ በአማራ ክልል፣ በደቡብና በሌሎችም ስፍራዎች ሥርዓቱ ለፈጸማቸው ጭፍጨፋዎች ተጠያቄ እንደሆኑ የሚናገሩት የዘ-ሐበሻ ምንጮች በድንገት ከዚህ ስልጣናቸው ተነስተው ወደ ፌደራል ጉዳዮች ሚ/ር መስሪያ ቤት ውስጥ እንዲሰሩ መላካቸው የስርዓቱን ደጋፊዎች ሳይቀር “ድርጅቱ በውስጡ ምን እየሆነ ነው?” በሚል እያነጋገረ ነው ብለዋል።
በሕወሓት/ኢሕአዴግ አገዛዝ ስር ያሉ ባለስልጣናት እርስበእርሳቸው አለመሰማማታቸው እንዲህ ያሉ ከስልጣን መነሳቶችና/ መዘዋወሮች በግልጽ የሚያሳዩ ናቸው የሚሉ አስተያየት ሰጪዎች አሉ።
ምንጭ ዘ-ሐበሻ