የኔልሶን ማንደላን ለቅሶና ቀብር ሳይ በጣም ተገረምሁ ብቻ ሳይሆን እፍሪቃዊ መሆኑ ራሱ አኰራኝ። ከዚህም ተነሥቼ፣
ታሪክን ወደኋላ መለስ ብዬ በኅሊናዬ መስተዋት ቃኝቼ ሳበቃ፣ ጊዜው እንደዛሬ ሁኖ ቢያመችለት ኖሮ፣ እንደሳቸው ሊለቀስ
የሚገባ ሰው በአፍሪቃ ምድር ከዚህ በፊት ታይቶ አይታወቅምን ብዬ ራሴን በራሴ ደጋግሜ ጠየቅሁ። ማንዴላ የሚደነቁት፣
በቀለሙ በመጀነንና፥ በዘመናዊ መሣርያው በመተማመን፣ በበላይነት ረግጬው ልግዛው ብሎ፣ ለብዙ ዘመናት በሥልጣን ላይ
ሁኖ ያሠቃይ የነበረውን ጨቋኙን የነጮች ግዛት ከነሥርዐቱ አሸንፈው፣ ለሀገራቸው ጥቊር ሕዝብ የድል ዋንጫ አጐናፅፈው፣
ነፃነቱንና ክብሩን ስለመለሱለት ነው። ግፈኞቹን የድሮ ጠላቶቻቸውንም እንደመበቀል ፈንታ በፍቅር ያዟቸው። ሁሉም
የደቡብ አፍሪቃ ዜጋ በጐሣና በዘር፤ በሃይማኖትና በቀለም ሳይለያይና ሳይከፋፈል፣ ታዲያ በመቻቻል፣ ባንድነትና በፍቅር
ተቀራርቦ እንዳንድ ሀገር ሕዝብ እንዲኖር አደረጉ። ለኻያ ሰባት ዓመታት በእስራት ራሳቸውን በመሠዋት፣ ጠላታቸውን
በማሸነፍ፣ ራሳቸውንና ሀገራቸውን ያኰሩ ደግና ብልህ መሪ፣ ሰውን በማንነቱና በእምነቱ ሳይሆን በሙያውና በችሎታው
የሚፈርጁ፤ ጠላትን እንኳ የሚራሩና የሚወዱ ሰው ነበሩ። ይኸንን በዐይነ ኅሊናዬ መላልሼ ካሰላሰልሁ በኋላ፣ የዓለምን
ታሪክ ደግሞ ቃኝቼ ሳበቃ አንድ እጅግ በጣም ታላቅ ሰው አገኘሁ። አፄ ምኒልክ።
አፄ ምኒልክ በሠሩት ሥራ፣ ባሳዩት ብልሃትና ደግነት፣ ከኔልሶን ማንዴላ በምንም መልክና ሚዛን ይበልጣሉ እንጂ፣ ያንሳሉ ብዬ አልገምትም። ይኸ የግሌ
ብቻ ሳይሆን ብዙ አፍሪቃውያንና የዓለም ምሁራን የሚጋሩት አስተያየት ነው።ኔልሶን የጥቊሮችን እኩልነት በአገራቸው ከማስከበር ውጭ በሌላው
ዘርፍ ብዙ አልገፉበትም። የደቡብ አፍሪቃ ጥቁር ሕዝብ በነጮች የተወረሰውን ሀብት በፍጹም መልሶ አላገኘም። ነጮቹ አሁንም እንደድሮው
በቊጥራቸው የአገሩ ሕዝብ ከመቶ ዐሥሩ እጅ እያሉ፣ ግን ከመቶው ሰማንያ እጅ በላይ የሚሆነዉን የሀገሩን ሀብት እየተቈጣጠሩ ናቸው። ይኸ
የማይካድ ሐቅ ነው። ከሁሉም የባሰ ደግሞ ያገራቸው ጥቁሮች በመጨረሻ ላይ ድል-ቢያደርጉም፣ በነጭ ተሸንፈው መገዛታቸው ራሱ በመንፈሳቸዉና
በታሪካቸው ውስጥ የማይሽር አሳዛኝ ጠባሳ ትቶባቸዋል። ስለዚህም እንደሌሎቹ ለአውሮጳውያን ቅኝ አገዛዝ እንደተዳረጉ ሕዝቦች ሁሉ የዝቅተኝነትና
የውርደት ስሜት በየሄዱበት እንደማይለያቸው ግልጥ ነው።
የአፄ ምኒልክ ሥራ ይኸንን ሁሉ ለኢትዮጵያውያን አስወግዶላቸው፣ ከፍተኛ በራስ የመተማመንና ከማንም (ፈረንጅም ጭምር) አላንስ ባይነትን፣
የልዕልናንና የኩራትን ስሜት እመንፈሳቸው ውስጥ ቀርጿል። ጆን ቦየስ የተባለ ጸሓፊ፣ የምሥራቅ አፍሪቃን የእንግሊዝ ግዛቶች ዙሮ ካየ በኋላ፣
ከኢጣልያን ወረራ በፊት ወደአዲስ አበባ ሲደርስ እጅግ የገረመው ነገር ቢኖር፣ ለመጀመርያ ጊዜ “አንድ አፍሪቃዊ ነጮችን እያዘዘ ቤት ሲያሠራቸው”
ማየቴና፣ ኢትዮጵያውያን ፈረንጆችን “ባሮች እያሉ ሲጠሩዋቸው” መስማቴ ነበር ይላል። እንዲሁም ኢጣልያ ሀገሩን ለሁለተኛ ጊዜ ሲትወርር ወደኬንያ
የሸሹትን የኢትዮጵያን ሰደተኞች፣ ቅኝ ገዢዎቹ እንግሊዞች፣ በተለመደው በዘር ተፋሰስ ድርድራቸው መሠረት፣ ከዕርከኑ ሥር ከነበሩት ከሌሎቹ
አፍሪቃዉያን ጋር ቢደረድሯቸው፣ ከፍተኛ ትርምስ ፈጠሩ። እንግሊዞች “ኢትዮጵያዉያን” የሚል ሌላ ከሌሎቹ አፍሪቃዉያን ከፍ ያለ ዕርከን ሲፈጥሩ
ብቻ ነው ሰላምና ሥርዐት የሰፈነው። ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ቢያውቅም ባያውቅም በገዛ ራሱ የመተማመንና የመንፈሳዊ ኩራት አለው ብል
አልሳሳትም። ይኸም የመንፈስ ልዕልና ስሜት የአፄ ምኒልክ የሥራ ውጤት ነውና ሁሌዬ ልመሰገኑ ይገባቸዋል። ኢትዮጵያዊ የሆነ ሁሉ ለሳቸው ተከፍሎ
የማይዘለቅ ከፍተኛ ውለታ አለበት።
አፄ ምኒልክ ኔልሶን ማንዴላን ይብለጡ እንጂ በብዙ መልክ ግን እንደሳቸው የታደሉ አልነበሩም። ማንዴላ የወረሱት በዘመናዊ መልኩ የተዋቀረ፣
አንድነቱ የጠነከረ፣ በሥልጣኔ የዳበረ፣ በዓለም መንግሥታት የታወቀ፤ ዳሩና ድንበሩ የማይደፈር መንግሥት ነው። ምኒልክ ግን ይኸ ዕድል
አልገጠማቸውም ብቻ ሳይሆን፣ መልሰው ያዋሀዱት የኢትዮጵያ መንግሥት ጥንታዊነትና አስደናቂ ታሪክ ቢኖረውም፣ ፈርሶ በመገነባት ላይ ያለ ነበር።
ለግንባታው አፄ ቴዎድሮስ መሠረቱን ጣሉ። አፄ ዮሐንስ ደግሞ ተመልሶ ከመፍረስ አዳኑት እንጂ ለግንባታው ጊዜና ዕድል ግን አላገኙለትም። እንግዴ
አሁን የሚንኖርባት በዘመናዊ መልኩ የተዋሀደችው የኢትዮጵያ ጥንታዊና አኲሪ ታሪኳ እንደተጠበቀ ሁኖ፣ በአብዛኛው የአፄ ምኒልክ እጅ ፍጡር ናት
ማለት ይቻላል።
እውነት ነው ኢትዮጵያ በብዙ ረገድ ከደቡብ አፍሪቃ ትለያለች። አንደኛ የቈዳዋ ስፋት፣ የመሬቷ ይዘትና ቅጽ፣ የሕዝቧ ባህልና ዐይነት፣ አንዳንዴ ይቀየር
እንጂ፣ ከዚህ በላይ እንዳልኩት፣ ከጥንት ዘመን የነበረች ሀገር ናት። እስከስምንተኛ ዘመን ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ፣ በግልጥ የአካላቷ ቀንድ ግዛቶቿ
የነበሩት አካባቢዎች አሁን የሉም። መናገሻዋ አክሱም በነበረችበት ወቅት፣ አሁን ጂቡትና ሱማሌ በመባል የሚታወቁት መንግሥታት ከዋኖች ግዛቶቿ
መካከል ነበሩ፤ ዛሬ ራሳቸዉን የቻሉ መንግሥታት ሁነዋል። ምናልባት የበሰለ፣ የተራቀቀና አርቆ የሚያስብ መንግሥት ሲኖራቸው፣ አንድ ቀን ወደ ጥንት
እናታቸው መመለሳቸው አይቀርም ይሆናል። እንዲሁም መሠረታዊ ግዛቷ የነበረችው የዱሯ ምድረ ባሕር፣ የቅኝ ገዢዎቿ በሰጧት ስም የሚትጠራው
የዛሬዋ ኤርትራ። የድብልቅልቅና የጨለማ ዘመን በሚባለው ከዘጠነኛ እስከዐሥራ ሁለተኛ ዘመን ድረስ በነበረው ጊዜ ውስጥ፣ የመሬቷ ቆዳ ይዘት ሆነ፣
ያስተዳደሩ ሥርዐት በግልጥ አይታወቅም። ይሁንና ከአፄ ዐምደ-ጽዮን እስከግራኝ ወረራ፣ ከዚያም በመጠኑ እስከዘመነ መሳፍንት ድረስ የነበረው የግዛቷ
መልክና ስፋት ከአሁኑ እንደሚበልጥ፣ የሕዝቧም ዐይነት ለየት እንደሚል ጥርጥር የለም።
ዳግመኛ ከደቡብ አፍሪቃ የሚለያት ዋናው ነገር ቢኖር፣ ኢትዮጵያ የተፈጠረችውና የተገነባችው ባዕዳን በሆኑ በውጭ ሀገር ወራሪዎች ሳይሆን በገዛ
ነዋሪዎቿ ትብብርና እጅ ነው። ኔልሶን ማንዴላ ሲታገሉ፣ “ነጮች ከሌላው የሰው ዘር በላይ ናቸው፥ እግዚአብሔር ዓለምን የማሠልጠን አላፊነትና አደራ
እጫንቃቸው ላይ ሰለጣለባቸው፣ ነጭ ያልሆነውን የሰው ዘር በሙሉ አንበርክኮ የመግዛት ግዴታ አለበት” የሚለው ፍልስፍናና አስተሳሰብ እንደነውር
በሚቈጠርበት ዘመን ነው። እንደገና አፄ ምኒልክ ግን በዚህ ረገድ በጣም ይለያሉ። የነጭ የበላይነት ፍልስፍናው በአሳብ ደረጃ በገነነበት ጊዜ ብቻ
ሳይሆን፣ በግብር በሰፈነበት፣ በመላው ጥቁርና ነጭ ዘር ባልሆነበት ዓለም ላይ በሰፊው በነገሠበትና፣ ምርኮውም በሆነበት ዘመን ነው ዘመናዊቷን
አጼ ምኒልክ Page 2 of 15
ኢትዮጵያን ያዋሀዷትና ሊገነቧት የበቁ። እንዲያዉም የነጭ ዘር ሕዝቡንና ሀገሩን እንደሌላው ዓለም ምርኮው ሊያደርግ ቢቃጣ፣ “የለም ሌላ ጋ ሂደህ
ተጀነን እንጂ፣ ኢትዮጵያን ሀገሬንና ሕዝቤን እንኳን አትነካብኝም” ብለው፣ ሕዝባቸውን በማስተባበር ከጐናቸው አሰልፈው፣ ነጩ ራሱ በፈጠረዉና፣
ይተማመንበት በነበረው መሣርያ ድል አድርገውት፣ ልኩን ያስገቡትና፣ የነጭ ዘር እንደሌላው የሰው ዘር መሆኑን፣ ለሱም ለራሱ ሆነ ለሌላዉም የዓለም
ሕዝብ በሙሉ ያስተማሩት፣ በዓለም ውስጥ የመጀመርያው መሪ ናቸው። ይኸንንም ከሳቸው በመማር ይሁን አብነታቸዉን በመከተል፣ ዘጠኝ ዓመት
ቈይተው ጃፓኖች ደግመውታል።
ያፄ ምኒልክ ትልቅነት የነጮችን አምባገነንንትና ጦር ማሸነፍ ብቻ አይደለም። ያገራቸው ሕዝብ ራሱ “የምኒልክ ነገር ይመስለኛል ተረት” እስከሚል ድረስ
ባስተዳደር፣ በለጋሥነት፣ ለሀገርና ለሕዝብ በሠሩት ሥራቸው ሆነ፣ ባሳዩት መርህና ፍቅር፣ በኢትዮጵያ ታሪክ ብቻ ሳይሆን፣ በዓለም ታሪክ ውስጥም
ወደር የላቸውም። በቅርቡ ልበ-ወለድ ታሪክ እየተፈጠረ፣ ሥራቸዉንና ዓላማቸውን በማጣመም፣ ክብራቸውን ስላጐደፈ፣ ምንነታቸውንም ስለገደለ፣
ቁሞ ማየቱ ተገቢ አይደለም በማለት ይህችን አጭር ጽሑፍ ለማበርከት ተገደድሁኝ። ቢትንዛዛም ረጋ ብላችሁ በጽሙና እንደምታነቧትና
እንደምትደሰቱባት፣ ዕውቀትም እንደምትቀስሙባት እተማመናለሁ።
በአገራችን “ማን ይንገር የነበረ፣ ማን ያርዳ የቀበረ” የሚባል አባባል አለ። አባባሉ ትክክል ነው። በአካል በቦታው ተገኝቶ በገዛ ዐይኑ አይቶ ከሚነግር
ሰው፣ የበለጠ ምስክርና ማስረጃ ሊኖር አይችልም። እኔም በአፄ ምኒልክ ዘመን አልኖርኩም። ግን የታሪክ ተመራማሪ እንደመሆኔ መጠን፣ በጊዜአቸውና
ከሞቱም በኋላ እስከቅርብ ጊዜ ድረስ፣ ስለሳቸው በኢትዮጵያና በሌላ አገር ሰዎች የተጻፈውን ሆነ፣ እሳቸውም በሕይወታቸው ዘመን
ለአስተዳዳሪዎቻቸውና ለሌሎች የጻፉትን ጽሑፎች በሰፊው አንብቤአቸሁአለሁ። በተጨማሪም ሳይጻፍ በአፈ-ታሪክ ሰለሳቸው የሚወራዉንም
ሰምቻለሁ። የታሪክ ምሁር እንደመሆኔ መጠን፣ የተጻፈዉን በሙሉ ደጉንም መጥፎውንም በድፍኑ እንደእውነት አድርጌ አልቀበለውም። ጽሑፉ
እውነተኝነት አለው ብዬ ከመቀበሌ በፊት፣ የታሪክ ምሁራን ዉስጣዊና ውጫዊ ኀሠሣዎች የሚሉትን ትንትኖች በጽሑፉ ላይ በመጠቀም፣ እውነቱን
ከሐሰቱ፣ ድርጊቱን ከምናቡ ማበጠር ይኖርብኛል።
ኀሠሣውም፣ ደራሲው የጻፈበትን ምክንያት፣ ለመጻፍስ ምን ወይንም ማን እንዳነሣሣው፣ ወጪውን ማን እንደሸፈነለት፣ ለጽሑፉ አንባቢ ደግሞ ምን
ዐይነት መልእክት ሊያስተላልፍ እንደፈለገ፣ የጽሑፉስ ግብ ምን እንደሆነ፣ ድርጊቱ በሚፈጸምበት ጊዜ በአካል ተገኝቶ ወይንም ከሌላ ምንጭ ወስዶ ነው
የጻፈው፣ የሚሉትንና እነሱንም የመሳሰሉትን ጥያቄዎች ማንሣት ያስገድደኛል። ጥያቄዎቹም የጽሑፉን እውነተኝነት ለመገንዘብ በጥቂቱም ቢሆን
ይረዳሉ። ለምሳሌ ያህል አንድ የኢጣልያን ተወላጅ የሆነ ዘውገኛና የስዊስ ሰው ባፄ ምኒልክ ላይ ቢጽፉ፣ ኢጣልያኑ ለመጽሐፉ ንጉሡ ከሠሩት ሥራዎች
መካከል የሚመርጠው የራሱን ዓላማና እምነት የሚያራምደውንና የሚያንጸባርቀውን እንጂ የሚፃረረውን አያጐላም። ቢመርጥም ያ ጥሩ ሁኖ የሚታየው
ድርጊት ከንጉሡ የሥራ ልማድ ውጭ እንደሆነ አድርጎት ያቀርበው ይሆናል።የዘውገኛው ጣልያን ዝንባሌ ኢትዮጵያ የሚደነቅ ጥንታዊ ታሪክ
ቢኖራትም፣ አሁን ያለችው በአረመነኔትና በጨለማ ዓለም ውስጥ ተዘፍቃ ስለሆነ፣ ኢጣልያ የማሠልጠን ግዴታ ሰላለባት፣ አገሩን በውድም በግድም
መያዝና ማስተዳደር አለባት ነው። ስለዚህም በጽሑፉ የአፄ ምኒልክን ሥራ ሁሉ፣ ደጉንም ጭምር ወደማጥላላት፣ ጭካኔያቸውን ያሳያል የሚለውን ጐን
ወደማጉላት ያዘነብላል። ስዊሱ ግን ሀገሩ በቅኝ ግዛት ቅርምቻ ፍላጎት ስለሌላት፣ አሳቡ ከመላ ጐደል ቀናናነት ይኖረዋል። ስለዚህም ኢትዮጵያ ከጥቁር
አፍሪቃ የተለየች ጥንታዊት የሥልጣኔ አገር መሆኗንና፣ አፄ ምኒልክም በዘመናዊ ሥልጣኔ ከገፉት አገሮች መካከል አንዷ እንዲትሆን፣ ሌት ተቀን
የሚሠሩ ታታሪ መሪ መሆናቸዉን ማሳየት ይሻል። ስለዚህም የንጉሡን አብዛኛዉን ሥራቸዉን ሲያወድስ፣ መጥፎ ጐን ካላቸው ደግሞ፣ ሌሎችም
በሳቸው ሁናቴና ቦታ የነበሩ መሪዎች የፈጸሙት ተመሳሳይ ፣እንዲያውም የከፋ ድርጊት መኖሩን ስለሚገነዘብ፣ አደባብሶት ያልፋል ወይንም አቃልሎት
ያቀርባል። በነዚህ ሁለት አወዛጋቢ ጽሑፎች መካከል አበጥሮ እውነቱ የት እንዳለ ማወቅ የታሪክ ባለሙያ ሥራ ነው።
ደጋግሜ እንዳዳመጥኹት፣ በየቃሌው [መነጋገርያ=ፓልቶኩ]ና፣ በሌላውም ዘመናዊ መገናኛ፣ በጐጥና በጐሣ ፖሊቲካ የሚመሩት ዓላማቸውና
እምነታቸው ዘውገኛነትን ማራመድ ስለሆነ ነው መሰለኝ፣ ሰለአፄ ምኒልክ ጠንካራ ጐን በፍጹም ሊያነሡና በእምነታችውም ውስጥ ሊያንጸባርቁት
አይፈልጉም። ዐዉቆ የተኛውን ማንቃት እንደማይቻል ሁሉ፣ እነዚህም በይፋ ለተወሰነ ዓላማ የቆሙ እንደመሆናቸው፣ ምንም ዐይነት ማስረጃ
ቢቀርብላቸው ስለአፄ ምኒልክ ጥሩነት ሊቀበሉ ዝግጁ አይሆኑም። እንደፈሊጥ የሚቈጥሩት ምንጮቻቸው፣ በየቡናና በየመሸታ ቤቱ ከመሳዮቻቸው
የሚወራው ወሬና ልበወለድ ታሪክ፣ ካልሆነም በቋንቋም በባህልም ባዕድ የሆኑት ፈረንጆች ለራሳቸው አገር ጥቅምና ለእንጀራቸው ሲሉ የጻፉት
ጽሑፎች ናቸው ። እነዚህም የእምነታቸው ባርያ ስላደረጓቸው፣ ማወናበድም ሥራቸው ሁኗል፤ እውነትም ነፃ እንዳታወጣቸው ይሸሿታል፣ አይጠጓትም
ማለት ይቻላል። ስለዚህ ይኸንን ጽሑፍ እንዳነበቡ፣ እንደልማዳቸው የጥላቻቸውን ነጐድጓድ፣ የስድባቸውንና የክሳቸውን ወጨፎ እንደሚያወነጭፉብኝ
አልጠራጠርም። ከዚህ በፊት እንዳየሁት፣ ከሊቁ እስከተራው፣ ሥራቸው ከሌሎች ለይቶ ግለሰቡን በተናጠልና በስውር ማጥቃት እንጂ እንዳይጋለጡ
ፈርተው በግሁድ አያደርጉትም።
እዚህ ላይ አንድ ነገር ማንሣት እሻለሁ። በሺ ሁለት መቶ መኻል ላይ በዋሺንግቶንና በአካባቢዋ ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ዜና በሚያሠራጭ
ኢትዮጵያዊነት በተባለ ሬድዮ ጣቢያ ላይ በተከታታይ ስለኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁናቴዎች ሰፋፊ ቃለ-መጠይቆች እሰጥ ነበር። ስለኦሮሞ ኅብረተ-ሰብ
እውነተኛውንታሪክ ብገልጽ፣ ቈሽታቸው ያረረባቸው ዐዋቂ ነን የሚሉ ጥቂት ኦሮሞን እንወክላለን ባዮች ስድስት ግለሰቦች1
፣ የተናገርሁትን እጅግ በጣም
አፋልሰውና አከላልሰው በማጣመም ጽፈው ለሁሉም አለቆቼ በተዋረድ2
ላኩ። ከነዚህም አንዱ ሊቅ አሰፋ ጀለታ ሲሆኑ፣ ስለኦሮሞ አንድ የምርምር
1
. ግለሰቦቹ በቴነሲ ዩኒቬርሲቲ በኅብረተ-ሰብ ጥናት ክፍል ውስጥ መምህር ሊቅ አሰፋ ጀለታ፣ ስሟን እንኳን በትክክል መጻፍ የማትችል አድራሻዋም
ምንኔቷም ያልታወቀ ሊቅ አስናቀች ነጋሳ (የእጇ ፊርማ ግን ያንድ በጆርጃ እስቴት ዩኒቬርሲቲ ውስጥ የሚያስተምር በደምብ የማውቀው የታሪክ ሊቅ
ይመስላል)፣ እንዲሁም ሙያቸውና አድራሻቸው ያልታወቀ አቶ በቀለ ቶሎሣና አቶ አበራ ተፈራ፣ የዋሺንግቶን የኦሮሞ እርዳታ ድርጅት ሊቀ-መንበር
ንጉሤ ቢራቱና፣ ክኮሉምቡስ ኦሃዮ የኦሮሞ እርዳታ ማኅበር ሠራተኛ አቶ ጉሉማ ባልቻ ነበሩ።
2
. እንዲሁም በተጨማሪ ለሲአይኤ፣ ለኮንግረስ ለሌሎችም እንደነየተባበሩት መንግሥታት የመሰሉ የዓለም ዐቀፍ ድርጅቶች ሬድዮ ጣቢያውን ሲከሱ
ልከዋል። Page 3 of 15
መጽሐፍ3
የጻፉ ምሁር ናቸው። ጽሑፉም ባንድ በኢትዮጵያ ታሪክ በጣም በታወቀ እንግሊዛዊ ምሁር ታይቶ፣ “ይኸ መጽሐፍ ለቈሻሻ መጣያ ቅርጫቴ
ካልሆነ በስተቀር ሌላ ምንም ዐይነት ጥቅም የለውም” ሲል አቃቂር የጻፈበት ነው። የኔም ግንዛቤ ከዚሁ ይከፋል እንጂ አይሻልም።
ዋና ቁም ነገር፣ እነዚህ ሊቅ አሰፋ ጀለታን የመሰሉት፣ ኢትዮጵያ አገራቸው ብዙውን ጊዜ የሚበላ አጥቶ ጦሙን ከሚያድር ከተራ ድኻ ግብር በተገኘው
ሀብት፣ በነፃ አስተምራቻቸው ለወግና ለማዕርግ ካበቃቻቸው ወዲያ፣ በየቦታው እየዞሩ፣ በቅኝ ገዢዋ ኢትዮጵያ እንደደቡብ አፍሪቃ ጥቊሮች
መብታችንን ተነፍገን በጭቆና እንኖራለን እያሉ መስበካቸው ብቻ ሳይሆን፣ ብልሹ አቋማቸውን መቋቋም ሲያቅታቸው የማይታመን ውሸት ፈጥረው
አቻቸውን ከሥራ እንዲባረሩ ዘመቻ እስከማካሄድ ድረስ መዘቀጣቸው ነው። በቅርብ ጊዜም በዶቼቬለ ሬድዮ በስጠሁት ቃለ-መጠይቅ ተበሳጭተው፣
ጥቂቶች እሜይሌን ከየት እንዳገኙት አላውቅም፣ የአቋሜን ስሕተት ሊያስረዱኝ ጽፈውልኝ ነበር። በጣም የገረመኝ ነገር ቢኖር፣ ሙያቸውና
ዕውቀታቸው በምንም መልኩ ከታሪክ ትምህርት የማይገናኝ ሁኖ ሳለ፣ በታሪክ ውስጥ ገብተው ሊፈተፍቱና ሊያስተምሩኝ ይሞክራሉ። ወይ ጉድ
አልሁኝ፣ ላምነው ስላልቻልኩ። ለነዚህ ዐይነቱ ታሪክ ማለት ማንም አፈ-ጮሌ ገብቶ የሚፈተፍትበት የጥናት ዘርፍ ይመስላቸዋል። ይኸንን ዐይነት
ክብረ-ቢስነት በኤርትራውያን ምሁራን ዘንድ አስቀድመን ስላየንና ሰለለመድነው፣ ብዙዎቻችን አንገረምም ይሆናል። ግን ታሪክ ሲደገም እያዩ ዝም
ማለት አላፊነትን መርሳት ነውና እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ተቃውሞውን በግልም በወልም በሥራ የማሳየት ግዴታ ያለበት ይመስለኛል4
። እንዳልኩት ይኸ
ጽሑፌ ከነዚህ አንጃ ግራንጃ ከሚነዙ ብዙ ውርጅብኝ እንደሚያመጣብኝ ርግጠኛ ብሆንም፣ እነርሱን ፈርቶ ወይንም ለማስደሰት ተብሎ በእውነት
የተመሠረት ሐቅን ላገር ሕዝብ ከማስተማርና ከማሳወቅ ወደኋላ ማለት የተጣለብንን አላፊነትን መርሳት ስለሆነ፣ ምንም ጊዜ ወደኋላ ማፈግፈግ
አይገባም።
ወደዋናው አርእስቴ ከመመለሴ በፊት አንድ ነጥብ ላንሣ። ይኸውም በኅብረ ብሔር የቆሙትን ይመለከታል። እነዚህ አፄ ምኒልክን በተመለከተ፣
በአቋማቸው እንደጐጠኞቹና እንደመንደርተኞቹ አክራሪዎች ባይሆኑም፣ ብዙውን ጊዜ የንጉሡን ደካማውን ጐን ማየትና መቀበል ያዳግታቸዋል። አፄ
ምኒልክ፣ ምንም እንኳ ወደር የሌላቸው ታላቅ መሪ ቢሆኑም፣ ሰው ናቸዉና፣ ሰው መሆናቸው አንዳንዴ በፍጹም እስከመረሳት ስለሚደርስ መጠንቀቅ
አስፈላጊ ነው። እውነት ከሁለት ጽንፈኞች ጐን ኑሮ አያውቅም። ሁሌዬ በመኻል ላይ መሆኑን አንርሳ።
ጽሑፌ በታቻለው መጠን አፄ ምኒልክ ማን እንደሆኑ፣ የኢትዮጵያን አንድነት መልሰው እንዴት እንዳሳደሱ፣ ከዚያም አገሪቷን እንዴት እንዳስተዳደሩ
ባጭሩ ሊገልጥ ይሞክራል። ለመሆኑ አፄ ምኒልክ ማናቸው ከሚል ጥያቄ ልጀምርና ከዚያ ወደሌላው አርእስት በረድፍ በረድፉ ልሂድ። ከመጀመሬ
በፊት ግን አንድ ነገር አጥብቄ ላሳስብ። ለሱም ጄነራል ጂገማ ኬሎ ካሉት ከፍተኛ ትምህርት ካዘለ ንግግር ልነሣ።
ጀነራል ጃገማ ኬሎን ታዉቋቸው እንደሆነ አላውቅም፤ ግን ጄነራሉ ገና በዐሥራ አምስት ዕድሜያቸው አካባቢ፣ ኢጣልያን ሀገራችንን ከወረረ በኋላ፣
ሽማግሌና ሕፃን ሳይለይ ሲገድል፣ ያገሩን ሀብት ሲዘርፍ፣ ሚስት ሲደፍር፣ ያልተከለውን ዛፍ ለገበያው ሲቈርጥ፣ ያላሳደገውን ፈረስ ቀምቶ ሲጋልብ፣
ያላቀናዉን መሬት ከሕዝብ ዘርፎ ከባሕርማዶ ላመጣው ወገኑ ሲሰጥ፣ ቤቶችንና ቅዱሳት ስፍራዎችን ሲያቃጥልና ሲያረኵስ አይተው፣
ወንድሞቻቸውንና እኅቶቻቸውን አስከትለው፣ ሊዋጉ ጫካ የገቡና፣ ኋላም በዚህ አፍላ ዕድሜያቸው፣ የሦስት ሺ ዐምስት መቶ አርበኞች መሪ የነበሩ፣
በብዙ ጐራ በመዋላቸው “የበጋው መብረቅ” የሚል ስያሜ የተሰጣቸው፣ ነፃነት ከመጣ በኋላም ለጄነራልነት ማዕርግ የበቁ መሪ ነበሩ። የኦሮሞ ብሔረ-
ሰብ እንደመሆናቸው፣ የልጅነታቸው ትልቁ ሕልማቸው፣ መላልሰው እልፍ ጊዜ ስለሰሙት፣ ሺ ግዳይ እንደጣሉት እንደቅድመ አያታቸው ጎዳና ነሞ፣
