Monday, August 25, 2014

ከጥቅሙ ጉዳቱ ይበልጣል (ፕ/ር መስፍን ወልደ ማርያም)

መስፍን ወልደ ማርያም
ሐምሌ 2006
ፕ/ር መስፍን ወልደ ማርያም
ፕ/ር መስፍን ወልደ ማርያም
ጉልበት አራዊት የሚተዳደሩበት ሕግ ነው፤ ሕገ አራዊት የሚባለው አራዊት የሚተዳደሩበት ጉልበት ነው፤ በአራዊት ዓለም ማናቸውም ነገር በጉልበት ያልቃል፤ በሰዎችም መሀከል ጉልበት አድራጊ-ፈጣሪ ሆኖ ጎልቶ ሲወጣ የአእምሮንና የኅሊናን መዳከም ወይም ጭራሹኑ አለመኖር ያመለክታል፤ ጉልበት አለን በማለት፣ ወይም ተመችቶናል በማለት፣ ወይም ጠያቂ የለብንም በማለት የማንኛውንም ሰው ሰብአዊ መብቱንና ሰብአዊ ክብሩን መግፈፍ ሦስት ነገሮችን ያመለክታል፤ አንደኛ ጉልበት እንጂ አእምሮና ኅሊና እንደሌለ፣ ሁለተኛ ጉልበት እንጂ ሕግ እንደማይከበር፣ ሦስተኛ በአንተ ላይ እንዲያደርጉብህ የማትፈልገውን አንተም በሰዎች ላይ አታድርግ የሚለውን ሕግ መጣስን ያሳያል፤ በመጨረሻም፣ ዘግይቶም ቢሆን በራስ ላይ ቅሌትን መጋበዝን ያስከትላል፤ የሌላውን ሰውነት ስናረክስ ሰውነትን በጠቅላላው ማርከሳችን ነው፤ ሰውነትን በጠቅላላው ስናረክስ ራሳችንን ከነጉልበታችን ማርከሳችን ነው፤ ራሳችንን፣ ሰውነታችንን ካረከስን በኋላ ዋጋ የለንም፤ ለራሳችን ዋጋ ከሌለን ለሌለች ሰዎችም ዋጋ አንሰጥም፤ ያኔ ክፉ በሽታ ይይዘናል፤ እግራችን ስር በወደቀ ሰው ስቃይ የምንደሰትና የምንስቅ፣ የምንፈነድቅ እንሆናለን፤ ያን ጊዜ የለየለት በሽተኛ ሆነናል።
ይሄ በሽታ ያቃዣል፤ ከሰው ሁሉ በላይ ያሉ ያስመስላል፤ አግሩ ስር የወደቀው አንድ ሰው የሰው ልጅ በሙሉ ይመስለዋል፤ በሽተኛነቱን ስለማያውቅ በሽታው ከሰው በላይ ያደረገው ይመስለዋል፤ እንዲህ ዓይነቱ በሽተኛ በሕግ አሰከባሪነት ሥራ ውስጥ ሲገባ ሕግ የአንድ ማኅበረሰብ ትምክህትና መከታ በመሆን ፋንታ የበሽተኞች በትር ይሆናል፤ በደርግ ዘመን የአራት ኪሎው ግርማ የሠራውን እናውቃለን፤ ዛሬ ደግሞ ልዩ ግርማዎች አሉ፤ መልካቸውን ከካሜራው ጀርባ ደብቀው በሰው ስቃይና አበሳ በሳቅ እየተንከተከቱ ጀብዱዋቸውን በቴሌቪዥን የሚደረድሩ ጀግኖች መጥተዋል፤ መሣሪያ ይዞ መሣሪያ ባልያዘ ሰው ላይ ጀግና መስሎ ለመታየት የሚሠራው ጨዋታ ራስን ክፉኛ ከማጋለጥ በቀር ሌላ ፋይዳ የለውም።
በኢትዮጵያዊ ሰውነት ላይ ማናቸውንም ከሕግና ከሰብአዊነት ውጭ የሆነ ሙከራ ለማድረግ የውጭ አገር ሰዎች ዕድሉን ይፈልጉት ይሆናል፤ ለነሱ ሰዎች ስላልሆን ሰብአዊነት አይሰማቸውም፤ ከአገራቸው ሕግም ውጭ በመሆናቸው በሕግ አይገዙም፤ ዋናው ውጤት ግን ለኢትዮጵያ ሕግ አስከባሪዎች የሚያስተምሩት ግዴለሽነት ነው፤ መታሰር በብዙ ምክንያቶች ይመጣል፤ ስለዚህ በሠለጠነው ዓለም የተለያዩ እስረኞች በተለያየ ሁኔታ ይጠበቃሉ፤ አንዳንዶቹ እንዲያውም በቤታቸው ውስጥ እየተጠበቁ ይቆያሉ፤ ኢትዮጵያ በራስዋ ሥልጣኔ በምትተዳደርበት ዘመን መሳፍንትና መኳንንት የሚታሰሩት በወርቅ ወይም በብር ሰንሰለት ነበር፤ ግዞትም፣ የቁም እስርም ነበር፤ ዛሬ በኢትዮጵያ ውስጥ እስረኞች ሁሉ እኩል ናቸው፤ በቃሊቲ ለየት ያለ አያያዝ የሚታየው ለሙስና ወንጀል ተጠርጣሪዎች ብቻ ነው።
ጉልበትን በጉልበት እቋቋማለሁ የሚል ሰው ሲሸነፍ አያስደንቅም፤ አዲስም አይደለም፤በአለፉት አርባ ዓመታት እየተሸነፉ ከትግሉ ሜዳ ወጥተው በተለያዩ የምዕራባውያን አገሮች የሙጢኝ ብለው የተቀመጡ አሉ፤ በተባበሩት መንግሥታት ደንብ የሙጢኝ ማለት መብት ነው፤ ይህንን መብት መጣስ የመንግሥተ ሰማያትን በር መድፈር ነው፤ በጎንደር የአደባባይ ኢየሱስን ቤተ ክርስቲያን በር መድፈር ነው፤ በአዲስ አበባ የቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያንን በር መድፈር ነው፤ በአዲስ አበባ የአንዋር መስጊድን በር መድፈር ነው፤ ወደመሬት ስንወርድም የሙጢኝ የተባለው አገርን መንግሥት መድፈር ነው፤ የተባበሩት መንግሥታት ደንብን መጣስ ነው፤ ለነገሩ የመንግሥተ ሰማያትን በር መድፈር ከተቻለ ሌላው ምን ያቅታል!
የሙጢኝ ያለን ሰው በአፈና መያዝና ወደአገር ማስገባት አንድ ችግር ነው፤ ይህ የጉልበተኛነት መገለጫው ነው፤ ሁለተኛው ችግር የተያዘው ሰው መብቱና ክብሩ ሳይጓደልበት ማስረጃዎችን ሰብስቦ ለነጻ ፍርድ ቤት አለማቅረቡ ነው፤ በቴሌቪዥን እንደታየው አካላዊ ጉዳት እንደደረሰበት ባይታወቅም፣ ጥልቅ መንፈሳዊ ጉዳት እንደደረሰበት ይታያል፤ በብዙ አገሮች ሕጎች አንድ ሰው ራሱን እንዲወነጅል አይገደድም፤ ሕጋዊ ምርመራም በቴሌቪዥን በአደባባይ አይካሄድም።
ስለዚህም በተጠርጣሪው ላይ የተደረገው ሁሉ ሕጋዊ አይደለም፤ በነጻ ፍርድ ቤት ቢቀርብም በቴሌቪዥን የተናገረው ሁሉ ቢያስታውሰውም በማስረጃነት የሚያገለግል አይመስለኝም፤ ስለዚህም ከጥቅሙ ጉዳቱ ይበልጣል።
ከአፍሪካ አህጉር ወጥቶ የቀይ ባሕርን አቋርጦ አንድ ሰው፣ ገና ወደፊት ክፉ ሊሠራ ይችላል በሚል ሂሳብ በጉልበት አፍኖ ማምጣት የብዙ ነፍሶች ዕዳን ተሸክመው በኢጣልያ ኤምባሲ የሙጢኝ ብለው ተደላድለው የተቀመጡትን የደርግ አባሎች ማስታወስ ግዴታ ይሆናል፤ አድርጋችኋል የተባሉትን ሰዎች የሙጢኝ የማለት መብት አክብሮ አስበሃል የተባለውን ሰው የሙጢኝ የማለት መብት መጣስ ከጥቅሙ ጉዳቱ ይበልጣል።
ከፖሊቲካና ከምናምኑ፣ ጉልበተኛነትንም ከማረጋገጡ በላይ ሌላ ትልቅ ነገር አለ፤ አገር የሚባል ነገር አለ፤ ይህ በአንድ ግለሰብ ላይ የተገኘ ጊዜያዊ ድል የአገርን ከብር የሚያጎድፍና የሚያቀል ይሆናል፤ የአንድ አገርን የመንግሥት ሥልጣን የያዘ አካል አንድ ግለሰብን በአደባባይ ከሕግ ውጭ ለማጥቃት ሲሞክር የራሱን ክብር ዝቅ ያደረግበታል፤ ስለዚህም ከጥቅሙ ጉዳቱ ይበልጣል።
በእኔ ዕድሜ ሰው በአደባባይ ሲገረፍ አይቻለሁ፤ ሰው ተሰቅሎ አይቻለሁ፤ የዚያን ዘመን የእውቀት ደረጃ የዚያን ዘመን የሰው ልጆች የመንፈስ እድገት ደረጃ ያመለክታል፤ የእውቀትም የመንፈስም ደረጃ በጣም ዝቅተኛ ነበረ ማለት ነው፤ ስለዚህም ይህንን ያደረጉትን ዛሬ አንወቅሳቸውም ይሆናል፤ የታሪካችን ጉድፍ መሆኑን ግን ልንፍቀው አንችልም፤ ስለዚህም ሌላ ጉድፍ እየጨመርንበት ታሪካችንን ማቆሸሹ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ይበልጣል።
ቅጣት በሕግና በሥርዓት ይደረግ ማለት ያጠፋ ሰው አይቀጣ ማለት አይደለም፤ ነገር ግን ምንም አቅም የሌለውን ሰው ይዞ በአደባባይ ማሰቃየትና ማዋረድ አገርንና ሕዝብን ማዋረድ ነው፤ የሰብአዊነትንም የሕጋዊነትንም ሚዛኖች ይሰባብራል።
ምንጭ ዘ-ሐበሻ