ብዙ ሰው በመግደል ጀግና መሆን ነበር። ታዲያ ይኸንን የሰማ አንድ ጋዜጠኛ ጀኔራል ጃገማን፣ “ልጅ ሳለህ ሕልምህ ለምን እንደቀድሞ አያትህ ሰው
በመግደል ብቻ ተወሰነ” ብሎ ቢጠይቃቸው፣ ጃገማ በጣም ሳቁና፣ “አየህ ጐበዝ፣ በዚያን ጊዜ ከሽማግሌዎቹና ከሞግዚቴ እሰማ የነበረው የቅድመ-አያቴን
ታሪክና ጦርነቱን ብቻ ነው። ሌላው ቀርቶ ከእረኛ ጋር እንኳ አልገናኝም ነበር። በቀበሮ ጒድጓድ ሁነህ ዓሣ ነባሪ ይታይሃለን። አይታይህም። ስለዚህ
እንዳሁኑ ልጆች ሐኪም፣ መሐንዲስ፣ ፓይለት፣ ሳይንቲስት … ለመሆን ላሰብ አልችልም። ምክንያቱ ደግሞ በኔ ዘመን ይኸ አልነበረም። እንደማንኛውም
ልጅ ሕልሜና ምኞቴ ከምሰማውና ከማየው የወጣ አይደለም” ብለው መለሱ። በጣም ጥሩ መልስ።
ጃገማ እንዳሉት ሰው የቀዬው ፍጡር ነው። አሳቡም ሆነ ምኞቱ የሚቀረፀውና የሚያንፀባርቀው በአካባቢውና በጊዜው ካለው፣ ካየው፣ ከሰማው ነው።
ያንድ መሪም ሆነ ሥራው መፈረጅ ያለበት እሱ በነበረበት ጊዜና ወቅት አንፃር እንጂ ለምን በኔ ጊዜ እንደሚሠራና እንደሚታሰብ አልሠራም ወይንም
አላሰበም ማለት አይቻልም። ለምሳሌ በብዙ አውሮጳውያን ዘንድ ከወደአንድ መቶ ተኩል ዓመታት በፊት፣ ሕፃናት በክፉ ዐይን ይታዩ ስለነበር፣
አለምንም ጥያቄ በተለያየ መልክ መግደሉ የተለመደና ከፍተኛ ተቀባይነትም ያለው ነበር። የኛ ሥራ አሁን እንደጭካኔ የሚታየውን እንደዚህ ዐይነቱ
ድርጊት መኖሩን፣ ለምንስ ያደርጉ እንደነበር ማወቅና በታሪክ ሂደት በጊዜያችን የመጣዉን መሻሻል ተገንዝበን በዚያው ላይ ይበልጥ እንዲሻሻል መገንባት
እንጂ ማውገዙ ዋጋ አይኖረውም። ሰንቱንስ አውግዘን እንዘልቃለን። ማውገዝ ብቻ ከሆነማ ማንኛውም የሰው ዘር የመኖር መብት የለውም፤ ከነአካቴው
ማለቅ አለበት። እያንዳንዱ ኅብረተ-ሰብ በታሪክ የፈጸመው ግፍ ተጽፎም ተነግሮም አያልቅም። የራስን ኅብረተ-ሰብ ዐመፅ እያስተሠረዩ፣ የሌላውን
ማጋነን ግን ፍርደ-ገምድልነትም ግብዝነትም ነው። ልክ በወንጌል ውስጥ የራሳቸውን ጉድ ሳያውቁ፣ ኢየሱስ አመንዝራይቱን ሴት በድንጋይ እንድትወገር
እንደጠየቁት ምሁራንና ፈሪሳውያን እንደማለት ነው። ይሁንና ዘመን በዘመን እየተተካ ሲሄድ፣ የሰው ልጅ ገጠመኝ እየሰፋ፣ የፈጠራውም ችሎታ
እየረቀቀ፣ የራሱም ሆነ የኅብረተ-ሰቡ ባሕርይና አስተሳሰብ እየተሻሻለ ይሄዳል፤ እየሄደም ነው። ከአውሬነት ወደሰብኣዊነት፣ ከግፍ ወደፍትሕ ወዳድነት
ያመራል።
ይሁንና ብዙዉን ጊዜ መሻሻሉን ያመጡት፣ በቀዬዉና በጊዜው አስተሳሰብና ልምድ ሳይገደቡ፣ አሻግረው ማየት የቻሉ በቊጥራቸው ጭብጥ የማይሞሉ
ሰዎች ናቸው። ፈረንጆች እነዚህን “enlightened” ይሏቸዋል። በአማርኛ ቋንቋችን “ከሣቲ” እንበለው። ሰው በአካባቢው ባህልና ልማድ ስለተዘፈቀ
3
. የመጽሐፉ አርእስት Asafa Jalata, Oromo Nationalism and the Ethiopian Discourse: The Search For Freedom
and Democracy, Red Sea Press, 1998 ነው።
4
. ለሊቅ አሰፋ ጀለታ መልስ፣ በጠበቃ ደብዳቤ ለዩኒቬርሲትው ተጽፎ፣ ፕረዚደንቱ ተገቢውን እርምጃ እንውስዳለን ብለው መልሰዋል። Page 4 of 15
ማየት ያልቻለዉን፣ ግን የተሻለ ኑሮና አስተሳሰብ እንዲያይ የሰውን አንጐል፣ አእምሮ የሚያበራ እንደማለት ነው። ባጭሩ፣ አንድ ሰው ወይንም ሕዝብ
ከተዘጋበት የባህልና የአሳብ ዋሻ ውጭ፣ ሰፊ ዓለም እንዳለ እንዲገነዘብ አላላ ሜዳውን የሚገልጥለት፣ የሚያሳይለት እንደዚህ ዐይነቱ ከሣቲ ነው።
አፄ ምኒልክም የቀዬአቸው ውጤት ቢሆኑም፣ ያሳለፉት ሕይወትና በየጊዜው ያጋጠሟቸው ሁኔታዎች አድማሳቸውን አስፍቶ፣ ከወዲህ ባሻገር ያለውን
እውነት አይተው፣ ለሌላውም እንዲከሥቱ አብቅቷቸዋል። የኢትዮጵያን አንድነት ለማሳደስና፣ ለዘመናዊ ሥልጣኔዋ መሠረት ለመጣል፣ በዘመኑ ከነበሩት
ታላላቅ ሰዎች ማንም እንደአፄ ምኒልክ የተሟላ ስጦታ የተሰጠውም ሆነ፣ ያለው መሪ አልነበረም ብል ስሕተት አይሆንም።
አፄ ምኒልክ ባባታቸው የንጉሥ ልጅ ቢሆኑም መርሳት የማይገባን አንድ ሐቅ አለ። እናታቸው ገረድ ናት። ምናልባትም በጦርነት ተማርካ እንደጊዜው
ልማድና ባህል ካንዱ የደቡብ ብሔረ-ሰብ በባርነት የመጣች ነበረች። ስማቸውም ቢሆን፤ ንጉሡ በተወለዱ ጊዜ፣ አያታቸው የመልካቸውን አለማማር፣
ዐይነ ፈጣጣ፣ ጥርሰ ገጣጣ መሆናቸውን በመገንዘብ፣ “ምን ይልህ ሸዋ፣ ምን ይልህ ሸዋ!” ሲሉ በማፌዝና በመገረም ያወጡት ነው እንጂ፣ የኋላ ኋላ
ትንቢትና ሕልም የሰፈነበት የኢትዮጵያ ዓለም፣ በትንግርት በማሳበብ አሳምሮት፣ ከመጀመርያው የኢትዮጵያ ንጉሥ ጋር ካያያዘው ከቀዳማዊ “ምኒልክ”
ጋር ግንኙነት የለውም። የሚገርመው ደግሞ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ዘውድ ሲጭኑ ስማቸውን ሳይቀይሩ የነገሡ የመጀመርያው ንጉሠ-ነገሥት ሳይሆኑ
አይቀሩም።
ይሁንና በአፄ ቴዎድሮስ ተማርከው እስከተወሰዱበት ጊዜ ድረስ፣ ያደጉት ከቤተ-መንግሥት ተባርረው ርቀው በመኖር፣ በናታቸው ሞግዚትነት በሌላ
ሀገር ከኦሮሞኛ ተናጋሪ ልጆች ጋር እየተጯጯሁ ነበር እንጂ፣ በድሎትና በቅንጦት በቤተ-መንግሥት ውስጥ አልነበረም። አባታቸውም ቢሆን ያገቡት
ሌላ ሚስት ናት። የምኒልክን አባትነት የተቀበሉትም፣ ወደው ሳይሆን፣ በናታቸው በተጠራው ስብሰባ ላይ ተገድደው ነው ይባላል። ታዲያ አፄ ምኒልክ
የመንግሥትን ሥርዐት የተማሩት፣ እንደገዛ ልጃቸው በታላቅ ጥንቃቄ ተንከባክበው ባሳደጓቸው ባፄ ቴዎድሮስ ሥር ሁነው ነው። ካፄ ቴዎድሮስ ጋር
መኖሩ፣ የሰሜኑን ባህልና አስተሳሰብ በቅርቡ ሁነው የመቅስምና የማዋሃድ ዕድል ሰጥቷቸዋል። ኢትዮጵያንም ለብዙ ዘመናት ሰላምና ዕረፍት ነፍገውዋት
ከሚያተራምሷት ባላባቶችና መሳፍንት እጅ፣ አንድነቷን መልሶ የመገንባትንም ፍቅር ከሳቸው የቀሰሙ ይመስላል። ከተራ ሴት ተወልደው ከተራው
ሕዝብ መኻል ማደጋቸው ደግሞ፣ የዚህን መደብ ኅብረተ-ሰብ ችግሩንና በደሉን፣ ምኞቱንና ሕልሙን በቅርቡ ሁነው እንዲያዩ ረድቷቸዋል ብዬ
አምናለሁ። እንደረዳቸውም ቀጥለን እንደምናየው ሥራቸው ራሱ ይመሰክራል።
ይኸ ሁሉ የሚያመለክተን አፄ ምኒልክ በግል ኑሯቸውና፣ በትውልዳቸው ዝርያ፣ ሕይወታቸዉን የቀረጸዉን የደቡቡንና የሰሜኑን፣ የገዢውንና የተራውን
ሕዝብ ባሕርይ ከመላ ጐደል ያንጸባርቃሉ ማለት ነው። ከዚያም አልፎ ተርፎ፣ የመጨረሻ ባለቤታቸው እቴጌ ጣይቱ ከኦሮሞ አባት ከጐጃሜ እናት
ናቸው። ወላጆቿ አፋቸውን የከፈቱት የአካባቢው ሰው በሚናገረው ቋንቋ ሁኖ፣ ለነገሩ አማርኛና ኦሮምኛ ይባል እንጂ፣ በየደማቸው ውስጥ ያለው ግን
የብዙ የኢትዮጵያ ብሔረ-ሰብ ቅልቅል ነው። የምኒልክ አባቶቻቸው ራሳቸው የአካባቢው ሕዝብ ዲቃላ ናቸው። እቴጌ ጣይቱ ባባታቸው የየጁ ኦሮሞ
ልጅ ቢሆኑም፣ በታሪክ ከጠቅላላው የኢትዮጵያ ሴቶች የሚለዩበት አንድ ነገር አለ። ግዕዝ ያዉቃሉ፤ ቅኔ ይቀኛሉ፤ በገና ይጫወታሉ፤ የውጩን ዓለም
ፖለቲካ አፍተልትለው ያዉቃሉ። ቅኔአቸውን በተመለከተ ባላቸው በሞቱ ጊዜ፡ ሲያለቅሱ፣
“ነጋሪት ማስመታት፣ እምቢልታ ማስነፋት ነበር ሥራችን፤
ሰው መሆን አይቀርም ደረሰ ጊዜያችን።” ብለው የገጠሙት፣ የግጥም ዕውቀታቸው በጣም የዳበረ መሆኑን ብቻ ሳይሆን፣ እሳቸው ራሳቸው የኢትዮጵያ
ሕዝብ ምን ያህል በባህል፣ በቋንቋ፣ በሃይማኖትና በትውልድ እንደተዋሀደና እንደተሳሰረ የሚመሰክሩ ብሩህና ሕያው ምሳሌ መሆናቸውን ያሳያል።
እንግዴህ በየዘመኑ መገናኛ መሣርያ ሁሉን ነገር አንዱ አፉን በከፈተው “ብሔረ-ስብ” በሚሉት የቋንቋ መነጽር ብቻ ለሚያዩት፣ ዘመናዊቷን ኢትዮጵያን
ያዋሀዷትና፣ ነፃነቷን ሳትነፈግ እንዲታድግ፣ ሕይወታቸውን እስከመሠዋት ድረስ በአድዋ ላይ የመሯትና የታገሉላት ባልና ሚስት፣ በየትኛውም ብሔረ-
ሰብ ሥር አይጠቃለሉም። የሚያገናኛቸው ኢትዮጵያዊነትና የኢትዮጵያውያን ቋንቋ ማለትም አማርኛ ብቻ ነው። እንደሁላችን መለዮአቸው ጥቊርነትና
ዲቃላነት ነው። በመልካቸው ጥቊር፤ በዘራቸው ቅያይጥ ነበሩ ማለት ይቻላል።
በሌላ መልኩ የአፄ ምኒልክና የእቴጌ ጣይቱ ጋብቻ በሰማይ የተደረገ ነው ለማለት እንገደላለን። ሁለቱም በሀብት፣ በትምህርት፣ በባሕርይም የተለዩና
ያልተመጣጠኑ ግለሰቦች ቢሆኑም፣ አንዱ የጐደለውን ሌላው ያሟላው ነበር ብቻ ሳይሆን፣ በደማቸውና በዘር ሐረጋቸው፣ ከመላ ጐደል ከመላው
የኢትዮጵያ ብሔረ-ሰብ ጋር የተሳሰሩም ነበሩ። አፄ ምኒልክም አገሪቷን የመሩትና ያስተዳደሩት እንደአባትና እንደእናት በመንከባከብ በፍቅርና በብልሃት
እንጂ እንደጥንቱዎቹም ሆነ እንደቀደሟቸው ሁለቱ ነገሥታት (አፄ ቴዎድሮስና አፄ ዮሐንስ) በኀይልና በማስፈራራት አልነበረም። በጐናቸው የእቴጌ
ጣይቱ ዐይነት ብቁና ቻይ ጓደኛ ባይኖሩ፣ የሥራቸው ውጤት የተለየ እንደሚሆን ጥርጥር የለኝም። የኢትዮጵያን ውህደት የወጠኑት ዳግማዊ አፄ
ቴዎድሮስ፣ በቀብሯ ጊዜ “እስኪ ጠይቁልኝ ርቃ ሳትሄድ፤ እቴጌ ተዋበች ሚስትናት [= ሚስት፣ እናት] ገረድ፣ ብለው ያለቀሱላት ብልህ፣ ጀግናና ውድ
ሚስታቸው በሞት ከተለዩአቸው በኋላ፣ ይበልጥ እንዲጨክኑ አድርጓቸዋል” ይባላል። ታዲያ እቴጌይቱ ቢኖሩ ያ ሁሉ ያዋሐዱት ሰፋፊ አገሮች
ከድተውአቸው፣ በመጨረሻ ላይ ጭብጥ የማትሞላ የመቅደላ ተራራ ንጉሥ ብቻ ሁነው ባልቀሩም ነበር ይሆናል። እዚህ ላይ መነሣት ያለበት ነገር
ቢኖር፣ የኢትዮጵያን የአንድነት ሥራ የወጠነው የቋራው ካሣ ኀይሉ (ዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ) ሆነ፣ አንድነቱን ግብ ያስመታው የሸዋው ምኒልክ ኀይለ
መለኮት፤ የትዳርና የሥልጣን ጓደኞቻቸው የየጁ ሴቶች ነበሩ።
ከዚህ ጠቅላላ ገለጻ ተነሥተን፣ አፄ ምኒልክ ያዋሀዱትን አገር በምን መልክ አስተዳደሩ ወደሚል ሐተታ ገብተን፣ ባጭሩ እንመልከትና ከዚያም ቀጥለን
ባላጋራዎቻቸው ወደሚሰነዝሩባቸው ወዳንዳንድ ነጥቦች እንለፍ። አፄ ምኒልክ በጦር ኀይልም ሆነ፣ “ሕዝብ በከንቱ እንዳያልቅ፣ ሀገር እንዳይጠፋ
በሰላም ግበር” የሚለውን ጥሪያቸውን ተቀብለው በፍቅር በተዋሀዱት አገሮች፣ የዘረጉት አስተዳደራቸው መዋቅር ሁለት የተጠማመሩ ግቦችን ያካተተ
ነበር ማለት ይቻላል። አንደኛው ሕዝብን በግድ ሳይሆን በፍቅርና በዘዴ መግዛት ሲሆን፣ ለዚህም በሕዝቡ ዘንድ እሱ የለመደውና የሚያውቀው ያገሩ
ባላባት ተቀባይነት ይኖረዋል ብለው ስላመኑበት፣ የተማረከዉን ገዢ መልሰው በቦታው ይሾሙ ነበር። ካልሆነም ልጁን ወይንም ሕዝቡ ተሰብስቦ
የመረጠውን ያስቀምጡ ነበር። መዋጋትንም ይመርጡት የነበረው ባላባቱ፣ በሰላም ግበር ብለው አስቀድመው ደጋግመው ለላኩት ጥሪ፣ አሻፈረኝ Page 5 of 15
ሲላቸውና፣ ሌላ አማራጭ ሲያጡ ብቻ ነበር። ሁለተኛው ዓላማ፣ ከዚህ በላይ እንደገለጽነው፣ ዘመኑ አውሮጳዉያን፣ ነጭ ያልሆነውን ዓለም
የሚቀራመቱበት ወቅት ስለነበር፣ ቅኝ ገዢዎቹ አገሩን ለመያዝ ልባቸው እንዳይዳዳ በግዙፉ በይፋ ማስታወቅ ስለሆነ፣ እነዚህ አገሩ በአፄ ምኒልክ ሥር
እንዳለና፣ ቢዳፈሩም ጦርነቱ በቀጥታ ከሳቸው ጋር መሆኑን እንዲረዱ፣ ከማዕከላዊ መንግሥት የተሾመ የታጠቀ የጥበቃ ኀይል በያገሩ ማስቀመጥ ነበር።
የውስጡ አስተዳደር ሙሉ በሙሉ በባላባቱ እጅ ስለሆነ፣ ሕዝብ ካልተበደለ በስተቀር፣ የጥበቃው ክፍል ባስተዳደሩ ጣልቃ አይገባም ነበር።
በዚህ መልክ የተዋቀረው አስተዳደር ራሱን የቻለ እንዲሆን ሲባል፣ እያንዳንዱ ባላባት ዓመታዊ ግብር ይከፍላል። ከዚህም ግብር፣ የጥበቃው ክፍል
ለራሱ የሚበቃውን ቀንሶ፣ የቀረውን ለመንግሥት ግምጃ ቤት ያስተላልፈዋል። ሁኖም ግብሩ የተጣለበት የደቡቡ ሕዝብ ከዉህደቱ በፊት፣ ራሳቸውን
በቻሉ በጥቃቅን የባላባቶች መንግሥታት ቢጤ ሥር ስለነበር፣ እንደሰሜኑ ሕዝብ ለማዕከላዊ መንግሥት ለብዙ ዘመናት ገብሮ አያውቅም። ስለዚህም
ትውፊቱ በሌለበት አካባቢ ግብር በመጣሉ፣ እንደግፍ ተቈጥሮ በመተቸት፣ ያፄ ምኒልክን ሥራ በቅኝ-ገዢነት እስከመተርጐም አድርሷል። እንዲህ
ዐይነቱ አቃቂር መሠረተ ቢስ ከመሆን አልፎ፣ በታሪክም ቢሆን በምንም መልኩ የማይደገፍ ነው። እንግሊዞች “ግብርና ሞት ሁለት አይቀሬ የመኖር ዕዳ
ናቸው” እንደሚሉ ሁሉ፣ አፄ ምኒልክ በግዛታቸው ሰላም ለማስፈር፣ ጸጥታ ለማስከበር፣ የሚወጣውን ወጪ ለመሸፈን፣ እንደማንኛውም መንግሥት
ግብር የማያስከፍሉበት ምክንያት የለም። ይልቅስ ግብሩ፣ ጊዜውንና የሕዝቡን አኗኗርና ችሎታ ያገናዘበ በመሆኑ፣ ንጉሠ ነገሥቱ ምን ያኽል አስተዋይና፣
የአገራቸውንና የሕዝባቸውን የዘለቀታ ጥቅም በደምብ የተረዱ መሆናቸውን ፍርጥ አድርጎ ያመለክታል።
ግብሩ በጠቅላላ ከሕዝቡ ዐቅም ጋር የተመጣጠነ ሁኖ፣ የክልሉን አስተዳደር ወጪ ችሎ፣ ቀሪው ለመንግሥት ግምጃ-ቤት ገቢ ያደርግ ነበር። ይኸም
ኢትዮጵያ ከውጭ አገር መንግሥታትና ከዓለም-አቀፍ አበዳሪ ድርጅቶች ገንዘብ ሳትበደር፣ ባላት ገቢዋ ብቻ ተቈጥባ፣ እጅግ በጣም ሰፊ አገር
ለማስተዳደርና፣ አንዳንድ የልማት ሥራ ለማካሄድ አበቅቷታል። አለመበደሯ ለአብዛኞቹ የእስያና የአፍሪቃ ሀገሮች ከደረሰባቸው መጥፎ ዕጣ(በተለይም
ግብፅን የገጠማት ዐይነት)፣ ማለትም አበዳሪዎቹ ክሳራቸውን ለመሸፈን በሚል ሽፋን አገሯን በዋስትና ከመያዝ አድኗታል። አካባቢው የታወቀ የተፈጥሮ
ምርት ከሌለው፣ በሰሜኑ ክፍል እንደተለመደውና ከጥንት ይሠራ እንደነበረው፣ መሬቱ ተሸንሽኖ በተወሰነ ሰው ቊጥር ይደለደልና በሰው ልክ ግብር
ይጣልበታል። በተራ ቋንቋ ገባር የሚባል ቃል ከዚህ የመነጨ ነው። ትርጒሙም “ግብር የሚከፍል” ማለት ነው።
ባህሉንና አሠራሩን ባልተረዱትና፣ ከአገራቸውና ከራሳቸው ጥቅም አንጻር በሚያዩት የፈረንጅ ጸሓፊዎች ላይ በመመርኰዝና ከታሪክ ሂደት ጋር
ካለማገናዘብ የተነሣ፣ ገባር መጥፎ ትርጒም ተስጥቶት ይገኛል። ይባስ ብሎ፣ ከፀጥታ ጥበቃው ክፍል በማያያዝ “የነፍጠኛ ሥርዐት” ብለው የሚጠሩትም
አሉ። ታሪክ ማጣመም ካልተፈለገ በስተቀር ትርጒሙ እውነቱን አያንፀባርቅም። ከጊዜው የአገሩ ምጣኔ ሀብትና የሕዝቡ ዕድገት ደረጃ፣ እንዲሁም
ከዓለም ዐቀፍ ሁናቴና የመንግሥታት ኀይል አሰላለፍ አንጻር ሲታይ፣ ምንም ብንል፣ ያኔ ከገባር የተሻለ አማራጭ ከቶውኑ አልነበረም። ቢኖር ኖሮ፣ አፄ
ምኒልክ በደስታ እንደሚቀበሉት በምንም አልጠራጠርም። ለዚህም ያኔ በመጠኑ በሥልጣኔ ደረጃ ከሌላው ክፍለ አገር ሻል ብላ ለሚትገኘው ለድሬዳዋ
ከተማ በ፳፰ ሠኔ ፲፰፻፺፰ ዓ.ም. አስተዳደርዋ እንደሌላው አካባቢ በባላባት መሆኑ ቀርቶ በመማክርት፣ ማለትም በሥራ አስኪያጅ ቡድን
እንዲትተዳደር ብለው ያወጡት ሕግ እንደማስረጃ ሊጠቀስ ይችላል። እንደዚሁም የወላይታ ባላባቶች በተራው ሕዝብ ላይ በደል ቢያበዙ፣ ሽረዋቸው
ከጥብቅ ማስጠንቀቂያ5
ጋር በ፪ ሠኔ ፲፱፻ ዓ.ም. ያቋቊሙት የሹማምንቶች መማክርትም ሌላ ምሳሌ ነው።
የገባር ሥሪት ባሕርይ በሰሜንም በደቡብም አንድ ዐይነት ሁኖ ሳለ፣ በኻያኛው ዘመን ላይ በደቡቡ ሥርዐት ሰፊ ለውጥ ስላሳየ፣ ልዩነቱ በአካባቢው
የተከናውኑ የሥራዎች ውጤት እንጂ ከመንግሥት የታወጀ አዋጅ ወይንም የተወሰደ እርምጃ ያመጣው ፍሬ አልነበረም። የሰሜኑ ክፍል በባላባቶች
በመበጥበጡ ምንም ዐይነት የልማት ሥራ ሳይካሄድበት በቁመናው ሲቀር፣ በደቡብ የዘመናዊ እርሻ ተዘርግቶ ሲያበቃ፣ ያመጣው ሀብትና ድሎት
ባላባቱንም ሆነ የማእከላዊ መንግሥት ሹሞችን ስለተፈታተነ፣ ሁለቱ አንዳንዴ በመተባበር፣ አንዳንዴ ደግሞ በተናጠል ተራ ሕዝቡን እያባበሉ ሆነ
እያዋከቡ፣ ወይንም ኀይል በመጠቀም መሬቱን እስከመንጠቅና ጥሎላቸው እስከሚሄድ አድርሰዉታል። ለምሳሌ አሩሲዎች ለከብታቸው ግጦሽ
እስከሚያጡ ድረስ መሬታቸዉን አጥተዉት ነበር። አፄ ምኒልክና ተከታዮቻቸው ጊዜውና ዐቅማቸው በፈቀደላቸው መጠን ከሕዝቡ ጐን ሁነው
አንዳንዴ በአዋጅ፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ ባለሥልጣኖቹን ሽረው ሌላ በመተካት ሳይታክቱ እንደተዋጉ ሰፊ ማስረጃዎች አሉ። የወለጋው ደጃዝማች ጆቴ
በተደጋጋሚ የመንግሥት ገንዘብ ሰረቀ ሲባል ዝም ያሉት አፄ ምኒልክ፣ ድሃውን አላግባብ ዘረፈ፣ ያልሆነ ቅጣት ቀጣ ሲባል ግን ምንም ሊታገሡት
አልቻሉም። በሸዋም በአሩሲም ኦሮሞች ከመሬታቸው መነቀላቸውን እንደሰሙ በአዋጅ ተመልሰው እንዲተከሉ አድርገዋቸዋል።
ይሁንና ሕግ ቢወጣም፣ ባለሥልጣኑ ተሽሮ በሌላ ቢተካም፣ ያገሩ አባባል “ሲሾም ያልበላ፣ ሲሻር ይቈጨዋል” ነበርና እምብዛም ንጉሠ-ነገሥቱ
እንደተመኙት አልቀናላቸውም። እንኳን ያኔ በዘመናዊ ሥልጣኔ ገና መዳዳት በመጀመር ያለች ኢትዮጵያን የመሰለ አገር ይቅርና፣ በዛሬይቱ በሥልጣኔ
ከዓለም ሁሉ በመነጠቀች አሜሪቃ እንኳን ሕግን ማስፈጸም ምን ያህል አስቸጋሪ እንደሆነ ብዙዎቻችን እናውቀዋለን። አፄ ምኒልክም ምንም እንኳ ለድሃ
እጅግ ቢቈረቈሩና በአዋጅም ሆነ፣ ታማኝ ገዢ በመሾም የተሻለ አስተዳደር ሊያመጡ ቢሞክሩ፣ ጊዜውና የባለሥልጣኖቹ ወደኋላ-ቀር አስተሳሰብ
አልተባበረላቸውም። ስለዚህም እሳቸውንም ሆነ የገባርን ሥርዐት በድፍኑ ማውገዝ ታሪክን ከማጣመምና ሂደቱን ካለመረዳት የተነሣ እንጂ እውነትነት
የለውም።
5
. ከማስጠንቀቂያው የምንረዳው ንጉሠ-ነገሥቱ ምን ያህል በባላባቶች ላይ እምነት እንዳጡ ነው። ለመማክርቱ ከሰጡት ማስጠንቀቂያ ለምሳሌ
ያህል፣ ቀጨብ ላድርግና ልጥቀስ። እናንተን “መርጬአችሁ ወላሞ ላይ መሾሜ ድሃዬን እንዲትጠብቁልኝ ነው፤… ደንብ ካደረግነው ከዓመት ግብሩና
እኔ ከማዝዘው ትእዛዝ በቀር.. ድሃው በምንም እንዳይነካ ይሁን።” እንደቀድሞቹ ሹሞች “አላግባብ ከሠራችሁና፣” ድሃው ተበላሁ ብሎ ከጮኸልኝ፣
“በገንዘብ ብቻ ሳይሆን ብዙ ቅጣት ትቀጣላችሁ”። ድሃው ከናንተም አንዱ በደለኝ፣ ገንዘብ በላብኝ ቢል፣ ተሰብስባችሁ ነገሩን አጣሩና አስጨርሱ።
ካልተቻላችሁ ግን ወደኔ ላኩልኝ። … “ከባላገሩ ግን በምንም በምንም አመካኝታችሁ የምትነኩት ገንዘብ የለም።”
Page 6 of 15
አንዳንዶቹ ታሪክን በማጣመም ብቻ አልተገቱም። ምኒልክ የኢትዮጵያው ሂትለር ብለው እስከመስበክ ደርሰዋል። መልሰው ያቋቋሙትን የኢትዮጵያን
አንድነት ራሱን፣ ከዚህ በላይ ጨረፍ አድርገን እንዳመለከትነው፣ከቅኝ ግዛትነት ጋር የሚያመሳስሉም አሉ። እንደነዚህ ዐይነቶቹ ስለሂትለርም ሆነ
ስለምኒልክ፣ ስለቅኝ አገዛዝም ምንም የማያውቁ ብቻ ሳይሆን፣ በእሬትና በሱካር፣ በጨለማና በብርሃን መካከል ያለዉን ልዩነት እንኳን ለይተው መንገር
የማይችሉ ቅለታሞች ናቸው ከማለት በስተቀር በሌላ ልፈረጁ አይችሉም። አንባቢዬን ልብ እንድትልልኝ እያማጠንሁ፣ እስኪ በነዚህ አርእስቶች ላይ
ላትኩር።
በሂትለር ልጀምር። ብዙዎቻችን እንደምናውቀው፣ ሂትለር የቆመው የራሱ ዘር ማለትም ጀርመን የሁሉንም ሰው ዘር ጨርሶ ፈጅቶ ሌላውን እንዲተካ
ነው። ሂትለር በጀርመን ዘር አምባገንነት እንጂ በሰው ዘር እኩልነት ከቶውኑ አያምንም። የዓለምን ሕዝብ በተፋሰስ ደርድሮ ሲያበቃ፣ ጥቁሮቹን
ያስቀመጠው ከሥሩ ዕርከን ነው። በሱ አስተሳሰብ፣ እልቂታቸዉም መፈጸም ያለበት ከሥር ካለው ጀምሮ ነው፣ ማለትም ከነዚሁ አፄ ምኒልክን ከሂትለር
ጋር ከሚያመሳስሉት ኢትዮጵያውያን ራሳቸው።
ከዚህም አልፎ፣ በሂትለር ዘንድ ሁሉም ጀርመን የጠራ ስላልሆነና፣ የጀርመንን ሕዝብ ባሕርይ ስለማያንፀባርቅ፣ ጠንቀኞች ናቸው ያላቸዉን አካለ-
ስንኩሎቸን፣ ደካሞችን፣ በሽተኞችንና፣ አጭሮችንም ጭምር ፈጅቷቸዋል። እነዚህ የፈረደባቸው የመጀመርያው ድርጎው ናቸው። ችግር ባይገጥመው
ኖሮ፣ ተራው በሱ ዘንድ በደምብ ነጣ ባላሉት ጀርመኖች በሆነ። የዓለም መንግሥታት እንደነቁ፣ ተረባርበው የቀረዉን ሌላዉን እምነቱን እግብር ላይ
ከማዋሉ በፊት አጠፉት እንጂ፣ ዝም ቢባልና ዕድሉ ቢገጥመው፣ በእምነቱ መሠረት ጥቁሮቹ መጀመርያዎቹ በሆኑ ነበር። ይሁንና መንግሥታቱ
ሊያጠፉት የቻሉት፣ አጠገቡ የነበሩትን ስድስት ሚሊዮን አይሁዶችን በአሰቃቂ ሞት ከፈጀ በኋላ ነው። በቅርብ ጊዜ እንደሰማሁትና እንዳነበብሁ፡
በአገራችን በዘዉገኝነት ጽንፈኞች የሚመሩት የሂትለር አድናቂዎችም፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ባንዳንድ ብሔረ-ሰብ ላይ የፈጸሙት እልቂት፣ ልክ ይኸንኑ
ኢሰብኣዊ ዐይነት ድርጊት ሳይተካከለው አይቀርም። ግን የአሁኑ የአገራችን ሰው ከመጮህና ከመለፍለፍ አልፎ በድርጊቱ መዘገነኑን በግብር ስለማያሳይ፣
ከእነዚህ አረመኔዎች አብዛኞቹ ካገር ቤት ወጥተው እንደሌላው ንጹሓን ስደተኞች መስለው፣ ማንም ሳይነካቸው፣ በምዕራብ አገር ተንደላቅቀውና
ተንፈላስሰው እየኖሩ ናቸው። ይኸም ኢትዮጵያውያን በንግግር እንጂ በተግባር ግን ምንም ያህል የሚረቡ እንዳልሆኑ ያስረዳል።
ወደዋናው ነጥብ ልመለስ። አፄ ምኒልክ ሂትለር የቆመለትን ሁሉ የሚፃረሩ ናቸው ቢባል በፍጹም ማጋነን አይሆንም። በሰው እኩልነት የሚያምኑ
እንደመሆናቸው፣ በዘር፣ በቋንቋ፣ በሃይማኖትና በባህል የተመሠረት የማንንም ልዩነት አይደግፉም። ለሰው ሕይወት ከፍተኛ ክብር እንዳላቸው፤ ከዚህ
በላይ በተደጋጋሚ እንደተገለጸው ለድኻ እጅግ ርኅሩኅና ተቈርቋሪ መሆናቸውን ሥራቸውና ጽሑፎቻቸው በሰፊው ይገልጻሉ። ለምሳሌ ያህል ጥቂቶቹን
ከዚህ በታች አሰፍራለሁ።
በሥልጣኑ በመጀነን፣ የገዛ ሕዝቡን ያጠቃ ለነበረ የጂማ ገዢ አባ ጂፋር ሲጽፉ ያሉት፣ ፈጣሪ መርጦህ ገዢ ቢያደርግህ፣ “በሰው መጨከን አይገባም።
ለስው ቢያዝኑ ዕድሜ ይሰጣል” ነው። ጣልያኖች ከተማረኩ በኋላ፣ ዓለም እስከሚገረም፣ ጠላቶቻቸው ራሳቸው ማመን እስከሚዳያግታቸው ድረስ፣
በክብር ይዘዉአቸው ተንከባክቧቸዋል። “የሰው ደም ለምን በከንቱ ይፈሳል” በማለት ወደ አድዋ ጦርነት ላለመሄድ ፈልገው ነበር። ጣሊያኖች ግን
ልመናቸውን እንደድካምና ፍርሀት በመቊጠር፣ ደጋግመው “አለመግባባታችንን በሰላም እንፍታ” ብለው ላደረጉት ልመና በሙሉ፣ አሻፈረኝ ሲሉ ብቻ
ነው ውጊያን የመረጡት። እንደገና በአምባላጌ ከተሸነፈ በኋላ፣ በመቀሌ ውጊያ ለብዙ ቀናት በጣም ጦራቸዉን የፈጀው የጣሊያን ሠራዊት በውኻ ጥም
ሊሞት ሲል፡ በሰላም ያሳልፉን ቢሏቸው ቢማረክ፣ አፄ ምኒልክ፣ የጦር መሪዎቻቸዉን ተቃዉሞ ዝም አሰኝተው፣ ጠብታችውን እንደያዙ መጫኛና
መጋለቢያ ከብት በገንዘባቸው ካገሩ ነጋዴ ገዝተው ሰጥተውት፣ በአጃቢ ነው የሸኙት። ይኸ ብዙ ያለም የጦር ጠበብቶችን እንኳን አስደንቋቸዋል።
አንዳንዶቹ (ጣሊያኖችቹን ጭምር) ምንኛ ጅል ናቸው እስከማለትም ደርሰዋል። ጅል ግን አልነበሩም። ዘዴኛ ናቸው። ጦርነቱን በጥብቅ ይከተል
ለነበረው ዓለም፣ ምን ያህል ሰላም ፈላጊ መሆናቸዉን ብቻ ሳይሆን፣ ሥልጣኔ የሚያስፈልጋቸው ኢትዮጵያዉያን ሳይሆኑ፣ ታዲያ ባሕር አልፈው፣ ብዙ
አገር ሰንጥቀው መጥተው፣ የሰውን ልጅ በግፍ በገዛ ሀገሩ ሊጨፈጭፉ የሚፈልጉ ጣሊያኖች መሆናቸውን ሊያስረዱ ነው የፈለጉት።
ይኸንን ዐይነት ርኅራኄና ደግነት ያሳዩት በውጭ አገር ጠላት ላይ ብቻ አይደለም፣ ባገራቸዉም ሰው ላይ ጭምር ነው። የጐጃሙ ንጉሥ ተክለ-ሃይማኖት
በተሸነፉ ጊዜ በጣም ቈስለው ሰለነበር፣ እንደተማረኩ በጋቢያቸው ቊስሉን ጠርገው እንዲታከሙ አድርገው ሲያበቃ፣ አዲስ-አበባ ወሰዷቸው። እዚያም
የንጉሥነታቸዉን ማዕርግ በምንም መልክ ሳያጐሉ ተንከባከቧቸው፤ በየቀኑም ይጐበኟቸዉና አብረውዋቸው ይበሉ ነበር። የጐጃም ጦር መሪ ራስ ደረሶ
አንድ ቀን ለቀልድ፣ “አፄ ምኒልክ ቢሸነፉ ምን ባደረግህ ነበር” ብሎ ሲጠየቅ፣ “እኛማ ብናሸንፍ ኖሮ፣ ቈርራርጠን ለአሞራ ነበር የምናበላው” ነው
ያለው። መልሱ አላንዳች ክርክር፣ የአፄ ምኒክን ታላቅነት ጥርት አድርጎ ያሳያል። እንዲሁም፣ ብዙ ጦር የፈጀባቸው የወላይታው ንጉሥ ጦና ሳይማረክ
ቢሸሽ፣ አፄ ምኒልክ፣ “እንዳያመልጥ ያዙልኝ” ብለው፣ ቈስሎ እንደተያዘ፣ ከዙፋናቸው ወርደው ከተቀበሉትና፣ “እንዲያው በከንቱ ሕዝብ አስጨረስኽ”
ብለው ከወቀሱት በኋላ፣ ቊስሉን አጥበዉና፣ በጋቢያቸው ጠርገው አሳክመውት ሲያበቃ፣ ሕዝቡን ሰብስበው፣ “ከእንግዴህ የሚያስተዳድርህ ልጄ
ወዳጄ ጦና ነውና ተገዛለት፤ ዐውቆ ሳይሆን ሳያዉቅ፣ እኔን የበደለ መስሎት፣ ሕዝብ አስጨረሰ እንጂ … ቂም የለንምና መልሼ እሱን ሾሜልሃለሁ” ነው
ያሉት።
በየቦታው እንደንጉሥ ጦና ተመልሰው የተሾሙት ባላባቶች፣ በገዛ ሕዝባቸው ላይ ግፍ መሥራት አናቆምም ቢሏቸው፣ የተጻጻፉት መልእክቶቻቸው፣ አፄ
ምኒልክ ምን ያህል “ድኻዬ ተበደለ” ለሚሉት ሕዝብ እንደሚቈረቈሩ በግልጥ ያሳያል። ለምሳሌ ያህል ብቻ ሦስት ልጥቀስ። አባ ጂፋር በባርያ ንግድ
ገናና የሆነችዉን ጂማን በሥርዐት እንዲያስተዳድርና ንግዱን አንዲያቆም ቢመከር፣ የአገሩን ሰው በባርነት መሸጥ ቢያቆምም፣ ወደአገሩ በሚገባው ኦሮሞ
ላይ ግን ጭካኔውን ቀጠለ። በዚህ ሥራው የተቈጡት አፄ ምኒልክ፣ “ወዳገርህ የመጣውን ጋላ … ከእጄ ገብተህ ጭቡ አድርገህ ባርያዬ ነህና፣ አንተንም
ልበድልህ፤ ልጅህንም አምጣና እንደከብት ልሽጠው፣ ልለውጠው አትበል፤ …የሰው ባርያ የለውም፤ ሁላችንም የእግዚአብሔር ባሮች ነን።” ብለው
ገሠፁት። እንዲሁም የወለጋው ገዢ ደጃዝማች ጆቴ ደግሞ የሕዝቡን መብት እየረገጠ፣ የተገፋው እንደጊዜው ልምድ ወደጃንሆይ እንዳይሄድ ቢከለክል፡
ከአፄ ምኒልክ “የተበደለ ድኻ ከኔ ዘንድ እንዳይመጣ አትከልክል፤ ተበደልሁ ብሎ ከጮኸ ደግሞ ጭራሽ ከሹመትህ እሽራሃለሁ” የሚል የቊጣ ደብዳቤ
ደረሰለት።
Page 7 of 15
ድኻን መበደል፣ በተለያየ መልኩ በሁሉም ግዛቶች የተስፋፋ ነው። የጐጃሙ ገዢና የአፄ ምኒልክ ከፍተኛ ባለሟላቸው የነበረው ራስ ቢትወደድ መንገሻ
አቲከም በደብዳቤ ተገሥፆ፣ የቅርብ ድኻውን ማሠቃየት እንዳቆመ፣ ንጉሥ አይደርሱብኝም በማለት፣ ያነ ሻንቅላ በመባል የሚታወቀውን ሕዝብ ባርያ
እያደረገ አጒላላ፣ አሰቃየ። አፄ ምኒልክ ነገሩን በሰላዮቻቸው እንደሰሙ፣ እየገበረ የሚኖረውን “ሻንቅላ … እንደ ከብት ሁሉ ባመት ባመቱ እየመለመልክ
ታስወጣለህ አሉ። …. ልጅህንም ስትድር የሰጠኸውን ሻንቅላም ሰምተናል። እንግዴህ ግን አንድ ሻንቅላ ተመልምሎ ካገሩ ወጣ ያሉኝ እንደሆነ፣ ሁለተኛ
እኔና አንተ መገናኛ የለንም።” ብለው የዛቻ መልእክት ላኩለት።
አፄ ምኒልክ ደግ ብቻ ሳይሆኑ ቀልደኛም ናቸው። በልጅነቴ ያነበብሁት መቼም የማልረሳ አንድ አፈ-ታሪክ አለ። በራቡ ዘመን ለማኝ እየመጣ፣
አጋፋሪዎቹ ችላ እያሉ ምንም ሳይሰጠው እየሄደ ነው የሚል ወሬ እንደሰሙ፣ አፄ ምኒልክ በግቢያቸው አንድ ደወል አሰቀሉ። ደወሉ በተደወለ ቊጥር
አስፈላጊውን የሚሰጥ ሠራተኛ ተቀጠረና ሁሉም ተደሰተ። አንዱን ቀን ግን አንድ ለማኝ ቢጤ ደውሎ ምን አስፈለገህ ቢባል፣ “ለማኝ እንኳ
አይደለሁም፤ የጃንሆይ ዘመድ ነኝና ላገኛቸው ፈልጌ ነው” ብሎ ሲመልስ፣ አፄ ምኒልክም ጉዳዩ እንደተነገራቸው አስገቡት አሉና ገባ። እያጫወቱት ራስ
ወረዳውን ቢያዩ፣ ዝምድናው አልታይ ሲላቸው ዝምድናችን በማን ነው ቢለው ቢጠይቁት፣ “ጃንሆይ፣ ባያቶቻችን በአዳምና በሔዋን ነዋ” አለ። ደግ
ቢለው አንድ ብር ሰጥተው ሲሸኙት፣ ጃንሆይ፣ እንዴት አንድ ብር ብቻ ሰጥተውኝ ይሽኙኛል ቢላቸው፣ “አዪ የተከበርክ እንግዳዬ፣ ባዳምና በሔዋን
ለሚዛመደኝ ሁሉ ቢሰጥማ ላንተ እኮ እሷም ቢትሆን አትደርስህም ነበር ” አሉ ይባላል።
አስተዳደራቸውን በተመለከተ፣ የውጭ ሀገር ጸሓፊዎች ራሳቸው አፄ ምኒልክ ኢትዮጵያን በጥበብና በፍቅር እንደሚያስተዳድሩ፣ ሕዝቡም
እንደሚወዳቸው ደጋግመው ይናገራሉ። አንድ ዊልቤ የተባለ በ1893 ዓ.ም. የደቡቡን አገር እስከሩዶልፍ ሐይቅ ድረስ ዙሮ ከጐበኘ በኋላ፣ “በዳር ሀገር
ያለው ሕዝብ በሙሉ ምኒልክ መልካም ሰው ነው ይላል፤ ምኒልክ ሁሉም ሰው በሃይማኖቱ ይደር ስላለ፣ በሕዝቡ መሀል አድልዎ ስለማያሳይና ጉልበት
ስለማይጠቀም ይወዱታል። የሚያወሩትም እንደሌሎቹ ንጉሦች ስለመሰለን ሸሽተን ነበር። በኋላ ግን ስሕተታችንን ስናዉቅ ይቅርታ ጠይቀን ተመለስን፤
… አሁን ግብራቸዉን እየገበሩ በሰላም ይኖራሉ።” ሲል ጽፏል። በቅርቡ በኢትዮጵያ ጥናት በመላው ዓለም ገናናነቱ የታወቀው ሰመ-ጥሩ ሊቀ ሊቃዉንት
ኡለንዶርፍ፣ “በምኒልክ ዘመን ያገሪቱ ክብር ከፍ አለ። የዘመናዊ አስተዳደር መሠረትም ተጣለ… ንጉሡም ያስተዳድሩ የነበሩት በዘመናዊነትና በጥበብ
ነው” ሲል ይናገራል።
እንግዴህ አፄ ምኒልክን ከሂትለር ጋር የሚያዛምዱትን ሰዎች የሚደግፋቸው ምንም ዐይነት መረጃ የላቸውም እያልኩ ነገሩ እንዳይንዛዛ በዚሁ ላብቃና
አሁን ኢትዮጵያን መልሶ የማዋሀዱን ሥራ ከቅኝ አገዛዝ ጋር የሚያመሳስሉትን ለማተት ልመለስ። ቅኝ ግዛት ማለት ባጭሩ የሌላውን አገር በኀይል
ወስዶ፣ ሀብቱን ዘርፎና ነጥቆ፣ ሕዝቡን ጨቁኖ መግዛት ማለት ሲሆን፣ ቅኝ ገዢ ያገሩን ሀብት ከመዝረፍ ውጭ ለነዋሪው ሕዝብ ደንታ የለዉም።
ይልቅስ ተገዢው ወገን ዝቅተኛ መሆኑን እንዲረዳ፣ ከገዢው ክፍል ጋር የእኩልነት ስሜት በፍጹም እንዳይሰማው፣ የራሱን ወገን ክብርንና ልዕልናን
የሚያረጋግጡ ደንቦችን ያወጣል። በአሽከርነት ሥራ ተቀጥረው ካልሆነ በስተቀር፣ በሌላ የሥራ ዘርፍም ሆነ፣ ጥሩ ገቢና ትርፋትርፍ በሚያመጣ ሙያ
እንዳይሰማሩ ያግዳል። ዋናው ዓላማ በአገሩ የራሱን ሕዝብ ለማስፈርና ለመቈጣጠር ስለሆነ፣ ባላገሩን ከለምለም መሬቱ ነቅሎት፣ ቀስ በቀስ በሰብኣዊ
መንገድ ሙቶ እንዲያልቅ ሲል በማይፈልገው ኰረኰንች መሬት ላይ ያጒረዋል።
ባጭሩ፣ የቅኝ ገዥዎች ዋና ዓላማቸው፣ ባላገሩን እንጨት ለቃሚ፣ ዉኻ ቀጂ፣ መሬት ቆፋሪ ማድረግ ነው። ባላገሩ ራሱ በከፈለው ግብርና፣ በላቡ
በሠራው መንገድም ሆነ የሕዝብ ማመላለሻ ላይ እንኳን መሄድ አይፈቀድለትም። ከተፈቀደም በንቀት “ለአገሬው ብቻ” ተብሎ በተመለከተበት በወራዳና
ብስብስ ክፍል እንጂ ፈረንጁ የሚቀመጥበት ከቶውኑ አይደፈርም።
የሴትንና የወንድን የወሲብ ዓለምንና ግንኙነትን በተመለከተ፣ ጋብቻና የርስ በርስ መቀራረብ ቀርቶ፣ ባላገሩ ፈረንጇን አትኩሮ ቢያያት እንኳ ተዳፈርኽ
ተብሎ ሊቀጣ፣ ሊገደል ይችላል። ለምሳሌ ያህል፣ የቦትስዋናው አልጋወራሽ የነበሩትና ኋላም አገሩን ከነፃነት በኋላ ለብዙ ዘመን ወደከፍተኛ ብልጽግና
የመሩት አቶ ሠረፀ ካማ፣ በተማሪነታቸው ወቅት በእንግሊዝ አገር በኦክስፎርድ ዩኒቬርሲቲ እያጠኑ እያሉ፣ ካንድ ተራ እንግሊዛዊት ጋር ሲወጡ ቢገኙ፣
[ነጭ] ተዳፍሯል ተብለው በቅጣት ትምህርታቸውን አቋርጠው ወዳገራቸው እንዲመለሱ ተገደዱ። ወደዚያ ሩቅ ሳንሄድ በጐረቤቶቻችን በኢጣልያን፣
በፈረንሳይና በእንግሊዝ ቅኝ ገዢዎች ሥር የነበሩትን ኬንያኖችንና ሱዳኖችን፣ ሱማሌዎችንና ኤርትራዉያንን ማየት ብቻ ይበቃል። በኢትዮጵያ ምድር
ላይ ኢትዮጵያውያን በነጮች ለጋብቻ ሲለመኑና በብዛትም ሲጋቡ፣ በነዚህ አገሮች ግን የሕልም እንጀራቸው እንደነበር ድፍኑ ዓለም ያውቀዋል። ሌላው
ቀርቶ ደፍረው በማየታቸው እንኳን እስከሞት ድረስ ከፍተኛ ቅጣት እንደተቀጡ የሚያሳዩ ሰፊ ማስረጃዎች አሉ።
በዚህ አንጻር ጥሬ ሰው ብቻ ነው ያፄ ምኒልክን ሥራ ከቅኝ ግዛት ጋር የሚያመሳስለው። አፄ ምኒልክ ልጆቻቸውን የዳሩት በጦር ሜዳ አሸንፈው
ላስገበሩት ባላባቶች ሲሆን፣ ባለሟሎቻቸው ደግሞ አብዛኞቹ ድል ተመትተው ምርኮኞቻቸው የነበሩ ሰዎች ናቸው። ከነዚህም አብዛኞቹ ከኢምንትነት
ተነሥተው በአገርና በዓለም ደረጃ ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል። ይኸንን በመረዳት ነው አፈ-ታሪክ ፊታዉራሪ ሀብተጊዮርጊስና ደጃች ባልቻ (ታሪኩ
እንደሰው ይቀያየራል) ድል የተመቱበትን ቦታ ደርሰው፣ አንዱ ለሌላው “ይኸ እኮ የተማረክንበት ሰፈር ነው” ቢል፣ አንደኛው ቀበል አድርጎ፣
“የተማረክንበት ሳይሆን፣ የተባረክንበት ነው ብትል ይሻላል” ሲል መለሰለት የሚለው።
አንድነትን ከመፍጠራቸው በፊት፣ ከላይ እንዳየነው፣ በየቦታው ይገዛ የነበረው የባላባቶች መንግሥት፣ የራሱን ሕዝብ ከታጐረበት ክልሉ ውስጥ
እንዳይወጣ ሲያስገድድ፣ ከሌላው አካባቢ ወደሱ አገር የሚገባውን ደግሞ ብዙውን ጊዜ ለባርነት ስለሚፈለግ ተመልሶ ካገሩ እንዳይወጣ ይከለክል
ነበር። አፄ ምኒልክ የኢትዮጵያን ሕዝብ ከዚህ ሁሉ የክልል መንግሥት አሰቃቂ ጭቈናና እሰር ነፃ አስወጥተው፣ በወደደበት እንደፈለገ እንዲኖር አደረጉ።
ልማዳቸውንም አንለቅም ላሉት እንደነጂማ ዐይነቶቹ ባላባቶች ደግሞ፣ “ማንም ሰው እወደደበት ቦታ ላይ ይኖራል እንጂ … በምንም መልክ ሊትይዘው
አይገባም፤ ድኻው እወደደው፣ እተመቸው ቦታ ይደር” ብለው የሰጡት ትእዛዝ ማንኛዉም የቅኝ ገዢ ያራምድ ከነበረው መርህ ጋር በጣም ተፃርራሪ
ነበር ማለት ይቻላል።
Page 8 of 15
ይልቅስ አፄ ምኒልክ ያደረጉት ታላቅ ሥራ ቢኖር፣ በየቦታው በነዚህ አምባገነን ባላባቶቻቸውና፣ ንጉሥ ነን ባዮች ገዢዎቻቸው ሥር፣ እንደእስረኞች
ከጠባቡ ግዛታቸው ውስጥ ታጉረው፣ በሚዘገንን ጭቈና ይማቅቁ የነበሩትን ኅብረተ-ሰቦች ነፃ አውጥተዋቸው፣ ባሰኛቸው ቦታ እንዲኖሩ፣ የመላዋን
ኢትዮጵያን ምድር ሀብታቸው ማድረጋቸው ነው። በቅርብ ጊዜ፣ አንዳንድ የጐሣ ጽንፈኞች አፄ ምኒልክ ያዋሀዷት ኢትዮጵያ “የኅብረተ-ሰቦች እስር-ቤት
ናት” እያሉ መስበክ ጀምረዋል። ታሪክን ባያውቁት ነው እንጂ እውነቱ ግን በባላባቶች ክልል ውስጥ ታስሮ የነበረውን ሕዝብ ነፃነት አቀናጀውለት፣
በፈለገበት ሄዶ እንዲኖርና፣ በሚሻው ሙያ እንዲሰማራ፣ ሕልሙን እውን እንዲያደርግ ሰፊ አገር ገንዘቡ አደርገው በእጁ ሰጥተውለታል።
አፄ ምኒልክ የሚወቀሱት ኢትዮጵያን በጦር ኀይል መልሰው አንድ ማድረጋቸው ከሆነ፣ ማንም መንግሥት አዲስም ሆነ ፈራርሶ የነበረው አንድም
ሳይቀር በሙሉ የተፈጠረው በጦር ኀይል ነው። በሕዝብ ስምምነትና ፍቅር የተቋቋመ መንግሥት በታሪክ የለም፤ ታይቶም አይታወቅም። አለ የሚል
በቅዠት ዓለም የሚኖር ብቻ ነው። ምኒልክም ሰው እንደመሆናቸው ሥራቸው የተከተለው ይኸንኑ ሕግ ነው። ከተራ ሰው የሚለዩት ባስተዋይነታቸውና
አርቆ በማየታቸው ነው።
መንግሥታት የሚቋቋሙት ደግሞ እንደሳቸው ባሉት አሻግሮና አርቆ ማየት ችሎታ ባላቸው ሰዎች ሲሆን፣ እነሱም ባንድ ታሪካዊ ተጨባጭ ሁናቴ
ተመሥርተውና፣ ጊዜውንና አጋጠምኝን በመጠቀም ነው። ለዚህም አሁን የሚናደንቃቸው መንግሥታት እንዴት አንደመጡ ማየት ይበቃል። ጥቂቶቹን
ልጥቀስ። ኀያሉና ገናናው የሮም መንግሥት ሲወድቅ፣ ፈራርሳ በተለያዩና፣ የርስ በርስ ጦርነት ዋና መለዮአቸው በሆኑ፣ የጐሣ ባላባቶችና መንግሥታት
ትገዛ የነበረችዉ ኢጣልያ፣ ጥንት በሮም እንዳንድ አገር ሁና መተዳደሯን መሠረት አድርጋ ነው፣ ከአንድ ሺ ሦስት መቶ ዘጠና አምስት ዓመታት በኋላ
እንደገና ተመልሳ የተቋቋመችው። እሥራኤል በቅዱስ መጽሐፍ ታሪክ ተመሥርታ ነው፣ በፈረሰችው በሁለት ሺ ገደማ ዓመቷ የተፈጠረችው። ጀርመን
ሦስት ሺ ከሚያክሉና ርስ በርስ ከሚፋጁ የጐሣ ባላባቶች በፈረንጅ አቈጣጠር በ1871 ዓ. ም. አንድ አገር የሆነችው ከኢምንት ተነሥታ ነው፤ ከዚያ
በፊት ጀርመን የተባለ አገር በታሪክ አልነበረም። አንድነቱን የመፍጠሩ ሥራ ለዘመናት በሰላም ቢሞከር ከንቱ ሁኖ ቀረ። በመጨረሻ ጀርመን ተዋሂዳ
ዛሬ በዓለም የሚትደነቅ አንድ ታላቅ ሀገር ለመሆን የበቃቸው፣ ያኔ የፕሩሲያ መሪ የነበረው ኦቶ ቢስማርክ፣ “በብረትና በደም” ከሚለው መፈክሩ
ተነሥቶ ከጐረቤቱ መንግሥታት ጋር ወዶ ባጫጫረው የጦርነት ኀይልና ባፋሰሰው ደም ነው።
ምኒልክ ግን አንድነቷ በተናደው በሁለት መቶ ያህል ዓመት ጊዜ ውስጥ ብቻ ነው ኢትዮጵያን መልሰው ያዋሀዷት። አጋጠመኙ የአውሮጳ አምባገነን
መንግሥታት አፍሪቃን ቅኝ ግዛታችው ለማድረግ መቀራመት ነበር። የአፄ ምኒልክ ዋና ሥጋታቸው ኢትዮጵያን የከበቧት አውሮጳውያን፣
ከአፍንጫቸውና ከሆዳቸው ባሻገር አልፈው ማሰብ የማይችሉ ባላባቶችን፣ በስጦታና በገንዘብ በማባበል፣ግዛቶቿን እየቈራረሱ እየያዙ ሰለነበር፣
ኢትዮጵያን አንድ ለማድረግ የወሰኑት ይኸንኑ ድርጊት ለማቆም ነው። ስለዚህም በባላባቶች እጅ ወድቀው የነበሩትን ግዛቶቿን መልሰው ከአንድ
ማእከላዊ መንግሥት ሥር በማድረግ ታደጓቸው። በዚህም ሥራቸው ማንኛዉም አእምሮ ያለው ኢትዮጵያዊ መኲራት ይገበዋል። እዚህ ላይ መረሳት
የሌለበት ነገር ቢኖር፣ ኢትዮጵያዉያን እንደአብዛኞቹ የዓለም አገሮች አንድነታቸው በባዕድ ተሠርቶ አልተሰጣቸውም። ምንም ጊዜ ቢሆን ራሳቸው
የታሪካቸው ሠሪዎች እንጂ ተቀባዮች ሁነው አያውቁም። ፍጡር እንደመሆናቸው መጠን ርስበርስ ቢጣሉም፣ አለመስማማታቸውን በመጠቀም
በታሪካቸውና በሀገራቸው ጣልቃ ሊገባባቸው የሞከረውን ግን ከመሪያቸው ጐን ተሰልፈው ተባብረው አጥቅተውታል።
አንዳንድ የፖለቲካ ጮሌዎች ነን ባዮች(አሁን በሥልጣን ያለውን መንግሥት ጭምር) አፄ ምኒልክ በአውሮጳውያን ኢምፔርያሊስቶች (ቄሳራዊ) ኀይሎች
ተረድተው በኢትዮጵያ ነፃ የነበሩትን አገሮችና መንግሥታት በቅኝ-ግዛትነት ያዙ እያሉ ይሰብካሉ። በጣም የሚገርመው ዛሬ አገሪቷን እየገዛ ያለው
መንግሥት ደፍሮ እንደዚህ ማለቱ ነው። ዝንጀሮ የራሷን ቂጥ ቲታ የሌላውን መልከ-ጥፉ ነው ትላለች እንደሚሉት ዐይነት ነው። አንደኛ፣ ሁሉም
እንደሚያውቀው፣ የአሁኑ መንግሥት ከጫካ ውስጥ ወጥቶ ወደአፄ ምኒልክ ቤተ-መንግሥት እየገሠገሠ ሊገባ የበቃውና፣ ድፍኑ ዓለም
እንደሚመሰክረው ሕዝቡን ረግጦ በጭካኔ እየገዛ ያለው፣ ራሱ ባመረተው መሣርያና በሠራው ጦር እንዳልሆነ የአደባባይ ምሥጢር ነው። ባይሆን አፄ