Friday, August 22, 2014

የውሸት አባት 2ኛ ሙት ዓመት ነዶ የማያልቀው [ሻማ] የኢትዮጵያ ሕዝብ

ግንቦት 20፣ 1983ዓም መለስ ወይም ለገሠ ወይም አስረስ ወይም ዜናዊ ወይም … ትክክለኛ ስሙን በውል የማናውቀው ከነጭፍሮቹ ቤተመንግሥት ገብቶ ራሱን አጼያዊ ፕሬዚዳንት፣ ቀጥሎም አጼያዊ ጠቅላይ ሚኒስትር፣ … በማድረግ ከሾመበት ቀን ጀምሮ የኢትዮጵያ ሕዝብ በኦፊሴል እንደ ሻማ ወይም እንደ ኩራዝ ተለኩሷል።
አቀጣጣዮቹ ምስለኔዎች ከሻማና ከኩራዝ ከፍ ብለው ብርጭቆ የለበሱ ፋኖሶች ሆነዋል። ለመለስና ለጭፍሮቹ የሚያበሩ ፋኖሶቹም (ኦህዴድ፣ ብአዴን፣ …)፣ ኩራዞቹም፣ ሻማዎቹም የበራላቸው ማሾዎች (ህወሃቶች) ሁሉም በአንድነት ዛሬ ላይ ደርሰዋል። ለኳሹም ተለኳሹም እያበሩ የአስለኳሹን ሁለተኛ ሙት ዓመት “እያከበሩ” ነው። በሌላ አነጋገር ለሙት መንፈስ እሣት አንድደው እየሰገዱ ነው። ተገድዶ እየነደደ ያለውን ሕዝብ፣ አዳዲሶቹ አስለኳሾች (የኃይለማርያም ደቦ አስተዳደር) ሕዝብን ሻማ ላደረገውና ከስሙ ጀምሮ በውል ማንነቱ ላልታወቀው ግለሰብ “ሻማ አብሩ” አሉለት።
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ ለሁለተኛው ሙት ዓመት “የውርስ መታሰቢያነት” ከዚህ በታች ያለውን የመክብብ ማሞን ጽሑፍ ሲያቀርብ በመለስ ሞት ላዘኑ ሁሉ ለሃዘናቸው መጉመጥመጫ እንዲሆን በማሰብ ነው። “የውሸት አባት” መለስ ነፍስ ካወቀበት ጊዜ ጀምሮ ስዩመ አብዮታዊ ዴሞክራሲ አጼ አድርጎ ራሱን በመሰየም ሕዝብን እንደሻማ ባነደደበት ዘመናት ከአንደበቱ ሲወጡ የተመዘገቡ ውሸቶች ስፍር ቁጥር የላቸውም።
በተለይ ግን በ1997ቱ ምርጫ ሰሞን ሕዝብ እንደ ሻማ ከመቃጠልና ከመንደድ የራሱን መሪ እንዳይመርጥ የዋሸው ውሸት ከዚህ በታች ሰፍሯል። ታዲያ ሕዝብ እንደ ሻማ ከመቅለጥ የሚያድነውን እንዳይመርጥ ለገደበ ግለሰብ እንዴት ሻማ ይበራለታል?!
“ማሾዎቹ” ደረት ቢደቁ፣ ከበሮ ቢደልቁ፣ ፈንዲሻ ቢበትኑ፣ አሸንዳ ቢዘሉ፣ ሠርግና ምላሽ ቢያደርጉ፣ “አንጓይ ፍስስ” ቢሉ፣ … ምክንያት አላቸው። እንደ ዱር አውሬ “የአገር ቅርስ” ሲሉት ውለው ቢያድሩ ከልካይ ሊኖራቸው አይችልም። በሚሊዮን ሕዝብ ችግር ላይ ቆመው ለሙት መንፈስ ቢንደባለሉ ደንታ የላቸውም። ሚሊዮኖች በሚያዝኑበት አገር፣ እስር ቤትና ማጎሪያዎች ውሥጥ የታፈኑት ሲቃ በሚያሰሙበት አገር እነርሱ ሙት ዓመትን አስረሽ ምቺው ቢያደርጉት ማን ተዉ ሊላቸው ይችላል?! ምክንያቱም ብርሃን ይፈልጋሉ፤ ለዚያ ደግሞ ነዶ የማያልቅ ሻማ ያስፈልጋል።
ለማንኛውም መጪው የምርጫ ጊዜ ነውና የወደፊቱን ውሸት ከዚህ በታች በሰፈረው የመክብብ ማሞ ጦማር እያጣቀሳችሁ የ… ዜናዊን ሙት ዓመት አክብሩ። ለኢትዮጵያ እውነተኛ ስም ያለውና ለዘመናት በዚያው ስሙ የሚጠራ መሪ ይስጣት።
“ውሸታም!”
ሰሞኑን (ይህ ጽሁፍ የተጻፈው በመስከረም 2002/Sept. 2009 ነው) የመገናኛ ብዙሃንን ትኩረት የሳበ አንድ ክስተት በአሜሪካ ተፈጽሟል። ፕሬዚዳንት ኦባማ በምርጫ ዘመቻቸው ጊዜ ቃል የገቡለትን የጤና ጥበቃ ማሻሻያ አዋጅ እንዲጸድቅ የሕዝብ ተወካዮችን ሰብስበው ንግግር በሚያደርጉበት ወቅት ከተቃዋሚ የሪፓብሊካኑ ወገን የማርጎምገምና የተቃውሞ ድምጽ ተሰማ። በተለይ ግን የጤናው ማሻሻያ አዋጅ “ሕገወጥ ስደተኞችን አያካትትም” የሚል ንግግር ባደረጉ ጊዜ ከደቡብ ካሮላይናው እንደራሴ “ውሸታም!” የሚል ድምጽ አስተጋባ።
እንደ እውነቱ ከሆነ በረቂቅ ሕጉ ላይ ሕገወጥ ስደተኞች የጤና መድኅን ዋስትና እንደማያገኙ በማያሻማ መልኩ የሰፈረ ጉዳይ ነው። እዚህ ላይ “ማነው ውሸታም?” የሚለውን ለመመርመር አይደለም ጉዳዩን የጽሁፌ መነሻ ያደረኩት። ሆኖም ግን ይህንን የሰማሁ ምሽት እንደራሴው ኢትዮጵያ ቢሆኑ ኖሮ ከምርጫ 97 ጀምሮ እስካሁን (2002ዓም) ድረስ ምን ያህል ጊዜ “ውሸታም!” እያሉ ይጮኹ ይሆን በማለት ያለፉትን አምስት ዓመታት (1997-2002ዓም) በምናቤ መቃኘት ጀመርኩና ከዚህ በፊት የተደረጉ ቃለመጠይቆችን ለመመርመር ወደኋላ ሄደኩ።
ማርክሲስታዊው ህወሃት ከበረሃ ወጥቶ የምኒልክን ቤተመንግሥት ከተቆጣጠረበት ጊዜ ጀምሮ ላለፉት 18 (አሁን 23) ዓመታት ከአመራሮቹ ስንሰማ የቆየነው ውሸት ጆሮ የሚገነጥል ሲሆን በተለይም የኢትዮጵያ ሕዝብ ድምጽ ከተሰረቀበት 1997ዓም ጀምሮ “ጠቅላይ ሚኒስትሩ” ለተለያዩ ምዕራባዊ የመገናኛ ብዙሓን “ሥልጣኔን እለቃለሁ” በማለት ሲቀደድ የነበረው ከቁጥር በላይ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም። ጥቂቱን ግን ከዚህ በታች አቅርቤዋለሁ። (ከአዘጋጆቹ፤ መለሳውያን በሙሉ የሙቱን መንፈስ 2ኛ ዓመት ስትዘክሩ የውሸት ውርሱንም አትዘንጉ)።
የቢቢሲው ጋዜጠኛ ስቲፈን ሳኩር ከምርጫ 97 በኋላ ለ“ጠቅላይ ሚኒስትር” ዜናዊ ሰኔ 27 ቀን 1997 ዓም ቃለመጠይቅ ባደረገበት ወቅት የሚከተሉትን ጥያቄዎች ጠይቆት ነበር።candle1
ስቲፈን፡- አሁን ስላለው አጀንዳ እንድጠይቅ ይፈቀድልኝ። እንደው እንደበልና የምርጫው ውጤት ፓርቲህን አሸናፊ አደረገው እንበል እና ይህ ከሆነ እንደገና ለሚቀጥሉት አምስት ዓመታት እንደገና በሥልጣን ላይ ትቆያለህ?
ዜናዊ፡- ያ ፓርቲዬ የሚወስነው ጉዳይ ነው።
ስቲፈን፡- አንተ ግን ምን ለማድረግ ነው የምትፈልገው?
ዜናዊ፡- እኔ ማድረግ የምፈልገውን ቆየት ብዬ የማስብበት ነው። ውሳኔዬም በሁኔታዎች ላይ የተመሠረተ ነው።
ስቲፈን፡- በእርግጥ ማድረግ የምትፈልገውን ወስነሃል። ማለቴ ለመመረጥ ተወዳድረሃል፤ ይህም ማለት ሥልጣኑን ትፈልገዋለህ ማለት ነው። (በሥልጣን መቆየት ባትፈልግ አትወዳደርም ነበር)
ዜናዊ፡- ሥልጣኑን የምፈልገው አገሬን ለማገልገል ነው። የማገለግለው ግን የምጨምረው እሴት ሲኖር ነው። … የምጨምረው እሴት አለኝ። ይህንንም እቀጥልበታለሁ የምጨምረው እሴት እስካለኝ ድረስ። በተመሳሳይ መልኩ ፓርቲዬ እሴት የማልጨምር መስሎ ሲያገኘው በማንኛውም ጊዜ ጠቅላይ ሚኒስትር ሊቀይር ይችላል።
“ውሸታም!”
ህወሃት/ኢህአዴግ ምርጫውን ካጭበረበረ 1 ዓመት ከ7 ወር በኋላ የዋሽንግተን ፖስት ጋዜጠኛ ስቴፋኒ ማክሩመን ታህሳስ 5፤1999ዓም ተመሳሳይ ጥያቄ አቅርባ ነበር።
ስቴፋኒ፡- ለሦስተኛ ጊዜ ለመመረጥ ዕቅድ አለህ?
ዜናዊ፡- ፓርቲዬ? ፓርቲዬ ለሦስተኛ ጊዜ ብቻ ሳይሆን ለአስረኛ ጊዜም ቢሆን ሊሞክር ይችላል።
ስቴፋኒ፡- አንተስ በግልህ?
ዜናዊ፡- እኔ በግሌ ይበቃኛል ነው የምለው።
“ውሸታም!”
ቀጥሎም ከዘጠኝ ወር በኋላ አሌክስ ፔሪ ከ“ታይም” መጽሔት ጳጉሜ 1፤1999ዓም የሚከተሉትን ጥያቄዎች አቀረበ።
አሌክስ፡- አብዛኛውን ጊዜ የአፍሪካ መሪዎች ሥልጣን ለመልቀቅ ሲያመነቱ ይስተዋላሉ። ሆኖም ግን ከዚህ በፊት በሥልጣን እንደማትቆይ ፍንጭ ስትሰጥ ቆይተሃል።
ዜናዊ፡- አሁን ሦስት ዓመት ብቻ ነው የቀረኝ።
አሌክስ፡- ከዚያ ሥልጣንህን ትለቅቃለህ?
ዜናዊ፡- ከዚያማ ሒደቱ ይቀጥላል።
አሌክስ፡- ለምንድነው ሥልጣን መልቀቅ የምትፈልገው?
ዜናዊ፡- እስካሁን ብዙ ቆይቻለሁ። ከዚህ በኋላ ባለው ጊዜ አዲስ ነገር ለማድረግ የማስብበት ይሆናል።
“ውሸታም!”
ዜናዊ ቀጣዩን ቃለመጠይቅ ሲያደርግ ደግሞ ከታይም መጽሔቱ አሌክስ ጋር ያደረገው ሦስት ወር እንኳን አልሞላውም ነበር። ጠያቂው የአልጃዚራው መሃመድ አዶው ምልልሱን ያደረገው ኅዳር 12፤ 2000ዓም ነበር።
መሃመድ፡- በቅርቡ ከጠቅላይ ሚኒስትርነት ሥልጣን የመልቀቁን ጉዳይ እያሰብክበት ነውን?
ዜናዊ፡- ከዚህ በፊት እንደተናገርኩት በጠቅላይ ሚኒስትርነት የማገለግልበት ይህ የመጨረሻው የሥልጣን ዘመኔ ነው (2002ዓም ማለቱ ነበር)።
“ውሸታም”
በዚሁ በ2000ዓም ግንቦት 4ቀን awate.com ከተሰኘ ድረገጽ ጋር ቃለምልልስ ያደረገ ሲሆን ጠያቂውም ሳሌህ ጆሃር ነበር።
ሳሌህ፡- በህይወት ዘመኔ ከሥልጣንህ ለቅቀህ “የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር” እየተባልክ በመጠራት ዩኒቨርሲቲ ውስጥ በማስተማር፣ መጽሐፍ በመጻፍ ወይም አንድ ፋውንዴሽን ስትመራ የማይበት ጊዜ ይመጣ ይሆን? እስቲ ንገረኝ።