ምኒልክ፣ ጊዜውና ሁናቴው አልፈቀደላቸውም እንጂ፣ አገሪቷ በመሣርያም ቢሆን የውጭ አገር ጥገኛ ሁና እንዳትቀር የራሷን መሣርያ እንዲታመርት
ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል። ሁለተኛ፣ ኢትዮጵያ ነፃነቷንና ህልውናዋን ለመጠበቅ፣ የጥንት ግዛቶቿን ለባዕድ አሳልፋ ላለመስጠት ሲትል፣ ባሕር ጥሰው
ከመጡባት ከቄሳራውያን መንግሥታት ከፍተኛ ግብግብ ውስጥ ገባች እንጂ የማንንም መሬት አልወሰደችም። እነዚህን ግዛቶቿን መልሳ ባትይዛቸው
ኖሮ፣ በቄሳራውያኑ እጅ በወደቁና የራሷንም ህልውና ባጣች። ይኸ የሚያጠራጥር አይደለም።
አፄ ምኒልክ ያዋሀዷቸው አገሮች ከጥንት ሲወርድ ሲዋረድ እስከጥቂት መቶ ዓመታት በፊት የኢትዮጵያ ግዛቶቿ የነበሩ ስለመሆናችው ሰፊ ማስረጃ አለ።
ይልቅስ በላይ እንዳየነው፣ ከዚያም እንደሚሰፉና አሁን እውስጧ ያልተከተቱ እንዳሉ የሚደግፉ ብዙ የታሪክ ሰነዶች ይመሰክራሉ። እዚህ ለምሳሌ
ያህል፣ ላመሉ ብቻ ልጥቀስ። የጥንቱን ትተን የቅርቡን ብቻ እንኳን ብንመለከት፣ በዐሥራ ስድስተኛው ዘመን ከግራኝ ወረራ በፊት ለስድስት ዓመት
(1520-1526) በኢትዮጵያ የኖረው የፖርቱጋሉ ፍራንቸስኮ አልቫረስ በጻፈው መሠረት የኢትዮጵያ የመሬት ሰፋት ከዛሬው ይበልጣል። በሱ አባባል፣
የኢትዮጵያውያን “ግዛት ሰፊ ነው። በቀይ ባሕር ጠረፍ ካለው ከታላቁ ወደባቸው ከቢሊ ተነሥቶ፣ ወደውስጥ ለሚጓዝ፣ የአዳልን ምድር አልፎ ሐድያን
ይጨምራል። በሕንድ ውቅያኖስ ደግሞ ሞጋዲሾ ይደርሳል… በጣም ሰፊና ሀብታም አገር አላቸው።” ስለግራኝ ወረራ በአጠገቡ ሁኖ ያየውና በሰፊው
የጻፈው፣ ሺሐብ አል-ዲን ኢትዮጵያን ስለማስገበር በሚለው መጽሐፉ ይኸንን የፍራንቸስኮን ጽሑፍ ያጸድቃል። በተጨማሪ ከግራኝ ወረራ በኋላ
ስለኦሮሞ ጐሦች ፍልሰት የጻፈው ታላቁ የኢትዮጵያ ደራሲ፣ መነኲሴው አባ ባሕርይ ንብረቱን ተዘርፎ በሰበቡ አካባቢዉን ሊለቅ የተገደደው በዛሬው
ገሙ ጎፋ ይኖር እንደነበር እናዉቃለን። ገሙ ጎፋ ደግሞ አባ ባሕርይን የመሰለ ሊቅ የሚኖርባት አገር ከነበረች፣ በቀለም ትምህርት የተራቀቁ ገዳማትና
አድባራት እንደነበሯት አይጠረጠርም። ይኸም ሊሆን የሚችለው አገሩ የኢትዮጵያ ግዛት ቢሆን ነው። በነዚህ በጠቀስናቸው ሦስቱ ጸሓፊዎች መሠረት፣
የኢትዮጵያ ወሰን በምሥራቅ የባሕረ-ኤርትራ ጠረፍ ሁኖ ሞቃዲሾን፣ በምዕራብ ደግሞ ገሙ ጐፋን ያጠቀልል እንደነበር በጥያቄ ዉስጥ የሚያስገባ
የለም።
ምኒልክ እንግዴህ ከጥንት ከአክሱማውያን ጊዜ ጀምሮ የኢትዮጵያ ግዛት እስከነበረው እስከሞቃዲሾ ድረስ ማስፋፋት ነበረባቸው። ግን ጊዜውና የነበረው
ዐቅማቸው አልፈቀደላቸዉም። ዋናው ነጥብ ግን አፄ ምኒልክ የሠሩት ሥራ፣ በግራኝ ወረራ ምክንያት ማእከላዊ መንግሥት በመድከሙ ፣ከቊጥጥሩ
ሥር የወጡትን ግን ከአክሱማውያን ዘመን ጀምሮ የኢትዮጵያ ግዛቶች የነበሩትን አገሮች፣ ከመላ ጐደል መልሰው ወደአንድነት ማምጣታቸው፣ በምንም Page 9 of 15
መልክ እንደቅኝ ግዛት ሁኖ መታየት አይችልም ነው። ከላይ የጠቀስናቸው ከሺ ዓመታት በላይ ፈርሶ ከቆየ በኋላ የተከናወነው የኢጣሊያን፣ አንዲሁም
ከኢምንት የተፈጠረው የጀርመን አንድነት፣ እንደቅኝ ግዛትነት ካልተፈረጀ፣ ከሦስቶ መቶ ዓመት በማያክል የጊዜ ገደብ ልዩነት የተፈጸመዉን የአፄ
ምኒልክን የውህደት ሥራ የቅኝ ግዛት ነው ማለት ፍርደ-ገምደልነት ብቻ ሳይሆን ዘረኝነትም በራስ-አለመተማመንም ነው ቢባል ሐሰት አይሆንም።
ማዕከላዊ መንግሥትን አድክመው ኢትዮጵያ ርስበርስ በሚበላሉና፣ ግዛቶቻቸዋንም በሚያተራምሱ ባላባቶች እንዲትከፋፈል፣ ከፍተኛ ሚና የተጫወቱት
የግራኛና የኦሮሞ ወረራ ናቸው ቢባል ስሕተት አይደለም። ግን አንድ አጥብቀን መረዳት ያለብን ነገር አለ። አሕመድ በን ኢብራሂም አል-ጋዚ (ዘ[ብሔረ]
ጋዚ) በሚል ስም የሚጠሩት ግራኝም ሆኑ ኦሮሞ ሁለቱም ኢትዮጵያውያን ናቸው። ግራኝ ካፄ ምኒልክ የሚለዩት ከአላፊውና ከጊዜያዊው የገዛ ራሳቸው
ጥቅም አልፈውና አርቀው ማየት አለመቻላቸውና፣ አገሪቷን በጥበብና በፍቅር በማስተዳደር ፈንታ የዝርፍያ፣ የንጥቂያና የግድያ ሜዳ በማድረጋቸው
ነው። አሕመድ በን ኢብራሂም አል-ጋዚ (ዘ[ብሔረ] ጋዚ) ታላቅና ጀግና ኢትዮጵያዊ የጦር መሪ መሆናቸው አይጠረጠርም። ሥልጣን የያዙት፣ ወደሩቁ
ሳንሄድ፣ ልክ በቅርብ ታሪካቸን ውስጥ እንዳየነው ሁሉ፣ እንደአፄ ቴዎድሮስና እንደአፄ ዮሐንስ፣ እጅግ በጣም ብዙ ጦር ሠራዊት ያሏቸውን
ባላንጦቻቸውን ድል በማድረግ ነው።
በዚህ ረገድ የውጭ ሊቃውንትና ሁሌዬ የእነሱን ፈር ከመከተል በስተቀር ሌላ ለየት ያለ የግላቸው አሳብ የማመንጨት ችሎታ ያጡት ብዙ የኢትዮጵያ
የታሪክ ምሁራን፣ የግራኝን ወረራ እንደሃይማኖት ጦርነት ወይንም እንደባዕድ አገር ጥቃት አድርገው ይመለከቱታል። እኔ ግን ይኸንን አስተያየት በፍጹም
አልጋራም። ሐረር የኢትዮጵያ ግዛት ከነበረና፣ እንደሌሎቹ ግዛቶች ለማዕከላዊ መንግሥት የሚገብር መሆኑ ከታወቀ፣ ጦርነቱ የሥልጣን ትግል እንጂ፣
የባዕድ ወረራ አለመሆኑ ግልጥ ነው። ከአፄ አሕመድ ጋር የተዋጉት ሰሜኖቹ ብቻ አይደሉም። ታሪካቸው እንደሚነግረን ከሆነ ሐረርም፣ ባሌም፣
አሩሲም፣ ሌሎችም እንደጉራጌ፣ ከምባታና ሐዲያም የመሳሰሉት በደቡብና በምዕራብ ያሉ አገሮች ተዋግተውዋቸዋል። ሃይማኖት እንደመሣርያና ሽፋን
ሁኖ ቢያገለግልም፣ የአፄው ዋናው ዓላማቸው ግን የተለመደው የሥልጣን ሽኩቻ ነበር።
አፄ አሕመድ በድል ያገኙትን መንግሥት “የኢትዮጵያ [የሐበሻ] መንግሥት” ብለው ማስተዳደራቸው ራሱ ጦርነቱ የሥልጣን መሆኑን
ያመለክታል፤ ከላይ እንዳልኹ አብዛኞቹ የአገራችን ታሪክ ምሁራን፣ የውጭ አገሮቹ የታሪክ ሊቃውንት ስለኢትዮጵያ የጻፉትን ፈለግ
በመከተልና፣ የተሳሳተ አመለካከታቸውን በማጠናከር፣ ክርስቲያንነትንና ኢትዮጵያዊነትን አዋሂደው ያያሉ። ሐቁ ግን እንደዚህ
አይደለም። ሥልጣኑን ክርስቲያን የሆኑት ነገሥታት ይቈጣጠሩት እንጂ፣ ኢትዮጵያ የተባለው መንግሥትና አገር ከጥንት ጀምሮ
በውስጡ የተለያየ ቋንቋና እምነት ያለውን ሕዝብ ያካተተ ነው። የነገሥታቱ ታሪክም ሆነ ግዙፉ ተጨባጭ ሁናቴ የሚያጠናክረው፣
ኢትዮጵያ በጣም ተወራራሽ እምነት፣ ባህልና ቋንቋ ባላት ሕዝብ የተጐነጐነች አገር መሆኗን ነው። በውስጧ የክርስቲያን፤ የእስልምና፣
የፈላሻና የጣዖትን እምነት የሚከታተሉት አሕዛብ ሁሌዬ እንደኖሩ ናቸው። አፄ ምኒልክም በቃላቸዉና ባስተዳደራቸው መላልሰው
በቀይ ቀለማቸው በአንበሳ ማኅተማቸው ይፋ ያደረጉት አገሪቷ የተለያየ እምነት ተከታይ ሕዝብ እንዳላት ነው።
ንጉሠ-ነገሥት አሕመድ ኢብራሂም በጦር ሜዳ ባለጀብዱ ቢሆኑም፣ ባስተዳደር ግን እንደአፄ ምኒልክ ታላቅነታቸውን ሳይሆን ምን ያህል ቅሌታምና
ደካማ መሆናቸውን ነው ያሳዩት። በጦር ሜዳ የተጐናፀፉትን ድል የተጠቀሙት፣ አገሩን በፍቅር፣ በቅንነትና በፍትሕ እንደማስተዳደር፣ ለራሳቸውና
ለተከተያዮቻቸው ብቻ የዘረፋና የግድያ ነው ያደረጉት። በየሄዱበት ታላላቅና ብርቅ የነበሩ የታሪክ ቅርሶችን አጠፉ፤ ጥንታዊነት ያላቸውን ቤተ-
ክርስቲያኖችንና ገዳማትን የኪነ-ጥበብ፣ የፍልስፍናና የምርምር ጥናቶች ከነበራቸው ብርቅ ከሆኑ ብራናዎቻቸው ጋር አቃጠሉ፤ የወርቅና የብር
ንብረቶቻቸውንና ቅርሳቸውን ዘረፉ፤ መነኮሳቱንና ካህናቱን አላንዳች ምሕረትና ርኅራኄ በጭካኔ ገደሉ። አገሪቷን ታሪክ የሌላት ድኃደግ አድርጓት
ወዳንድ ዐምስት መቶ ዓመታት ወደኋላ መለሷት። የሠሩት ተግባር ከጠላትም ሆነ፣ ከማንም የአገር መሪና የእስላም ሃይማኖት ተከታይ የሚጠበቅ
አልነበረም። በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ እንዲህ ዐይነት ያስተዳደር ብቃትና ችሎታ ያጣ፣ ቅለታምና ግፈኛ መሪ በመሆን የመጀመርያውን ቦታ ይያዙ እንጂ
በመጠኑም ቢሆን የሚመስሏቸውን አያጡም። አሁንም ቢሆን አሉ ማለት ይቻላል።
አፄ ምኒልክ ክርስቲያን ቢሆኑም፣ የሠሩት ሥራና የተከተሉት ያስተዳደር መርህ የተንተራሰሰው በሃይማኖት እምነት ላይ አይደለም፤ ፍትሕንና ቅንነትን፣
ያገርን ጥቅምና የየሕዝቡን ባህል መሠረት አድርጎ ነው። ወደኋላ ቀርነት ካለውና፣ የአገርን ጥቅም የሚፃረር ሁኖ ከታያቸው ደግሞ፣ ባህልንና እምነትን
በዘዴ የሚዋጉ ሰው ነበሩ። የወሎው ንጉሥ ኢማም መሐመድ ዓሊ (የኋላው ራስ ሚካኤል) ከገበረላቸው በኋላ፣ ታላቅ ግብር አዘጋጅተው፣ አብረው
ሲበሉ የተመለከተ፣ እንደዚህ ዐይነት ጉድ ዐይቶ የማያውቅ ሠራዊታቸው ተበሳጭቶ ቢያጒረመርም፣ “የወሎ ሰው [እግዚአብሔር] አሁን የሰጠንን አገር
አብረው የሚገዙ፣ በኋላም በርሱ ቸርነት መንግሥተ ሰማያት አብረውን የሚገቡ [ወንድሞቻችን] ናቸውና አትጥሉብኝ። … ወሎን በፍቅርና በትሕትና
እየሳብሁ አሁን ለዚህ ዓለም ግዛት፣ በኋላም በክርስቶስ ቸርነት፣ ለመንግሥተ ሰማያት ለማብቃት እንጂ ለመዝረፍና ለማጥቃት አልመጣሁም። … አሳቤ
ዘወትር በጐ ነው አትክፉኝ… አላሳፈርኳችሁምና እናንተም እንግዳዬን በመሸኘት አታሳፍሩኝ።” ብለው ነው የተበጣበጠውን ሠራዊታቸውን
አሳምነውኑት ያረጋጉት። ቈይተው ያገራቸውን ሕዝብ ይበልጥ ይግረምህ ሲሉ ደግሞ፣ ብላቴን ጌታ ኅሩይ እንደገለጹት፣ ለዚሁ “ላልተጠመቀ እስላም”
ኢማም መሐመድ ዓሊ፣ “የተጠመቀችውን ክርስቲያን” ልጃቸውን ወይዜሮ ሸዋረጋን ዳሩለት። በዚያው ልክ ደግሞ ንጉሠ-ነገሥቱ በማንም የኢትዮጵያ
ዜጋ ላይ የባዕድ እምነት ሆነ ቋንቋ በጒልበት እንዲጫንበት አይወዱም ነበር። የጅማው አባ ጅፋር በባርያ ፈንጋይነት ከገነነው ከዛንዚባር መንግሥት ጋር
ግንኙነት ፈጥሮ ሲያበቃ፣ የግዛቱ ቋንቋ ዐረብኛ፣ ነዋሪዉና መጤው ደግሞ በግድ እስላም እንዲሆን ቢያስገድድ፣ “አገሩን የዐረብ አገር ማድረግህ
እንደሆነ፣ ቊርጡን ንገረኛና፣ ውላችን ይፍረስ” ብለው ነው ያስጠነቀቁት።
ያፄ ምኒልክ መላ አስተዳደራቸው የተከተለው መርህ እንደቀድሞቹ ነገሥታት የሃይማኖትን ገለልተኝነት በመጠበቅ ነው። ይኸም ኢትዮጵያን
በክርስቲያንም ሆነ በእስላም መሪዎች ከሚተዳደሩት አገሮች በጣም ይለያታል። ለምሳሌ ያህል በዐሥራ ስድስተኛ ዘመነ ምሕረት ላይ፣ የአውሮጳ
ነገሥታት በሙሉ ሕዝባችን ነው ብለው የሚጠሩት የራሳቸውን ሃይማኖት የሚከተለውን ብቻ በመሆኑ፣ ክርስቲያኑን ሕዝብ ካቶሊክና ፕሮተስታንት
እያሉ ለያይተውት ሲያጨፋጭፉና፣ ከየሃይማኖታቸው ግዛት ሲያባርሩ፣ ከነሱ ሦስት መቶ ዓመት ቀደም ብሎ የኖረው ክርስቲያኑ የኢትዮጵያ ንጉሥ-
ነገሥት ዐምደ-ጽዮን ግን “እኔ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚኖሩ የመላው እስላሞች ንጉሥ ነኝ” በማለት፣ አገሪቱ ሳታዳላ ሁሉንም እምነት አስተናጋጅ መሆኗን
ይገልጥ ነበር። Page 10 of 15
አፄ ምኒልክ፣ ከግራኝም ሆነ፣ የግራኝን አብነት በመከተል በንግሣቸው ዘመን እስላሙን ካሳደዱት ከባላንጣቸው ከአፄ ዮሐንስ በጣም ይለያሉ።
እንዲሁም ዘመናዊ መገናኛ ስልክና የባቡር ሐዲድ በሚያስገቡበት ጊዜ፣ የቤተ-ክህነት መሪዎች ቢቃወሟቸዉና፣ ሕዝቡም እንዲነሣባቸው ቢሞክሩ፣
በመኳንንቶታቸው ፊት ለጳጳሱ የሰጡት መልስ፣ እነዚህ ቅዠተኞች ሥራዬን ማደናቀፍ ካላቆሙ፣ ያለኝ ምርጫ ሃይማኖቴን መለወጤ ነው እስከማለት
ድረስ ከቤተ-ክህነቱም ከወግ-አጥባቂዎችና አክራሪዎች ጋር በጥብቅ መፋለማቸው የሳቸውም ሆነ የኢትዮጵያ ፖልቲካ ከሃይማኖት ነፃ መሆኑን
በአስተዳደራቸውም በአቋማቸዉም በግልጥ አሳይተዋል።
በቅርብ ጊዜ አበራ ቶላ የተባሉ ጸሓፊ “የኦሮሞ መስፋፋትና የምኒልክ በኀይል መያዝ ጨለማው ጐን በኢትዮጵያ6
” በሚል አርእስት አንድ ጽሑፍ
በኢትዮመዲያ” ዘግበዋል። ከመግቢያው ላይ ጠቅለል ባለ-መልኩ የሚናገሩት ታሪካዊ ድርጊቶች መጠነኛ እውነተኝነት ቢኖራቸውም፣ የኦሮሞ
መስፋፋትን ከአፄ ምኒልክ ማስገበር በማነፃፀር የሚናገሩት ሐተታ፣ ባሁን ወቅት በሰፊው የተሰራጨውን ተረት ከማስተጋባት በስተቀር፣ ጥልቀትና ቁም-
ነገረኝነት የለውም እላለሁ።
አንደኛ ኦሮሞም ሆነ ኦሮሞች የሚሉት ቃላት ራሳቸው ምን ማለት መሆናቸውን ደራሲው አብራርተው አይገልጡም። ኦሮሞ ማለት የድሮውን “ጋላ”
የሚለውን ቃል የሚተካ ከሆነ፣ ንግግሩ በሙሉ አከራካሪ ከመሆን አልፎ የጸሓፊውንም ዕውቀት ያስጠይቃል። “ጋላ” የሚለው ቃል መሠረታዊ
አመጣጡና ለመጀመርያ በጥቅም ላይ የዋለው በግዕዝ ቋንቋ ሥነ-ጽሑፍ ሲሆን፣ ትርጒሙ በተወሰነ የኑሮ ዐይነት የተሰማራ፣ ወይንም ያልተገረዘና
ክርስቲያን ያልሆነ ኅብረተ-ሰብን እንጂ፣ በቋንቋ ዝምድና የተሳሰረ፣ ወይንም በደምና በመወላለድ ያንድ ምንዝላት ወይንም ያንድ እንጅልሽ የሥጋው
ቊራጭ ያጥንቱ ፍላጭ የሆነ ሕዝብን አያመለክትም። ስለዚህም ነው ቃሉ ከግብፅ ምዕራብ ለሚኖረው በርበር፣ ለሱዳኑ ድንቃ፣ በኢትዮጵያም ውስጥ
ላሉት ለተለያዩት እንደነአፋርና፣ በኦሞ ወንዝ አካባቢ ለሚኖሩ ዐይነቶቹ ኅብረተ-ሰቦች በሙሉ ሲሰጥ የሚታየው።
ጸሓፊዎቹ “ጋላ” የሚለውን ቃል፣ እንደጠቅላላ መጠርያ ከመጠቀማቸው በፊት፣ የኅብረተ-ሰቡን ስም ጠቅሰው ሲያበቁ፣ ሁለዬ እንደመለዮው አድርገው
“የሚባል” የሚለውን ቃል ይጨምሩበታል። ለምሳሌ፣ ከግብፅ ቀጥሎ ከሚገኘው አገር (ከበስተምዕራቡ) መጥቶ በሰሜን ግብፅ ያለውን ገናናውን
የአስቄጥስን ገዳም ይዘርፍ የነበረውን የበርበርን ኅብረተሰብ ሲገልጥ፣ ጸሓፊው “በርበር” የሚባል “ጋላ” ይላል። በኢትዮጵያም ልክ እንደዚሁ “ቱለማ”
የሚባል “ጋላ”፣ “ከረዩ” የሚባል “ጋላ”፣ “ሜጫ” የሚባል “ጋላ” እያለ ነው የተለያየ የኅብረተ-ሰብን ክፍል የሚገልጠው። እነዚህ ኅብረተ-ሰቦች የሚጋሩት
ነገር የትውልድና የዘር ሳይሆን፣ ሰብአ-ትካትነትንና በዘረፋና በዘላንነት መኖርን፣ ወይንም የከረስተኑና የተገረዙ አለመሆናቸውን ነው። “በርበር፣
“ድንቃ”፣ “ሜጫ”፣ “ቱለማ” የሚሉት ቃላት የኅብረተ-ሰቡን ምንነት ሲገልጡ፣ “ጋላ” ግን የኑሯቸውን ዐይነት ነው የሚያሳየው። እነዚህ ዘላን
እንደመሆናቸው የተወሰነ መሬትና አካባቢ የላቸውም። ስለዚህም ነው ጸሓፊዎቹ ሌላውን በግብርና ተደላድሎ በተወሰነ መሬት ላይ የሚኖረውን ሕዝብ
በመሬቱ ስም፣ “የመተከል ምድር”፣ “የጋፋት ምድር” “የአማራ ምድር” ብለው ሲጠሯቸው፣ ለጋላ ሲሆን ግን የታወቀ “ምድር” የለውም ብለው በማሰብ፣
ወደ”መኖርያው” ፣ “ወደ አገሩ” ተመልሶ ሄደ የሚሉት። ለዚህም ነው ደግሞ ማዕከላዊው መንግሥት በሌላው ዐመፀኛ ነው በተባለ ሕዝብ ላይ
እስከ”ምድሩ” ድረስ ሄዶ ሲዘምትበት፣ በ”ጋላ” ላይ ግን ተመሳሳይ እርምጃ መውሰድ ይሳነው የነበረው።
ፍሬ ነገሬ “ኦሮሞ” ስለሚለው ቃል ሐተታ ሳይሆን፣ ዘውገኞች ስለዚሁ ኅብረተ-ሰብ የሚስብኩት ስብከት ልበ-ወለድና አንጃ ግራንጃ እንጂ ተጨባጭ
ማስረጃ እንደሌላቸው ለማስገንዘብ ነው። ሕዝቡ በባህልም ሆነ፣ በቋንቋና በዝርያ በፍጹም አይገናኝም። ኢትዮጵያን ከመውረሩ በፊት ሆነ፣ በአፄ
ምኒልክ መሪነት ኢትዮጵያ ተመልሳ እስከተዋሀደችበት ጊዜ ድረስ፣ አንድነት ያለው የኦሮሞ ሕዝብም ሆነ መንግሥት ከቶዉኑ አልነበረም፤ ኑሮም
አያውቅም። በኢትዮጵያ አንድነት ዋዜማ ላይ፣ ጥንት “ጋላ” በመባል የሚታወቀው ሕዝብ ራሱ፣ ዘላንነቱንና በዝርፍያ መኖሩን ትቶ በነገሥታቱ ጥረትና
በጊዜያዊ ሁናቴዎች መለወጥ፣ በየሰፈረበት ሁሉ በፍላጎቱ አካባቢውን መስሎ በግብርና መኖር ጀምሯል። በምሥራቅ፣ በደቡብ፣ በአዜብና በባሕር ያለው
የእስልምና ተከታይ ሆነ፤ በሰሜንና በምዕራብ እንደ ጐጃምና በጌምድር ባሉት አካባቢዎች የሰፈረው ደግሞ ወደኦርቶዶክስ እምነት ገባ። ኦርቶዶክስ
የሆነው ከማዕከላዊ መንግሥት ውስጥ ተዋቅሮ ከፍተኛ ሚና ሲጫወት፣ የወሎና የአዜቡ እስላም በበኩሉ ርስበርስ ጦርነት በሚፋጁ በተለያዩ ጥቃቅን
የባላባቶች መንግሥታት ቢጤ ተቋቋመ። አፄ ምኒልክ ናቸው በበርስበርስ ጦርነት ከመጨራርስ ያዳኗቸውና ሁሉንም እንደሌላው የኢትዮጵያ ኅብረተ-
ሰብ ወደውህደት አምጥተው በሰላምና በፍቅር እንዲኖር ያደረጉት።
አለቅጥ የሚደነቀው የጋዳውም ሥርዐት ቢሆን በአፍሪቃ ውስጥ በዚያ የሥልጣኔ ዕድገት ደረጃ ያሉት ብዙዎቹ ኅብረተ-ሰቦች ከመላ ጐደል የሚጋሩት
አወቃቀር ነው። ሥርዐቱ ሲመረምር አሳፍሪ እንጂ የሚደነቅ ሁኖ አይታይም። ለምን እንደዚህ እንዳልኩ ላስረዳ። የጋዳ ሥርዐት በደምሳሳው ሲታይ፣
የመዋቅሩ ቁልፍና ዋና ሊባል የሚቻለው ሉባ የተባለው ማዕርግ ወይንም ዕርከን ነው። ስለሉባነት በቅርቡ ያጠናውና በሥራ ላይ ያየው፣ አንድ የዐሥራ-
ሰባተኛ ዘመን ጸሓፊ በሚለው ከተመሠረትን፣ “ሉባነትን እስከሚያገኝ ድረስ የኅብረተ-ሰቡ አባል አይገዘርም ብቻ ሳይሆን፣ ልጅ እንኳ ቢወልድ
እንደወላጅ ሁኖ በሥነ-ሥርዐት በማሳደግ ፈንታ፣ እንደውሻ ቡችላ እውጭ ይጥለዋል። በዚህ ሹመት ላይ ባለ ጊዜ ውስጥ ሰው ካልገደለ ደግሞ፣
ጠጒሩን አይላጭም፤ የግድያ መለዮው ስለሆነ ጒቱም አያሳድግም፤ ታድያ የሞት ፍርድ እንደተፈረደበት ሰው ዘወትር እያለቀሰ፣ በሐዘን ውስጥ ተዘፍቆ
ይኖራል እንጂ።” ማንም በሠለጠነው በዛሬ ዘመን የሚኖር፣ ልብ ያለው ሰው፣ በዚህ ዐይነት ሥርዐት መኲራት ቀርቶ፣ የመደገፍ ስሜት እንኳ ቢያሳይ
ለሰው ህልውና እንደከፍተኛ ጠንቅ ሁኖ ስለሚታይ ጭንቅላቱን መመርመር፣ ከኅብረተ-ሰቡም መገለል ይኖርበታል ተብሎ ነው የሚታሰበው። በዚህ
የማይስማማ ካለ፣ እሱ ራሱ የአእምሮ ችግር እንዳለው ይቈጠራል።
እውነቱ ጋዳና ግድያ በቃላት ይለያዩ እንጂ ትርጒማቸው አንድ ነው። እጅና መዳብ ናቸው። ዝርፍያ የሥርዐቱ ዋና አንቀሳቃሽ ሞተርና ኀይል ነው።
ይኸንን ነው እንግዴህ ከዐሥራ ስድስተኛው ዘመነ ምሕረት ጀምሮ “ጋላ” የተባለው ኅብረተ-ሰብ በመላ ኢትዮጵያ ይፈጽም የነበረው። ይኸም ማለት
6
. Abera Tola, “Ethiopia: Dark side of Oromo Expansions and Menilek Conquests,” Ethiomedia, January
4, 2014. Page 11 of 15
በምቾትና በድሎት ይኖር ወደነበረው ኅብረተ-ሰብ ሊገድልና ሊዘርፍ ይዘምታል። የተዋጋው ሕዝብ ተሽንፎ ቢገኝ፣ በጅምላ በመጨፍጨፍ፣ የነፍሰ-
ጡሮች እናቶችን ሆድ በመዘርጠጥ፣ የደሙን ጥም ለማርካትና፤ የጀብዱን ሚርጋ ለማስቈጠር ሲል ራስ በመቊረጥ፤ አባለ-ዘር በመጒመድ ያለቀው
ሕዝብ ተቈጥሮ አያልቅም። የውጭ አገርም ሆኑ የኢትዮጵያ ጸሓፊዎች “ጋላ”ን በተመለከተ የሚስማሙበት ነገር ቢኖር በነዚህ ነጥቦች ላይ ነው።
እዚህ ላይ፣ ጥቂቶቹን ብቻ ላመሉ ልጥቀስ። በዐሥራ ስድስተኛ ዘመነ-ምሕረት ሁናቴውን በቅርቡ ካዩት የኢትዮጵያ ጸሓፊዎች ልጀምር። አገሩ “በጋላ
እጅ ተመዝብሮ በረኻና ጫካ በመሆኑ ከእንስሳና ከዱር አራዊት በስተቀር ሰውም ሆነ እርሻ በፍጹም የለበትም።” ቱላማ የሚባል ጋላ መጥቶ፣
“መንፈቁን ጐጃም” ምንም ሳያስቀር ደምስሶ አጠፋው፤ ሴቶችንና ከብትን ማረከ። የገደለው ሰው ቊጥር ስፍር የለዉም። “ጋላ ጐጃምን መውረር
ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ እንደዚህ የገደለበትና የማረከበት ጊዜ ከቶውኑ የለም።” ክርስቲያኑ ብቻ አይደለም ይኸ ዐይነት ዕልቂትና ጥፋት ከጋላ
የደረሰበት። ታዲያ ያመለጠ የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ አልነበረም ቢባል ሐሰት አይሆንም። ያኔ ሻንቅላ በመባል የሚታወቀው ሕዝብ ማእከላዊው
መንግሥት በአስቸኳይ እንዲደርስለት ያቀረበው ጩኸት፣ “የከብትና የሰው ምርኮ ወሰደብን፤ ስፍር ቊጥር የሌላቸውን ጀግኖቻችንን ገደለብን፤ የቀሩት
ጀግኖቻችን የሴት ፍርሀት ይዟቸዋልና፣ ጌታችን [ንጉሥ] ሆይ እንዲትታደገን ፈጥነህ ድረስልን” ነው የሚለው። ግድያው የአረመኔነት ሳይሆን የአውሬነት
ነው። ካልሰለበ፣ ጡት ካልቈረጠ፣ ሆድ ካልዘረጠጠ፣ ቸብቸቦ ካልሰበሰበ ስሜቱ አይቀሰቀስም። እነዚህ ድርጊቶች የጀብዱነቱና የታላቅነቱ ዋና
መግለጫውና መስፈርያው ነበሩና።
እንግዴህ የዛሬው “ኦሮሞ” የትላንትናው “ጋላ” ነው ካልን፣ በዚህ ስም የሚጠራው ኅብረተ-ሰብ በኢትዮጵያና በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ያደረሰው ጉዳትና
ጥቃት፣ የፈጸመው የሰውና የከብት ዕልቂት፣ የንብረትና የታሪክ ቅርስ ጥፋት፣ በሰው አንደበት ተገልጾ፣ በመጻሕፍት ተጽፎ አያልቅም ማለት ይቻላል።
ከግራኝ ብዝበዛ ያመለጡት ቤተ-ክርስቲያኖችና ቤተመንግሥቶች እውስጣቸው ከነበሩት የታሪክ ቅርሶችና መጻሕፍቶች ጋር ድራሻቸው ጠፍቷል።
ይኸንን እንደሰደድ እሳት ባገሩ ላይ ያደርስ የነበረውን ዕልቂት አይተው ነው እንግዴህ፣ በመጤ ሃይማኖታቸው ሰበብ ከኢትዮጵያ የተባረሩት ካቶሊኮች፣
ኦሮሞችን አምላክ ኢትዮጵያውያንን በነሱ ላይ በፈጸሙት ግፍ ተቈጥቶ ሊበቀል ሲል የላከው “የእግዚአብሔር መቅሠፍት” ነው ብለው የተረጐሙት።
እንግዴህ እንደዚህ የመሰለውን የአውሬነት ተግባር ከአፄ ምኒልክ ድርጊት ጋር ማነጻጸር ሚዛነ-ቢስነት ብቻ ሳይሆን ፍርደ-ገምደልነትም ነው ማለት
ይቻላል። ታሪክ አይደግፈውም፤ ጤናማም ሰው አያደርገዉም። ከዚያም አልፎ ተርፎ፣ ታሪክ የሚነግረን ያለው፣ ሺ ኪሎሜትር ሰንጥቆ ሄዶ የሌላውን
ኅብረተ-ሰብ መሬት ወርሮ የያዘውን ሕዝብ፣ አፄ ምኒልክ በግፍ ቅኝ ግዛት አደረጉት ማለትም እውነትን ከማፋለስና ዘበት ከመናገር በስተቀር ሌላ ቁም-
ነገር አይኖረውም።
ይኸ እንዳለ ሁኖ ከጥፋትም አንዳንድ ጥሩ ነገር አይታጣም። ኦሮሞች አገሩን በግድያና በዘረፋ ቢያራቆቱትም፣ ወንዶችንና አርጊቶችን በሚዘገንን ሁናቴ
ጨፍጭፈው ቢገድሉም፣ ሴቶችንና ልጆችን ከአገሩ ከብት ጋር ማርከው መውሰድ ልማዳቸው ነበር። ዕድለ-ቢሶቹ ሴቶች ከማራኪዎቻቸው ልጆች
ይወልዱ፣ የተማረኩትም ልጆች በተራቸው አድገው ከብሔረ-ሰቡ ጋር ይጋቡ ነበርና፣ ኦሮሞች ወደድንም ጠላንም፣ የኢትዮጵያን ሕዝብ
አቀያይጠዉታል። ስለዚህ ዛሬ ማንም ሰው አፉን ከፍቶ የኔ ዘር ንጹሕ ነው ሊል በፍጹም አይችልም። የሚልም ካለ ወይ ውሸታም፤ ካልሆነ ደግሞ
ትዝብትንና ይሉኝታን የማይፈራ ውሸታምና የሚናገረውን የማያውቅ መሆን አለበት።
እንግዴህ የኢትዮጵያዊ ፍቹ በቃሉ ትርጒም መሠረት፣ “ፊቱ የጠቈረ” ብቻ ሳይሆን፣ በተጨማሪ በዘሩ “የተከለሰ ቅይጥ” መሆንንም ያመለክታል።
መለዮውም ጥቊርነትና ድቃላነት ነው። አንድ የታሪካችን ምሁር የሆነ ኢጣልያናዊ ኢትዮጵያን “የሕዝብ ሙዝዩም” ይላታል። ሐቁ ግን አገሪቷ ብቻ
ሳትሆን፣ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊም ጭምር “የሕዝብ ጥርቅማጥርቅም” ነው፤ በደሙ ውስጥ አብዛኞቹ የኢትዮጵያ ነገዶች አሉበት ማለት ይቻላል።
ለዚህም ያበቃው የማዕከላዊ መንግሥት መፍረስና የኦሮሞ ወረራ ሲሆን፣ ወረራው የኢትዮጵያን ሕዝብ አድሶታል፤ በታሪክ፣ በደም፣ በቋንቋ፣ በባህል
አስተሳስሮ እንደሰርገኛ ጤፍ ወንድማሞችና እኅትማሞች አድርጓል። ወይንም ከዚያም በተሻለ አባባል ለመግለጥ፣ የሥጋ ቊራጭ፣ ያጥንት ፍላጭ ሁኖ
ደም በደም ተቀላቅሏል፡ በዚህ መልክ የተዋሀደ ሕዝብ ነው እንግዴህ ተመልሶ ዘመናዊቷን ኢትዮጵያን በምኒልክ መሪነት ያዋሀዳት። በዚህ የተቀደሰ
ሥራ፣ በፊታውራሪነት የመሩት ደግሞ ኦሮሞቹ ራሳቸው ናቸው።
እንደዚህ ያልኩበት ምክንያት ግልጽ ነው። አፄ ምኒልክ ያደጉት ከኦሮሞች ጋር እየተጯጯሁ ሲሆን፣ አለኦሮሞች ድጋፍ፣ አለነሱ ኀይልና ሠራዊት ከአፄ
ቴዎድሮስም እጅ ማምለጥም ሆነ፣ ወዳባታቸው ግዛት ገብተው መንገሥ፣ ዘመናዊቷንም ኢትዮጵያን ማዋሀድ አጠያያቂ በሆነ። ወደደቡብ፣ ምዕራብና
ባሕር የዘመተው ሠራዊት ከጦር መሪ እስከዝርዝር ድረስ ኦሮሞ ነበር ማለት ይቻላል። እንዲህ ስል የሌሎቹን ሚና ማሳነሴ ወይንም ማጥላላቴ ሳይሆን
ከራስ ጐበና ጀምሮ እስከተራው ኦሮሞ ድረስ በኢትዮጵያ ምድር በተወሰነ አካባቢ ባገሪቷ ያንድነት ግንባታ ያደረጉትን አስተዋጽኦ ለማጉላት ነው።
እውነት ነው፣ ሌሎችም እንደየዐቅማቸው ድርሻቸውን በጋራ ተዋጥተዋል። ይኸም ቢሆን ግልጥ ነው፤ ግን ላመሉ ነካ ላድርገው።
አፄ ምኒልክ በተዋሀደች ኢትዮጵያ ላይ ለመንገሥ የበቁት የመጀመርያው ንጉሠ-ነገሥት ይሁኑ እንጂ፣ አብዛኛው የውህደት ሥራ የተከናወነው በአፄ
ዮሐንስ ሥር መሆኑን መርሳት አይገባም። በአፄ ዮሐንስ መሪነት፣ ሰሜኑን ንጉሠ-ነገሥቱ ራሳቸው፣ ምዕራቡን ንጉሥ ተክለ-ሃይማኖት፣ ከመኻል ደግሞ
ሁነው ምሥራቁን፣ ደቡብንና ምዕራቡን፣ ባሕሩንና አዜቡን ንጉሥ ምኒልክ ሁነው ነው በመተባበር የአፄ ቴዎድሮስን ያንድነት ግብ አስመቱት። እነሱም
ብቻቸውን አልነበሩም፤ እያንዳንዱ ችሎታቸውና ብቃታቸው በይፋ በጦር ሜዳ በተመሰከረላቸው ታላቅ የጦር-መሪዎች ተረድተው ነው፤ ራስ አሉላ
በሰሜን፣ ራስ ደረሶ በምዕራብ፣ ራስ ጐበና በመኻል አገር ነበሩ፣ ማለትም የትግርኛ፣ የአማርኛና የኦሮምኛ ኅብረተ-ሰብ ቋንቋ ተናጋሪ አባላት። ብዙ
ጒድለት ቢኖራቸውም፣ አፄ ዮሐንስ በዚህ ሥልጣን አደላድለው በማስተባበር ችሎታቸው፣ ንጉሥ ምኒልክ ደግሞ ተመጣጣኝ ጒልበት እያላቸው
የንጉሠ-ነገሥታቸውን ሥልጣን እንደጊዜው ልማድ አንዴም ሳይዋጓቸው በመቀበላቸው፣ መደነቅ አለባቸው።
በቅርቡ የአፄ ምኒልክን ስም የማጒደፍ ዘመቻ ያተኰረው ንጉሠ-ነገሥቱ በአሩሲ ውስጥ አኖሌ በተባለ ቦታ ፈጸሙ በተባለ ግፍ ላይ ነው። የእናቶችን
ጡት ቈረጡ፤ ብዙ ሕዝብ ጨፈጨፉ እየተባለ ይወራል። ለመታሰቢያም በቦታው ሐውልት ተሠርቷል ይባላል። እንደሚወራዉና ለኔም እንደመሰለኝ፣
የታሪኩ ምንጭ በኤርትራዊው በተስፋዬ ገብረ-አብ የተጻፈው “የቡርቃ ዝምታ” የተባለው የልበ-ወለድ ድርሰት ይመስላል። Page 12 of 15
እንግዴህ “ሞኝና ውሃ እንደወሰዱት ይሄዳል” እንደሚባለው ቅሌታም ብቻ ነው ልበ-ወለድን እንደእውነት፣ ምናብን እንደድርጊት አድርጎ የሚወስደው።
ከዚያም አልፎ ደራሲው የታሪክ ባለሙያ መሆን ይቅርና የዐሥራ-ሁለተኛ ክፍል ትምህርት እንኳን ማጠናቀቅ ያልቻለ ግለስብ ነው። በዚህ በፈጠራ
ጽሑፍ ተመሥርቶ ሐውልት የሚያሠራው ግለ-ሰብም ሆነ ባለሥልጣን በግድየሌሽነት የሕዝቡን ገንዘብ ማባከን ብቻ ሳይሆን፣ ሕዝቡን ራሱን ምን ያህል
ወደኋላ የቀረ በማሰኘት በዓለምና በታሪክ ፊት እያስገመተ ነው። ርግጠኛ ነኝ የአኖሌ ሕዝብ የሚጠጣ ንጹህ ዉሃ፣ የሚመላለስበት ዘመናዊ መንገድና
መጓጓዣ፣ በሽተኛውን የሚያስታምምበት የተደራጀ ሕክምና ቤት፣ ልጆቹን የሚያስተምርበት ማለፍያ ትምህርት-ቤትና፣ ትምህርቱንም ከጨረሰ ወዲያ
የሚሰማራበት አስተማማኝ የሥራ ዘርፍ የለውም ይሆናል። የሐውልቱ ገንዘብ በተረት ላይ በተመሠረተ ድርጊት ከሚውል፣ በእነዚህ አገልግሎቶች ላይ
ቢጠፋ፣ ሕዝቡን ምንኛ በጠቀመው፤ አሠሪውንስ ምንኛ ባስመሰገነው።
ድርጊቱ እውነት ቢሆንስ ሐውልት ለምን አስፈለገ። ኢጣልያኖች ሰንቱን አሩሲ፣ ስንቱን ኦሮሞ ጨርሰው የለ፤ ለምን ለዚሁ መታሰቢያ አልተሠራም።
እውነቱን እንነጋገር ከተባለ፣ በኢትዮጵያ ምድር ለተሠራው ግፍ ሁሉ ሐውልት እንሥራ ከተባለ ደግሞ፣ ከብዛቱ የተነሣ እንኳን ለሰው መኖርያ፣ ለእግሩ
ማሳረፍያ የሚሆን መሬት አይገኝም ይሆናል። አሩሲ ራሱ ቋንቋው ኦሮሞኛ ነው ይባል እንጂ፣ ሕዝቡ ግን ከመቶ ሰባው በትውልዱ የከምባታ፣ የሐዲያና
የጒራጌ ነው። እንግዴህ በዚህ መሬት በሌላው የተፈጸመው ሳይቈጠር፣ በኦሮሞች እጅ ብቻ ያለቀውን የነዚህን ሕዝብ ቊጥር የያንዳንዱ ቤት
ያውቀዋል። እንግዴህ ለነሱም ሐውልት ያስፈልጋቸዋላ። እኔ ራሴ የማወራው የግሌ ታሪክ አለኝ።
በሁለተኛው የኢጣልያን ወረራ ወቅት የኢትዮጵያ ጦር እንደተፈታ፣ በከምባታ ላይ የጐሦች ጦርነት በመባል የታወቀ ከፍተኛ ዘመቻ ተካሂዶ ሕፃንና
ዐዋቂ፣ ሴትና ወንድ፣ ወጣትና ሽማግሌ ሳይለይ ብዙ ሕዝብ ዐለቀ። ከብትና ንብረት ተዘረፈ። ብዙዎች ተማርከው የደረሱበት ጠፋ። ይኸ ዐይነት ሰለባና
በደል ከደረሰባቸው መካከል ቅርብ ቤተሰቦቼ ነበሩ። እናቴ ጡቷን ተቈርጣ፤ ሆዷን ተዘርጥጣ ሙታለች ተብላ እሜዳ ላይ ተጣለች። እናቷና ጫቅላ
እኅቷ ግን ተማርከው ከተወስዱ በኋላ ደብዛቸው ጠፋ። ሌላው ሕፃን ወንድሟ ግን የምርኮና የጥፋት ዕጣ ባይገጥመውም አባለ-ዘሩን ተቈርጦ በሜዳ
እንዲሞት ከተጣለ በኋላ በሕይወት ቢቀርም ወራሪዎቹ ጐሦች በያንዳንዱ ቤተ-ሰብና በመላው አገር ያደረሱት ዕልቂትና በደል በሰው አንደበት ተነግሮ
አያልቅም ብቻ ሳይሆን የሰቀቀኑ ርዝራዥ እስካሁን ድረስ በያንዳንዱ ቤተ-ሰብና ግለ-ስብ ጆሮ ውስጥ ይጮሃል። ለዚህም ዐይነቶቹ በጐሦች ለተፈጸመ
አሰቃቂ ግፍ ሐውልት ያስፈልጋል ማለት ነው።
በሥልጣን ያለው መንግሥት ከሽፍትነት ወደአፄ ምኒልክ ዙፋን ያደረስውን ዘመቻ የጀመረው ስሙን ባወረሰለት በመጀመርያ ወያኔ ትግል ላይ
ተመርኲዞ ነው ይባላል። አንዳንድ ታሪክ ጸሓፊዎች ለመጀመርያው ወያኔ መነሾው በኢትዮጵያ መንግሥት የተፈጸመው ያስተዳደር ጒድለት ነው ይላሉ።
እኔ ራሴ የሰማሁት ታሪክ ግን ከዚህ በጣም ይለያል። ያስተዳደር ጒድለት ማሳበቢያ ሊሆን ይችላል እንጂ፣ የመነሾው ጥንተ-መሠረቱ ግን የደጋ ትግሬው
ሕዝብ ከትውልድ ሲወርድ ሲዋረድ እንደመጣው ትውፊት በዘላኑ ኅብረተ-ሰብ ላይ ያካሄድ የነበረውን የዘረፋ፣ የግድያና የጥቃት ዓመታዊ ዘመቻውን
እንዲያቆም በመንግሥት ባለሥልጣኖች ስለተከለከለ ነበር። እንግዴህ ይኸ ዐይነት ዐመታዊ ዘመቻ ምን ያህል ግድያና ዕልቂት በዘላኑ ሕዝብ ላይ
ለዘመናት እንዳደረሰ እናውቃለን። ዘመቻው አባትና እናት ገድሎ ብዙዎቹን ልጆች ድኃደግ እንዳደረገ፣ የስንቶቹን እናቶች ጡት እንደቈረጠ፣ ስፍር-
ቊጥር የሌላቸውን ወንዶች እንደሰለበ፣ ከብትና ንብረት እንደዘረፈ፣ ሴቶችና ሕፃናት ማርኳቸው እንደወሰደ፤ በኅብረተ-ሰቡ ላይ ምን ያህል ሽብርና
ፍርሀት ይፈጥር እንደነበረ፣ ስንቱንስ በጋለሞታነት እንዳስቀረ መገመት አያዳግትም። አፄ ምኒልክ ባንድ ቀን በጥቂት ሰዓት ውስጥ ፈጽመዋል የሚባለው
ግፍና ጭካኔ ከዚህ በያመቱ ከሚደጋገመው ድርጊት ጋር ቢወዳደር ኢምንት ነው ማለት ይቻላል። ታዲያ ለዚህስ አረመናዊ ጭፍጨፋ ለምን ሐውልት
አያስፈልግም። በዚህ የአሳብ መስመር ከቀጠልን ደግሞ በሥልጣን ያለው መንግሥት አላንዳች ምክንያት በግፍ የጨፈጨፋቸውና ያስጨፈጨፋቸው
እልፍ አእላፋት ንጹሓን አሉ። ለነሱስ ለምን በየቀዬአቸው የመታሰቢያ ሐውልት አይሠራላቸውም።
በአሩሲ አፄ ምኒልክ ምን እንዳደረጉ ማወቅ ከተፈለገ አጥጋቢ ጽሑፍ ስላለን፣ በፈጠራና በስብከት ላይ መመሠረት አያስፈልግም። ጽሑፎቹ
የሚያስረዱት አሩሲ ምን ያህል ለአፄ ምኒልክ እጅግ ባለውለታ እንደሆነ ነው። ነገሩም እንደዚህ ነው። አገሩን ባስገበረው በቱላማ ጦር ላይ፣ ጥቂት
የአሩሲ ሰው ባንድ ባላባት ተመርቶ፣ ሌሊት ተነሥቶ ጦሩ በሠፈረበት ቦታ አደጋ ቢጥልበትና ከሺ በላይ ሠራዊት ቢፈጅበት፣ ካፄ ምኒልክ ረዳት ጦር
ተላከ። ይኸ ረዳት ጦር ሌሊቱን ሲጓዝ፣ ደግሞ እንደገና ተመልሶ አደጋ ሊጥል ከሚሄደው ከአሩሲ ሰው ጋር በድንገት በመንገድ ላይ ተገናኘና
በመካከላቸው በተፈጠረው ግጭት ብዙ ሰው ዐለቀ። የኦሮሞ ጦር እንደመሆኑ፣ በኅብረተ-ሰቡ ልማድ ጡት ቈርጦ፣ እጅ ጐምዶ ይሆናል። የጊዜው
ልማድ ስለሆነ ምንም አይገርምም፤ ሌላው ቀርቶ በአድዋ ጦርነት እንኳን ተፈጽሟል። ደጋግሜ እንዳልኩት፣ ታሪክ መዳኘት ያለበት ከጊዜው አንፃር
ነው።
የሚደነቀውና የንጉሠ-ነገሥቱ አሽማጦች የረሱት ነገር ቢኖር ግን፣ አፄ ምኒልክ እቦታው እንደደረሱ የወሰዱት እርምጃ ነው። በየትም አገር
እንደሚደረገውና እንደጊዜው ልማድ መሠረት፣ ጦራቸው የማረከውን የአሩሲን ሰው ሁሉ ባርያ አድርጎ ይዞ ቢቈይባቸው፣ ንጉሡ ከፍተኛ
ተቃውሟቸውን አሰሙ። ሠራዊታቸውን በሙሉ ሰብስበው፣ “አሩሲን ከግራኝ ወዲህ የገዛውና ያስገበረው የለም። እኛ ጥንትም የኛ [አገር] ነው ብለን
መጣንበት እንጂ ርሱ አልመጣብንም። ባለማወቁ እከላከላለሁ ብሎ ዐለቀ፤ ተጐዳም። ግን ባርያ አድርገን ልንገዛው አይገባንም፤ ወንድማችን ነውና።
የማረክኸውን የሰው ምርኮኛ ሁሉን ልቀቅልኝ። በዐዋጅ ከለመንሁህ በኋላ ወስልተህ የአሩሲን ሰው ባርያ አድርገህ የተያዝህ ከተገኘህ እጣላሃለሁ፤ ልቀቅ
ብዬሃለሁና ልቀቅ።”በማለት እንዲለቅ በአዋጅ አስገደዱትና ተለቀቀ። ባገሩም ታማኝና ብቁ ነው ብለው የሚያምኑትን አስተዳዳር ሹመው
ወደመናገሻቸው ተመለሱ።
ይኸንን የአፄ ምኒልክን ድርጊት ሌሎች የቅኝ ገዢዎች ከወሰዱት እርምጃ አንፃር እስኪ ከጥቂቶቹ ጋር እናስተያይ። ጀርመኖች የታንዛንያ ሕዝብ
ባስተዳደራቸው ግፍ አንገፍግፎት ሸፍቶ፣ አንዲት ትንሽ ምሽግ ቢጤ ሰብሮ፣ ጥቂት ሰው ቢገድልባቸው፣ ረዳት ጦር ተልኮ ሁለት መቶ ሺ ሰው በጭካኔ
ገደሉ። እንዲሁም የናምቢያ ሕዝብ በጨካኝ አስተዳደራቸው ተማርሮ በዚሁ መልክ ቢነሣባቸው፣ የተላከው ረዳት ጦር አንድም ሰው ሳይቀር እንዲገድል
ታዝዞ፣ ከመቶ ሰማንያውን እጅ አረደ። የቀረው ሊያመልጥ የቻለው ወደጐረቤት መንግሥት ሸሽቶ ብቻ ነው። እንዲሁም ፈረንሳዮች የማዳጋስካር ሕዝብ
ተበደልሁ ብሎ ቢነሣባቸው፣ ሰማንያ ሺውን አላንዳች ምሕረት ጨፈጨፉ። በጐረቤታችን ኬንያ እንግሊዞች በየቀኑ፣ “ዛሬ ሁለት መቶ ሻንቅላ ገደልን፤ Page 13 of 15
ዛሬ ደግሞ ዐምስት መቶ…” እያሉ ለቅኝ ግዛት ሚኒስትር ወደለንደን የሚልኩትን መግለጫ ያነበበ፣ ስለሰው ሕይወት ነው የሚናገሩት ወይንስ ስለወፍ
ብሎ መገረሙ አይቀርም።
የአሩሲ ዐይነቱ የስም ማጥፋት ዘመቻ በአፄ ምኒልክ ላይ ሲደረግ የመጀመርያው አይደለም፤ የመጨረሻም እንደማይሆን ርግጠኛ ነኝ። ዛሬ በሥልጣን
ላይ ያለው መንግሥት እንደገባ፣ ሊቅ ነጋሦ ጊዳዳ ከፍተኞች የኦሮሞ ባለሥልጣኖችን ሰብስበው፣አፄ ምኒልክ በጦር ኀይል አሸንፈው፣ የኦሮሞን ሕዝብ
አላንዳች ርኅራኄ የጨፈጨፉበትና ለነፃነቱ ብዙ መሥዋዕት ከፍሎ በግፍ የተገፈፈበት ወዳሉበት ቦታ ወደጨለንቆ እየደነፉና እያጕራሩ እንደሄዱ
ብዙዎቻችን ረስተን ይሆናል። እኔ በተፈጥሮዬ ከፈረንጅ ኋላ ቱስ ቱስ የሚል ሰው አልወድም። ይሁንና ሊቅ ነጋሦን ያገኘሁኋቸው ገና ተማሪ ሳለሁ
በኢጣልያን አገር በሮም ከተማ በዚህ መልክ ነው። ሁናቴው ደስ ባይለኝም፣ የታሪክ ሰው መሆናቸውን ስለማውቅ፣ ላናግራቸው ብሻ፣ ፈረንጁ
ጓደኛቸው በሥነ-ሥርዐቱ ሲያነጋግረኝ፣ እሳቸው ግን ሊቀርቡኝም ሊያነጋግሩኝም አልፈለጉም። ይልቅስ ያኔ ለሥልጣን እጩ ለነበረው መንግሥት
በመመልመል ላይ እንደነበሩ ጓዶቻቸው ሁሉ፣ እሳቸውም ኲምሽሽ ብለው ቁመው ከሩቅ በፍራቻ በስርቆሽ ማየት እንጂ ሰላም እንኳን አላሉም።
ድርጊታቸው ከቃል ይበልጥ ይናገራልና ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ስለሰውዮው ያለኝ ግምት በጣም ዝቅተኛ ነበር። የጨለንቆው ጉዳይ ሲመጣ፣ ከነጭራሹኑ
አዘቀጠው ብቻ ሳይሆን የታሪክ ዕውቀታቸው ምን ያህል አሳዛኝ እንደሆነም ተገለጠልኝ።
የጨለንቆ ውጊያ የተካሄደው ግብፆች ሐረርን ሲለቁ ከሾሙት ከአደሬው አሚር አብዱላሂ ጋር መሆኑን ማንም ያዉቃል። አሚሩ ያነ ቆቱ የተባለውን
የሐረርጌን የኦሮሞ ገበሬ በክፉኛ ጨቁኖ የሚገዛ፣ በሐረር ከተማው ሕዝብ ራሱ ብዙ በደል በመፈጸሙ በጣም የተጠላ ብቻ ሳይሆን፣ የኢጣልያን
መልእክተኞችን በጭካኔ በመግደሉ፣ አካባቢውን ይዘው የነበሩት የፈረንጆች መንግሥታት አጋጣሚውን ተጠቅመው የአሚሩን ግዛት ሊቀራመቱ
በዝግጅት ላይ ነበሩ። አፄ ምኒልክ ሐረርጌ እስከዐራት መቶ ዓመት ድረስ የኢትዮጵያ ግዛት እንደነበረ አገናዝበውት ሲያበቁ፣ አሚር አብዱላሂን በሰላም
እንዲገብር ቢጠይቁት፣ ከቱርክ የበለጠ መንግሥት የለም ካለ በኋላ፣ እርስዎ እስላም ከሆኑ እገብርልዎታለሁ ሲል፣ ሽርጥ፣ ጥምጥምና መስገጃ ምንጣፍ
ላከላቸው። ቀጥሎም ሠራዊታቸው የገና በዓል እያከበረ ተዘናግቶ ሳለ፣ በድንገት ደርሶ የመድፍ ተኲስ ከፈተባቸው። የአፄ ምኒልክ ሠራዊት ከመ ቅጽበተ
ዐይን በሚደንቅ መንገድ ተፈናጥሮ ደርሶ፣ መድፎቹን ማርኮ ቢተኲስ፣ ውጊያው ሳይታሰብ እንደጀመረ ሳይታሰብ በፍጥነት ዐለቀ። ነገሩ የተገላቢጦሽ
ሆነ እንጂ፣ ፍጻሜው ልክ የሮሜው ገናና የጦር መሪ የነበረው ጁልዩስ ቄሣር “መጣሁ፤ አየሁ፤ አሸነፍሁ” እንዳለው ቢጤ ነው። እንግዴህ በአካባቢው
የነበሩት አውሮጳውያን እንደጻፉት፣ ሐረር “የተያዘችው አለምንም ደም መፍሰስና ዝርፍያ” ነበር። እንዳይዘረፍም በየቤቱ በራፍ የአፄ ምኒልክ ዘብ ቁሞ
ይጠብቅ ነበር። አፄ ምኒልክም እንደደረሱ ሁሉም ሰው እንደባህሉና እንደሃይማኖቱ እንዲስተዳደር ማስጠንቀቂያ ሰጥተው የአሚሩን አጎቶች ሹመው
ተመለሱ። ጠፍቶ የነበረው አሚር አብዱላሂ ራሱ ከተደበቀበት ወጥቶ፣ ሐረር የኢትዮጵያ አገር መሆኑን በማሳወቅ፣ “ገብቼ ልገዛ; አገርዎን አያጥፉት”
ሲል ላከ።
እንግዴህ ሊቅ ነጋሦ ኦሮሞች ነፃነታቸውን ያጡበትና ታላቅ ዕልቂት የደረሰባቸው የሚሉት የጨለንቆ ውጊያ እውነቱ እሳቸው ከሚሉት እጅግ በጣም
የራቀ ነው። ይልቅስ አፄ ምኒልክ ኦሮሞችንና ሱማሌዎችን ከጭቈና አላቅቀውአቸው ነፃ አወጥቷቸዋል፤ ሐረርጌም ከአውሮጳ ቅኝ ግዛትነት አምልጣ፣
ከዐራት መቶ ዓመት በኋላ ከናቷ ኢትዮጵያ ጋር ተቀላቀለች። የሚያሳዝነው ግን ሊቅ ነጋሦ ጊዳዳ ተራ የታሪክ ምሁር ብቻ አይደሉም። ምርምራቸውን
ያካሄዱት በኢትዮጵያ ባሕር በወለጋ ውስጥ ባለው በሳዮ ኦሮሞ ላይ ከሺ ሰባት መቶ ሠላሳ እስከ ሺ ስምንት መቶ ሰማንያ ስድስት (1730-1880) ዓ.ም.