ዜናዊ፡- በጣም ትክክል ነው። እኔም ያንን ቀን እየናፈኩት ነው። ሩቅ እንደማይሆን አስባለሁ።
ሳሌህ፡- ይህ ማለት እንግዲህ ለሌሎች ሁሉ ምሳሌ ትሆናለህ ማለት ነው?
ዜናዊ፡- ምንም ጥርጥር የለውም። ነገን ልትኖረው እንደምትችል እርግጠኛ ልትሆን አትችልም። ሆኖም ግን እንደማንኛውም ሰው እኖራለሁ ብዬ በማሰብ ከሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት በኋላ (ከ2002ዓም ጀምሮ ማለቱ ነበር) “የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር” ብለህ ልትጠራኝ ትችላለህ።
“ውሸታም!”
ውሸቱ ግን በዚህ አላቆመም። በመጋቢት 24፤ 2001ዓም የቢቢሲዋ ዘይነብ ባዳዊ ቃለመጠይቅ ባደረገችለት ጊዜ ይህንኑ ሥልጣን የመልቀቅ ጥያቄ አንስታ ነበር።candle 2
ዘይነብ፡- ከዚህ በፊት (ባቀረበችው ጥያቄዎች) እንደጠቆምኩት ከ1983 ዓም ጀምሮ በሥልጣን ላይ ነበርክ። አንዳንድ ጊዜ ከሥልጣን የምትለቅበት ጊዜ እንደደረሰ ስትናገር ቆይተሃል። ሌላ ጊዜ ደግሞ ራስህን የፓርቲህ ወታደር አድርገህ ስትናገር ትደመጣለህ። መቼ ነው (ከሥልጣን የምትለቅበትን) እርግጠኛውን ቀን የምትነግረን? ምክንያቱም ከምናያቸው ነገሮች ስንነሳ ይህ በአፍሪካ መሪዎች ዘንድ የሚታየውን “ያለኔ …” የሚለውን አስተሳሰብ ትደግፋለህ እንድንል እያደረከን ነው ያለኸው። ማለትም ምትክ የሌለው መሪ ዓይነት (እየሆንክ ነው)፤ ለሁለት ዓስርተ ዓመታት በሥልጣን ቆይቻለሁ የሚል ዓይነት?
ዜናዊ፡- ራሴን ምትክ የሌለው መሪ አድርጌ አላውቅም። እናም ማንኛውም ሰው ራሱን ለፓርቲም ሆነ ለአገር ምትክ የሌለው አድርጎ የሚቆጥር ከሆነ ያ ፓርቲም ሆነ አገር መኖር ይገባዋል ብዬ አላምንም።
ዘይነብ፡- ታዲያ መቼ ነው ቁርጥ ያለውን ቀን የምትናገረው?
ዜናዊ፡- ፓርቲዬ ካቀረብኩት ዕቅድ ጋር ሲስማማ ያኔ ይሆናል።
ዘይነብ፡- ዕቅድህ ምን እንደሆነ ልትነግረን ትችላለህ? በ2002ዓም ምርጫ ይካሄዳል?!
ዜናዊ፡- ዕቅዴማ ይህ የመጨረሻው የሥልጣን ዘመኔ እንደሚሆን ማረጋገጥ ነው።
“ውሸታም!”
በዚህ አላበቃም! ሰኔ 10፤2001ዓም የፋይናንሺያል ታይምስ የአፍሪካ ቢሮ አርታኢ የሆነው ዊሊያም ዋሊስ ይህንኑ ማለቂያ የሌለውን የሥልጣን መልቀቅ ጥያቄ አቅርቦ ነበር። ሆኖም አጠያየቁን ቀየር አድርጎት ስለነበረ የውሸቱ ለከት የት እንደደረሰ በግልጽ እንዲያሳይ አድርጎታል።
ዊሊያም፡- ከዚህ ቀደም ከሥልጣን ለመውረድ ፈቃደኛ እንደሆንክ ስትናገር ቆይተሃል። በዚህ ዙሪያ ያለውን እንቅስቃሴ ምን እንደሚመስል ብታስረዳን?
ዜናዊ፡- በአሁኑ ጊዜ በፓርቲያችን ውስጥ ውይይት እያደረግን ነው። ይህም በፓርቲያችን ውስጥ የምናደርገው ውይይት ሰዎች ሊገምቱት ከሚችሉት በላይ በጣም ብስለት የተሞላበት ነው። ስለ መለስ ብቻ አይደለም የምንነጋገረው። በትጥቅ ትግሉ የተሳተፈው የቀድሞው ትውልድ በአዲስና የትጥቅ ትግል ተሞክሮ በሌለው ትውልድ እንዴት ሊተካ ስለሚችልበት ሁኔታ እየተወያየን ነው። ለፓርቲያችን ሲባል ይህ መሆን ያለበት ጉዳይ ነው። ስልትን በተመለከተ ማለትም ጊዜው መቼ ይሆናል የሚለው ቁርጥ ያለ መልስ ላይኖር ይችላል። (ምርጫ መጣ ክህደት ተጀመረ) ክርክሩም በዚሁ የሚቀጥል ነው። ሆኖም ግን የቀድሞው አመራር በአዲስ መተካት አለበት በሚለው ላይ ግን አለመስማማት የሚባል ነገር አይኖርም። ይህ ከመፍትሔዎቹ አንዱ ነው፤ ብቸኛው መፍትሔ ግን አይደለም። ስለዚህም የእኛ ግምባር በአመዛኙ ሌሎች ግምባሮች ከሚያጋጥማቸው የመፈረካከስ አደጋ አምልጧል ብዬ አምናለሁ።
ዊሊያም፡- እና የሚቀጥለው ዓመት (2002 ማለቱ ነበር) በሚደረገው ምርጫ አትወዳደርም ማለት ነው?
ዜናዊ፡- እያልኩ ያለሁት እኔ በግሌ ይበቃኛል ነው የምለው። እኔ ብቸኛው ተኳሽ አይደለሁም። ለበርካታ ጊዜያት ጠቅላይ ሚኒስትር በነበርኩበት ጊዜም በድምጽ ብልጫ በመሸነፍ የማልፈልገውን ነገር ሳደርግ ቆይቻለሁ። በተለይም በኤርትራ ጦርነት ወቅት ሳልፈልገው የማልስማማበትን ሆኖም ግን የፓርቲዬ ውሳኔ በመሆኑ ብቻ ያንን ሳስፈጽም ኖሬአለሁ። በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታዎች ወቅት ሁለት አማራጮች አሉኝ። ለሥልጣን መልቀቅ ወይም የብዙሃኑን ውሳኔ መቀበል። ይህ ሲሆን እኔ የራሴን አቋም አቀርባለሁ፤ ሌሎችም የራሳቸውን አቋም ያቀርባሉ፤ ክርክሩም ይቀጥላል። ተስፋ የማደርገው ሁላችንም አንድ የመግባቢያ ነጥብ ላይ እንደርሳለን ብዬ ነው። ያም ሲሆን እኔም ህይወቴን ሙሉ ከተዋጋሁለት ፓርቲዬ መልቀቅ ሳያስፈልገኝ እንደቀጥል ይሆናል። ከመንግሥት ሥልጣኔ ከለቀቅሁ በኋላም እንኳን በፓርቲዬ በአባልነት መቀጠል እፈልጋለሁ። እናም ተስፋ የማደርገው ሁላችንም አንድ የመግባቢያ ነጥብ ላይ እንደርሳለን ብዬ ነው። ልዩነቶቻችን ደግሞ ያንን ያህል ትልቅ አይደሉም።
ዊሊያም፡- ታዲያ ይህ የሚሆነው መቼ ነው? በቅርቡ የምታደርጉት የፓርቲ ስብሰባ አላችሁ?
ዜናዊ፡- አዎን፤ መስከረም ላይ ስብሰባ አለን።
ዊሊያም፡- እናም ያኔ ነው በውሳኔው ላይ የምትከራከሩት?
ዜናዊ፡- አዎን፤ ግን ከዚያ በፊት ውይይቱ ይካሄዳል፤ …
ዊሊያም፡- ወደፊት ማነው የሚተካህ?
ዜናዊ፡- ያንን ውሳኔ ለፓርቲዬ እተወዋለሁ፤ …
ዊሊያም፡- ኢትዮጵያውያን ለምንድነው በእርግጥ ሥልጣን ትለቃለህ ብለው የማያምኑት?
ዜናዊ፡- ምክንያቱም ከዚህ በፊት በኢትዮጵያ ሲደረግ ስላላዩ ነው።
ዊሊያም፡- ነገር ግን እያደረክ ያለው ያንኑ የሚከተል እንደሆነ ነው።
ዜናዊ፡- እኔ ይህንን ዓይነት አስተሳሰብ ለማስወገድ ነው የምፈልገው፤ …
ዊሊያም፡- እናም ይህ ማለት ሙሉ በሙሉ ከማንኛውም ተግባር ትገለላለህ ማለት ነው?
ዜናዊ፡- ያ ካልሆነማ የአመራር ለውጥ ሊኖር አይችልም። ነገር ግን ያንን ካደረግን በኋላ ፓርቲዬ ወይ መጽሐፍ እያነበብኩና እየጻፍኩ እንድቀመጥ ወይም ሌላ የፓርቲ ሥራ እየሠራሁ እንድቀጥል ይወስናል።
ዊሊያም፡- የፓርቲ ሥራ ማለት ሊቀመንበርነት?
ዜናዊ፡- አይመስለኝም፤ ምክንያቱም ጠቅላይ ሚኒስትሩ የፓርቲው ሊቀመንበር መሆን አለበት። ያ ደግሞ ጡረታ ለወጣ ሰው ሊሰጠው የሚገባ ሥልጣን አይደለም።
“ውሸታም!”
እንግዲህ የኢትዮጵያ ሕዝብ እንደዚህ ዓይነት ቅጥፈት (እና ተራ የቁጭ በሉዎች ቀደዳ) ላለፉት 18ዓመታት (ጽሁፉ በ2002ዓም የተጻፈ ነው) ሲቀደድለት ቆይቶ ህወሃት በሚቆጣጠረው ቴሌቪዥን ለአዲሱ ዓመት አዲስ ዜና – ትኩስ ዜና – ሰበር ዜና – ተሰበረለት። “ምትክ አልባው ጠቅላይ ሚኒስትር ከመጪው 2002 ጀምሮ ሥልጣናቸውን ለአምስት ዓመታት እንዳራዘሙት …” አበሰረልን። ሞት ቀድሞ candle bombበ“ውርስ” መታወቅ ጀመረ እንጂ በመጪው 2007 ምርጫም ወይ ፍንክች ይል ነበር። መለስ “ሥልጣኔን እለቃለሁ” ሲል ፓርቲው ደግሞ “አትለቅም” እያለ ገመድ ሲጓተቱ ኖረው የመለስ ሞት ለምን የሰማዕት ሆነ? “አልለቅም” ያለው የፓርቲው (ኢህአዴግ) ስህተት መሆኑ በግልጽ እየታወቀ እስካሁን ድረስ በተለይ የህወሃት ፖሊት ቢሮ አባላት መሪያቸውን “አንድደው በመግደል” ለምንድነው ያልተከሰሱት?
ውሸታሙን መለስ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከተገላገለው ሁለት ዓመት ሆኗል። የውሸቱ መጠን ቀንሷል ለማለት ባይቻልም ሕዝብ ግን በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ያሉትን የተቀናቃኝ ፖለቲካ ፓርቲዎችም ሆነ ህወሃት/ኢህአዴግ የሚያቅሙትን ውሸት እየሰማ ይታዘባል፤ ታሪክም ትዝብቱን ይመዘግባል።
ታዲያ ላለፉት 23ዓመታት “የኤሌክትሪክ ኃይል” በነጻነት በሌላት አገር ራሱን ሻማ አድርጎ ሲያበራ በግፍ የኖረ ሕዝብ ለምን በግድ “ሻማ አብራ” ማለት ያስፈልገዋል? ግፍን የሚያይ አለ! ያንን ግፍ ቆጥሮ ደግሞ ፍዳ የሚያስቆጥር፤ በሰፈሩት መስፈሪያ የሚሰፍር ከሁሉ የበላይ፤ ልዕለኃያል አለ። ነዶ የማያልቀው ሕዝብ እየደረሰበት ያለውን ግፍ ይመለከታል። “አንድ ቀን ግፍ ወደተነሣበት ይመለሳል”።
source www.goolgule.com

Thursday, August 21, 2014

የግንቦት 7 ሕዝባዊ ስብሰባዎች በዓለም ሃያ ስድስት ታላላቅ ከተሞች

ግንቦት 7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ በመላው ዓለም ላይ ከሚገኙ አባላት፣ ደጋፊዎቹና በአጠቃላይ ከኢትዮጵያውያን  ጋር በወቅታዊ ሁኔታዎች ላይ ለመመካከር ዝግጅቱን አጠናቋል።
በዚህም መሠረት ከዚህ በታች በተዘረዘሩት 26 የዓለም ታላላቅ ከተሞች ሕዝባዊ ስብሰባዎችን ተጠርቷል።
  1. በላስቤጋስ                   ዩ ኤስ አሜሪካ              ረቡስ ኦገስት 27 ቀን
  2. በሂውስተውን               ዩ ኤስ አሜሪካ              ቅዳሜ ኦገስት 30 ቀን
  3. በአትላንታ                   ዩ ኤስ አሜሪካ              እሁድ ኦገስት 31 ቀን
  4. በዋሺንግተን ዲሲ                     ዩ ኤስ አሜሪካ              እሁድ ኦገስት 31 ቀን
  5. በቦስተን                    ዩ ኤስ አሜሪካ              እሁድ ኦገስት 31 ቀን
  6. በሎስ አንጀለስ              ዩ ኤስ አሜሪካ              ቅዳሜ  ሴፕተምበር 6 ቀን
  7. በሳንቲያጎ                   ዩ ኤስ አሜሪካ              እሁድ ሴፕተምበር 7 ቀን
  8. በቶሮንቶ                    ካናዳ                        እሁድ ኦገስት 31 ቀን
  9. በካልጋሪ                    ካናዳ                        ሴፕቴምበር 1 ቀን
  10. በደርባን                     ደቡብ አፍሪቃ               እሁድ ኦገስት 31 ቀን
  11. በጆሃንስበርግ                ደቡብ አፍሪቃ               እሁድ ኦገስት 31 ቀን
  12. ቬሪኒንፍ                    ደቡብ አፍሪቃ               እሁድ ኦገስት  31 ቀን
  13. ሩስተምበርግ                ደቡብ አፍሪቃ               እሁድ ኦገስት 31 ቀን
  14. ፍራክፈርት                  ጀርመን                     ቅዳሜ ኦገስት 30 ቀን
  15. ሙኒክ                       ጀርመን                     እሁድ ኦገስት 31 ቀን
  16. ሄልሲንኪ                   ፊንላንድ                    ቅዳሜ ኦገስት 30 ቀን
  17. አምስተርዳም                ኒዘርላንድስ                   ቅዳሜ ሴፕተምበር 13 ቀን
  18. ኦስሎ                        ኖርዌይ                      እሁድ ኦገስት 31 ቀን
  19. ለንደን                       እንግሊዝ                   ቅዳሜ ሴፕተምበር 6 ቀን
  20. ስቶክሆልም                 ስዊድን                      ቅዳሜ ሴፕተምበር 6 ቀን
  21. ፐርዝ                        አውስትራሊያ               እሁድ ኦገስት 31 ቀን
  22. ሜልቦርን                             አውስትራሊያ               እሁድ ሴፕቴምበር 7 ቀን
  23. ቴላቪቭ                     እስራኤል                    ሐሙስ ሴፕቴምበር 11 ቀን
  24. ብራሰልስ                             ቤልጂየም                   እሁድ ሴፕቴምበር 14 ቀን
  25. ኦክላን                      ኒዩ ዚላንድ                 እሁድ ኦገስት 31 ቀን
  26. ሲኡል                      ደቡብ ኮርያ                 እሁድ ኦገስት 31 ቀን
በእነዚህ ስብሰባዎች ሁሉ የንቅናቄዓችን ዋና ፀሐፊ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ሥራዎች ይወሳሉ። ወያኔን ማስወገድ በሚቻልበት ስልቶች ላይ ውይይት ይደረጋል። እስከዛሬ ድረስ ንቅናቄዓችንን ለመቀላቀል የተቸገራችሁ ወገኖች ይህንን አጋጣሚ እንድትጠቀሙበት ጥሪ እናደርጋለን።  በማናቸውም ምክንያት አባል ሳይሆን ደጋፊ መሆን ለምትፈልጉ ወገኖቻችንን የደጋፊዎች ምዝገባ ሥርዓት አዘጋጅተናል፤ እድሉን ተጠቀሙበት።
ኑ! ኢትዮጵያ አገራችንን፣ ኢትዮጵያዊ ወገናችንን እና ራሳችን ነፃ ለማውጣት እና በሀገራችን ፍትህ እንዲሰፍን ለማድረግ የሚደረገውን ትግል ይቀላቀሉ። ከዘወትር የህሊና ወቀሳ ይገላገሉ። ለዚህ ትግል ሁሉም የሚያበረክተው ነገር አለ። ስለሆነም በአቅራቢያዎ ወደሚደረገው የግንቦት 7 ስብሰባ ይምጡ፤ ጥያቄዎች ካልዎት ይጠይቁ።
አሁን ወሳኝ የትግል ምዕራፍ ላይ እንገኛለን። ትግላችን ሶስት የትግል ስልቶችን ያስተባበረ ነው – ሕዝባዊ ተቃውሞ፣ ሕዝባዊ እምቢተኝነት እና ሕዝባዊ አመጽ። ትግላችን በአገር ውስጥም ከአገር ውጭም ነው።
በውጭ አገራት የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ከድጋፍ ሰጪነት ወደ ተግባራዊ ተሳትፎ የተሸጋገሩበት ወቅት ነው። ይህ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባዋል። የወያኔ ድርጅቶችና የወያኔ ሹማምንት በየትኛው አገር ተዝናንተው እንዲኖሩና እንዲነግዱ አንፈቅድላቸውም። በእነዚህ ስብሰባዎች ስለዚህ ጉዳይ ይመከራል።
ኢትዮጵያዊያን ወጣቶች ለኢትዮጵያ ክብርና ነፃነት ሕይወታቸውን ለመሰዋት ተነስተዋል። በእነዚህ ስብሰባዎች የአርበኛ ወጣቶቻችንን ጥረት እንዘክራለን። ሺዎች እንዲቀላቀሏቸው ጥሪ እናደርጋለን። በሁሉም ስብሰባዎች በአገር ውስጥም በውጭ አገርም የሚገኝ ኢትዮጵያዊ ወጣት ትግሉን እንዲቀላቀል ጥሪ ይደረግለታል።
በሁሉም ስብሰባዎች ለኢትዮጵያ የመከላከያ ሠራዊት አባላት ጥሪ  ይደረጋል። የሠራዊቱ መሪዎች የፋሽስት ወያኔ ባለሟሎች ቢሆኑም ሠራዊቱ ግን ከኢትዮጵያ አብራክ የወጣ ኢትዮጵያዊ ነው። ሠራዊቱ የወያኔ መጠቀሚያ ከመሆን የነፃነት ታጋዮችን እንዲቀላቀል፤ ያ ካልተቻለም ለወያኔ ሥልጣን እንዳይሞት፤ ወገኑን እንዳይገል ጥሪ ይደረግለታል።
መጥተው የእነዚህ ታሪካዊ ስብሰባዎች አካል ይሁኑ።
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!!
source www.ginbot7.org

Saturday, August 16, 2014

በሰማያዊ ፓርቲ የአርባ ምንጭ አስተባባሪዎች የተጀመረው እስር ተጠናቅሮ ቀጥሏል

ሰማያዊ ፓርቲ እንደዘገበው፦
blue party
ከአሁን ቀደም አራት የሰማያዊ ፓርቲ የአርባ ምንጭ አስተባባሪዎች በሽብርተኝነት ስም መታሰራቸው ይታወቃል፡፡ እነዚህን እስረኞች ያሉበትን ሁኔታና የዞኑን አደረጃጀት ለመጎብኘት ከአዲስ አበባ (ከማዕከል) የድርጅት ጉዳይ ኃላፊው አቶ ብርሃኑ ተክለያሬድና የድርጅት ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ አባል የሆነው ዮናስ ከድር ለጉብኝት በሄዱበት ወቅት ሲያስተባብሩ የነበሩት አባላት ከማዕከል የሄዱት የፓርቲው አመራሮች ሲመለሱ ለእስር መዳረጋቸውን ከአካባቢው የደረሰን መረጃ ይጠቁማል፡፡
በመሆኑም አቶ ከሳሁን አየለ የተባለው የሰማያዊ ፓርቲ አርባምንጭ አስተባባሪ ከአዲስ አበባ የመጡትን የፓርቲው አመራሮች ጋር በመሆን የዞኑን አደረጃጀትና በእስር ላይ ያሉትን የፓርቲው አስተባባሪዎች አስጎብኝቷል በሚል መታሰራቸው ታውቋል፡፡ በተመሳሳይ ሻምበል ካሳ የታሰሩትን ጠይቀሃል በሚል ለእስር መዳረጋቸውንና ነፃነት የተባለው የፓርቲው አስተባባሪ ከሰማያዊ ፓርቲ ጋር እንዳይሰራና በታሰሩት ላይ እንዲመሰክር በማስፈራሪያ መለቀቁ ታውቋል፡፡
በዞኑ የሚገኙ የሰማያዊ ፓርቲ አባላትና ደጋፊዎች እስራትና መከባ እየደረሰባቸው ሲሆን በአሁኑ ወቅትም ሉሉ መሰለ፣ በፈቃዱ አበበ፣ ካሳሁን አየለ፣ ሻምበል ካሰና ኢ/ር ጌታሁን የተባሉት የፓርቲው አስተባባሪዎችና አባላት በእስር ላይ እንደሚገኙ ለመረዳት ተችሏል።
ምንጭ ዘ-ሐበሻ

Tuesday, August 12, 2014

የ”ብርቱው ሰው” መልዕክት – ከቃሊቲ እስር ቤት (በኤሊያስ ገብሩ)

‹‹ለእውነት መቆም ካልተቻለ ስብዕና ይወርዳል፣ ሕሊናህም ይሞታል››‹‹የክስ እና የእስር መብዛት … የድል ጊዜ እየቀረበ መሆኑን ያሳያል››
ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ (ከቃሊቲ እስር ቤት)
‹‹እ… እስክንድር “The Iron man’’?››
የቃሊቲ ጠባቂ ፖሊስ
————————————–
ጥቁር ሰኞ (Black Monday) ከሚሉት ወገን አይደለሁም፤ በአባባሉም አላምንም፡፡ እያንዳንዱ ግለሰብ በሁሉም ቀናቶች ጥሩም ሆነ ጥሩ ያልሆነ ሁነቶችን ሊያስተናግድ ይችላል፡፡ ይህንን ማለት የወድድኩት ዛሬ ሰኞ በመሆኑ ነው፡፡ ብዙዎች ዕለተ ሰኞ እንደሚከብዳቸው እና እንደሚጫጫናቸው ይናገራሉ፡፡ በቀናት መጥቆር እና መንጻት ማመናችንን ትተን፣ እያንዳንዱ ቀናቶችን ለሥራ እና ለመልካም ነገሮች በአግባቡ ብንጠቀምባቸው መልካም እያልኩ ወደዋናው ርዕሰ ጉዳዬ ላምራ፡-
18 ዓመት ተፈርዶበት በቃሊቲ ወህኒ ቤት ታስሮ የሚገኘውንና እጅግ የማከብረውን ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋን በቃሊቲ ከጠየኩት አንድ ወር ገደማ ሆኖኝ ነበር፡፡ ባለፈው ሳምንት ልጠይቄው አስቤ፣ በአዲስ የጋዜጣ ሥራ ተጠምቼ ስለነበር ሳልችል ቀረሁ፡፡ ዛሬ ግን፣ ከመኝታዬ እንደተነሳሁ የናፈቀኝን እስክንድርን ለመጠየቅ ወደቃሊቲ ማምራት እንዳብኝ ወሰንኩና ጉዞዬን ጀመርኩ፡፡