የጊዜ ገደባ ውስጥ ስለነበር ከማንም ይበልጥ ስለኦሮሞ ታሪክና ውህደት እንደሚያዉቁ ይጠበቅባቸዋል። የሐረርንም ጭምር። ታዲያ የሐረር ኦሮሞ
ተጨቁኖ የነበረውና ማንነቱን ያጣው፣ በአፄ ምኒልክ ሳይሆን በግብፆች ሥር መሆኑን እንኳንስ እንደሳቸው ያለው ምሁር የታሪክ ጀማሪም ያውቀዋል።
የአፄ ምኒልክ አስተዳደር አብነታዊና በሁሉም ዘንድ የተወደደ እንደነበር ሌላው ቀርቶ አውሮጳውያን ባላንጦቻቸው እንደሚመሰክሩ አይተናል።
ከዚህ በላይ ባጭሩም ቢሆን እንደተገለጸው፣ አፄ ምኒልክ ያቋቋሙት ያስተዳደር ሥርዐት በዛሬ ዘመን ሲታይ ወደፈዴሬሽንነት ይጠጋል። መሠረታዊ
መመዘኛው ባህልና ታሪክ እንዲሁም የሕዝቡ ምቾትና ልምድ ሲሆን፣ አንዳንዴ ሃይማኖትንም ቋንቋንም ጭምር የሚያስተናግድ ቢሆንም፣ በነኚህ
መለዮች ብቻ ተወስኖ እንደመንጋ ከብት ባንድጋ አያጉራቸውም። ጐጃምና በጌምድር የሚዋስኑ አገሮች ናቸው፤ በሃይማኖትና በቋንቋ አንድ ናቸው።
ሁኖም የተለየ ታሪክና ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ የራሳቸው የሆነ ያስተዳደር ትውፊት ስላላቸው ልዩነታቸውን እንደያዙ ቀጥሏል። እንደዚሁም አብዛኛው
የወለጋና የከፋ ሕዝብ በሃይማኖትም ሆነ በቋንቋ ተመሳሳይነት ቢኖራቸውም፣ በታሪክ፣ በባህልና ባስተዳደር የየግላቸው ስለነበሩ ልዩነታቸው
እንደተጠበቀ ሁኖ ተዋቅሯል። አወቃቀሩ ማናቸውም ጤናማና እውነተኛ የፈዴሬሺን ሥርዐት ያላቸው አገሮች የተከተሉት ነው ለማለት ይቻላል።
ለምሳሌ የአሜሪቃን ፈዴሬሽን የመሠረቱት ዐሥራ ሦስቱ መንግሥታት በቋንቋ፣ በትውልድ፣ በእምነትም አይለዩም። እናት አገራቸውን እንግሊዝን
አሸንፈው ነፃ በወጡ ጊዜ በዐሥራ ሦስቶቹ ፈንታ በአንድ መንግሥት ብቻ መዋቀር ሲችሉ፣ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣውን የየግላቸውን አስተዳደር
ላይለቁ ብለው በፌዴሬሽን ተቋቋሙ። ሌሎችም በሠለጠኑ አገራት ያሉት በፌዴሬሽን የተዋቀሩት መንግሥታት (ለምሳሌ ያህል እንደጀርመን ያሉት)
የተከተሉት መልክ ነው።
አፄ ምኒልክ ዘመናዊነትን ባገር ውስጥ ለማስገባት ያልነኩት የሥልጣኔ መስክ፣ ያላደረጉት ጥረት የለም። በያንዳንዱ መስክ ከፍተኛ ተቃውሞ
ገጥሟቸዋል። ግን ሁሉንም በትዕግሥትና በብልሃት በመያዝ ተወጥተው አስፈላጊ መሠረቶችን በመጣል፣ ኢትዮጵያን በዘመናዊ ሥልጣኔ ተራማጅ
ኀይሎች አንዷ እንድትሆን ለማድረግ በቅተዋል። በጣሉት መሠረት ላይ ማነጽና የተሻለች ኢትዮጵያ መገንባት የያንዳንዱ የተከታዩ ትውልድ አላፊነት
ነው።
ደጋግሜ እንደተናገርሁት፣ አፄ ምኒልክ በተለያዩ ባላባቶች ሥር ሁኖ እርስ በርሱ ይተላለቅ የነበረውን ሕዝብ፣ ባንድ ሰንደቅ ዓለማ ሥር ሰብስበው አንድ
ቤተሰብ አድርገውታል። በርስበርስ ፍጅት ፈንታ፣ ተከባብሮ፣ ተቻችሎና ተፋቅሮ እንዲኖር ለማድረግ ሲሉ ባደረጉት ድርጊት የተወሰነ መሥዋዕት
መኖሩ ርግጥና የማይካድ ነው። ሁኖም ሌሎች ብዙዎች አገሮች ለዚሁ ዓላማ ሲሉ ከከፈሉት ጋር ቢነፃፀር መሥዋዕቱ በጣም ዝቅተኛ ነው ማለት
ይቻላል። ሁኖም አንዲት እናት ሕፃኗ እንደተወለደ ምንም እንኳን አሰቃቂ ቢሆንም፣ ምጧን ረስታ በሕፃኗ ደስታ ተዉጣ እንደምትቀርና ርብርቦሿና
ትኩረቷ በሙሉ ጫቅላዋ አድጎ ለወግና ለማዕረግ እንዲደርስላት ሌት ተቀን አለዕረፍት እንደምትንከባከብ ሁሉ፣ እኛም የኢትዮጵያን ያንድነት ግብ Page 14 of 15
ለመምታት የተፈጸመውን ሥቃይና የተከፈለውን መሥዋዕት በእልልታ፣ በጸጋና በደስታ ተቀብለን፣ መሯሯጥና መሽቀዳደም ያለብን ሙጪቷን አገር
አደጋ ሳይነካት አንድ ሁነን በጥንቃቄ ገንብተን በዓለም-አቀፍ መድረክ ላይ ሳትደፈር ተከብረና ተፈርታ ከፍተኛ ሚና እንዲትጫወት ማብቃት ነው።
አንድ መረዳት የሚገባን ነገር ቢኖር፣ ከውጥኑ ጀምሮ ሙሉ በሙሉ ፍጹም ሆኖ የተቈረቈረ አገር በታሪክ ውስጥ እስካሁን ድረስ አልታየም፤ ሊታይም
አይችልም። ቢሆንማ የትውልድ መተካካት ዋጋ አይኖረውም ነበር። ምክንያቱም ሥራው ሁሉ በፊተኛው ትውልድ ፍጹም ሁኖ ተሠርቶ ካለቀና
ከተላለፈ፣ ተረካቢው ትውልድ የራሱን ታሪክ የሚሠራበትን ዕድል ያጣል። አሁን በዓለም ተፈርታና ተደንቃ የሚትኖረው አሜሪቃ እንኳ እንዴት
እንደተቈረቈረች ቢናይ፣ ህልውናዋ የተጣለበት መሠረት ከልክ በላይ አሳዛኝና ግፈኛ ነበር ማለት ይቻላል። ቈርቋሪዎች አባቶች ተብለው የሚጠሩት
መሥራቾቿ በጣም ከፍ ያለና ከዚህ በፊት ባለም ታሪክ ተሰምቶ ያልተወቀ መልእክት ያዘለ መግለጫ ቢያስተጋቡም፣ በግብር ላይ የታየው ግን አነሳው
የቀረውን አብዛኛውን ሲጨቊን ነው። ሕጓ ለሁሉም ሰው የመኖር፣ ደስተኛና ነፃ የመሆን መብት ማንም የማይፈለማቸው ከእግዚአብሔር የተሰጡት
የተፈጥሮ መብቶች ናቸው ቢልም፣ ከሰው እንደማይቈጠሩ፣ ወይንም እኩል አይደሉም ተብለው ስለሚታሰቡ፣ ሕጉ ሴቶችን፣ ጥቊሮችንና፣ ያገሩን
ተወላጅ ራሳቸውን ህንዶቹን፣ እንዲሁም ድሆችንና መሃይምኖችን አያጠቃልልም ነበር። ባጭሩ የአሜሪቃ አብዮት የተባለው ሥርዐት የፈጸመው ተግባር
እግዚአብሔር መርጦ ለሥልጣን ያበቃል የሚለውን የፖሊትካ መርህ፣ የገዢው ክፍል ዋና መመዘኛው መሆን ያለበት ሀብቱ ነው በሚል ተካ፤ ሕዝባዊ
መንግሥት ወይንም ደሞክራሲም ተብሎ የተቋቋመው አስተዳደር፣ ጥንተ መሠረቱ በሀብታሙ የነጭ ወንድ ለሀብታሙ [የነጭ ወንድ] የተመረጠ
መንግሥትን እንጂ ሌላውን የአገሩን ነዋሪ ያካተተ አልነበረም። ሌሎቹ፣ በጾታ፣ በቀለምና በዘር፣ እንዲሁም በዕውቀትና በሀብት ሰበብ የተነፈጉትን
መብቶቻቸውን ያገኙት፣ የተጧጧፈ ትግል በየጐራቸውና በየፊናቸው በማካሄድ ነው። እነዚህ በየመስካቸው የተቀናጁት ድል፣ አገራቸውን እጅግ በጣም
አሻሽሎ፣ የማንም ሰው መመዘኛው ችሎታውና ምግባሩ እንጂ አስፈላጊ እስካልሆነ ድረስ ከቶውኑ በሌላ ዐይነት መለኪያ ማንም መፈረጅ የለበትም
የሚለውን አቋም የመንግሥታቸው መርህ ለማድረግ በቅተዋል።
አፄ ምኒልክ ያዋሃዷት ኢትዮጵያ አሜሪቃን ከላይ ባየናቸው ልዩነቶች ተመሥርቶ፣ ለዘመናት ከከፋፈላትና ካተራመሳት የመድሎ የአስተዳደር እንከን ነፃ
ሁና የተቋቋመች አገር መሆኗን ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ ገልጫለሁ። በዘርና በጾታ፣ወይንም በቋንቋ፣ ካልሆነም በሃይማኖት ወይንም በንብረት ምክንያት
ለባርነት የተዳረገ፣ ወይንም ለሥልጣን እንዳይታጭ፣ ለወግና ለማዕርግ እንዳይበቃ የተደነገገ ሕግም፣ ኅብረተ-ሰብም፣ የኅብረተ-ሰብ መደብም
በኢትዮጵያ የለም። በዚህ ረገድ ባንረዳ ነው እንጂ አፄ ምኒልክ አንድ አድርገው ያስረከቡልን ኢትዮጵያ በጣም የተባረከች አገር ናት፤ ተረካቢዉም
ትውልድ እጅግ ዕድለኛ ነው ማለት ይቻላል። ይኸም ሁናቴ ኢትዮጵያን ከብዙ በዘመናዊ ሥልጣኔ ከገሠገሡ መንግሥታት ይለያታል።
የኢትዮጵያ ችግሯ በዘመናዊ ሥልጣኔ ወደኋላ-ቀርነትና የዘመናዊ ዕውቀት እጥረት ነው። ከመዋሃዷ በፊት ባላባቶችና ጐሦች ትርፍ ጒልበታቸውንና
ሀብታቸውን በርስበርስ ፍጅት በማዋል፣ አገሪቷን ወደጦር ሜዳነት ለውጧት ነበር። ይኸንን አፄ ምኒልክ አከተሙት። ሁላቸውንም ጠበኞች በድሮዪቷ
ኢትዮጵያ ጐጆ ሥር ሰብስበው ሲያበቃ፣ ከንግዴህ ወዲያ እያንዳንዱ ትርፍ ጒልበቱንና ሀብቱን በፈለገበት የትምህርት ገበታ ዙርያ እንዲያውል፤
በተመረቀበትም ሙያ ተሰማርቶ ያዋሀዷትን አገር በተራው እንዲያሻሽል አደራ ሰጥተው ወደማይመለሱበት ዓለም ሄዷል።
ጀነራል ጃገማ ኬሎ እንዳሉት፣ በአስተሳሰብም ሆነ በሙያ ዘርፍ ጠባብ በነበረው በጐሦችና በባላባቶች ዓለም ይኖሩ የነበሩት አባቶች የጀብድነታቸ
መለኪያና ምልክት በሚጥሉት ግዳይ በሚያስቈጥሩት ሚርጋ የተመጠነ ነበር። አሁን ግን ይኸ ዐይነት ድርጊት ያልተገራ አውሬ ብቻ ነው የሚፈጽመው።
በዛሬ ዘመን የጀብዱ ሚርጋ የሚቈጠረው እያንዳንዱ ለአገርና ለኅብረተ-ሰብ ዕድገትና ልማት በሠራው ሥራ ነው። ከዚያም አልፎ በተሰማራው የሙያ
ዘርፍ በሚያገኘው ፍልሰፋና ምርምር እኩዮቹን ሲያስከነዳና፣ ለዓለም ሕዝብ በጠቅላላ ጠቃሚ አገልግሎት ሲሰጥ ነው። አፄ ምኒልክ ይኸንን ዓላማችን
አድርገን ባገር ውስጥም ሆነ በዓለም መድረክ ላይ እንድናበረክት ዕድሉንና በሩን በሰፊው ከፍተዋል። እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ እውድድሩ ሜዳ ገብቶ
ድርሻውን ለአገሩም ለዓለምም መክፈል እንዲችል መንፈሱን አደራጅተዋል፤ አገሩን አደላድለው ካበቁ በኋላ የዘመናዊ ሥልጣኔን መሠረት ጥለው
ሜዳውን አመቻችተዋል። ካርል ማርክስ እንዳለው በበግነት ስሜት እንጂ በሰብኣዊ ልቡና የማይመራውን የጐሣንና የባላባቶችን ዓለም ማድነቅም ሆነ
ከሞተበት ለማንሣት መሞከር ከታሪክ ጋር ግብግብ መያያዝ ነው። አያዋጣም፤ እንዲሁም እሳቸውን ራሳቸውን መውቀስ፣ ከሙት ጋር መሟገት ሰለሆነ
ርባን የለዉም። የራስን ድርሻ መወጣትና የተረከቡትን አሻሽሎ ማስተላለፍ ግን በታሪክ የሚጠየቅ ግዴታ ነው።
አፄ ምኒልክ የወረሷት ኢትዮጵያ በውስጥም በውጭም ጠላት ፊት ለፊት በመፋጠጥ ላይ ስለነበረች ህልውናዋ ራሱ አጠይያቂ ነበር። ሲለዩአት ግን
ህልውናዋና ነጻነቷ በመላው ዓለም የተረጋገጠ ብቻ ሳይሆን፣ በነጮች የቅኝ ግዛት ቀንበር ሥር ለነበሩት ሁሉ አለኝታቸውና የነፃነት ጨረራቸው፣
የህልውናቸው ዕርቡን ነበረች። “በልቤ ውስጥ ኢትዮጵያ ሁሌዬ ልዩ ቦታ አላት። ወደፈረንሳይና ወደእንግሊዝ፣ እንዲሁም ወደአሜሪቃ ባንድጋም ሆነ
ለየብቻቸው ሽርሽር ከመሄድ ይልቅ፣ እጅግ በጣም ይጐመጀኝ የነበረው ኢትዮጵያን የመጎብኘት ፍላጎት ነበር። ኢትዮጵያን ስጐበኝ፣ የገዛ ራሴን ጥንተ
ልደት ብቻ ሳይሆን አፍሪቃዊነቴንም ጭምር ቈፍሬ የማገኝ መስሎኝ ይታየኝ ነበር።” ሲል ኢትዮጵያን በመወደስ ኔልሶን ማንዴላ የጻፈው ስሜትና
አስተያየት በአብዛኛው ጥቊር ሕዝብ ልብ ውስጥ ያለ ነው ቢባል ሐሰት አይደለም።
ኔልሶን ማንዴላ ውዳሴውን የጻፉት አሻፈረኝ አልቀበለውም ብለው ለኻያ ሰባት ዓመት ሕይወታቸውን በእስር ቤት በመጐሳቀል የሰውበት በጐሦች
ክልልና ሥርዐት የተዋቀረ መንግሥት እምኒልክ ቤተ-መንግሥት ከመቀመጡ በፊት ነበር። ከእስር ቤቱ እንደተፈቱ መጀመርያ ላይ ከጐበኙት አገሮች
መካከል አንደኛይቷ የሚያደንቋት የአፄ ምኒልክ ኢትዮጵያ ነበረች። ዘውገኞቹ ሥልጣን ከጨበጡ በኋላ ግን በአገሪቷ ጠፈር ላይ በየጊዜው እየበረሩ
ሲያልፉም ሆነ ብዙ ዕድልና ገጠመኝ ኑሮላቸው እያለ፣ አንድ ጊዜም እንኳን አልመጡም፤ ዞር ብለውም ሊያዩ አልፈለጉም። ርግጠኛ ነኝ የወሰዱት አቋም
አፄ ምኒልክንም፣ ልክ በዘረኛው የደቡብ አፍሪቃ መንግሥት ራሳቸው እንደማቀቁ ሁሉ፣ በጐጠኛው መንግሥት ቀንበር ሥር የሚጥረውን የኢትዮጵያን
ሕዝብ ላያሳዝኑ ብለው ይሆናል። እንግዴህ ከዚህ የከፋ ኲነኔ ሊኖር አይችልም። ለአፄ ምኒልክም ሆነ እሳቸው ላዋሀዷት ኢትዮጵያ ያላቸውን
አድናቆትና ሙገሳ በሰላ አንደበታቸው፣ በወርቃማ ብዕራቸው ጽፈው ለልጅ ልጅ የሚተላለፍ ዕጹብ ድንቅ የሆነ ማስታወሻ ትተዋል። በመላ ዓለም
ታላቅነታቸው የተወደሰው ኔልሶን ማንዴላ ያከበሯቸውና ያደነቋቸው አፄ ምኒልክና ሥራቸው፣ በጥራዘ-ነጠቁና እቤተ-ክርስቲያን ውስጥ እንደገባ ውሻ
በየሄደበት በሚባረረው ቢዋረዱና ቢጠሉ በፍጹም አይደንቅም። መጠበቅም ያለበት ነው። ሥራቸው ጥርት አድርጎ የሚያሳየው ተቃራኒውን ነው። የአፄ
ምኒልክን ታላቅነትና ገናናነት፣ የአሽሟጣጮቻቸውን ከንቱነትና ብኩንነት። Page 15 of 15
***************************
+++++++++++++++++++
ኢትዮሚድያ - Ethiomedia.com
February 9, 2014
Wednesday, February 12, 2014
Monday, February 10, 2014
የህወሓት የልደት በዓል ህዝባዊ ስብሰባ አስተጓጐለብኝ - ዓረና
- Written by አበባየሁ ገበያው
አቶ አብርሃ ደስታ ለአዲስ አድማስ እንደጠቆሙት፤ ባለፉት ሳምንታት በሁመራ ከተማ ህዝባዊ ስብሰባ ለማካሄድ ቅስቀሳ ሲያደርጉ የሰነበቱ ሲሆን፤ ስብሰባውን ቅዳሜ እና እሁድ እንዳያደርጉ ተከልክለው ለትናንት አርብ ፈቃድ አግኝተው ነበር፡፡ ይሁንና በሰላማዊ መንገድ ህዝባዊ ጥሪ አድርገን ቅስቀሳውን በተሳካ ሁኔታ ከፈፀምን በኋላ በህወሓት የልደት በዓል ተጨናንቀናል፤ የተቃውሞ ስብሰባ ማድረግ አትችሉም፤ ህገወጥ ናችሁ” ተባልን ብለዋል - አቶ አብርሃ፡፡
ህዝባዊ ስብሰባው በፓርቲው ፖሊሲ፣ በኢትዮ-ኤርትራና ኢትዮ-ሱዳን ድንበር ጉዳይ እንዲሁም በአገር ሉዓላዊነት ዙርያ የሁመራን ህዝብ ለማወያየት ያለመ ነበር ያሉት የፓርቲው ሥራ አስፈፃሚ አባል፤ ኢህአዴግ የተለያየ ምክንያት ይደርድር እንጂ ስብሰባችንን ያስተጓጐለው ፓርቲያችን ስጋት ስለሆነበት ነው ብለዋል፡፡
ከሁለት ሳምንት በፊት ፓርቲው በዓዲግራት ስብሰባ ለማካሄድ ቅስቀሳ ሲያደርግ፣ አባላቱ እንደተደበደቡና እንደታሰሩበት አቶ አብርሃ አስታውሰዋል፡፡
ምንጭ አዲስ አድማስ
Friday, February 7, 2014
የመሬት ቅርምት በአስቸኳይ ይገታ!!!
“የግብርና ሚኒስትር” በሚል “የሆድ ሲያውቅ፤ ዶሮ ማታ” ስያሜ የወያኔ የመሬት ሽያጭ ጉዳይ አስፈፃሚው የሆነው የሥርዓቱ ቀንደኛ አገልጋይ “መሬት መቀራመት ኢትዮጵያን ጭራሽ አይመለከታትም” ብሎ ሲናገር የሰማነው እና ያነበብነው በከፍተኛ ትዝብት ነው።
ለመሆኑ የመሬት ቅርምት ከኢትዮጵያ በላይ ማንን ሊመለከት ነው? ሱዳንን፣ ኤርትራን፣ ሳውዲን፣ ቻይናን፣ ህንድን ወይስ አሜሪካን? ከራሱ ከወያኔ ሹማምንት የተራረፈው መሬት ለአረብ አገራትና ለእስያ ቱጃሮች በነፃ የሚታደለው ኢትዮጵያ ውስጥ አይደለምን? ባዕዳን የሚረከቡት መሬት ስፋት በሄክታር መለካት ሲሰለቻቸው “ቤልጂየምን የሚያክል” እያሉ በስጦታ ያገኙትን መሬት በአገር ስፋት የሚለኩት ኢትዮጵያ ውስጥ አይደለምን? የመሬት ቅርምት ኢትዮጵያን ካልተመለከተ ከቶ ማንን ሊመለከት ነው?
ወያኔ ለም መሬት ለራሱ ማግበስበሱ ሳያንስ “ልማታዊ ባለሀብቶች” እያለ ለሚያሞካሻቸው ለቅርብም ለሩቅም አገራት ቱጃሮች ሰጥቶ ባለሀገሩን አርሶ አደር ሜዳ ላይ በተነ። መጤው ቱጃር ባለመሬት ሆኖ ባለሀገሩ ለስደት አሊያም ለቀን ሠራተኝነት ተዳረገ። ይህ ግፍ የሚፈጥረው ስቃይ የማይበቃ ይመስል “በእቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” እንዲሉ መሬት ሻጩ “የመንግሥትና የሕዝብ ሀብት የሆኑ ነፃ መሬቶችን ብቻ ነው ለሰፋፊ የግብርና ኢንቨስትመንት የምንሰጠው። ማንም ከቀዬው አልተፈናቀለም” እያለ ይዘባበትብናል። “የመንግሥትና የሕዝብ ሀብት” የሚባለው መሬት የወያኔ የግል ሀብት ከሆነ ሃያ ሶስት ዓመታት መቆጠራቸው እኛ ብቻ ሳንሆን እሱም ያውቀዋል።
አባቶቻችንና እናቶቻችን ለብናኝ አፈር በመሰሰት ጎብኚዎችን እግር አሳጥበው ሲሸኙ እንዳልነበር ዛሬ በልማት ስም ከጋምቤላ እስከ መተማ፣ ከባሌ እስከ ሰላሌ፣ ከከፋ እስከ አፋር ያለው መሬታችን በሙሉ ወይ በወያኔ ሹማምንት አሊያም በባዕዳን ቱዳሮች ይዞታ ሥር ሆኗል። ኢትዮጵያዊያን አርሶ አደሮች፣ ወንዶችና ሴቶች፣ ጎልማሳዎችና ወጣቶች፣ ሕፃናት ሳይቀር የአዳዲሶቹ ባለመሬቶች ተቀጣሪዎች ሆነዋል። ጉልተኛው ሥርዓት ከቀድሞው በባሰ መልኩ ተመልሶ መጥቷል።
ወያኔ እንደሚያወራው ሰፋፊ መሬቶችን የመስጠት ዓላማው ግብርናችንን ለማዘመን ከሆነ ኢትዮጵያዊያን ባለሀብቶች ጠፍተው ነው እሩቅ ምስራቅ እስያ ድረስ የተጓዘው? እነሱስ ለምንድነው ለሊዝ የሚጠየቁትን እዚህ ግባ የማይባለውን ገንዘብ እንኳን ከራሷ ከኢትዮጵያ ተበድረው የሚከፍሉት? ይህ ምን ዓይነት ሥርዓት ነው? ከዛሬ አርባና አምሳ አመታት በፊት በሁመራ፣ ተንዳሆና ስምጥ ሸለቆዎች ውስጥ ሰፋፊ ዘመናዊ እርሻዎች የነበሯቸው ኢትዮጵያዊያን ነበሩ። ያኔ ኖረው ዛሬ እንደምን ላይኖሩ ቻሉ? የመሬት ባለቤት የመሆን መብት ያለው ኢትዮጵያዊ ወያኔ ብቻ እንዲሆን የተደረገው ለምንድነው? ኢትዮጵያ፣ ወያኔ ወይም የወያኔ አሽከር ላልሆነ ኢትዮጵያዊ ምኑ ነች? ባለሃገሩን መሬት አልባ፤ ባዕዳንን ደግሞ ባለመሬት ማድረግ ምን ያስከትላል?
ኢትዮጵያ ውስጥ መሬት እጅግ ከፍተኛ ዋጋ ያለው ግብዓት መሆኑ ከማንም የተሰወረ አይደለም። ኢትዮጵያ ውስጥ መሬት ከግብዓትም በላይ የፓለቲካ ሥልጣን ምንጭም ነው። ለዚህም ነው በኢትዮጵያ ፓለቲካ የመሬት ጥያቄ ቁልፍ የፓለቲካ ጥያቄ ሆኖ የቆየው። ደርግ መሬትን ከጉልተኞችም ከአርሶ አደሮችም በአዋጅ ቀምቶ የመንግሥት በማድረግ መንግሥትን አሳብጦ ገበሬውን አዳከመው። ወያኔ ይኸንኑ መሬት ያለአዋጅ ከመንግሥት ቀምቶ የራሱ በማድረግ ራሱን አሳብጦ ገበሬውን ከቀደሞው በባሰ አዳከመው። አሁን ደግሞ ይባስ ብሎ ይህንኑ መሬት ለባዕዳን በመስጠት ገበሬውን በአጠቃላይ ከመሬት ነጥሎ የቀን ሠራተኛ እያደረገው ነው። ይህ ከጪሰኝነት እጅግ የባሰ ባርነት ነው።
በወያኔ እና ታማኝ ተላላኪዎቹ እየተፈፀመ ያለው የመሬት ቅርምት ኢትዮጵያዊያንን አገር የሚያሳጣ፤ ስብዕናችንን የሚያዋርድ፤ ክብራችንን የሚገፍ፤ ሀብታችንን የሚያዘርፍ በመሆኑ በአስቸኳይ መቆም ይኖርበታል።
ሰው ባገሩ ሰው በወንዙ
ቢበላ ሳር ቢበላ መቅመቆ
ይታወቅ የለም ወይ ሰውነቱ ታውቆ
ቢበላ ሳር ቢበላ መቅመቆ
ይታወቅ የለም ወይ ሰውነቱ ታውቆ
ግንቦት7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ለባዕዳን መሬታችንን፣ አገራችንን፣ ነፃነታችንን ሰጥተን ከሚገኘው ጥቅም … ባለቅኔው እንዳለው … ሰውነታችን ታውቆ፣ ክብራችን ተጠብቆ ሳርም ይሁን መቅመቆ መብላት እንመርጣለን። የመሬት ቅርምት በአስቸኳይ ይገታ። አገራችንን ለማዳን ቆርጠን እንነሳ።
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!!
Wednesday, February 5, 2014
ኢትዮጵያን ከቅርጫ ለማትረፍ
ከፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማርያም
ትርጉም በነጻነት ለሀገሬ
እ.ኤ.አ በ2008 “የኢትዮጵያ ጋሻ“ ተብሎ በሚጠራው የሰሜን አሜሪካ የሲቪል ማህበረሰብ ስብስብ ጉባኤ ላይ በመገኘት የእናት አገር ኢትዮጵያን ሉዓላዊነት መጠበቅ በሚል ርዕስ ስሜትን የሚቀሰቅስ ንግግር አድርጌ ነበር፡፡
በዛሬዋ ዕለት እዚህ የተሰባሰብንበት ዋናው ምክንያት አቶ መለስ ዜናዊ እናት አገራችንን መቅን አሳጥተው ለመበታተን እንዲመቻቸው በበረሃ ሳሉ ነድፈው ያመጡትን ጭራቃዊ ዕቅድ እና ዕኩይ ምግባር ለማውገዝ እና ለማስቆም ነው፡፡ አቶ መለስ የአሰብን ወደብ አሳልፈው በሰጡበት ወቅት ዝምታን በመምረጣችን ወደብ አልባ የመሆንን ዋጋ ከፍለናል፡፡ እ.ኤ.አ በ1998 ባድመ ተወረረች፣ እናም የ80,000 ኢትዮጵያውያን ህይወትን የበላ መስዋዕትነት ተከፍሎ ጠላቶቻችን ከግዛታችን እንዲወጡ ተደረገ፡፡ ሆኖም ግን አቶ መለስ በብርሃን ፍጥነት ተገልብጠው የኢትዮጵያን አንጸባራቂ የጦር ሜዳ ድል ቀልብሰው የዲፕሎማሲያዊ ሽንፈትን በመጋት በእርቅ ሰበብ ስም ባድመን ለወራሪው ኃይል አሳልፈው ለመስጠት ስምምነት አደረጉ… (ዛሬ) በምዕራብ ኢትዮጵያ የሚኖሩ ወገኖቻችን በግልጽ እንደነገሩን የአያት ቅድመአያቶቻቸውን መሬት እና መኖሪያ ቤታቸውን ሳይቀር አቶ መለስ ለሱዳኑ አምባገነን [በዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት በወንጀል ለሚፈለጉት እና ከፍትህ ለማምለጥ እራሳቸውን በመደበቅ ተወሽቀው ላሉት] መሪ ኦማር አልባሽር አሳልፈው ለመስጠት በሚስጥር ስምምነት ፈጽመዋል…
ያንን ንግግር ካደረግሁ ከስድስት ዓመታት በኋላ እንኳን በሚያሳዝን ሁኔታ እናት አገራችንን ለመበታተን አቶ መለስ ከበረሃ ውስጥ ነድፈው ያመጡትን ጭራቃዊ ዕቅድ እኩይ ምግባር ለመቀልበስ ባለመቻላችን አዝናለሁ፡፡ አቶ መለስ አሁን በህይወት የሉም፣ ሆኖም ግን እኛን እንዲያጠፋ ጥለውት ከሄዱት ተንኮላቸው ስራቸው ጋር ፊት ለፊት ተጋትረናል፡፡ “መልካም ሰዎች ዝም ስላሉና ምንም ባላማድረ ጋቸው ይሆን ተንኮል የሚበረታው” የሚለው አባባል እውነታነት አለውን? በመጨረሻም ተንኮልና ጭራቃዊነት ድል ተጎናጽፏልን?