ሳሪስ አቦ አካባቢ የመኪና መንገድ ተጨናንቆ ተዘጋግቷል፡፡ ከአዝጋሚው የመኪና ጉዞ በኋላ ቃሊቲ ደረስኩ፡፡ ለመግቢያ ሰዓት (6፡00) የቀረው አስር ደቂቃ በመሆኑ ከታክሲ ወርጄ መሮጥ ግዴታዬ ሆነ፡፡ ቃሊቲ በታችኛ በር ከገባሁ በኋላ መዝጋቢ ፖሊስ እስኪመጣ ድረስ እስረኛ ጠይቀው የሚወጡ ጠያቂዎችን ማየት ጀመርኩ፡፡ የእስረኛ ቁጥር ብዙ፣ የጠያቂውም እንደዚያው! ‹‹መቼ ይሆን! የታሳሪ እና የጠያቂዎች ቁጥር በሀገራችን የሚቀንሰው?›› ስል ራሴን ጠየኩ፡፡ በወቅቱ ግን መልስ አላገኘሁለትም፡፡
የጥዋት ጠያቂዎች እየወጡ ሳለ የድምጻዊ ኤፍሬም ታምሩ የቀደምት ሥራዎቹ የሆኑ ለስላሳ ዘፈኖች በተከታታይ በትልቅ ስፒከር ሲንቆረቆሩ ነበር፡፡ ለስለስ ያሉ የሀገራችን ድምጻውያን የቀደምት ሥራዎች ከሚከፈትባቸው ቦታዎች መካከል አንዱ ቃሊቲ ነው፡፡ በተለያዩ ጊዜያቶች እነእስክንደርን፣ ርዕዮት ዓለሙንና ውብሸት ታዬን ለማጠየቅ ስሄድ አድምጬ አውቃለሁ፡፡
****‹‹እ… እስክንድር “The Iron man’’››****
ከምዝገባ በኋላ የተለመደውን ፍተሻ አልፌ ጭር ወዳለው የቃሊቲ ግቢ ዘለኩኝ፡፡ አንድ ጠባቂ መጣና ‹‹ማንን ልጥራልህ?›› አለኝ፡፡ ‹‹እስክንድር ነጋን›› አልኩት፡፡ ወዲያው ፈገግ እያለ ‹‹እ… እስክንድር “The Iron Eskidner-NEgaaman’’ (ብርቱ ሰው)›› በማለት ሊጠራልኝ ሄደ፡፡ የጥበቃው ፖሊስ እንዲህ ማለቱ ትንሽ አግራሞትን ፈጥሮልኝ ነበር፡፡ ‹‹እስክንድር ብርቱ መሆኑን እነሱም ያውቃሉ ማለት ነው?›› በማለት ለራሴ ፈገግ አልኩ፡፡ [ብርቱ ሰው! በሚል ርዕስ ‹‹ፋክት›› መጽሔት ላይ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ በአንድ ወቅት ስለእስክንድር ጽፉ ነበር፡፡ ኢቲቪም ባሳላፍነው ሳምንት የፍትህ ሚኒስቴር አምስት መጽሄቶችንና አንድ ጋዜጣን በወንጀል ክስ መከሰሱን ተከትሎ ባስተላለፈው ዜና እና በ‹‹ሕትመት ዳሳሳ›› ፕሮግራም ላይ ይህ ርዕስ እና የእስክንድር ፎቶግራፍ ያለበት የመጽሔቱን የፊት ገጽ በተደጋጋሚ ሲታይ ነበር] ፖሊሱም ይህን አይቶ ሊሆን ይችላል የሚል ግምት አደረብኝ፡፡
ወዲያው እውነተኛ ፈገግታ የማይለየው እስክንድር ፈገግ እያለ ወደእኔ መጣ፡፡ በአጋጣሚ በር ጋር ስለጠበኩት በአካል በደንብ ለመገናኘት ዕድሉን አገኘን፤ ጠባቂዎቹም ዝም ስላሉን ተቃቅፈን ሰላምታ ተለዋወጥን፡፡ ከሰላምታው በኋላም እስክንድር ትንሽ ጎንብስ ብሎ፣ አንገቴ ላይ የጠመጠምኩትን ስካርፍ ጫፍ ላይ የነበረውን የኢትዮጵያ ባንዲራ በሁለት እጆቹ ይዞ ሳመው፡፡ የእስክንድር ትህትና መቼም ተነግሮ አያልቅ ብዬ ዝም አልኩ፡፡
*****‹‹ሰርካለም እንዴት ነች?››******
ሁለት ጥበቃዎች ከግራና ከቀኝ ሆነው ማውራት ጀመርን፡፡ ‹‹ስለመጣህ ደስ ብሎኛል?›› አለኝ፡፡ ‹‹እስኬው እኔም ናፍቀኸኝ ነበር፤ ሥራ ስለበዛብኝ ነው መምጣት ያልቻልኩት›› አልኩት፡፡ ‹‹ከዚህ በፊት ቅድሚያ ለሥራ! ብዬሃለሁ›› አለኝና ‹‹አሁን ላይ ብዙ ነገሮች አሉ፤ ከየቱ እንጀምር? በኋላ ይሄንን ሳልጠይቀው? ይሄንን ሳልነግረው? ብዬ እንዳላስብ›› በማለት ጥያቄውን በፈገግታ አስከተለ፡፡
‹‹አንተ ደስ ካለህ ነገር ጀምር›› አልኩት፡፡ ፈጠን ብሎ ‹‹ሰርካለም እንዴት ነች? ታገኛታለህ?›› በማለት ጠየቀኝ፡፡ ‹‹ደህና ነች፡፡ አልፎ አልፎ በማኅበራዊ ሚዲያ አገኛታለሁ፡፡ ነፍቆትም ማደጉን በፎቶፍራፉ ተመልክቻለሁ፡፡ የእሷንም የቅርብ ጊዜ ፎቶፍራፍ ፌስ-ቡክ ላይ አይቼዋለሁ፤ ደህና ናቸው›› በማለት መለስኩለት፡፡
‹‹በጣም ናፍቀውኛል›› የእስክንድር ምላሽ ነበር፡፡ …በእሱ ቦታ ራሴን ሳስቀምጠው እጅግ የሚከብድ ነገር ነው፡፡ ግን የእስክንድር በጣም ጠንካራ ነው፤ መንፈሱም ጭምር፡፡ …
‹‹አቤል (ዓለማየሁ) ደህና ነው?›› ሲልም በድጋሚ ጠየቀኝ፡፡ ‹‹ደህና ነው፡፡ ባለፈው ሳምንት ሊጠይቅህ መጥቶ በር ተዘግቶበት መመለሱን ነግሮኛል›› አልኩት፡፡ ‹‹አመሰግናለሁ›› በለው፡፡ [ጓደኛዬ ጋዜጠኛ እና መጽሐፍ ጸሐፊ አቤል አለማየሁ ያለ ማንም ቆስቋሽ፣ በራሱ ተነሳሽነት የታሰሩ ጋዜጠኞችን እና ፖለቲከኞችን ከሚጠይቁ የተወሰኑ ሰዎች መካከል አንዱ ነው፡፡ በአሁን ወቅት በቂሊንጦ እስር ቤት የሚገኙት በፍቃዱ ኃይሉ (በፍቄ) እና ተስፋለም ወልደየስ፣ እንዲሁም በቃሊቲ የምትገኘዋ ማህሌት ፋንታሁን (ማሂ) በራሳቸው ተነሳሽነት የታሰሩትን በመጠየቅ አውቃቸዋለሁ፡፡ ይህ እስከዳር ዓለሙ (ቹቹ)ን፣ መሳይ ከበደንና ኢዩኤል ፍስሐንም ይጨምራል]
ከሰሞኑ ፍትህ ሚኒስቴር በአምስት መጽሄቶችና በአንድ ጋዜጣን አቀረብኩት ስላለው ክስ እስክንድር ሰምቷል፡፡ ‹‹ክሱ ለሚዲያዎቹ ደረሳቸው እንዴ? ‹‹ዕንቁ›› መጽሄትም በክሱ ላይ ስላለበበት አንተን አስቤህ ነበር?›› አለኝ፡፡
‹‹ከፍቄ (የዕንቁ መጽሔት ማኔጂንግ ዳይሬክተር) ጋር ተደዋውለን ነበር፡፡ እስከአሁን ባለኝ መረጃ መሰረት ክሱ አልደረሳቸው …ሕግን አክብረን በሕግ ማዕቀፍ ውስጥ ሰርተናል፤ አሁንም በሕግ ማዕቀፍ ውስጥ በመስራት አምናለሁ፤ ከዚህ ባለፈ ግን በግሌ የሚመጣብኝ ነገር ካለ ለመቀበል ዝግጁ ነኝ፡፡ ጋዜጠኝነት ከፍርሃት ጋር አብሮ አይሄድም፡፡ እየፈሩ ጋዜጠኝነት የለም፤ ይህ የግል እምነቴ ነው›› በማለት ብዙ ጊዜ ለቅርብ ጓደኞቼ በጨዋታ አጋጣሚ የማካፍላቸውን ሀሳብ ለእስክንድርም ነገርኩት፡፡
‹‹ዴሞክራሲ እንዲሁ አይመጣም፡፡ ዋጋ ያስከፍላል፡፡ ሰዎች ዋጋ ለመክፈል ዝግጁ መሆን አለባቸው፡፡ አንተም ዋጋ መክፈል ካለብህ መክፍል አለብህ፡፡ ግን ጨካኝ አትበለኝ፡፡ ጨካኝ ሆኙም አይደለም፤ መሆን ያለበት ግን ይሄ ስለሆነ ነው፡፡ (እስክንድር ያመነበትን ፊት ለፊት ነው የሚናገረው) ….ለተከሰሰሱት ሚዲያዎች በሙሉ አንድ ከልቤ ውስጥ ያለ አንድ መልዕክት አስተላልፍልኝ? በማለትም ጥያቄውን አስከተለ፡፡
‹‹እሺ››
እስክንድር ቀጠለ፡- ‹‹በክሱ መምጣት ልትደነግጡ አይገባም፡፡ ኢህአዴግ ሊከስስና በፍ/ቤት እንድትቀጡም ሊያደርጋችሁ ይችላል፡፡ ይሄንን ከዚህ በፊትም አይተነዋል፡፡ እናንተ ግን በታሪክ፣ በሕዝብና በህሊናችሁ ፊት ነጻ ናችሁ፡፡ የክስ፣ የእስርና የስደት መብዛት ሰላማዊ ትግል መኖሩንና ትግሉም እየሰራ መሆኑን ያሳያል፡፡ ሰላማዊ ትግል እና የመብት ጥያቄዎች ሲኖሩ እስር እና ክስ ይኖራሉ፡፡ አንዳንዴም ሞት ይኖራል፡፡ ክሱን ተከትሎ እኔ በግሌ ሁለት ዓይነት ስሜት አለኝ፡፡ ሰዎች ሲከሰሱ እና ሲታሰሩ አዝናለሁ፣ ይሰማኛል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ሰላማዊ ትግል እየተሰራ እና ውጤት እያመጣ አድርጌ እቆጥረዋለሁ፡፡ እስር እና ክስ በበዙ ቁጥር የድል እና እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚፈጠርበት ጊዜ እየቀረበ መሆኑን አመላካች ነው፡፡ አይዟችሁ! ኢህአዴግ ሊፈርድባችሁ ይችላል፡፡ ነገር ግን፣ በታሪክ ፊት ነጻ ናችሁ፡፡ መንግሥቱ ንዋይ እኮ ያለአግባብ ተፈርዶበታል፤ በታሪክ፣ ሕዝብና በህሊናው ፊት ግን ነጻ ነው፡፡››
አያይዞም፣ ስለማርቲን ሉተር ኪንግ አንድ የግል ታሪክን አስታውሶ አወጋኝና ‹‹ኤልያስ፣ ለእውነት መቆም አለብን፡፡ ለእውነት መቆም ካልተቻለ ስብዕና ይወርዳል፣ ሕሊናህም ይሞታል፡፡›› በማለት ምክሩን ለገሰኝ፡፡
ሁለቱ ፖሊሶች ‹‹በቃችሁ!›› የሚል ድምጻቸውን አሰሙ፡፡ ከእስክንድር ጋር በ30 ደቂቃ ውስጥ ብዙ ቁም-ነገሮችን ተለዋውጫለሁ፤ መቼም ሁሉም አይጻፍ? ከእስክንድር ጋር ልለያይ ስል ባለቤቱ ሰርካለም ፋሲል እስክንድር 18 ዓመት የተፈረደበት ዕለት ከፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፒያሳ ድረስ አብረን ስንሄድ ደጋግማ የነገረችኝ ቃል ይበልጥ በውስጤ አቃጨለ፡፡
‹‹እስክንድር ማለት ላይብረሪ ነው፡፡ እሱን ማሰር አንድ ቤተ-መጽሐፍት እንደመዝጋት ይቆጠራል››
ሰርኬ፣ እውነትሽን ነው፡፡ ይሄንን ትናንትም በማወቅ አምን ነበር፣ ዛሬም ይበልጥ አውቄያለሁ፡፡
በመጨረሻ እስክንድር ‹‹እገሌ እገሌ አልልህም፤ ሁሉንም አከብራችኋለሁ፣ እወዳችኋለሁ›› በልልኝ ብሎ ተሰናበተኝ! እንግዲህ የእስክንድርን ሰላምታ አድርሻለሁ፡፡
የኢትዮጵያ አምላክ ከህሊና እስረኞች ጋር ይሁን!
ምንጭ የኢትዮጵያ ሜዲያ መድረክ