ኢትዮጵያ በአቶ መለስ ዜናዊ ቅርጫ መግባት
እ.ኤ.አ ዴሴምበር 2013 የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የሆኑት ዓሊ ካርቲ የኢትዮጵያ እና የሱዳን ገዥ አካላቶች “ፋሻጋ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ የነበረውን የድንበር አለመግባባት እና በሌሎች አካቢዎችም ያሉትን የድንበር ማካለል ስራዎችንም በሰላማዊ መንገድ ለማጠናቀቅ ስምምነት አድርገናል“ በማለት በግልጽ ተናግረዋል፡፡ ስለሁለቱ አገር መሪዎች አስመልክቶ ካርቲ እንዲህ ብለዋል፣ “የመጨረሻውን የማካለል ስራ ለመተግበር ታሪካዊ ስምምነት አድርገናል፡፡“ የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት በኢትዮጵያ እና በሱዳን መካከል ያሉትን “የድንበር ውዝግቦች” በማስመልከት ለሚቀርቡ አስተያየቶች ሁሉ ምንም ዓይነት ሀሳብ እንደማይቀበል ጠቅሶ ሲናገር፣ “በጠረፉ በተወሰኑ የወሰን ድንበር ነጥብ ቦታዎች ላይ“ በጣም ቀላል የሆኑ አለመግባባቶች ከመኖር በስተቀር ሌላ ቸግር እንደሌለ አስረግጠው ተናግረዋል፡፡
ባለፉት ሳምንታት የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት መምሪያ እንደ ዔሌ አንገቱን ብቅ ጥልቅ እያደረገ በድብቅነት እና ማደናገር በተላበሰ ስልት/strategy “የድንበር ማካለሉን ጉዳይ“ እና “መጠነሰፊ ጠቀሜታ“ አላቸው እያለ ከበሮ የሚደልቅላቸውን “የደህንነት ትብብር ስምምነት፣ የኢኮኖሚ፣ የግብርና፣ የትምህርት እና የባህል“ “የስትራቴጅክ ስምምነት ማዕቀፍ“ በማለት በሚጠራቸው ጉዳዮች ላይ እምነት እንዲያድርብን የፕሮፓጋንዳ ዘመቻዎችን በመሰለቅ ጊዜውን በከንቱ አሳልፏል፡፡
እ.ኤ.አ በ2001 “ለድንበር ውዝግቡ” ይሰጡ የነበሩት ምክንያቶች አሁን እየተሰጡ ካሉት ምክንያቶች ፍጹም የተለዩ ነበሩ፡፡ በዚያን ጊዜ የሱዳን ገዥ አካል እንደገለጸው የድንበር ማካለሉ ስራ አስፈላጊነቱ “የአልቃዳሪፍን ግዛት በሰሜን ኢትዮጵያ ከሚገኘው የትግራይ ግዛት ጋር ‘ለማልማት እና ለማቆራኘት‘ የሚል ነበር… ሁለቱ አካባቢዎች በጣም ለም የነበሩ ሲሆኑ፣ ከዚህም በላይ አልቃዳሪፍ ለሱዳን የዳቦ ቅርጫት ተደርጎ የሚቆጠር ነበር… ከአልቃዳሪፍ እስከ መቀሌ ያለው የመኪና መንገድ…እየተጠገነ እና ደረጃው ከፍ እየተደረገ ነው… የትግራይ ግዛት ከዚህ በመነሳት በዚህ በኩል ወደ ቀይ ባህር የሚያሸጋግረው ዕድል ስለሚያገኝ እና አልቃዳሪፍ ደግሞ ከፖርት ሱዳን ጋር የሚያገናኘው ስለሆነ ተቃሚ ይሆናል፡፡ በዚህም መሰረት ፖርት ሱዳን ለመቀሌ በኤርትራ ግዛት ከሚገኘው የአሰብ ወደብ እና በሶማሌ ግዛት ከሚገኘው የበርበራ ወደብ የበለጠ ቅርብ ትሆናለች…“ የሚል ነበር፡፡
እ.ኤ.አ በ2008 አቶ መለስ ዜናዊ ከሱዳን ጋር የተደረገውን “ስምምነት” አስመልክቶ በውሸት ባህር ውስጥ እየተንቦጫረቁ የጭቃ ጅራፋቸውን ማጮህ ጀመሩ፡፡ በዚያው ዓመት በግንቦት ወር ላይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤታቸው ሙልጭ አድርጎ በመካድ ለመጀመሪያ ጊዜ አንድም ጋት የሚሆን የኢትዮጵያን መሬት ለሱዳን አሳልፎ ለመስጠት የተደረገ ሰምምነት የለም የሚል መግለጫ ሰጠ፡፡ ያ መግለጫ በውጭ የሚገኙትን “የዜና አውታሮች” እና “ኃላፊነት የማይሰማቸው” በበሬ ወለደ የፈጠራ ወሬ የተሰማሩ ሽብር እና ፍርሀትን በህብረተሰቡ ዘንድ የሚነዙ አሸባሪዎች ናቸው በማለት ከሷቸው ነበር፡፡ የሱዳን ባለስልጣኖች ግን ያንን መግለጫ በሚጻረር መልኩ “ከኢትዮጵያ መሬት እንዳገኙ“ በይፋ በአደባባይ ተናግረዋል፡፡ በግንቦት አጋማሽ አቶ መለስ እና አጫፋሪዎቻቸው የመሬት ማደሉን ሚስጥር ደብቀው ማቆየት ባለመቻላቸው ወደ ቀድሞው ታሪካቸው ለመመለስ ተገደዋል፡፡ በድንበር ማካለሉ ወቅት አንዳንድ የቅድመ ስራ እንቅስቃሴዎች ብቻ እንደተከናወኑ፣ እናም የተጠናቀቀ ነገር የለም በማለት በግልጽ ተናግረዋል፡፡ በቀናት ጊዜ ውስጥ አቶ መለስ እና አጫፋሪዎቻቸው ሌላ አዲስ ቅጥፈትን ፈብርከው ብቅ አሉ፡፡ የሆነው “ቀደም ሲል በንጉሱ እና በደርግ ዘመን ከሱዳን ጋር የተደረጉ ስምምነቶችን ተግባራዊ አደረግን” ብለው ጭራ ቀረሽ ዉሸት ፈጠሩ፡፡
የኢትዮ ሱዳን የድንበር ጉዳይ ኮሚቴ ጉዳዩን በግልጽ ሲያቀርበው እና በተጨባጭ በድንበሩ ባሉ አካባቢዎች ላይ ምን እየተደረገ እንዳለ ይፋ ሲያደርግ እስከ አፍ ጢሙ ተቀብትቶ/ሞልቶ የነበረው የውሸት ጎተራ መፈረካከስ ጀመረ፡፡ በአቶ መለስ ለሱዳን መሬት ዕደላ ፖሊሲ ምክንያት የተጎዱ ዜጎቻችን ለአሜሪካ ድምጽ የአማርኛው አገልግሎት እና ለሌሎች ዓለም አቀፍ ብዙሃን መገናኛ ተቋማት ቃለመጠይቅ መስጠት ጀመሩ፡፡ በመሬት ዕደላው ምክንያት ቀጥተኛ ተጎጅ የሆኑ ወገኖቻችን አያት ቅደመ አያቶቻቸው ጠብቀው ያቆዩት መሬት በሱዳን ኃይሎች እየተወረረ ይዞታቸው ሲወሰድባቸው እና ከቀያቸው እና እትብቶቻቸው ከተቀበሩባቸው ቦታዎች ሲባረሩ የነበረውን ሁኔታ በመረረ አኳኋን የተሰማቸውን ቅሬታ በሰፊው ማሰማት ጀመሩ፡፡ የእርሻ መሳሪያዎቻቸው እና የመገልገያ ቁሳቁሶች በሱዳን ወራሪ ኃይሎች መወረሱን ገለፁ:: እንዲሁም በርካታ ኢትዮጵያውያን በሱዳን እስር ቤቶችም ታስረው እንዲማቅቁ አስታወቁ፡፡ በዚያን ጊዜ አቶ መለስ ምንም ምርጫ አልነበራቸውም፣ በግዴታ ሳይወዱ መሬት ለመስጠት ከሱዳን ጋር መፈራረማቸውን ለማመን ተገደዋል፡፡
እ.ኤ.አ በሜይ 2008 አቶ መለስ ከኦማር አልባሽር ጋር ያደረጉትን ስምምነት እንዲህ በማለት ይፋ አድርገዋል፣ “እኛ ኢትዮጵያውያን እና የሱዳን መንግስት የድንበር ማካለሉ ስራ በሚሰራበት ወቅት ከሁሉቱም ወገን አንድም ዜጋ እንዳይፈናቀል ለማድረግ ስምምነት ተፈራርመናል… በ1996 የወሰድነውን መሬት መልሰን ለሱዳን ሰጥተናል፣ ይህ መሬት ከ1996 ዓ.ም በፊት የሱዳን ገበሬዎች ይዞታ ነበር፡፡ አንዳንድ የብዙሃን መገናኛ ተቋማት እንደሚያናፍሱት ሳይሆን በድንበሩ ዙሪያ አካባቢ አንድም የተፈናቀለ ዜጋ የለም፡፡”
እ.ኤ.አ በ2008 በዊክሊስ (የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ አመራር ሚስጥር ሰነድ) ሌላ ወሳኝ የሆኑ መረጃዎች ይፋ ተደርገዋል፡፡ “የቀድሞው የህዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ ማዕከለዊ ኮሚቴ አባል እና የቀድሞው የመከላከያ ሚኒስትር የነበሩት አቶ ስዬ አብርሃ እንዲህ በማለት ተናግረዋል፣ ‘አቶ መለስ በኢትዮጵያ እና በሱዳን መካከል ተፈጥሮ የነበረውን የድንበር ውዝግብ ውጥረት ለማርገብ ጥረት በሚያደርጉበት ወቅት “ለአማራ ክልል ትልቅ ዋጋ ሊያስከፍል የሚችል ግዙፍ መሬት“ አቶ መለስ ለሱዳን ሰጥተዋል፡፡ እናም የአቶ መለስ አገዛዝ “በድብቅ ይዞ ለማቆየት ሞክሯል” አሉ አቶ ስዬ አብርሃ::
ቀደም ሲል አቶ መለስ፣ አሁን ደግሞ የዕኩይ ምግባር ውርስ አጫፋሪዎቻቸው ያንን ስምምነት “በድብቅ ይዘው ለማቆየት” በመውተርተር እና በመዳከር ላይ ይገኛሉ፡፡ ሆኖም ግን እ.ኤ.አ በ2008 አቶ መለስ ከኦማር አልባሽር ጋር ባደረጉት ስምምነት ላይ የሰጡት መግለጫ አንዳንድ ጠቃሚ ምልክቶችን ይሰጣል፡፡ እራሳቸው አቶ መለስ ባመኑት እ.ኤ.አ በግንቦት 2008 በእርሳቸው እና በኦማር አልባሽር መካከል በተደረገው “የመሬት መስጠት ስምምነት” ዝርዝር የስምምነቱን ሁኔታ የሚያመላክት መሆኑ የሚያጣያይቅ አይደለም፡፡ “የስምምነቱን” ሁኔታ ስናጠናው አቶ መለስ በስምምነት መዝገቡ ላይ በርካታ ጠቃሚ ማስረጃዎችን አስቀምጠዋል፡፡ “ስምምነቱ” 1ኛ) መሬቱ በሚሰጥባቸው አካባቢዎች ሰዎችን ሊያፈናቅል የሚችል ጥያቄ መነሳት እንደሌለበት 2ኛ) ከድንበር ማካለሉ ጉዳይ ጋር በተያያዘ መልኩ ከማካለል ስራው ጋር ተያይዞ ጉዳት የሚደርስባቸውን ሰዎች ጥቅሞች የማስጠበቅ ሁኔታ መኖር እንዳለበት 3ኛ) በኢትጵያውያን ገበሬዎች በህገወጥነት መልክ ተይዞ የነበረ የተባለውን መሬት ለሱዳን ገበሬዎች የባለቤትነት መብትን ማስጠበቅ 4ኛ) በ1996 ዓ.ም በህገወጥ መልክ በኢትዮጵያውያን ተይዞ የነበረውን መሬት ለሱዳናውያን መመለስ የሚሉት ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡
በአቶ መለስ ፈቃድ እና አዛዥነት በእራሳቸው እና በኦማር አልባሽር የተፈረመው መሬት የመስጠት ስምምነት “የ1902 የግዌን መስመር/Gwen Line of 1902” (የ1902 የአንግሊዝ-ኢትዮጵያ ስምምነት) እየተባለ የሚጠራው “በኢትዮጵያ እና በሱዳን መካከል ያለውን ድንበር” መስመር ማስያዝ ከሚለው ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት እንደሌለው መገንዘብ ሊሰመርበት የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡ እንደዚሁም እ.ኤ.አ ከ1974 በፊት በንጉሱ ዘመን እና በደርግ ዘመን ከ1995 እስከ 1991 ድረስ የተረቀቁ እና የተፈረሙ የድንበር መካለል ወይም ደግሞ መፍትሄ መስጠት ስምምነቶች ካሉ ከዚህ ስምምነት ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት የላቸውም፡፡ እ.ኤ.አ ከ1996 መጀመሪያ አካባቢ ጀምሮ አቶ መለስ በእራሳቸው ፈቃድ ከድንበር እና ተመሳሳይ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ መልኩ ያደረጉት “ስምምነት” በአቶ መለስ ግላዊ አተያይ የሱዳን መሬት በኢትዮጵያውያን በኃይል የተቀማ ነው በማለት በግላቸው ያደረጉት ህገወጥ እርምጃ እንጅ ሌላ ምንም ዓይነት ማስረጃ የሌለው እርባናቢሰ ስብከት መሆኑ በውል ሊጤን ይገባል፡፡
የኢትዮጵያን “ግዙፍ መሬቶች” በድብቅ እና ለህዝብ ይፋ ሳያደርጉ በሚስጥር ለሱዳን የሚሰጡበት “ስምምነት” ምክንያቱምንድን ነው”?
አቶ መለስ እና አቶ ኃይለማርያም በአጠቃላይ “በድንበር ስምምነቱ” ዙሪያ እያቀረቡት የነበረው እና ያለው የውሸት ፍብረካ ድሪቶ ሪፖርት እውነታውን ለመደበቅ ከሚሽመደመደው ድሁር አስተሳሰባቸው ያለፈ ፋይዳ አይኖረዎም፡፡ እውነተኛው የድንበር መስጠት ስምምነት እ.ኤ.አ በ2008 ተጠናቁአል፡፡ በምንም ዓይነት መልኩ ቢሆን አቶ መለስ “ግዙፍ የሆነ መሬት ከአማራ ክልል” ቆርሰው ፈርመው፣ አትመው እና አሽገው ለሱዳን መስጠታቸውና በድብቅ “በድብቅ ተይዞ እንዲቆይ” መጣራቸው የሚያጠያየቅ ጉዳይ አይደለም፡፡ እ.ኤ.አ በ2014 የኢትዮጵያ የይስሙላው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ የአቶ መለስን የበከተ ውሸት እንደተለመደው “በሀሰት መጋረጃ ደብቀው” ለዘላለም ለማቆየት በማሰብ ሌላ ዘርዘር ያለ ፖለቲካዊ ድራማ ለመተወን በመውተርተር ላይ ይገኛሉ፡፡
አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ እና ጌቶቻቸው የኢትዮጵያን ህዝብ ሊያታልሉ፣ ሊያጭበረብሩ እና በውሸት ሊደልሉ የሚችሉ ይመስላቸዋል፡፡ እነዚህ የዕኩይ ምግባር ባለቤቶች መሬትን ያህል ነገር በድብቅ ሸፍኖ የመስጠት ጨዋታቸውን ኢትዮጵያውያን የማያውቁ እና የማይገነዘቡ ሞኞች አድርገው ይቆጥራሉ፡፡ እነርሱ ይህን የሞኝነት ጨዋታቸውን እንደፈለጉ መጫወት ይችላሉ፣ ሆኖም ግን አቶ ኃይለማርያም አንድ ጥያቄ እንዲመልሱልኝ እፈልጋለሁ፣ ይኸውም “ ‘ከአማራ ክልል ግዙፍ መሬቶችን ቆርሰው የሰጡት’ “ድብቅ የሚስጥር ስምምነቶችን የት እንዳስቀመጧቸው ሊያሳዩኝ ይችላሉን? አቶ መለስ እ.ኤ.አ በ2008 እና አሁን ደግሞ አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ እና የዕኩይ ምግባር አጋሮችዎ የድብቅ ስምምነቶችን ከህዝብ ፊት ደብቃችሁ ከፊታችሁ ላይ የውሸት መጋረጃ በማድረግ ለመዝለቅ የምትፈልጉት ለምንድን ነው?” ከአገር መሬት ቆርሳችሁ ለባዕድ አገር ስትሰጡ በአገሪቱ ህገመንግስት ስልጣን ለተሰጠው ፓርላማ (ለተወካዮች ምክር ቤት) ተብዬው ለይስሙላ እንኳን ቢሆን መቅረብ የለበትምን“? ህገመንግስቱ የሚለው ሌላ የስርዓቱ ቁንጮዎች የሚያደርጉት ሌላ! አራምባ እና ቆቦ!
ከላይ ለቀረቡት ጥያቄዎች መልሱ ቀላል ነው፣ እ.ኤ.አ 2008 አቶ መለስ የተናገሩለት “የሚስጥር ስምምነት“ እና አሁን ደግሞ አቶ ኃይለማርያም እያነበነቡት እንዳለው አይደለም እውነታው፡፡ ህዝብ ግብር እየከፈለ በሚያስተዳድራቸው መገናኛ ብዙሀን ብቅ እያሉ በእብሪት የሚያሰራጩት ነጭ ውሸት ነው፡፡ በእርግጥ አቶ መለስ ይዋሻሉ ማለት “መለስ ወይስ መቀልበስ” መጠሪያ ስማቸው ነው፡፡ ሁሉም አፍጥጠዉ ይዋሻሉ፡፡ አቶ መለስ እና አቶ ኃይለማርያም ከኦማር አልባሽር ጋር በስምምነቶች ላይ ያስቀመጧቸው ቃላት፣ ሀረጎች እና ዓረፍተ ነገሮች ወደ እውነት ተግባርነት የሚሸጋገሩ ከሆነ ከዚህ ጋር ተያይዘው የሚመጡ አደጋዎች ምን ሊሆኑ ይችላሉ? በእውነት እነዚህ የኢትዮጵያን ሉዓላዊ የግዛት አንድነት በመዳፈር መሬቱን እየቆረሱ ለመስጠት ተፅፈው ተፈረመው የተደበቁ ስምምነቶች የአቶ መለስን እና የአቶ ኃይለማርያምን ቀጣፊነት የሚያስረዱ መረጃዎች ሊሆኑ አይችሉምን?
ድብቅነት በኢትዮጵያ በመግዛት ላይ ላለው ገዥው አካል ዋና መለያ ባህሪው ነው፡፡ ነገሮችን ደብቆ በመያዝ እያንዳንዱን በማሞኘት ላይ ይገኛሉ፡፡ አቶ መለስ በህይወት በነበሩበት ጊዜ እና በአሁኑ ጊዜ ያሉት ሎሌዎቻቸው ደግሞ የቅብብሎሽ ዱላውን ከጌታቸው ራዕይ በመቀበል በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ እያሳዩ ያሉት ንቀት የህዝቡን ምንነት ሳይገመግሙ እና ሳይረዱ በራቁት ገላው ላይ ሱፍ እየጎተቱ መሆኑን በውል ሊያጤኑት ይገባል፡፡ አቶ መለስ እና ጋሻጃግሬዎቻቸው አሰብን እና ባድመን በቤሣ ቁርጥራጮች ካስረከቡ በኋላ ዝምታ ብቻ መልስ ስላገኙ ከዚያ ነገር አንድ ቁም ነገር ተምረዋል፡፡ ይኸውም ኢትዮጵያውያንን እና የኢትዮጵያን ግዛት የእነርሱ የግል እንደፈለጉ የሚለውጧት፣ የሚሸጧት የህግ ተጠያቂነት የሌለበት የግል ንብረታቸው መሆኗን አረጋገጡ፡፡
በመለስ/ኃይለማርያም ከምዕራብ ኢትዮጵያ የግዛት አንድነት መሬት በመቁረስ ለሱዳን ለመስጠት የሚደረግ ማንኛውም “ስምምነት” ህገመንግስታዊ አይደለም፡፡
እ.ኤ.አ. ወደ 2008 መለስ ብለን ስናይ አቶ መለስ የኢትዮጵያን መሬት ቆርሰው ለሱዳን ወይም ደግሞ ለማንም ቢሆን ለመስጠት ህጋዊ ስልጣን የላቸውም ብዬ ተከራክሬ ነበር፡፡ ዛሬም ቢሆን አቶ ኃይለማርያም የኢትዮጵያን መሬት ቆርሰው ለሱዳን የመስጠት ህጋዊ መብትም ሆነ ስልጣን የላቸውም፡፡ ይህንን ካልኩ ዘንድ አቶ መለስ “ከአማራ ክልል ግዙፍ የሆነ መሬት” ቆርሰው ለሱዳን ለመስጠት “ስምምነት” እንደተፈራረሙ አጠያያቂ ነገር አይደለም፡፡ አቶ ኃይለማርያም እና ጌቶቻቸው ይህን ህገወጥ የመሬት ዕደላ ዕኩይ ተግባራቸውን “የስልታዊ/ስትራቴጂክ ስምምነት ማዕቀፍ” በማለት የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ በመክፈት ጣፋጭ በማስመሰል በማር የተለወሰ መርዛቸውን ሊግቱን ይፈልጋሉ፡፡ እውነታው ግን በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ በስልጣን ላይ ያለው ገዥ አካል ምንም ዓይነት የኢትዮጵያን መሬት ለሱዳንም ሆነ ለማንም ሌላ አገር አሳልፎ የመስጠት ህገመንግስታዊም ሆነ ዓለም አቀፋዊ መብትም ስልጣንም የለዉም፡፡
በመጀመሪያ ደረጃ ሊታይ የሚችለው ይህ የተካሄደው የድብቅ ስምምነት የኢትዮጵያን ህገመንግስት አንቀጽ 12 የሚጻረር ስለሆነ የህገመንግስት ጥያቄን ያስነሳል፡፡ አቶ መለስ በህይወት በነበሩበት ጊዜ እና እርሳቸውን ተክተው በመስራት ላይ ያሉት የአሁኖቹ ገዥዎቻችን ከኢትዮጵያ ህዝብ እና ከተወካዮች ምክር ቤት በሸፍጥ ደብቀው ከኦማር አልባሽር ጋር ያደረጉትን የሚስጥር “ስምምነት” እየተባለ የሚጠራውን ተግባራዊ ለማድረግ ይፍጨረጨራሉ፡፡ በኢትዮጵያ ህግመንግስት አንቀጽ 12 ስር (“የመንግስት የስራ ድርሻ እና ተጠያቂነት“) እንዲህ ይላል፣ “መንግስት ተጣያቂነት እና ለህዝብ ግልጽነት ባለበት ሁኔታ ስራውን ይሰራል… ማንም የህዝብ ባለስልጣን ወይም ተመራጭ በህግ የተሰጠውን ስልጣን በህግ አግባብ ካልተጠቀመ ተጠያቂ ይሆናል፡፡” አቶ መለስ እና ተኪዎቻቸው “የህዝብ ባለስልጣን” እንደመሆናቸው መጠን ግልጽነት እና ተጠያቂነት ባለበት ሁኔታ ስራቸውን ለማከናወን ህገመንግስታዊ ግዴታ አለባቸው፡፡ ለህዝብ ሳይቀርብ እና የስምምነቱ ሁኔታም በዝርዝር ምን እንደሆነ ሳይታወቅ እንዲሁም ህጋዊ ስልጣን የተሰጠው የተወካዮች ምክር ቤት ሳያጸድቀው የአገርን የግዛት አንድነት በመጣስ መሬት ቆርሶ ለሌላ አገር ለመስጠት በእራስ ፈቃድ የሚደረግ የሚስጥር ስምምነት የህገመንግስቱን አንቀጽ 12 ይጻረራል፣ ሙሉ በሙሉም ህገመንግስቱን ይደፈጥጣል፡፡
እዚህ ላይ በአቶ መለስ እና በተኳቸው የዕኩይ ምግባር ተባባሪዎቻቸው ሸፍጥ በተሞላበት ሁኔታ በስውር መሬት ለሱዳን ለመስጠት እየተደረገ ካለው ሁኔታ ጋር በተያያዘ መልኩ ቁልፍ የሆኑ የህግ ጥያቄዎች ይነሳሉ፡፡ እነዚህም፣ 1ኛ) አቶ መለስም ሆኑ አቶ ኃይለማርያም በኢትዮጵያ ስም ሆነው ቀያጅ የሆኑ “ስምምነቶችን” ወይም “ውሎችን” በግል ለመፈረም ህገመንግስታዊ ስልጣን አላቸውን? 2ኛ) በአቶ መለስም ሆነ በአቶ ኃይለማርያም ፊርማ የሚደረጉ “ስምምነቶች” ከኢትዮጵያ ህገመንግስት አኳያ ህጋዊ ጠቀሜታ ሊኖራቸው ይችላልን? 3ኛ) በአቶ መለስ እና በአቶ ኃይለማርያም የሚደረግ/ጉ ስምምነት/ቶች በቀጣይነት በኢትዮጵያ ስልጣንን በሚይዙ መንግስታት ተግባራዊ መሆን የሚችል/ሉ መሆን እና አለመሆኑ/ናቸው ከዓለም አቀፍ ህግ አንጻር እንዴት ሊታይ ይችላል? 4ኛ) በአቶ መለስ እና አቶ ኃይለማርያም በተፈረመ ስምምነት የተሰጠ የትኛውም በሱዳን የተያዘ የኢትዮጵያ ግዛት በዓለም አቀፋዊ ህግ መሰረት በሌላ አገር እንደተያዘ ሊታይ የሚችል ነው ወይስ አይደለም? 5ኛ) የኢትዮጵያ ህገመንግስት በግልጽ እንዳስቀመጠው “የፌዴራል መንግስቱ ስልጣን እና ኃላፊነቶች” መካከል “የውጭ ፖሊሲ ማውጣት እና መተግበር፣ ዓለም አቀፍ ውሎችን መዋዋል እና ማጽደቅ“ “የፌዴራል መንግስቱ” አጠቃላይ የውጭ ግንኙነቶች እና ስልጣኖች በስራ አስፈጻሚ ማኔጅመንት ተፈርመው የውጭ ግንኙነት መስኮች እና “የዓለም ዓቀፋዊ ስምምነቶች“ በፓርላማው ይጸድቃሉ/አይጸድቁም፡፡ አንቀጽ 55 (12) በግልጽ እንዳስቀመጠው ዓለም ቀፍ ስምምነቶችን በሚመለከት በስራ አስፈጻሚው ተፈርሞ ለተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ በፓርላማው ታይቶ ይጸድቃል፣ የተወካዮች ምክር ቤት ከተሰጡት ዋና ዋና ኃላፊነቶች አንዱ ስራ አስፈጻሚው ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን ህጎችን ፈርሞ ሲያቀርብለት ፓርላማው መርምሮ ያጸድቃል፡፡”
የአቶ መለስ እና አቶ ኃይለማርያም በራሳቸው ፈቃድ መሬት ለመስጠት የሚያደርጓቸው “ስምምነቶች” የህገመንግስቱን አንቀጽ 55 (12) የሚደፈጥጥ ነው፡፡ አቶ መለስ እና አቶ ኃይለማርያም ከሌላ መንግስታት ጋርም ስምምነቶችን ለመደራደር እና ለመፈረምም ይችላሉ፡፡ በህገ መንግስቱ የተሰጣቸው ስልጣን ለመደራደር፣ ለማርቀቅ እና ዓለም አቀፋዊ ስምምነቶችን በመፈረም ላይ ብቻ የተወሰነ ነው፡፡ ሆኖም ግን አቶ መለስ እና አቶ ኃይለማርያም ከሌላ መንግስታት ጋር የሚያደርጓቸው “ስምምነቶች” ፊርማ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአንቀጽ 55 (12) በግልጽ እንደተቀመጠው ሁሉ ካልጸደቀ በስተቀር የተጻፈበትን ወረቀት ዋጋ ያህል አያወጣም፡፡
አቶ መለስ እና አቶ ኃይለማርያም ሁለቱም መሬት ለመስጠት ከሱዳን ጋር ያደረጓቸውን ስምምነቶች ፓርላማው እንዲያጸድቃቸው ለማቅረብ ፈቃደኞች አልሆኑም፡፡ እንዲሁም በጨዋነት መንፈስ ቢያንስ ፓርላማው እንዲወያይበት እንኳ ስምምነቶች ለመስጠት ፈቃደኞች አልሆኑም፡፡ ስምምነቶችን ፓርላማው እንዲያጸድቃቸው ለማቅረብ አለመቻል ህገመንግስታዊ የስራ ኃላፊነት ድርሻን እና መርሆዎችን የጣሰ ከመሆኑም በላይ ፓርላማው ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን ለማጽደቅ ባለው ስልጣን ላይ እየተደረገ ያለ ጣልቃገብነትን የሚያመላክት ነው፡፡
አንቀጽ 86 “የውጭ ግንኙነት መርሆዎችን“፣ የ“ፌዴራል መንግስትን“ (የጠቅላይ ሚኒስትሩን፣ የተወካዮች ምክር ቤትን) ኢትዮዮጵያ ከሌሎች አገሮች ጋር እና ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ጋር ያላትን ግንኙነት ይገልጻል፡፡ አንቀጽ 86 ንኡስ አንቀጽ 1 እና 3 የፌዴራል መንግስቱ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ “በእኩልነት እና በጋራ ጥቅም ላይ የተመሰረተ፣ ዓለም አቀፍ ህጎች እንዲከበሩ የማድረግ፣ የኢትዮጵያን ህዝብ ጥቅም ማስጠበቅ“ እና ዓለም አቀፍ ህጎች እና ስምምነቶች እንዲከበሩ፣ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት እና ከህዝብ ፍላጎት በተጻራሪ የሚቆሙትን እንደማይቀበል በግልጽ ያስቀምጣል፡፡
አቶ መለስ እና አቶ ኃይለማርያም ከሱዳን ጋር የተፈረመውን ስምምነት ሚስጥር አድርገው የያዙበት ዋናው ምክንያት እነዚህ ስምምነቶች የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት በግልጽ በአገጠጠ እና በአፈጠጠ መልኩ የሚጥሱ መሆናቸውን ስለሚያውቁ ዕኩይ ምግባሮቻቸውን ለመደበቅ ያሰቡት የሸፍጥ ስራ ነው፡፡ እነዚህ የሸፍጥ ሰዎች “ስምምነቶችን” ሚስጥር ማድረግ ይፈልጋሉ ምክንያቱም የኢትዮጵያን ጥቅም አሽቀንጥረው የጣሉ በመሆኑ እውነታው በተጫባጭ ጎልቶ እንደሚታይ እና ከኢትዮጵያ ጥቅም በተቃራኒ የቆሙ ከሀዲዎች መሆናቸውን ያውቃሉ እና ነው፡፡ ስምምነቱን ሚስጥር አድርጎ መያዝ ከላይ ከተጠቀሱት የተለዬ ሌላ ምክንያት በፍጹም ሊኖር አይችልም፡፡ በሌላ በኩል ሚስጥር አድርገው የያዟቸውን ስምምነቶች ግልጽ ያድርጉ እና እኔ እነዚህ ስምምነቶች የተደረጉት እኩልነትን ባዛነፈ መልኩ ነው፣ ኢትዮጵያን ብቸኛ ተጎጅ ያደረገ ነው እያልኩ የምሟገተውን በመርታት ማስተባበል ይችላሉ፡፡
አንቀጽ 9 (“የህጎች ሁሉ የበላይ“) ይህንን አስመልክቶ ህገመንግስቱ የአገሪቱ የህጎች ሁሉ የበላይ መሆኑን በግልጽ ያስቀምጣል፡፡ ሁሉም ህጎች፣ ወጎች፣ ልማዶች እና በመንግስት አካላት የሚደረጉ ውሳኔዎች ወይም የህዝብ ባለስልጣኖች ከዚህ ጋር በተያያዘ መልኩ ተጻራሪ ሆነው ከተገኙ ተፈጻሚነት አይኖራቸውም፡፡ ሁሉም ዜጎች፣ የመንግስት አካላት፣ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ ሌሎች ማህበራት እና ባለስልጣኖቻቸው ህገመንግስቱን ማክበር ማስከበር እና በህጎቹም መገዛት… ማንኛውም ስልጣንን ለመያዝ የሚፈልግ አካል ሁሉ በህገመንግስቱ ከተደነገገው ውጭ ስልጣንን ለመያዝ ማሰብ የተከለከለ መሆኑን በግልጽ ያመላክታል፡፡”
በአቶ መለስ እና አቶ ኃይለማርያም የሚደረግ ማናቸውም “ስምምነት” “ውል” “የጋራ ስምምነት” “ድርድር” አንቀጽ 55 (12)፣ አንቀጽ 86 (2) (3) ተፈጻሚነት አይኖረውም፡፡ በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ህገመንግስት ተፈጻሚነት የማይኖረው ህግ ወደፊት ስልጣን የሚይዙ ህጋዊነትን የተላበሱ ተከታታይ የኢትዮጵያ መንግስታት ሊቀበሉት የማይችል ዓለም አቀፍ ህግ በኢትዮጵያ ተፈጻሚነት ሊኖረው ይችላልን?