Sunday, August 10, 2014

ESAT Tikuret Mesay Mekonen with DC Activists on Redwan Hussien Protest


‹‹አያ ጅቦ ሳታመኻኝ ብላኝ›› በበፍቃዱ ሃይሉ (ከእስር ቤት የተላከ ማስታወሻ)

‹‹ታዲያ ጥፋቴ ምንድን ነው ትላለህ?!››፣ ብሎኛል አንዱ መርማሪዬ ስለዞን ዘጠኝ እና እኔም እራሴ እንደጦማሪም እንደአራማጅ ተራማጅም ሠራሁ የምላቸውን ነገሮች ዝርዝር ነግሬው ሳበቃ፡፡ በኋላ ላይ በእስር ቤት ቋንቋ ከ‹‹አባሪዎቼ›› ጋር መገናኘት ከተፈቀደልን በኋላ ስንጠያየቅ  ለካስ ሁላችንም ይቺኑ ጥያቄ ተጠይቀናል፡፡ ይኼ ነው እንግዲህ የምርመራችንን ሒደት የሚገልፀው ጥያቄ፡፡ ‹‹ተጠርጥረን›› የተያዝንበትን ጉዳይ የሚያረጋግጥ ሥራ ሠርተን ባለመገኘታችን (ወይም ‹‹ባለመናገራችን››) ታዲያ ጥፋትህ ምንድን ነው? ተባልን፡፡ ምርመራው የኛን ነፃ መሆን አለመሆን ለማጣራት ሳይሆን ጥፋት ለማግኘት ነበር፡፡ ብዙዎች ‹መንግሥት ዞን ዘጠኝን ለምን ሁለት ዓመት እንደታገሠው› ግራ በመጋባት ይጠይቃሉ፤ ባሕሪው አይደለምና፡፡ የኢትዮጵያ ሀሳብን የመግለጽ ነጻነት ምኅዳር በቀላሉ እንደገመቱት ተይዘን፣ ተመርምረንና ‹‹ተገኘባችሁ›› የተባልነው ‹‹ የግንቦት 7 [እና ኦነግም ጭምር] አባልነት [ብሎም ግብ አስፈጻሚነት] ›› በሽታ ለተከሳሽነት አብቅቶናል፡፡ ቀጣዩ የክርክር ሂደት ነው፡፡
Befekadu Hailu
Befekadu Hailu
ከዚያ በፊት ግን ዞን ዘጠኝን በሩቅም በቅርብም የሚያውቁ በግራ መጋባት መልስ እንደሚሹ በማሰብ ይቺን አጭር ማስታወሻ ለመጻፍ ተገድጃለሁ፡፡ የእስራችን ሂደት ምን ይመስላል? የምርመራችንስ? እውን የግንቦት ሰባት አባል ነን? [ታዲያ] ለምን ታሰርን? በቅርቡ እንፈታ ይሆን?
ደቂቅም ይሁን ሊቅ ስለኢትዮጵያ ፖለቲካዊ እውነታ የሚጽፍ ማንኛውም ሰው [ኢትዮጵያ ውስጥ ሳለ] አንድ ቀን እታሰር ይሆን እያለ መስጋቱ አይቀርም ፡፡ ለዚህም ይመስለኛል ፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማርያም በአንድ መጽሐፋቸው ላይ ሰው ነገረኝ ብለው የኢትዮጵያ ሕዝብን በሦስት የመደቡት፡- የታሰረ፣ ታስሮ የተፈታ እና ወደፊት የሚታሰር በማለት፡፡ እርግጥ ዞን ዘጠኝ ‹‹ሐሳቡን መግለጽ ፈርቶ ዝም ያለ ሁሉ እስረኛ ነው›› ብሎ መደምደም ሦስቱም ምድብ አንደኛው ውስጥ ያጠቃልለዋል ‹‹የታሰረ›› በሚል፡፡ ዞን ዘጠኞች ጦማራችንን በከፈተን በሁለት ሳምንት ሲታገድብን እና ሌላ ስንከፍት ግና መጨረሻ ላይ ታጋቾቹ እኛ እንደምንሆን እናውቅ ነበር፡፡ ያንን የሚያረጋግጥ ተደጋጋሚ የደህንነቶች ክትትል እና ምልክቶች ስለደረሱን መታሰራችን ማስደንገጡ ባይቀርም ያልተጠበቀ ግን አልነበረም፡፡
እስሩ በክትትሉ የተገኘነውን ስድስት የዞን ዘጠኝ አባላት እና ሦስት ጋዜጠኛ ጓደኞቻችንን መሆኑን በተለይ የጋዜጠኞቹ [ቢያንስ ለእኛ] ያልተጠበቀ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ የኋላ ኋላ ስንመለከተው ግን በእኛ አስታኮ እነሱንም ማሰሩ የታሰበበት ዘመቻ እንደሆነ መገመት አይከብድም፡፡ እኛን በቁጥጥር ስር የማዋሉ ሒደትም ቢሆን በቅጡ የታሰበበት ነበር ሁላችንም (ከአስማማው በቀር) ከቀኑ በ11፡00 ገደማ በያለንበት ስንያዝ አስማማው በማግሥቱ ታስሯል፡፡  ሌሎቻችን ቤታችን በሚፈተሸበት ሰዓት ሕጉ የሚፈቅድበት ሰዓት(12፡00) አልፎ ነበር፡፡ በቁጥጥር ስር ካዋሉን በኋላ የሕገ-ወጥ አያያዝ ሰለባ የመሆናችን ሂደት የሚጀምረው ከዚህ ነው፡፡
ማዕከላዊን በክፉ ስሙ ቀድሞ ለሚያውቀው ሰው ግቢውን መርገጥ በራሱ ልብን ያርዳል፡፡ ሆኖም በልቤ /ጓደኞቼም እንደእኔ ሳይሰማቸው አይቀርም/ አንደኛ እኛ ጸሐፊ እንጂ ወታደር ወይም ሰላይ ባለመሆናች፣ ሁለተኛ መቼም ከበፊቱ የተሻለ ሰብዓዊ አያያዝ ሳይኖርም አይቀርም የሚል የዋህ ተስፋ በማሳደሬ ብዙም አልተሸበርኩም ነበር፡፡ የገባሁ እለት ከታሳሪዎች በተሰጠኝ ማብራሪያ ‹‹ሳይቤሪያ›› መግባቴን አወቅኩ፡፡ ከዚያ የ HRW-They want confession የተሰኘ ሪፖርት ላይ የተፃፉ ነገሮች ሁሉ ትክክል መሆናቸውን ለመረዳት የፈጀብኝ ከአንድ ሳምንት ያነሰ ጊዜ ነበር፡፡
ምርመራ ማዕከላዊ ስታይል
ምርመራ በማዕከላዊ ከብልጠት ይልቅ ጉልበት ይበዛበታል፡፡ መርማሪዎቹ የምርመራ ችሎታቸው ተጠርጣሪውን የተጠረጠረበትን ጉዳይ ከማውጣጣት ይልቅ የምርመራ ችሎታ እንዳላቸው ለማሳመን የሚጥሩበት ጊዜ ይበዛል፡፡ ይህም አልሰራ ሲል ጥፊ፣ ካልቾ፣ ከአቅም በላይ ስፖርት ማሰራት እና ግርፋት ድረስ ይዘልቃሉ፡፡ ይህ እንግዲህ እኔ ላይ ከተፈራረቁብኝ አምስት መርማሪዎች እና ሌሎችም አብሮ ታሳሪዎቼ ከነገሩኝ የተረዳሁት ነው፡፡ እርግጥ ሌሎች ‹‹እርቃንን ቁጭ ብድግ›› የሰሩ ተጠርጣሪዎችም ገጥመውኛል፡፡ ከባባድ ቅጣት (ወፌ ላላ ግርፋት፣ ጥፍር መንቀል) የደረሰባቸው ሌሎች ታሳሪዎች አብረውኝ የታሰሩ ቢሆንም ይህ የተፈፀመባቸው ግን ወደማዕከላዊ ከመምጣታቸው በፊት  ነው፡፡ ከነዚህ መካከል የሀሮማያ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ይገኙበታል፡፡ የሚገርመው በዚህ ዓይነቱ ምርመራ የሰጡት ቃል ለማመሳከርያ ማዕከላዊ መምጣቱ ነው፡፡ በተመሳሳይ መልኩ ወደማዕከላዊ ከመዛወራቸው በፊት ከባድ ቅጣት የተቀጡበትን ቦታ የት እንደሆነ እንዳያውቁ አይናቸው ተሸፍኖ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ እሥረኞችም መኖራቸው ነው – የደርግን ‹‹ቤርሙዳ›› ያስታውሳል!
እናም በሚያዋርድ እና ክብርን በሚነካ ስድብ በሚያስፈራ የቤቱ (የማዕከላዊ) ጥላ እና ኃይል በተቀላቀለበት የምርመራ ሂደት የተከሳሽ ቃላችንን ሰጠን፡፡ ቃላችን መቶ በመቶ እውነት አልነበረም፡፡ ጫናው በበረታ ቁጥር መስማት የሚፈልጉትን ‹‹ዓመፅ ለመቀስቀስ ፈልገን›› የመሳሰሉ በራስ ላይ ፈራጅ (Self-incriminating) ሐረጎችን እየተናገርን ነበር፡፡ ያም ግን ለመርማሪዎቻችን በቂ አልነበረም፡፡ ስለዚህ በሚጽፉበት ሰዓት እያንዳንዷን ‹‹ሠራን›› ያልነውን ሁሉ ሊያስከስሰን በሚችልበት ሁኔታ እየገለበጡ እና እየበጠበጡ ፃፉት፡፡ አንዳንዶቻችን እየተከራከርን ሲያቅተን ፍርድ ቤት ይፍታው ብለን ፈረምን፣ቀሪዎቻችን የቻልነውን ያህል ተደብድበንበት ፈረምን፡፡ ‹‹ከተናገርኩት ቃል ውጪ አንድም ቃል አልፈርምም›› በሚል እስከመጨረሻው ታግሎ የተሳካለት አቤል ብቻ ነበር፡፡
በምርመራው ሂደት የተረዳነው ነገር ቢኖር የማዕከላዊ መርማሪዎች ብቃት (Intelligence) አርጩሜ ብቻ መሆኑን ነው፡፡ እኔ ምርመራ ሲባል ይመስለኝ የነበረው ፖሊሶች ተጠርጣሪዎችን ፈፀሙ ስለሚባለው ነገር በቂ መረጃ ይዘው ግፋ ቢል ለምንና እንዴት እንደፈፀሙት ማውጣጣት ነበር፡፡ ‹‹ዕድሜ ለማዕከላዊ›› የተረዳሁት ነገር ቢኖር ምርመራ ማለት ለካስ ‹‹የሠራኸው ወንጀል ምንድን ነው?አውጣት!›› ማለት ኖሯል- ማዕከላዊ ስታይል፡፡ ‹‹ነጻ ነኝ›› ቢሉ ሰሚ የለም፡፡ አንዴ ታስረሃል ወንጀል ሊገኝብህ የግድ ነው፤ ካልሆነ ይጋገርብሃል፡፡