አንቀጽ 9 (4) የኢትዮጵያ ህገመንግስት እንዲህ ይላል፣ “በተወካዮች ምክር ቤት የጸደቁ ዓለም አቀፍ ስምምነቶች“ የአገሪቱ የህጎች ሁሉ የበላይ ናቸው፡፡” ሌሎችስ በኢትዮጰያ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያልጸደቁ ዓለም አቀፍ ህጎች ምን ሊባሉ ነው? ይህንን ጥያቄ ለመመለስ ማንም ቢሆን የህገመንግስት ልሂቅ መሆንን አይጠይቅም፣ ዓለም አቀፍ ህጎች በኢትዮጵያ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እስካልጸደቁ ድረስ የተጻፉበትን ወረቀት ያህል ዋጋ አያወጡም፡፡ ማንም ህጋዊነትን ተላብሶ ስልጣን የሚይዝ ቀጣይ የኢትዮጵያ መንግስት ተፈጸሚነት በማይኖራቸው ህጎች ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን የመፈጸም ግዴታ የለበትም፡፡ ኢትዮጵያ እንደዚህ ያሉትን ስምምነቶች የማውገዝ እና ሱዳኖች ከህግ አግባብ ውጭ በተጽዕኖ ከያዟቸው ይዞታዎች ለኢትዮጵያ አስረክበው በዓለም የህግ አግባብ መሰረት ከኢትዮጵያ ግዛት እንዲወጡ ይደረጋል፡፡
የዓለም አቀፋዊው ህግ ስምምነቶች በመንግስታት መካከል መተግበር እንዳለባቸው ግዴታ የሚጥል እንደመሆኑ መጠን (ስምምነቶች መጠበቅ አለባቸው በሚለው መርሆ መሰረት) እንደዚሁም የተወሰኑ የህግ ማዕቀፎች መንግስት ሊያወግዛቸው እና ከመተግበርም ሊቆጠብ የሚችልባቸው (ሊያቋርጣቸው) ወይም ደግሞ በመጀመሪያ ስምምነቶቹ በሚፈረሙበት ጊዜ ስህተት ተሰርቷል ብሎ ካመነ እና ካረጋገጠ ስምምነቶችን ሊሰርዛቸው ወይም ከስምምነቶች እራሱን ሊያገል እንደሚችል ዕድል ይሰጣል፡፡
የቬና ስምምነት በህግ ውል ላይ ውዝግብ በሚነሳበት ጊዜ ውሳኔ ሊያሳልፍ እንደሚችል ብዙ ስምምነቶች የህግ መሰረት የሌላቸው ብሎ ውድቅ ሊያደርግ እንደሚችል በግልጽ ያስቀምጣል፡፡ አንቀጽ 46 (1)፣ (2) (“ተፈጻሚነት የማይኖራቸው ውሎች“) ተፈጻሚነት የማይኖራቸውን ስምምነቶች ከአንድ አገር “የውስጥ ህጎች” አንጻር ተፈጻሚነት ሊኖራቸው እንደማይችል ከግንዛቤ በማስገባት እንዲህ ይላል፣መንግስት ለአንድ ስምምነት ተገዥ ሊሆን የሚችለው በሀገሩ ያለውን ህግ የሚጥስ እስካልሆነ ድረስ እና ያደረገው ስምምነትም በአገሪቱ ካለው የህግ ማዕቀፍ ጋር የማይቃረን እስከሆነ ድረስ ብቻ ነው፡፡በተግባር እና በልማድ መተግበር ካለበት ሁኔታ ውጭ በሆነ መልኩ አንድ መንግስት በእራሱ ህግ አውጥቶ ስምምነት ቢገባ ተፈጻሚነት ሊኖረው አይችልም፡፡
አንቀጽ 49 የሚከተለውን መብት ያጎናጽፋል፣ “አንድ መንግስት ከሌላ እምነት ከማይጣልበት መንግስት ጋር ስምምነት ቢዋዋል ይህ ውል ተፈጻሚነት አይኖረውም“ አንቀጽ 50 እንዲህ ይላል፣ “መንግስት ከሌላ መንግስት ጋር በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ የማይገባ ጥቅም በመስጠት ውል የተዋዋለ ከሆነ ያ ውል በአገሪቱ ህግ ተፈጻሚነት አይኖረውም“ መንግስቱን ወይም ደግሞ የመንግስቱን ተወካይ በማስገደድ የተደረገ ስምምነት ካለ ይህ የግዳጅ ስምምነት ስምምነቱን ለማፍረስ መሰረት ይሆናል፡፡
ሊካድ የማይችለው ነገር እነዚህ ተአማኒነት የሌላቸው ስምምነቶች በአቶ መለስ እና በአቶ ኃይለማርያም በሁለቱም ባለስልጣኖች የተፈረሙ ቢሆንም ከላይ በግልጽ ለማመልከት እንደተሞከረው ከኢትዮጵያ ህገመንግስት አንጻር ተፈጻሚነት አይኖራቸውም፡፡ ሌሎች ሊነሱ የሚችሉ ጥያቄዎች ቢኖሩ የሚከተሉት ናቸው፣ 1ኛ) አንቀጽ 55 (12) ከሚፈልገው የህግ ማዕቀፍ አንጻር ከሱዳን ገዥ አካል ጋር ገና ስምምነቶቹ ሲፈረሙ ግልጽ በሆነ መልክ ጉዳዩ ለሚመለከተው ፓርላማ ቀርቦ እንዲጸድቅ የተደረገ መሆን አለመሆኑ፣ 2ኛ) ስምምነቱ በሚከናወንበት ወቅት “ሙስና” እና “የማጭበርበር ወንጀል” የነበረ ወይም ያልነበረ መሆኑ፣ 3ኛ) ስምምነቱ በሚካሄድበት ጊዜ “አስገዳጅነት” ያላቸው ወይም ለማስገደድ የሚያበቁ ድርጊቶች የነበሩ ወይም ያልነበሩ መሆናቸው፣ በኢትዮጵያ ወገን በኩል ህጉን መርምሮ የማጽደቅ ሂደት ያልተከናወነ ስለነበር ኦማር አልባሽርን በሚጠቅም መልኩ የተፈጸመ እንዲሁም ስምምነቱ ለኢትዮጵያ የተወካዮች ምክር ቤት እንዲቀርብ እና እንዲጸድቅ ያልተደረገ ስለሆነ የተፈጻሚነት ዕድል እንደማይኖረው የሚያጠራጥር አይደለም፡፡ በቬና ስምምነት መሰረት ሱዳን ለኢትዮጵያ መንግስት ስምምነቱን የማጽደቅ ዕድል መስጠት እንዳለባት የህግ ግዴታ አለባት፡፡ እራሷን ከጉዳዩ ጋር በማስተሳሰር በተለመደው ልምድ እና እምነት መሰረት ሱዳን ስምምነቱን ለማጸደቅ ስራዎችን ልትሰራ ይገባል፡፡ በአጠቃላይ ከስምምነቱ ጋር በተያያዘ መልኩ ሚስጥር ሆኖ መያዙ እና በስምምነቱ ዙሪያም ምንም ዓይነት ፍንጭ እንዳይኖር ድብቅ ለማድረግ ከሚደረገው ጥረት አንጻር ወደፊት ስምምነቱን በጥልቀት እና በዝርዝር በመመርመር የሚገኘው የመረጃ ውጤት ሙስና፣ የማጭበርበር ወንጀል እና የግዳጅ ውል ሆኖ ይገኛል፡፡
የኢትዮጵያን መሬት ለሱዳን የመስጠት ስምምነቶችን ተፈጻሚነት የመሆን ዕድል የሚጻረሩ ሌሎች ህገመንግሰታዊ ጉዳዮች
አቶ መለስ እና አቶ ኃይለማርያም ግዙፍ የሆነ መሬት “ከአማራ የግዛት ክልል” በመቁረስ ለሱዳን በማስረከባቸው የአማራን ህዝብ የጋራ መብቶች ደፍጥጠዋል፡፡ “ስምምነቶቹ” አንቀጽ 39ን (የብሄር ብሄረሰቦች እና ህዝቦች መብት) እንዲሰጥ ስምምነት በተደረገበት መሬት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን በግዳጅ ከሉዓላዊ ግዛታቸው በመነጠል ከፍላጎታቸው ውጭ ወደ ሱዳን አሳልፎ የሚሰጥ ስለሆነ ህጉ ተፈጻሚነት እንዳይኖረው ይጻረራል፡፡ አቶ መለስም ሆኑ አቶ ኃይለማርያም መሬት የማስመለስ፣ ብልህነት በጎደለው መልኩ በግዛት ላይ እና በግዛቱ በሚኖሩ ህዝቦች ላይ ድርድር የማድረግ ወይም ደግሞ በእራሳቸው ውሳኔ “የብሄሮችን እና የህዝቦችን” በመሬታቸው ላይ ያላቸውን መብት በመንጠቅ ሳይጠየቁና ምክር እንዲያደርጉ ዕድል ሳያገኙ በሌላ አባባል ሪፈረንደም ሳይሰጥ የመሬት ግዛታቸውን በድብቅ በተሸፈነ ሴራ በመንጠቅ ለሌላ አገር አሳልፎ የመስጠትም ሆነ ስምምነት የማድረግ ህገመንግስታዊ ስልጣን የላቸውም፡፡ በዓለም አቀፋዊ ህግ መሰረት መንግስት የአንድን አገር ሉዓላዊ ግዛት ለሌላ ባዕድ አገር አሳልፎ ከመስጠቱ በፊት ሊሰጥ በታሰበው መሬት ላይ ወይም በዚያ ግዛት ላይ የሚኖሩ ህዝቦችን የማማከር ግዴታ አለበት፡፡ ማማከር ሲባልም የህግ ሂደቱን ለመጠበቅ እንጅ መንግስት ከዚህ ጉዳይ ጋር በተያያዘ መልኩ እጁን ዘው አድርጎ በማስገባት ምንም ዓይነት ውሳኔ መስጠት እንደማይችል ልብ ሊባል ይገባል፡፡ ይህም ሆኖ “በአማራ ክልል የሚገኘውን ግዙፍ የመሬት ግዛት” ለሱዳን መንግስት አሳልፎ ለመስጠት ስምምነት ከመፈራረማቸው በፊት በአቶ መለስም ሆነ በአቶ ኃይለማርያም በኩል ህዝቡን ለማማከር የተሞከረ ነገር የለም፡፡
ከዚህም በላይ የኢትዮጵያ ህግመንግስት አንቀጽ 2 የሚከተለውን መብት ያጎናጽፋል፣ “በዓለም አቀፍ ህግ ስምምነት እና ኢትዮጵያም ተቀብላ ባጸደቀቸው ህግ መሰረት የኢትዮጵያ ሉዓላዊ የግዛት አንድነት በአገሪቱ ውስጥ የሚገኙ አባል ክልላዊ መንግስታት ፌዴሬሽን ድንበሮችን አካትቶ የያዘ ነው፡፡“ ይኸ ህገመንግስታዊ ቋንቋ የአገር ውስጥ እና የውጭ የወሰን ድንበሮቻቸው ሲካለሉ እና ሲዘጋጁ “የክልል አባል መንግስታት” የሚኖራቸውን ቀጥተኛ ሚና መስተጋብር በግልጽ ያሳያል፡፡ የህገመንግስቱ አንቀጽ 2 የኢትዮጵያ የፌዴራላዊ መንግስት አካል መሬቱን ለሱዳን አሳልፎ የሚሰጠውን ስምምነት ከመፈረሙ በፊት “በአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት” የወሰን ክልል ውስጥ የሚኖረው ህዝብ ሪፍረንደም/referendum (ጠቅላላ የህዝብ ድምጽ) ማድረግ እንዳለበት በግልጽ አስቀምጦታል፡፡
ከሱዳን ጋር የተደረገው ህገወጥ ስምምነት ተፈጸሚነት ስለማይኖረው ብዙም አያሳስብም
በአቶ መለስ፣ አቶ ኃይለማርያም እና ጓዶቻቸው የተደረገው ህገወጥ ስምምነት ተፈጻሚነት የማይኖረው ቢሆንም በመጠኑም ቢሆን አሳስቦኛል፣ ሆኖም ግን በግልጽ እና ጥልቀት ባለው መንገድ ሳገናዝበው ብዙ የሚያሳስበኝ አይሆንም፡፡ “ስምምነት” እየተባለ ስለሚጠራው ጉዳይ ብዙ የሚታወቁ ድብቆች አሉ፡፡ ስምምነቶቹን ካባ ደርበው ትልቅ ነገርን እንደፈረሙ እናውቃለን፡፡ ሆኖም ግን ምን እንደደበቁ በእርግጠኝነት ለመናገር አይቻልም፡፡ ስምምነቶቹን ከህግ አግባብ ውጭ በሙስና እንዳደረጉ እናውቃለን፣ ሆኖም ግን የሙስናውን ስፋት እና ጥልቀት እስከምን ድረስ እንደሆነ በግልጽ አይታወቅም፡፡ ስምምነቶቹ ሲፈጸሙ ማታለል እንዳለባቸው እናውቃለን፣ ሆንም ግን የማታለሉ ደረጃ እስከምን ደረጃ እንደሆነ አናውቅም፡፡ ስምምነቶቹ ሲፈጸሙ ማጭበርበር እንዳለባቸው እናውቃለን፣ ሆኖም ግን የማጭበርበሩ ስፋት እና ጥልቀት ደረጃ እስከምን ድረስ እንደሆነ አናውቅም፡፡ የስምምነት ሰነዶች ሲፈረሙ ሁሉንም ዓይነት ያካተቱ ማጭበርበሮች እንዳሉ እናውቃለን፣ ሆኖም ግን የማታለል፣ የማጭበርበር እና የመሰሪነት ዓይነቶችን አናውቅም፡፡ በድብቅ የተፈረሙት ስምምነቶች እና አሁንም ሚስጥር ሆነው የተያዙት ድሁር እና ኮሳሳ ስምምነቶች ወደፊት በጊዜ ሂደት እርቃናቸውን ወጥተው ሚስጥሩ ግልጽ የሚሆንበት ጊዜ ይመጣል፡፡ ”እውነት ለዘላለም ተቀብራ እንደማትኖር ሁሉ ተንኮልም በዙፋን ላይ ለዘላለም ተቀምጣ አትኖርም”፡፡
የኢትዮጵያ የግዛት ሉዓላዊነት አንድነት በምንም ዓይነት መልኩ ለድርድር አይቀርብም፡፡ አቶ መለስ ዜናዊ፣ አቶ ኃይለማርያም ዳሳለኝ…ሌላም ማንም… ቢሆን በኢንቨስትመንት የማስመሰያ ጨዋታ የኢትየጵያን ለም መሬቶች በቅርጫ ለሱዳን፣ ለሳውዲ ወይም ለህንድ “ባለሀብቶች” ሊሰጥ አይችልም፡፡ እውነታው ግን ጀሴ ጀምስ እና ወሮበላ ጓዶቹ (በአሜሪካ የታውቁ ዘራፊዎች) የዘረፏቸውን ባንኮች ለሌላ የመስጠት መብት እንዳላቸው አድርገው እንዳሰቡት ሁሉ የኢትዮጵያ ቁንጮ አምባገነን መሪዎች ደግሞ የኢትዮጵያን ለም መሬት የመስጠት መብት እንዳላቸው ቆጥረውታል፡፡
ጥንታዊ የሆነች ኢትዮጵያ የምትባል አገር አለች፣ የእኛ እናት ሀገር፡፡ ኢትዮጵያ በክልል መከፋፈል የለባትም፣ “በጎሳ ፌዴራሊዝም” መበጣጠስ የለባትም፣ ወይም ደግሞ በድንበር መካለል ሰበብ “ስምምነት” መሰረት ግዛቷ መሸጥ የለበትም፡፡ ወደ የግዛት ሉዓላዊነት አንድነቷ የተጠበቀች ኢትዮጵያ ስንመጣ ኦሮሞ ኢትዮጵያ የለችም፣ አማራ ኢትዮጵያ የለችም፣ ትግሬ ኢትዮጵያ የለችም፣ ጉራጌ ኢትዮጵያ የለችም… ወይም ደግሞ ጋምቤላ ኢትዮጵያ የለችም፡፡ በቀላሉ አነጋገር የኢትዮጵያ ህዘቦች ኢትዮጵያ ናት ያለችው፡፡ በሉዓላዊነት የግዛት አንድነት ዙሪያ በመሰባሰብ ኢትዮጵያ የማትከፈል እና የማትከፋፈል መሆኗን በማመን መተባበር አለብን፡፡ ምንጊዜም ቢሆን ጠንቃቃ ሆነን መገኘት አለብን፣ እናም ከመቃብር አፋፍ ላይ ሆነው ለማትረፍ የሚፈልጉ ተንኮለኛ ጭራቆችን እራሳቸው በመቃብር ውስጥ እንዲቀሩ እናድርግ፡፡ አምላክ ሁላችንንም አንድ አድርጎ እንደፈጠረን ሁሉ በፍቅር እና በመከባበር በአንድነት በመኖር ለአምባገነንነት፣ ለጨፍጫፊነት፣ ለመለያየት ቦታ መስጠት የለብንም፡፡ ዛሬም አንዲት ኢትዮጵያ! ነገም አንዲት ኢትዮጵያ! ለዘላለምም አንዲት ኢትዮጵያ!
ኢትዮጵያ ለዘላለም በክብር ትኑር!
ጥር 27 ቀን 2006 ዓ.ም
ምንጭ የኢትዮጵያ ሜዲያ መድረክ
Monday, February 3, 2014
''ከዚህ በኋላ ስለጀግኖቹ ንጉሶች እየዘፈኑ መኖር ያብቃ፤ ታሪካቸውም እኛም በጀግንነታችን እንጠብቀው'' - የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር በጎንደር
(ምንሊክ ሳልሳዊ በጎንደር የተካሄደውን ህዝባዊ ስብሰባ እንዳለ ተጀምሮ እስኪያልቅ እንዳስቀመጠው አቅርበነዋል)
በጎንደር ከተማ የተካሄደው ሰላማዊ ሰልፍ ህብረተሰቡ
የአካባቢው አስተዳዳሪዎችን ማስፈራሪያ እና ጥርነፋ
ተቋቁሞ የወጣ ሲሆን ቅዳሜ እለት በተሳካ ሁኔታ
ተካሄዷል፡፡ በጎንደር መስቀል አደባባይ በርካታ የከተማው
ነዋሪዎች የወጡ ሲሆን ሀገራዊ ዜማዎችንና መፈክሮችን
አሰምተዋል።
ተጠብቆ የቆየው ባባቶቻችን ደም
እናት ኢትዮጵያ ያስደፈረሽ ይውደም
ሉዓላዊነታችንን አናስደፍርም
አባቶቻችን ያስረከቡንን መሬት አሳልፈን አንሰጥም
ወያኔ አምባገነን ነው ወደሚለው መፈክር ተገብቷል
ወያኔ አይወክለንም ከፍ ባለ ድምፅ እየተስተጋባ ይገኛል መስቀል አደባባይ በዝማሬ የታጀበ መፈክር እየተሰማ ነው
የሰማያዊ ፓርቲ አስተባባሪ ለህብረተሰቡ በዚህ አስቸጋሪ ወቅትና አምባገንን ስርዓት ውስጥ ሆናችሁ የሀገራችን ጉዳይ ያገባናል ብላችሁ
ስለመጣችሁ እናመሰግናለን በሚል ንግግር ፕሮግራሙን ከፍተው የሰልፉን አላማ አብራርተው የፓርቲውን ሊቀመንበር ወደ መድረክ
ጋብዘዋል፡፡ የፓርቲው ሊቀመንበርም ለተሰላፊዎቹ ባስተላላፉት መልእክት ለወጣቶች የሀገራቸውን ክብር እንዲያስጠብቁ እራሳቸውንም
ከፍርሀት እና ከስጋት በማላቀቅ ለራሳቸውም ለሀገራቸውም አለኝታ እንዲሆኑ፤ እንዲሁም ስርዓቱ ላይ ያሉት አስተዳደሮች ስልጣን
ወቅታዊ መሆኑን አውቀው በኢትዮጵያ ድንበር ላይ እየተፈጸመ ያለውን ደባ እንዲያስቆሙ ከታሪክ ተጠያቂነት እንዲድኑ፤
ለልጆቻቸውም ውርደትን ሳይሆን ክብርን እንዲያወርሱ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ፓርቲውም የጠራውን ሰልፍ እና ማስተላለፍ የፈለገውን
መልእክት በተሳካ ሁኔታ አስተላልፎ ፕሮግራሙን አጠናቋል፡፡ ፓርቲውም በአካባቢው የሚገኙ የፓርቲው አስተባባሪዎችን እንዲሁ
የጎንደር እና የአካባቢው ህዝብን ለዚህ ሰልፍ መሳካት ላደረጉት አስተዋጽኦ ከፍ ያለ ምስጋና አቅርቧል፡፡
የጎንደሩ የተቃውሞ ሰልፍ ሲጠናቀቅ ህዝቡ በመሬቱ ቀልድ እንደማያውቅ በአደባባይ አስረግጦ አሳውቋል። የሰማያዊ ፓርቲ
ሊቀመንበር ኢንጅነር ይልቃል ጌትነት ''ከዚህ በኋላ ስለጀግኖቹ ንጉሶች እየዘፈኑ መኖር ያብቃ ታሪካቸውም እኛም በጀግንነታችን
እንጠብቀው'' ብለዋል። በስልክ ያናገርኳት አንዲት የጎንደር ወጣት አሁን ገና በአይናችን መጡብን ብላኛለች። ለሱዳን ሊሰጥ ነው
የሚለው ወሬ ከተሰማ ወዲህ ኢትዮጵያውያን በሀገር ቤት ድምጻቸውን ሲያሰሙ የጎንደሩ የመጀመሪያው ነው።
ጎንደር ላይ የተካሄደው ሰልፍ ባማረ መልኩ ተጠናቀቀ ለሰልፉ መሳካት ትልቅ ሚና ለተጫወቱት የጎንደር ወጣቶች፣ የሰማያዊ ፓርቲ
አመራሮች እና አባላት እንዲሁም በማህበራዊ ድህረ ገፆች ህዝቡን በመቀስቀስ እና መረጃ በማስተላለፍ ሰልፉ እንዲሳካ ላደረጉት
በሙሉ ከፍ ያለ ምስጋና ይገባቸዋል።
የኢትዮጵያ ትንሣኤ እየቀረበ ነው!!
እምዬ ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!!
ኢትዮሚድያ - Ethiomedia.com
February 2, 2014
በጎንደር ከተማ የተካሄደው ሰላማዊ ሰልፍ ህብረተሰቡ
የአካባቢው አስተዳዳሪዎችን ማስፈራሪያ እና ጥርነፋ
ተቋቁሞ የወጣ ሲሆን ቅዳሜ እለት በተሳካ ሁኔታ
ተካሄዷል፡፡ በጎንደር መስቀል አደባባይ በርካታ የከተማው
ነዋሪዎች የወጡ ሲሆን ሀገራዊ ዜማዎችንና መፈክሮችን
አሰምተዋል።
ተጠብቆ የቆየው ባባቶቻችን ደም
እናት ኢትዮጵያ ያስደፈረሽ ይውደም
ሉዓላዊነታችንን አናስደፍርም
አባቶቻችን ያስረከቡንን መሬት አሳልፈን አንሰጥም
ወያኔ አምባገነን ነው ወደሚለው መፈክር ተገብቷል
ወያኔ አይወክለንም ከፍ ባለ ድምፅ እየተስተጋባ ይገኛል መስቀል አደባባይ በዝማሬ የታጀበ መፈክር እየተሰማ ነው
የሰማያዊ ፓርቲ አስተባባሪ ለህብረተሰቡ በዚህ አስቸጋሪ ወቅትና አምባገንን ስርዓት ውስጥ ሆናችሁ የሀገራችን ጉዳይ ያገባናል ብላችሁ
ስለመጣችሁ እናመሰግናለን በሚል ንግግር ፕሮግራሙን ከፍተው የሰልፉን አላማ አብራርተው የፓርቲውን ሊቀመንበር ወደ መድረክ
ጋብዘዋል፡፡ የፓርቲው ሊቀመንበርም ለተሰላፊዎቹ ባስተላላፉት መልእክት ለወጣቶች የሀገራቸውን ክብር እንዲያስጠብቁ እራሳቸውንም
ከፍርሀት እና ከስጋት በማላቀቅ ለራሳቸውም ለሀገራቸውም አለኝታ እንዲሆኑ፤ እንዲሁም ስርዓቱ ላይ ያሉት አስተዳደሮች ስልጣን
ወቅታዊ መሆኑን አውቀው በኢትዮጵያ ድንበር ላይ እየተፈጸመ ያለውን ደባ እንዲያስቆሙ ከታሪክ ተጠያቂነት እንዲድኑ፤
ለልጆቻቸውም ውርደትን ሳይሆን ክብርን እንዲያወርሱ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ፓርቲውም የጠራውን ሰልፍ እና ማስተላለፍ የፈለገውን
መልእክት በተሳካ ሁኔታ አስተላልፎ ፕሮግራሙን አጠናቋል፡፡ ፓርቲውም በአካባቢው የሚገኙ የፓርቲው አስተባባሪዎችን እንዲሁ
የጎንደር እና የአካባቢው ህዝብን ለዚህ ሰልፍ መሳካት ላደረጉት አስተዋጽኦ ከፍ ያለ ምስጋና አቅርቧል፡፡
የጎንደሩ የተቃውሞ ሰልፍ ሲጠናቀቅ ህዝቡ በመሬቱ ቀልድ እንደማያውቅ በአደባባይ አስረግጦ አሳውቋል። የሰማያዊ ፓርቲ
ሊቀመንበር ኢንጅነር ይልቃል ጌትነት ''ከዚህ በኋላ ስለጀግኖቹ ንጉሶች እየዘፈኑ መኖር ያብቃ ታሪካቸውም እኛም በጀግንነታችን
እንጠብቀው'' ብለዋል። በስልክ ያናገርኳት አንዲት የጎንደር ወጣት አሁን ገና በአይናችን መጡብን ብላኛለች። ለሱዳን ሊሰጥ ነው
የሚለው ወሬ ከተሰማ ወዲህ ኢትዮጵያውያን በሀገር ቤት ድምጻቸውን ሲያሰሙ የጎንደሩ የመጀመሪያው ነው።
ጎንደር ላይ የተካሄደው ሰልፍ ባማረ መልኩ ተጠናቀቀ ለሰልፉ መሳካት ትልቅ ሚና ለተጫወቱት የጎንደር ወጣቶች፣ የሰማያዊ ፓርቲ
አመራሮች እና አባላት እንዲሁም በማህበራዊ ድህረ ገፆች ህዝቡን በመቀስቀስ እና መረጃ በማስተላለፍ ሰልፉ እንዲሳካ ላደረጉት
በሙሉ ከፍ ያለ ምስጋና ይገባቸዋል።
የኢትዮጵያ ትንሣኤ እየቀረበ ነው!!
እምዬ ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!!
ኢትዮሚድያ - Ethiomedia.com
February 2, 2014
Subscribe to:
Posts (Atom)