አሁን ሳስበው ማዕከላዊ ፈርሶ በሥር-ነቀል ለውጥ እንደገና መቋቋም ያለበት ተቋም ነው፤ ቢያንስ በሁለት ምክንያት፡፡ አንደኛ የምርመራው ሂደት (በራሳችን ጉዳይ እንደተረዳሁት) ትዕዛዝ አስፈፃሚነት ይስተዋልበታል፡፡ ማለትም በመርህ የሚመራ አይደለም፡፡ ሁለተኛ ምርመራው እውቀት መር አይደለም፡፡ ይህ ደግሞ የአገሪቱን ደህንት አደጋ ውስጥ የሚጥል ጉዳይ በምርመራው ድክመት ሳይታወቅ ሊታለፍ ይችላል፡፡ ይህ ችግር የተከሰተው ደግሞ መርማሪ ፖሊሶቹ ከብቃት ይልቅ ለታዛዥነት የተመቹ ታማኞች ሆነው በመመልመላቸው ነው፡፡
‹‹ፍየል ወዲህ ቅዝምዝም ወዲያ››
በምርመራው ሂደት የተጨቀጨቅነውም ሆነ ተገድደን የፈረምነው ጽሑፎቻችንን የበይነ መረብ ዘመቻዎቻችንን፣ የወሰድናቸው ስልጠናዎችም ሆኑ አንዳንዶቻችን የሰጠናቸው ስልጠናዎች አመፅ ለማስነሳት መሆኑን ‹‹እመኑ›› በሚል ስለነበር የጠበቅነው ግፋ ቢል በወንጀለኛ መቅጫው አንቀጽ 238 ወይም 257 ሊከሱን አስበው ነው ብለን ነበር፡፡ ይሁን እንጂ የክስ መዝገቡ ሲመጣ ‹‹ሽብር›› ያውም ከአስራ አምሰት ዓመት እስከ እድሜ ልክ የሚያስቀጣ አንቀጽ 4 መሆኑን ሳውቅ በበኩሌ ሳቄ ነበር የመጣው፡፡
ማስረጃ ተብለው ከክስ መዝገቡ ጋር የተያያዙት በአብዛኛው ጽሑፎቻችን፣ የዘመቻዎቻችን፣ የጋዜጣ መግለጫዎች እና በተለያዩ ሥልጠናዎች ወቅት የተዘጋጁ የሥልጠና መመሪያዎች (Manuals) ናቸው፡፡ ከዚህ በተረፈ ከግንቦት 7 እና ከኦነግ ጋር ያገናኛችኋል የተባልነው በሦስት ‹‹ሰነዶች›› ነው፡፡ አንደኛው ናትናኤል ኢሜይል ውስጥ በጥቅምት 2001 ተልኮለት የተገኘ የግንቦት 7 የዜና መጽሔት ነው፡፡ ይህ እንግዲህ ገና የፀረ-ሽብርተኝነት ሕጉ አዋጁ ሳይወጣ፤ ግንቦት ሰባትም አሸባሪ ከመባሉ በፊት መሆኑ ነው፡፡ ሁለተኛ ሶልያና ቤት ተገኘ ተብሎ እናቷ ‹‹ቤቴ ውስጥ አልተገኘም፣አልፈርምበትም›› ያሉት እና ለግንቦት 7 ሕዝባዊ ኃይል ሰራዊት ምልመላ መመዘኛ ሰነድ ነው፡፡ ይህ የሶሊ የዘለቀ አቋም ለሚያውቅ ሙግት አያስፈልገውም፡፡ እኔ እንደውም ትዝ ያለኝ ከመታሰሬ በፊት የትዊተር ፕሮፋይሏ ውስጥ የነበረው ‹‹no for war›› የሚል መፈክር ነው፡፡ ሦስትኛው ደግሞ ማሕሌት ኮምፒውተር ውስጥ የተገኘው የኦነግ ፕሮግራም ነው፡፡ በርግጥ አብረው የተገኙት የሌሎች የኦሮሞ ፓርቲዎች ፕሮግራሞች ማስረጃ ተብለው አለመቅረባቸው መረዳት ብቻ – እሷም ለምን ፕሮግራሙን እንደያዘችው፤ እነሱም ለምን የኦነግን እንደመረጡ ያጋልጣልና የእመኑኝ ሙግት አያስፈልገንም፡፡ በመሰረቱ ሦስቱንም ‹‹ሰነዶች›› መያዝ ከቡድኞቹ ጋር ግንኙነት መመሥረት የሚሰሩትንም መውደድ ማለት አየደለም፡፡ ይህም ለመሪዎቻችን ባይታያቸውም እንኳ ለወገኖቻችን የጠፋቸዋል ብዬ አላስብም፡፡
ሌላውና በአስቂኝለቱ ተወዳዳሪነት የሌለው ውንጀላ ‹‹48 ሺሕ ብር በናትናኤል በኩል ተቀብለው ተከፋፍለዋል›› የሚለው ነው፡፡ ይህ ብር ፤‹‹አሸባሪ›› ከተባሉት ቡድኖች የተወሰደ እንዲመስል በሚያደናግር አገላለጽ የተጻፈ ቢሆንም የክስ መዝገቡ ውስጥ የተያያዘውና ገንዘቡ የመጣበት ደረሰኝ እንደሚያረጋግጠው የተላከው ከARTICLE 19 ነው፡፡ ይህንን ጨምሮ በእስር ላይ ለምትገኝ ጋዜጠኛ ቤተሰቦች መደገፊያ /ለእስረኛይቱም ማበረታቻ/ የተላከ መሆኑን ለመርማሪዎቹ በዝርዝር አስረድተናቸዋል፡፡ ይህንን እያወቁ ውንጀላውን ማኖራቸው እውነትም እኒህ ሰዎች ወንጀለኞች ናቸው ብለው አምነው ሳይሆን ‹‹ከቻልን አደናግረን እናስቀጣቸዋለን (የማይችሉበት ሁኔታ አይታየኝም)፣ካልቻልን ደግሞ በቀጠሮ ጊዜ እንገዛበታለን፣ ነጻ እስኪወጡም ቢሆን በእስር እናቆያቸዋለን›› የሚል ክፉ ምኞት ነው፡፡
… ሳታመኻኝ ብላኝ!
አህዩት ከታች አያ ጅቦ ከላይ ሆነው ወራጅ ውሀ እየጠጡ ነበር አሉ፡፡ ነገር ያማረው አህዩትን ‹‹አታደፍርሽብኝ›› ሲላት ነገሩ የገባት አህይትም ‹‹ሳታመኸኝ ብላኝ›› አለችው ይባላል፡፡ የኛም ነገር እንደዚያው ነው፡፡
ፖሊስ ሲይዘን እኛ ላይ ይህ ነው የሚባል የመክሰሻ መረጃ አልነበረውም፤ እንዲያውም ከስማችን በቀር የሚያውቁት ነገር አልነበረም፡፡ ሌላው ቀርቶ ከደህንነቶታቸው በአንዱ ልከንላቸው የነበረውን የጽሑፋችንን ስብስብ እንኳን ሳያነቡት ነበር የያዙን፡፡
አሁንም ማስረጃ ብለው ከክስ መዝገባችን ጋር ያያያዙት ቢያንስ በእኔ ግምት ዘጠና በመቶ የሚሆነው ‹‹ሰነድ›› እኛው ነፃ ያወጣናል ብለን የሰጠናቸው ጽሑፎቻችን ናቸው፡፡ በመርማሪዎቻችን ንግግር ውስጥ እኛ ላይ ወንጀል የማግኘት Desperate ፍላጎት አይተናል፡፡ ምናልባትም እንደገመትነው ቢያንስ እስከ 2007ቱ ምርጫ ድረስ ከማኅበራዊ ሚዲያ ገለል እንድንልላቸው ፈልገዋል፡፡ ከዚህ የተሻለም አማራጭ አልታያቸውም ይሆናል፡፡
በእስካሁኑ ሂደት የማዕከላዊን ለገዢው ፓርቲ ወገንተኝነት በዓይናችን አይተን አረጋግጠናል፡፡ ቀጣዩ ደግሞ የፍትሕ ሥርዓቱን በአደባባይ መፈተሽ ይቀረናል፡፡ ለአሁኑ ግን በቅርቡ እንፈታ ይሆን… የሚል ጥያቄ ‹ሕጋዊ› ሳይሆን መላ ምታዊ አማራጮችን እገምታለሁ፡፡
ኢህአዴግ ወይም የኢህአዴግ መንግሥት የሚያዘው ፖሊስ እኛን በቁጥጥር ሥር ሲያውለን ስለወንጀላችን ማረጋገጫ (ጠበቆች Beyond reasonable doubt) እንደሚሉት ዓይነት ባይኖረውም መቼም የሆነች ስህተት ሳላገኝባቸው አልቀርም በሚል ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ወትሮም የተንቦረቀቀ የሚባለው የፀረ-ሸብርተኝነቱ አዋጅ ውስጥ የሚጥለን ነገር በቀላሉ ማግኘት አልቻሉም፡፡ አለመቻላቸው ግን የተነሱበትን እኛን የመክሰስ ዓላማ አላጠፋውም፡፡  የክስ መዝገቡን ሲያዘጋጁ አንድም የረባ ዐረፍተ ነገር ሳይጽፉ ይዘውን ፍርድ ቤት መቅረባቸው በራሱ አንድም የረባ ጥርጣሬና ማረጋገጫ እንደሌላቸው አመላካች ነው፡፡ ቢሆንም በቅርቡ ይለቁናል የሚል ግምት የለኝም፡፡ ለምን?
1ኛ. ኢህአዴግ በጣም የሚናደድባቸው እና ታሳሪውን በሚያዋርድ መልኩ ካልሆነ በቀር ከማያደርጋቸው ነገሮች ውስጥ አንዱ- አንዴ ያሰረውን ተቺውን ፤ ያውም ብዙ ደጋፊ ያለውን መፍታት ነው፡፡ ኢህአዴግ እንደልጅ እልህ ይጋባል ማለቴ ነው፡፡ (ይህንን ስል የእስራችንን ኢፍትሀዊነት የተመለከቱትን ጩኸቶች መጥላቴ አይደለም፤ ያለ እነርሱ መንፈሳችን አይጠገንም ነበር፡በአደባባይ የምናመሰግንበት ቀን ይመጣል)
2ኛ. መጀመሪያ የተጠራጠሩበት እና ኋላ የዋጧት ጥርጣሬያቸው፤ ማለትም (ምርጫውን ተከትሎ) አመፅ ማስነሳት በሚሉት ጉዳይ ላይ እቅድ እንደሌለን ቢያምኑም እንኳን ምናልባት እምነታቸው ከተሳሳተ Risk መውሰድ አይፈልጉም፡፡ ( መጀመሪያም የቀለም አብዩት ዶክመንተሪ አዝማሚያ ያስታውሷል)
3ኛ. ምንም እንኳን ዓመፅም፤ሽብርም  የማስነሳት ፍላጎትም አቅምም፤  እንደሌለን ቢያምኑም የገዥው ፓርቲ ጠንካራ ተቺዎች መሆናችንን ስለሚያውቁ እና ስላልወደዱልን ፍርድ ቤት በምንመላለስበት ረዘም ያለ ጊዜ ባለው እስር ወቅት ቢያንስ የእስርን ምሬት እንድንቀምሳት ይፈልጋሉ፡፡ ቅጣትን ጨርሶ በነፃ መለቀቅ እንደማለት፡፡
4ኛ. ኢህአዴግ መፍረድ አይፈራም፡፡
ምንጭ የኢትዮጵያ ሜዲያ መድረክ

Saturday, August 9, 2014

የመከላከያ ሰራዊት አባላት ለመለስ ፋውንዴሽን ገንዘብ እንዲያዋጡ መጠየቃቸውን ተቃወሙ

ነሃሴ ፪(ሁለት)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የኢሳት የመከላከያ ምንጮች እንደገለጹት የሰራዊቱ አባላት ለመለስ ፋውንዴሽን ገንዘብ እንዲያዋጡ በተጠየቁበት ወቅት ተቃውሞ
አሰምተዋል። በባድሜ አካባቢ የሰፈሩት የመከላከያ አባላት በደሞዝ ክፍያ ሳምንት መነሻው 200 ብር ሆኖ በየደረጃው ያሉ ወታደሮች እንደ ማእረጋቸውና ደሞዝ መጠናቸው
እንዲከፍሉ ሲጠየቁ፣ የሰራዊቱ አባላት ደሞዛችን አይቆረጥም በማለት ተቃውሞ አሰምተዋል።
ደሞዝ ከፋዮቹ ከላይ የመጣ መመሪያ ነው በሚል ሊያግባቡዋቸው ቢሞክሩም የሰራዊቱ አባላት ፈቃደኞች ሳይሆኑ ቀርተዋል። አንድ የ3ኛ ሻለቃ አንደኛ ጋንታ አባል የሆነ ወታደር
አመጹን መርተሃል ተብሎ ሊታሰር ሲል አምልጦ እስከነመሳሪያው ተከዜ ውስጥ ገብቶ መሞቱ ታውቋል። ይህንን ተከትሎ መጠናኛ ብጥብጥ መነሳቱን ምንጮች አክለው ገልጸዋል።
በአሁኑ ሰአት ውጥረቱ እንዳለ ሲሆን፣ ከመከላከያ እየጠፉ የሚሄዱትም ቁጥራቸው እየጨመረ ነው።
ባለፉት 3 ቀናት መከላከያን ጥሎ የጠፋ አንድ  ወታደር እንደገለጸው፣ ሰራዊቱ በከፍተኛ ምሬት ውስጥ እንደሚገኝና የሚከዳው ሰራዊት ቁጥርም ከፍተኛ መሆኑን ተናግሯል። በተከዜ
አካባቢ በሚካሄደው የኮንትሮባንድ ንግድ የአንድ አካባቢ ሰዎች የሆኑ የመከላከያ አዛዦች እየተጠቀሙ ነው የሚለው አባሉ፣ ከእነሱ ውጭ ያለው የመከላከያ አባል በችጋር እየተጠበሰ
ባለበት ወቅት ለመለስ ፋውንዴሽን በሚል እንደገና መዋጮ መጠየቁ ብዙዎችን ስሜት የረበሸ ሆኗል ብሎአል።
እነሱ ተጨማሪ ገቢ አላቸው፣ እኛ ግን የምትሰጠንን ደሞዝ እንኳ ቆጥበን ለቤተሰቦቻችን እንዳንረዳ በመዋጮ እና በሰበብ አስባብ ይወስዱብናል ሲል ተናግሯል።
በኢትዮጵያ በወታደራዊ አዛዦችና በተራው ሰራዊት መካከል ከፍተኛ የሆነ የኑሮ ልዩነት አለ። አብዛኞቹ የመከላከያ መኮንኖች የህወሃት አባላት ሲሆኑ፣ በአዲስ አበባ እና በኢትዮጵያ
ዋና ዋና ከተሞች ዘመናዊ ቪላዎችንና ፎቆችን ሰርተው በወር በመቶሺዎች የሚቆጠር የኪራይ ገቢ ያገኛሉ።  በአገሪቱ ውስጥ የሚካሄደውን የኮንትሮባንድ ንግድ የሚያስፈጽሙት፣
በመከላከያ ስም ያለቀረጥ የሚያስገቡዋቸውን እቃዎች በርካሽ በመሸጥ ህጋዊዎቹን ነጋዴዎች እያከሰሩ ከስራ ውጭ እያደረጉዋቸው መሆኑን በርካታ ነጋዴዎች ለኢሳት ይናገራሉ።

Friday, August 1, 2014

የህወሃት ሽብር መቆም አለበት!

ዛሬ በኢትዮጵያ መሬት ላይ ያለ አሸባሪ ወያኔና ወያኔ ብቻ ነው። በኢትዮጵያ ውስጥ ሰዎችን በፖለቲካ አመለካከታቸው፣ መንግስት በመተቸታቸው በግልጽ በመጻፋቸውና በአደባባይ በመናገራቸው ከዚህም አልፎ በጥርጣሬ በተለይም በብሄረሰብ ማንነታቸው እያሳደደ የሚያፍን የሚያሰቃይና የሚገል የሽብር ተቋም ካለ ወያኔ ብቻ ነው። በኢትዮጵያ መሬት ላይ ሰላማዊ ዜጎችን ኢላማ ያደረገ የተቃውሞ ሃይል በተግባርም ሆነ በአስተሳሰብ ከወያኔ ውጪ አንዳች ሃይል የለም።
አፋኙ የወያኔ ስርአት በተለየም የህዝቡን ሀብትና ንብረት እየዘረፉ የሚቀማጠሉት የህወሃት መሪዎችና ሎሌዎቻቸው የተቃውሞ ድምጽ በሰሙ ቁጥር እንደሚሸበሩና እንቅልፍ አጥተው እንደሚያድሩ ይታወቃል። አፍነውና ዘርፈው ገለው የሚገዙት ህዝብ ግፍ በዛብኝ ብሎ በተናገረ ቁጥር የሚሸበሩት እነሱ ብቻ እንጂ ህዝቡ አይደለም።
በኢትዮጵያ ምድር ያለው አሸባሪ ወያኔ ብቻ መሆኑን ሺ ምሳሌዎችን ጠቅሶ ማስረዳት ይቻላል። ሶስት አመት ሙሉ የሰላም እጃቸውን እየዘረጉ ከልመና ባልተለየ ሁኔታ መብታቸውን የጠየቁና ድምጻችን ይሰማ ያሉት የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ማንንም ዜጋ አላሸበሩም። የተገላቢጦሽ እነሱ አሸባሪ ተብለው የግፍ ሰቆቃ ይፈጸምባቸዋል። ጋዜጠኞችና ጦማሪዎቹ መንግስት ያወጣውን ህግ እንዲያከብር ስለጠየቁ በአደባባይ ስለጻፉ ግፍ ይፈጸምባቸዋል። እነሱ ያሸበሩት ሀገርና ህዝብ የለም። ከመንገድ ላይ ጎትተው እንደ እባብ ቀጥቅጠውና ፈነካክተው በማግስቱ ፍርድ ቤት ያቀረቧት ወየንሸት ሞላ የተባለች ባለ ተስፋ ወጣት የወያኔ አረመኔዎች በሙስሊሙ ህዝብ ላይ የሚሰሩትን ጭፍጨፋ እግር ጥሏት ከማየትና ከመታዘብ ውጪ ያሸበረችው ሰው፣ ሀገር የለም። በየወህኒ ቤቱ እና አፈና ጣቢያው ታስረው የሚቀጠቀጡት የኦሮሞ ልጆች ለጥያቄያቸው መልስ ሲጠብቁ ከመጨፍጨፍ ያለፈ የፈጸሙት እብሪት የለም። በየክልሉ ቀና ብለህ ባለስልጣን ተናገርክ፣ ጥያቄ ጠየቅክ፣ ባለስልጣን ደፈርክ፣ ተሰብስበህ አየንህ ወዘተ እየተባለ የሚገረፈው እንደ እንስሳ እየተገደለ የሚጣለው ገበሬ የሰራው ወንጀል የለም። አሸባሪም አይደለም! በየቦታው ቦንብ እየቀበረ አፈንድቶ ንጹሃንን ገድሎ ሊያፈነዱ ሲሉ ፈንድቶባቸው ራሳቸውን ገደሉ ብሎ በአደባባይ የሚሳለቀው አሸባሪው ህወሃት እንጂ ንጹሃኑ አይደለም።
የኛ መሪ አንዳርጋቸው ከልጅነት እድሜው ጀምሮ ራሱን ለህዝብ ነጻነት የሰጠ አርበኛ እንጂ አሸባሪ አይደለም። በተመሳሳይ ውንብድና ከጎረቤት ሀገር ድረስ በአለም አቀፍ የወረበሎች ውንብድና መንገድ ወያኔ እያፈነ የገደላቸው አሮሞዎችና፣ ሱማሌዎች፣ አኙዋኮች፣ አማሮችና ሌሎችም ነጻነት ከመፈለግ ውጪ ያሸበሩት ህዝብና ሀገር የለም።
በኢትዮጵያ ምድር የነጻነት ድምጽና ኮሽታ በሰማ ቁጥር የሚሸበረው ህወሃትና በለሟሎች ብቻ ናቸው። ይህ የነጻነት ድምጽ ደግሞ እየጎላ መሄዱ የማይቀር ነውና ወያኔ ሰፈር ሽብር ይሆናል።
የኢትዮጵያ ህዝብ ሆይ! ወጣት፣ ሴት፣ ሽማግሌ፣ ገበሬ እና በየቦታው ያላችሁ የኢትዮጵያ ልጆች ሁሉ! አሸባሪህ ወያኔና ወያኔ ብቻ መሆኑን አውቀህ በገዛ ሀገርህ ላይ ነጻነት በተመኘህና በጠየቅህ ጊዜ ሁሉ ለሽብር ጥቃቱ ኢላማ ያደረጉህን ወያኔ ተባብረን ከላያችን ለማውረድ ተነስ! በያለህበት እምቢ በል! ለወያኔ የሚጠቅም የመሰለህን ነገር ሁሉ አታድርግ! አትተባበር! ሸቀጣቸውን አትግዛ! ወያኔዎችን ከማህበራዊ ሂወትህ አግል! የቻልክ ሁሉ ደግሞ የነጻነት አርበኞችን ዛሬ ነገ ሳትል አሁን ተቀላቀል!!! ነጻነታችን ያለው በእጃችን ላይ መሆኑን አትዘንጋ። ግንቦት 7 ሁልጊዜም ከመቼውም ጠንክሮ ከጎንህ ነው።
የወያኔን ሽብር በተባበረ ሃይል እናቁመው!
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!!!
www.ginbot7.org